ቅዳሜ 22 ኦገስት 2020

የአዳል በግ

 

አንዱ ደወለልኝና የአገራችን ደቡባዊት ከተማ ስም ጠራልኝና እዛ ከተማ ውስጥ እና ዙርያዋ የሚገኙ ወጣቶች የአዳል በጎች ናቸው እንዴ? አለኝ።
እኔ እስከማውቀው የአዳል በግ ባለቤት/ባለበጉ ያልሆነ ከግልገልነት እስከ ሙክትነት እድሜው ዘወር ብሎ ያላየው ገዝቶ እየነዳ ወስዶ የሚያተርፍበት፣ የገዛ አርዶ አወራርዶ ነግዶ የሚያተርፍበት፣ ሌላው የደላው ደግሞ በልቶ ከርሱን የሚሞላበት ነው።
ሻጭም በርሱ ስሜት እየለካ በጉን ብሔርና ክልል ይሰጠዋል፤ ከበግነት ማንነት የአዳል በግነት መለያ ያላብሰዋል።የበጉን ሥጋና ቆዳ አዋዶ ይሸጠዋል።
ይሕንን የዋህ ሲጠሩት አቤት፣ ሲሸጡት ገዢን ተከትሎ የሚሄድ፣ ሲያርዱት ለምን ብሎ በማይጠይቅ በግ ለሰው የተመሰለው፤ ለዚያውም በክፉ ሰው ከሰውነት ልክ በወረደ ክብርን ጠርቶ ውርደትን በመረጠ ሰው አለማቀፋዊ ማንነቱን በውስን ሥፍራ በጠባብ መንደር በብሔር የተሸበበ ሰውን ይወክል ዘንድ የተገደደ በግ ነው። የአዳል በግ።
እነዚህ ሰወች ደግሞ ከሰውም ይልቅ ለአውሬነት የሚቀርቡ፣ አውሬያዊ ጸባይ ያላቸው። ሰውን ቁልቁል ዘቅዝቀው የሚሰቅሉ፣ ብሔርን መሰረት አድርገው ለይተው ገድለው አስክሬንን የሚያክል ነገር ያለ ባህላችንና እምነታችን መሬት ለመሬት የሚጎትቱ፣ እንደ አገር ድሃ እና ለማኝ አገር፣ እንደ ሕዝብ ለሰው ልጅ የሚገባውን የተመጣጠነ ምግብ መመገብ አይደለም በአግባቡ በልተን የማናድር፣ እንዲሁ ብሔርና ሐይማኖትን መሠረት በማድረግ ሐብት ንብረትን ለማውደም እንደ መንጋ የሚነዱ፣ መንግሥትን ያህል ተቋም በጥቅም በመገዛት ለዚያውም ለጠላት አገር መንግሥት ለመገልበጥ ላይ ታች የሚሉ የሰው እንክርዳዶች።
እነዚህ ናቸው በየዋሁ በግ የተመሰሉት፤ በአንድ በኩል እውነትም ሲታዩ በጎች ናቸው ለሚያርዳቸው የሚታዘዙ፣ ገድሎና ዘልዝሎ ሊበላቸው ከቋመጠ ጋር የሚውሉ። በሬ ካራጁ እንዲሉ። ክፋታቸው እንዳለ ሆኖ ያሳዝናሉ።
እንደ በግ ግር የሚሉ፣ የማያስቡ የማያስተውሉ፣ የሚጠቅማቸውን ለይተው የማያውቁ። ከትናንት ውድቀትና ስህተት የማይማሩ። አልፎ ተርፎ ከራሳቸውም ሥህተት ጭምር የማይማሩ።
ይህ ጓደኛዬ ስለነዚህ ወጣቶች ሲያወራልኝ በስሜት ነበር በውስጡ የሚንተከተከው ደም የቆዳውን ከለር እስኪቀይር ነበር ደሙ ፈልቶ በስሜት እያወራኝ ያለው።
እውነት ግን ምን ሆነናል?
ምንስ እየሆንን ነው?
ምንድን ነው የነካን?
እስከማውቀው ኢትዮጵያዊነት እንዲህ አልነበረም፤ እርግጥ ነው ጥንትም አንዳንድ አገርና ሕዝብን ለጥቅም ሲሉ አሳልፈው የሚሸጡ አሉ። ነበሩም በመጠን እና በይዘታቸው ግን ይሕን እንደማያክሉ የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ። "የአበሻ ጀብዱ" የሚለው መጽሐፍ ቋሚ ምሥክር ነውና።
ይህ ተግባር ጓደኛዬ በጠቀሳት አንዲት ከተማ የተወሰነ የተወገዘ ተግባር ብቻ አይደለም። ዋና ከተማችንን ጨምሮ እንጂ።
የወደሙ ሐብት ንብረቶች፣ የሞቱ ሰወች፣ የጎደለ አካል ከአንድ የጦርሜዳ ውሎ በላይ ነው። እንደ አገርም እንደ ሕዝብም በአለም መድረክ የተዋረድንበት። ገዳይም ሟችም እኛው ራሳችን ... የሆንበት አሳፋሪ ተግባር።
የሚላስ የሚቀመስ የሌለው መናጢ ድሃ ወጣት ንብረት ሲያወድም የሥራ ገበታው ሥራ አጥ ወገኖቹ ሰርተው ደመወዝ አግኝተው ቤተሰብ የሚያስተዳድሩበትን ሥፍራ ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ንብረት የሚያቃጥል።
በደጉም በክፉም ጊዜ ጸጥታ በማስፈን፣ ሰላማችን እንዳይደፈርስ ዘብ የሚቆሙ የጸጥታ አካላትን መግደል፣ አካል ማጉደል ያጎረሰ እጅ ነካሽነት ነው።
ለነዚህ አረመኔዎች የአዳል በግነት ምግባራቸውን የሚገልጥ የነውረኝነታቸው መገለጫ ሥም ሳይሆን የክብር ሥም ነው የሚሆነው። ለአዳል በጎች ደግሞ እንዲህ ጭካኔ በተሞላ ተግባር በሚሰማሩ ከሰውነት ክብር በወረዱ በመንጋ በሚያስቡ በመንደር በተወሰኑ ወጣቶች መመሰል ስድብ ነው።
ቀጣይ ትውልድ የማፍራት ተግባር ላይ ቤተሰብ ትልቅ ድርሻ እንዳለው እሙን ነው በመቀጠል የአካባቢው ማህበረሰብ የሐይማኖት አባቶች የአገር ሽማግሌዎች የትምህርት ቤት መምህራን ወዘተ እያለ ይቀጥላል። እስከ ማስታውሰው እነዚህ አካላት በኔ ማንነት ውስጥ ድርሻቸውን ስለምገነዘብ ለነዚህ አካላት ትልቅ ክብር ነበረኝ። እነርሱ በውስጤ ባሰረጿት የአንዲት ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ውስጤ በፍቅር ብርሃን ይንቦገቦጋል የመንደርተኝነት ጨለማ አልዋጠኝም። "ኑ ቡና ጠጡ" የምትል የመልእክት ድምጽ ከወላጆቼ እንደሰማሁ በቀጫጭን እግሮቼ ብን ብዬ በርሬ ዘር፣ ቀለም፣ ሐይማኖት፣ ብሔር ሳልለይ ቡና ጠጡ ብዬ ከመጥራት ወዲያ መከፋፈልን ባላየሁበት ማህበረሰብ ውስጥ እንዴት ዛሬ በሐይማኖት፣ በብሔር ተከፋፍሎ ጸብ ግድያ ማፈናቀል ንብረት ማውደም ከየት መጣ?????
ማንስ በመካከላችን የሐሳብ እንክርዳድ ዘር ዘራ?
የሐይማኖት መምህራን በምሣሌ ሲያስተምሩ አንድ ገበሬ መሬቱን አርሶ አለስልሶ ስንዴ ዘራበት ሰብሉ ከቡቃያነት አልፎ ከፍ ማለት ሲጀምር እርሻውን ቢመለከት አረም ወርሮታል እንደልማዱ ቤተሰቡን ሰብስቦ የአከባቢውን ሰው ደቦ ጠርቶ የበቀለውን አረም አረመው። በመቀጠልም የዘራው ዘር አብቦ ካፈራ በኋላ ተመልሶ ቢመለከተው ንጹሕ የስንዴ እርሻ በእንክርዳድ ተወርሯል። የእምነት መምህራን ይህንን የስንዴ እርሻ በእንክርዳድ መወረር አመስጥረው ሲያስተምሩ "እንክርዳዱን" የዘራው ጠላት ሰይጣን እንደሆነ ያስተምራሉ።
በዚህ ትውልድ መካከልም የሰው ልጅ እንደ ሰው ሲፈጠር እንዲህ በመከፋፈል ሳይሆን ከአንድ አዳም እንደተገኘን አሁንም የእምነት ተቋማት የሥነ ፍጥረት ትምህርት አስተምህሮ ያስረዳናል። እንዲህ በመከፋፈል እንድንባላ እንድንጋጭ አንዱ ሌላኛውን እንዲያሳድድ ንብረት እንዲያወድም አገር እስከ ማፍረስ የሚያደርስ ግጭት እንዲፈጠር የሚያደርጉ ተግባራት ይከናወናሉ። ይህን እንዲሆን ማን አደረገ? ካልን ሁላችንም የምንገነዘበው የሰይጣንን ተግባር የሚተገብሩ በትውልድ መካከል የእንክርዳድ ዘርን የሚዘሩ አክቲቪስቶች፣ ፖለቲከኞች፣ "ከእውቀት ነጻ " ምሁራን ተብዬዎች፣ ሚዲያዎች ወዘተ ናቸው።
ችግሩን ማወቅ የመፍትሔው አጋማሽ ነው እንዲሉ ምሁራን ትውልዱ ራሱን እንዲህ በውስጣችን እንክርዳድ የሚዘሩትን ምን ማድረግ ይጠበቅበታል? መንግሥት? የእምነት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ወዘተ ምን ያድርጉ?
አስቀድመን እንደተናገርን በስንዴ እርሻ ውስጥ የበቀለውን የእንክርዳድ ዘር ገበሬው በመኸር ወቅት ስንዴውን ከእንክርዳዱ በጥበብ እንዲለይ በየደረጃው ያለን ስለ ሕዝባችን ሃላፊነት የሚሰማን ግለሰብ እና በተለያየ የመንግሥት ሃላፊነት በመውሰድ ሠላም የማስፈን፣ ጸጥታ የማስከበር፣ ሕግን የማስከበር ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላት በጥበብና በማስተዋል እራሳችንንና ወገናችንን ከጠላት ዲያቢሎሳዉያን ልንጠብቅ እና ልንከላከል ይገባል።
ወደ መሬት ስናወርደው ሕብረተሰቡ የሚደርሰውን መረጃ ከማህበራዊ ሚዲያ፣ ከኤሌክትሮኒክ ሚዲያ፣ ከህትመት ሚዲያ፣ ወዘተ የምናገኛቸውን መረጃዎች ብስል ከጥሬ መለየት የሚጠቅመውን ከማይጠቅመው፣ እውነተኛውን ከሐሰተኛው መለየት ይጠበቅበታል።
ሕዝብን ከጥፋት አገርን ከመበታተን ሐብትና ንብረትን ከውድመት የሚታደጉ የጸጥታና የደህንነት አካላት አገርንና ሕዝብን ለመታደግ ያገኙትን ሳይንሳዊ ጥበብ ፖለቲከኞችን እና መሪዎችን ከመጠበቅ፣ ተፎካካሪዎችን መረጃ ከመጥለፍ እና ከማገት ተጠብቀው አገርን እና ሕዝብን ከጥፋት ለመታደግ የእለት ተለት አገር ውስጥ የሚሰራጩ መረጃዎችን በማሰስ በመተንተን ጥፋት ከመፈጠሩ ንብረት ከመውደሙ የሰው ህይወት ከማለፉ አስቀድሞ ሊያከሽፍ ጥፋተኛውንም በቁጥጥር ሥር ማዋልና ለሕግ ማቅረብ ይኖርበታል።
የሕግ አስፈጻሚ አካላት እና በተለያዩ ተግባራት ላይ የተሰማራው ባለስልጣን ህግን ከለላ በማድረግ ጥፋት ላይ የተሰማሩትን ፈቃድ ከመስጠት በዘለለ የየእለት ተግባራትን ትክክለኛነት መመዘን፣ እርምትና እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል። ይህንን ካልከወንን ጥፋቱ ቀላል አይሆንምና። እንደ ምሳሌ ብናነሳ በማህበረሰብ መካከል የመከፋፈል ቅስቀሳ የሚያደርጉ ሚዲያዎች አስቀድመው ሕጋዊ ከለላ ለማግኘት በሕጋዊ መልኩ ፈቃድ ወስደው ሥራ ጀምረዋል። ግብር ይከፍላሉ። ሕግ ባለበት አገር ውስጥ ሕጋዊ መስለው ይንቀሳቀሳሉ። ይህ ብቻ በቂ አይደለም። ብሮድካስት ባለስልጣን በየወቅቱ ሥራቸውን መፈተሽ፣ እርምት መውሰድ፣ እርምጃ መውሰድ፣ ወዘተ ይኖርበታል። ይህ ሳይሆን ሲቀር ግን የሚደረገው ሩጫ "ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ" ይሆንብናል። እነርሱ የተቋቋሙበትን አላማ ካሳኩ በኋላ ማስጠንቀቅያ መሥጠት፣ ለመዝጋት መሯሯጥ በሕዝብ ላይ መዘባበት ይሆናል። ሌሎችም እንዲሁ ተጠቅሰው ተዘርዝረው የማያልቁ አስቀድመን አስበን በመከወን ከጥፋት ልንታደግ የሚገቡ ተግባራት አሉን።
ብዙውን ጊዜ እንደታዘብኩት ከሆነ አንድ ነገር ከሆነ በኋላ ህጉን ስንተች ስለ አገሪቱ ሕግ መላላት ስናወራ ይደመጣል። እንደ ኢትዮጵያ ከ98% በላይ ሐይማኖተኛ በሆነ ማህበረሰብ መካከል ስለ ምድራዊ ሕግ መጨቃጨቅ ለኔ ውሃ የማያነሳ ሀሳብ ነው ምክንያቱም እንደ ሐይማኖተኛነታችን እምነትን እንደተቀበለ እና እንደመንፈሳዊ ሰው ምድራዊ ሕግ ለሰው ልጅ ኢምንት ነውና። ምድራዊ ሕግ ስለ መደፈር ፍትሕ ከመስጠቱ በፊት መረጃና ማስረጃ ይሻል። መንፈሳዊ ሕግ ግን ስለ ዝሙት "ያየ የተመኘ አመነዘረ" ይላል። በእምነት ጥላ ሥር ላደገ ማህበረሰብ ሴትን ልጅ ለመድፈር አይነሳሳም። ሕጉ ላልቷል ሥጋት አይሆንበትም። ሕጉን ሳይሆን የሚያወግዘው ዝሙትን ነውና። ስለዚህ የእምነት ተቋማት እና የእምነት ተቋማት መምሕራን ትውልድን በመቅረጽ ላይ ድርሻና ግዴታ አለባቸው። እንዲህ ስንል ግን በእምነት ስም የሚነግዱትን ስመ አምላክ ነጋድያንን ልብ ልንል ይገባል። እነርሱም የትውልዱ ነቀርሳዎች ስለሆኑ።
እንግዲህ እንደ በግ እንዳንነዳ ምን እናድርግ?
በግ ላለመሆን ያለን ብቸኛ አማራጭ ሰው መሆን ነው።
ሰው ስንሆን:-
እንደ ሰው እናስባለን
እንደ ሰው እንኖራለን
ሰዋዊ እሳቤ ይኖረናል
እንተሳሰባለን
እንከባበራለን
በሐሳብ የበላይነት እናምናለን
የሰውን ክቡርነት እናምናለን
ለሕግ እንገዛለን
በጥቅም አንገዛም
አገርና ሕዝብን አንሸጥም
ሕዝብን ለፖለቲካ ፍጆታ አናባላም
ንብረት አናወድምም
አካል አናጎድልም
ሕይወት አንቀጥፍም።
ሰው ክቡር ሆኖ ሳለ አያስተውልም እንስሳትን መሰለ እንዲል እኛም ወደ ማስተዋል ተመልሰን እንደ ሰው እንኑር።
ደረሰ ረታ
ሐምሌ 7/2012

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...