እሑድ 18 ሜይ 2014

ክፍል አምስት … … አጋጣሚ



ከመች ወዲህ ነዉ እንዲህ ማምሸት የጀመረችዉ? ከቤት እንዳትወጣ አላልኩሽም? ለመሆኑ ስንት ሰዓት ነዉ የወጣችዉ? ቆይ ስራ በቃኝ! ለተወሰነ ግዜ ማረፍ እፈልጋለሁ ብላ ሥራዋን በገዛ ፈቃዷ የለቀቀችዉ ለመዞር ነዉ እንዴ? እንደከብት እሷን ለመጠበቅ እኔ የግድ እዚህ መዋልና ማምሸት አለብኝ? …. … (ለጥያቄዎቿ መልስ የሚመልስላት ስታጣ ብቻዋን አዉርታ አዉርታ ሲበቃት ስልኳን መደወል ጀመረች፤ ) ደግሞ ስልኳንም ዘግታዋለች፡፡
ነይ እስኪ ወደዚህ ምንድን ነዉ አላማችሁ? ቆይ እስኪ እናንተ ከብቶች ናችሁ እንዴ ያለጥበቃ የማትኖሩት? አልበዛም እንዴ? (ቁጣዋ እየጨመረ መጣ የሚሰማት ሰዉ ግን አልነበረም፤) ምን ይዘጋሻል!
‹‹ እኔን ነዉ? ››
እና ማን አለ? እስካሁን የማወራዉ ለማን መስሎሻል?
‹‹ እስካሁን አዉሪ እንጂ አንዱም አይመለከተኝም፤ … … እኔኮ የቤቱ ጠባቂ እንጂ የሰዉ ጠባቂ አይደለሁም፡፡ ቆይ እስኪ ስራዬ ምንድን ነዉ? ገረድ ነኝ ወይስ እናንተ በተበጣበጣችሁ ቁጥር ሸምጋያችሁ ነኝ? ድርሻዬን አሳዉቁኝ …. ….›› ( በዚህ ቤት ዉስጥ ለመጀመሪያ ጊዜዋ ነዉ እንዲህ አይነት ቃላት ስትናገር፤ )
(ተፋጠዉ ተያዩ ጥፋተኛዉ ማን እንደሆነ መለየት እስኪከብድ ድረስ ዝምታ በመካከላቸዉ ሰፈነ) ‹‹ በያ ንገሪኝ፤ ሥራዬ ምንድነዉ? በቃ መልስ ከሌለሽ ሥራዬን ሳላዉቅ መኖር ስለማልፈልግ አሰናብቺኝ፡፡ ›› (ጆሮዋ ጭዉ አለባት የምትሰማዉን ማመን አቃታት)፤( የልብስ ማስቀመጫ የላስቲክ ሻንጣዋን ሰብስባ ሸኚኝ!) አለቻት፡፡
ቆይ ምን አጠፋሁ? ሁላችሁም እንደጠላት አያችሁኝ …. እሷ ከልጅነቷ ጀምሮ ልጅነቴን ትቼ ህይወቴን ሰዉቼ እንደልጅ እያየሁ የማስበዉን ነገር ሁሉ ለሷ ባደርግ አንድም ቀን ስትደሰት አላያት፤ ይልቅ …፡፡
‹‹ ደፈርሽኝ አትበይኝና … መቸስ እዚህ ቤት ከገባሁ ዓመታት ተቆጥረዋል የሁላችሁንም አመል ለይቼዋለሁ፤ … … አንቺም ለሁሉም እኔ ነኝ የማዉቅላችሁ ማለቱን ታበዢዋለሽ፡፡ እንኳን በከተማዉ በኛም አካባቢ ዛሬ ዛሬ እንዲህ አይነቱ ቀርቷል … … ሲጀመር ይህንን የእብድ ከተማ ሳትፈልግ ከእናቷ ነጥለሽ አመጣሻት፤ ሲቀጥል ለበዓል እንኳን እንደ ህጻን ልጅ ነዉ ይዘሻት የምትንቀሳቀሺዉ … ፡፡ በይ ሲልሽ ትልቋን ሴትዮ በስራ ቦታዋ እንኳን ሳይቀር ያለዉን ሁኔታዋን ካለተቆጣጠርኩሽ እያልሽ ጠዋት ማታ ሰላሟን ብትነሻት ሥራዋን ለቀቀች! ለቤት ዳረግሻት፤ እቤት መቀመጡ ቢሰለቻት ገና ዛሬ ብታመሽ የት ሄደች ብለሽ ጉሮሮዬን ይዘሽ አለቅ አልሽኝ፡፡ እስኪ በዚህ ሁኔታዋ ብትገናኙ እንዴት እንደምትጎጃት አስበሽበታል? ››

የኛ አሳቢ ማሰብም አልፈልግም!
‹‹ እንግዲያዉስ ከጎንሽ ታገኛታለሽ››
አታስፈራሪኝ! አታስፈራሪኝ … እኔ ልጅት ፈርቼም አላዉቅም፤ ፈሪ አይደለም ያሳደገኝ! … እሺ …. ምን ትላለች እቺ!
‹‹ ላስፈራራሽ ፈልጌ አይደልም የሰዉ ልጅ ደግሞ ምናልባት አዳፋ ስለለበሰ እቺ አይባልም አማርኛሽን አስተካክይ የፀዳ ብትለብሺ ያፀዳሁትና ለዚህ ክብር ያበቃሁሽ እኔ ገረድሽ እንደሆንኩ አትዘንጊ!...››
ይቅርታ! ስለተናደድኩ ነዉ፤….
‹‹ መጀመሪያም እየተነጋገርን ያለነዉ ስለተናደድሽ መስሎኝ የምናወራዉ፤ እንኳን አንቺ እኔ እንኳን በሰዉ ቤት ሰራተኝነት እየኖርኩ ሰልጥኛለሁ እድሜ ለአዲስ አበባ… ለራስሽ እወቂበት … ንዴት ማንንም አልጠቀመም፡፡ የደኸየበት እንጂ የበለፀገበት የለም፡፡ ሰማሽኝ?››
በሳል ልጅ ነሽ! በፍፁም … በፍፁም … አስቤዉ አላዉቅም፤ …
‹‹ እስኪ አንድ ነገር ልጠይቅሽ? … … ››
አስፈቅደሽኝ የጠየቅሽኝ ጊዜ መኖሩን አላዉቅም ነበር …
‹‹ ከባለቤቱ ያወቀ … ይባላል በኛ አገር እናንተ ደግሞ ምን እንደምትሉ አላዉቅም፤ ካንቺ አዉቃለሁ ብዬ አይደለም … ሰዎች ስንባል እግዚአብሔር የሚናገረንን አንሰማም! ሁሌ ግን ከቤቱ ተገኝተን በፀሎት እንለምነዋለን እሱ የሚመልስልንን ለማዳመጥ ግን ጊዜ የለንም፡፡ የአዲስ አበባ ሰዉ ታቦቱ ከየደጁ እያለለት ከእግዜር የራቀ ሰዉ ቢኖር እሱ ነዉ፤…. አንቺ ደግሞ አንዷ ነሽ! … እስኪ ለምንድን ነዉ ያላገባሽዉ? … ሰዉ ጠፍቶ ነዉ? …. ላንቺ የሚሆን ወንድ ስላልተወለደ ነዉ? … አይደለም፡፡ ….. ምን ለማለት እንደፈለኩ ገብቶሻል? …››
(እንደተስማማች ለመግለጽ ጭንቅላትዋን ላይ ታች ነቀነቀችዉ፤)
‹‹ ጠንቋይ ለራሱ ሳያዉቅ ለሰዉ አዉቃለሁ ማለቱ ነዉ ክፋቱ … አንቺም፤ …  (ቀና ብላ ተመለከተቻት፤) ለምንድን ነዉ እንኳን ሴቱ ወንዱ እዚህ ቤት አቀርቅሮ የሚኖረዉ? (አለማወቋን ለመግለጽ ጭንቅላቷን ግራና ቀኝ ወዘወዘችዉ) … አንድ ቀን … አንድ ቀን ጠብቂ … ›› (አቋረጠቻት)
ምን?
‹‹ ዲቃላ ….›› (አትጨርሺዉ! ጆሮዋን ይዛ አንገቷን ደፍታ ተቀመጠች)
‹‹ በቃ ሰዎች በህይወታቸዉ ጣልቃ ሲገባባቸዉ ህይወታቸዉ ፈሩን ይለቃል፤ ሳይወዱ የወለዱትን ይክዳሉ፣ … ያፈቀሩትን ይርቃሉ፣ … በተበላሸ ህይወት ዉስጥ እንዲዳክሩ ይገደዳሉ፡፡››
                           *** //////////////***********************//////////////***
‹‹ ባለፉት ዓመታት እኔ ባዳዋን የልቧን ስታጫዉተኝ ነበር፤ አንቺን ግን አብራችሁ የመዋል የማደራችሁን ያህል እንድትሰማሽ እንጂ ልትሰሚያት ዝግጁ ስላልሆንሽ ምንም ለማለት አትፈቅድም፤ ለምን ይመስልሻል ከሳሎን ይልቅ ማድቤ ከኔ ጋር የምትርሞጠሞጠዉ? ሙያ ለመማር? ስራ ልታግዘኝ? የሚመች ስፍራ ሆኖ ነዉ? አልነበረም፤ እህትሽ ልቧ ተሰብሯል፣ በአንቺ ጣልቃ ገብነት የምታፈቅረዉን ሰዉ አታለች፣ የማትፈልገዉን ህይወት ኖራለች፣ በድብቅ እየኖረች ስለነበረ በጨለማ ዉስጥ እንድትጓዝ ተገዳለች፣ … ዛሬ ደግሞ ዕድል ፊቷን ወደሷ ብታዞር አንቺም እንደገና ፊትሽን አዞርሽባት … እባክሽን ልለምንሽ ፊትሽን ከነዚህ ልጆች ላይ አንሺ! ›› (ጆሮ ግንዷ ላይ የሚጮኸዉ ነገር ድምፁ እየጨመረ ሄደ፤)
                             ////////////************/////***********/////////////
ጣፋጭ ከንፈሮች እንደነበሩህ ታዉቅ ነበር?
‹‹ ዛሬ ነዉ ቀምሼ ያረጋገጥኩት ብዬ እንድዋሽሽ ትፈልጊያለሽ? ››
ዉሸት አልፈልግም፤ ህይወቴ የተሞላዉ ዉሸት እና ድብብቆሽ ነዉ …
‹‹ ምን ማለት ነዉ? …››
እንዲህ አይነት ጥያቄም ሁለተኛ እንዳትጠይቀኝ፤ ከዚህ በኋላ መዋሸትም ሆነ እንድዋሽ አልፈልግም … የጠለሸ ማንነቴን በፍቅር ፀበል ማንጻት ብቻ ነዉ የምፈልገዉ ….
‹‹ ጥሩ ጊዜ ነበር ያሳለፍነዉ … በጣም ነበር ደስ ያለኝ፤ ….››
ይቅርታ ግን ከቤትህ መጥቼ አሳሳትኩህ አይደል?
‹‹ ቤት የእግዚአብሔር ነዉ ፍቅርም እግዚአብሔር ነዉ ስለዚህ በእርሱ በቤቱ ተገኘን ማለት ነዉ፤ ››
አሁን ጊዜዉ እየሄደ ስለሆነ እንዉጣ አይደል?
‹‹ ለምን ትንሽ አትጫወችም መክሰስ ነገርም ልስራና ባይሆን በልተሸ … ››
አይሻልህም ባድር? ጥሩ ትቀልዳለህ አይደል እቤትህ እንድመጣ ካረከኝ በኋላ ከንፈሬን ስትመጥ ስትመጥ ከዋልክ በኋላ ደግሞ ምን ቀረህና ነዉ ‹‹ ባይሆን ›› የምትለዉ? (ኮስተር ብላ ስታናግረዉ የምትለዉ ሁሉ ተምታታበት)
‹‹ እንዴ … እ… አንቺ …እ… ››
አትንተባተብ ራሴ ነኝ የመጣሁት አዉቄ ነዉ፤ ተነስ አሁን እንሂድ!
‹‹ በቃ መሄድሽ ካለቀረ ገላሽን ለቅለቅ በይና … ››
ይህን ጠረንማ ዉሃ ሲወስደዉ ማየት አልችልም፤ ባይሆን ልብሶቼን አቀብለኝ ….
‹‹ መታጠብማ አለብሽ እኔም መታጠብ ስለምፈልግ አብረን እንታጠባለን… ››
ታዲያ እንደዛ አትልም እንዴ የምን ዙሪያ ጥምጥም ትሄድብኛለህ እንደ ሊማሊሞ መንገድ ….
‹‹ ሊማሊሞን ታዉቂዋለሽ እንዴ?››
ወንድሜ ሹፌር ነዉ፤ እሱ ነዉ የሚነግረኝ አስጎብኚ ነዉ ….
‹‹ በቃ ነይ እንታጠብ …››
ራቁቴን እኮ ነኝ ፎጣ አቀብለኝ፤ …. ቆይ ቆይ ማነዉ ልብሴን በጠቅላላ ከገላዬ ላይ ያወላለቃቸዉ? ሰክሬ ነበር እንዴ ፓስታዉ የተሰራዉ በአልኮል ነዉ እንዴ? መቸስ የሚጠጣ አልቀመስንም፤ …
‹‹ ራቁትሽን መሆንሽን ማን ነገረሽ? ቅድም እንደዚሁ አልነበረ እንዴ ከኔ ጋር ተኝተሸ እንደዛ ነፍሳችንን በገነት ዛፍ ስር ፍቅራችንን ስንቀጭ የነበረዉ፤  ራቁትሽን ነዉ ያገኘሁሽ ራስሽ ታወልቂ መላዕክት ያዉልቁልሽ እኔ የማዉቀዉ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን የጎደለ አካል ካለሽ ከቤት ሳትወጪ ፈልጊ በኋላ … ››
በኋላ ምን?
‹‹ የተወረሰ ንብረት አይመለስም ፤ …. ››
አሁን ዓይናችን ስለተገለጠ መደበቅ ፈለኩ ልደበቅ፤….
‹‹ በዓይኔ ብርሃን ላይሽ ብፈልግስ?››
ትሳሳታለህ አለበለዚያም ትሳሳልኛለህ፤ እነዚህ የፈኩ የፍቅር አበቦች፣ እነዚህ ያጎቸጎቹ የፍቅር ነዶ ክምሮች፣ እነዚህ የማር ወለላ የመሰሉ ንፁህ ፍቱን መድሃኒቶች፣ … በእህቷ ጭካኔ እንዲህ አጉል ሲሆኑ ስታይ ትንሰፈሰፍልኛለህ! የወንድነት ጭካኔህ ካየለብህ ትጨክንብኛለህ! የቆመ ለወደቀ አያዝንምና በቆመዉ ምሳርህ የወደቀ ማንነቴን ትቆርጥብኛለህ …. ይቅርብን፡፡
‹‹ ግዴለሽም እሺ በይኝ …››
አሳየሁህ ተንሰፈሰፍክ አይደል? ወንድ ሲባልኮ ያደረ ነገር ያመዉ ይመስል ለነገ የምትሉት ነገር የለም አይደል? ሁሉንም በአንድ ቀን አጠናቃችሁ ወደላይ ሲላችሁ ማደሩን ነዉ የምትፈልጉት፡፡
‹‹ እኔ እንደዛ አይደለሁም … እሳት የጫርንበትን ስስ ገላችንን በዉሃ እንድናቀዘቅዘዉ ፈልጌ ነዉ ››
ለነገሩ አንተ ሸኝተኸኝ ስትመለስ ባዶ ቤት ስለሚጠብቅህ መቀዝቀዝ ስላለብህ እሺ እኔ ግን እህቴ ስላለችልኝ እንኳንስ ገላዬ ነፍሴም በረዶ ስለምትሰራ ግዴለኝም፤ … ና! እንታጠብ (በማለት ያሻረጠችዉን ፎጣ ጥላ ራቁቷን ወደ መታጠቢያ ክፍል አመራች)፤ (ዝምታ በመካከላቸዉ እንደሰፈነ ከላይ የሚወርደዉ ቀዝቃዛ ዉሃ በገላቸዉ ላይ ሲያርፍ እየፈላ ያለ ይመስል እንፋሎት ይወጣዉ እንደነበር ማንኛቸዉም አያዉቁትም ነበር፤ ዝምታ ፊታዉራሪ ፍቅር ቀኛዝማች የሆነበት ጊዜ  ላይ ናቸዉ፡፡ )
ቅድምኮ በማለት ዝምታዉን ሰበረችዉ ….
‹‹ ቅድም …ምን?››
ስልክ ስታወራ፤
‹‹ መቼ?››
ቅድም ነዋ የሆነች ልጅ ስሟን የማላዉቃት….
‹‹ ከቢሮኮ ነዉ ፤ …››
ባክህ አሁንማ ገብቶኛል! ባይገባኝ እዚህ ዉስጥ ገባልህ ነበር? … ግን በጣም ነበር የተናደድኩት፤
‹‹ ለምን? ››
ለምን ብለህ አትጠይቀኝ ስንቴ ነዉ የምነግርህ፤ … ብዙ ‹‹ለምን?›› የሚባሉ ጥያቄዎች በህይወታችን ዉስጥ መልስ ላይኖራቸዉ ዝም ብለዉ የተነሱ ጥያቄዎች ናቸዉ፡፡
‹‹ ለምሳሌ ….››
አሁን እንዲህ መሆናችን ራሱ ለምን ተብሎ ቢጠየቅ መልሱ ከዝምታ በቀር ምንም አይደለም፡፡
‹‹ በቃ እሱን እርሺዉ፤ …››
አየህ አይደል ለምን እንደምትሸሽ መልስ ስለሌላቸዉ ነዉ፤ … ግንኮ መልስ አለዉ ዉስጣችን ባለ ዉሸት ስለሚጫን አለበለዚያም ስሜታችን እኔ ቀድማለሁ እኔ ቀድማለሁ ግብ ግብ ስለሚይዙ መልሱን እንዘለዋለን … እንደጊዜ ማባከንም እንቆጥረዋለን፡፡
 ግን ደስ ብሎሃል?
‹‹ እንደዚያ ተብሎ አይጠየቅም ባይሆን ምን ያህል ደስ እንዳለኝ ጊዜ ካለሽ መለካት የነበረብሽ አንቺ ነበርሽ …››
እስኪ ምኔን ወደድከዉ?
‹‹ ሁለመናሽን …››
ዘርዝራቸዋ!
‹‹ ስንቱን ልዘርዝር ከላይ ብጀምር ፀጉርሽ፣ ግንባርሽ፣ ዓይንሽ፣ አፍንጫሽ፣ …. እ…. ‹‹ከንፈር›› የሚለዉን ስሙን ለመጥራት አቅም ያነሰዉ ይመስል በአመላካች ጣቱ ከንፈሯን፣አገጯን፣ አንገቷን፣ … እየነካ እየዳሰሰ … ከላይ በሚወርደዉ ዉሃ መካከል በስስት እየተመለከታት ፀጥታ ነግሶ፣ የልባቸዉ ምት ፀጥታዉን እያደፈረሰ፣ ዉሃዉ ዉበት ይዞ እየሄደ፣ ፍቅር ይዞ እየመጣ፣…. ደሳሳዉ ከአንገቷ ወርዶ ደረቷን ሰንጥቆ እንዳለፈ ሁለት መንታ መንገድ ሲያጋጥመዉ አመልካች ጣቱ አቅም አነሰዉ ቀጭን ወገቧን አንቀዉ የያዙ እጆቹ እርዳታ ተጠይቀዉ የመጡ ይመስል ያንን መንታ መንገድ ግራ ቀኝ አሳብረዉ የጤፍ ክምር ይመስር በጥንቃቄ የተሰሩ ጉብታዎች መፈልፈል ጀመሩ፤ ፍሬዉን መሸከም እንዳቃተዉ የማሽላ ተክል አንገቷ ጭንቅላቷን መሸከም ተስኖት ደረቱ ላይ ስብር አለ፡፡ የወደዳቸዉን ነገሮች ይዘረዝሩ የነበሩ የተባበሩት እጆቹ ከስፍራዉ ተነስተዉ እንብርቷን እንደጠቆሙ አቅም ሲያንሳቸዉ ወገቧ ላይ ለማረፈ ተገደዱ እጆቹ ወገቧ ላይ እንዳረፉ እጆቿም አንገቱ ላይ ተጠመጠሙ፡፡ አፏ በአፉ ዉስጥ ቀለጠ፤ እንደፀበል አንዳቸዉ በአንዳቸዉ ተፀብለዉ ተፈወሱ….. ፡፡ ››
               *******////////////*****///////*******
ከቤ የዩኒቨርቲ ትምህርቱን ባጠናቀቀበት በባህርዳር ዩኒቨርስቲ የማስተማሩን ስራ እንደቀጠለ ቤተሰብ ጥየቃ እንኳን ብሎ ወደ አገሩ አልተመለሰም፣ ቤተሰቡንም ያገኛቸዉ ለምርቃት እንደመጡ ብቻ ነዉ፤ ከዚያ በተረፈ በልጅነቱ በደረሰበት የልብ ስብራት ወደ አገሩ የመመለስ ህልም የለዉም፡፡
ይሁን እንጂ የግድ ቀን ስለመጣ አሁን የትምህርት ዕድል አጋጥሞት በአስቸኳይ ሊሄድ ስለሆነ አቅመ ደካማ እና ድሃ ቤተሰቦቹን ሊሰናበት ወደ አገሩ መጥቷል፤ አሁንም በልቡ ያለችዉን የልጅነት ፍቅረኛዉን በልብ እንደስንቅ ይዞ ባህር ለመሻገር ቤተሰቡን እየተሰናበተ ይገኛል፡፡ ከቤ ምናልባት ትምህርቱን እስኪጨርስ ድረስ ቤተሰቦቹ በህይወት ካሉ ሊመለስ ይችላል፤ አለበለዚያ ግን እንደሌሎች ኢትዮጵያዉያን ጓደኞቹ ስደተኛ ሆኖ ይህን የዕዉቀት ሃብቱን ለባእዳን ያዉለዋል፡፡እምዬ ኢትዮጵያም እንደገና በሱ የወላድ መካን ትሆናለች፡፡አይ ጭንቅላት! ምናለ ተጨማሪ የትምህርት ዕድሉ በቀረበትና ያለዉን ላገሩ ባዋለዉ፡፡
                       ፡፡******************////////////////******************፡፡
በስድስተኛዉ ክፍል ያገናኝን!

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...