ሆሳዕና በዓብይ ፆም ሰባተኛዉ ሳምንት ሲሆን ሆሳዕና ማለት የመጽሐፍ
ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንዳስቀመጠዉ ‹‹አሁን አድን›› ማለት ነዉ፡፡ስለሆሳዕና ከወንጌላዉያን ከሉቃስ በቀር ሶስቱም ወንጌላዉያን
ፅፈዉ እናገኘዋለን፤ ማቴዎስ 21 ቁጥር 9-15፤ማርቆስ 11 ቁጥር 9 እና ዮሐንስ 12 ቁጥር 13 ናቸዉ፡፡
የእስራኤል ሕዝብ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘዉ ‹‹ሆሣዕና›› በማለት እየጮሁ
ኢየሱስን ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ አጅበዉ ተቀብለዉት ነበር፡፡ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ሊገባ ከኢየሩሳሌም አቅራቢያ ሲደርስ ከደቀ
መዛሙርቱ ሁለቱን ከፊት ለፊታቸዉ ከምትገኝ መንደር ልኮ አህያ እና ዉርንጫ ከታሰረችበት ፈተዉ ይዘዉለት እንዲመጡ አዘዛቸዉ፡፡ አህያይቱን
ይዘዉለት በመጡ ጊዜ ‹‹እነሆ ንጉስሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በዉርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል
›› ትንቢተ ዘካርያስ 9 ቁጥር 9 እንደተባለዉ በአህያይቱ ጀርባ ላይ በመሆን ወደ ከተማይቱ ገባ፡፡
ኢየሱስ ወደ ከተማዉ ሲገባ (ከኢየሩሳሌም ቤተመቅደስ ድረስ አስራ ስድስት
ምዕራፍ ተጉዟል፤ አስራ አራቱን በእግሩ ሲጓዝ ሁለቱን ምዕራፍ ግን በሁለቱ አህያ ጀርባ ላይ በጥበብ በአንድነት ተቀምጦ ሄደ፡፡)
ህዝቡ ልብሱን ከአህያዉ ጀርባ ላይ አድርጎለት እና እንኳንስ አንተ የተቀመጥክባት አህያ መሬት መርገጥ የለባትም ብለዉ የዛፍ ዝንጣፊ
በየመንገዱ እያነጠፉ ተቀበሉት፤(የዛፍ ቅጠል አይደለም የሰሌን ዝንጣፊ ነዉ ቢሉ አብርሃም ይስሐቅን፣ይስሐቅም ያዕቆብን፣በወለዱ ጊዜ
እስራኤል ከግብፅ በወጡ ጊዜ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘዉ አመስግነዋልና እስራኤላዉያንም ሆሳዕና በአርያም እያሉ በነሱ ልማድ የዘንባባ
ዝንጣፊ ይዘዉ አመስግነዉታል፡፡ ስለምን በሰሌን ቅጠል/ዘንባባ ይዘዉ አመሰገኑት ቢሉ ዘንባባ እሳት አይበላዉም ለብልቦ ብቻ ይተወዋልና
አንተም ባህሪህ ረቂቅ የማይመረመር ነዉ ሲሉት ነዉ፤ ) ወደ ኢየሩሳሌምም በገባ ጊዜ ህዝቡ ‹‹ይህ ማን ነዉ?›› እያሉ ሲጠይቁ
ነበር፡፡ ገሚሲቹም የፊቱን ወዝ አይተዉ ‹‹ነቢይ ነዉ›› ሲሉም ተደምጠዋል፤ … ኢየሱስም ወደ ከተማዉ ከገባ በኃላ ወደ ቤተመቅደስ
ነበር ያመራዉ፡፡(በአህያ ጀርባ ላይ ሆኖ ቤተመቅደስን ሶስቴ ዞሮዋል፤)‹‹ … ወደ መቅደስ ገባና (ብሩን ለወርቅ ወርቁን ለብር
የሚለዉጡበትን ሥፍራቸዉን አፈረሰባቸዉ፤ በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አወጣ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጮችንም
ገበታዎች የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠና ቤቴ የፀሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎአልና እናንተ ግን የወንበዴዎች ጋሻ የሌባ
ዋሻ አደረጋችኋት›› አላቸዉ፡፡ ገበያ የተሠረቀዉን የተቀማዉን ይሸጡበታልና እንዲህ አለ፡፡
( በዚህ ጊዜ የተፈፀመዉ ምሥጢራት በቤተክርስቲያን አባቶች ሲነገር አስራ ስድስቱ ምዕራፍ አስሩ
የአስርቱ ቃላት፣ አራቱ የኪዳንት ሲሆን እነሱም፡- ኪዳነ ኖኅ፣ክህነተ መለከ ጼዴቅ፣ ግዝረተ አብርሃም እና ጥምቀተ ዮሐንስ ናቸዉ፡፡
ሶስቴ ቤተመቅደስን መዞሩ የስላሴ ሶስትነት ምሳሌ ነዉ፡፡ )
በመቅደስ ቆይታዉ ዓይነ ሥዉራንንም ፈዉሷቸዉ ነበር፤ … ህጻናትም
‹‹ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ›› እያሉ አመሰገኑት፡ አመሻሽ ላይም ትቷቸዉ ቢታንያ ሄዶ አደረ፡፡
ኢየሩሳሌም፡-
ከባህር ወለል በላይ 750 ሜትር ገዳም ከፍ ብላ የምትገኝ ከተማ ናት፤ የስሟ ትርጓሜ ‹‹የሰላም ከተማ›› ማለት ነዉ፡፡
የእስራኤል ህዝብ፡-
አስራ ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች ቤተሰብ ናቸዉ፤እስራኤል ማለት ያዕቆብ ማለት ነዉና ህዝቡ በሱ ስም ይጠራል፡፡
በአህያ ላይ መቀመጡ፡- ትንቢቱ ይፈፀም ዘንድ ነዉ፤ምሳሌዉ ቀድሞ አባቶች ነቢያት ዘመነ ጸብዕ/መጥፎ የሆነ እንደሆነ በፈረስ ተቀምጠዉ፡ ዘመኑ
የሰላም የሆነ እንደሆነ ደግሞ በአህያ ተቀምጠዉ መነሳንስ ይዘዉ ይታዩ ነበርና የሰላም ዘመን ዘመነ ምህረት መጥቷል ሲል በአህያ
ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ ጌታ ራሱ ሰላም ሆኖ ሳለ እንደምን በአህያ ላይ ተቀምጦ መጣ ቢሉ ምሥጢሩ ባህያ የተቀመጠ ሸሽቶ
አያመልጥም አሳዶም አይዝምና፤ እሱም ካልፈለጉኝ አልገኝም ከፈለጉኝ አልታጣም ሲል ነዉ በአህያ ላይ ተቀምጦ መምጣቱ፡፡ አንድም ነቢያት
ደመና እየጠቀሱ፣ በእሳት ሰረገላ፣ በመርከብ ሲጓዙ ታናሽ በሆነች በአህያ ተቀምጦ መምጣቱስ እንደምን ነዉ ቢሉ ንጹሐን በሆኑ ታናናሾች
አድሬባቸዉ ኖራለሁ ሲል ነዉ፡፡
የሁለቱ አህያ ምሳሌነት ደግሞ ትልቋ ሸክም የለመደች የምትጫን ስትሆን
ትንሿ ደግሞ ሸክም ያለመደች መሆኗ ትልቋ ህግን መሸከም የለመዱ የእስራኤል ምሳሌ፣ ትንሿ መሸክም ያልጀመረችዉ ደግሞ የአህዛብ ምሳሌ
ነች፡፡ አህዛብ ሕግ መጠበቅ ያልለመዱ ናቸዉና፡፡ አንድም ትልቋ መሸከም የለመደችዉ የኦሪት መተግበር የተለመደዉ የሕገ ኦሪት ምሳሌ
ሲሆን ትንሿ ደግሞ መሸከም ያልመድችዋ መተግበር ያልተለመደዉ የአዲስ ኪዳን ሕግ ምሳሌ ናት፤
የአህያ ከእስር መፈታት፡- ሰዉ ሁሉ ከማዕሰረ ሃጥያት ተፈተዉ መምጣታቸዉን ለማጠየቅ የተደረገ ምሥጢር ነዉ፤ እስራኤል ዘነፍስ የተባልን እኛን ከሃጥያት ቁራኝነት ሊፈታን በአህያ ዉርንጫ ላይ ተቀምጦ መጣ፡፡
ልብሳቸዉን ከአህያዋ ጀርባ ላይ ማድረጋቸዉ፡- ኮርቻ ስለሚቆረቁር ጨርቅ/ልብስ አይቆረቁርምና የማትቆረቁር ህግ ልሰራላችሁ መጣሁ ሲል ነዉ፤ አንድም ልብስ የሰዉነትን
ነዉር እንዲሰዉር አንተም ከባቴ አበሳ ነዉራችንን የምትሰዉር ነህ ሲሉ ልብሳቸዉ አነጠፉለት፡፡
ሆሳዕና በአርያም ለዳዊት ልጅ እያልን እናመሰግንሃለን፤ ለክብርህ ይሆን
ዘንድ ልብሳችንን አዉልቀን እናነጥፋለን … ዘንባባ ይዘንም እንቀበልሃለን፡፡አበሳችንን ልትደመስስ ራስህን ዝቅ አድርገህ የመጣህልን
ልዑለ ባሕሪ እግዚአብሔር ሆይ ክብር ምስጋና ላንተ ይሁን! በቤተመቅደስ ተገኝተህ ቤትህን ከሌቦች ዋሻነት እንዳፀዳኸዉ እንዲሁ ዛሬም
በቤትህ ተገኝተህ ሌቦችን ከቤተመቅደስ አስወጣልን፡፡ በስምህ እየነገዱ በስምህ ጥቅም የሚያጋብሱትን፣ ከአስመሳይ አገልጋዮች ሰዉረን
፣ ቃልህን ባስተማሩ በአጸፋዉ ገንዘብ የሚጠይቁትን ቃልህን ከመዳኛነት
ወደ ገንዘብ ማጋበሻነት የቀየሩትን አስታግስልን፡፡ ስምህን መነገጃ ያደረጉትን ስመ አምላክ ነጋድያንን ልብ ስጣቸዉ፤ ከተያዝንበት
የሃጥያት ቁራኝነት ፍታን፣የአህያይቱን ትንሽነት ሳትንቅ በጀርባዋ ተቀምጠህ ወደ ቤተመቅደስ እንደገባህ አሁንም ጌታ ሆይ በሃጥያት
መተዳደፉችንን ተመልክተህ ሳትንቀን በልባችን ንገስበት፣ ህጻናት እና ድንጋይ እንዲያመሰግኑህ የፈቀድክ ለምስጋና አንቃን፣ እንድናመሰግንህ
ፍቅርህን በልቦናችን ምስጋናህን በአንደበታችን አሳድርብን፡፡
ሆሳዕና በአርያም! ጌታ ሆይ አሁን አድነን! ጌታ ሆይ ጤናችንን አሁን
መልስልን!
አሜን! ቃለ ሕይወትን ያሰማልን።
ምላሽ ይስጡሰርዝ