ጊዜው ከባለፈው ምንም ለውጥ የለው ሁለመናው ተመሳሳይነትና አንድነት አለው ግን እኔና አንተ ተለውጠናል ነቀፌታ በዝቶብናል በሥጋ ሥራ ወጥመድ ተጠምደን በውዳሴ ከንቱ ተጠልፈን በትዕቢት ወድቀናል የትላንት ማንነታችንን ዘንግተን ዛሬን ጠፍተናል ለሁሉ ነገር የነበረንን የቀድሞ ፍቅራችንን ትተናል፤
ወንድማለም በደንብ በቅርብ አውቅሃለሁ ታውቀኛለህ የቀድሞ ፍቅርህን ትተሃል ባለፈው በክፍል አንድ እንደፃፍኩልህ በጀማሪነት ስሜታችን ወቅት የነበረው አጠቃላይ ፍቅራችን ቀዝቅዟል መንፈሳዊነት ይናፍቅህ ነበር መዝሙር መዘመሩ ከበሮ መምታቱ ጉባኤ መሄድ ከወንድሞች ከእህቶች ዘንድ መገሰፁ ንሰሐ መግባቱ ሥጋና ደሙን መቀበሉ ገዳማት አድባራት በእግር ሄዶ ተሣልሞ መምጣቱ ማገልገሉ … ወዘተ ይናፍቅህ ነበር እጅግም ታፈቅር ነበር ለነዚህ የነበረህ ፍቅር በሰዎች ዘንድም በቤተክርስቲያንም ተመስክሮልህ ነበር ለጊዜው በነበረው ፍቅርህ በቤተክርስቲያን ሰነባብተህበትም ነበር ዛሬ ዛሬ ግን ያኔ የነበረውን የቀድሞ ፍቅርህን ትተሃል ለቤተክርስቲያን ካለህ ፍቅር የተነሳ የምትቀናው መንፈሳዊ ቅናት በውስጥህ የሚቀጣጠለው ይጠፋ የማይመሰለው የመንፈሳዊነት ፍቅርህ ትዝ ይለኛል ይልቁንም ለወንድሞችና ለእህቶች ትንሽ ትልቅ ሳትል የምታሳየው ፍቅርህ የማልዘነጋው ነገር ነው አፅዋማትና የንግስ በአላት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት የማህበር አገልግሎት በመጣ ቁጥር ታሳየው የነበረው ሰለቸኝ ደከመኝ የማይሉ በፍቅር የተዋጠ የመታዘዝ ውበትህ ዕለት ዕለት ለሌሊት እንቅልፍ ለቀን እረፍት ሳያሰኝህ የምትተጋው ትጋትህ አርአያነት የነበረው መንፈሳዊ ሕይወትህ ከፊቴ ድቅን ይላል፤ ወንድማለም መንፈሳዊነትን በጀመርንበት ሰሞን ያንተ ፍቅር የነበረው ሕይወትህ በሰዎች ሁሉ ዘንድ ያንተነት ሕይወትህ የት ይደርሳል ሲያሰኘን ነበር የከረመው ዛሬ፤ ዛሬ ግን ከቀድሞ ስፍራህ አለመኖርህ በትናንት ማንነትህ አለመገኘትህ በያኔው ሕይወትህ በወደፊት ዓላማህ ፀንተህ አለመገኘትህ እጅግ አሳዝኖናል ምንም እንኳን በነፍሳችን ዝለን እንዳንደክም የፀኑትን ማሰብ ቢገባንም ያንተ የቀድሞ ፍቅርህን መተው ለኛ ለነገ ማንነት አስግቶናል በደሙ የተመሰረተች ቅድስት ቤተክርስቲያን ምንም መናወፅ የማይኖርበት የሲኦል ደጆች የማይችሏት ቢሆንም የቀድሞ ፍቅራቸውን የተው ሰዎች መታጎሪያ መሆኗ እጅግ አሳዝኖናል ወንድማለም የእናቴ ልጅ የቀድሞ ፍቅርህ የዛሬ ግን ማንነትህ ቁልጭ ብሎ ቢታየኝም ዛሬም ድረስ ከምህረት አደባባይ ከደጉ ንጉስ ደጅ ከቅድስት ቤተክርስቲያን ደጅ ነውና ያለኸው የቀድሞ ምግባርህን ፍቅርህን ትህትናህን አገልግሎትህን … ወዘተ ገንዘብ አድርግ ‹‹እንግዲህ ከወዴት እንደወደቅህ አስብ ንሰሐም ግባ የቀድሞውንም ሥራህን አድርግ አለዚያ እመጣብሃለሁ ንሰሐም ባትገባ መቅረብህን /ሕይወትህን መንፈሳዊነትህ ልጅነትህን ማንነትህን ርስትህን … / ከስፍራው እወስዳለሁ›› ይላልና ጠንቀቅ በል በቅርብ የማውቅህ ወንድሜ ዛሬን በመድረሰህ ያለህ መስሎሃል ነገር ግን ሳትዘነጋው ዕለት ዕለት ልታስበው ልታደርገውም የሚገባህ ነገር ንሰሐ ነውና ንሰሐ ግባ ተበልተህ ማለቅህንም አትዘንጋ የቀድሞ ፍቅርህ ትተሃልና ተጠንቀቅ ፍቅርን ገንዘብ አድርግ፡፡
በቅርብ ለማውቅህ ወንድሜ በቅርብ ከምታውቀኝ ወንድምህ
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ