ሰኞ 18 ኦገስት 2014

"በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነዉ፤"



ደብረ ታቦር ከገሊላ ባህር በምዕራብ ደቡብ በኩል አስር ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ተራራ ሲሆን ከባህር ጠለል በላይ ከፍታዉ 572 ሜትር ነዉ፡፡
ደብረ ታቦር፡-
1.     ባራቅ ሲሳራን ያሸነፈበት ተራራ ነዉ፡፡ መሳፍንት 4፡6-14
2.    ሳኦል እንደ ሳሙኤል ትንቢት ከሶስት ሰዎች ጋር የተነጋገረበት ነዉ፡፡ 1ኛ ሳሙኤል 10፡3
3.    ደብረ ታቦር በዛብሎን ዕጣ ያለ ለጨራራ ልጆች የተሰጠ ቦታ ነዉ፡፡ 1ኛ ዜና መዋዕል 6፡77
4.    ጌታችን ክብረ መለኮቱን የገለጠበት ቦታ ነዉ፡፡ ማቴዎስ 17፡1-8
ጌታ በማንኛዉም ቦታ ክብረ መለኮቱን መግለፁን ትቶ ደብረ ታቦርን ለምን መረጠ?
አንድም ትንቢቱ ይፈፀም ዘንድ
" ሰማያት ያንተ ናቸዉ ምድርም የአንተ ናት አለምንና ሞላዋን አንተ መሰረትክ ሰሜንና ደቡብን አንተ ፈጠርክ ታቦርና አርሞን በስምህ ደስ ይላቸዋል፡፡" መዝሙር 88፡11-12 የተባለዉ ይፈፀም ዘንድ ነዉ፡፡ ከሌሎች ተራሮች ሁሉ ደብረ ታቦርን የመረጠዉ ሌላዉም ተራራ ከመሬት እንዲርቅ የመለኮትም ምሥጢር ከሰዉ የራቀ የጠለቀ መሆኑን ለማጠየቅ ነዉ፡፡
ሌላዉ፡-

ተራራ የወንጌል ምሳሌ ናት፡፡ ተራራ ሲወጡት ያስቸግራል ከወጡት በኋላ ግን ሁሉን ያሳያል፡፡ ወንጌልም ሲማሯት ታስቸግራለች፤ ከተማሯት በኋላ ግን ፅድቅንና ኋጢያትን ለይታ ስታሳዉቅ ደስ ታሰኛለች፡፡
ተራራ፡- የመንግስተ ሰማያት ምሳሌ ናት፡፡ ተራራን በብዙ ድካምና ጣር እንደሚወጧት ከወጡበት በኋላ ግን ሁሉን ነገር ከእርሷ ላይ ሆኖ ሲያዩ ደስ እንደሚል መንግሥተ ሰማያትንም በብዙ መከራ ያገኛታል፤ ከተገኘች በኋላ ግን ደስታዋ እጥፍ ድርብ ነዉና፡፡
እግዚአብሔር ለሙሴ ሕጉን የሰጠዉና ያስተማረዉ በሲና ተራራ ነበር፤
ለሐዋርያት ሥለምፅአት ያስተማራቸዉ በደብረ ዘይት ተራራ ነበር፤
ወደ ሰማያትም ያረገዉ ከዚያዉ ነዉ(ከቢታንያ መሃል ከተማ ነዉ፡፡)
ሌሊት ሌሊት ሲፀልይ የነበረዉ በደብረ ዘይት ተራራ ነበር፤
አንድም ተራራ የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናትና ቤተክርስቲያን የሰማይቱ ኢየሩሳሌም የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ በመሆኗ ነዉ፡፡
ከሐዋርያት መካከል ለምን ጴጥሮስ፣ዮሐንስ እና ያዕቆብ ብቻ ተመረጡ?
ጴጥሮስ ዮሐንስንና ያዕቆብን ብቻ መምረጡ ክህደትም ሆነ የእርሱ ፍቅር በእነዚህ ፀንቶ ስለተገኘ ነዉ፡፡
ጴጥሮስ፡- ጌታ ሞቱን በፀሎት ሐሙስ ቢነግረዉ ጰጥሮስ የጌታ ፍቅር አስገድዶት (ሳስቶለት ጌታ ሆይ አትሙት በአንተ ፈንታ እኔ ልሙት ቢለዉም በሌላ በኩል ሹመት ሽልማት ሽቶ ነበርና ነዉ፡፡ እርሱ ክብሩ ሰማያዊ እንጂ ምድራዊ እንዳይደለ ለማሳወቅ ነዉ፡፡ ማቴዎስ 16፡22 )
ያዕቆብ እና ዮሐንስም፡-በእናታቸዉ አማካይነት በግራ እና በቀኝ እንዲሾማቸዉ ማለትም ጌታ በነገሰ ጊዜ አንዱ ቀኝ አዝማች አንዱ ግራ አዝማች እንዲሆኑ እናታቸዉ ጌታን ለምናላቸዉ ነበርና እርሱ ግን የምድራዊ ንጉስ ሳይሆን ሰማያዊ ንጉስ መሆኑን እንዲያዉቁ ነዉ፡፡
ሌሎቹን ሐዋርያት ትቶ ዮሐንስ ያዕቆብንና ጴጥሮስን ይዞ ወደተራራ ለምን ወጣ?
ለይሁዳ ፡- ሃጥያተኛ ጌታዉን የሚሸጥ ቃልኪዳንን ያፈረሰ ከሃዲ በመሆኑ ኋጥእ ሰዉ የእግዚአብሔርን ክብር አያይም (ኢሳይያስ 26፡10) ተብሎ ትንቢት ተነግሮለታልና ስለዚህ ይሁዳ ኋጢያተኛ በመሆኑ የእግዚአብሔርን ክብር እንዳያይ ነዉ፡፡
ለይቶ ይሁዳን ብቻ ትቶ ሌሎቹን ሐዋርያት እንዳይወስድ በዚህ ምክንያት ይሁዳ የመሸጡን ምክንያት ምሥጢረ መንግሥቱን ቢለየኝ አሳልፌ ለሞት ሰጠሁት የሚል ምክንያት እንዳይፈጥር ነዉ፡፡ ይሁን እንጂ ለዮሐንስ ለያዕቆብ እና ለጴጥሮስ በደብረታቦር የተገለፀዉ ምሥጢር ( ክብረ መለኮት ) በመንፈስ ተገልፆላቸዋል፡፡
ጌታችን ሥጋን ተዋህዶ በገዘፈዉ ነገር ቢታያቸዉ ብዙዎች የገዘፈዉን እንጂ የረቀቀዉን ምሥጢር ማስተዋል ተስኖአቸዉ እርሱ አምላክ መሆኑን ማወቅ ተስኖአቸዉ ነበር፡፡ ለሐዋርያትም እያዩ እንደ ዳሰሱት አብረዉት እየዋሉ እያደሩ ቢያስተምራቸዉም እርሱ ግን የስጋና የነፍስ ፈጣሪ አምላካቸዉ መሆኑን ያዉቁ ይረዱ ዘንድ ነዉ፡፡
ወደ ደብረ ታቦር ተራራ ከወጣ በኋላ ፡-
ጌታችንና መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ተቀደሰችዉ ስፍራ ወደ ታቦር ተራራ ከወጣ ጊዜ (በኋላ) በተከተሉትና በታቦር ተራራ አብረዉት በተገኙት ደቀመዛሙርት ( ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስ) በፊታቸዉ ባለዉ ብርሃናዊ መለኮት በእሳታዊ ወላፈን ብርሃንን ለብሶ ፣ ተጎናፅፎ ተለወጠባቸዉ፡፡ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ እንደምነዉ ቢሉ እሳተ መለኮት (መለኮትን የተዋሐደ) ሰዉ ነበርና፡፡ ልብሱም ከወተት የነጣ ብርሃናዊ ነጭ ሆነ፡፡ እንደምነዉ ቢሉ ንፁህ ባህርይ ነዉ፡፡
ራዕይ 1፡14 "ራሱና የራሱ ጠጉርም እንደ ነጭ የበግ ጠጉር እንደ በረድም ነጭ ነበሩ፤ አይኖቹም እሳት ነበልባል ነበሩ …"  
ማቴዎስ 17፡2 " በፊታቸዉም ተለወጠ ፊቱም እንደ ፀሐይ ይበራ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ፡፡ እነሆም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸዉ፡፡"
ይህ ታሪክ በሚፈፀምበት ሰዓት ከሰማይ የአብ ቃል በነጎድጓድ ሲሰማ ሁሉም ደነገጡ በተጨማሪም እግዚአብሔር እኔን ማን ትሉኛላችሁ? ባላቸዉ ሰዓት አንተ ሙሴ ነህ አንተ ኤልያስ ነህ ብለዉ ሲናገሩ የነበሩት በግልፅ ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንዲህ በማለት የምስክርነት ቃል ሲሰጡ ታዩ ተሰሙ፡፡ ለምሳሌ ፡-
ሙሴ፡- የእኔ የሙሴ አምላክ፣ ጌታ፣ ፈጣሪ፣ ይበሉህ እንጂ ማነዉ? ሙሴ እያለ የሚጠራህ እያለ ሙሴ ከፈጣሪዉ ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጋገር አዩት፤
ኤልያስም፡-በደመና ዉስጥ በመሆን ይህንኑ ቃሉ መልሶ ከልዑለ ባህሪ ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጋገር ታየ፡፡ በተጨማሪም ፡-
ሙሴ እግዚአብሔርን እኔ ባህር ብከፍል ጠላቴን ዳታንና አቤሮንን ብገድል ደመና ብጋርድ መና ባወርድ ዉሃ ከጭንጫ ባፈልቅ እስራኤላዊያንን ከፈርኦን ግዞት ባስለቅቅ ባንተ ሃይል ነዉ፡፡ ለዚያዉም እስራኤልን ከክፋታቸዉ መልሶ ማዳን አልተቻለኝም አንተ ግን የዓለም መድኋኒት ስትሆን መግደልና ማዳን ይቻልሃል፡፡ እያለ ይመሰክር ነበር፡፡
ኤሊያስ፡- እኔ ሰማይን ብለጉም እሳትን ባዘንም ባንተ ሃይል ነዉ፤ እስራኤልንም ከክፋታቸዉ መልሼ ማዳን አልተቻለኝም፡፡ አንተ ግን ማዳን በእጅህ ነዉ አዳንካቸዉም እያለ ሲናገር በሌላ በኩል ሙሴና ኤሊያስ መሆናቸዉ ለማረጋገጥ በምሳሌ ታዩአቸዉ፡፡ የተገለጡትም ሙሴ አንደበቱ ኮልታፋ በመሆኑ ሲናገር በአንደበቱ መኮላተፍ ታወቀ፤ ኤልያስ ደግሞ ደግሞ ፀጉራም ነበር፡፡ ስለዚህ በፀጉሩ ታወቀ፡፡
ጌታ እግዚአብሔር ከሌሎች ነቢያት ሙሴ እና ኤሊያስን ለምን አመጣቸዉ?
ሙሴ፡- ፊትህን ልየዉ እባክህን ክብርህን አሳየኝ ቢለዉ ሰዉ አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አትችልም ብሎት ነበርና፡፡ ኦሪት ዘፀአት33፡18-20 ጥያቄዉን ሊመልስለት ራሱን አዘጋጅቶ ሊታየዉ ጠራዉ፤
ኤልያስ፡-ኤልያስ ብዙ ተአምራትን ካደረገ በኋላ በክብር በእሳት ሰረገላ ወደላይ ተነጥቆ ነበር፤ ጴጥሮስ ዮሐንስና ያዕቆብም በደብረ ታቦር ጌታን ኤልያስ ይሆናል ብለዉ ስለተጠራጠሩ ለማስረጃነት ( ለማሳመኛ ) ኤልያስን ከመንበረ ፀባኦት ጠርቶ በፊታቸዉ አሳያቸዉ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ቢጠራጠሩትም እርሱ የሙሴ እና የኤልያስ ፈጣሪ እንጂ ሙሴ ወይም ኤልያስ እንዳይደለ እንዲረዱ ሁለቱን ብቻ ጠራቸዉ፡፡
ሁለቱን ከነቢያት ሶስቱን ከሐዋርያት አምጥቶ በደብረ ታቦር የመገለጡ ምክንያት፡-
ተራራዉ የቤተክርስቲያን ምሳሌ ስለሆነች ነቢያትን በብሉይ ሐዋርያትን በሐዲስ በመመስል ነቢያት እና ሐዋርያትም በደብረ ታቦር ተራራ ላይ መገለፃቸዉ በቤተክርስቲያን ሐዲስም ሆነ ብሉይ እንደሚሰብክ ለማጠየቅ( ለማሳወቅ) ነዉ፡፡
አንድም ቤተክርስቲያን የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ በመሆኗ መንግሥተ ሰማያትን ነቢያም ሆኑ ሐዋርያት እንደሚወርሷት ለማጠየቅ ነዉ፤ በተጨማሪም ከህጋዉያን ሙሴን ከደናግላን ኤልያስን ማምጣቱ ደናግልም ህጋዉያንም የመንግሥተ ሰማያት ባለቤት መሆናቸዉን ለማሳወቅ ነዉ፡፡ አንድም ከሙታን ሙሴን ከህያዋን ኤልያስን ማምጣቱ በህጉ ያሉ ቢሞቱም እንኳ ከእርሱ ፊት ህያዉ መሆናቸዉን ለማስረዳት ነዉ፡፡ መዝሙር 115፡6(5) " የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነዉ፡፡"
በየዓመቱ (ነሐሴ 13 ቀን ) ደብረ ታቦርን (እግዚአብሔር አብን) የምናከብረዉ ለምንድን ነዉ?
ደብረ ታቦር እያልን የምናከብረዉ ጌታ የመለኮቱን ክብር የገለፀዉ በታቦር ተራራ ስለሆነ በተጨማሪም እግዚአብሔር አብ የወልድን የእግዚአብሔር ልጅነት የመሰከረዉ በደብረ ታቦር ተራራ ላይ በመሆኑ በመታሰቢያነት ደብረ ታቦር ( የእግዚአብሔር አብን ዕለት እናከብራለን)፡፡
ችቦ የሚበራዉ፡- እግዚአብሔር አብ የምወደዉ የምወልደዉ ልጄ ይህ ነዉ ብሎ በተናገረ ጊዜ የመለኮቱ ብርሃን የመንፀባረቁ ምሳሌ ነዉ፡፡ ጅራፍም የነጎድጓድ ምሳሌ ነዉ፡፡
ዳቦዉ የሚደፋዉ፡- (ዳቦ ሲደፋ ከላይ እሳት ከታች እሳት ከመሃከሉ ህብስት እንደሚገኝ ሁሉ እርሱም ክርስቶስ ከእመቤታችን ማህፀን ለዓለም ሁሉ ለማዕድነት የመቅረቡ ምሳሌ ነዉ፤)
ማጠቃለያ፡-
ብዙ ጊዜ ስለሚነሳ ችቦ መብራት ያለበት በቃዜማዉ ማታ 12፡00 ሰዓት ነዉ፡፡ ምክንያቱም ለበዓላት ዋዜማ የሚቆሙ ከክብሩ እለት በፊት ነዉና፡፡
ስለ ደብረ ታቦር ከብዙ ባጭሩ በወፍ በረር ይህንን ያህል ካልኳችሁ ነገሬን ከመቋጨቴ በፊት ቅዱስ ጴጥሮስ ያለዉን መድገም ወደድኩ " በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነዉ" በቅድስናዉ ስፍራ በታቦር ተራራ ምሳሌ በሆነችዉ ምሥጢር በሚገለጥባት፣ የክርስቶስ ስጋ በሚፈተትባት፣ ሰዉ እና መላዕክት በሚገኙባት፣… በቤተክርስቲያን መሆን መልካም ነዉ፡፡ ተመልሶ ሲመጣ ከቤተክርስቲያን አይጣን፡፡ አሜን ፡፡ ይቆየን፡፡  

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...