ሐሙስ 20 ማርች 2014

Part one “… … አጋጣሚ”

“የህዳር ሚካኤል ካለፈ አንድ ወር ሆኖታል ታህሳስ ከገባ ደግሞ 11ኛ ቀኑ ነዉ እንደከዚህ በፊቱ በፌስ ቡክ እናወራለን፣ ምሥጢሬን ሁሉ ነዉ የምነግረዉ አንድም የምደብቀዉ ነገር አልነበረኝም፤ እህቴ እቤት ዉስጥ የጤና ባለሙያ ሆና ሳለ ትንሽም ራሴን ሲያመኝ በጣምም ምቅቅ ብዬ ጨጓራዬ ሲያሰቃየኝ የማወራዉ ለሱ ነበር፡፡
በጣም እጅግ ሲበዛ በ…ጣ ም ይመክረኛል፣ ያፅናናኛል እኔም ምን እንደሆነ አላዉቅም እፅናናለሁ፣ ወዲያዉ የማላዉቀዉ ጤንነት ይሰማኛል፡፡ በነበረን ጊዜያት አንዴ ብቻ ነዉ የማደርገዉን ነገር ያልነገርኩት እሱንም አስቤዉ አልነበረም በዚያን ጊዜ ሲጠፋብኝ በጣም ቅር አለኝ፤ በነጋ ቁጥር የፀሐይ ብርሃን ሳይሆን የርሱ ድምጽ ነበር የሚናፍቀኝ፣ ስልኬን ስሰጠዉ ምንም ቅሬታ አልነበረኝም ፣ የመኖሪያ ቤቴን ሰፈር ሁሉ ስነግረዉ ደስ እያለኝ ነበር፣ አሁን ግን እነዛ ድምጾቹ የሉም ርቀዉኛል፤ የሚገርመዉ ድምፁን የምናፍቀዉ ኔትወርክ በሌለበት ስፍራ ነዉ፡፡ ተራራ ባየሁ ቁጥር ሞባይሌን እንደ አቅጣጫ መጠቆሚያ ከመዳፌ አላርቃትም ነበር፤አሁንም አሁንም ደጋግሜ አያታለሁ ቻርጅ ባየሁ ቁጥር መሰካት ነዉ ከሞባይሌ ርቄ መሄድ ጥሩ ስሜት ከማይሰሙኝ ነገሮች መካከል ዋነኛዉ ነበር፡፡ ቀናቶች እየነጎዱ ጤናዬም መለስ እያለ ስለመጣ ወደ አዲስ አበባ መመለስ ፈለኩኝ እንድመለስ ያደረገኝ የጤናዬ ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ እሱን የማግኘት ፍላጎቴ ካቅሜ በላይ ስለሆነብኝም ጭምር እንጂ ፡፡ ለነገሩ ወደዚህ ስመጣ ስራዬን ለቅቄ ነበር የመጣሁት ልቤ ግን ክፍል ለማለት ወደኃላ አልል አለኝና አስጨነቀኝ፡፡ደብረ ብርሃን ስደርስ ጭንቀቴ እየጨመረ ሄደ፣ መንገዱ ራቀብኝ፣
መነሐሪያዉ ሁሉ ባዶ መሰለኝ፣አዲስ አበባ የሚል መኪና ሳጣ ተስፋ ቆረጥኩ …. … ስልኬን ደጋግሜ አየሁት ኔትዎርኩ ሙሉ ነዉ፤ ልዱዉል እልና የሆነ ነገር እጄን ይይዘዋል፡፡ ሴትነቴም “አንቺ አርፈሽ አትቀመጭም” ይለኛል …. …. እዉነትም ሴትነቴንማ ማስደፈር የለብኝም እልና ራሴን እንደመገሰፅ እላለሁ የዉሸቴን መሆኑ እየገባኝ፡፡
አሁንም ምክሮቹ፣ማፅናኛዎቹ፣ነጎድጓዳማነት ባህሪ ያላቸዉ ድምፆቹ፣ …… አንድ ባንድ ጆሮዬ ላይ እየተመላለሱ ያቃጭሉብኛል፤ … … (ጨካኝ! እንደዉም አላናግረዉም … … አደራሽን የጻድቃኔዋ እመቤት መቻሉን ስጭኝ፣ ማን ስለሆነ ነዉ የሰዉን ስልክ ወስዶ፣ ሰፈሬን ሳይቀር ጠንቅቆ አዉቆ እንዲህ የሚጫወትብኝ) እያልኩ መነሃሪያ ዉስጥ ቁጭ ብዬ አጉተመትማለሁ፡፡
 “አዲስ አባ አድስ አባ የሞላ አንድ ሰዉ” ይላል የሚኒባሱ ረዳት ዞር ስል እነዚያ እኛም ከጠዋት ጀምረን የአዲስ አበባን መኪና እየጠበቅን ነዉ ከጠበል ነዉ የመጣነዉ ያሉት ሰወች የተቀመጡበት ቦታ ላይ የሉም፤ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ሰዉ ብንን ብዬ ሮጬ ወደ መኪናዉ ስሄድ ቅድም አይተዉኝ የነበሩ እናት፡ ምን ነክቶሽ ነዉ የሰዉ አገር ላይ በሰላም ወደ ቤትሽ መግባት ትተሸ የምትዞሪዉ በረከትሽንም ወደቤትሽ ነዉ ይዘሽ መግባት ያለብሽ እንደዉ የዛሬ ልጆችኮ ሁሉ አይቅርብን ናችሁ ቀድሞ ነገር ወደገዳም ባትመጡ ከመጣችሁ ደግሞ ተመልሳችሁ እዛዉ ያበደች አገራችሁ እስክትገቡ ድረስ ምናለ ብትረጋጉ?ትደርሱበታላችሁኮ ኧረ ተዉ፤
ዉስጤ የተቃጠለ ነገር እያለ ሌላ ከዉጭ የሚመጣ ነገር የመስማት አቅም ስላልነበረኝ ዝም አልኳቸዉ፤
ረዳቱን መዉጫ ቆርጦ እንዲመጣ ከነገረዉ በኃላ ሞተሩን አሙቆ ሾፌሩ ወደ በሩ ተጠጋ፡፡ጉዞ ወደ አዲስ አበባ ሊጀመር፤
የተቀመጥኩት መስኮት ጥግ ስለነበር ተመቻችቼ ለትራንስፖርት የሚሆነኝን ሳንቲም ነጥዬ ካወጣሁ በኃላ ሞባይሌን ድምፁን አጥፍቼ ቦርሳዬ ዉስጥ በብስጭት ወረወርኳትና  ነጠላዬን ተሸፋፍኜ ደገፍ ከማለቴ እንቅልፍ ይዞኝ ሄደ፡፡ … … …
መኪናዉ ፈሱን እየረጨ ይበራል እኔም ንዴቴን አምቄና ተግሳፄን ዋጥ አድርጌ እንቅልፌን እየለጠጥኩ ጎዞዉ ቀጥሏል፤ … … እነ ሸኖ ሰንዳፋ በኬ አሌልቱ ተጋምሰዉ ካራ ልንደርስ ትንሽ ሲቀረን ወራጅ በሚል አጠገቤ በነበሩት እናት ድምፅ ከእንቅልፌ ነቃሁ … … ሴትዮዋ ሳይሄዱ እማማ! አልኳቸዉ
“አቤት! ልጄ” አሉ ወደኔ ዞር እያሉ
ቅድምኮ … … ብዬ ዝም አልኩኝ
“ቅድም ምን?... …”
ዝም አሁንም … …
“ወራጅ! ወራጅ አልኩህኮ ልጄ አልሰማኸኝም?”
“ሰምቼዎታለሁ ቦታ አጥቼ ነዉ ልያዝና አወርዶታለሁ”
ቅድም የጠፋሁትኮ የትም ሄጄ አይደለም ቁጭ ባልኩበት በሃሳብ ጭልጥ ብዬ ስላልሰማሁ ነዉ ፤ …. …
አላስጨረሱኝም “ሃሳብሽንማ እዛዉ …. እዛዉ ደጇ እንጂ ማራገፍ የነበረብሽ አሁን መንገድ ላይ ማንቀላፋት ምን የሚሉት ነዉ … ወራጅ ልጄ አሳለፍከኝ፤”
ብለዉ ጥለዉኝ ወረዱ ለዓይን ያዝ ያደርግ ስለነበር ስንት ሰዓት እንደሆነ ለማየት ሞባይሌን ሳወጣ ብዙ ሚስድኮል (Missed call) አገኘሁ በአንድ በኩል ድምፁን ማጥፋቴ እንቅልፌን እንድተኛ ስለረዳኝ ደስ ሲለኝ በሌላ በኩል ደግሞ በማላዉቀዉ መንገድ ቆጨኝ ፤
ቁልፉን ከፍቼ ስመለከት የአንድ ሰዉ ተደጋጋሚ ጥሪ እንደነበር ተረዳሁ ስሙን ሳየዉ ምንም አልመሰለኝም ከፊት ለፊቴ እንዳላየዉ አጠፋሁት፣ አሁን ደግሞ ያልተነበበ አንድ የጽሑፍ መልዕክት (SMS) አለኝ ፡፡
እንዲህ የሚል ነበር ፡- “ለምን 16 ግዜ እንደ ደወልኩ ታዉቂያለሽ ኪዳነ ምህረትን ስለምትወጂት ነዉ ግን ያረጋገጥኩት እንደማትወጃት ነዉ ስልኩን አታንሺ በፌስ ቡክ ላይም የፃፍኩልሽን መልዕክት አንብበሽ አትመልሺ ግን እባክሽ ጥፋቴን ሳላዉቅ ስቀር ስለሚያመኝ ጥፋቴን ነገሪኝ … … ሌላዉ ይቅር!”
ዉስጤን በገዛ ጥፋቴ አደነደንኩት የጽሑፍ መልዕክቱንም ከሳጥኔ አጠፋሁት ማሰብ ሁላ አልፈልግም መኪናዉ መገናኛ ላይ አራገፈን እኔ ግን በጭንቅላቴ የተሸከምኩትን ሸክም ማራገፍ ሳልችል ጤናዬ ተመልሶልኝ በሌላ ጤና መታወክ ተነድፌ ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ እማማ እንዳሉት ሳላራግፈዉ የመጣሁት ነገር ቢኖር የርሱን ነገር ነዉ በጆሮ ግንዴ ላይ እየደጋገመ የሚጮኸዉን፡፡
ለካ ለጸበል እንደምሄድ ያሰብኩትን ሁሉ ስለምነግረዉ የነገርኩት መስሎኝ ሳልነግረዉ ሄጃለሁ ያ ያልነከርኩት ነገር ለጸበል መሄዴን ነበር፤ እሱም ሲጨነቅ ምን አድርጊያት ነዉ? ብሎ ግራ ሲጋባ ሰንብቷል እኔም በአካል ከማላዉቀዉ ሰዉ ጋር ስጣላ፣ ስናፍቅ፣ ስጠብቅ፣ …. ስንቱን ነገር ስሆን ከርሜ መጥቻለሁ፡፡ እንደመጣሁ እንደዛ ልበሳጭ ፣ ልወስን እንጂ ጥፋቱ የራሴዉ ስለሆነ እንደምንም ብዬ ይቅርታ ጠይቄ ተመልሰን እንደ ድሮአችን ሆንን፡፡ እኔ ግን ምን አስዋሸኝ በጣም ናፈቀኝ፤ ነፍሴ ሁላ ተጠማችዉ፡፡አንድ ቀን ተሳስቶ እንገናኝ ቢለኝ ካፉ አላስጨርሰዉም … ግን እሱ አይናፋር ሆኖ ይሁን ፣ አክበሮኝ፣ ወይ ኮርቶብኝ ይሁን በማላዉቀዉ ሁኔታ አንድም ቀን እንገናኝ ብሎ ጠይቆኝ ሳያዉቅ ቀረ አንዳንዴ እንደ ሞኝ ያደርገኝና ምናልባት ጠይቆኝ እምቢ ብየዉ እንደሆነ እልና የተፃፃፍናቸዉን ወደ ኃላ ተመልሼ አነባቸዋለሁ፡፡ እሱቴ አድርጎትም አያዉቅ፣ ባለትዳር ይሆን እልና አስባለሁ ይሁና ምን ችግር አለዉ እኔ ሴቷ እንደዛ ያላልኩ እሱ ምን ልሁን ነዉ እንዲህ የሚዘንጥብኝ እልና ብቻዬን እብሰለሰላለሁ፡፡ የሚገርመዉ ስንገናኝና በፌስቡክ ስናወራ ከመደሰቴ በቀር በምንም አጋጣሚ ይህን ጥያቄ ላነሳለት አላስብም በሽታዬ የሚነሳብኝ ከመስመር ሲወጣ እና ሳጣዉ ያገረሽብኛል፣ብርድ ብርድ ብርክ ብርክ ይለኛል፡፡ “እሱ ሲፈራ እኔ ስኮራ” አለች ጓደኛዬ ይህ አጉል መኩራት ግን በጣም እየጎዳኝ የዚህ ጥሩ ሰዉ ፍቅር  አ.. አይ ናፍቆት እየጎዳኝ እኖራለሁ፡፡
ነገሩ ግን ስር እየሰደደ ሲመጣ ከዕለታት አንድ ቀን እንደ ልማዴ ከራሴ ጋር ስማከር ቆየሁና ከተኛሁበት ብድግ አልኩና እንደ ነገሩ እራሴን አዘገጃጀሁና ወደ ፎቶ ቤት አመራሁ ወንደሰን ስቲድዮ ፎቶ በተለያየ አይነት ስታዬል ተነሳሁና ይዤ መጣሁ፤ ይዤ ልምጣ እንጂ ምን እንደማደርግ በቅጡ አላሰብኩበትም ነበርና ስሄድ ያሰብኩት ሃሳብ ዉሃ በላዉ፡፡ ፎቶዉን አነሳሴ ፕሮፋይሌ ላይ የተለጠፈ እኔን የሚገልጥ ምንም አይነት ምስል ስላልነበረ ነገሩ ሁሉ አሁን እየተገለጠልኝ ስለመጣ ምናልባት ፎቶዬን ያየ እንደሆነ ምናልባት ሊያየኝ ይጓጓ እንደሆነ የሚል ሃሳብ ይዤ ነበር የተነሳሁት ሃሳቡ ጥሩ ቢሆንም በጄ ያለዉ ፎቶግራፍ ወረቀት እንጂ ሶፍትኮቲ ስላልነበረ ስካን መደረግ ነበረበት አለበለዚያም ካሜራዉ የግድ በጄ መኖር ነበረበት፡፡ ስራ ካቋረጥኩ ወራቶች ስለተቆጠሩ በጄ ላይ ምንም ቀሪ ሳንቲም ስላልነበረ የትም ሄጄ ይህን ማድረግ አልቻልኩም፤ እህቴ የፎቶ ካሜራ እንደነበራት ባዉቅም የት እንዳለ ስለማላዉቅ ደዉዬ መጠየቁን ፈራሁ፡፡ እህቴ ከቤታችን ሃይለኛ ናት! ሁለት ታላላቅ ወንድሞች ስለነበሩኝ እነሱ ካለበት ይዘዉልኝ እንዲመጡ ለሁለቱም ደዉዬ ነገርኳቸዉ እንኳን ጠይቄአቸዉ እንዲሁም ስራ በመፍታቴም ሆነ ታናሽ እህታቸዉ በመሆኔ ልዩ ፍቅር ነበራቸዉና አንደኛዉ ምሳ ሰዓት ላይ ሁለተኛዉ ደግሞ በጣም አሪፍ ካሜራ ማታ ይዞልኝ መጣ፡፡ ግን የሚያሳዝነዉ ወደ ኮምፒዉተሬ ፎቶግራፉን የማስተላልፍበት ገመድ(cable) ስላልነበረኝ የግድ የእህቴን መጠቀም ነበረብኝ፡፡ ወንድሞቼ ማታ የምሰራዉን ሲያዩ በጣም ሲያበሽቁኝ ነበር ያመሹት በቃ እህታችን እቤት ስትተኛ መዋሉን በድል ልታጠናቅቅ ነዉ፣ ፎቶዎቿን በፌስቡክ ለጥፋ አግቡኝ ልትል ነዉ፤ በማለት ቢያበሽቁኝም እኔ ግን ያሉት ከዚያ የማይተናነስ ስለሆነ ጆሮዬን ሳልሰጣቸዉ ስራዬን ቀጠልኩ እህቴ ግን የምን እንደዚህ ለልጅ ፊት መስጠት ነዉ በማለት ተቆጣቻቸዉ፡፡ ለእህቴ ሁሌም ልጅ ልሁንጂ እኔ የማላዉቀዉ ነገር የለም የወር አበባዬ ሁሉ ሲመጣ እኔ ምንም እንደማለዉቅ ነገር እርሷ ነበረች ሁሉን ነገር ገዝታ የምትመጣዉ፡፡
ሰዉየዉ የማይሞቀዉ የማይበርደዉ ነዉና እንደዚያ ተጨንቄ ተጠብቤ ለርሱ ብቻ ብዬ የለጠፍኩትን ስንቱ ስንት ነገር ብሎ ስፅፍ ሲለክፈኝ እሱቴ መዉደዱን የሚገልጽ ነገር (like) ከማድረግ ዉጭ ምንም አላለም፡፡ ይሄኔ ደሜ ፈላ የተደፈርኩ ያህል ስሜት ተሰማኝ፣ በአንድ በኩል እንደማልፈለግ እየገባኝ መጣ ግን ከዚህ በፊት በነበረኝ ህይወቴ ከወንድ ጋር እንኳን ሆኜ አይኑን የሚጥልብኝ ሰዉ እጅግ ብዙ ነበር አሁን ግን ምን እንደተፈጠረ ግራ እስኪገባኝ ድረስ እርሱ ድርግም አርጎ ዘጋኝ፡፡ የሚገርመዉ የቁም መስታወት ጋር ቆሜ ራሴን ለረጅም ሰዓት ቆሜ ካየሁ በኃላ ሰራተኛችንን አምራለሁ? ብዬ ቀጥታ መጠየቁን አፈርኩና ጠርቻት ከሳሁ አይደል? ብዬ ጠይቃታለሁ፤ በዕድሜዬ ወፍሮኮ አላዉቅም እርሷ ደግሞ የማይባለዉን ሁሉ ዉዳሴ ከንቱ እንደ ወንድ ታዥጎደጉድብኝ ጀመር፡፡ አቤት እንዴት እንደምታምሪ! እዚህኮ ተኝተሸ መዋልሽ በጀሽ እንጂ ወደቤትሽ መመለሻም መንገድ አታገኚም ነበር እስኪ ወደዛ ዞር በይስቲ እስቲ…እስቲ ቂጥሽ ደሞ እንዴት ያምራል፣ ስምንት ቁጥር ነዉ የምትሉት አዲስ አበቤዎች እንደዛም አይደል እንዴ አይ ልጅት እስኪ በአባትሽ አጥንት ይዤሻለሁ እስቲ እዚህ ከምትጋደሚ አንዳንዴ ወጣበይና ይህን ወንድ ታዝበሽዉ ነይ፡፡ ዝም በይ! ብዬ ስጮህባት ብን ብላ ከፊቴ ጠፋች፡፡እኔም ተመልሼ ከአልጋዬ ላይ ተቀምጬ በትካዜ ቀኔን አረዘምኩት ሰራተኛችን በጣም ታከብረኝ ስለነበር እንደዛ መናገርዋን እንደነዉር ቆጥራ በኔ መቆጣትም ተደናግጣ ምሳ ብይ ሳትለኝም ብን ብላ ጠፍታ ዋለች፡፡
ፈልጌ ሳገኛት ምን ሆነሽ ነዉ ምሳዬን ሳትሰጪኝ? ብላት
“እህ! በምን ዓይኔ ልይሽ ብዬ ግራ ቢገባኝ ነዋ እንደዛ ፊት አገኘሁ ብዬ ስቀላምድ ነዋ መጥፋቴ፤”
 አንቺኮ ምንም አላጠፋሽ እንደዉ እኔ ዝም ብሎ የሆነ ነገር ሲያበሳጨኝ ነዉ አንቺን የተቆጣሁት ይቅርታ! አልኳት፡፡
“ለምኑ ነዉ ደሞ ይቅርታ እኔ ባጠፋሁ ደሞሳ ባላጠፋስ እኔን ይቅርታ እማይደረገዉን በሉ ይተዉትና ምሳ ምን ላምጣ፡፡” ሲፈልጋት አንቺ ሲፈልጋት እንደዛሬዉ ነገረ አለሙ ሲደበላለቅባት አንቱ እያለች ስታስቀኝ ትዉላለች ሾርባ እንድታመጣልኝ ነገሬያት ልብሴን ልቀይር ወደ መኝታ ክፍሌ አመራሁ፡፡
“እንደዉኮ ደግነቱ እዚህ ግቢ ከኔ በቀር የሚዉል ሌላ ሰዉ ማለቴ ወንድ የለም እንጂ እንደ ህጻን … … ብላ አፏን አፍና ሳቀች፤”
 ምን! ብዬ አፋጠጥኳት
“ኧረ ዝም ብዬ ነዉ የሰይጣን ጆሮ ይደፈን … … ይደፍሮታል ብዬ ነዉ፡፡”
 ብዙም ቀልድ ጥሩ አይደልም ብዬ ዝም አልኳት በልቤ ግን የሆነ ደስታ ተሰማኝ ስለመደፈሬ አልነበረም እንደዉ የሴትነት ስሜት አለ አይደል መጥቶ በላዬ ላይ ክልብስ አለብኝ፡፡የቀረበዉን ምግብ በልቼ በረንዳ ላይ ተቀመጥኩና ግቢዉን መቃኘት ጀመርኩ ሻይ ይምጣ? አለችኝ እነደማልፈልግ ስነግራት ላብቶፑን አንከብክባ አመጣችልኝ፤
“እንዲሁ ከሚቆዝሙ ይችን ይዘዉ ፈገግ ይበሉ” ብላኝ ስትሄድ ነገሩን ሁሉ ያወቀችብኝ መሰለኝ፡፡
እንዳለችዉም ፌስቡክ ከመክፈቴ ቀጥታ እሱን መፈለግ ጀመርኩ የለም! … … ፤ ብዙ መልዕክቶች ግን በዉስጥ መስመር መተዉልኛል አንደኛዉ ብቻ ሲሆን የተቀረዉ በጠቅላላ የወንዶች ነዉ ሁሉም መንፈሳቸዉ አንድ ነዉ የኔ ቆንጂ፣ በጣም ታመሪያለሽ፣ … I miss you ወዘተ ነበሩ፡፡ ከዛ ሁሉ የሳበኝ የርሱ መልዕክትና የሴት ጓደኛዬ ነበር፡፡ እሱ እንደ ልማዱ ስለጤናዬና ስለመጥፋቴ ትንሽ ከማዉራቱ በቀር ምንም ፍንጭ የሌለዉ ነገር ሲሆን ጓደኛዬ ደግሞ ቅዳሜ ማታ አዲስ የሆነ የጓደኞቿ ወንድም ክለብ ስለከፈተ ተጋብዘናልና እንሂድ የሚል ጥሪ ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ እሷ ከባልዋ ጋር ስትሄድ እኔ ደሞ እንደ መጀመሪያ ልጃቸዉ ስርስራቸዉ ሄዳለሁ ለድሮዉ ምንም አይመስለኝም አሁን ግን በጣም ደበረኝ፡፡ማንም እየመጣ አብረን እንደንስ እያለ እያስፈቀዳቸዉ ሲጎትተኝ ያለምንም ተቃዉሞ በደንብ ደንሼ መጣ ነበር ላሁን ግን እንደዛ የምሆን ስላልመሰለኝ ምንም ምላሽ አልሰጠኃትም፡፡
ድንገት እንደተቀጣጠረ ሰዉ ቀጥታ መስመር ላይ ሲገባ አገኘሁት ወዲያዉ ሰላም ስለዉ መልዕክቱን ከላኩ በኃላ በመጣደፌ ራሴን ታዘብኩት በሴትነቴም እፍረት ተሰማኝ ደስ የሚለዉ ነገር እሱም ወዲያዉ ስለመለሰልኝ ያ ሁሉ ቅሬታ እንደጉም በኖ ጠፋ፡፡
ምነዉ ጠፋህ?      
“አንቺ ነሽ እንጂ የጠፋሽዉ እነደዉም ምን አጠፋሁ ብዬ ሁላ ልጠይቅሽ ነበር፤”
በአካል ነዉ ወይስ …. …
“ምነዉ! በየትኛዉ ይሻላል?”
እንደ ጥፋትህማ ከሆነ በአካል ነበረ፤
“ታዲያ ስለጥፋቴ ምህረት የማገኝበት ከሆነ ምን ችግር አለዉ መጣለሁ”
የት ብለህ?
“ሰፈሩን ነገረኝና ቤታችሁን ግን አላዉቀዉም” ሲለኝ ስፍስፍ አረገኝ
አልጠፋብህም ማለት ነዉ ሰፈራችን ?
“መቼ መጣሁ?”
ማለቴ የነገርኩህ እንጂ
“አዎ!”
አሁን የት ሆነህ ነዉ?
“እቤት”
ምን ትሰራለህ?
“ምንም “
ታዲያ በስራ ቀን እቤት ለምን ተገኘህ?ማለቴ ስራ የለም ?
“አይ!” አለ “……እንዳንቺ እቤት ልሁን ብዬ ነዉ”
ማን አለ?
“ማንም!”
ብቻህን ?
“አዎ!”
ልምጣ?  በድንጋጤ የድማሚት ያህል ድምጽ ያለዉ ነገር ሲጮህ ዉስጤ ተሰማኝ የባሰ ደግሞ የርሱ ቶሎ መልስ አለመመለስ ጭንቀቴን ጣሪያ አስነካዉ፤ቆይቶ ቆይቶ ….
“እሺ!”  ብሎ ሲመልስልኝ
እቤት እንዳልሆነና ሰፈር ለማለት እንደሆነ ልቤ እያወቀ እሱን ለማስረዳት ተፍ ተፍ አልኩ
“ገብቶኛል!”
ታዲያ መቼ ይሁን? አልኩት በአንድ አፍ ብዬ ከአፉ የወጣዉን ሃሳብ ደግሞ ሳይዉጠዉ፤
“መቼ ይሁን?” በማለት ጥያቁዉን ወደኔ መለሰዉ
በቃ ነገ አልኩት፤
 “ዛሬ ስንት ነዉ?”
ታህሳስ 11 አልኩት
“እንደዉም ይመቸኛል ….” ብሎ የመለሰዉን መልስ ሳነብ ነፍሴ ዉስጤ ቀለጠች ዛሬ አሁን ያለሁበት ሰዓት ጠዋት ይሁን ማታ ለማጣራት ሰራተኛችንን ጠርቼ ስጠይቃት በሳቅ ልትሞት ደረሰች፤የሆነዉ ሆኖ ታኅሳስ 12 ቀን ቤቱ ሄድኩ እልሃለዉ፡፡ ብላ ትረካዋን ቀጠለችልኝ እኔግን ለዛሬ እዚህ ላይ አቋረጥኩት እሷ የተረከችልኝን እኔ እንዳለ ምንም ሳልጨምር በተከታይ ክፍል ዳግም እስክመጣ ቸር ያቆየን!!

በክፍል ሁለት እንቀጥላለን፡፡ ”

1 አስተያየት:

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...