ሐሙስ 25 ኤፕሪል 2013

የአጋጣሚ ነገር ….


ዛሬ ሰኞ መጋቢት 9/2005 ዓ.ም. ነዉ፤ ሰኔና ሰኞን አለመሆን እንዳለ ሆኖ ለሰራተኛና ለተማሪ ደሞ የባሰዉን ነዉ፡፡
የትራንስፖርት ችግር ደግሞ ሰኞ አያዉቅ ማክሰኞ የለ ሁሌ ችግር ነዉ ለነገሩ ለእናንተ መንገር ለቀባሪዉ አረዱት ይሆንብኛል፡፡
አሁን ስለትረንስፖርት ችግር ላወራ አይደለም፤እንዲያዉም እናቴ በአፍ ይሄዳል ትል ነበርና  … … መተዉ ሳይሻል አይቀርም፡፡
……….. ነገሩ እንዲህ ነዉ፡- በጠዋት ተነስቼ ወደ ሥራ ገበታዬ እያመራሁ ነበር ፤ መኪናዉ ጉዞዉን ጀምሯል እንሄዳለን፣ እንሄዳለን … መንገዱ አያልቅም ወይ አያስኬድም፡፡
አንዳንድ  ሰዎች የትራንስፖርት መዘጋጋቱን ምክንያት(ተገን) በማድረግ ትዉዉቅ ይጀምራሉ (በአራዳ ቋንቋ ይጀናጀናሉ!) ፡-
በተለይ የከተማ አዉቶቡስ ላይ፤ ለነገሩ አዉቶቡስ አፈጣጠሩ ራሱ ለማፋቀር ይመስላልና ይመቻል፡፡
ቢመቻቸዉ ነዉ መሰል ከስሬ በአንድ ወንበር ላይ የተቀመጡ ጥንዶች(እዚያዉ ጥንድ ለመሆን የበቁ) አጠገባቸዉ ለነበርኩት ለኔም በማይሰማ ድምፅ ያወራሉ (ኧረ እንዲያዉም ይጀናጀናሉ) ሲያወሩ ሲያወሩ ቆዩና እየተጠጋጉ እየተጠጋጉ ሄዱ ከዝያ ጭንቅላቱ እንደከበደዉ ሙዝ አቀረቀሩ ድምፃቸዉ እየጠፋ እየጠፋ ሄደ ግን እያወሩ ነዉ … ወሬ ስለምወድ ነዉ መሰል የማዳመጥ አቅሜን አጠራቅሜ ሞከርኩ ሳይሳካልኝ ቀረ ተስፋ ባለመቁረጥ ስጠባበቅ፡-
“ቅዳሜ አይመቸኝም” የሚል ምላሽ ሰማሁ
“ከሰኞ እስከ ዐርብም ትምህርት አለኝ“ አለች በድጋሜ
አንድ ነገር ጠረጠርኩ ” እንገናኝ እንዳላት”፤
አሁንም ያወራሉ ያወራሉ ድምፀቸዉ ይወርዳል አንገታቸዉ ይሰበራል ይጠጋጋሉ እንደገና ቀና ከፍ  ይልና እንደገና ይጠፋሉ፣ምታ ደሞ በመካከላቸዉ ጥልቅ ይልና በየራሳቸዉ መንገድ በሃሳብ ይጓዛሉ፡፡
በስንት ጭንቅ “ታድያ መቸ ነዉ የሚመችሽ ” አላት፤
መቸ እንደምትነግረዉ ባይታወቅም “እነግርሃለሁ“ አለቸዉ፤
እንዲህ እና እንዲህ እያልን መንገድ ተጋመሰ መዉረጃዬ ተቃረበ ለዛሬ ምነዉ ሩቅ ቦታ በሄድኩ አስባለኝ፤
ስልክ ሲለዋወጡ አላየሁም አልሰማሁም፣ ሲስማሙና መቼ እንደሚገናኙ የደረሰኝ መረጃ የለም፤
… … …. ጥያቄ ቢጤ ወደናንተ ልሰንዝር፡-
የነዚህ ሰወች መጨረሻ ምን ይሆን?
አግባብነቱስ ምን ያህል ይሆን?
መቸ ነዉ የሚገናኙት?
የት ነዉ የሚገናኙት?
ተገናኝተዉስ ምን ያደርጋሉ?
… … እናንተስ ከምትወዱት/ ከምትወዷት ጋር እንዴት ነበር የተዋወቃችሁት?
የት ተገናኛችሁ ?... ምን አደረጋችሁ?... በፖስታ ነዉ ወይስ በስልክ ነበር የምትገናኙት?.... ሰዉ በመላላክስ የተገናኛችሁ ሃሳባችሁን ስጡበት፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...