እሑድ 22 ጁን 2014

አለመግባባትን ለማሰወገድ



በመኖር ዉስጥ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በምን መልኩ መፍታት ይቻላል?
Image:Resolve Conflict in Marriage Step 8.jpg
የሰዉ ልጅ በህይወት ዘመኑ ረጅምም ይሁን አጭር፣ አስደሳችም ሆነ አሳዛኝ የሆነ ህይወን መኖሩ ግድ ነዉ፡፡በዚህ ወቅት ሁሌ መግባባቶች ብቻ ናቸዉ ብሎ ማሰብ የማይታሰብ ጉዳይ ነዉ፡፡ታዲያ አለመግባባት ካለ ይህንን አለመግባባት እንዴት መፍታት ይቻላል? ዋናዉና መሠረታዊዉ ጥያቄ ነዉ፡፡
ወደ መፍትሄዉ ከመሄዳችን በፊት እስኪ አለመግባባቶች ከምን እና ከማን ዘንድ ይፈጠራሉ የሚሉትን በጥቂቱ እንመልከት፤
ü  ባለትዳሮች (ባል ከሚስት ወይም ሚስት ከባል ጋር)
ü  ወላጆች (ቤተሰብ) ከልጆች ጋር ልጆች ከቤተሰብ/ከወላጅ ጋር፤ (ቤተሰብ በጠቅላላዉ እርስ በርስ ሠላም ዝር የማይልበት ቤት
ü  ፍቅረኞች (ወንዱ ከሴቷ ሴቷ ከወንድ ፍቅረኛዋ ጋር)
ü  ጓደኛሞች (ወንዶች ከወንዶች፣ ሴቶች ከሴቶች፣ ወንዱ ከሴት፣ ሴቷም ከወንድ ጋር ) ትንሽ በሚባሉ ችግሮች የሚፈጠሩ አለመግባባቶች
ü  መንግስትና ህዝብ (ባለመደማመጥና ባለመከባበር እኔ ነኝ የምገዛህ ወይም የማስተዳድርህ፣ አንተ አትገዛኝም ወይም አታስተዳድረኝም አለበለዚያም ወደ ሥልጣን ያመጣሁህ እኔ ነኝ … እንዳመጣሁህ አወርድሃለዉ….)
ü  መንግሥት ከመንግሥታት/ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች (በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች እና ኃይልን ለማሳየት በሚሞከር ትንኮሳ፣ በጉርብትና፣ በድንበር ጉዳይ፣ ቅኝ ለመግዛት በማሰብ እና ላለመገዛት መወሰን፣….)
ü  መንግሥት ከተቋማት ጋር (በሪፖርት፣ በዜና እወጃ፣ ምሥጢር በማዉጣት፣ ጫና በመፍጠር ፣ ጥቅማ ጥቅሞችን በማስቀረት፣ ሌሎች ወገኖችን በማሳመፅ፣ አላስፈላጊና አወዛጋቢ አዋጆችን በማወጅ፣ ….)
ü  ወዘተ
ችግሮች የሚፈጠሩበትን አካባቢ እንዲህ በጥቂቱ ከዘረዘርን በማዕከልነት መፍትሔዎችን እንዲሁ በጥቂቱ ማንሳቱ አወያይ እና ሌሎችንም ሻል ያሉ ምፍትሔዎችን በተጠና መልኩ ያመጣሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለጊዜዉ ጥናቱን ለባለሙያዎቹ ልተዉና ይሆናሉ የምላቸዉን እነሆ ብያለሁ፡-

ከመፍትሔዎቹ መካከል በዋናነት ለኔ የታዩኝ፡-
1)     ችግሩ ያለዉ በሌላኛዉ ወገን ነዉ የሚለዉን አመለካከት ወይም እምነት በፍፁም ማስወገድ (ምናልባት ሊከብድ ይችል ይሆናል ምንም ቢከብድ ይህንን ሳያደርጉ መፍትሔ ማፈላለግና መስማማትን መናፈቅ የህልም ያህል እዉነት አይሆንም፤) ወደ ዉስጥ ማየት የችግራችን ትልቁ መፍትሔ ነዉና፡፡ ጊዜ ወስደን ወደራሳችን ስንመለከት ቢያንስ ራሳችንን እናገኘዋለን/ እናዉቀዋለን ያ ደግሞ በዉስጣችን እንደ እሳት ለተቀጣጠለ አለመግባባት መረጋጋትን/ መስከንን ያመጣልናል፤ በመረጋጋትና በሰከነ አዕምሮ መረጋጋት ደግሞ ይህ ነዉ ተብሎ ሊጠቀስ ከሚችል በላይ መፍትሔ ያመጣል፡፡ ወደ ዉስጣችን እንይ …..
2)    የችግሩ ባለቤት መጨረሻ ላይ ሙሉ በሙሉ እኛ እንኳን ሆነን ብንገኝ እና ቢረፍድብን በፀጋ ተቀብለንና ተሸንፈን ለዉጡን ለማምጣት ሰላሙን ለማዉረድ ቁርጠኛ መሆን (ቁርጠኝነት ሳይኖር ለይምሰል ብናደርገዉ ችግሩ መልኩን ቀይሮ በሌላ መንገድ መምጣቱ አይቀርምና፡፡ ) በተለይ እርቃችንም ሆነ ስምምነታችን ስለአንድ ስለምንወደዉ ስለምንፈልገዉ ነገር ብለን ከሆነ ትክክል አይደለም ምክንያቱም ዛሬ እጅግ በጣም ወደናቸዉ ትልቅ ዋጋ የምንከፍልላቸዉ ነገሮች ከጊዜ ብዛት ወረታችን ያልቅና ልንጠላቸዉ እንችላለን፣ ነገ ሌላ ነገር ልንፈልግ እንችላለን፣ በነገ ሕይወታችን ሌላ ችግር ሊፈጠር ይችላል ( መቸስ ችግር ተለይቶን የሚኖርበት ዘመን የለምና፤ ) ያኔ እነዚህ ችግሮች ሲከሰቱ ትላንት ለይስሙላ ያደረግናቸዉ መስማማቶች ትልቅ ዋጋ ያስከፍሉናል፡፡ ለጊዜዉ ጥለነዉ ወደመጣነዉ አለመግባባት ህይወት ዉስጥ ይዝፍቁናል፡፡ ባልና ሚስት ( ባለትዳሮች ) በዘመናቸዉ ሲጋጩ ለመፍትሔ ሲነጋገሩ ለጊዜዉ በሚል ብቻ ከላይ ከላይ ቢያወሩና የዛሬን ብቻ ትግባ ከዚህ በኋላ ክፉ ነገር መሃላችን አይገባም ብለዉ ራሳቸዉን ቢሸነግሉ እና ችግር ቢያጋጥማቸዉ ያንን ያጋጠማቸዉን ችግር ካለዉ ጋር ደምረዉ ማየታቸዉ እና ችግሩን ከባድ እና የማይፈታ አድርገዉ ማየታቸዉ አይቀሬ ነዉ፡፡ አገራትም ቢሆኑ ለጊዜዉ የሰዉ ህይወትና ንብረት ከሚወድም ብለዉ አለበለዚያም ከችግሩ ይልቅ ለአደራዳሪያቸዉ ቦታ በመስጠት የተለያዩ ስምምነቶችን ቢፈራረሙም የተኩስ አቁም ስምምነቶችን ቢያደርጉም በተወሰኑ የጊዜ ርቀት ግጭቱን እንደገና ማስነሳታቸዉ እና ሰላም ማጣታቸዉ የማይቀር ነዉ፡፡ እንዲያዉም አንዳንድ ስምምነቶችና እርቆች ባለጉዳዮቹ ላይ ያጠነጠነ ስምምነት/ ዕርቅ ሳይሆን ‹‹ ጠላት ለምን ደስ ይበለዉ ›› በሚል ጠላትን ለማሳፈር የሚመስልበት ጊዜም አለ፤ ‹‹ ወረኛም ያዉራ ጠላትም ይፈር እኛስ ሆነናል ፍቅር በፍቅር ›› እንደሚባለዉ፡፡ ቁርጠኞች እንሁን … …
3)    በችግሩ ላይ ብቻ መነጋገር (ዉይይቱን ግለሰቦች ላይ ያነጣጠረ አለማድረግ ማንም ሰዉ ሲነኩት አይወድምና ) ጠላታችን ሠዉ ሳይሆን ያ መጥፎ ተግባር ወይም ስርዓት ስለሆነ ምንም እንኳን የድርጊቱ ባለቤት ሠዉየዉ አስቀድመን ባነሳናቸዉ ሁለት መሠረታዊ ሃሳቦች ትንሣኤ ልቡና ስላገኘ መጥፎዉን ነገር በጋራ መታገል፡፡ ሲጀመር ሰወች መጥፎዎች አይደሉም የሚል እሳቤ ሊኖረን ይገባል የሰዉን ልጅ መጥፎ የሚያሰኘዉ ተግባሩ ነዉና ያ ተግባር ደግሞ መጥፎ ሲሆን አድራጊዉም በሰራዉ ስራ ይጠራልና አንድ ወታደር በጦርነት ስም ጦረኛ ተብሎ እንደሚጠራ፡፡ ይህ ሰዉ በሰላም ወቅት ሰላማዊ ሰዉ እንደሆነ ሁሉ ዛሬ በመካከላችን ሰላም ከመጥፋቱ የተነሳ ፀብ ከመካከላችን ቢገባም የትላንቱ ሰላማዊ ሰዉ እንደሆነ መዘንጋት የለብንም፡፡ የማንክደዉ ይህ ሰዉ ዛሬ አስቀይሞን ፣ በድሎን፣ ጠላታችን ሆኖ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን መሰረታዊ ጠላታችን ሰዉየዉ ሳይሆን በመካከላችን የገባዉ ጉዳይ/ችግር ነዉ ጠላታችን፡፡ ሊወገድም የሚገባዉ ጣልቃ የገባዉ ችግር ብቻ ነዉ፡፡ በአገራትም መካከልም ስላለዉ ሽኩቻ ያነሳን እንደሆነ እስራኤልና ፍልስጤም፣ ኢራንና ኢራቅ፣ ሰሜንና ደቡብ ሱዳን፣ ሰሜን ኮርያና ደቡብ ኮሪያ፣ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ … ህዝቦች ሳይሆኑ በጥቅሞችና/በድንበሮች እንጂ ሌላ የእርስ በርስ ፀብ የላቸዉም ሰወችም እንዲሁ ናቸዉ፡፡ ጠላታችን ሰዉ ሳይሆን ያልተግባባንበት ጉዳይ እንደሆነ ሁሌ ልብ እንበል …
4)    የተሻለ ነገር በመስራት ፍቅርን ማዳበርና ዘላቂ ሰላምን እዉን ማድረግ ( በመሃል ያለን አለመግባባት ማስወገድና ዝም ማለት ብቻ መፍትሔ አይደለም፤ ዝምታዉ ያለፈን ጊዜ ማጠንጠኛ ይሆናልና ቀሪዉን መጪ ጊዜ ያለፈን መርሻ የፊተኛዉን ጊዜ ብሩህ ለማድረግ መልካም ነገርን መፍጠር እና መስራት ….) አገራት ሰላም ባጡ እና ግጭት ዉስጥ በገቡ ጊዜ ያጠፉትን/ ያወደሙትን ነገሮች በጋራ የማልማት/ ወደ ቀደመ ቦታ የመመለስ ልምድ ቢያዳብሩ መልካም ነዉ፡፡ ( አሜሪካ ሳዳም ሁሴንን ከስልጣን ለማዉረድ ኢራቅን እንዳልነበረች ካደረገች በኋላ ወደነበረችበት ለመመለስ ለማድረግ እንደሞከረችዉ ፣ እንደሊቢያም ቢሆን፤ ኢትዮጵያ እና ኤርትራም እንዲሁ አድርገዉ ቢሆን፡፡ ባለትዳሮችም፣ፍቅረኞችም፣ባልንጀሮችም … እንዲሁ አንዳቸዉ ለአንዳቸዉ ቢካካሱ ፣ ቢተሳሰቡ፣ ፍቅርን ቢያደረጁ መልካም ነዉ እላለሁ፤ ቁርሾን ከማስወገዱም አልፎ ተርፎ ነገ ሊመጣ የሚችለዉን ዳግም መበጣበጥ ያሰቀረዋል ፍቅርንም ያደረጃልና፡፡ ) ያለፈዉን ጊዜ ትቶ በሰላም በፍቅር በልማት በአንድነት ላይ ያተኮረ ስራን መስራት የተሻለ ይሆናል፡፡
5)    ለቀጣይ ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ (ይህ የሚያሳየን እንደ ብልህ ሰዉ ከትናንትና ዉድቀት መማራችንና ለነገ ጠንካራ ሰዎች እንድንሆን ዝግጁ ያደርገናል፡፡) ሰዎች ዛሬ ወይም ትናንት ለተከሰተዉ መፍትሔ መስጠትና እርቅ ማዉረድ እንችላለን ነገር ግን ያለፈዉ ጊዜ ተመልሶ እንዳይመጣ ጥቃቅን ከምንላቸዉ ችግሮች አንስተን ትላልቅ እስከምንላቸዉ ችግሮች ላይ ትልልቅ አትኩሮት ሰጥቶ መጠንቀቅ፣ ለሚነሱትም እንከኖች ተመጣጣኝ አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት አንችልም፡፡ ወዳጃችን ሁሌ ወዳጅ መስሎ ይታየናል ትላንት ያጋጨን ጉዳይ ተመልሶ የማይመጣ ( የዉሾን ጉዳይ ያነሳ ዉሾ ይሁን እንላለን፤ ነገር ግን ጦራችንን ከድንበር ላይ ፈቅ አናደርግም … ) መፍትሔዉ ይህ አይደለም ‹‹ ከመጣብኝ አለቀዉም/አለቃትም ›› ማለት ሳይሆን ትናንት/ዛሬ ካጋጨን ጉዳይ ጋር ተመሳሳይነት ያለዉ ጉዳይ ካለ አፍረጥርጦ መነጋገር እና መስማማት፤ ተመልሶ አይመጣም የሚል ሙሉ እምነት መፍጠር ባይቻልም ግን ከምንጩ ለማድረግና ቀጣዩ ጊዜ በሰላም እጦት እንዳይደርስ ጥንቃቄ ማድረግ፡፡   
6)    የተለያዩ ሙከራዎችን ማድረግ ( ችግርን ለመፍታት የመፍትሔ አማራጮቻችን ብዙ መሆን አለበት፣ ስልቹ መሆን የለብንም):: ያደረግናቸዉን ጥቂት ነገሮች ከማሰብ ያላደረግናቸዉን ብዙ ነገሮች በማሰብ እና ተግባር ላይ በማዋል ልዩነቶችን ማጥበብ ይሻላል፡፡
7)    ሌላ ወገንን ጣልቃ አለማሰገባት (በሰዉ ቁስል እንጨት ስደዱበት) እንደሚባለዉ ሠዉ የገባበት ጉዳይ ከራስ ስለማይሻል ሌላ ወገን መሃል እንዲገባ ለመፍቀድ አለመቸኮል ( እንዲህ ስል ሰዉ አያስፈልግም ማለቴ አይደለም፤ መፍትሔዉ በእጃችን እንዳለ ልጠቁማችሁ ከመፈለግ የተነሳ እንጂ ) ምንም እንኳን ችግሮች ቢኖሩም ሰዉ ለሰዉ መድሃኒት ነዉና፡፡ ቢሆንም ‹‹ ከባለቤቱ ያወቀ … ›› እንደሚባለዉ ከማንም እና ከምንም የተሻለ መፍትሔ በእጃችን አለና፡፡
8)    ጊዜ መምረጥ (በችግሩ ላይ መወያየትን እንደ አንድ መፍትሔ ከወሰድን ዘንድ የመወያያ ጊዜ መምረጥ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል የምናናግረዉ ሰዉ በደከመዉ ሰዓት፣ (ከሰዓት በኋላ ወይም ከሥራ ከወጣ በኋላ አሊያም ሥራ ላይ እያለ)፣ በተበሳጨ ሰዓት፣ ችግሩ እንደተፈጠረ ወዲያዉ፣ የተፈጠረዉን ነገር ከረሳዉ በኋላ፣ (እጅግም መፍጠን እጅግም መዘግየትአላስፈላጊ ነዉ፤)) ለመነጋገር ጊዜ መምረጥ አስፈላጊ መሆኑን እንዳመንበት ሁሉ ችግሩ ከመከሰቱ በፊትም ቢሆን የሰዉ ልጅ የሚነጋገርበትና የሚወያይበት ሰዓት እና ጊዜ ያስፈልገዋል፡፡
9)    ቀጥታ ወደ ጉዳዩ ዘሎ አለመግባት (ይህ ድርጊት የሰዉየዉን ሁኔታ የምንቃኝበት ይሆናል በቃ ዛሬ መነጋገር አለብን ብለን ወስነን ስለመጣን ብቻ ነገሩን ማንሳቱ የበለጠ ነገሩን የምናስብብት ይሆናልና) ሠዉየዉ ያለንበትን ሁኔታ ማየትና የሚያስኬድና የምንፈልገዉን ዉጤት ሊያስገኝልን እንደሚችል ሙሉ እምነት ሲኖረን መጀመሩ የተዋጣ እና ስኬታማ ያደርገናል፡፡
10)   ስለችግሮቻችን ስንነጋገር በጓደኞቻችን ላይ ጣታችንን አንቀስር ( አንተነህ! አንቺ ነሽ! ) መባባል የለብንም፤
11)    በምንነጋገርበትም ሰዓት ተቀራርበን በተረጋጋ መንፈስ መነጋገር አስፈላጊና ቅርበትን የሚፈጥር ይሆናል፤ አብረዉ ከመቀመጥም አልፎ ዓይን ለዓይን ፊት ለፊት መተያየት ሌላኛዉ አስፈላጊዉ ጉዳይ ነዉ፡፡
12)   ስንነጋገር መተማመን መቻል አለብን! ራሳችንን እንደምናዳምጥ እና ሌሎችም እንዲያዳምጡን እንደምንፈልገዉ ሁሉ ሌሎች የሚናገሩትን እንዲሁ ማዳመጥ እንዳለብን ልብ ልንል ይገባል፡፡በደንብ እያደመጥናቸዉ ከሆነ ሰዎች በቃላት መግለፅ የተሳናቸዉን የአካል ቋንቋ ልንረዳላቸዉና ስሜታቸዉን ልናዳምጥ እንችላለንና፡፡ያኔ ምን እንደሚፈልጉ ምን ሊሉ እንዳሰቡ እንረዳቸዋልን፡፡
13)   እርግጠኛ እና ሙሉ እምነት ሊኖረን ይገባናል ( በምናነሳቸዉ ነጥቦች እርግጠኞችና አሳማኝ ጉዳዮችን በማንሳት በአጭር ቃላት ማሳመን የምንችልበት መሆን አለብት፤ አለመግባባት ከተፈጠረብን ሠዉ ጋር ረጃጅም ሃሳቦችን የመደማመጥ ዕድል እና ትዕግሥት ልንነፍግ እንችላለንና፡፡ ሌላኛዉ እንደምናሳካዉ እንደምንስማማ ሙሉ እምነት ሊኖረን ይገባል ባለቤቱ ያቀለለዉን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበለዉም እንዲባል እኛ ያላመንበትን ዕርቅና ሠላም ባላጋራችን ሊቀበለዉ ዝግጁ አይሆንምና፡፡)
14)   ሰዉ ከሰዉ ጋር ሲኖር ችግር መኖሩ እሙን ቢሆንም ለብቻ መብሰልሰል አስፈላጊ አይደለም፤ ምንም እንኳን ለጥቂት ወቅት ብቻ ለብቻችን መሆን ምንም እንኳን አስፈላጊ ቢሆንም ከዉስን ሰዓት በላይ መቆየት የማይመከርና ይልቁንም ለብቻ ከመሆን ተቀራርቦ መወያየት የሚመከርና ወደር የሌለዉ መፍትሔ ነዉ፡፡
15)   በመጨረሻም ሁለቱም ወገን መፍትሔ ፈላጊዎች ከሆኑ ለሚነጋገሩት ነገር ታምነዉ መወያየት አለባቸዉ፤(የዉሸታቸዉን የሚነጋገሩ ከሆነ መፍትሔ ሳያገኙ ጊዜዉ ይጠናቀቃል ሌላም ክፍተት ሊፈጥር እንደሚችል ይገመታል) አለበለዚያ ችግሩ ጉንጭ አልፋ ይሆናል፡፡
16)   የመጨረሻ ግን ከሁሉም የመጀመሪያዉ የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን እንኳንስ በፀብ፣ በሐሳብ ልዩነት መለያየት በሞት እንኳን መለያየት የእግዚአብሔር ፈቃድ ከሆነ ለበጎ ነዉና፡፡ ‹‹ የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን ብለን ዝም አልን፤ ›› እንዲል የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...