ሰኞ 5 ሜይ 2014

I forget my English ደብተር

ወቅቱ በኛ ዘመን ነዉ ‹የኛን ዘመን› እንግዲህ ቆጥራችሁ ድረሱበት፤ ፍንጭ ለመስጠት ያክል ዛሬ የአማሪኛ ቋንቋን ከብሔሩ ተወላጅ ዉጭ ያሉ ተማሪዎች ‹‹ አማርኛ ›› ብሎ ከመጥራት በስተቀር መናገር እንደተጠመደ ፈንጂ በሚታይበት ሁኔታ እንዳለ ሁሉ እኛም እንግሊዝኛን ከA (ኤ) እስከ Z (ዜድ) ብቻ በሚመስለን ዘመን እንደማለት ነዉ፡፡ የቋንቋ ነገር ከተነሳ አይቀር አንድ ጓደኛዬ እዚሁ መዲናችን አዲስ አበባ ዉስጥ በሚገኝ የግል ባንክ አንድ ዘመዷ ተቀጥራ ለዋስትና ስትሄድ ወደ ህንፃዉ እንደገባች የህንፃዉ ትልቅነት ግራ ስላጋባት መረጃ ትፈልግና አንዷን የባንኩ ሰራተኛ መረጃ ትጠይቃታለች ባነከሯም (የባንኩ ሰራተኛ) በአማርኛ ቋንቋ ለጠየቀቻት ጓደኛዬ አማርኛ እንደማትችል ትመልስላታለች፡፡ ጓደኛዬም የምትሰማዉ ነገር ግራ ይገባትና ‹‹ እንዴት ነዉ የማትችይዉ?›› ብላ ትጠጥቃታለች፡፡
‹‹ በቃ አልችልማ ›› ብላ ግግም ያለ ምላሽ ትሰጣታለች፤
‹‹ እያናገርሽኝ ያለዉኮ በአማርኛ ነዉ ታድያ ይሄንን እንዴት ቻልሽ ወይስ መረጃ መስጠት በአማርኛ መስጠት አትችይም? ›› ትላታለች ፤
የባንክ ባለሙያዋም ‹‹ በቃ ተሳስቼ ነዉ››  ትልና አሁንም በአማርኛ ትመልስላታለች፤
እንግዲህ እንዲህ ቋንቋዉን እየቻሉ መናገር ለሚጠሉት ቋንቋ ‹መግባቢያ› ሳይሆን መዋጊያ የጦር መሳሪያ እየሆነባቸዉ ያለበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነዉ ያለዉ፡፡ (እግረ መንገዳችንንም የግድ እስካልሆነ ድረስ እንዲህ ዘርና ቋንቋ እየመረጡ የሚቀጥሩ መስሪያ ቤቶች ከአካሄዳቸዉ ቢመለሱ የሚሻል ይመስለኛል፤ መልዕክቴ ነዉ፡፡ )

ከዚህ ወጣ ስንል ደግሞ በአገራችን በኢትዮጵያ ይልቁንም በመዲናችን በአዲስ አበባ አብዛኛዉ የንግድ ስያሜ፣ ምግብ ቤቶች፣ የተለያዩ መገበያያ ስፍራዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣የተለያዩ ተቋማት ፈራቸዉን እየለቀቁ ስያሜያቸዉ ሁሉ ባህላቸዉን ጨምሮ አገርኛነቱን ለቆት ይገኛል፤ አዉሮፓ ያለን እስኪመስለን ድረስ መልኩ ተቀይሯል ሃይ የሚላቸዉ ጠፍቷል፡፡
ትምህርት ቤቶች በአጠቃላይ የሚያስተምሩት ወይም ለማስተማርም የተዘጋጁት የባእዳንን ቋንቋ እና ባህል ነዉ፤ ይህ ደግሞ ዛሬ በጥቂቱ እያየን ያለነዉ ችግር ነገ ትልቅ የአገር ችግር ይሆናል፡፡ አገርም ተረካቤቢ ታጣለች ማለት ነዉ፤ የአገር ዉስጡ አልበቃ ብሏቸዉ ዉጭ በመላክ ቻይናና የተለያዩ አዉሮፓ እና አሜሪካ አገራት ልጆቻቸዉን የሚያስተምሩ ባለስልጣናት እና ባለሐብቶች ጥቂት አይደሉም፡፡ኢትዮጵያዊ ማንነት የሌላቸዉ ተተኪ ትዉልድ ዉጭ የሚሰለጥን አያስፈልግም ባንልም እንዲህ በአገር ሳይኮሩ ነገ ምን አይተዉ አገር ይረከባሉ፡፡
እዚሁ አገራችን ከሚማሩት አገር ተረካቢ ልጆቻችን መካከልም አብዛኛዉ የመንግስት ትምህርት ቤት ልጃቸዉን ማስተማር የማይፈልጉ እና የመንግስት ትምህርት ቤትን የሚያወግዙ ጥቂት የማይባሉ ናቸዉ፡፡ ነገር ግን የትምህርት ፖሊሲዉን የቀረፁት ራሳቸዉ ናቸዉ ሆኖም አላመኑበትም፡፡ ምንም እንኳን የመንግስት ትምህርት ቤት ይህን ያህል ለማስተማር ባያስመኝም ካለዉ የግል ትምህርት ቤት የተጨማለቀ አገርን፣ ባህልን፣ማነነትን …ወዘተ የሚያስዘነጋ ድርጊት ሳይሻል አይቀርም፡፡ በዚህ ተስቦ የተለከፈች አንድ ጓደኛዬ ልጆቿን ከምታስተምርበት ትምህርት ቤት ያጋጠማትን ነገር ስትነግረኝ አንዱ እናቱ አረብ አገር ከሄደች በኋላ ልጄ የተሻለ ትምህርት ቤት ገብቶ ይማርልኝ ያለች እናት ልጇን ቤተሰቦቿ ከመንግስት ትምህርት ቤት አቋርጦ የግል ትምህርት ቤት እንዲገባ ያደርጉላታል፡፡ ልጅም እንደተባለዉ ያደርጋል፤ ትምህርቱን ይቀጥላል በግል ትምህርት ቤት ማለት ነዉ፡ ከእለታት አንድ ቀን ደብተሩን ረስቶ ይመጣል፡፡
 መምህርቷ ደብተሩን ለምን ጥሎ እንደመጣ ትጠይቀዋለች እርሱም ረስቶ እንደመጣ በአማርኛ ይመልሳል፤ መምህርት በእንግሊዝኛ እንዲመልስላቸዉ ግድ ይሉታል፡፡ እሱ እንግሊዝኛን የተማረዉ ለዚያዉም ቋንቋዉን ባግባቡ ባልተማሩ መምህራን በእንግሊዝኛ ክፍለ ጊዜ ነበረና እየተጨናነቀ የእንግሊዝኛ ቃላት እየለቃቀመ  ‹‹ I forget my English ደብተር ›› በማለት የሞት ሞቱን ይመልሳል፡፡ የክፍሉ ተማሪ በጠቅላላ ‹‹ ደብተር›› በሚለዉ በአነጋገሩ ይስቁበታል፤ በዚህ ብቻ አላበቃም ለዚህ እንግዳ ልጅ የመምህሯ ዱላ ተከተለዉ ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ክፍለ ጊዜዉ እስኪጠናቀቅ ድረስ ተማሪዉ ትምህርቱን መከታተል አልቻለም ነበር፡፡ ይህንን ዘግናኝ ታሪክ ጓደኛዬ ልጇ እቤት እንደገባች እየሳቀች እንደነገረቻት ነገረችኝ፡፡ በጣም ነበር የዘገነነኝ ፤ ያጫወተችኝ ይህ ብቻ አልነበረም ፡-
 የወላጆች ስብሰባ ተብሎ በየሶስት ወሩ ይሰበሰባሉ የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብና ወላጅ በአንድ አዳራሽ ተሰብስበዉ ሪፖርት ይቀርባል፡፡ … ብዙ ነገር ከተወራ በኋላ ለወላጆች ‹‹ ልጆቻችሁን አማርኛ አስጠኗቸዉ … በዚህ ዓመት ሁሉም ተማሪ በጣም ዝቅተኛ ዉጤት ስላመጡ ትምህርት ቤቱን ሊያስወቅሱት አይገባም … ›› ይባሉና ወላጅ ማስጠንቀቂያ ይሁን ማሳሰቢያ ይሰጠዋል፡፡ ብዙ ክርክሮች ይደረጉና ትምህርት ቤቱን ‹‹አማርኛን በአግባቡ ስለማያስተምር ነዉ …››፣                  ‹‹ በእንግሊዝኛ ብቻ እንዲያወሩ ስለምታደርጉ ነዉ…›› ወዘተ የሚል አስተያየት ለትምህርት ቤቱ ይሰጠዋል፤ …. እነሱም በፍፁም ብለዉ ሽምጥጥ አርገዉ ይክዳሉ፡፡ እንግዲህ የትምህርት ጥራታችን ምን ይመስላል? ካልን ትምህርቱ ቋንቋ ብቻ እየሆነ መጥቷል፤ መንግስትም ፈቃድ ከመስጠት ዉጭ ለድርጊቱ አፋጣኝ መፍትሔ ሲሰጥ አይታይም፡፡ መጨረሻችን ምን ይሆን?
ይህም ዘመን ጥሩ አይደለም የኛም ዘመን የድንቁርና ዘመን ጥሩ አይደለምና እንደሚሆን አርጉት አንድ በእኛ የትምህርት ዘመን በእዉነት የተደረገ እንድ ቀልድ የሚወራ ነገር ልንገራችሁና ላብቃ ‹‹ መምህሩ በቋንቋ ክፍል ጊዜ ክፍል ገብተዉ ያስተምራሉ ተማሪዉም በጸጥታ ሲያዳምጣቸዉ ይቆይና እሳቸዉም የሚያሳትፍ ትምህርት ለተማሪዉ ማስተማር ይጀምራሉ፤ ተማሪዎቹን የቢላ ምስል እያሳዩ Knife (ክናይፍ) እያሉ ያስጠናሉ ሁሉም ክናይፍ እያለ ይከተላቸዋል፡፡ አንድ ተማሪ ብቻ ‹‹ ናይፍ ›› ይላል ድምፁን ከፍ አድርጎ መምህሩ ከተማሪዉ መሃል ማንነቱን ያጣሩና ይደርሱበታል፡፡ በትራቸዉን እንደያዙ ለብቻዉ ‹‹ ክናይፍ ›› በል ይሉታል፤ እሱም ናይፍ ብሎ ይመልስላቸዋል፡፡ መመህሩ ‹‹ የመምህሩን ትዕዛዝ አልተቀበልክም›› በሚል ዉጣ ይሉታል፡፡ ተማሪዉ ምን ‹‹አጠፋሁና ነዉ የምወጣዉ?›› ብሎ መምህሩን ማብራሪያ ይጠይቃል፤ የዛሬ ልጅ ቢሆን የሚመልሰዉን እያሰባችሁ ፡፡ እሱም ምንም አላጠፋሁም ጥራ አሉኝ በትክክለኛ ስሙ ጠራሁት ጥፋት የለብኝም ይላቸዋል፤ መምህሩ እንግዲያዉስ የማትወጣ ከሆነ ይሉና የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ጋር ይከሱታል፡፡
ርዕሰ መምህሩም ክሱን ያዳምጡና ተማሪዉን አስጠርተዉ ይጠይቁታል የሆነዉን ነገር ሳይዋሽ ይነግራቸዋል፡፡ መምህሩም ግራ ቀኙን አዳምጠዉ ፍርድ ሲሰጡ እንዲህ ነበር ያሉት Both of you are wrong (ቦዝ ኦፍ ዩ አር ወሮንግ) ብለዉ አሰናበቷቸዉ ይባላል፡፡ ታዲያ ይህ ትዉልድ ከማን ይማር?
የትምህርት ፖሊሲዉ ችግር አለበት፣ መምህሩ ችግር አለበት፣ ተማሪዉ ችግር አለበት፣ ባለሐብቱ ትምህርት ቤት ሲከፍት ችግር አለበት፣ የትምህርት አሰጣጡ ዓላማ ችግር አለበት፣ … ምን ይሻለናል? ለቋንቋ ያለን አመለካከት ለባህላችን ለሃይማኖታችን ካለን አመለካከት እጥፍ ድርብ ጊዜ በልጧል፡፡

ቋንቋ ማወቅ አላስፈላጊ ነዉ እያልኩ አይደልም፤ የሌላ አገር ቋንቋ አያስፈልግም እያልኩም አይደለም፡፡ ነገር ግን የኛን ሆነ የሌላዉን አገር ቋንቋ እንግባባበት እንጂ አናምልከዉ ሌላ አመለካከትም አንስጠዉ አንከፋፈልበት ፍቅር የሌለዉ ቋንቋ ፣ ተንኮል የተሞላበት ቋንቋ ከማግባባት ይልቅ ይለያያልና፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...