እሑድ 4 ሜይ 2014

ክፍል ሁለት …. … የፀየሙ ገጾች (አዲስ አበባ)

  

ብዙ መልኮችና ብዙ ስሞች ያሉዋት አዲስ አበባ አንዱ መጠሪያዋ አራዳ ነበር፤  አራዳና አዲስ አበባ ተነጣጥለዉ የሚታዩ አልነበሩም፡፡ በአንድ ወቅት ታላቁ ሰዉ አቶ ይድነቃቸዉ ተሰማ ስለ አዲስ አበባ በሬድዮ ፕሮግራም ተጠይቆ ሲናገር እንዲህ ነበር ያለዉ፡- ‹‹ የአዲስ አበባዉ ስታድየም አሁን አለበት ቦታ እንዲሠራ ሐሳብ ሲቀርብ ኳስ ሜዳዉን ከከተማ ዉጭ አደረጋችሁት ተብለን ተወቀሰን ነበር፤ ›› እንግዲህ በወቅቱ አዲስ አበባ ምን ያህል ጠባብና ስንት ህዝብ ይኖርባት እንደነበር መገመት ቀላል ነዉ፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ስታድየምን ያህል ነገር ሲሰራ ከከተማ ወጥቷል ከተባለ የስልጣኔ ጥጓ ምን ያህል ድረስ እንደነበረ መገመትም አይዳግትም፡፡ በቅርቡ እንኳን በ 20 እና በ 30 አመታት ጊዜ ዉስጥ እንኳን የነበራትን ገጽ ብንመለከት አዲስ አበባ እንኳንስ የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ልትሆን ይቅርና ለዋና ከተማነት እንኳን የምትመረጥ አልነበረችም፤ ካረጁ ቤቶቿ እና ከፈራረሱ መንገዶቿ አንፃር፡፡ በዚህ የታሪክ አጋጣሚ በ1879 ዓ.ም. የቆረቆሯት አጼ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ተነስተዉ የትናንትናዋን ባለጎፈሬዋን እና የዛሬዋን ‹ዉብና ድንቅ› እንዲሁም ሰፊ ከተማ በወቅቱ ከነበረዉ ጋር ለማነጻጸር ‹‹ ዕድል ›› ቢገጥማቸዉ ምን ይሰማቸዉ ይሆን? ያስብላል፡፡  
እንደዉ የሚሉትን ነገር ገምቱ ብንባል ዘና ለማለትና በዚያዉም ምሳ ነገር ለመጋበዝ የቀድሞዉን ‹‹ኢምፔሪያል›› የዛሬዉን     ‹‹ ጣይቱ ሆቴል›› ዉሰዱኝ ሳይሉ እንደማይቀሩ እንገምታለን፤ እኛም መቸስ የጠየቁትን አንነፍጋቸዉም እንወስዳቸዋለን፡፡ መቸስ ስለ ጣይቱ ሆቴል ከተነሳ አንድ እዉነት ልንገራችሁ፡- በራዲዮ የቀረበ ነዉ፤ እኔም ከ100ኛ ዓመት በዓል መዘከሪያ መጽሔት ላይ ያገኘሁት ነዉ፡፡
 ላዲላስ ፋራጎ ይባላል፡፡ ጋዜጠኛ ነዉ፡፡ላዲስ ፋራጎ ከለገሃር ባቡር ጣቢያ ተነስቶ ጣይቱ ሆቴል ይሄዳል፡፡ከጅቡቲ፣ከድሬደዋና ከአዋሽ ተሸክሞት ከመጣዉ አዋራና ላብ ለመገላገል ቸኩሎ ነበር፡፡
ከመኝታ ቤቱ ሲገባ ግሩም የሆነ የገላ መታጠቢያ ገንዳ (ባኞ) በማግኘቱ እጅግ ተደስቶ ቦዩን ጠራና ‹‹ ገላዬን ስለምታጠብ ገንዳዉን ሙላልኝ ›› ይለዋል፡፡
ቦዩም (አስተናጋጁ) ስንት ታንካ (ጀሪካን) ዉሃ ላስመጣልዎ ›› ይለዋል፡፡
ፈረንጁ ግራ ይገባዉና ‹‹ ገንዳዉን ሙላልኝ ነዉ የምልህ፡፡ ቧንቧዉን ክፈተዉ፡፡›› ይለዋል፡፡
 አሁንም ቦዩ ይመልስና ‹‹ ገላዎን መታጠብ ከፈለጉ የሚፈልጉትን የዉሃ መጠን ይንገሩኝ፡፡ ያንዱ ታንካ ዉሃ ዋጋ አራት ግርሽ (ጠገራ ብር ወይም ማርያቴሬዛ) ነዉ፡፡ ›› ይላል፡፡  (ገንዳዉን የሚሞላዉ ስድስት ታንካ (108 ሊትር) ዉሃ ነዉ፡፡) ላዲስላስ ፋራጎ ቀጠለና ‹‹ እንዴ? የቧንቧዉን ዉሃ በታኒካ ልክ ታስከፍላላችሁ ማለት ነዉ?›› ሲል ቦዩን ጠየቀዉ፤
ቦዩም ‹‹ አይደለም! ዉሃዉ የሚመጣዉ ከፍል ዉሃ ነዉ፡፡ ኩሊዎ (ተሸካሚ) ይላኩና ፍልዉሃ ሄደዉ ታኒካዉን በፈላ ዉሃ ከሞሉ በኋላ ተሸክመዉ ያመጡታል፡፡ አንድ ኩሊ ዳዉን 6 ታኒካ ዉሃ ይሞላዋል፡፡ ገላዎን አንዴ ታጥበዉ መለቅለቅ ከፈለጉ ደግሞ ተጨማሪ ታኒካ ዉሃ ማስመጣት ያስፈልጋል ›› አለዉ፡፡
‹‹ገንዳችሁ ላይስ የተተከለዉ ቧንቧ?››
‹‹ እንዳልኩዎት ዉሃዉ የሚመጣዉ ክፍል ዉሃ ነዉ፡፡››
ላዲስላስ ፋራጎ ገባዉ፡፡ ገንዳዉ ላይ የተተከለዉ ቧንቧ ለጌጥ ነበር፡፡

ይህ እንግዲህ የ125 ዓመት ታሪክ ነዉ ፤ ዛሬም ከዚህ ረጅም ዓመታት በኋላ እንደድሮዉ ዉሃዉ ከፍል ዉሃ ባይመጣም ለገላ መታጠቢያ ዉሃ ስንቸገር ቤተሰቦቻችን ወይም አከራዮቻችን አለበለዚያም በእንግድነት ያረፍንበት መኝታ ክፍል አከራዮች ዉሃ የሚመጣዉ ከለገዳዲኮ ነዉ ቢሉን ግር አይለንም፡፡ የዉሃ ችግር ‹‹ ከጥንት ነዉ ከመሰረቱ ›› እንደሚባለዉ ነዉና፡፡ ምን ይሄ ብቻ የአዲስ አበባን ነዋሪ የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት በዘመናዊ መልኩ መንግስት እየሰራ ያለዉ የጋራ መኖሪያ ቤት ችግር አንዱና ዋነኛዉ ዉሃ እንደሆነ የሚኖርበት ያዉቃል፡፡ የባሰዉን ለንጽጽር አነሳን እንጂ ከተማዋ ዉሃ እንደጠማት 125ኛ ዓመትዋን አከብራለች ማለት ያስደፍራል፡፡ እንግዲህ ካነሳን አይቀር ላዲስላስ እና የአዲስ አበባ ነዋሪ ብዙ ነገሮች ያመሳስሉታል፤ ይኸዉም ደግሞ እሱ በጣይቱ ሆቴል ያንን በመሰለ ባኞ ቤት ዉሃ በጀሪካን አስቀድቶ ለመጠቀም እንደተገደደ እንዲሁ የአዲስ አበባ ነዋሪ በሚኖርበት 3ኛ እና 4ኛ ፎቅ ላይ ባሻት ጊዜ በምትመጠዉ ዉሃ ተማሮ በጀሪካን እየተሸከመና እያሸከም ፎቅ መዉጣት አይቶት የማያዉቀዉን ባኞ ቤት እንደጌጥ እንቁልልጬ እየተባለ አንድ ቀን ገላዉን ሳይታጠብበት ህይወቱ ያለፈች ይኖራል፡፡ ባኞ ቤቱ ዉስጥ የተገጠመዉ ዕቃ ሁሉ ለጌጥ እስኪመስል ድረስ፡፡ የዛሬ 125 ዓመትም አዲስ አበባ ዉሃ በጀሪካን እንደቀዳች ዛሬም ከነዋሪዉ ጀርባ ላይ ጀሪካን አልወረደም፡፡
ከብዙ ድካም በኋላ በአዲስ አበባ ቧንቧ ጉረሮ ዉሃ ቢንቆረቆር እንዲህ ብለዉ ተቀኝተዋል፤(የቧንቧ ዉሃዉ በምኒልክ የስዊዝ ሙያተኛ በአልፈርድ ሊግ እንደተሰራ ይነገራል፤ መሳፍንቱና መኳንንቱም በሊግ ላይ ዉሃ ወደታች እንጂ ወደላይ አይፈስም በሚል መጠነኛ የማይባል እንቅፋት ሆነዉበት ነበር፡፡ ነገር ግን በንጉሱ ትዕዛዝ መሰረት ስራዉን ሊቀጥልና ሊሳካለት ችሏል፡፡ )
‹‹ እንዲህ ያለ ንጉሥ የንጉሥ ቄናጣ፣
ዉሃ በመዘዉር አየር የሚያወጣ፤
ያደፈዉ ሊታጠብ የጠማዉ ሊጠጣ፣
አሁን ከዚህ ወዲያ ምን ጥበብ ሊመጣ! ››
እንግዲህ አዲስ አበባ ከዚህ ቀደም እንደጠቀስነዉ በኅዳር ወር 1879 ትቆርቆር እንጂ መች ቀን እንደሆነ የትኛዉም የታሪክ ተመራማሪ እንዲህ ነዉ ፣ በዚህ ቀን ያለን ሰዉ እስካሁን አላገኘንምና እኛም እንዲህ ነዉ አንላችሁም፡፡ ነገር ግን አዲስ አበባ ከጊዜ ብዛት የሥልጣኔ ማዕከል እየሆነች እንደመጣች እንነግራችኋለን፡፡
‹‹ አዲስ አበባ 1879-1979 ›› የተሰኘዉ መጽሔት እንዲህ ያስቀምጠዋል፤ (ገጽ 16-17)
v  በ1897 የራሺያ ቀይ መስቀል ሆስፒታል ተቋቋመ፡፡
v  በ1898 የመጀመሪያዉ ሲኒማ ቤት ተከፈተ፡፡
v  በ1905 የአቢሲንያ ባንክ ተከፈተ፡፡
v  በ1907 እቴጌ ሆቴል ሥራዉን ጀመረ፡፡
v  በ1908 ምኒልክ ትምህርት ቤት ተከፈተ፡፡
v  በ1910 በራሺያ ሆስፒታል ሥፍራ ላይ የምኒልክ ሆስፒታል ተቋቋመ፡፡
v  በ1911 የመንግሥት ማተሚያ ቤት ሥራ ላይ ዋለ፡፡
በነዚሁ ዘመናት አቅራቢያ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ሌሎችም የሕንፃ ሥራዎች ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡
v  በ1900 – 1913 ወደ አንድ መቶ የሚጠጉ ዘመናዊ ቤቶች ተሠሩ፡፡( እነዚህ ቤቶች የሠሩት በጣት የሚቆጠሩ የገዥዉ መደብ አባላት ሲሆኑ ከ12 – 14 ሺ የሚገመተዉ የከተማዉ ሰፊ ሕዝብ በድንኳን ይኖራሉ፡፡)
v  የሸክላ ሥራ በእነዚህ ዓመታት ተጀመረ፡፡ የመጀመሪያዉ የሸክላ ቤት በ1898 በቤተመንግሥቱ ቅጥር ግቢ ተሠራ፡፡ የሸክላ ሥራ እሰከ 1907 ማለትም ፋብሪካዉ እስከተቋቋመበትም፡፡ ይህንኑ የሸክላ ፋብሪካ ያቋቋሙት አንዱ ኢጣሊያዊ ሲሆን ሶስቱ ደግሞ ግሪኮች ናቸዉ፡፡
(ከላይ እንዳየናቸዉ የሸክላ ፋብሪካዉም ሆነ ማተሚያ ቤቱ የትኛዉ እንደሆነ መጽሔቱ የሚገልጸዉ ነገር የለም፡፡)
v  በ1903 አከባቢ የቤት መሥሪያ የብረት ጉራጅና ሌሎችም ብረት ነክ የቤት መሥሪያዎች ወደ አዲስ አበባ የገቡት ከድሬደዋ ጅቡቲ የባቡር ሃዲድ ከተከፈተ በኋላ ሲሆን አምጭዉም ኦክስ ካርት የተባለዉ የትራንስፖርት ካምፓኒ ነዉ፡፡ ይህም ካምፓኒ ለድሬደዋ ከተማና ለአዲስ አበባ ከ50ሺህ ያላነሱ የቤት ክዳን ቆርቆሮዎች ከ1905 – 1906 አስገብቷል፡፡( ይሁን እንጂ ይህን ያህል ቆርቆሮም ቢገባ ብዙ ዘመናዊ ቤቶችም ቢገነቡ አብዛኛዉ የከተማ ነዋሪ ይኖር የነበረዉ በሳር ቤት ክዳን እና በድንኳን እንደነበረ ይነገራል፤ ዛሬም ‹‹ የዘሬን ብተዉ … ›› ያለች አዲስ አበባ ይመስል በጣም እጅግ ብዙ ዘመናዊ ቤቶች ቢኖሩዋትም የዚያኑ ያህል አብዛኛዉ የከተማዉ ነዋሪ የሚኖረዉ ጣሪያቸዉ ባደፉና ግድግዳቸዉ የአፈር ከመሆኑ አልፎ ተርፎ የፈራረሱ ናቸዉ፡፡)
v  በ20ኛዉ ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ ሶስቱ ታዋቂ ጎዳናዎች ምኒልክ ጎዳና፣ ራስ መኮንን ጎዳና እና ሩሊኦን ቼፍኑክስና ጎዳና ከቤተመንግስት አንቶ ወደ አቢሲንያ ባንክ ከዚያም ወደ እቴጌ ሆቴል ሲወስድ፣ ሁለተኛዉ ደግሞ ከእንጦጦ መንገድ አንስቶ የራስ መኮንን ድልድይ አቋርጦ ወደ መርካቶ ይመጣና ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል በማድረግ ወደ አዲስ ዓለም ያመራል፡፡ ሶስተኛዉ ከመርካቶ ተነስቶ የምኒልክን ጎዳና አቋርጦ በፈረንሳይ ሆቴልና በቺፍኑክስ ጎዳና በማለፍ ወደ ፍል ዉሃ ይወስዳል፡፡ (እንዲሁም ከመርካቶ አንስቶ ወደ ተለያየ አቅጣጫ የሚወስዱ ሶስት ወይም አራት የሚሆኑ መንገዶች ስማቸዉ ባይጠቀስም በዚሁ ጊዜ እንደተሰሩ ይታወቃል፡፡ የዛኔዎቹ ሶስትና አራት መንገዶች እንዳሉ ሆነዉ አዲስ አበባን ዘመናዊ ያሰኙ ደረጃቸዉን የጠበቁ መንገዶች እንደ ልጃገረድ ቀለበት አጥልቀዉላት ይገኛሉ ረጅም እድሜ ለነዋሪዋና ለኢህአዴግ ይሁንና፡፡)
v  በ19ኛዉ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ ድልድይ የተሠራዉ በእንጨት ሲሆን የሰጠዉም ጥቅም አጭር ነዉ፡፡እንዲሁም የመጀመሪያዉ የድንጋይ ድልድይ የተሠራዉ በ1902 በራሺያዉ ኢንጅነር ሲሆን ኢንጅነሩም ድልድዩን የሠራዉ አንድ ጓዳቸዉን የቀበና ወንዝ ስለወሰደዉ በዚህ ሳቢያ በምኒልክ ሆሲፒታልና በራሺያ ቆንስል መካከል በሚገኘዉ የቀበና ወንዝ ላይ የድንጋይ ድልድይ ተሠራ፡፡ (የቀበና ድልድይ አንድ የዉጭ ዜጋ ስለወሰደ መሰራቱን እንስማ እንጂ ስንቱን ኢትዮጵያዊ እንደወሰደና ዝም እንደተባለ ልብ ልንለዉ ይገባል፡፡) ሁለተኛዉ የድንጋይ ድልድይ የራስ መኮንን ድልድይ ሲሆን የመጠሪያ ስያሜ ያገኘዉ ከተሠራበት ጊዜ አንስቶ ነዉ፡፡
v  በአዲስ አበባ ሁለት ወይም ሶስት የሚሆኑ የእህል ወፍጮዎች በመቋቋማቸዉ በምግብ አዘገጃጀት ለዉጥ ሊያስከትል ችሏል፡፡(እነዚህም ወፍጮዎች አንዱ ወይም ሁለቱ በግሪኮች ሲተከሉ አንደኛዉ የእህል ወፍጮ ግን የተተከለዉ በምኒልክ ነዉ፡፡ ይህ ወፍጮ የተተከለዉ ከቤተመንግሥቱ አካባቢ ሲሆን የቤተመንግሥቱ ሰዎችና አለቆች እንዲሁም የአከባቢዉ ኅብረተሰብም ይጠቀምበት ነበር፡፡ በእኔ ዕድሜ እንኳን በሶስት አስርት አመታትና ከዚያ ቀደም ዛሬንም ጨምሮ አብዛኛዉ የአገራችን ገጠራማ ክፍል የሃብት መገለጫዉ ወፍጮ ቤት መትከል ነበር፤ አሁንም በብዙ ቦታ ዋና ከተማዋን ጨምሮ በእህል ወፍጮ እጦት ሲቸገሩ ይስተዋላል፡፡)v  ይስተዋላል፡፡)/ አጼ ምኒልክ የአዉሮፓዉያን ሥልጣኔ ወደ ሀገራችን ለማስገባት ጥረት ባደረጉ ቁጥር እንቅፋት ይገጥማቸዉ ነበር፡፡ የእህል ወፍጮ ባስገቡ ጊዜም ተመሳሳይ ተቃዉሞ በሕዝቡ ዘንድ ደርሶባቸዋል፡፡ ‹‹ የሠይጣን ሥራ ነዉ፡፡ ሰይጣን ነዉ የሚፈጨዉ ›› እያሉ፤ ሕዝቡ በዚህ የእህል ወፍጮ አላስፈጭም ብሎ ቢያስቸግራቸዉ፤ አጼ ምኒልክ ከቤተመንግስት እህል አስመጥተዉ ራሳቸዉ እዚያዉ ቆመዉ አስፈጭተዉ ወደ ቤተ መንግሥት ይዘዉ በመሔድ በሕዝቡ ዘንድ ያለዉን ኋላ ቀር አስተሳሰብ አስወግደዋል፡፡ ይሉናል ከዋቀዮ ታችበሌ የተገኙት መረጃዎች፤ ምንም እንኳን አዲስ አበባ ዛሬ እንዲህ አሸብርቃ ደምቃ ብናያትም ዛሬ ድረስ ህዝቦቿ ጥሎባቸዉ አዲስ ነገር ለመቀበል ዝግጁ አለመሆናቸዉን ብዙ ማሳያዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ የጋራ መኖሪያ ቤት ወደ አገራች ሲገባ ‹‹አይረባም›› ከማለት ጀምሮ ብዙ ነገሮች ተወርተዋል ዛሬ እንዲህ ተሰልፈዉ ሊመዘገቡና ሳልሞት አሳየኝ እያሉ እድሜ ከፈጣሪ እየለመኑ ሊጠብቁ ፣ ሃይገር የተሰኘዉ መካከለኛ የትራንስፖርት ሰጪ መኪና ሲመጣ፣ ባጃጅ፣ ቢሾፍቱ የከተማ አዉቶቡስ፣አቶዝ  … ሥራ ሲጀምሩ አይረቡም ህዝቡን ሊፈጁት ነዉ ሲባል ነበር፤ አሁንም የማያምን ትዉልድ የቀላል ባቡር ፕሮጀክት ሲጀመር፣ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሲበሰር ከግብፅ እኩል የተቃወሙ ብዞዎች ነበሩ ይህ የሚያሳየዉ በሚኒልክ የሥልጣን ዘመን ብቻ ሳይሆን ያጋጠመዉ አሁን ባሉትም መሪዎች ያጋጠመ ያለመሰልጠን አባዜ ነዉ፡፡  /
v  በዚሁ ዘመን የዳቦ መጋገሪያ ማሽን የገባበትም ዘመን ነበር፤
v  በ1914 ዘመናዊ ልኳንዳ ቤትም በአዲስ አበባ ሊታይ ችሏል፤
v  ስለ መጠጥ ቤቶች ያነሳን እንደሆነ (ምግብ ቤቱ አንድ ሆኖ ሳለ እቴጌ ሆቴል እሱንም የሚመገቡበት የዉጭ ዜጎችና የወቅቱ ሹማምንት ነበሩ፤) ዕድገቱ በጣም ፈጣን ነበር፡፡ለዚህም እንደማሳያነት በ1908 ሃምሳ የነበሩት መጠት ቤቶች በ1913 ወደ 100 ከፍ ብለዋል፤ እንዲሁም በ1922 ወደ አንድ ሺህ አከባቢ ዕድገት አሳይቷል፡፡(በዚህ ወቅት የነበሩ መጠጥ ቤቶች የሚሸጡት ጠጅ ብቻ ሳይሆን ጠላና አረቄ ወይም የግሪክ ባራንዲም ነበር፡፡) በግሪክ የአልኮል መጠጥ ስልጣኔ ወደ አገራጋችን የገባዉ ጠጭነት ዛሬ ድረስ አዲስ አበባን ሰካራም ከማድረጉ አልፎ ብዙ ቤቶች ለአልኮል መጠጥ መሸጫነት ስራቸዉን ፈተዋል፤ ነዋሪዉም ከምግቡ ቀጥሎ ሰርቶ የሚገባዉ ለመጠጥ ሆኗል፤ አዲስ አበባ!
v  የሰዉ ልጅ የስልጣኔዉ መገለጫ ልብስ መልበሱ ነዉና የአሜሪካዉ የልብስ ስፌት መኪና ሲንጀር ካምፓኒ ወደ አገራችን የገባዉም በ1909 ነበር የመኪናዉም መሸጫ ዋጋ 150 ብር ስለነበረ በትንሽ ጊዜ ዉስጥ ብቻ በመቶ የሚቆጠሩ የልብስ ስፌት መኮኖች ወደ አገራችን ገቡ፡፡የልብስ ስፌት ባለሞያዎች ወደ አገራችን ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡

በክፍል ሶስት ይጠብቁን! የፀየሙ ገጾች

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...