እሑድ 8 ጁን 2014

ክፍል ስድስት… … … አጋጣሚ



ረጅም ዕድሜን ባልኖርም ሊደርሱብኝ የሚችሉትን አስተናግጃለሁ፣ ማየት የነበረብኝን አይቻለሁ፣ ደስታንም ሃዘንንም ከእህቴ የበለጠ አዉቃለሁ፣ ( ከእህቴ እንደምበልጥ የማረጋግጥልህ እሷ በህይወቴ ጣልቃ እየገባች አዉቅልሻለሁ ስትለኝ ይህንን ሁሉ እንደማዉቅ አለማወቋ በቂ ማረጋገጫ ነዉ፤ እስኪ እኔን ከእናቴ ፈርማ ተረክባ ቢሆን አሁን ያለሁበት ሁኔታ ለምን እንደሚዳርጋት አስበኸዋል? ) አሁን ከምነግርህ በላይ አዉቃለሁ፤ ነገር ግን እስካሁን የማዉቀዉ መጥፎ ነገሮችን ነዉ ጥሩ የተባሉትንም ቢሆን ከእርሷ የተሻለ አዉቃለሁ፡፡ የሚገርመዉ ስለግል ህይወቴ ዕድል ሳትሰጠኝ ስለ አገር ጉዳይ ቁጭ አድርጋ ታወራኛለች፤ እስኪ አስበኸዋል እኔ አሁን ስለ አገር የሚያገባኝ ሴት ነኝ የኔን ነፃነት ነፍጋኝ ዲሞክራሲ ስለጠማት እና ስለራባት አገር እኔ ምን አግብቶኝ ነዉ ከእሷ ጋር ስለ አገር ጉዳይ ለማዉራት በጠረጴዛ ዙሪያ የምሰደረዉ? ስለፍቅር እየተከለከልኩ ስለ ፖለቲካ የሚፈቀድልኝ እንዴት ነዉ ነገሩ? እኔ የሚገርመኝ ፖለቲካል ሳይንስ ታጥና ህክምና ግራ ግብት ይለኛል፡፡ ለምን አታገቢም ስትላት መጀመሪያ አገር ባለቤት ይኑራት ትልሃለች፤ ለምንድን ነዉ የራስሽ ነገር የማይኖርሽ ስትላት አሁን ጊዜዉ አይደለም ስንት አንገብጋቢ ነገር እያለ ትልሃለች፤ እሷን የሚያንገበግባት የእኔና የአገር ጉዳይ ብቻ ነዉ፡፡
ልብ በለህ ስማኝ እሷ ወንድ የምታዉቀዉ ስለፖለቲካ ጉዳይ ለማዉራትና በህክምና ሊረዳ በስራ ቦታዋ ሲመጣ ብቻ ነዉ፤ ባለፈዉ አንዱ ከቤት ድረስ ቢመጣ ሁላችን ደስ ብሎን ( መቸስ በባህላችን ሴት ልጅ ወንድ ይዛ እቤት ድረስ ስትመጣ የቱንም ያህል ደስ የማይል ጉዳይ መሆኑ ግልፅ ቢሆንም ይህ የሚያሳየዉ የጉጉታችን ልክ መጠነ ሰፊ መሆኑን ያመላክታል ) ግድግዳዉ ላይ ጆሮአችንን ለጥፈን ( አንድያዉን ለስነን ብትለዉ ይቀላል) ብናዳምጥ ብናዳምጥ አንዳች ነገር አጣንባት ከጆሮዬ ይሆን ብዬ አብራኝ የነበረችዉን የቤታችን አባል ሰራተኛይቱን ብጠይቅ እሷም እንደኔዉ ተበሳጭታ ኖሮ እሷቴ አናዳችም ስለሴትና ወንድ ያወራችዉ ነገር እንደሌለ ነገረችኝ፤ ያዉ የፈረደበትን ፖለቲካ እቤት ድረስ ይዛ መጥታ ታቦካዉ ጀመረ እንጂ፡፡ አሁን እስቲ ማን ይሙት ‹‹ የዘመናችን ብቸኛዋ ፖለቲከኛ ሴት ለመባል ነዉ ወይስ … ›› እስኪ እንደዉ ብቻ ተወኝ፤ ነገረ ዓለሙ ሁላ ፖለቲካ ፖለቲካ የሸተተበት ዘመን ላይ ደርሰን ህጻን አዋቂዉ አልጋና ትራሱ ሁሉ ፖለቲካ ሆኖ ፍቅር ጠፋ አንዴ እኔ ብገኝ በምን እናጥፋሽ ብለዉ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡
( እነማን ናቸዉ ለማለት ፈለኩና የሞቀ ወሬያችንን በኔ ጣልቃ ገብነት እንዳልገታዉ ፈራሁና እየተከታተልኳት መሆኔን አንገቴን ላይ ታች በመነቅነቅ ገለጽኩላት፤) 
ከዚህ ቀደም እንዳወራነዉ ከልጅነት ጓደኛዬ ሌላ ተባራሪዎቹን ሳንቆጥር አንድ ሶስት ወንዶችን በደንብ አዉቃለሁ፤ ነገር ግን ይህቺ ክፉ እህቴ ሁሌ ጥላዋን እያጠላችብኝ እንደዛፍ ላይ እንቅልፍ አስሬ እየባነንኩ ነበር የምኖረዉ፡፡ የመጀመሪያዉ በጣምም ሃብታም ባይባል ለኔ ከበቂ በላይ ሊይዘኝ የሚችለዉ አቅም ነበረዉ ከነበረዉ ገንዘብ ይልቅ ፍቅሩ ይግደለኝ፣ እንክብካቤዉስ ብትል፣ በተለይ በተለይ የትም ስንገባ የነበረዉ ክብር እመቤት የሆንኩ ያህል ነበር የሚሰማኝ ወንበር ስቦ አስቀምጦ፣ የመኪና በር ከፍቶ አዉርዶ አስገብቶ፣ … ስንቱን ልበልህ ከልቡ ነበር ግን ‹‹ ባሪያ ላመሉ … ›› እንደሚባል ልክስክስ ነበር፤
እኔ ሳላንሰዉ የከለከልኩት ነገር ሳይኖር ይቀላዉጣል፡፡ ሰማሁ ዝም አልኩት ደግመዉ ነገሩኝ ጠየኩት ‹‹ የጠላት ወሬ ነዉ ›› ቢለኝ እኔም የጠላት ወሬ ነዉ ብዬ እሱን አመንኩት፤ ቢደጋገምብኝ ተከታተልኩት በዓይኔ በብረቱ ባየዉ መከርኩት ዘከርኩት ሽምጥጥ አድርጎ ካደኝ ‹‹ አንቺዉ ታመጭዉ አንቺዉ ታሮጪዉ ›› አለ ያገሬ ሰዉ እንግዳዉስ ካንተ ከመጣ ብዬ እየወደድኩት ተለየሁት፡፡ ሁለተኛዉ ምንም ታሪክ የሌለዉ ሲሆን ሶስተኛዉ ደግሞ በፌስቡክ የተዋወኩት ልጅ ነዉ ፀባዩ ይገልሃል ፍቅሩስ ብትል ከአንዳንድ ነገሩ በቀር የመጀመሪያዉን ያስከነዳዋል፤ ደሞዝተኛ ነገር ነዉ ነገር ግን ሰዉ ለካ ብዙ ስላለዉ አይደለም ትንሽም ባግባቡ ለያዘዉ ብዙ ነዉ ጥንቃቄዉና ንጽህናዉ ልነግርህ አልችልም፡፡ ያለበት ክፉ አመል በቃ እሱ የያዘዉ ነገር እዉነት መስሎ ከታየዉ ልምምጫ የሚባል ነገር አያዉቅም እኛ ሴቶች ደግሞ ልምምጫ ምሳችን ነዉ፡፡ ፍቅር ይችላል ይህን የምታየዉን ወገቤን ይዞ ፍቅር ሲሰራ አፉ ሳክስፎን የሚጫወት እጆቹ ጊታር የሚመቱ ይመስላሉ፡፡በተገናኘን በመጀመሪያዉ ወር በአስራ ስድስት ዋዜማ በአስራ አምስት ምሽት በአንድ ትልቅ ሆቴል አልጋ ይዘን ምሽቱን የሙሉ ባንድ ጭፈራ አስመሰልነዉ ወሲብና የጊታር ጨዋታ እንደሚመሳሰሉ ያን እለት አረጋገጥኩ ለካ ፍቅር ካለበት ወሲብ አይሰለችም፡፡
እንደነገርኩህ የጅነት ጓደኛዬ ከቤ ባለዉ የትምህርት ብቃት ከባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ከተመረቀ በኋላ እዛዉ ቀርቶ እንደነበር ፣ የማስተመሩንም ስራ ትቶ ለሁለተኛ ዲግሪዉ ወደ ዉጭ አገር እንደሄደ፣ የሚያሳዝነዉ ነገር እንዲህ እንደረከስኩ ሳያዉቅ ዛሬም በልቡ እንደያዘኝ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እኔን በማለት ለሰባት አመታት አይቷቸዉ የማያዉቃቸዉን ቤተሰቦቹን ጥየቃ ብሎ በመሄድ እኛ ቤት ተመላልሶ ቢያጣኝ ከሰዉ ዘንድ አድራሻዉን አስቀምጦ እንደሄደ ሰማሁ፡፡ የተረጀመች እህቴ ለቀሶ ለመድረስ ስትሄድ ሰዉ አገኘን ብለዉ መልዕክቱን ሲሰጧት ያችን የፍቅር ድልድይ ሰብራት መጣች የተሰጣትን የመገናኛችንን አድራሻ የያዘች ወረቀት ቀደደቻት፡፡
‹‹ፍቅር እንደመጀመሪያዉ አይሆንም ነዉ … ፍቅር አንዴ ነዉ፤ ››ሲባል የሰማሁ መሰለኝ ይህንን ነገር ከሰማሁ ጀምሮ ማብቂያ የሌለዉ ሃዘን ተቀመጥኩኝ፣ እርሱ ጋር እንጂ እኔ ጋር ፍቅር እንደሌለ ተረዳሁኝ፣ አንገቴን አስደፋኝ፣ አፈርኩኝ፣ … ሆኖም ግን ዛሬም እንደትናንቱ ሲያጣኝ ተስፋ እንደሚቆርጥብኝ ተረዳሁ፡፡ በራሴ ላይ የዕድሜ ልክ ፅኑ ፍቅር የማጣት ቅጣት በየንኩ፤ … ዳግም ላላፈቅር ፣ ዳግም የወንድ ጭን ዉስጥ ላልገኝ፣ የቀዘቀዘ ገላዬን የወንድ ስሜት ላያሞቀዉ ቃል ገባሁ፡፡ ያ ቤቱ ድረስ ሄጄ የፍቅርን ሻማ የለኮስኩለት ወንድ ሜዳ ላይ ጥዬ፣ የልቡን በር ሰብሬበት ጥዬዉ ወጣሁ፣ ፍቅር በመስተጥ ቀርቤዉ ብቀላ በሚመስል አኳሃን ልቡን ሰርቄዉ ተለየሁት፣ ዉትወታዉና ልመናዉ ላይገባን ፊት ነስቼዉ ወራቶች ተቆጠሩ፡፡ ቁጭ ብዬ ለማዉራት ዕድል አልሰጥህ ብለዉ በየጊዜዉ የደብዳቤ መአት ከቤት ይቆየኛል፡፡ የቅርብ ጓደኞቹ ሳይቀሩ አላስወጣ አላስገባ እያሉ መከራዬን አሳዩኝ፤ … የርሱ ግፍ ነዉ መሰል ዛሬ እንዲህ ምስቅልቅሌ ወጥቶ ከሰዉነት ጎዳና ወጥቼ ክብሬን ዝቅ አድርጌ ሴትነቴን አዋርጄ ከባንኮኒ ስር መገኘት፣ ተከፈት ከተባለ ጭፈራ ቤት ማንጋት ስራዬ ሆኗል፡፡ይህንን ዉርደት እህቴ አታቅም ጠባቂዬ ይህ መረጃ የላትም … እሷን ብሎ ፖለቲከኛ እቤት ስንት ነገር እያረረባት ስለአገር ጉዳይ ታማስላለች፤ ተመልከት እንግዲህ የኛን አገር ፖለቲከኞች እንዲህ ናቸዉ ራሳቸዉ ከጫማቸዉ ስር ይጥሉንና በአደባባይ ስለ ዲሞክራሲ ያናፋሉ፡፡ ራሳቸዉ ድንግልናችንን ገርስሰዉ ስለሴቶች መብት ታጋይ ነን ይሉናል፣ ራሳቸዉ ያጫርሱንና የኛ ፖለቲካ መሃሉም ዳሩም ብሔር ብሔረሰብ ነዉ የምንታገለዉ ስለብሔር እኩልነት ነዉ እያሉ ቆዳቸዉን ያዋድዳሉ፡፡ እስኪ እኔ ነኝ ያለ ስለሰዉ ልጅ ክብር ይታገል ከሚከፋፍሉን፤ …
አሁን በቃኝ አገሬ የምላት የነፃነት አገር ከሌለኝ፣ ቤተሰብ የምለዉ ፍቅር ሰጥቶ ነፃነቴን አክብሮ ምርጫዬን ተቀብሎና ወዶ ምሳሌ ሆኖ የሚያኖረኝ ከሌለ እኔም ( እምባዋ ቀደማት ያቺ ደስተኛ ሴት ፍልቅልቅ የደሰ ደስ ያላት ዉብ እምባዋ በፊቷ ላይመጠነኛ ጎርፍ ሰሩ) እኔም እንደ ሰዉ እሰደዳለሁ በቃ! በቃ በድሃ አገር ላይ የሰዉ ልጅ የመጨረሻ አማራጭ ስደት ነዉ፤ ስደት! እስደዳለሁ፡፡ ያለነገር ታቦት ከመንበሩ ሰዉ ከአገሩ አይሰደድም፡፡ አደራህን ምሥጢሬን ስለምታዉቅ ጠግባ ነዉ እያለ ምላሱን ለሚያሾልብኝ ምላሹን ስጥልኝ፣ ጠግቤ አይደልም፣ የሚሰራኝን ስላሳጣኝ አይደለም፤ የሠላም ማጣት፣ የፍቅር ማጣት ፣ የአርአያ ማጣት፣ በሰላም ወጥቶ በሰላም መመለስን ማጣት፣ እህት ጠላት ስትሆን ይህንን ቆሞ ከማየት  …. የመነጨ ነዉ በልልኝ፡፡
*************///////////////////////******************
ቀናት እየበረሩ ወደ ዓመታት ተቀየሩ ነገሮች እንደቀልድ ታሪክ ሆኑ፤ የራቁት እየቀረቡ ከአፍንጫችን ስር ደረሱ፡፡ ትናንት ከርቀት ያወራንላቸዉ ከመንደራችን ደርሰዋል ርቀዉ የሄዱ ዛሬ ጎረቤቶቻችን ሆነዋል፡፡ ከቤ ከዓመታት በኋላ ትልቅ ሰዉ ሆና እዛዉ የሰዉ አገር እየሰራ እየተማረ የሶስተኛ ዲግሪዉን ለመስራት የጥናት ስራዉን ‹‹ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና ልማት ›› ላይ ጥናት ለማድረግ አዲስ አበባ ከገባ ቀናት ተቆጥረዋል፤ የመንግስት አካላት፣ ባለሃበቶች ሳይቀሩ ተቀብለዉ እንዳነጋገሩት የዉጭ ጉዳይ እና የፀረ ሙስና ኮምሽን ለአገር ዉስጥ ጥናቱ አስፈላጊዉን ትብብርና እና ሙሉ ወጪዉን እንደሚሸፍኑለት በየቢሮአቸዉ ለመንግስትና ለግል ሚዲያዎች መግለጫ መስጠታቸዉ የሰሞኑ አበይት ወሬ ነበሩ፡፡ሚድያዎች ሰሞኑን ትኩስ ወሬያቸዉ ሁሉ ስለ ከበደ ነዉ ( እጩ ዶክተር ከበደ እያሉ ያሞካሹታል ) ምስሎቹ የህትመት ገጾችን አድምቀዉታል ለአዘጋጆች ጥሩ የገቢ ምንጭ ለአገሪቱም የሚሊንየሙ ግብ መምቻ ጥሩ ጥናት ይሰራልናል በማለት መንግስትም ህዝብም ተስፋ ጥሎበታል፡፡ አቶ ከበደን አግኝቶ ለመጋበዝ ፈቃድ ማዉጣት እስኪያስፈልግ ድረስ እሱን ማግኘት ከባድ ነገር ሆኗል፤ ሆቴሎች መዝናኛ ስፍራዎች አቶ ከበረ ለግብዣ ሊመጣ ይችላል በሚል ተይዟል የሚሉ ጽሁፎች በየወንበሩ ተለጥፈዉ ይታያሉ፡፡  
/////////////////////**********************////////////////////
በተለመደ ባህላችን ሰዉ ሲሄድ መሸኘት ልማድ እንደመሆኑ መጠን አምርራ አገር ጥላ ለመሄድ የተነሳችዉን ጓደኛቸዉን ለመሸነት ወንዱም ሴቱም ተገኝተዋል፤ መጠጡ እንደጉድ ይጠጣል ፣ መልዕክቶች በስልክ በጽሑፍ መልዕክት ይዥጎደጎዳል፣ የሚገርመዉ ማነነቱ ያልታወቀ ደብዳቤ አድራሻ ሳይፃፍበት ለጓደኛዋ ለቤቲ እንድትሰጣትና እንድታነበዉ ተደረገ፡፡ ቤቲ መልዕክቱ አስቸኳይ ሊሆን ይችላል በሚል ሰበብና ለወሬም ከመቸኮላቸዉ የተነሳ ወደ ጓሮ ሄደዉ ማንበብ ጀመሩ፡፡
 ጸጋዬ ይበቃሃል
          ጸጋን ለሰው ልጆች የሚያድል የፍቅር ባለቤት ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አባቱ እግዚአብሔር አብ የባህርይ ሕይወት የሰው ልጅ አጽናኝ የሆነ መንፈስ ቅዱስ በእኛ እና በቅዱሳኑ አንደበት በምድር እና በሰማያት ለዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን፡፡
          አክብሮትን ናፍቆትን ፍቅርን ለዘለዓለም የማልነፍግሽ ተወዳጇ ፍቅሬ ለጤናሽ ከመላው ቤተሰቦችሽ እና ጓደኞችሽ ጋር እንደምን አለሽልኝ በትንሹ የአመል ባሪያ አድርጎ ከዘን ኩርፊያችን በስተቀር በድጋሚ ለዘለዓለም የአባቶቻችን አምላክ ልዑለ ባህርይ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን ደህና ነኝ፡፡
          ውዴ ፍቅሬ ልበልሽ በፍርሐትና በሥጋት … ነገንና ከነገ በስትያ ያለውን ቀን ስለማናውቀው እያስፈራኝና እያሰጋኝ ስለሆነ ….
          ‹‹ትምክህት የሚያስፈልግ ነው፤ አይጠቅምም … እመካለሁ፤ ስለራሴ ግን ከድካሜ በቀር አልመካም፡፡ ልመካ ብወድ ሞኝ አልሆንም እውነትን እላለሁና፤ ነገር ግን ማንም ከሚያይ ከእኔም ከሚሰማ የሚበልጥ አድርጎ እንዲቆጥረኝ ትቼአለሁ፡፡ … ጸጋዬ ይበቃሃል … የክርስቶስ ኃይል ያደርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ፡፡ …››
‹‹ጸጋዬ ይበቃሃል››
          ጸጋ፤ ‹‹ካሪስ›› የሚለውን የግሪክ ቃል የሚተረጉም ሲሆን ሶስት የዕብራይስጥ ቃላትን አሳብ ይይዛል፤ እነርሱም ‹‹ሞገስ››፣ ‹‹ፍቅር›› እና ‹‹ምሕረት›› ወይም ‹‹ቸርነት›› በተሰኙ የአማርኛ ቃላት ይተረጎማሉ፡፡
          ጸጋ ማለት ከላይ እንደዘረዘርነው ሞገስ፣ ፍቅር፣ ምህረት፣ /ቸርነት/ ከሆነ ለሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይበቃሃል የተባለው ጸጋ እውነትም ይበቃዋል ምነው ቢሉ ዛሬ ዓለም በአጠቃላይ እኛን ጨምሮ ልባችንን እያሳወረ ያለው ሃብት ንብረት ትልቅነትና የበላይነት … ወዘተ ሊበቃን አልቻለንምና አንድም ዳግም ሃብት፣ ንብረቱ … ይበቃሃል አልተባለምና ጸጋዬ ይበቃሃል እንጂ፡፡
          ዛሬም ለእኔና ለአንቺ ለሌላውም ጸጋው ይበቃናል ሞገስ ፍቅር ምህረት ቸርነት ካለን ሌላ ነገር ሁሉ ትርፍ ነውና፡፡ ይህንንም ባለፈዉ ታመሽ ጻድቃኔ ሄደሽ በመጣሽ ጊዜ በደንብ እንደተረዳሽ በአንደበትሽ ነግረሽኛልና ብዙም አልልም፡፡
          ሐዋርያው ከላይ መናገር ሲጀምር ስለ ‹ትምክህት› ይናገራል፡፡ ትምክህት የሠሩትን ሥራ ማጋነን ራስን ማክበር በሥራ በኃይልና በችሎታ መታመን ራስንም ማመስገን ነው፡፡ ስለመመካት የሰው ልጅ በእግዚአብሔር እንጂ በራሲ ሊመካ እንደማይገባው ብዙ ጊዜ ደጋግሞ ተናግሯል፡፡
          እኛም ብንሆን በሥጋ እንመካ ብንል ምናልባት የምንመካበት ከጥቃቅን አንስቶ ግዙፍ ድረስ ሊኖር ይችላል ነገር ግን መመካት የሚገባ ስላልሆነ አንመካም እንመካስ ብንል ራሳችንን እንመርምርና እኛ ማን ነን? እንደ እኔ እንደ እኔ ከሆነ እንደ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከድካሜና ከታናሽነቴ በስተቀር የሚያስመካን ነገር የለኝም ቢኖረኝም እንኳን ሞኝ የሚያሰኘኝ ነገር ቢሆንም አሁንም እላለሁ፡፡ ለሁላችንም የክርስቶስ ኃይል ያድርብን ዘንድ ጸጋውም ይበዛልን ዘንድ በብዙ ደስታ በድካማችን /ድሆች ብንሆን በክርስቶስ ኢየሱስ ባለጸጎች መሆናችን አላዋቂዎች ስንሆን በርሱ አዋቂዎች በመሆናችን … ወዘተ ልንመካ እወዳለሁ ይገባናልም፡፡
ጸጋው ይበቃሃል÷ ጸጋው ይበቃሻል÷ ጸጋው ይበቃናል
          እኔ አንቺ እነርሱ ሁላችንም ዛሬ ያለነው ጸጋው ስላልበቃን የጸጋን ትርጉም የጸጋን ጥቅም ስላልተገነዘብን ሁሉ ሞልቶን ሳለ ባዶዎች ሆነናል በክርስቶስ ኢየሱስ ባለጸጎች ሆነን ሳለ ድሆች ሆነናል ጸጋውን ትተን ምድራዊ ነገር ሽተን ናፍቆናል የሚታይ የሚጨበጥ የሚዳሰስ አንቱ የሚያሰኘን ነገር በስተቀር አልታይ ብሎናል የመላው ዓለም ሕዝብ የአንድ ቤተሰብ ያህል ወይንም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ያህል መሆን ሲገባው የጸጋው መጓደል ከጸጋው ጎደሎዎች መሆናችን እኔና አንቺን በየመንገዱ ሰላም ነስቶናል አነታርኮናል ፍቅርን አጉድሎብናል ሞገስ ፍቅር ቸርነት ምህረት አጥተናል፤ ለምን?
          ለዚህ ጥያቄ መልስ ሰጥተን በአጭሩ ካልቀጨነው ነገ በውስጣችን ካደገ በኃላ መልስ አይኖረውም ይህ እንዳይሆንብን የምንፈልግ ከሆነ ትልቅ መንፈሳዊ ተጋድሎ ይጠበቅብናል፡፡ ማን ይሆን የሚጋደል ብርቱ ሰው? እንጂ፤
          ጸጋው በሙላት በውስጣችን ቢሆን ኖሮ እምነት ዓላማ ሰማዕትነት በውስጣችን ይገለጥ ነበር፡፡ በዓለም ካለን በሥጋዊ ዐይናችን አይተን ተስፋ የምናደርገው ነገር በመንፈሳዊ ሕይወታችን እያለን በተትረፈረፈልን ነበር፡፡
          የኔ ፍቅር በተገለጠ ዓይናችን ተያይተን ዛሬ ቅርፊቱ ሲወድቅልንና ማየት ስንጀምር ስትመለከችኝ ማንነቴ የሚያሳፍር የሚያነጫንጭ የማያስመካ፣ የማያኮራ፣ እዚህ ግባ የማልባል ሆንኩብሽ ይሆን? ወይስ ሳታውቂኝ ቀርበሽኝ ስታውቂኝ ጠላሽኝ ባዶነቴ አልዋጥ ብሎ አንገሸገሸሽ ፊትሽ ተደንቅሬ ሰላም ነሳሁሽ? እህ ያልሽበት ጆሮ ጉድ አመጣ? ለዚህ ነው በየመንገዱ በየቀኑ የምንኮራረፈው ለምን? ግን ለምን ውዴ?
          እስኪ መሰረተ ሐሳባችን አንስተን እንመልከት ወዳጅነት ለምን ይፈርሳል? ወንድማማቾችስ መተማመን እያቃታቸው ለምን በየወንዙ ዳር ይማማላሉ? ፍቅረኛማቾችስ ለምን ይለያያሉ? መግባባትስ እያቃታቸው ለምን ግጭትን ይፈጥራሉ? ለምንስ እግር እግርን ይመታዋል? ጥርስስ ምላስን ለምን ይነክሰዋል? ዝም ብሎ ድንገት ይሆን? እግዚአብሔር ፈቅዶ? ሰይጣን ፈትኗቸው? ሰው መሐላቸው ገብቶ? አይደለም፡፡ እስኪ ጥቂት ምክንያቶችን እንጥቀስ፡-
1.      እምነት መጥፋት፡- እምነት ብኩርና /ተቀዳሚ ነገር/ ነው ትናንት ሁሉም ነገር ስንወጥነው ማንን ነበር ያመን ነው? ማንን ነበር ተስፋ ደረግነው? ዓይናችንን ከሰዎች ላይ ነቅለን ወደ ሰማይ አልነበረም የሰቀልነው? እርሱ ያውቃል ብለን አይደል እንጂ የጀመርነው? ይህንን ያህል እውቀት ይህንን ያህል ካፒታል በባንክ ካለህ ደሞዝህ ካለህ ይበቃሃል ብለን ነበር እንዴ የጀመርነው? አይደለም፡፡
የእግዚአብሔርን ሥጦታ ጸጋውን አስበን ጸጋው ፍቅሩ ቸርነቱ ምህረቱ ሞገሱ ይበቃናል ብለን እንጂ ዛሬ ታዲያ ምን መጣ እምነትሽን የጣልሽብኝን የወደድሽኝን ያከበርሽን ያህል ጠላሽኝ? ጥያቄዬ ለምን ጠላሽኝ አይደለም መብትሽ ነውና ነገር ግን እኔ ምክንያት አልሁን ታናሽነቴ ባዶነቴ ምክንያት አይሁን ለማለት እንጂ፡፡
     እምነት እየጠፋ ሲመጣ ያመኑትን መክዳት የወደዱትን መጥላት ያከበሩትን ማቅለል … ትልቅ ነገር ስላልሆነ አይደንቀኝም፡፡
2.      ዓላማ ሲዘነጋ፡- የተጀመረው ዓላማ ሩቅ እና ጥብቅ መሆኑን ዘንግተን እንናጋለን ተፈረካክሰንም ለውድቀትና ለመለያየት እንበቃለን ሰዎች ወዳጅነት የመሠረቱበትን ጥንተ ዓላማ ሲስቱት የህብረታቸውን ምክንያት ሲዘነጉት ጠብና ክርክር ተላልፎ መሰጣጣትና መበላላት የዘወትር ተግባር ይሆናል፡፡
እስራኤል ከግብፅ ባርነት ሲወጡ ‹‹ማርና ወተት የምታፈሰውን የአባቶቻቸውን ርስት ከነአንን መውረስ›› ዓላማቸው መሆኑን ልዑል እግዚአብሔር ደጋግሞ ነግሯቸዋል፡፡ የሮቤል ነገድ የምናሴ ነገድ እኩሌታና የዳን ነገድ ግን ዓላማቸውን ዘነጉትና ከዮርዳኖስ ወዲህ በሚገኘው ለምለም መሬት ለመቅረት ወሰኑ፡፡ ከፊታቸው ኃያላን ጠላቶች እያሉ ወንድሞቻቸውን አሳልፈው ሰጥተው እነርሱ ግን የድሎትን ኑሮ ለመኖር ተመኙ፡፡
እኔና አንቺም እንደነርሱ ከፊት ለፊታችን ታላቁን የህይወት መንገድ ከፊታችን ተጋፍጦን ፈተና እየጠበቀን የሥጋ ፈቃዳችንንና አምሮታችንን ለማሟላት በጊዜያዊና አጓጊ በሚያብረቀርቅ ነገር ግን ወርቅ ባልሆነ ነገር ተታለን ‹‹የድሎት›› ሕይወት ለመኖር አንናፍቅ ዓለማችንን መንገዳችንን ሕይወታችንን … አንዘንጋ፡፤ የሚደላ የሚመች አጓጊ ልብን አነሳሽ የሚያኮራ የሚያስመካ ሕይወት አጋጥሞሽ ይሆን? እሰየው እርሱም ከሆነ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ቅሉ መጨረሻው ባይሰምርም የኛ ነገር ጅምር እንጂ ውጥን ስለሌለው፡፡
3.     ሰማዕትነት ሲቀር፡- ማናቸውም ዓይነት ወዳጅነት ይነስም ይብዛም ሰማዕትነትን ይጠይቃል ይልቁንም የኔና ያንቺ ሕይወት የጀመርነው ጉዞ /ዓላማ/ ሰማዕትነት እንደ ጥንቱ አንገትን ለስለት ሥጋን ለእሳት መስጠት አይደለም አብረን ስንኖር በፍቅር አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ መባባል መደማመጥ በግልጽ መነጋገር መወያየት ችግሮችንም መፍታት እንጂ፡፡ ትዝ ይልሻል እንዴት እንደተገናኘን እንዴት ፍቅር እንደጀመርን መቸስ አለዉ ብልሽ ወይም ይኖረዋል ብለሽ እንዳልመጣሽ ተስፋ አደርጋለሁ ፍቅሬ ማርኮ አስቀረሽ እንጂ፤
በተለይ ደግሞ ክርስትናን መሠረት ያደረገ ኅብረትና ወዳጅነት ሰማዕትነት ከሌለው እንደሚጮህ ናስ እንደሚንሻሻም ፅናጽል ይሆናል፡፡ ሰማዕትነት የቀረቡት ሕይወት ሰማዕትነት የተለየው ኅብረት /ግንኙነት/ በምንም ዓይነት በውስጡ ፍቅር መተሳሰብና መተባበር ሊኖር አይችልም፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ጎን ጎኑን ከሚወጋው ሰይጣን ለመገላገል ሦስት ጊዜ ለእግዚአብሔር ያቀረበው ጥያቄ ‹‹ተወው ጸጋዬ ይበቃሃል›› የሚል መልስ ያገኘው የእውነተኛ የክርስቲያን ሕይወት /የፍቅር፣ የትዳር ጓደኝነት/ ያለ ተጋድሎ መኖር ስለሌለበት ነው፡፡
እኛም ዛሬ ለጓደኝነታችን ለፍቅራችን ለነገው ‹ትዳራችን› ምናልባት ያስፈልጉናል የምንላቸው ‹ከሰው በታች› እንዳንሆን ሃብት ንብረት እውቀት ብርና ወርቅ መኪና ቤት ውበት ታዋቂነት … ወዘተ ስንለምነው ጸጋዬ ይበቃሃል ጸጋዬ ይበቃሻል ጸጋዬ ይበቃችኋል ነው የአንድዬ መልሱ ማን ይሆን ታዲያ ጸጋ ቸርነቱ፣ ጸጋ ሞገሱ፣ ጸጋ ምህረቱ፣ ጸጋ ፍቅሩ ይበቃኛል የሚል አንቺ? ወይንስ ማን ይሆን? እንጃ፡፡
ሰማዕትነት ማለት ክርስቲያኖች /ጓደኞች ፍቅረኛሞች ባለትዳሮች እኔና አንቺ/ በዚህ ዓለም በጉድለት የሚኖሩት ሕይወት ማለት ነው፡፡ ይህም ሲባል ከጊዜያቸው፣ ከጉልበታቸው ከዕውቀታቸው ከማናቸውም ያላቸው ነገር ሁሉ የተረፋቸውን እንደ ፈሪሳዊው ሳይሆን ያላቸውን እንደ መበለቷ ለእግዚአብሔር የሚሠጡበት ሕይወት ማለት ነው፡፡
ሰማዕታት ሕይወታቸውን ሲሠው ትርፍ ሕይወት በተቀማጭነት ስለነበራቸው አልነበረም ያላቸውን ሰጥተው በጉድለት መኖር የክርስትና ጉዞ ጠባይ በመሆኑ እንጂ፡፡ ዛሬ የኔና የአንቺም ሕይወት የሚከፈልበት ሰማዕትነት ሁሉን መተው ተቻችሎ መኖር አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ ማስፈለግ የትዳር የፍቅር ጉዞ ጠባይ ስለሆነ ነው ነገር ግን ይህንን ትተን የዛሬን ጊዜያዊ ተድላ ደስታ ካሰብን ከናፈቅን በዓይን የሚታይ በእጅ የሚዳበስ ከጠበቅን ሕይወት ጣዕምና ትርጉም የላትም፡፡
በአንድ ወቅት በደብረ አሰቦ /ደብረ ሊባኖስ/ ከባድ ድርቅና ረሃብ ተከስቶ ነበር፤ እህልና ውኃ ጠፍቶ ብዙ መነኮሳት በችግር ላይ ነበሩ፤ አንድ ጊዜ ከፍተኛ የውኃ ጥም በመነኮሳቱ ላይ ተከስቶ እያለ አንድ ምዕመን አንድ ጽዋ ውኃ ለገዳሙ አበምኔት /አስተዳዳሪ/ ለአቡነ ፊልጶስ ይዞ ይመጣል፡፡ አቡነ ፊልጶስ ግን ከኔ የባሰ የጠማው ወንድሜ እገሌ አለ ብለው ለሌላው መነኩሴ ላኩለት ያም መነኩሴ ከእኔ የባሰ የተጠማ ወንድሜ እገሌ አለ ብሎ ለሌላው መነኩሴ ላከለት ያም ለሌላ እንዲህ እንዲህ እያለች የጽዋው ውኃ ሳትጎድል ወደ አቡነ ፊልጶስ ተመለሰች፡፡ በዚህም ብፁዕ እጨጌ አቡነ ፊልጶስ ተደነቁ፤ የገዳሙን መነኮሳት በሙሉ ሰብስበውም ‹‹ተመልከቱ ይህችን የፍቅር ፍሬ›› ብለው ጠጡ፡፡ የጽዋው ውኃ ግን አልጎደለችም ሁሉም መነኮሳት ከውኃው ጠጡ አሁንም አልጎደለችም በዚህ ጊዜ እጨጌ ፊልጶስ ‹‹ይህ የፍቅርና የሰማዕትነት ውጤት ነው፤ እኔ መጀመሪያ ለእኔ ይድላኝ ብዬ ብጠጣት ኖሮ ይህች ውኃ ለእኔም አትበቃም ነበር፤ አሁን ግን በፍቅራችን የተነሣ ሁላችንም አረካች›› ብለው ተናገሩ፡፡
እርግጠኛ ነኝ የተክለሃይማኖት ታላቁ ገዳም ብዙ ጊዜ ተመላልሰሻል ሳታዉቂዉ ነዉ እንጂ ይህንን በረከት ይዘሽ መጥተሻልና ዛሬ ተጠቀሚበት፤ ዛሬም የጠፋው የፍቅርና የሰማዕትነት ፍሬ ውጤት እንጂ እህል ውሀ ብርና ወርቅ መኪናና ቤት … ወዘተ አይደለም፡፡ እውነተኛ ፍቅር መካከላችን ካለ ከሞላ የማይጎድለው የእግዚአብሔር ጸጋው ይበቃናል እምቢ ካልን ሁሉም ይቀርብናል፡፡ ለኔ ብቻ ይድላኝን ገንዘብ አናድርግ፡፡
ውዷ ፍቅሬ ጸጋው ይበቃናል ከዚያ ሁሉ ይጨመርልናል ብለሽ ሰማዕትነት ከፍለሽ አፍቅረሽኝ ከሆነ ጸጋው ይበቃናል፡፡ አለበለዚያ ግን ያንቺ አይደለሁም የኔ አይደለሽም ይቅርብን እንጂ ሌላ ምክንያት አንፈልግ፤ ከዚህ ባሻገርም እንደምስኪን አይተሸኝ በማዘን ወደሽኝ ልታፈቅርኝ ራስሽን እያስጨነቅሽ ከሆነ ተሳስተሻል ተስተካከይ፡፡ ለኔም ባትሆኚ ለመጀመሪያዉ ፍቅረኛሽ ለከቤ እንጂ ለማንም አትሁኚ እዉነተኛ ፍቅር ከእርሱ ዘንድ ናትና፡፡
‹‹አስቀድማችሁ ጻድቁንና መንግስቱን እሹ ከዚያ በኃላ ሁሉ ነገር ይጨመርላችኃል››
‹‹ነገር ግን ዳግመኛ በኅዘን ወደ እናንተ እንዳልመጣ ስለ እኔ ቆረጥሁ፤ እኔስ ባሳዝናችሁ እንግዲያስ በእኔ ምክንያት ከሚያዝን በቀር ደስ የሚያሰኘኝ ማን ነው? ደስ ሊያሰኙኝ ከሚገባቸውም በመምጣቴ ሃዘን እንዳይሆንብኝ ይህንኑ ጻፍሁላችሁ ደስታዬ የሁላችሁ ደስታ ነው ብዬ በሁላችሁ ታምኛለሁና፡፡ በብዙ መከራና ከልብ ጭንቀት በብዙም እንባ ጽፌላችሁ ነበርና ይህም እናንተን አብዝቼ የምወድበትን ፍቅር እንድታውቁ እንጂ እንዳሳዝናችሁ አይደለም፡ ይላልና፤ ዛሬ ነገ ልትሄጂ የደስታሽ ቀን መሆኑን ሰምቻለሁ ተለመኚኝ ብዙ ጸጋ በዚህ አለሽና ከዚህች ከተቀደሰች አገር አትሂጂ፤ በፌስ ቡክ እንድትወጂኝ ፍቅሬም እንድትሆኚኝ ያደረገሽ ሌላ ሃብት የለኝም እና ዛሬም ስሚኝ፡፡
ጸጋዬ ይበቃሃል
የሰላም አምላክ እግዚአብሔር ሰላሙን ፍቅሩን አንድነቱን መተሳሰቡን መከባበሩን መደማመጡን ለሁላችን ያድለን ያስጀመረንን ያስጨረሰን ፍቅራችንን ከፊት ይልቅ ያብዛ ይጨምር ጀመሩ አቃታቸው ተውት ከመባል ይሰውረን ‹‹ለሌላ አትሁኚ›› አሜን! ደብዳቤዉን አጣጥፋ ከጡት ማስያዣዋ ዉስጥ ከተተችዉ፤ ፍቅር ሲገለጥ እንዲህ ነዉና፡፡


////////////////////////************************////////////////////////
ጭፈራዉ ደርቷል፣ መጠጡ ጠቀድቷል፣ ሌሊቱ የደስታ ሌሊት ነዉ ወደ ዉስጥ ከቤቲ ጋር ሲገቡ ፉጨት ቤቱን አንቀጠቀጣት ሁላችሁም ዋንጫችሁን ለነገዋ ተጓዥ አንሱ ጠጡ ተደሰቱ አለ ዲጄዉ፤ ሁሉም ዋንጫዉን እንዳነሳ ቤቲ በመሃል በማስቆም ሁኔታ እጇን አጨበጨበች ፀጥታ ቤቱ ላይ ነገሰ ‹‹ አንድ ጊዜ ደስታችን ይቀጥላል የሁላችንም ጥያቄ የነበረዉ ምላሽ የሚያገኝበት ሰዓት ላይ ደርሰናል፤ ጓደኛችን ወደ መድረክ መጥታ በራሷ አንደበት የምስራቹን ትነግረናለች፡፡ ጓደኛዬ ወደ መድረክ …›› ብላ ወረደች፡፡
ጓደኞቼ ስላደረጋችሁልኝ ሽኝት በጣም አመሰግናለሁ፣ ያልጠበኩት ነገር ነዉ የተደረገልኝ፣ የናይት ክለቡንም ባለቤት እና ሰራተኞቹን በአጠቃላይ ላመሰግን እወዳለሁ፣ ሁላችሁም የፍቅራችሁን መግለጫ በአካልም በስልክም ዛሬም ከዚህም በፊት ሃሳቤን ካሳወኩበት ሰዓት ጀምሮ አትሂጂ ስትሉኝ ነበር፤ ነገር ግን አሁን ከመካከላችሁ ተለይተን በወጣንበት ሰዓት ዉስጥ በደረሰን መልዕክት ….( ደብዳቤዉን ከፍ አድርጋ እያሳየች) መሰረት … ድንገት የመዝናኛዉ ባለቤት ወደ ጆሮዋ ጠጋ ብሎ የሆነ ነገር ካላት በኋላ ‹‹ ይቅርታ መዝናናቱ ይቀጥላል ስላቋረጥኳችሁ ይቅርታ ያልጠበቅነዉ እንግዳ የመዝናኛ ቦታችንን በዛሬዉ ምሽት ለመዝናኛነት መርጠዉ ወደዚህ ስፍራ እየመጡ ስለሆነ በክብር እንቀበላቸዋለን፡፡ ወጪዉንም የዉጭ ጉዳይ ሚኒስተራችን ከታላቅ አክብሮት ጋር እንደሚሸፍኑት መልዕክታቸዉን አስተላልፈዋል፡፡ አመሰግናለሁ አሁን ወደ ዉስጥ በመግባት ላይ ስለሆኑ እንቀበላቸዉ ›› የተቋረጠዉ ደስታ እጥፍ ድርብ ሆኖ ቀጠለ ፉጨት ጭፈራዉ ቀለጠ እንግዶች ወደ ዉስጥ እየገቡ ናቸዉ ማይኩን እንደያዘች መድረኩ ላይ ያለችዉ ወጣት‹‹ …. ጉዞዬን መሰረዜን ልነግራችሁ ነዉ፤ ›› የሚገቡት እንግዶች አይናቸዉ በአጠቃላይ ወደ መድረኩ ነበር፤ አንደኛዉ ሰዉ ግን ባለበት ሳይንቀሳቀስ ደርቆ ቀረ እንግዳ ተብሎ አቀባበል የተደረገለት ሰዉ፣ መንግስት ይህንን ግብዣ ያዘጋጀለት ሰዉ፣ ሚዲያዎች ያንቆለጳጰሱት ሰዉ ከበደ፡፡ ሊዲያ አለ ደርቆ የቀረበት ቦታ ላይ እንደቆመ ማይኩን የያዘችዉ ለግላጋ ወጣት ስሟን ተጠራጠረችዉ ብዙ ዓመት ወደ ኋላ እዚህ አዳራሽ ዉስጥ ታሪኩን የሚያዉቅ በአካልም ያየዉ የሌለ ሰዉ የልጅነት ፍቅረኛዋ ከቤ፤ ከቤቤቤቤቤ…….. በያዘችዉ ማይክ ስሙን አስተጋባችዉ፡፡ ያ ትልቅ ሰዉ! ያ የተከበረ ሰዉ! ተጠመጠመባት፤ ….  ሊዲያ የዘመኔ ፍጻሜ፣ የምርቃቴ አክሊል፣ የክብሬ ዘዉድ፣ ካባ ላንቃዬ፤ ….
(የክፍል ስድስትና የአጋጣሚ መጨረሻ ) በትዕግሥት ስለተከታተላችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...