ዓርብ 4 ኤፕሪል 2014

ተማሪ ቤቴ



ተማሪ
ቤቴ


የማሪያም መቀነት በሰማይ ላይ ዉበት ፈጥራ በ..ር……ቀት ያየናት እንደሆነ
እኔ ነኝ እኔ ነኝ…እኔ ነኝ… በሚል በፍቅር እንጋጫለን እኔ ነኝ ቀድሜ ያየሁት ለማለትና የቀዳሚነቱን ስፍራ ለማግኘት፤(በሰማይ ላይ ይታዩ የነበሩ የቃል ኪዳን ምልክቶች ሁሉ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ላይታዩ የማሉ ይመስል ሰማዩ ጠቁሯል )
ከእንቅልፉ ዘግይቶ የተነሳ ቁርሱን አልበላ ያለ ትምህርት እንዳይረፍድበት ግማሽ ዳቦ ይቆረስና ይዘህ ብረር ይባላል፡፡በትናንሽ መዳፎቹ ብርር…….ርር እያለ እየከነፈ እየበረረ ……እ ….የ ….ቆነጠረ …… እየበላ….. እያስጎመጀን……እየበረረ ወደ እኛ ያቀናል …. ጥላ ስር…… ዛፎቹ…. ጎጆዎቹ ስር….. ….. ልንሰባሰብ ….. ፊደል ልንዘራ ….ልንበትን ልናጭድ ልንወቃ …. ደግመን ልንዘራ……
በርቀት ያየነዉ እንደሆነ ገሚሶቻችን ደስ ሲለን ገሚሶች ደግሞ እንደማብሸቅ ይቃጣናል፤
እንቅልፋሞ … እንቅልፋም …እን…ቅ…ልፋም እንቅልፋም …. እያልን ከፊት ከፊት እንሮጣለን ትንሽ ከኛ አቅሙ ሻል ካለ መግቢያ ቀዳዳ እስኪጠፋን እንሮጣለን (እንደዛሬዉ በሰርቪስ ፣ በኮንትራት ታክሲ ፣ ወላጅ እግረመንገዳቸዉን ጣል አርገዉ መሄድ የለም )
 ከፍሎ እንደ ሚሰጠን ያወቅን ደግሞ ወደርሱ ሮጥ ብለን ያልከፋዉን ሰዉ ለጥቅማችን ስንል አይዞህ በማለት እናባብለዋለን ፤ ከወዳጆቻችን ስለ ዳቦ እንኳረፋለን
አለሁልህ በሚል ስሜት ፀጉሩን እየደባበስን ከጎናችን ሸጉጠን እጅ እጁን እናያለን እርሱም የልማዳችንን የባቄላ ፍሬ የምታክል ዳቦ ቆርሶ ያቀምሰናል(ያሻጽትተናል)
እቺን ብቻ
ቆረስ ያደርግና ይጨምራል
ለኔስ ሌላኛዉ ይጠይቃል
ቆርሶ ይሰጠዋል
ሌላኛዉም ሲበር ይመጣል
ዳቦ የያዘበትን እጆች ወደኋላ ይደብቃቸዋል
ሲሮጥ የመጣዉ ክፍት ይለዉና አይኖቹ እምባ እንደማቅረር ይላሉ
እነዚያ ወደኋላ የሸሹት እጆች እዚያዉ መቆየት ይሳናቸዉና ትንሽ ቁራሽ ይዘዉ ይመጡና እንባ ያቀረሩትን አይኖች እንባ ያብሳሉ፤
ተረኛ መጋቢያችንን ግራና ቀኝ አጅበን ጎዞአችንን እንቀጥላለን እሱም ክብር ቢጤ እየተሰማችዉ ጀነን እያለ ያችን የተረፈች ዳቦ እንቁልልጨ እያለ ይዘባነናል፡፡
ያለደረሰዉ ባለተረኛ ፀጉሩን እያከከ ይጠጋል በእዩልኝ መንፈስ ትንሽ ቆርሶ ይሰጣል
ሌላዉ እንዲሁ ሲበር ይመጣና እጁን ይዘረጋል
እነዚያ መዳፎቸ የነማን እንደሆኑ ጀብራሬዉ ከመሃላችን ቀና ብሎ ይመለከትና ባለፈዉ አልሰጥህም አላልከኝም አልሰጥህም በማለት ብድራቱን በመመለስ አንጀቱን ቂቤ ያጠጣል
አኩራፊ የሆነ ጥሎ ሲሄድ ብልህ ቆሞ ይለምናል ሰጪም የዋህ ነዉና
እኔ እንዳንተ አደለሁም ይልና በደንብ ቆረስ አድርጎ በመስጠት ያስደስተዋል(ይበቀለዋል)፡፡
የቀረችዋን ቁራሽ እንዳለ ከአፉ ሲከታት እና እጁን እያራገፈ የሂዱልኝ በቃ አለቀ መልዕክቱን ስናይ ልጆች አይደለን ለዛዉም የሰዉ ልጅ የበላንበትን እጅ ጥለን ዉለታዉን ዘንግተን ቅድም ስር ስሩ እንዳላላልን ጥለነዉ እንበራለን፤….. ብርርርር……..ርር. ወደ ትምህርት ቤታችን የኔታ ጋር
ስንሮጥ ስንሮጥ …..ስንሮጥ ፣ ስንበር ስንበር….ስንበር ልባችን ድዉ ድዉ እያለች የኔታን በርቁ ስናያቸዉ የባሰ ልብ ምታችን ይጨምራል፤
እናንተ ልጆች ….
አቤት የኔታ…..(በተቆራረጠ ድምፅ)
እንደዉ ምን ላርጋችሁ? (በስጨት ይሉና)
ምንም! የኔታ (ሁላችንም በአንድ ድምፅ)  
ምንም? … (ንዴታቸዉ ይጨምራል) ሁላችንም በአንድ ድምፅ ማለታችን እየገባቸዉ ማነዉ ምንም ያለዉ ይሉናል በዚያ ቡቡ ልባቸዉ፤
እሱ ነዉ እሱ ነዉ… እ…ሱ እ….ሱ እ..እ..እሱ ነዉ የሚል ጫጫታ የየኔታን ዙሪያ ገባ ያደምቀዋል (የሰፈር ሰዉ የኔታ ትምህርት መጀመራቸዉን ያዉቅና ለልጆቹ ጩኸት ራሱን ያሰናዳል )
የኔታም አንዱን የፈረደበትን ይጠሩና በዚያ ደረቅ አርጩሜያቸዉ አለበለዚያም በጭራቸዉ ቸብ ቸብ ያድርጉትና
ማን ነዉ ተረኛ የሚያስቆጥር ብለዉ የተረኛዉን ማንነት ከሰማይ ገፅ ላይ ገልጠዉ እንደሚያነቡ ነገር የሰማዩን ፊት ቀና ብለዉ ይመለከታሉ፡፡ ከሄዱበት ሰማይ ቤት ሲመለሱ ተረኛዉ ከፊታቸዉ ቆሞ የማስጀመሪያዉን ቡራኬ ከርሳቸዉ ሊቀበል ከፊታቸዉ አንገቱን ሰበር አርጎ እየጠበቃቸዉ ነዉ፡፡
ያችን በብጫቂ ጨርቅ የተጠቀለለች ዘመናትን በመባረክ ያስቆጠረች የእንጨት መስቀላቸዉን አንገታቸዉ ላይ እንደተቋጠረች ጎንበስ በማለት አሳልመዉ ትምህርት ይጀመራል፡፡
የኔታ ለትንሽ ቆይታ ቃኘት ቃኘት ያደርጉና መስመር መያዙን ከተመለከቱ በኋላ አሁንም ዕድሜ የተጫናትን መነፅራቸዉን በእጅ ከተዘጋጀ ማስቀመጫ ከረጢታቸዉ በጥንቃቄ ካወጡ በኋላ በጥንቃቄ ካይናቸዉ ይሰኩና ዳዊታቸዉን ከማህደታቸዉ በማዉጣት ፀሎታቸዉን ይጀምራሉ፤ የየኔታን ዳዊት መግለጥ የተመለከተ አመለኛ ወሬዉን ያደራል፣ ይላፋል፣ይጣላል፣ደብቆ የያዛትን ጥሬ ይቆረጥማል….
የኔታ ምንም ዳዊት ቢደግሙ ማየት አያቋርጡምና እኛም በተለይ ጥሬዉን የሚቆረጥመዉን ጓደኛችንን ተለይቶ መብላቱን ቀንተንበት ይሁን ተናደን አይታወቅም ከዚህም ከዚያም የኔታ ….የኔታ…. ብለን ሰፈሩን በጥሪ እናቀልጠዋለን፤
የኔታ ከዓይናቸዉ የሰኳትን መነፅር ነቅለዉ ቀና ሲሉ ሁላችንም እናቀረቅራለን፡፡
ዝምታችንን ያዩ የኔታ ፀሎታቸዉን በአርምሞ ይቀጥላሉ ተረኛዉም ፊደል ማስቆጠሩን ካቆመበት ይቀጥላል፤
ሀ ግዕዝ (አስቆጣሪዉ)
ሀ ግዕዝ (ደማቅ በሆነ ጩኸት ቆጣሪዉ)
ሁ ካዕብ
ሁ ካዕብ
ሂ ሳልስ
ሂ ሳልስ
(ይቀጥላል…..)
                       ሸ…….
                  
አሁንም ይቀጥላል እኛም እንቀጥላለን
አስቆጣሪያችንም ድምፁ እየቀነሰ እየቀነሰ….እየ….ቀ…ነ …ሰ ሲሄድ ይባስ ብሎ የኛም ድምፅ በቁጥር እየመነመነ ሲሄድ የድምፁ ዉጥረት ረገብ ሲል ፀሃይዋ እየጠነከረች ሲሄድ የኔታም ሌሊት በአገልግሎት ብዛት ያጡትን እንቅልፍ ሸለብ አርጎአቸዋል፤
አስቆጣሪዉ ተረኛ ጣጣዉ ብዙ ነዉና ቀስ ብሎ ዳዊታቸዉን ተቀብሎ ከስራቸዉ ያስቀምጠዋል
ሀ ይላል
ሀ ይሉታል ጥቂት ከእንቅልፍ የተረፉትና የበረቱት
ሐ እጅግ በጣም ጥቂቶች
መ አሁንም እያነሱ እየሄዱ
….
….
ቀ ብሎ የሚመልስ አንድ ወይ ሁለት ሰዉ ነዉ
በ ሲል ሁሉ ተኝተዋል
ተ ይበል አይበል ማንም የሚሰማዉ የለም የኔታ ሲነቁ የሚደርስበትን የሚያዉቀዉ እሱ ስለሆነ እንዳፈጠጠ ቆሞ ይጠብቃል፡፡  
-----,,,*******---------,,,,,,
ከመቀመጫዉ ይሄድና የተጎሳቆለችዉን የፊደል ገበታ ወስዶ
መልዕክተ ዮሐንስን … ይደግማል
አሁንም ከጨረሰ ከአአትብ ገጽየ ይጀምርና አቡነ ዘበሰማያትን ፣ በሰላመ ቅዱስ ገብርኤልን ይዘልቀዋል…. አሁንም አሁንም ተማሪዎቹንና የኔታን ደጋግሞ እንቅልፍ በናፈቁ አይኖቹ ይመለከታቸዋል፤
ከመሃል አንዱ ሲዘል ያጠራቀማትን መድፉን(ፈሱን መሆኑ ነዉ) እምብዉ ሲያደርግ የተኛዉ ሁሉ አፍንጫዉን እዬያዘ የርሱ የራሱ ይሁን የማን እንደሆነ እያጣራ መቀመጫዉን ያስተካክላል፡፡
አንተ ነህ አንተ ነህ …. መወነጃጀሉ ይደራል፤
የኔታም ከድካማቸዉ ትንሽ ተንፈስ ብለዉ በልጆች ጫጫታ ከእንቅልፋቸዉ ይነቁና ዓይናቸዉን በጋቢያቸዉ ጫፍ እየጠራረጉ ዳዊታቸዉን ከእጃቸዉ ላይ ይፈልሁታል መዳፋቸዉ ዉስጥ መደበቂያ ዋሻ ያለ ይመስል …. አስቆጣሪዉ ካስቀመጠበት አንስቶ እጅ እየነሳ ያቀብላቸዋል፡፡
ብዙ ተኛሁ እንዴ አንተ ይሉታል በቀስታ
አልተኙም ፤…..ብሎ ይዋሻቸዋል
ሰማይዋን ቀና ብለዉ ይመለከቱና የዕረፍት ሰአት መድረሱን ለልጆቹ ያበስሩዋቸዋል፡፡
ልጆቹ በደስታ ብዛት ከተቀመጡበት እየበረሩ እየበረሩ ስፍራዉ አልበቃ ይላቸዋል ሰከን ብላ የነበረችዋን ሰፍር ቆሌዋን ይገፉዋታል፡፡ ሲያስቆጥር የነበረዉ ትንሽ ሮጥ ሮጥ ይልና አቅም ይከዳዉና ጫወታዉን ይተዉና ከተቀመጠበት ያንቀላፋል፡፡
የኔታ እንቅልፋቸዉን ስለጨረሱ ንቁ ናቸዉ፤ ተማሪዎችም አብረዉ ስላጠናቀቁና አንድም ስለሚፈሩዋቸዉ ማንም የሚጠኛ የለም ተኝቶ የተገኝ በየኔታ የሚደርስበትን ቅጣትና ተማሪዎቹ የሚስቁበትን ሳቅ ስለሚያዉቀዉ አይተኛም፡፡
--,,******************************++++++++++++++++++++++********************
የኔታ ተማሪዉን በመከፋፈል ትምህርቱን በአይነት በአይነት ያስቀጥሉታል
ፊደል የጨረሰዉ ፊደል አስጠኝ ይሆናል፣ ቁጥር የጨረሰዉ ቁጥር ያስቆጥራል….መልዕክተን …. አቡነ ዘበሰማያትን….ዳዊትን እያሉ ይከፋፍሉታል፤(የዛሬዎቹ የአስኮላ የኔታዎች ተማሪዎቻቸዉን ለቁምነገር እዉቀትን ለማስፋፋት ቢሆን  ጥሩ ነበር አንድ ለአምስት ማደራጀቱ መልካም ነበር ዉስጠ ወይራ ባይሆን ) እሳቸዉ ከተቀመጡበት የረበሸዉን ወገን ይሸመግላሉ፣ ይቀጣሉ፣ የተዛነፈዉን ያስተካክላሉ ወደ አዲስ ምዕራፍ ሲሸጋገሩ ብቻ መንገድ ያሳያሉ…. ከዚያ በተረፈ ይፀልያሉ፡፡ የኔታ መምህራችን! የኔታን ያኑርልን ! የየኔታን ዕድሜ ይጨምርልን! የየኔታን ዕድሜ ይስጠን! እንቀጥላለን፡፡      

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...