ረቡዕ 10 ሴፕቴምበር 2014

መልካም አዲስ ዓመት፡

ራስን ሁልጊዜ በአሸናፊነት ዙፋን ላይ …
ይህ ዓለም የዉድድር ዓለም እንደመሆኑ መጠን ይበልጡኑ የሰዉ ልጅ ትልቁን ዉድድር በተሳታፊነት እና በበላይነት ሚናዉን ይወጣል፡፡ ይሁን እንጂ በዉድድሩ ሁሉም በመንፈሰ ጠንካራነትም ሆነ አልሸነፍ ባይነት መንፈስ መሸነፍን አይወድም፡፡ ሁሌም እርሱ አሸናፊ ቢሆን እና በድል ቢያጠናቅቅ ደስ ይለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ዉድድሩ በአንድ ሰዉ የበላይነት ( አንደኝነት ) መጠናቀቁ ግድ ይላል፡፡   ሆኖም ሁሉም ሰዉ በአንደኝነት ሊጨርስ ይቻለዋል፤ ጨርሻለሁ ብሎ ማመንም ማሳመንም ይችላል፡፡ እንዴት?
ሁሉም ሰዉ የሥራ ድርሻ እንዳለዉ የታመነ ነዉ፤ ሁሉም ወደ ዉድድሩ የሚገባዉና የአሸናፊነት አክሊሉን ሊደፋ የሚችለዉ እየሰራ ባለዉና በሚሰራዉ መስክ ነዉ፡፡ ማንም ሰዉ አንተ እየሰራህ ያለዉን ሥራ አንተ በምትሰራዉ መንገድ አይሠራም፣ አልሠራምም፤ ስለዚህ ይህንን ሥራ በምታጠናቅቅበት ሠዓት አሸናፊዉ አንተ ነህና፡፡ ተወዳዳሪህን ባታሸንፈዉ ሥራህን አሸንፈሃልና፡፡የሰዉ ልጅ በአሸናፊነት ዙፋን ላይ ለመቀመጥ ሁል ጊዜ ሥራዉን ማሸነፍ አለበት፡፡ በተገቢዉ ሁኔታ ተጀምሮ እስኪያልቅ ሥራዉን ካወቀ፣ ከሰራ፣ ካጠናቀቀ፣ እሱ ሰዉ ባለድል ነዉ፡፡

ሁላችንም ከፊታችን በሚመጣዉ አዲስ ዓመት ራሳችንን ሁል ጊዜ በአሸናፊነት ዙፋን ላይ ማስቀመጥ የሚችል ልዩ ሞራል ባለቤት እንድንሆን መልካም ምኞቴን ገልፃለሁ፤ መልካም አዲስ ዓመት፡፡

ሰኞ 18 ኦገስት 2014

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነዉ፤"



ደብረ ታቦር ከገሊላ ባህር በምዕራብ ደቡብ በኩል አስር ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ተራራ ሲሆን ከባህር ጠለል በላይ ከፍታዉ 572 ሜትር ነዉ፡፡
ደብረ ታቦር፡-
1.     ባራቅ ሲሳራን ያሸነፈበት ተራራ ነዉ፡፡ መሳፍንት 4፡6-14
2.    ሳኦል እንደ ሳሙኤል ትንቢት ከሶስት ሰዎች ጋር የተነጋገረበት ነዉ፡፡ 1ኛ ሳሙኤል 10፡3
3.    ደብረ ታቦር በዛብሎን ዕጣ ያለ ለጨራራ ልጆች የተሰጠ ቦታ ነዉ፡፡ 1ኛ ዜና መዋዕል 6፡77
4.    ጌታችን ክብረ መለኮቱን የገለጠበት ቦታ ነዉ፡፡ ማቴዎስ 17፡1-8
ጌታ በማንኛዉም ቦታ ክብረ መለኮቱን መግለፁን ትቶ ደብረ ታቦርን ለምን መረጠ?
አንድም ትንቢቱ ይፈፀም ዘንድ
" ሰማያት ያንተ ናቸዉ ምድርም የአንተ ናት አለምንና ሞላዋን አንተ መሰረትክ ሰሜንና ደቡብን አንተ ፈጠርክ ታቦርና አርሞን በስምህ ደስ ይላቸዋል፡፡" መዝሙር 88፡11-12 የተባለዉ ይፈፀም ዘንድ ነዉ፡፡ ከሌሎች ተራሮች ሁሉ ደብረ ታቦርን የመረጠዉ ሌላዉም ተራራ ከመሬት እንዲርቅ የመለኮትም ምሥጢር ከሰዉ የራቀ የጠለቀ መሆኑን ለማጠየቅ ነዉ፡፡
ሌላዉ፡-

እሑድ 22 ጁን 2014

አለመግባባትን ለማሰወገድ



በመኖር ዉስጥ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በምን መልኩ መፍታት ይቻላል?
Image:Resolve Conflict in Marriage Step 8.jpg
የሰዉ ልጅ በህይወት ዘመኑ ረጅምም ይሁን አጭር፣ አስደሳችም ሆነ አሳዛኝ የሆነ ህይወን መኖሩ ግድ ነዉ፡፡በዚህ ወቅት ሁሌ መግባባቶች ብቻ ናቸዉ ብሎ ማሰብ የማይታሰብ ጉዳይ ነዉ፡፡ታዲያ አለመግባባት ካለ ይህንን አለመግባባት እንዴት መፍታት ይቻላል? ዋናዉና መሠረታዊዉ ጥያቄ ነዉ፡፡
ወደ መፍትሄዉ ከመሄዳችን በፊት እስኪ አለመግባባቶች ከምን እና ከማን ዘንድ ይፈጠራሉ የሚሉትን በጥቂቱ እንመልከት፤
ü  ባለትዳሮች (ባል ከሚስት ወይም ሚስት ከባል ጋር)
ü  ወላጆች (ቤተሰብ) ከልጆች ጋር ልጆች ከቤተሰብ/ከወላጅ ጋር፤ (ቤተሰብ በጠቅላላዉ እርስ በርስ ሠላም ዝር የማይልበት ቤት
ü  ፍቅረኞች (ወንዱ ከሴቷ ሴቷ ከወንድ ፍቅረኛዋ ጋር)
ü  ጓደኛሞች (ወንዶች ከወንዶች፣ ሴቶች ከሴቶች፣ ወንዱ ከሴት፣ ሴቷም ከወንድ ጋር ) ትንሽ በሚባሉ ችግሮች የሚፈጠሩ አለመግባባቶች
ü  መንግስትና ህዝብ (ባለመደማመጥና ባለመከባበር እኔ ነኝ የምገዛህ ወይም የማስተዳድርህ፣ አንተ አትገዛኝም ወይም አታስተዳድረኝም አለበለዚያም ወደ ሥልጣን ያመጣሁህ እኔ ነኝ … እንዳመጣሁህ አወርድሃለዉ….)
ü  መንግሥት ከመንግሥታት/ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች (በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች እና ኃይልን ለማሳየት በሚሞከር ትንኮሳ፣ በጉርብትና፣ በድንበር ጉዳይ፣ ቅኝ ለመግዛት በማሰብ እና ላለመገዛት መወሰን፣….)
ü  መንግሥት ከተቋማት ጋር (በሪፖርት፣ በዜና እወጃ፣ ምሥጢር በማዉጣት፣ ጫና በመፍጠር ፣ ጥቅማ ጥቅሞችን በማስቀረት፣ ሌሎች ወገኖችን በማሳመፅ፣ አላስፈላጊና አወዛጋቢ አዋጆችን በማወጅ፣ ….)
ü  ወዘተ
ችግሮች የሚፈጠሩበትን አካባቢ እንዲህ በጥቂቱ ከዘረዘርን በማዕከልነት መፍትሔዎችን እንዲሁ በጥቂቱ ማንሳቱ አወያይ እና ሌሎችንም ሻል ያሉ ምፍትሔዎችን በተጠና መልኩ ያመጣሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለጊዜዉ ጥናቱን ለባለሙያዎቹ ልተዉና ይሆናሉ የምላቸዉን እነሆ ብያለሁ፡-

እሑድ 8 ጁን 2014

ክፍል ስድስት… … … አጋጣሚ



ረጅም ዕድሜን ባልኖርም ሊደርሱብኝ የሚችሉትን አስተናግጃለሁ፣ ማየት የነበረብኝን አይቻለሁ፣ ደስታንም ሃዘንንም ከእህቴ የበለጠ አዉቃለሁ፣ ( ከእህቴ እንደምበልጥ የማረጋግጥልህ እሷ በህይወቴ ጣልቃ እየገባች አዉቅልሻለሁ ስትለኝ ይህንን ሁሉ እንደማዉቅ አለማወቋ በቂ ማረጋገጫ ነዉ፤ እስኪ እኔን ከእናቴ ፈርማ ተረክባ ቢሆን አሁን ያለሁበት ሁኔታ ለምን እንደሚዳርጋት አስበኸዋል? ) አሁን ከምነግርህ በላይ አዉቃለሁ፤ ነገር ግን እስካሁን የማዉቀዉ መጥፎ ነገሮችን ነዉ ጥሩ የተባሉትንም ቢሆን ከእርሷ የተሻለ አዉቃለሁ፡፡ የሚገርመዉ ስለግል ህይወቴ ዕድል ሳትሰጠኝ ስለ አገር ጉዳይ ቁጭ አድርጋ ታወራኛለች፤ እስኪ አስበኸዋል እኔ አሁን ስለ አገር የሚያገባኝ ሴት ነኝ የኔን ነፃነት ነፍጋኝ ዲሞክራሲ ስለጠማት እና ስለራባት አገር እኔ ምን አግብቶኝ ነዉ ከእሷ ጋር ስለ አገር ጉዳይ ለማዉራት በጠረጴዛ ዙሪያ የምሰደረዉ? ስለፍቅር እየተከለከልኩ ስለ ፖለቲካ የሚፈቀድልኝ እንዴት ነዉ ነገሩ? እኔ የሚገርመኝ ፖለቲካል ሳይንስ ታጥና ህክምና ግራ ግብት ይለኛል፡፡ ለምን አታገቢም ስትላት መጀመሪያ አገር ባለቤት ይኑራት ትልሃለች፤ ለምንድን ነዉ የራስሽ ነገር የማይኖርሽ ስትላት አሁን ጊዜዉ አይደለም ስንት አንገብጋቢ ነገር እያለ ትልሃለች፤ እሷን የሚያንገበግባት የእኔና የአገር ጉዳይ ብቻ ነዉ፡፡
ልብ በለህ ስማኝ እሷ ወንድ የምታዉቀዉ ስለፖለቲካ ጉዳይ ለማዉራትና በህክምና ሊረዳ በስራ ቦታዋ ሲመጣ ብቻ ነዉ፤ ባለፈዉ አንዱ ከቤት ድረስ ቢመጣ ሁላችን ደስ ብሎን ( መቸስ በባህላችን ሴት ልጅ ወንድ ይዛ እቤት ድረስ ስትመጣ የቱንም ያህል ደስ የማይል ጉዳይ መሆኑ ግልፅ ቢሆንም ይህ የሚያሳየዉ የጉጉታችን ልክ መጠነ ሰፊ መሆኑን ያመላክታል ) ግድግዳዉ ላይ ጆሮአችንን ለጥፈን ( አንድያዉን ለስነን ብትለዉ ይቀላል) ብናዳምጥ ብናዳምጥ አንዳች ነገር አጣንባት ከጆሮዬ ይሆን ብዬ አብራኝ የነበረችዉን የቤታችን አባል ሰራተኛይቱን ብጠይቅ እሷም እንደኔዉ ተበሳጭታ ኖሮ እሷቴ አናዳችም ስለሴትና ወንድ ያወራችዉ ነገር እንደሌለ ነገረችኝ፤ ያዉ የፈረደበትን ፖለቲካ እቤት ድረስ ይዛ መጥታ ታቦካዉ ጀመረ እንጂ፡፡ አሁን እስቲ ማን ይሙት ‹‹ የዘመናችን ብቸኛዋ ፖለቲከኛ ሴት ለመባል ነዉ ወይስ … ›› እስኪ እንደዉ ብቻ ተወኝ፤ ነገረ ዓለሙ ሁላ ፖለቲካ ፖለቲካ የሸተተበት ዘመን ላይ ደርሰን ህጻን አዋቂዉ አልጋና ትራሱ ሁሉ ፖለቲካ ሆኖ ፍቅር ጠፋ አንዴ እኔ ብገኝ በምን እናጥፋሽ ብለዉ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡
( እነማን ናቸዉ ለማለት ፈለኩና የሞቀ ወሬያችንን በኔ ጣልቃ ገብነት እንዳልገታዉ ፈራሁና እየተከታተልኳት መሆኔን አንገቴን ላይ ታች በመነቅነቅ ገለጽኩላት፤) 
ከዚህ ቀደም እንዳወራነዉ ከልጅነት ጓደኛዬ ሌላ ተባራሪዎቹን ሳንቆጥር አንድ ሶስት ወንዶችን በደንብ አዉቃለሁ፤ ነገር ግን ይህቺ ክፉ እህቴ ሁሌ ጥላዋን እያጠላችብኝ እንደዛፍ ላይ እንቅልፍ አስሬ እየባነንኩ ነበር የምኖረዉ፡፡ የመጀመሪያዉ በጣምም ሃብታም ባይባል ለኔ ከበቂ በላይ ሊይዘኝ የሚችለዉ አቅም ነበረዉ ከነበረዉ ገንዘብ ይልቅ ፍቅሩ ይግደለኝ፣ እንክብካቤዉስ ብትል፣ በተለይ በተለይ የትም ስንገባ የነበረዉ ክብር እመቤት የሆንኩ ያህል ነበር የሚሰማኝ ወንበር ስቦ አስቀምጦ፣ የመኪና በር ከፍቶ አዉርዶ አስገብቶ፣ … ስንቱን ልበልህ ከልቡ ነበር ግን ‹‹ ባሪያ ላመሉ … ›› እንደሚባል ልክስክስ ነበር፤

ሐሙስ 22 ሜይ 2014

የዳንኤል እይታዎች Daniel Kibret's views: ‹‹የሚገሥጹንን ሁሉ መቅጣት የለብንም››

የዳንኤል እይታዎች Daniel Kibret's views: ‹‹የሚገሥጹንን ሁሉ መቅጣት የለብንም››: click here for pdf ብጹዕ አቡነ ዮሐንስ በሊቅነታቸው፣ በቆራጥነታቸው፣ ለየት ባለ አስተሳሰባቸውና ለነገሮች በሚሰጡት አስደናቂ ምላሽ የሚታወቁ የትግራይ ሊቀ ጳጳስ ነበሩ፡፡ እስካሁንም እርሳቸውን በተመለከተ ...

እሑድ 18 ሜይ 2014

ክፍል አምስት … … አጋጣሚ



ከመች ወዲህ ነዉ እንዲህ ማምሸት የጀመረችዉ? ከቤት እንዳትወጣ አላልኩሽም? ለመሆኑ ስንት ሰዓት ነዉ የወጣችዉ? ቆይ ስራ በቃኝ! ለተወሰነ ግዜ ማረፍ እፈልጋለሁ ብላ ሥራዋን በገዛ ፈቃዷ የለቀቀችዉ ለመዞር ነዉ እንዴ? እንደከብት እሷን ለመጠበቅ እኔ የግድ እዚህ መዋልና ማምሸት አለብኝ? …. … (ለጥያቄዎቿ መልስ የሚመልስላት ስታጣ ብቻዋን አዉርታ አዉርታ ሲበቃት ስልኳን መደወል ጀመረች፤ ) ደግሞ ስልኳንም ዘግታዋለች፡፡
ነይ እስኪ ወደዚህ ምንድን ነዉ አላማችሁ? ቆይ እስኪ እናንተ ከብቶች ናችሁ እንዴ ያለጥበቃ የማትኖሩት? አልበዛም እንዴ? (ቁጣዋ እየጨመረ መጣ የሚሰማት ሰዉ ግን አልነበረም፤) ምን ይዘጋሻል!
‹‹ እኔን ነዉ? ››
እና ማን አለ? እስካሁን የማወራዉ ለማን መስሎሻል?
‹‹ እስካሁን አዉሪ እንጂ አንዱም አይመለከተኝም፤ … … እኔኮ የቤቱ ጠባቂ እንጂ የሰዉ ጠባቂ አይደለሁም፡፡ ቆይ እስኪ ስራዬ ምንድን ነዉ? ገረድ ነኝ ወይስ እናንተ በተበጣበጣችሁ ቁጥር ሸምጋያችሁ ነኝ? ድርሻዬን አሳዉቁኝ …. ….›› ( በዚህ ቤት ዉስጥ ለመጀመሪያ ጊዜዋ ነዉ እንዲህ አይነት ቃላት ስትናገር፤ )

ማክሰኞ 6 ሜይ 2014

አንድ አድርገን: ‹‹ዛሬ በከፍተኛ አዘቅት ውስጥ የወደቀችው አገራችሁን ኢትዮጵያን እና ሃይማኖታች...

አንድ አድርገን: ‹‹ዛሬ በከፍተኛ አዘቅት ውስጥ የወደቀችው አገራችሁን ኢትዮጵያን እና ሃይማኖታች...:  ‹‹ ዛሬ በከፍተኛ አዘቅት ውስጥ የወደቀችው አገራችሁን ኢትዮጵያን እና ሃይማኖታችሁን ለመታደግ በሃይማኖት ጸንታችሁ መንፈሳዊ ተጋድሎ አድርጉ››   አለቃ አያሌው ታምሩ ሚያዚያ 23 ቀን 1983 የሰማዕቱ ቅዱስ ጊ...

ሰኞ 5 ሜይ 2014

I forget my English ደብተር

ወቅቱ በኛ ዘመን ነዉ ‹የኛን ዘመን› እንግዲህ ቆጥራችሁ ድረሱበት፤ ፍንጭ ለመስጠት ያክል ዛሬ የአማሪኛ ቋንቋን ከብሔሩ ተወላጅ ዉጭ ያሉ ተማሪዎች ‹‹ አማርኛ ›› ብሎ ከመጥራት በስተቀር መናገር እንደተጠመደ ፈንጂ በሚታይበት ሁኔታ እንዳለ ሁሉ እኛም እንግሊዝኛን ከA (ኤ) እስከ Z (ዜድ) ብቻ በሚመስለን ዘመን እንደማለት ነዉ፡፡ የቋንቋ ነገር ከተነሳ አይቀር አንድ ጓደኛዬ እዚሁ መዲናችን አዲስ አበባ ዉስጥ በሚገኝ የግል ባንክ አንድ ዘመዷ ተቀጥራ ለዋስትና ስትሄድ ወደ ህንፃዉ እንደገባች የህንፃዉ ትልቅነት ግራ ስላጋባት መረጃ ትፈልግና አንዷን የባንኩ ሰራተኛ መረጃ ትጠይቃታለች ባነከሯም (የባንኩ ሰራተኛ) በአማርኛ ቋንቋ ለጠየቀቻት ጓደኛዬ አማርኛ እንደማትችል ትመልስላታለች፡፡ ጓደኛዬም የምትሰማዉ ነገር ግራ ይገባትና ‹‹ እንዴት ነዉ የማትችይዉ?›› ብላ ትጠጥቃታለች፡፡
‹‹ በቃ አልችልማ ›› ብላ ግግም ያለ ምላሽ ትሰጣታለች፤
‹‹ እያናገርሽኝ ያለዉኮ በአማርኛ ነዉ ታድያ ይሄንን እንዴት ቻልሽ ወይስ መረጃ መስጠት በአማርኛ መስጠት አትችይም? ›› ትላታለች ፤
የባንክ ባለሙያዋም ‹‹ በቃ ተሳስቼ ነዉ››  ትልና አሁንም በአማርኛ ትመልስላታለች፤
እንግዲህ እንዲህ ቋንቋዉን እየቻሉ መናገር ለሚጠሉት ቋንቋ ‹መግባቢያ› ሳይሆን መዋጊያ የጦር መሳሪያ እየሆነባቸዉ ያለበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነዉ ያለዉ፡፡ (እግረ መንገዳችንንም የግድ እስካልሆነ ድረስ እንዲህ ዘርና ቋንቋ እየመረጡ የሚቀጥሩ መስሪያ ቤቶች ከአካሄዳቸዉ ቢመለሱ የሚሻል ይመስለኛል፤ መልዕክቴ ነዉ፡፡ )

እሑድ 4 ሜይ 2014

ክፍል ሁለት …. … የፀየሙ ገጾች (አዲስ አበባ)

  

ብዙ መልኮችና ብዙ ስሞች ያሉዋት አዲስ አበባ አንዱ መጠሪያዋ አራዳ ነበር፤  አራዳና አዲስ አበባ ተነጣጥለዉ የሚታዩ አልነበሩም፡፡ በአንድ ወቅት ታላቁ ሰዉ አቶ ይድነቃቸዉ ተሰማ ስለ አዲስ አበባ በሬድዮ ፕሮግራም ተጠይቆ ሲናገር እንዲህ ነበር ያለዉ፡- ‹‹ የአዲስ አበባዉ ስታድየም አሁን አለበት ቦታ እንዲሠራ ሐሳብ ሲቀርብ ኳስ ሜዳዉን ከከተማ ዉጭ አደረጋችሁት ተብለን ተወቀሰን ነበር፤ ›› እንግዲህ በወቅቱ አዲስ አበባ ምን ያህል ጠባብና ስንት ህዝብ ይኖርባት እንደነበር መገመት ቀላል ነዉ፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ስታድየምን ያህል ነገር ሲሰራ ከከተማ ወጥቷል ከተባለ የስልጣኔ ጥጓ ምን ያህል ድረስ እንደነበረ መገመትም አይዳግትም፡፡ በቅርቡ እንኳን በ 20 እና በ 30 አመታት ጊዜ ዉስጥ እንኳን የነበራትን ገጽ ብንመለከት አዲስ አበባ እንኳንስ የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ልትሆን ይቅርና ለዋና ከተማነት እንኳን የምትመረጥ አልነበረችም፤ ካረጁ ቤቶቿ እና ከፈራረሱ መንገዶቿ አንፃር፡፡ በዚህ የታሪክ አጋጣሚ በ1879 ዓ.ም. የቆረቆሯት አጼ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ተነስተዉ የትናንትናዋን ባለጎፈሬዋን እና የዛሬዋን ‹ዉብና ድንቅ› እንዲሁም ሰፊ ከተማ በወቅቱ ከነበረዉ ጋር ለማነጻጸር ‹‹ ዕድል ›› ቢገጥማቸዉ ምን ይሰማቸዉ ይሆን? ያስብላል፡፡  
እንደዉ የሚሉትን ነገር ገምቱ ብንባል ዘና ለማለትና በዚያዉም ምሳ ነገር ለመጋበዝ የቀድሞዉን ‹‹ኢምፔሪያል›› የዛሬዉን     ‹‹ ጣይቱ ሆቴል›› ዉሰዱኝ ሳይሉ እንደማይቀሩ እንገምታለን፤ እኛም መቸስ የጠየቁትን አንነፍጋቸዉም እንወስዳቸዋለን፡፡ መቸስ ስለ ጣይቱ ሆቴል ከተነሳ አንድ እዉነት ልንገራችሁ፡- በራዲዮ የቀረበ ነዉ፤ እኔም ከ100ኛ ዓመት በዓል መዘከሪያ መጽሔት ላይ ያገኘሁት ነዉ፡፡
 ላዲላስ ፋራጎ ይባላል፡፡ ጋዜጠኛ ነዉ፡፡ላዲስ ፋራጎ ከለገሃር ባቡር ጣቢያ ተነስቶ ጣይቱ ሆቴል ይሄዳል፡፡ከጅቡቲ፣ከድሬደዋና ከአዋሽ ተሸክሞት ከመጣዉ አዋራና ላብ ለመገላገል ቸኩሎ ነበር፡፡
ከመኝታ ቤቱ ሲገባ ግሩም የሆነ የገላ መታጠቢያ ገንዳ (ባኞ) በማግኘቱ እጅግ ተደስቶ ቦዩን ጠራና ‹‹ ገላዬን ስለምታጠብ ገንዳዉን ሙላልኝ ›› ይለዋል፡፡
ቦዩም (አስተናጋጁ) ስንት ታንካ (ጀሪካን) ዉሃ ላስመጣልዎ ›› ይለዋል፡፡
ፈረንጁ ግራ ይገባዉና ‹‹ ገንዳዉን ሙላልኝ ነዉ የምልህ፡፡ ቧንቧዉን ክፈተዉ፡፡›› ይለዋል፡፡
 አሁንም ቦዩ ይመልስና ‹‹ ገላዎን መታጠብ ከፈለጉ የሚፈልጉትን የዉሃ መጠን ይንገሩኝ፡፡ ያንዱ ታንካ ዉሃ ዋጋ አራት ግርሽ (ጠገራ ብር ወይም ማርያቴሬዛ) ነዉ፡፡ ›› ይላል፡፡  (ገንዳዉን የሚሞላዉ ስድስት ታንካ (108 ሊትር) ዉሃ ነዉ፡፡) ላዲስላስ ፋራጎ ቀጠለና ‹‹ እንዴ? የቧንቧዉን ዉሃ በታኒካ ልክ ታስከፍላላችሁ ማለት ነዉ?›› ሲል ቦዩን ጠየቀዉ፤
ቦዩም ‹‹ አይደለም! ዉሃዉ የሚመጣዉ ከፍል ዉሃ ነዉ፡፡ ኩሊዎ (ተሸካሚ) ይላኩና ፍልዉሃ ሄደዉ ታኒካዉን በፈላ ዉሃ ከሞሉ በኋላ ተሸክመዉ ያመጡታል፡፡ አንድ ኩሊ ዳዉን 6 ታኒካ ዉሃ ይሞላዋል፡፡ ገላዎን አንዴ ታጥበዉ መለቅለቅ ከፈለጉ ደግሞ ተጨማሪ ታኒካ ዉሃ ማስመጣት ያስፈልጋል ›› አለዉ፡፡
‹‹ገንዳችሁ ላይስ የተተከለዉ ቧንቧ?››
‹‹ እንዳልኩዎት ዉሃዉ የሚመጣዉ ክፍል ዉሃ ነዉ፡፡››
ላዲስላስ ፋራጎ ገባዉ፡፡ ገንዳዉ ላይ የተተከለዉ ቧንቧ ለጌጥ ነበር፡፡

ቅዳሜ 3 ሜይ 2014

የፀየሙ ገጾች (Part One)

‹‹ ይህች ቦታ ለኛም ለነፋሱም ትመቸናለች፡፡ እንጦጦ ብርድ ነዉ፡፡ እዚህ ከተማ እናብጅ፡፡ ቦታዋንም አዲስ አበባ ብያታለሁ፡፡›› እቴጌ ጣይቱ
‹‹ እቴ አዲስ አበባ ብለሽ መሰየምሽ ደግ አድርገሻል፡፡ አዲስ አበባ በያት፡፡›› ዳገማዊ አጼ ምኒልክ
ጸሐፊ ትዕዛዝ ገ/ሥላሴ ስለ አዲስ አበባ አመሰራረት ሲናገሩ ‹‹ … ጣይቱ ከድንኳናቸዉ በር ሆነዉ ሲመለከቱ የአካባቢዉን የተፈጥሮ ዉበትና የአየር ንብረት ሁኔታ በማድነቃቸዉ ምኒልክን ፍል ዉሃ አካባቢ ቤት ለመሥራት እንዲፈቀድላቸዉ ጠየቁ፡፡ ምኒልክም ፈቃደኛ ሆነዉ የቤቱ ሥራ በፍጥነት ተጀመረ፡፡›› ይለናል፤
የአዲስ አበባ 100ኛ ዓመት በተከበረበት ወቅት የተዘጋጀዉ የበዓሉ ማክበሪያ መጽሔትም ‹‹ … አዲስ አበባ ከ1883 - 1979 ዓ.ም. ድረስ በርዕሰ ከተማነት የተጫወተችዉ ሚና እጅግ በጣም ብዙና መሠረታዊም ነዉ፡፡›› በማለት ስለአዲስ አበባ ርዕሰ መዲናነት ያስነብበናል፤ ዛሬም አዲስ አበባ የአፍሪካ አገራት መዲና ሆና እንዳለች እኛ የዛሬዎቹ ትዉልድ የዓይን ምስክሮች ነን፡፡
በአንድ ወቅት የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ክቡር መለስ ዜናዊ በቴሌቪዥን መስኮት ስለ አዲስ አበባ ሲናገሩ ‹‹ … አዲስ አበባ አሁን እንደምታዩዋት ለነዋሪ ምቹ አይደለችም ስለዚህ አሁን ካላት ሶስት መልክ ቢያንስ ወደ ሁለት ልናጠጋጋት ግድ ይላል፤ ስለዚህ እንደገና እንሰራታለን …›› ብለዉ እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነዉ፡፡አጼ ምኒልክም አዲስ አበባን ሲቆረቁሩዋት ከጫካነት ነበር መነሻዋ አሁንም ከ100 ዓመት በኃላ ከጫካ የማትሻል ጎስቋላ ከተማ ናት ነገር ግን የአፍሪካ መዲና ነች፡፡ ለዚህ ነዉ አሁንም አዲስ አበባ እንደገና መሰራት ያስፈለጋት፤ እየተሰራችም ትገኛለች፡፡
አዲስ አበባ የማይካድ ሀቅ ነዉ አሮጌ መንደር ነች!

ዓርብ 2 ሜይ 2014

ክፍል አራት ….. ….. አጋጣሚ

የክፍል ሶስት መጠናቀቅ ብዙም ቀጣዩን ክፍል እንድንጓጓለት ባያደርገንም አንድ ነገር ይዞ እንደሚመጣ ግን ተስፋ እናደርጋለን፤ ከፊሎች ደግሞ በጉጉት ጠብቀዉታል ይህ አጋጣሚ መጨረሻዉ ምን ይሆን? እያሉ ለሁላችሁም ክፍል አራትን እነሆ እላለሁ፡፡ መልካም ንባብ ! የማነበብ ባህላችንን እናዳብር፡፡


‹‹ በልቼ ዕቃ ሳላጥብ ማዋልና ማሳደር አልወድም ንጽህና የሌላትንም ሴት እንደዛዉ አልወድም ፣ ማንንም ቢሆን …. አላደረገችዉም እንጂ እናቴም ብትሆን
ይቅርታ አጥቤ እስክመጣ አልበም ነገር ልስጥሽ እንድትደበሪበት?››
ቆይ ሴት እያለማ ወንድ ልጅ ምንም ቢሆን ዕቃ አያጥብም ባይሆን የእስካሁኑ እንግድነት ይብቃኝና እኔ ልጠብ (የሴትና የቄስ እንግዳ የለዉም ሲባል ስለምሰማ) አልኩት የዉሸቴን ዉስጤ ግን የሚፈልገዉ  በአልበሙ ገጾች ላይ ከተሰደሩት መካከል አንድ ጉብል አንገቱ ላይ ተጠምጥማ፣ እሱ ደግሞ እንደ ዘንዶ ወገቧን አለቅ ብሎ ‹‹ችቦ አይሞላም ወገቧ›› እያለ ሲያወድሳት ያለበትን ፎቶግራፍ አይቼ ልቤ እንዲያርፍ ፈለኩ ምንም እንኳን እሱን ፎቶ ለማየት የዉስጥ ጥንካሬ ባይኖረኝም፤
‹‹ በፍፁም አይደረግም እስካሁን ያደከምኩሽ አንሶ በዛ ላይ …. የማይታሰብ ነዉ፤ ባይሆን ….››
ምን አደከምከኝ መብላት ያደክማል እንዴ? ያወራነዉ ሁለታችን ምን የተለየ ነገር አደረኩና ነዉ ያደከምከኝ? …. ‹‹ ባይሆን›› ያልከዉ ምኑ ነዉ?
‹‹ ባይሆን ሌላ ጊዜ ማለቴ ነዉ፤ ››
ልላ ጊዜ መቼ? ልቤ ከቅድም ይልቅ አሁን የባሰ መምታት ጀመረ፤ ደስስስ    …. …ስ አለኝ በቃ ዳግም በዚህ ቤት እንደምስተናገድ ተስፋ ሰነኩ፡፡
‹‹ የእስካሁኑ ይሁን ብለናል አሁን ለምን ፍራሹ ላይ አትቀመጭም … … እኔ ሳህኖቹንና ድስቱን ልጠብ የተዝረከረከ ቤቴን ላጽዳ ድንገት እንግዳ እንኳን ቢመጣ፤ ››
እንዴ የሚመጣ ሰዉ አለ እንዴ? … በማለት ፍራሹ ላይ ልቀመጥ ጫማዬን ላወልቅ የነበረችዉ ሴትዮ ‹‹ ባለህበት ቁም ›› የሚል ወታደራዊ ትዕዛዝ እንደደረሰዉ ሰዉ በንቃት ባለበት ቆምኩ፤
‹‹ ኧረ ስቀልድሽ ነዉ እንኳን ሌላ ሰዉ ቤቴ እኔንም በስራ ቀን ቤቴ እንዲህ በብርሃን ያገኘችኝም ዛሬ ነዉ ››
አብረን ተገኘና፤ … ታድዬ አልኩ ሳላዉቀዉ አልሰማኝም ነበርና መልስ አልሰጠኝም
‹‹ ጫማሽን አዉልቂና ዘና ብለሽ ተቀመጭ የወንደላጤ ፍራሽ ስለሆነ ግዴለም፤››

ማክሰኞ 22 ኤፕሪል 2014

እኔ ወድሻለሁ!


እንዲያ እየጠላሽኝ
እንዲህ እየወደድኩሽ
እንዲህ እየባተትኩ
አንቺን ካልመሰለሽ
እንዲያ እያልኩ … ደፋ ቀና
አንቺን ከመሰለሽ በህይወቴ የምዝናና፣
.
.
.
አንቺ እንዲህ ከሆንሽ
እንዲህ ካሳሰበሽ
ሰላሙን ከነሳሽ
እንዲህ  ካናገረሽ
እኔን ምን አለፋኝ
ምንስ አደከመኝ?
የተደፋ ዉሃ ዳግም ላይቀና፤
.
.
.
እቴ ሙሽራዬ
ዉዴ የኔ ፍቅር
የኔ ተናፋቂ
ሽቅርቅሯ እመቤት
ስሚኝ ልማልልሽ
በሙሉ ዕድሜዬ
በሙሉ ጤናዬ
በሙሉ ህይወቴ
…. እኔ ወድሻለሁ!
ጥላችን ተወግዶ ፍቅራችን እንዲፀና፡፡
፡፡
፡፡
፡፡

ክፍል ሦስት …… አጋጣሚ

ባለፉት ጊዜያት በሁለት ተከታታይ ክፍል ስለ አንዲት እህታችን የህይወት ታሪክ የሚዳስስ ‹‹ …. …. አጋጣሚ ›› በተሰኘ ተከታታይ ጽሑፋዊ ትረካ መልክ ስንከታተል እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነዉ፤ እነሆ በቀጠሮ የቆየዉ ክፍል ሶስት በጉጉት ሲጠበቅ ከነበረዉ በክርስትና እምነት ተከታዮች የትንሳኤ በዓልን ማግስት ምክንያት በማድረግ በደስታና በፌሽታ ክፍል ሶስትን እንድትኮመኩሙት ተጋብዛችኃል፡፡መልካም ንባብ!የማንበብ ልማዳችን ይዳብር!

                                           …… አጋጣሚ

‹‹ዛሬ የት ልትሄጂ ነዉ? ቤቱን የኛን አገር ጥምቀት አስመሰልሽዉኮ … ›› በማለት የተለመደ ንትርኳን ጀመረች፤ የምትሰራዉ በደመወዝ ሆነ እንጂ ቁርጥ ቤተሰብ ነች፡፡ አንድም ቀን ባዳነቷን አስቤዉም አላዉቅም፣ ከእኔ ጋርማ እንደ ታላቅና ታናሽ ነዉ የሚያደርገን፤ … በንትርክ ቤቱን ድምቅ እናደርገዋለን፡፡
ምን አገባሽ?
‹‹የማገባዉንማ አንቺን አማክሬ አይደለም የማገባዉ፤ ደሞ እንዲህ እንደ ከተማ ወንድ፡ ወንድ ይሁን ሴት ለመለየት ግራ የገባዉ ሳይሆን ከሩቅ ሲያዩት ወንድ ወንድ የሚሸት ወንዳወንድ ነዉ የማገባዉ፡፡ ››
ደሞ ለአዲስ አበባ ወንድ ምን ልታወጪለት ነዉ?
‹‹ አታፍሪም ለአዲስ አበባ ወንድ ወግነሽ ስትሟገችኝ ››
ለምን አፍራለሁ?
‹‹ እስኪ ምኑ ነዉ ወንድ የሚመስለዉ? ››
ፈጣሪ ወንድ አድርጎ የፈጠራቸዉን ምንድን ናቸዉ ልትይ ነዉ?
‹‹ ወዴት! ወዴት! እኔ የማወራሽ ስለሁኔታቸዉ፤ አንቺ የምታወሪዉ ስለ አፈጣጠራቸዉ …. በፍፁም አይገናኝም፡፡››
እስኪ አስረጂኝ፤
‹‹ አለባበሳቸዉ ብትይ፣ የፀጉር አሰራራቸዉ፣ የጆሮ ሎቲ፣ …. ምን ቀራቸዉ?››
ፋሽን ነዉኮ! ፀጉር አሰራራቸዉም ደግሞ ሚኒሊክ ነዉ ቴዉድሮስ ተሰርቶት ነበርኮ የጆሮዉም ቢሆን ምንም ማለት አይደል፤ …
‹‹ምን ! ( የድንጋጤ ድምፅ ) የጉድ ቀን አይመሽ ነዉ የሚሉት፤ እኛም ቤት ጉዱ አለና ዝም ብለን ነዉ የዉጭዉን የምንነቅፈዉ ….. በቃ ተይዉ፡፡ ለመሆኑ የትኛዉ ወንድ ነዉ የጀግና መሳሪያ ሊያነግት የሚቻለዉና ነዉ የቴዉድሮስን ሹሬባ የሚሰራዉ አናዉቀዉምና ነዉ ድንጋይ ከመወርወር ወዲያ የአዲስ አበባ ወንድ ምን ያዉቅና …. ምኑስ ነዉ ፋሽን? ቂጡን ጥሎ መሄዱ? ዝቅ ባለ ቁጥር ከፍ እያደረጉ መሄዱ ነዉ ፋሽን? ይሕ ነዉ ወንድነት? ይህ ነዉ ባል የሚሆነዉ? ለምን እድሜ ዘላለሜን ቆሜ አልቀርም ሁለት ሴት አንድ ቤት ዉስጥ ምን እንሰራለን?››

እሑድ 13 ኤፕሪል 2014

ዳቦ ለሚለምነዉ ወንድሙ ድንጋይ የሚሰጥ ማነዉ?

ማንኛችንም ወንድማችን ተርቦ ዳቦ ሲለምነን ረሃቡን ያስታግስበት ዘንድ በዳቦ ፋንታ ድንጋይ የሚሰጠዉ ማንም የለም፡፡ በዚህ ምድር ላይ ተፈጥሮ በድሎትም ሆነ በስቃይ ዉስጥ የሚመላለስ ማንኛዉም ፍጥረት በክርስቶስ ኢየሱስ ወንድማችን ነዉ፡፡ ወንድማችን እስከሆነ ድረስ ደግሞ በወንድሙ የሚጨክን ሰዉ ነፍሰ ገዳይ ነዉ፤(አትግደል እንደተባለ ሰምታችኃል እኔ ደግሞ ወንድማችሁን በዳቦ እጦት እንዳትገድሉት አስታዉሳችኃለሁ ሃይማኖቱ፣ዜግነቱ፣ብሔሩ …ምንም ይሁን ምንም፤ሰዉየዉ ምንም ይሁን ማንም) ነፍሱን ማቆያ ዳቦ እንሰጠዋለን፡፡ ምግብ በዋናነት የሚያገለግለዉ ለቁመተሥጋ ነዉና አንድም ሥጋችን ተደግፋ ያለችዉ በምግብ ላይ ነዉና ወንድማችንን ሲርበዉ ቁራሽ ምግብ ስንከለክለዉ ሥጋዉ ከነፍሱ እንድትለይ ፈቅደናልና ነፍሰ ገዳይ ነን፡፡ በቅዱሳት መፃህፍት ላይ ተጽፈዉ የሃይማኖት መመሪያዎች ከሆኑት መካከል አንዱ ሕግ ‹‹አትግደል›› የሚል ነዉና በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ሕግ ሽረናል፤ አንድም ደግሞ ይህ ሕግ ሲፃፍ ለዚህኛዉ እምነት ተከታይ፣ ለዚያኛዉ ብሔር፣ ለዚህኛዉ ጎሣ፣ ወይም ዘርና ቀለም አይልም ስለሆነም ሲራብ አለማብላታችንና ዝምታችን በቀላሉ ከምናየዉ ‹አለማብላት› በዘለለ ነፍሰ ገዳዮች ነን ማለት ነዉ፡፡ ከእግዚአብሔር ሕግም ባሻገር የወንጀለኛ ሕጉን አንቀጽና ቁጥር ባልጠቅስም በየትኛዉም ዓለም ሕግ ነፍስ ማጥፋት አይፈቀድም ወንጀልም ነዉ፡፡ በነፍሳችን ምንም እንኳን ወዲያዉ በዓይናችን አይተን በእጃችን ዳሰን የምንፈራዉ ቅጣት ባይደርስብንም ቅሉ በምድራዊ ህግ ግን ለእስርና በገንዘብ መቀጮ ከዚያም ባሻገር የከፋ ፅኑ ቅጣት ሊኖረዉ ይችላል የተለያዩ የቅጣት ማቅለያዎች ግምት ዉስጥ ካልገቡ በቀር፡፡
 ተርቤ አላበላችሁኝም!
ወቅቱ በኢ/ኦ/ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ የፆም ወቅት እንደመሆኑ መጠን ያለፉትን ሰባት ሳምንታት በፆምና በጸሎት በምፅዋትና በስግደት አሳልፈን አሁን የዐብይ ፆም የመጨረሻዉ ሳምንት ላይ እንገኛለን፤

ሆሳዕና በአርያም

ሆሳዕና በዓብይ ፆም ሰባተኛዉ ሳምንት ሲሆን ሆሳዕና ማለት የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንዳስቀመጠዉ ‹‹አሁን አድን›› ማለት ነዉ፡፡ስለሆሳዕና ከወንጌላዉያን ከሉቃስ በቀር ሶስቱም ወንጌላዉያን ፅፈዉ እናገኘዋለን፤ ማቴዎስ 21 ቁጥር 9-15፤ማርቆስ 11 ቁጥር 9 እና ዮሐንስ 12 ቁጥር 13 ናቸዉ፡፡
የእስራኤል ሕዝብ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘዉ ‹‹ሆሣዕና›› በማለት እየጮሁ ኢየሱስን ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ አጅበዉ ተቀብለዉት ነበር፡፡ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ሊገባ ከኢየሩሳሌም አቅራቢያ ሲደርስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ከፊት ለፊታቸዉ ከምትገኝ መንደር ልኮ አህያ እና ዉርንጫ ከታሰረችበት ፈተዉ ይዘዉለት እንዲመጡ አዘዛቸዉ፡፡ አህያይቱን ይዘዉለት በመጡ ጊዜ ‹‹እነሆ ንጉስሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በዉርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል ›› ትንቢተ ዘካርያስ 9 ቁጥር 9 እንደተባለዉ በአህያይቱ ጀርባ ላይ በመሆን ወደ ከተማይቱ ገባ፡፡
ኢየሱስ ወደ ከተማዉ ሲገባ (ከኢየሩሳሌም ቤተመቅደስ ድረስ አስራ ስድስት ምዕራፍ ተጉዟል፤ አስራ አራቱን በእግሩ ሲጓዝ ሁለቱን ምዕራፍ ግን በሁለቱ አህያ ጀርባ ላይ በጥበብ በአንድነት ተቀምጦ ሄደ፡፡) ህዝቡ ልብሱን ከአህያዉ ጀርባ ላይ አድርጎለት እና እንኳንስ አንተ የተቀመጥክባት አህያ መሬት መርገጥ የለባትም ብለዉ የዛፍ ዝንጣፊ በየመንገዱ እያነጠፉ ተቀበሉት፤(የዛፍ ቅጠል አይደለም የሰሌን ዝንጣፊ ነዉ ቢሉ አብርሃም ይስሐቅን፣ይስሐቅም ያዕቆብን፣በወለዱ ጊዜ እስራኤል ከግብፅ በወጡ ጊዜ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘዉ አመስግነዋልና እስራኤላዉያንም ሆሳዕና በአርያም እያሉ በነሱ ልማድ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘዉ አመስግነዉታል፡፡ ስለምን በሰሌን ቅጠል/ዘንባባ ይዘዉ አመሰገኑት ቢሉ ዘንባባ እሳት አይበላዉም ለብልቦ ብቻ ይተወዋልና አንተም ባህሪህ ረቂቅ የማይመረመር ነዉ ሲሉት ነዉ፤ ) ወደ ኢየሩሳሌምም በገባ ጊዜ ህዝቡ ‹‹ይህ ማን ነዉ?›› እያሉ ሲጠይቁ ነበር፡፡ ገሚሲቹም የፊቱን ወዝ አይተዉ ‹‹ነቢይ ነዉ›› ሲሉም ተደምጠዋል፤ … ኢየሱስም ወደ ከተማዉ ከገባ በኃላ ወደ ቤተመቅደስ ነበር ያመራዉ፡፡(በአህያ ጀርባ ላይ ሆኖ ቤተመቅደስን ሶስቴ ዞሮዋል፤)‹‹ … ወደ መቅደስ ገባና (ብሩን ለወርቅ ወርቁን ለብር የሚለዉጡበትን ሥፍራቸዉን አፈረሰባቸዉ፤ በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አወጣ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠና ቤቴ የፀሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎአልና እናንተ ግን የወንበዴዎች ጋሻ የሌባ ዋሻ አደረጋችኋት›› አላቸዉ፡፡ ገበያ የተሠረቀዉን የተቀማዉን ይሸጡበታልና እንዲህ አለ፡፡
( በዚህ ጊዜ የተፈፀመዉ ምሥጢራት በቤተክርስቲያን አባቶች ሲነገር አስራ ስድስቱ ምዕራፍ አስሩ የአስርቱ ቃላት፣ አራቱ የኪዳንት ሲሆን እነሱም፡- ኪዳነ ኖኅ፣ክህነተ መለከ ጼዴቅ፣ ግዝረተ አብርሃም እና ጥምቀተ ዮሐንስ ናቸዉ፡፡ ሶስቴ ቤተመቅደስን መዞሩ የስላሴ ሶስትነት ምሳሌ ነዉ፡፡ )
በመቅደስ ቆይታዉ ዓይነ ሥዉራንንም ፈዉሷቸዉ ነበር፤ … ህጻናትም ‹‹ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ›› እያሉ አመሰገኑት፡ አመሻሽ ላይም ትቷቸዉ ቢታንያ ሄዶ አደረ፡፡
ኢየሩሳሌም፡- ከባህር ወለል በላይ 750 ሜትር ገዳም ከፍ ብላ የምትገኝ ከተማ ናት፤ የስሟ ትርጓሜ ‹‹የሰላም ከተማ›› ማለት ነዉ፡፡
የእስራኤል ህዝብ፡- አስራ ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች ቤተሰብ ናቸዉ፤እስራኤል ማለት ያዕቆብ ማለት ነዉና ህዝቡ በሱ ስም ይጠራል፡፡
በአህያ ላይ መቀመጡ፡- ትንቢቱ ይፈፀም ዘንድ ነዉ፤ምሳሌዉ ቀድሞ አባቶች ነቢያት ዘመነ ጸብዕ/መጥፎ የሆነ እንደሆነ በፈረስ ተቀምጠዉ፡ ዘመኑ የሰላም የሆነ እንደሆነ ደግሞ በአህያ ተቀምጠዉ መነሳንስ ይዘዉ ይታዩ ነበርና የሰላም ዘመን ዘመነ ምህረት መጥቷል ሲል በአህያ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ ጌታ ራሱ ሰላም ሆኖ ሳለ እንደምን በአህያ ላይ ተቀምጦ መጣ ቢሉ ምሥጢሩ ባህያ የተቀመጠ ሸሽቶ አያመልጥም አሳዶም አይዝምና፤ እሱም ካልፈለጉኝ አልገኝም ከፈለጉኝ አልታጣም ሲል ነዉ በአህያ ላይ ተቀምጦ መምጣቱ፡፡ አንድም ነቢያት ደመና እየጠቀሱ፣ በእሳት ሰረገላ፣ በመርከብ ሲጓዙ ታናሽ በሆነች በአህያ ተቀምጦ መምጣቱስ እንደምን ነዉ ቢሉ ንጹሐን በሆኑ ታናናሾች አድሬባቸዉ ኖራለሁ ሲል ነዉ፡፡
የሁለቱ አህያ ምሳሌነት ደግሞ ትልቋ ሸክም የለመደች የምትጫን ስትሆን ትንሿ ደግሞ ሸክም ያለመደች መሆኗ ትልቋ ህግን መሸከም የለመዱ የእስራኤል ምሳሌ፣ ትንሿ መሸክም ያልጀመረችዉ ደግሞ የአህዛብ ምሳሌ ነች፡፡ አህዛብ ሕግ መጠበቅ ያልለመዱ ናቸዉና፡፡ አንድም ትልቋ መሸከም የለመደችዉ የኦሪት መተግበር የተለመደዉ የሕገ ኦሪት ምሳሌ ሲሆን ትንሿ ደግሞ መሸከም ያልመድችዋ መተግበር ያልተለመደዉ የአዲስ ኪዳን ሕግ ምሳሌ ናት፤
የአህያ ከእስር መፈታት፡- ሰዉ ሁሉ ከማዕሰረ ሃጥያት ተፈተዉ መምጣታቸዉን ለማጠየቅ የተደረገ ምሥጢር ነዉ፤ እስራኤል ዘነፍስ  የተባልን እኛን ከሃጥያት ቁራኝነት ሊፈታን በአህያ ዉርንጫ ላይ ተቀምጦ መጣ፡፡
ልብሳቸዉን ከአህያዋ ጀርባ ላይ ማድረጋቸዉ፡- ኮርቻ ስለሚቆረቁር ጨርቅ/ልብስ አይቆረቁርምና የማትቆረቁር ህግ ልሰራላችሁ መጣሁ ሲል ነዉ፤ አንድም ልብስ የሰዉነትን ነዉር እንዲሰዉር አንተም ከባቴ አበሳ ነዉራችንን የምትሰዉር ነህ ሲሉ ልብሳቸዉ አነጠፉለት፡፡
ሆሳዕና በአርያም ለዳዊት ልጅ እያልን እናመሰግንሃለን፤ ለክብርህ ይሆን ዘንድ ልብሳችንን አዉልቀን እናነጥፋለን … ዘንባባ ይዘንም እንቀበልሃለን፡፡አበሳችንን ልትደመስስ ራስህን ዝቅ አድርገህ የመጣህልን ልዑለ ባሕሪ እግዚአብሔር ሆይ ክብር ምስጋና ላንተ ይሁን! በቤተመቅደስ ተገኝተህ ቤትህን ከሌቦች ዋሻነት እንዳፀዳኸዉ እንዲሁ ዛሬም በቤትህ ተገኝተህ ሌቦችን ከቤተመቅደስ አስወጣልን፡፡ በስምህ እየነገዱ በስምህ ጥቅም የሚያጋብሱትን፣ ከአስመሳይ አገልጋዮች ሰዉረን ፣  ቃልህን ባስተማሩ በአጸፋዉ ገንዘብ የሚጠይቁትን ቃልህን ከመዳኛነት ወደ ገንዘብ ማጋበሻነት የቀየሩትን አስታግስልን፡፡ ስምህን መነገጃ ያደረጉትን ስመ አምላክ ነጋድያንን ልብ ስጣቸዉ፤ ከተያዝንበት የሃጥያት ቁራኝነት ፍታን፣የአህያይቱን ትንሽነት ሳትንቅ በጀርባዋ ተቀምጠህ ወደ ቤተመቅደስ እንደገባህ አሁንም ጌታ ሆይ በሃጥያት መተዳደፉችንን ተመልክተህ ሳትንቀን በልባችን ንገስበት፣ ህጻናት እና ድንጋይ እንዲያመሰግኑህ የፈቀድክ ለምስጋና አንቃን፣ እንድናመሰግንህ ፍቅርህን በልቦናችን ምስጋናህን በአንደበታችን አሳድርብን፡፡
ሆሳዕና በአርያም! ጌታ ሆይ አሁን አድነን! ጌታ ሆይ ጤናችንን አሁን መልስልን!


ዓርብ 11 ኤፕሪል 2014

ቴሌና መብራት የዘመን መቀሶች

አሁን አሁን ትናንት ተገናኝተን ዛሬ ስንገናኝም ጭምር ሳይቀር ጠፋህ/ሽ መባባል ባህላችን እየሆነ እንደመምጣቱ ያህል ተገናኝተንም ስንለያይ ስልክ እንዳለዉ እንኳን እርግጠኞች ሳንሆን ‹‹ደዉላለሁ›› መባባሉን እንደ ቻዉ እየቆጠርነዉ መጥተናል፡፡ እንደዚያ ሲሆን እኔም የዚያዉ አካል ነኝና ትናንት ከአንድ ጓደኛዬ ጋር አብረን አመሽተን ከተለያየን በኃላ ካልሸኘሁሽ/ህ ሳንባባል ተለያይተን ሁለታችንም ወደ ታክሲ መያዣችን ተበተንን፤ (ተበተኑ አይደል የሚለዉ ፌዴራል ፖሊስ ሁለት ሆነን ስንቆም እኔም በቅጂ አማርኛዉን ተጠቅሜያለሁ፤) እኔም መንገዴን አጋምሼ ሁለተኛዉን ወደ ሰፈሬ የሚወስደኝን የህዝብ ትራንስፖርት ከያዝኩ በኃላ ትራንስፖርት አግኝታ ወደቤቷ መግባቷን መጠየቅ ስለነበረብኝ ደወልኩ፤ የባጡን የቆጡን እያወራን መግባት አለመግባቷን ሳልጠይቅ ስልኩ ተቋረጥ፡፡ ብለዉ ብሰራዉ የቴሌ ኔትወርክ ሞቼ እገኛለሁ እናንተን ካገናኘሁ ብሎ ድርቅ አለ፤ አንዴ ‹‹የደወሉላቸዉን ደንበኛ ማግኘት አይችሉም›› ስትለኝ፣አንዴ ‹‹መስመሮቹ ሁሉ ለጊዜዉ ተይዟል›› ስትለኝ ፣ ተማርሬ ቆይቼ ደዉላለሁ ብዬ ተዉኩት …. ቆይቼ ለመሞከር ባስበኩት መሰረት የስልኬን ቁልፍ ከፍቼ ስሞክር ጢጢጥ እያለ ዝግት ፣ጢጢጥ እያለ ዝግት …. ነገሩ አልገባህ ሲለኝ ተዉኩት፡፡ እንዲህ እና እንዲህ እያልኩ ወደ ሰፈር ስቃረብ ይባስ መብራትም ጠፍቶ ‹‹በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ›› አይደል የሚባለዉ ‹‹እንኳንም እናቴ ሞታብኝ እንዲሁም አልቅስ አልቅስ ይለኛል›› ያለዉ ቴሌ እንኳንስ መብራት ኃያል መብራት አጥፍቶበት እያለም በቅጡ የማይሰራዉ የቴሌ ኔትወርክ ከጓደኛዬ ጋር እንዳንገናኝ ለያቶን አደረ፡፡
መቸስ እግዚአብሔር እንደ መብራት ኃይልና እንደ ቴሌ አይደለምና የጨለማዉን አስፈሪ ግርማ ሞገስ በብርሃን ተካዉና ቀኑን በብርሃን ሞልቶ ዛሬን በሰላም አገኘናት፤ ‹‹ጥረህ ግረህ የላብህን ወዝ ብላ›› ተብለናልና ቀኑን ሙሉ ላይ ታች ስንል ዉለን ከስራ መልስ፡፡ መቸስ ቴሌን ትላንት ለያይተኸናል ብለን አናኮርፈዉ ነገር ባቆራረጠን መስመር ዳግም ለመገናኘት የሞባይሌን ቁልፎች ተጭኜ
 ‹‹ሃሎ!›› አልኳት ጓደኛዬን 
ሃሎ! አልችኝ ርቀቱ የዉጭ ስልክ እስኪመስል ድረስ በሚርቅ ድምፅ (ሰሞኑን ‹አይሰማም› ሆኗል፤ የቴሌን ኔትወርክ የለከፈዉ ልክፍት፤ ለመሆኑ 75 አካባቢ ምናምን አጠናቀኩ ያለዉ በፊት የሚሰሩትን አቋርጦ ነዉ ወይስ ለማይሰራላቸዉ ሰርቶ ነዉ ያጠናቀቀዉ? ካካካ ….. )
ሃሎ ብለን የጀመርነዉን ሃሎ እያልን እንዳይቋረጥብን ወደ ገደለዉ እንደመግባት ትላንት የተቋረጠበትን ሁኔታ አንስተን የተቋረጠዉ በኔትወርክ ምክንያት እንደሆነ፣ እቤት ስገባ መብራት ባለመኖሩ ምክንያት እንዳልደወልኩ፣ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ባይኖረዉም በሳምንት ይመጣልን የነበረዉ ዉሃ ሳይመጣ እንደቀረ ሳወራት በስርአት ስታዳምጠኝ ከቆየች በኃላ መጨረሴን ስታዉቅ እንደጋዜጠኛ ‹‹እንግዲህ ያሉትን ሁሉ ምሬት እና አቤቱታ የሚመስል አስተያየት ሰምተናል በእርግጠኝነት የሚመለከታቸዉ የስራ ክፍሎች በሰፈራችሁ የተከሰተዉን ችግር የኔትወርክ መቆራረጥ፣የመብራት በተደጋጋሚ መጥፋት፣የዉሃ ችግር …. ሰምተዉ መፍትሄ እንደሚሰጧችሁ እርግጠኖች ነን…. ስለደወሉ እናመሰግናለን!›› ብላ ፍርስ ብላ ሳቀችብኝ፤ እሷም እየሳቀች ወደ ቤቷ እኔም ሳወራ የቀለለኝን ድብርት ይዤ ጨለማ ወደ ነገሰበት ሰፈሬ፡፡
በአገር ዉስጥም ከአገር ዉጭም ያላችሁ ወገኖቻችን ለትንሣኤ በዓል ደዉላችዉ ምናልባት ቴሌ ካገናኘን ‹‹የእንኳን አደረሳችሁ›› ምኞት መግለጫችሁን ስታስተላልፉ እኛ ስለ ስልክ እና መብራት መቋረጥ ብናወራችሁ አደራችሁን ቅር እንዳትሰኙብን! ከወዲሁ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡ ምን እናድርግ መንግስት አልሰማ ቢለን ለመንገደኛዉ ሁሉ እናወራ ጀመር እግረ መንገዱን መንግስት ጆሮ ይደርስ እንደሆነ ብልን፤ መንግስትም ቀጥታ ከምንነግረዉ በሃሜት መልኩ የሚወራዉን መስማት የጀመረ ይመስል ቀጥታ ለህዝቡ ጥያቄ መልስ ነፍጓል፡፡
መንግስታችን ለብቻችን ሆነን ያወራነዉን ነገር እምቢ ስላልከኝ ይኸዉ ሰዉ ፊት ታዛቢ አስቀምጬ ነዉ የምነግርህ እኛ ሰፈር ዉሃ፣መብራት፣ ስልክ …አማሮናልና መላ በለን! ድሮ ‹‹ወጥ እና ወንድም ማስፈራሪያ ነዉ›› እየተባልን ነበር ያደግነዉ አሁን ግን እራት ሰዓት ላይ ሻማ ይለኮስና አለበለዚያም የአንደኛችን የሞባይል ብርሃን ተጠቅመን እራት ስንበላ ዉሃ ቀርቦልን ‹‹ብርሃንና ዉሃ … ማስፈራሪያ ነዉ›› እንባል ጀምረናል፡፡ እንዲያዉም ሌላ ሰፈር እንደሰማሁት በእኛ ጊዜ ቀን  ላይ ስናጠፋ ማታ ጨላማ ሲሆን በር ተዘግቶብን በጨለማ ጨለማ ላይ በመቆም እንቀጣ ነበር፤ ዛሬ ይኸዉ ‹‹ደግ›› ልበለዉ እንጂ ደግ ዘመን ላይ ስንደርስ ህፃናት በመብራት/በብርሃን ይቀጡ ጀምረዋል ‹‹መብራት አብርቼ ነዉ የማስቀምጥህ እየተባለ›› አሉ፡፡ ብርሃንም እንደ ድሮ ጨለማ ለማስፈራሪያ ሆነ ሲባል ሰምቻለሁ… አቤት መጨረሻችን …እግዚኦ!
ምን እንደምፈራ ታዉቃልችሁ ዛሬ መብራት ሰፈራችን የለም፣ ዉሃ ተረኛ አይደለንም እንደምንለዉ ሁሉ ፈጣሪ የአፌን አይቁጠረዉና ዳቦ፣ እንጀራ፣ ጤፍ፣ስንዴ፣ሽንኩርት፣ዘይት …. ገበያ ላይ የሚገኙት በወረፋ እንዳይሆን ነዉ፡፡ ፈጣሪ ክፉዉን አርቆ ደጉን ያቅርብልን!
መብራት ኃይልን እንደ ቴሌ ፈርሶ በመሰራት ሰበብ ህዝቡን አያሳቁብን!(እንደምርቃት ነገር ስለሆነ አሜን እንበል ጎበዝ የደረሰበት ያዉቃልና እንኳን ፈርሶ የሚሰራ መስሪያ ቤት ፈርሶ የሚሰራ ቤት ራሱ በጣም ችግር አለዉና፤) በየሄድንበት ሁሉ ስለ ዉሃ፣መብራት እና ኔትወርክ መጥፋት የምናወራበት ሳይሆን አገራችን ነዳጅ አግኝታ ስለሱ የምናወራበትን ዘመን ያቅርብልን! (አሜን!)
የአባይ ግድብ በጠንካራ ክንዳችን ተገንብቶ መብራት ከሚጠፋበት ይልቅ የምንሸጥበትን ቀን ቅርብ ያድርገዉ! (አሜን!)
 ሳንቲም የሚሸጡ ልጆች ወልደን ከማሳደግ አገራችን ኢኮኖሚዋ ጣሪያ ነክቶ ለዜጎቿ የዜግነታቸዉ የምትከፍል አገር ያድርግልን!(አሜን!)
ዜጎቿ ተሰደዉ ሞቱ፣ገደሉ፣ራሳቸዉን አጠፉ፣ሲሰደዱ በረሃ ላይ ሞቱ፣ …. ከመባል ተላቀን ምዕራባዊያን ፣ አዉሮፓዉያን በዲቪ የሚመጡባት፣ ስራ አጥ በዛብን ብለዉ ለስራ ፍለጋ የሚሰደዱባት ያድርግልን!(አሜን!)
መንግስት ለመገልበጥ፣ ስልጣን ለመንጠቅ፣ … ብለን ከመሯሯጥ እግዚአብሔር ሰዉሮን መሪዎቻችን የስልጣን ዘመኔ ተጠናቋል የሚተካኝን መሪ ምረጡ ብሎ ለምርጫ ቦርድ ሲያሳዉቅ ‹አንተዉ ምራን›፣ ተመችተኸናል እባክህ አንድ የስልጣን ዘመን ድገም ‹‹በሞቴ አፈር ስሆን›› ብለን ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተን ስልጣን መልቀቁን የምንቃወምበት፣ የሰልፍ ፍቃድ የምንጠይቅበትን  ዘመን ፈጣሪ ያምጣልን!(አሜን!)  

ዘመናችንን እንዳናጣጥምበት መቀስ የሚሆኑብንን እግዚአብሔር ያርቅልን!(አሜን!)

ዓርብ 4 ኤፕሪል 2014

ክፍል ሁለት ….. …. አጋጣሚ፤

ባለፈዉ  በ " ክፍል አንድ " የአንዲትን ወጣት የህይወት አጋጣሚ በራሷ አንደበት ስትተርክልን እንደነበረ ክፍል አንድን የተከታተለ የሚያስታዉሰዉ ነገር ነዉ፤ዛሬም ቀጣዩን የህይወቷን አጋጣሚ እንዲህ በአንደበቷ ታጫዉተናለች፡፡ መልካም ንባብ!
እንግዲህ የአጋጣሚ ነገር የት እንደሚጥል አይታወቅም አሁን ሳወራህ በህይወቴ ያሳለፍኳቸዉ ነገሮች ሁሉ ህልም ነዉ የሚመስሉኝ፤
በዕድሜዬ ሁለት አስርት ዓመታትን ሳስቆጥር በሰፈርና በሃይስኩል እንዲሁም ብዙ የፍቅርም የጥላቻም የሃዘንም ገጠመኞች አሉኝ፡፡ እንደ ፍቅር ግን ሬት የለም ሬት! እዉነቴን ነዉ የምልህ ፍቅር ሬት ነዉ! ሰወች የት አባታቸዉ አይተዉ ስለጣፋጭነቱ እንደሚያወሩኝ አላወቅም፤ ምናልባት የፍቅር ህይወታቸዉን በተገላቢጦሽ የኖሩ ሰወች እዉነት መስሏቸዉ ሊሆን ይችላል፡፡ ሰወች ስንባል ይልቁንም ሴቶች የሌላኛዉን የወንዱን ማለቴ ነዉ ህይወት ስለማንኖርለት፣ ህመሙን ስለማንታመምለት፣ ስቃዩን ስለማንሰቃይ ነዉ እንጂ አጋራችን/ፍቅረኛችን እኮ በኛ በሴቶች የተነሳ ሙት ነዉ! የለምኮ ሞቷል! በድኑኮ ነዉ አጠገባችን የቆመዉ…. … ፤ ለሞቱ ደግሞ ተጠያቂዎቹ እኛዉ ነን፡፡
የአሻራ ምርመራ የለም እንጂ በነፍሱ ዉስጥ፣ በደሙ ዉስጥ፣ በስራስሮቹ ፣ ከኪሱና በዋሌቱ ዉስጥ ተጣብቀን ደሙን የመጠጥን እኛ ነን፤ ሴቶች …. … ግን የዋሁ ወንድ ነገር ተገላብጦበት ህይወት አደንዝዛዉ ያለእኛ መኖር እንደማይችል በበድን ምላሱ ለሃጩን እያዝረበረበ ይነግረናል፤ እኛም ሰምተን እንዳልሰማ ይህ ደምፅ የሙት ነዉ ብለን ሳንቃወም ስጋዊና ደማዊ ሰዉነታችን በሙቀት ይቀልጣል፡፡
ዉዴ! ነፍሴ! ማሬ! ሃኒ!.... በሚሉ ጉንጫልፋ ቃላት እያንቆለጳጰሰን እኛን ሲያጣ መኖር እንደማይችል፣ ነፍሱ እንደምትወጣ ያለመጠራጠር ያወራል…. የሞተዉኮ ገና ከሴት እንደተገናኘ ነዉ…. አላወቀም እንጂ ሞትኮ ወደ ገነት ዘዉ ብሎ የገባዉ …. አዳምን ጠርንፎ ከገነት ያስወጣዉ …. ቁልቁል ተዘቅዝቆ ሱባኤ የገባዉ … ወንድነቱን ሁሉ ረስቶ እንደ ሴት ለነገሩ ያኔ ሴት አልነበረችም  የማያዉቀዉን ማንባት የተለማመደዉ ሔዋን ከመጣች በኃላ ነዉ፡፡
… … …
የድሮ ልጆችኮ እየተባለ ይደሰኮራል እንጂ ድሮኮ ነበር ገና ተማሪ ቤት ሲከፈት በእንቁጣጣሽ ጭፈራ ያገኘናትን ድቃቂ ሳንቲም በመያዝ አይናችን የገባዉን ጠጠር ከረሜላ፣ የጉንፋን ከረሜላ እና ድቡልቡሏን ማስቲካ በመግዛት ወንዶችን ስናማልል የነበረዉ፤ ማን አለ አሁን ይህን ዘመን በክፉ የሚያነሳ? ማንም! … ታዉረን ስለነበረ ነዉ ምክንያቱ! እና ግን ከዛን ጊዜ ጀምሮ በዛ ጨቅላ አዕምሮ ነበር ወንዶችን የምናጠምደዉ …. … ካካካ ….(ደማቅ ሳቅ)

ተማሪ ቤቴ



ተማሪ
ቤቴ


የማሪያም መቀነት በሰማይ ላይ ዉበት ፈጥራ በ..ር……ቀት ያየናት እንደሆነ
እኔ ነኝ እኔ ነኝ…እኔ ነኝ… በሚል በፍቅር እንጋጫለን እኔ ነኝ ቀድሜ ያየሁት ለማለትና የቀዳሚነቱን ስፍራ ለማግኘት፤(በሰማይ ላይ ይታዩ የነበሩ የቃል ኪዳን ምልክቶች ሁሉ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ላይታዩ የማሉ ይመስል ሰማዩ ጠቁሯል )
ከእንቅልፉ ዘግይቶ የተነሳ ቁርሱን አልበላ ያለ ትምህርት እንዳይረፍድበት ግማሽ ዳቦ ይቆረስና ይዘህ ብረር ይባላል፡፡በትናንሽ መዳፎቹ ብርር…….ርር እያለ እየከነፈ እየበረረ ……እ ….የ ….ቆነጠረ …… እየበላ….. እያስጎመጀን……እየበረረ ወደ እኛ ያቀናል …. ጥላ ስር…… ዛፎቹ…. ጎጆዎቹ ስር….. ….. ልንሰባሰብ ….. ፊደል ልንዘራ ….ልንበትን ልናጭድ ልንወቃ …. ደግመን ልንዘራ……
በርቀት ያየነዉ እንደሆነ ገሚሶቻችን ደስ ሲለን ገሚሶች ደግሞ እንደማብሸቅ ይቃጣናል፤
እንቅልፋሞ … እንቅልፋም …እን…ቅ…ልፋም እንቅልፋም …. እያልን ከፊት ከፊት እንሮጣለን ትንሽ ከኛ አቅሙ ሻል ካለ መግቢያ ቀዳዳ እስኪጠፋን እንሮጣለን (እንደዛሬዉ በሰርቪስ ፣ በኮንትራት ታክሲ ፣ ወላጅ እግረመንገዳቸዉን ጣል አርገዉ መሄድ የለም )
 ከፍሎ እንደ ሚሰጠን ያወቅን ደግሞ ወደርሱ ሮጥ ብለን ያልከፋዉን ሰዉ ለጥቅማችን ስንል አይዞህ በማለት እናባብለዋለን ፤ ከወዳጆቻችን ስለ ዳቦ እንኳረፋለን
አለሁልህ በሚል ስሜት ፀጉሩን እየደባበስን ከጎናችን ሸጉጠን እጅ እጁን እናያለን እርሱም የልማዳችንን የባቄላ ፍሬ የምታክል ዳቦ ቆርሶ ያቀምሰናል(ያሻጽትተናል)
እቺን ብቻ
ቆረስ ያደርግና ይጨምራል
ለኔስ ሌላኛዉ ይጠይቃል
ቆርሶ ይሰጠዋል
ሌላኛዉም ሲበር ይመጣል
ዳቦ የያዘበትን እጆች ወደኋላ ይደብቃቸዋል
ሲሮጥ የመጣዉ ክፍት ይለዉና አይኖቹ እምባ እንደማቅረር ይላሉ

ዋጋ የሚያሰከፍሉ ጥፋቶች!

ትዉልዱ የሚከፍለዉ ነገር ግን ሊከፍለዉ የማይገባዉ ዋጋ! ይህ ትዉልድ ስለ ሃገሩና ስለ ሃይማኖቱ የከፈለዉን ዋጋ ምንም የሚወዳደረዉ የለም፤ ይልቁንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከማንም ክርስቲያን ልብ ዉስጥ ከማይጠፉት ከምዕመናኖቿ ጋር የተወጣቻቸዉን ሁለት ክፉ አጋጣሚ እንመልከት፡-
. የዮዲት ጉዲት
.የግራኝ መሐመድ …. እያሉ መቀጠል ይቻላል፤
ነገሥታት እና መንግስታት በመጡ ቁጥር አንዳቸዉም አልበጇትም ሊያስብል በሚችል መልኩ ጠላቶቿ ነበሩ፡፡ በእግዚአብሔር ቸርነትና በሕዝቦቿ አንድነት ግን የተቃጣባትን መከራ ሁሉ ብዙ ዋጋዎችንም ከፍላ ቢሆን ተወጥታዉ እነሆ 21ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ደርሳለች ሆኖም ግን ጠላቶቿ እየበዙ ሄዱ እንጂ ወዳጅ አላፈራችም፡፡
እንደ ግራኝ መሐመድና እንደ ዮዲት ጉዲት ቀጥታ በቤተክርስቲያን ላይ ታጥቀዉ አይምጡ እንጂ ጉዳት በማድረሱ ግን (ከሁለቱ ዘመናት የተረፉትን ንዋየ ቅድሳት በማቃጠል፣በመዝረፍ፣በማሸሽ፣ቤተክርስቲያንን በማቃጠል፣ካህናትን በማሰር፣በማወክ፣በመግደል …. ) ከትላንት ሳይብስ አይቀርም፡፡ ትላንት ርስት ጉልት የነበራት ቤተክርስቲያን ዛሬ አጥሮቿ እየተነቀሉ ይገኛል፤ ታላላቅ ሃገራዊና ሃይማኖታዊ ፋይዳ ያላቸዉን ሥራ የሰራች ቤተክርስቲያን ለእነሱ አካሄድ ስላልተመቸች ባሏት ልጆች ዳር ድንበሯን አናስደፍርም፣ የአባቶቻችንን ርስት አንሰጥም ባሉ ….ወዘተ ምክንያቶች ከአሸባሪነት እየፈረጇት ይገኛል፡፡
አላስፈላጊ ዋጋ መክፈል ብልህነት ሳይሆን ከየዋህነትም አልፎ ጅልነት ነዉ!
ሰዉ ለሚጠቅመዉና ለተጠቀመበት ነገር ዋጋ ይከፍላል፤ መክፈልማ አለበት ህግም ያስገድደዋልና፡፡

ሐሙስ 20 ማርች 2014

Part one “… … አጋጣሚ”

“የህዳር ሚካኤል ካለፈ አንድ ወር ሆኖታል ታህሳስ ከገባ ደግሞ 11ኛ ቀኑ ነዉ እንደከዚህ በፊቱ በፌስ ቡክ እናወራለን፣ ምሥጢሬን ሁሉ ነዉ የምነግረዉ አንድም የምደብቀዉ ነገር አልነበረኝም፤ እህቴ እቤት ዉስጥ የጤና ባለሙያ ሆና ሳለ ትንሽም ራሴን ሲያመኝ በጣምም ምቅቅ ብዬ ጨጓራዬ ሲያሰቃየኝ የማወራዉ ለሱ ነበር፡፡
በጣም እጅግ ሲበዛ በ…ጣ ም ይመክረኛል፣ ያፅናናኛል እኔም ምን እንደሆነ አላዉቅም እፅናናለሁ፣ ወዲያዉ የማላዉቀዉ ጤንነት ይሰማኛል፡፡ በነበረን ጊዜያት አንዴ ብቻ ነዉ የማደርገዉን ነገር ያልነገርኩት እሱንም አስቤዉ አልነበረም በዚያን ጊዜ ሲጠፋብኝ በጣም ቅር አለኝ፤ በነጋ ቁጥር የፀሐይ ብርሃን ሳይሆን የርሱ ድምጽ ነበር የሚናፍቀኝ፣ ስልኬን ስሰጠዉ ምንም ቅሬታ አልነበረኝም ፣ የመኖሪያ ቤቴን ሰፈር ሁሉ ስነግረዉ ደስ እያለኝ ነበር፣ አሁን ግን እነዛ ድምጾቹ የሉም ርቀዉኛል፤ የሚገርመዉ ድምፁን የምናፍቀዉ ኔትወርክ በሌለበት ስፍራ ነዉ፡፡ ተራራ ባየሁ ቁጥር ሞባይሌን እንደ አቅጣጫ መጠቆሚያ ከመዳፌ አላርቃትም ነበር፤አሁንም አሁንም ደጋግሜ አያታለሁ ቻርጅ ባየሁ ቁጥር መሰካት ነዉ ከሞባይሌ ርቄ መሄድ ጥሩ ስሜት ከማይሰሙኝ ነገሮች መካከል ዋነኛዉ ነበር፡፡ ቀናቶች እየነጎዱ ጤናዬም መለስ እያለ ስለመጣ ወደ አዲስ አበባ መመለስ ፈለኩኝ እንድመለስ ያደረገኝ የጤናዬ ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ እሱን የማግኘት ፍላጎቴ ካቅሜ በላይ ስለሆነብኝም ጭምር እንጂ ፡፡ ለነገሩ ወደዚህ ስመጣ ስራዬን ለቅቄ ነበር የመጣሁት ልቤ ግን ክፍል ለማለት ወደኃላ አልል አለኝና አስጨነቀኝ፡፡ደብረ ብርሃን ስደርስ ጭንቀቴ እየጨመረ ሄደ፣ መንገዱ ራቀብኝ፣

ማክሰኞ 18 ማርች 2014

ጊዜና ዘመን

ጊዜ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ይታሰባል ይከወናል ትናንት ዛሬን እየሆነ ይቆጠራል፤ ትናንትናና ዛሬ ተደማምሮ ሳምንት ሳምንታትና ቀናት ተደማምረው ወራትና ዓመታትን /ሦስት መቶ ስልሳ አምስት ቀናትን/ ይሰጣሉ፡፡ ከአዳም ጀምሮ ዓመት ይቆጠራል፡፡ የዓመታት ጥርቅም ዘመን ተብሎ ይጠራል ዘመን ረጅም ጊዜ ነው ወይም አንድ አይነት አገዛዝ አምልኮ ሌላም የተደረገበት ጊዜ መጠሪያ ነው፡፡
       ዘመን የተፈጠርንበት /የተወለድንበት/ ትምህርት የጀመርንበት፣ ሥራ የያዝንበት፣ መከራን ያየንበት፣ ከውድቀታችን የተነሳንበት፣ የተማመንበት፣ የተፈወስንበትወቅት ማስታወሻ /መጠሪያ/ ሊሆን ይችላል፡፡
       ወደ ፍሬ ነገሩ ልምጣና ከብዙ ሰዎች አንደበት ስሰማና ከብዕራቸው የዕምባ ጠብቃ ሳነብ ብዙዎች ዘመንና ጊዜን ሲደግፉ በከንቱ ስሙን ሲያጠፉ ሲኮንኑ አዳምጣለሁ አነባለሁ ‹‹አይ ዘመን፣ አይ ጊዜ›› ‹‹ጊዜው ነው፣ ዘመኑ ነው›› ሲሉ ነገር ግን ጊዜና ዘመን ምን አደረገ ምንስ በደለ ጊዜና ዘመን በራሱ ምን ያመጣው ለውጥ ምንስ ያደረሰው ተፅዕኖ አለ? አንዳንድ ፀሐፍት እንደሚሉት ዘመንና አህያ አንድ ነው ይላሉ አህያ እንዳሸከሟትና የጫኑባትን ይዛ እንደምትገኝ ዘመንም

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...