ቅዳሜ 22 ኦገስት 2020

እራስን ተጠያቂ ማድረግ መለማመድ (ክፍል አንድ)

 

እራስን ተጠያቂ ማድረግ መለማመድ
ክፍል አንድ
ነሐሴ 10/2012 አ.ም
ነገሩ እንዲህ ነው፤ ዛፎች ስለሆነባቸው፣ እየሆነባቸው ስላለ፣ ሊሆንባቸው ስላለው ጉዳይ ለመምከር ስብሰባ ተቀመጡ።
አጀንዳዎቻቸውን አንድ በአንድ ነቅሰው አውጥተው ከተወያዩ እና በብዙ ጉዳይ መግባባት ላይ ከደረሱ በኋላ በአንደኛው አብይ ጉዳይ ላይ መግባባት ባለመደረሱ ምክንያት ስብሰባው አጀንዳውን በይደር አሳድሮ ተስማምቶ ተበተነ።
በበነጋታው በተለመደው ሰአት፣ በተለመደው ቦታ፣ ሁሌም በስብሰባው ላይ የሌሎች ዛፎች ጥቃት የኛም ጥቃት ነው የነርሱ ጉዳት እኛንም ያገባናል የሚሉ ገንቢ ሐሳብ ለመስጠት ውይይቱን በሐሳባቸው ለማዳበር፣ የተጣመመውን ለማቃናት፣ የጎበጠውን ለማቅናት፣ የጎደለውን ለመሙላት፣ ወዘተ የሚገኙ የተለመዱ ዛፎች በመሰብሰቢያው ዋርካ ጥላ ስር ተሰድረዋል።
ሰብሳቢውና ምክትል ሰብሳቢው በሰአታቸው ቢገኙም ጸሐፊው የክብር መዝገቡን ይዞ በሰአቱ ባለመገኘቱ የስብሰባው መጀመሪያ ሰአት ወደፊት ገፍቷል።
በዚህም የተነሳ ብዙዎች ዛፎች ማጉረምረም ጀምረዋል። ከየቦታው የግል ወሬ፣ ሐሜት፣ በትናንትናው እለት ፋይላቸው የተዘጉትን ጉዳዮች በተናጠል እያነሱ ክርክር ጦፏል፣ አስተያየት ሰጪ ዛፎችን ትችት እና ድጋፍ በየቦታው ይወራ ጀመር፣ ገሚሱ ስብሰባው ላይ መገኘቱን እየኮነነ ያልተገኙትን ዛፎች ማድነቅ ተያይዞታል፣ ...
ከመድርኩ ላይ ተገማሽረው የተቀመጡት ምክትል ሰብሳቢ ጠና ያሉ ዛፍ የጊዜውን መሄድ ጀንበሯን በመመልከት ወደ ዋናው ሰብሳቢ ጆሮ ጠጋ በማለት አንሾካሸኩ ዋና ሰብሳቢው ዛፍም ሰአቱ በመሄዱ እና በጸሐፊው ማርፈድ መጨነቃቸው ከፊታቸው ላይ ይነበባል። ከአንደበታቸው አውጥተው አይናገሩት እንጂ ብስጭትም ይታይባቸዋል። ምላሻቸውን ጭንቅላታቸውን በመነቅነቅ ገለጡላቸው።
ተሰብሳቢው ጫጫታው የንብ መንጋ መስሏል ድምጹ በአራቱም አቅጣጫ ይተማል። አንዳንዶችም አርፋጆች እየተንጠባጠቡ ያልተጀመረውን ስብሰባ ምንም እንዳልተፈጠረ ማርፈዳቸው እንኳን ሳይታወቃቸው ይቀላቀሉ ጀመር።
የስብሰባው አጀንዳ ይለያይ እንጂ የስብሰባው ይዘት እና የተሰብሳቢ ግዴለሾች መብዛት ከሰው ልጅ ስብሰባ ጋር ብዙ አንድ የሚያደርገው ነገር አለ።
ጸሐፊው እየተንጎማለሉ በተሰብሳቢው መካከል አአልፈው መድረኩ ላይ ተሰየሙ፤ መዝገባቸውን ገለጥ ገለጥ አደረጉ፣ ከደረት ኪሳቸው የንባብ መነጥራቸውን አወጡ ... "ጸጥታ" አሉ። ፍየል ከመድረሷ ... አሉ አበው። የሰማቸው አልነበረም። አሁንም "ጸጥታ" አሉ ... ድምጹ በረታ። ድምጻቸውን ለማስተካከል በሚመስል ሁኔታ ጉሮሯቸውን ጠራረጉ። ይኸን ጊዜ የድምጡ ሃያልነት ጋብ እያለ መጣ።
ሰብሳቢው ዛፍ የምንተፍረታቸውን ተሰብሳቢውን ይቅርታ ጠየቁ።
የተሰብሳቢው ዛፍ ቁጣ ጨመረ፣ ማጉረምረሙ በረታ፣ ተቃውሞቸውን በጭብጨባም በፉጨትም ገለጡ ... ተቃውሞው ጸሐፊው አርፍደው መጥተው ይቅርታ መጠየቅ ሲገባቸው እንዴት ከኛ እኩል የተገኙት ሰብሳቢ ይቅርታ ይጠይቃሉ አይነት እንድምታ አለው።
ስብሰባው ተጀመረ።
ሐሳቦች መንሸራሸር ጀመሩ።
ጉርምርምታ አልፎ አልፎ እንዳለ ነው፤ ከሚሰጠው አስተያየት በይዘትም በጥራትም ጉርምርምታው ውስጥ ይንጸባረቅ ነበር። ነገር ግን እጃቸውን አውጥተው የመናገር መብታቸውን ተጠቅመው አይናገሩም፣ አስተያየታቸውን አይሰጡም፣ ወይ ተቋውሟቸውን አይገልጡም። ዛፎችንም ከሰው የሚያመሳስላቸው ጸባይ ያለ ይመስላል።
ጉርምርምታው ይኑር እንጂ ስብሰባው ቀጥሏል አስተያየቶችም ከየቦታው ይሰጣሉ።
አለመግባባቶች በረቱ፤
ደርበብ ያሉት ምክትል ሰብሳቢ ተናጋሪውን ዛፍ እና የሚያጉረመርሙትን በመሃል እያቋረጡ፥ ይቅርታ ዛፎች ሳቋርጣችሁ እጅግ እያፈርኩ ነው። ጭርንጫፎቻቸውን በሐዘኔታ እየነቀነቁ "ምን ነካን?
ኧረ ተው ሰሚ ምን ይለናል?
ተመልካችስ ቢሆን?
ለአገር ምድሩ ለሰው ቢባል ለእንስሳ ስንት አይነት መድሃኒት እየሆንን እንዴት ለራሳችን ጊዜ አንዲት መፍትሔ እንጣ ... ዛፎች? ኧረ ተው ኧረ እግዜሩስ ምን ይላል? ከምድር በታች ያሉትስ አባቶቻችን አያዝኑብንም?" አሉ እጅግ በመከፋት።
ስብሰባው ቀጠለ፤
ስርአት አልበኛው እና ቆንጠር ቆንጠር የሚሉት አጭሩ ጸሐፊ ቆጣ ብለው "ስርአት ይዛችሁ ስብሰባውን ትከታተሉ እንደሁ ተከታተሉ አንዳንድ የምትረብሹ ዛፎችም አደብ ብትገዙ ይሻላል። አይ የምትሉ ከሆነ ደግሞ በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት ቅጣቱን መጣል አቅቶን አይደለም ትዕግስታችን በርትቶ እንጂ ..."
የተሰብሳቢው ጫጫታ የጸሐፊውን ንግግር አቋረጣቸው፤ ጸሐፊው አርፍደው ከመምጣታቸው ይቅርታ አለመጠየቃቸው ከዚያም አልፎ ተርፎ ሥርአት ለማስያዝ ስለቅጣት ማንሳታቸው ዛፎችን አስቆጣቸው።
ሰብሳቢው ራሳቸውን ታመሙ በሰላም ተጀምሮ በሰላም ይጠናቀቃል ብለው ያሰቡት ስብሰባ በመዘግየት ተጀምሮ በጭቅጭቅ እና በንትርክ አጀንዳው ላይ ረብ ያለው ሐሳብ ሳይነሳ ሰአቱ ነጎደ።
ለግላጋ ቁመና ያላቸው ዛፍ ከመቀመጫቸው ብድግ አሉ እርሳቸው ከመቀመጫቸው ብድግ ሲሉ የመሰብሰቢያው ዋርካ ቅጠሎች ረገፉ፤ ጎንበስ ብለው ተሰብሳቢውን ይቅርታ ሲጠይቁ ጸጥታ ሰፈነ፣ ሠላም ወረደ በጫጫታው ምክንያት እየጨመረ የመጣ ሙቀት ረገብ አለ።
ስብሰባው በተለመደው ግርማ ሞገሱ ተጀመረ ስርአት ነገሰ።
ተናጋሪ ሲናገር አድማጭ ጸጥ አለ፤
አስተያየቱን ሲጨርስ ደጋፊ ሲያጨበጭብ ተቃዋሚ አልያም ሌላ አስተያየት ያለው እጅ በማውጣት ሐሳቡን መሥጠት ቀጠለ።
ይሁን እንጂ ምንም የረባ፣ ለመፍትሔ የቀረበ አስተያየት እስከ አሁን አልተሰነዘረም።
ሁሉም አስተያየቶች ከመፍትሔው ይልቅ ችግሩ ላይ ያጠነጠኑ ውይይቶች ነበሩ።
እርግጠኛ ሆኖ ከሚናገረው ይልቅ ይመስለኛል እያለ የሚናገረው አስተያየት በቁጥር ይበዛ ነበር።
ጊዜው እየገፋ ተሰብሳቢውም እየተሰላቸ ሰብሳቢዎችም ስብሰባው በይደር እንዳይቀጥል በስጋት እየተዋጡ ተሰብሳቢዎችም ጉዳያቸውን ከመጤፍ ሳይቆጥሩ ስብሰባውን እየተው ሹልክ እያሉ መውጣት ጀምረዋል።
ይህ ድርጊት ደግሞ የሰብሳቢዎችን እና የቀሩትን ተሰብሳቢ ቀልብ እየሰረቀው መጣ።
አስተያየት ስጪዎች ሐሳብ ከመጨረሳቸው የተነሳ ይሁን ምክንያቱ በውል ባልታወቀ ምክንያት እየተነሱ እገሌ እንዳለው እያሉ አስተያየት በመሥጠት ተሰብሳቢውን አሰለቹት፦
"አካሄድ" አሉ ጸሐፊው "እባካችሁ ጊዜያችሁን ለመጠቀም ሌሎች ያነሱትን ሐሳብ ስለያዝን አትድገሙት አዲስ ሐሳብ ከሌላችሁ ስብሰባውን እንጠቅልለው" አሉ። ሲመጡ አርፍደው ለመሄድ ፈጣን የሆኑ ኮሚቴ እግዜር ይሰውር።
ሰብሳቢው ስብሰባውን እየመሩ እንደሆነ ለማጠየቅ በተረጋጋ መንፈስ "ግድየለም ይምሽ ይኸንን ጉዳይ ሳንቋጭ ለተበዳዮች መፍትሔ ሳናመጣ፣ እንባቸውን ሳናብስ፣ እልቂታቸውን ማቆም ቢያቅተን መቀነስ የሚያስችል መፍትሔ ሳናመጣ ጉባኤው አይፈታም" አሉ።
አስተዋይ ይኑር።
በእድሜ ጠና ያሉት ዋርካ ወገባቸው እየተንቋቋ ከመቀመጫቸው ብድግ እንደማለት አሉ፥
ሁሉም ዛፍ በአንድ ድምጽ ይቀመጡ አይነሱ ... በአባቶቻችን ተቀምጠው ይናገሩ ... አሏቸው።
ግድየለም እግዜሩም እናንተም እንድትሱሙኝ ቁሜ ልናገር ብለው ተነሱ።
በክፍል ሁለት የቀረውን እንድንቀጥል ይቆየን።
የቴሌግራም አድራሻዬ ይከታተሉኝ።
ለሎሎች ይደርሳቸው ዘንድ ማጋራትን አይርሱ።
ሐሳብ አስተያየትዎን ለመስጠት አይቆጠቡ።
ነሐሴ 10/2012 አ.ም
ደረሰ ረታ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...