ዓርብ 11 ኤፕሪል 2014

ቴሌና መብራት የዘመን መቀሶች

አሁን አሁን ትናንት ተገናኝተን ዛሬ ስንገናኝም ጭምር ሳይቀር ጠፋህ/ሽ መባባል ባህላችን እየሆነ እንደመምጣቱ ያህል ተገናኝተንም ስንለያይ ስልክ እንዳለዉ እንኳን እርግጠኞች ሳንሆን ‹‹ደዉላለሁ›› መባባሉን እንደ ቻዉ እየቆጠርነዉ መጥተናል፡፡ እንደዚያ ሲሆን እኔም የዚያዉ አካል ነኝና ትናንት ከአንድ ጓደኛዬ ጋር አብረን አመሽተን ከተለያየን በኃላ ካልሸኘሁሽ/ህ ሳንባባል ተለያይተን ሁለታችንም ወደ ታክሲ መያዣችን ተበተንን፤ (ተበተኑ አይደል የሚለዉ ፌዴራል ፖሊስ ሁለት ሆነን ስንቆም እኔም በቅጂ አማርኛዉን ተጠቅሜያለሁ፤) እኔም መንገዴን አጋምሼ ሁለተኛዉን ወደ ሰፈሬ የሚወስደኝን የህዝብ ትራንስፖርት ከያዝኩ በኃላ ትራንስፖርት አግኝታ ወደቤቷ መግባቷን መጠየቅ ስለነበረብኝ ደወልኩ፤ የባጡን የቆጡን እያወራን መግባት አለመግባቷን ሳልጠይቅ ስልኩ ተቋረጥ፡፡ ብለዉ ብሰራዉ የቴሌ ኔትወርክ ሞቼ እገኛለሁ እናንተን ካገናኘሁ ብሎ ድርቅ አለ፤ አንዴ ‹‹የደወሉላቸዉን ደንበኛ ማግኘት አይችሉም›› ስትለኝ፣አንዴ ‹‹መስመሮቹ ሁሉ ለጊዜዉ ተይዟል›› ስትለኝ ፣ ተማርሬ ቆይቼ ደዉላለሁ ብዬ ተዉኩት …. ቆይቼ ለመሞከር ባስበኩት መሰረት የስልኬን ቁልፍ ከፍቼ ስሞክር ጢጢጥ እያለ ዝግት ፣ጢጢጥ እያለ ዝግት …. ነገሩ አልገባህ ሲለኝ ተዉኩት፡፡ እንዲህ እና እንዲህ እያልኩ ወደ ሰፈር ስቃረብ ይባስ መብራትም ጠፍቶ ‹‹በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ›› አይደል የሚባለዉ ‹‹እንኳንም እናቴ ሞታብኝ እንዲሁም አልቅስ አልቅስ ይለኛል›› ያለዉ ቴሌ እንኳንስ መብራት ኃያል መብራት አጥፍቶበት እያለም በቅጡ የማይሰራዉ የቴሌ ኔትወርክ ከጓደኛዬ ጋር እንዳንገናኝ ለያቶን አደረ፡፡
መቸስ እግዚአብሔር እንደ መብራት ኃይልና እንደ ቴሌ አይደለምና የጨለማዉን አስፈሪ ግርማ ሞገስ በብርሃን ተካዉና ቀኑን በብርሃን ሞልቶ ዛሬን በሰላም አገኘናት፤ ‹‹ጥረህ ግረህ የላብህን ወዝ ብላ›› ተብለናልና ቀኑን ሙሉ ላይ ታች ስንል ዉለን ከስራ መልስ፡፡ መቸስ ቴሌን ትላንት ለያይተኸናል ብለን አናኮርፈዉ ነገር ባቆራረጠን መስመር ዳግም ለመገናኘት የሞባይሌን ቁልፎች ተጭኜ
 ‹‹ሃሎ!›› አልኳት ጓደኛዬን 
ሃሎ! አልችኝ ርቀቱ የዉጭ ስልክ እስኪመስል ድረስ በሚርቅ ድምፅ (ሰሞኑን ‹አይሰማም› ሆኗል፤ የቴሌን ኔትወርክ የለከፈዉ ልክፍት፤ ለመሆኑ 75 አካባቢ ምናምን አጠናቀኩ ያለዉ በፊት የሚሰሩትን አቋርጦ ነዉ ወይስ ለማይሰራላቸዉ ሰርቶ ነዉ ያጠናቀቀዉ? ካካካ ….. )
ሃሎ ብለን የጀመርነዉን ሃሎ እያልን እንዳይቋረጥብን ወደ ገደለዉ እንደመግባት ትላንት የተቋረጠበትን ሁኔታ አንስተን የተቋረጠዉ በኔትወርክ ምክንያት እንደሆነ፣ እቤት ስገባ መብራት ባለመኖሩ ምክንያት እንዳልደወልኩ፣ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ባይኖረዉም በሳምንት ይመጣልን የነበረዉ ዉሃ ሳይመጣ እንደቀረ ሳወራት በስርአት ስታዳምጠኝ ከቆየች በኃላ መጨረሴን ስታዉቅ እንደጋዜጠኛ ‹‹እንግዲህ ያሉትን ሁሉ ምሬት እና አቤቱታ የሚመስል አስተያየት ሰምተናል በእርግጠኝነት የሚመለከታቸዉ የስራ ክፍሎች በሰፈራችሁ የተከሰተዉን ችግር የኔትወርክ መቆራረጥ፣የመብራት በተደጋጋሚ መጥፋት፣የዉሃ ችግር …. ሰምተዉ መፍትሄ እንደሚሰጧችሁ እርግጠኖች ነን…. ስለደወሉ እናመሰግናለን!›› ብላ ፍርስ ብላ ሳቀችብኝ፤ እሷም እየሳቀች ወደ ቤቷ እኔም ሳወራ የቀለለኝን ድብርት ይዤ ጨለማ ወደ ነገሰበት ሰፈሬ፡፡
በአገር ዉስጥም ከአገር ዉጭም ያላችሁ ወገኖቻችን ለትንሣኤ በዓል ደዉላችዉ ምናልባት ቴሌ ካገናኘን ‹‹የእንኳን አደረሳችሁ›› ምኞት መግለጫችሁን ስታስተላልፉ እኛ ስለ ስልክ እና መብራት መቋረጥ ብናወራችሁ አደራችሁን ቅር እንዳትሰኙብን! ከወዲሁ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡ ምን እናድርግ መንግስት አልሰማ ቢለን ለመንገደኛዉ ሁሉ እናወራ ጀመር እግረ መንገዱን መንግስት ጆሮ ይደርስ እንደሆነ ብልን፤ መንግስትም ቀጥታ ከምንነግረዉ በሃሜት መልኩ የሚወራዉን መስማት የጀመረ ይመስል ቀጥታ ለህዝቡ ጥያቄ መልስ ነፍጓል፡፡
መንግስታችን ለብቻችን ሆነን ያወራነዉን ነገር እምቢ ስላልከኝ ይኸዉ ሰዉ ፊት ታዛቢ አስቀምጬ ነዉ የምነግርህ እኛ ሰፈር ዉሃ፣መብራት፣ ስልክ …አማሮናልና መላ በለን! ድሮ ‹‹ወጥ እና ወንድም ማስፈራሪያ ነዉ›› እየተባልን ነበር ያደግነዉ አሁን ግን እራት ሰዓት ላይ ሻማ ይለኮስና አለበለዚያም የአንደኛችን የሞባይል ብርሃን ተጠቅመን እራት ስንበላ ዉሃ ቀርቦልን ‹‹ብርሃንና ዉሃ … ማስፈራሪያ ነዉ›› እንባል ጀምረናል፡፡ እንዲያዉም ሌላ ሰፈር እንደሰማሁት በእኛ ጊዜ ቀን  ላይ ስናጠፋ ማታ ጨላማ ሲሆን በር ተዘግቶብን በጨለማ ጨለማ ላይ በመቆም እንቀጣ ነበር፤ ዛሬ ይኸዉ ‹‹ደግ›› ልበለዉ እንጂ ደግ ዘመን ላይ ስንደርስ ህፃናት በመብራት/በብርሃን ይቀጡ ጀምረዋል ‹‹መብራት አብርቼ ነዉ የማስቀምጥህ እየተባለ›› አሉ፡፡ ብርሃንም እንደ ድሮ ጨለማ ለማስፈራሪያ ሆነ ሲባል ሰምቻለሁ… አቤት መጨረሻችን …እግዚኦ!
ምን እንደምፈራ ታዉቃልችሁ ዛሬ መብራት ሰፈራችን የለም፣ ዉሃ ተረኛ አይደለንም እንደምንለዉ ሁሉ ፈጣሪ የአፌን አይቁጠረዉና ዳቦ፣ እንጀራ፣ ጤፍ፣ስንዴ፣ሽንኩርት፣ዘይት …. ገበያ ላይ የሚገኙት በወረፋ እንዳይሆን ነዉ፡፡ ፈጣሪ ክፉዉን አርቆ ደጉን ያቅርብልን!
መብራት ኃይልን እንደ ቴሌ ፈርሶ በመሰራት ሰበብ ህዝቡን አያሳቁብን!(እንደምርቃት ነገር ስለሆነ አሜን እንበል ጎበዝ የደረሰበት ያዉቃልና እንኳን ፈርሶ የሚሰራ መስሪያ ቤት ፈርሶ የሚሰራ ቤት ራሱ በጣም ችግር አለዉና፤) በየሄድንበት ሁሉ ስለ ዉሃ፣መብራት እና ኔትወርክ መጥፋት የምናወራበት ሳይሆን አገራችን ነዳጅ አግኝታ ስለሱ የምናወራበትን ዘመን ያቅርብልን! (አሜን!)
የአባይ ግድብ በጠንካራ ክንዳችን ተገንብቶ መብራት ከሚጠፋበት ይልቅ የምንሸጥበትን ቀን ቅርብ ያድርገዉ! (አሜን!)
 ሳንቲም የሚሸጡ ልጆች ወልደን ከማሳደግ አገራችን ኢኮኖሚዋ ጣሪያ ነክቶ ለዜጎቿ የዜግነታቸዉ የምትከፍል አገር ያድርግልን!(አሜን!)
ዜጎቿ ተሰደዉ ሞቱ፣ገደሉ፣ራሳቸዉን አጠፉ፣ሲሰደዱ በረሃ ላይ ሞቱ፣ …. ከመባል ተላቀን ምዕራባዊያን ፣ አዉሮፓዉያን በዲቪ የሚመጡባት፣ ስራ አጥ በዛብን ብለዉ ለስራ ፍለጋ የሚሰደዱባት ያድርግልን!(አሜን!)
መንግስት ለመገልበጥ፣ ስልጣን ለመንጠቅ፣ … ብለን ከመሯሯጥ እግዚአብሔር ሰዉሮን መሪዎቻችን የስልጣን ዘመኔ ተጠናቋል የሚተካኝን መሪ ምረጡ ብሎ ለምርጫ ቦርድ ሲያሳዉቅ ‹አንተዉ ምራን›፣ ተመችተኸናል እባክህ አንድ የስልጣን ዘመን ድገም ‹‹በሞቴ አፈር ስሆን›› ብለን ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተን ስልጣን መልቀቁን የምንቃወምበት፣ የሰልፍ ፍቃድ የምንጠይቅበትን  ዘመን ፈጣሪ ያምጣልን!(አሜን!)  

ዘመናችንን እንዳናጣጥምበት መቀስ የሚሆኑብንን እግዚአብሔር ያርቅልን!(አሜን!)

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...