ማክሰኞ 2 ኤፕሪል 2013

በቅርብ ለማውቅህ ወንድሜ 1

በቅርብ ለማውቅህ ወንድሜ
‹‹…. የምነቅፍብህ ነገር አለኝ…››

ወቅቱ የዚህ የሽብር ወቅት መገባደጃ የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት በር መክፈቻ ሰሞን ነበር እኔ አንተ እነዚያ በአጠቃላይ ሁላችንም በአብተ ክርስቲያናት ጥላ ሥር መሰባሰብ የጀመርነው ጊዜውን እንደማትዘነጋው ተስፋ አለኝ በአሥራ ዘጠኝ ሰማንያዎቹ ውስጥ፤ በአብያተ ክርስቲያናት አጸድ ሥር እየተሰባሰብን የቤተክርስቲናችንን ጥንታዊ የአባቶቻችንን ቋንቋ ወንጌልን እየተማርን በየመንገዱ በየጓዳው በየትምህርት ቤቱ በየመንደሩ ‹‹ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየኝ ማነው? …›› የሚለውን መዝሙር እየዘመርን አንገት ደፍተን እጅ እየተነሳሳን ትህትናን እየሰበክን ሰንበት ት/ቤት መማርን የጀመርንበትን ሠሞን የዛሬውን አያድርገውና ሲጠሩን አቤት ሲልኩን ወዴት የምንልባትን ሰሞን የጠዋት ተማሪ ከሆንን አሥራ አንድ ሰዓት ለሚጀመረው መርሐ ግብር አሥር ሰዓት ስንሄድ ስምንት ሰዓት ለሚጀመረው የቅዳሜና እሁድ ጉባኤ ምሳችንን በልተን አረፍ እንኳን ሳንል በረን ከቤተክርስቲያን የምንገኝበት ወቅት ያለጥርጥር እንደማትዘነጋው እገምታለሁ በቅርብ የማውቅህ ወንድሜ ከአፍ እስከ ገደፍ ጢም የሚለው የቤተክርስቲያን ደጃፍ ሁለት ሦስት ሆነን ከጀመርንበት እስከ አሁኑ ያለውን እዚያው ስላለህ በደንብ አድርገህ ታውቀዋለህ የፆምና የፀሎቱንስ ነገር ቢሆን ቀጥ ብለን ሳንነቀነቅ ሳንሰስት አንድ መዝገበ ፀሎት ሙሉ ሲጥ አድርገን ጨርሰን የዕለቱን መዝሙረ ዳዊት ደግመን ኪዳን አድርሰን ቅዳሴ አስቀድሰን እንደማይበቃን ታስታውሳለህ ሱባኤስ ቢሆን ላባችን የክረምት ጎርፍ እስኪመስል በኛ ላይ እስኪወርድ የጣቶቻችን አንጓ የፆም ወቅት አሻራን ይዘው እስኪቀሩ የምንሰግደውስ ስግደት በቃችሁ ‹‹ትሞታላችሁ›› እየተባልን እንኳን ለዚያውም ያለጥሬ ንክች አናደርግም የምንለው የፆም ወቅት ትዝ ይልሃል? … ስንቱን ላንሳው ብቻ ሁሉም ትዝ ይለኛል የእንግዳ መስተንግዶውስ እቤታችን የመጣውን እግሩን አጥበን ያለንን አብልተን እንደ አባቶቻችን ሥርዓት አልጋም ይሁን ምንጣፋችንን ለቀን የምናስተኛው በጉባኤም እንግዳ መምህር ሲመጣ ተራችንን ለቀን አስተምሩን የምንለው ትዘነጋዋለህ … አገልግሉስ ስንባል የሁለትና የሦስት ሰዓት መንገድ ሁለት ሁሉት ሆነን እንደ ሐዋርያት በፍቅር የጀመርንባቸውን ሰሞን ታስታውሰዋለህ … ወንድማለም ብቻ ምን ዋጋ አለው የአንድ ሰሞን ሰዎች ብቻ ሆነን ‹‹ሠሞነኛ›› የሚል ቅጥያ ሥም ይዘን ቀረን፤
‹‹ጀማሪ ክርስቲያን ከጳጳስ ይበልጣል›› እንዲሉ አበው ሲተርቱ ጀማሪ አርበኞች ብቻ ሆነን ቀረን፤ ከትናንቱ ቦታ ጠፍተን ከትናንቱ ዓላማችን ተናውፀን የሩቅ ተመልካች ሆነን ቀርተናል በቅርብ የማውቅህ ወንድሜ ምናልባት እኔኮ አንተ እንደምትለው በነበር የቀረሁ አይደለሁም፡፡ ዛሬም አለሁ አገለግላለሁ፤ እፆማለሁ፤ እፀልያለሁ፣ እሰግዳለሁ፣ ሱባኤም ሲኖር እመጣለሁ ትለኝ ይሆናል ወንድማለም ሁለመናህ ይገባኛል ሃሳብህ ሃሳቤ ግብርህ ግብሬ ነው ምንም አይጠፋኝም ግና ትላንት በነበርክበት እምነት ዛሬ አለህ? በትላንትና በዛሬ አድራጎትህ መካከል ባለው ለውጥ አታፍርበትም ሕሊናህን አልሸጥክም ‹‹ሰው ምን ይለኛል?›› በሚል ትብታብ አልተተበተክም ለኃጢአት ተገዢ አልሆንክም ነፍስህን እንደያኔው ለእግዚአብሔር አደራ ሰጥተህ ነው ያለኸው ሰው ሰራሽ ሮቦት አልመሰልክም? … ወንድማለም ብቻ ባጠቃላይ በሁለት እግር የሚንቀሳቀስ ሰው መሰል እንስሳ መስለሃል ‹‹ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም እንስሳትን መሰለ›› እንዳለው ልበ አምላክ ዳዊት፤ ደግሞስ ያኔ የምትፆመው የፆም ሰዓት፣ የጸሎት ብዛት፣ የስግደቱ መጠን፣ ለአገልግሎት ያለህ ፍቅርና ትህትና፣ አኗኗርህን የቤተክርስቲን መምጫ ሰዓትህ ለውጥህ በአጠቃላይ ምን ያህል ለውጥ አምጥቷል የክርስትና ሕይወት ፍሬህ ከትናንቱ ዛሬን ስንት አፍርተህ ተገኝተሃል ሰላሳ፣ ስልሳ ወይስ መቶ ያማረ ፍሬ አልያም ዝም ብሎ ገለባ ወደ እሳት የሚጣል እንክርዳድ ብቻ ለማንኛውም መልሱ ላንተው ትቼ ትዝ ማሰኘቱን አሁንም እቀጥላለሁ፡፡
በቅርቡ የማውቅህ ወንድሜ ለመሆኑ ‹‹መሰባሰባችንን አንተው›› የሚለው የልበ አምላክ ዳዊትና የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አባታዊ መልዕክትን ዛሬ ዛሬ እንዴት ነው እየተጠቀምከበት ያለኸው? በመንፈሳዊ ሕይወት ልትጎለብትበት፣ ለአገልግሎት ልትበረታበት፣ እርስ በርስ ልትተያዩበት፣ ኤልያስ አንዱ ለአንድ መሰናክል ሊሆንበት፣ ልትተጫጩበት፣ ወሬ ልታወሩበት፣ ልትደልቱበት፣ … ወይስ ለምንድን ነው? ወንድማለም ‹‹ይህ ምስጢር ታላቅ ነው›› ብሎ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመሰከረለትን ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹ጋብቻ መልካም መኝታውም ንፁህ ይሁን›› ብሎ ያስጠነቀቀውን አንተ በቤተክርስቲን ምስጢርና ስርዓት ሽፋን ምን እየሰራህ ነው ያለኸው በውኑ የምታደርገውን ድርጊት እግዚአብሔር የወደደው ይመስልሃል? ‹‹… አይዞሽ መንፈሳዊ ሕይወትሽ ሳይዘናጋ ሥጋዊ ኑሮሽም ሳይጓደል አብረን እንኖራለን›› ብለህ ሔዋንን የምትሸነግልበት የሽንገላ ከንፈርህ መቼ ድረስ የሚቆይ የትስ የሚያደርስህ ይመስልሃል? ልብ በል ወንድሜ ከዚህም ባሻገር የምነቅፍብህ ነገር አለኝ የሆነውስ ሆኗል አንዳንዶች እንደሚሉትም ‹‹ላለፈ ክረምት ቤት አይሰራም›› ብለን እኔና አንተ ልንቀመጥ አንችልም ላለፈው ላፈሰሰው ሕይወታችን በንሰሐ እያደሰን ለሚመጣው ሕይወታችን ደግሞ በሥጋና ደሙ አንፀን የምንቆይ መሆን ግዴታችን ነውና፡፡
በቅርብ የማውቅህ ወንድሜ አድርጌአለሁ ለውጥ አሳይቻለሁ የሚል ስሜት በላይህ ይሰማኛል እውነት ነው አድገሃል ለውጥም አሳይተሃል ከዚህ ወዲያ ማደግ ከዚህ ወዲያ መለወጥ ምን አለ? እንደ ካሮት በትዕቢት ፈርጥመህ ቁልቁል ወደታች አድገሃል እንደ እስስት ገላ ዘመኑን የጉባኤውን መሳሳት የሰውን መዳከም ተመልክተህ ከቀድሞ ምግባርህ ርቀህና ቀርተው ለውጥ አሳይተሃል? … ወንድማለም የእናቴ ልጅ መቼ ይኼ ብቻ ‹‹ሥራህንና ድካምህን ትዕግሥትህንም አውቃለሁ ክፉዎችንም ልትታገሥ እንዳትችል እንዲሁም ሳይሆኑ ሐዋርት ነን መናፍቃንን የሚሉትን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ ታግሠህማል›› እውነት ነው የእናቴ ልጅ በቤት ቁጭ ብለህ እስከ አንድ ቀን በደንብ እስከምትጠፋበት ዕለት ድረስ ከደሞዝህ አሥራት በኩራት የመክፈል ሥራህንና ድካምህ በእውነት እኔም ሳልቀር በቀሪ ደረሰኝህ አውቃለሁ እኪነኩህ ብቻ ድረስ አፍንጫህ ላይ ያለችውን ትዕግሥትህን በደንብ አድርጌ አውቃለሁ ይልቁንም አፅራር ቤተክስቲን መናፍቃንን በትምህርተ ወንጌል ልትገስፅ እየተገባህ ብርቱ መሰል ደካማ ትዕግስትህንም አውቃለሁ ዳሩ ግን ‹‹በእውነት ስለ እውነት ስለክርስቶስ መንግሥት ጸንተህ አልደከምክምና የምነቅፍብህ ነገር አለኝ የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃል፡፡›› አንተም አትሰለችም ብዕሬም አትነጥብም ደግሜ እፅፋለሁ፤ ተለውጠህ ቆየኝ፡፡
በቅርብ ለማውቅህ ወንድሜ ከቅርብ ከምታውቀኝ ወንድምህ


ይቀጥላል

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...