ባለፉት ጊዜያት በሁለት ተከታታይ ክፍል ስለ አንዲት እህታችን የህይወት ታሪክ የሚዳስስ ‹‹ …. …. አጋጣሚ ›› በተሰኘ ተከታታይ ጽሑፋዊ ትረካ መልክ ስንከታተል እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነዉ፤ እነሆ በቀጠሮ የቆየዉ ክፍል ሶስት በጉጉት ሲጠበቅ ከነበረዉ በክርስትና እምነት ተከታዮች የትንሳኤ በዓልን ማግስት ምክንያት በማድረግ በደስታና በፌሽታ ክፍል ሶስትን እንድትኮመኩሙት ተጋብዛችኃል፡፡መልካም ንባብ!የማንበብ ልማዳችን ይዳብር!
…… አጋጣሚ
‹‹ዛሬ የት ልትሄጂ ነዉ? ቤቱን የኛን አገር ጥምቀት አስመሰልሽዉኮ … ›› በማለት የተለመደ ንትርኳን ጀመረች፤
የምትሰራዉ በደመወዝ ሆነ እንጂ ቁርጥ ቤተሰብ ነች፡፡ አንድም ቀን ባዳነቷን አስቤዉም አላዉቅም፣ ከእኔ ጋርማ እንደ ታላቅና ታናሽ
ነዉ የሚያደርገን፤ … በንትርክ ቤቱን ድምቅ እናደርገዋለን፡፡
ምን አገባሽ?
‹‹የማገባዉንማ አንቺን አማክሬ አይደለም የማገባዉ፤ ደሞ እንዲህ እንደ ከተማ ወንድ፡ ወንድ ይሁን ሴት ለመለየት
ግራ የገባዉ ሳይሆን ከሩቅ ሲያዩት ወንድ ወንድ የሚሸት ወንዳወንድ ነዉ የማገባዉ፡፡ ››
ደሞ ለአዲስ አበባ ወንድ ምን ልታወጪለት ነዉ?
‹‹ አታፍሪም ለአዲስ አበባ ወንድ ወግነሽ ስትሟገችኝ ››
ለምን አፍራለሁ?
‹‹ እስኪ ምኑ ነዉ ወንድ የሚመስለዉ? ››
ፈጣሪ ወንድ አድርጎ የፈጠራቸዉን ምንድን ናቸዉ ልትይ ነዉ?
‹‹ ወዴት! ወዴት! እኔ የማወራሽ ስለሁኔታቸዉ፤ አንቺ የምታወሪዉ ስለ አፈጣጠራቸዉ …. በፍፁም አይገናኝም፡፡››
እስኪ አስረጂኝ፤
‹‹ አለባበሳቸዉ ብትይ፣ የፀጉር አሰራራቸዉ፣ የጆሮ ሎቲ፣ …. ምን ቀራቸዉ?››
ፋሽን ነዉኮ! ፀጉር አሰራራቸዉም ደግሞ ሚኒሊክ ነዉ ቴዉድሮስ ተሰርቶት ነበርኮ የጆሮዉም ቢሆን ምንም ማለት አይደል፤
…
‹‹ምን ! ( የድንጋጤ ድምፅ ) የጉድ ቀን አይመሽ ነዉ የሚሉት፤ እኛም ቤት ጉዱ አለና ዝም ብለን ነዉ የዉጭዉን
የምንነቅፈዉ ….. በቃ ተይዉ፡፡ ለመሆኑ የትኛዉ ወንድ ነዉ የጀግና መሳሪያ ሊያነግት የሚቻለዉና ነዉ የቴዉድሮስን ሹሬባ የሚሰራዉ
አናዉቀዉምና ነዉ ድንጋይ ከመወርወር ወዲያ የአዲስ አበባ ወንድ ምን ያዉቅና …. ምኑስ ነዉ ፋሽን? ቂጡን ጥሎ መሄዱ? ዝቅ ባለ
ቁጥር ከፍ እያደረጉ መሄዱ ነዉ ፋሽን? ይሕ ነዉ ወንድነት? ይህ ነዉ ባል የሚሆነዉ? ለምን እድሜ ዘላለሜን ቆሜ አልቀርም ሁለት
ሴት አንድ ቤት ዉስጥ ምን እንሰራለን?››
እንዲህ የምትገርሚ ልጅ መሆንሽን አላቅም ነበር
‹‹ የበላይ ልጅ ነኝኮ የዚያ የቆፍጣናዉ … እንዴት ብታይኝ ነዉ … እንኳን ወንዱ እኔ ሴቷ የበላይ ዘለቀን አጽም
አናስወቅስም፤ ለመሆኑ እንዲህ ቤቱን እና የልብስ ሳጥንሽን ያመስሽለት ወንድ ወይስ ሴት ነዉ?››
(ረጅም ሳቅ) ኧረ ወንድ ነዉ፤ …. ምነዉ?
‹‹ የታጠቀ ነዉ ያጠለቀ?››
ደግሞ ምንድን ነዉ ልዩነቱ?
‹‹ ወንድ ልጅ ጫማዉም ሱሪዉም ጠበቅ ሲል ነዉ ሙሉ ወንድ የሚሆነዉ አለበለዚያ ሱሪዉን ይጎትታል ወይስ ይመክታል?
እስኪ ንገሪኝ! ለነገሩ የዘንድሮ ሴቶችም ሴት አሰዳቢዎች ናችሁ›› (በጣም ተናዳለች)፤
እሷ የባጡን የቆጡን ስታወራ እኔ ወደ መሰናዳቴ ገባሁ፣ ግን ዉስጤን ረብሻዋለች ጥያቆዎቿ ዉስጤ ይጮሃሉ መልስ! መልስ!
እያሉ ስለማላዉቀዉ ሰዉ፤ ምንም ማለት ስለማልችል ዝምታን መረጥኩ፡፡
ቀሚስ፣ሱሪ፣ታይት፣ቁምጣ ሱሪ በታይት፣አጭር ቀሚስ በታይት፣…. ግራ ገባኝ ቤቱን ተመልሼበት የምመጣ አልመስልም፤ እዉነቷን
ነዉ ቤቲ ሴቶች በተቻለን አቅም ወንዶችን በዉበታችን መማረክ እንወዳለን የምትለዉ በተለይ የመጀመሪያ ቀን ቆንጆ ሆነን መታየት እንፈልጋለን
ለዚያ መሰለኝ እኔም ላይ ታች የምለዉ፡፡ የምለብሰዉ ልብስ እንኳን ምርጫዉ እስኪጠፋኝ ግራ የተጋባሁት … ቤት ጋር ለመደወል ስልኬን
አንስቼ ልደዉል አልደዉል በሚሉት ሃሳቦች መካከል ተንሳፍፌ ቀረሁ፡፡
የስልኩ የደዉል ድምጽ በርቀት ጥርት ብሎ ይሰማል፤
ጠርቶ ጨረሰ ስልኩን የሚያነሳዉ የለም፤
ደግሜ ደወልኩ ‹‹የደወሉላቸዉን ደንበኛ ሊያገኟቸዉ አይችሉም›› በዚህ ሰዓት እንዲህ አይነት ድምፅ መስማት አልፈልግም፤
አሁንም ሞከርኩ ፀጥ አይናገር አይጋገር፤ በሰራተኛዋ ሞባይል ለመደወል ወሰንኩኝ ….
‹‹ የደወሉላቸዉ ደንበኛ ለጊዜዉ ….›› አላስጨረስኳትም ዘጋሁት
እንደገና ስሞክረዉ የቤቲ ስልክ ጠራልኝ ….. …. ኧረ ቤቲ አንሺዉ … እንዴ ቤቲ ሰዉ ሲጨነ …. ቅ አታዉቂም?
‹‹ሃሎ ሚሚዬ! ስልኩንኮ የት እንዳረኩት አጥቼኮ ነዉ ….››
ስንት ነገር አለ እንዴት ስልክሽን ያረግሽበት ቦታ ይጠፋሻል?
‹‹ ምን አስደወለሽ ዝም ብለሽ አትመጭም!››
የት ነዉ የምመጣዉ? ባክሽ አሁን እሱን ተይና የምልሽን አድምጭኝ፤
‹‹ ምንድን ነዉ እሱ እንዲህ አስቸኳይ ነገር ተገኝቶ በስልክ ….››
ጊዜ የለኝም አልኩሽኮ! (ቁጣ የተቀላቀለበት ነበር ድምጼ የጀመረችዉን አላስጨረስኳትም)
‹‹እሺ ወደ ጉዳይሽ ግቢ!››
ይኸዉልሽ ቤቲዬ ዛሬ ከትልቅ ሰዉ ጋር ቀጠሮ አለኝ፤ የምሄደዉ ደግሞ አሁን ነዉ! በጣም አርፍጃለሁ ስለዚህ
….››
(አቋረጠችኝ) ‹‹ ወንድ ነዉ ሴት?››
ወንድ! ወንድ ነዉ ቤቲ! ሴት ቢሆን አንቺ ጋር ምን አስደወለኝ?( ቱግ ቱግ ማለቴ እየጨመረ ነዉ ለሌላጊዜ ከእህቴ
የበለጠ የማከብራት እንኳን ተቆጥቼ ጮክ ብዬ ድምጼንም ከፍ አድርጌ አዉርቻት አላዉቅም)
‹‹ ለስራ ነዉ ሚሚዬ?››
አይደለም!
‹‹ ምን አይነት ነዉ? ማለቴ …››
አላዉቀዉም!(ይህንን ቃል ብዉጠዉ ደስታዉን አልችለዉም )
‹‹ ታድያ የማታዉቂዉ ሰዉ ጋር … ››
ቤቲዬ አትጨርሺዉ! ምን መሰለሽ አዉቀዋለሂኮ፤ በአካል ነዉ እንጂ የማላዉቀዉ …. (ድንብርብሬ ወጣ)
‹‹ ታድያ ምን መረጥሽ ወይስ ምንም ….››
አልመረጥኩም!
‹‹ እስኪ አንድ ሁለት ልብስ አዉጭና …››
ቤትዬ ቁምሳጥን ዉስጥ የቀረኝ ልብስ የለም ሁሉንም አዉጥቼ ግራ ሲገባኝ …..ግራ ሲገባኝ ነዉ የደወልኩት!
‹‹ በቃ ምን ታደርጊያለሽ መሰለሽ ….››
እሺ … (የምትለኝ ከአፏ ልነጥቃት ምንም አልቀረኝም)
‹‹ ቆይ ግን ምሳ ነዉ ወይስ …››
አይደለም! ምን እንደሆነ አላዉቅም …. ዝም ብሎ ነዉ…..እ… በቃ አለ አይደል …እንገናኝ …. ተባብለን ነዉ ዝም
ብሎ …(እየቆየ ሲሄድ ስራዬ እያሳፈረኝ መጣ፤ ደግሞ ለዛሬዋ ድርጊቴ ለእያንዳንዷ ቤቲ አሁን አብራኝ ታዉራ እንጂ ጥሩ ዋጋ ታስከፍለኛለች!)
‹‹ ደግሞ እስካሁንም ይህን ያህል ላልታወቀ ነገር
ማዉራታችን ጅንስ ለብሰሽ ሂጂ …. ቻዉ! ስራ አለብኝ››
ቤቲን ስለማከብራት ነዉ እንጂ እንዴት ጅንስ ሱሪ ልበሺ ትይኛለሽ? እላት ነበር …. በቃ እሷ አለች ማለት አለች
ነዉ ልብሶቹን እንዳለ ሰብስቤ ወደ ቁም ሳጥን ዉስጥ እያስገባሁ አንድ ጅንስ ሱሪ አስቀረሁ …
ተረኛዋ እየሮጠች መጣች ከኔ ጋር የቀራት ነገር ያለ ይመስል፤
‹‹ አንቺ ግን እንደዚህ ሰዉ ማስረሳት አለ እንዴ?››
ስለ ምን ነዉ የምታወሪዉ?
‹‹ ስለ ሰዉዬሽ ነዋ!››
ስለ ሰዉየዉ ምን? …..
‹‹ ወንድ ነዉ ወይስ …. ማለቴ እንደዉ የአዲስ አበባ ‹ሴት ወንድም› ነዉ ማለቴ ነዋ!››
ሴት ወንድም ማለት ምንድን ነዉ?
‹‹ ጥያቄዬን ሳትመልሽ ጥያቄ መጠየቅ በጥብቅ የተከለከለ ነዉ ››
አላዉቀዉም! (መበሳጨት ጀመርኩ መንፈሴ ሁላ ዉሃ ተቸለሰበት ስሜቴን አበረዱት)
አፏን አፍና ወደ ማዕድ ቤት እየሳቀች ሄደች! (ቀላሉ የምትተወኝ አልመሰለኝም ነበር ትታኝ ሄደች)
*********** ////*********//////****************
የለበስኩት ጅንስ ይሁን እንጂ ዉስጤ በደንብ ዝግጁ ነዉ፤ ጠረኔ ሁል ጊዜ እንደዚህ ቢሆን ደስታዉን አልችለዉም ‹የተቀመመች›
ሽቱ ነበር የተቀባሁት፡፡ የተቀመመች ማለት እኔ የማዘጋጃት የተለያዩ የወንዶች ሽቱ ዉህድ ናት፤ ልዩ! እጅግ ልዩ ጠረን ….
ሰዓቴ 2፡45 ላይ አመለከተኝ ገና ጠዋት ነዉ ግን ሜክሲኮ ደርሻለሁ፤ ደግሜ ደጋግሜ ሰዓቴን ባየዉም በየእይታዬ መካከል
ቢበዛ የአምስት ደቂቃ ዕድሜ ልዩነት ነበር ያለዉ፡፡
3፡15 ሰዓት ደወልኩለት ወዲያዉ አነሳዉ፤ ‹‹ምነዉ ስልኩ ላይ ተቀምጠህ ነበር እንዴ?›› አልኩት …..
ረጅም ሳቅ ሳቀ! ሳቁ ደስ ይለኛል
ሳናወራ ሰከንዶች አለፉ … ሳቁን አፍኖ ‹‹ሃሎ!›› አለኝ
አቤት!
‹‹ እንዴት አደርሽ? ተኝተሻል ወይስ….››
የተኛሁ መስላለሁ? (ምናለበት ተነስቻለሁ ብዬ ብመልስ …. ሴቶች ስንባል ችግር አለብን ቀጥታ መመለስ አይሆንልንም፤
ደስታችንን እንደ ጠዋት ጤዛ የምናተነዉ ዙሪያ ጥምጥም ስንሄድና ሰበብ ስናበዛ ነዉ፡፡)
‹‹ ማለቴ ጠዋት ነዉ ብዬ ነዋ መቸስ ስራ የማትሄጂ ከሆነ በጠዋት መነሳቱ …. ››
አልተኛሁም! አንተ ተኝተሃል እንዴ?
‹‹ ተኝቻለሁም! ተነስቻለሁም ማለት ይከብዳል …መሃል ላይ ነዉ፤ … ››
እንዴት?
‹‹ ተነሳሁና … መጸዳጃ ቤት ገብቼ ተመልሼ አልጋዉ ላይ ጋደም አልኩኝ! ለዛ ነዉ አልተነሳሁም ተኝቻለሁም አይባልም
ያልኩሽ››
ረሳኸዉ እንዴ?
‹‹ ምኑን? ››
ቀጠሮዉን ነዋ!
‹‹ ሰዓትኮ አልተነጋገርንም ዛሬ መሆኑን እንጂ ….››
እኔኮ ሜኪሲኮ ነኝ!
‹‹ ምነዉ ሳትደዉይልኝ?››
ችግር የለዉም ብዬ ነዋ፤ …. በዛ ላይ እንቅልፋም
ስለሆንክ እንዳልረብሽህ በዬ ነዉ …
‹‹ ማን ነገረሽ? ››
አወኳ!
‹‹ ዝም ብሎ ማወቅ አለ እንዴ? ››
አዎ!
‹‹ ዘዴዉን ለኔም አስኮርጂኝ! እኔም ስለ አንቺ እንዳዉቅ››
የኔንስ እኔ ነግርሃለዉ … ለሌላ ሰዉ ከፈለክ ግን ሰዉየዉን ደጋግመህ በህልምህ ማየት …..
‹‹ በህልም? በህልም …. ›› (ረጅም ጊዜ ዝምታ ሰፈነ)
ካልተነሳህ እስክትነሳ ወደ አንተ ሰፈር ቀረብ ልበል እንዴ?
‹‹ ይቻላል! እንደዉም ሰፈራችንን አስተዋዉቅሻለሁ … ማለቴ አስጎበኝሻለሁ፤››
በቃ ተዘጋጅና ዉጣ እኔ ታክሲ ይዤ መጣለሁ!
***********/////////////******////////////**************
እንዲህ ወንድ ልጅ ለማግኘት እንኳን ቀድሜ የተገኘሁበት በታክሲም የሄድኩበት ወቅት ትዝ አይለኝም፤ ለምንድን ነዉ
እንደዚህ የሆንኩት? የጤና ያድርግልኝ!ዛሬ ደግሞ ሰዓቱ ሲዘገይ ታክሲዉ ይበራል ወዲያዉ አስር ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ የቀጠሮ
ቦታዉ ላይ ደረስኩ ፤ የሆነ ካፍቴሪያ ደርሼ ሻይ አዘዝኩና ያለሁበትን ካፍቴሪያ ጠቅሼ የጽሑፍ መልዕክት ላኩለት፡፡
ወዲያዉ ደወለ፤
‹‹ ሃሎ!››
አቤት!
‹‹ ከምኔዉ ደረስሸ?››
ምነዉ ፈጠንኩ እንዴ?
‹‹ በጣም እንጂ! እስከዛሬ እኔን የሚያክል ፈጣን ያለ አይመስለኝም ነበር ዛሬ ግን ክብረወሰን በመስበር ጭምር የሚበልጠኝ
ሰዉ አንቺ ተገኘሽ፤ … ››
በጣም ሳኩኝ፤ ምንም እንኳን ነገሩም የሚያስቅ ቢሆንም እኔ ግን በራሴ ሳኩኝ …. ከዚህ በላይ ቤትህ አልመጣ እንግዲህ
…
‹‹ ለምን አትመጪም ዝም ብለሽ ካፌ ከምትቀመጪ፤… ››
(አላቅማማሁም!) ይሻላል ብለህ ነዉ? ሰፈሩን አላዉቀዉ፣ እሱን አላዉቀዉ፣ ያለሁበትን ስሜት አላዉቀዉም፤ ቤቲ ‹‹ማነዉ?›› ነዉ ያለችኝ?ማነዉ እሱ… የዚህን ጥያቄ መልስ መመለስ አልፈለኩም
‹እሺ መጣሁ › አልኩት፡፡
***** ****** *******
‹‹ በቃ እሱ ጋር እንደወረሽ ወደ ዉስጥ የሚያስገባ መንገድ አለ ፣ አንደኛን ቅያስ ታልፊ እና ሁለተኛዉን እንዳገኘሽ
በስተ ቀኝ ወደ ዉስጥ ትገቢያለሽ አሁን ደሞ የሆነ ምግብ ቤት ስታገኝ ወደ ግራ ትታጠፊያለሽ እዛጋ ሆነሽ ቀና ስትይ የሚታየዉ መስኮት
የኔ ቤት ነዉ፤››
እንዴ አንተ ወተህ አትቀበለኝም እንዴ?
‹‹ እወጣለሁ …. ምናልባት ስልክ እምቢ ካለ ለቅድመ ጥንቃቄ ብዬ ነዉ ››
እቤት ማን አለ?
‹‹ አሁን እኔና የአንቺ ….››
በቃ አልመጣም!
‹‹ ለምን?››
ሰዉ ካለ ምን ሰራለሁ!
‹‹ ሰዉ ከሌለ ምን ትሰሪያለሽ? … ስለ ሰዉ መኖር ማን አወራ እኔ ያልኩትን ሳታስጨርሺኝ ጣልቃ እየገባሽ ነዉ እንጂ
… አሁን እኔ ቤት ያለነዉ እኔ እና ያንቺ ድምጽ ብቻ ነን ….››
ልቤ መምታቱን እንደ ዛሬ አዳምጬዉ አላዉቅም … በጣም ይመታል፤ የልብ ጤንነት ምርመራ ያደረኩ ነዉ የመሰለኝ፡፡
ያለኝ ቦታ ሆኜ ደወልኩለት የዛሬ አመጣጤ ሁሉ ፈጣን ነበር አሁን ገና 4፡00 ሰዓት ሊሆን ነዉ፤ ዉጣ አልኩት
….
‹‹ የት ደረስሽ?›› እያለ በመስኮት አንገቱን ሲያወጣ ስልኩን ዘጋሁት …
ልቤ የደሬት በር እየደቃ እኔ ደግሞ የሱን በር ማንኳኳት ጀመርኩ፤ የልቤን ምት ድምጽ በእኔ በርማንኳኳት አሸንፌዉ
ወደ ዉስጥ ዘለኩ!
(አስቴር ረጅም ዘለግ ያለ እያለች የዘፈነችለት መልከ መልካም ያለምንም ጥርጥር ይህ ሰዉ መሆን አለበት አልኩኝ በልቤ፤
ልቤ ምቱን ቀንሶ የማደርገዉን ነገር ይከታተላል፡፡ )
አራት ወንበሮች ያሉት የምግብ ጠረጴዛ፣ የተነጠፈ ፍራሽ፣ እንደ ነገሩ ለበስ የተደረገ አልጋ፣ ወደ ዉስጥ ተጋርዶ
በዉል የማይታዩ የማብሰያ እቃዎች፣የልብስ ቁምሳጥን …. በቃ ቤቱ ከዚህ ወዲያ የሚታይ ነገር የለዉም፡፡ ከቆይታ ብዛት ልቤ መረጋጋቱን ሳዉቅ ቤተኛ እየሆንኩም ስመጣ ከተቀመጥኩበት
ኩርሲ ጀርባ መታጠቢያ ቤት አለ፡፡
ፍራሽ ላይ ቁጭ ብሎ ወደ ላይ እያየኝ ክላሲካል ሙዚቃ በሚመስሉ እና በግድ በሚሰሙ ድምፆቹ ጣፋጭ ወሬ ያወራኛል፤
ጆሮዬ ይስማ እንጂ እኔና ልቤ ግን ሌላ ነገር እናወራለን፣ ዉበት እናደንቃለን፣ ዓይን አገላለጥ አከዳደን፣ የአፍ አከፋፈት ለዛ
እና የአፍ አገጣጠም ስርዓት፣ … ያላየሁት ነገር የለም ይህ ግን ዛሬ ብቻ ያየሁት ነገር ነዉ፡፡ አቤት ሥነ ስርአት! አቤት ጨዋነት!
ገዳይ ነዉ፡፡
ለሁለት ሰዓት አንዳች እንግድነት ሳይሰማኝ ሳወራ ቆየሁ እንኳን በአካል በፌስቡክ ሳወራዉ አልጠግበዉም ነበር፤ አወራሁት
አይገልጠዉም እኔ ደስ ቢለኝም እሱ ግን የተቀመጥኩበት ቦታ እንዳልተመቸኝ በማሰብ ጭንቀት ሊገለዉ ነዉ፡፡ በተጨማሪ ግማሽ ሰዓት
ካወራን በኃላ እያወራን ምን የመሰለ ፓስታ ሰርቶ ምሳ በላን፤ ሲያጎርሰኝ እጁ አፌን ሲነካኝ የሆነ ከባድ ሃይል የተሸከመ የኤሌትሪክ
መስመር የነካሁ ያህል ነዘረኝ፡፡
እንግዳዉ እንዳልሆንኩ የሚያስታዉቀዉ ለምሳ የሚሆን ነገር ምንም አለመዘጋጀቱ
ነበር የነገረኝ፤ ለነገሩ ፌስቡክ ላይ የተነጋገርነዉ ሰፈር እንደምንገናኝ እንጂ እቤት እመጣለሁ የሚል ‘’ፈጣጣ’’ ሃሳብ አልነበረኝም፡፡
እቤት የመሄድ ማሻሻያ ሃሳብ ራሱ የመጣዉ ዛሬ ጠዋት እንደመሆኑ መጠን ምንም ስህተት በሱ በኩል አላየሁም፤ እኔም ያረኩት ነገር
ስህተት ነዉ ብዬ አላስብም፡፡
ብቻ ጣፋጭ ቀን ነበር፤
….
(ምግብ ራሱ ጣፋጭ ስለሆነ በአንድ
ጊዜ አያልቅምና እንደ ተለመደዉ በቀጣዩ ክፍል በክፍል አራት ጣፋጭነቱን ሳይለቅ እንዘልቀዋለን! መልካም ቆይታ፡፡)
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ