♥️ በሐዋርያት ሥራ ምዕ ፩፥፲፬ ላይ እንደተጻፈ የባሕርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ በተነሣ በአርባኛው ቀን ደቀ መዛሙርቱን ወደ ቢታንያ በማውጣት “እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ” ብሎ ሰማያዊ ሀብትን ሰማያዊ ዕውቀትን ገንዘብ እስኪያደርጉ ድረስ በኢየሩሳሌም እንዲቆዩ አዝዞ በምስጋና ዐረገ፡፡
♥️ ስለምን እንዲኽ አዘዛቸው? ቢሉ መንፈስ ቅዱስን ከመቀበላቸው በፊት ፈሪዎች ነበሩና ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ባልተቀበለ ሰውነታቸው አይሁድ መከራ አጽንተውባቸው ሃይማኖታቸውን እንዳይክዱ፡፡
♥️ዳግመኛም ኅሊናቸውን በተመስጦ ለማቆየት፡፡
❤️ ሌላው መንፈስ ቅዱስ የሚወርደው በጽርሐ ጽዮን ነውና ከአንዱ ወደ አንዱ ሲዘዋወሩ እንዳይቀርባቸው ነው፡፡
♥️12ቱ ሐዋርያት፣ 72ቱ አርድእት፣ 36ቱ ቅዱሳት አንስት በማርቆስ እናት በማርያም ቤት ኹነው በይሁዳ ምትክ ማትያስን አስገብተው፤ ሰማይ ምድር የማይወስኑትን አምላክ በማሕፀኗ የተሸከመች የድንግልና ጡቶቿን ያጠባች ቅድስት ድንግል የሌለችበት ጉባኤ ከጸጋ መንፈስ ቅዱስ የተለየ ነውና የመስቀል ሥር ስጦታቸውን “የኢየሱስ እናት ማርያምን” ይዘው በአንድ ልብ ኾነው በጸሎት መትጋት እንደዠመሩ ሉቃስ ጽፏል (የሐዋ ፩፥፲፬)፡፡
♥️ ከዚያም ልክ በሦስት ሰዓት “መጽአ ግብተ እምሰማይ ድምፅ ከመ ድምፀ ነፋሰ ዐውሎ” ይላል ከወደ ሰማይ እንደ ዐውሎ ነፋስ ያለ ድምፅ ነጒዶ ተሰምቶ ያሉበትንም ቤት መላው ይኽም የሚያስተምረን ማኅደረ መንፈስ ቅዱስ የኾነች እመቤታችን ያለችበትና የምትጠራበት ጉባኤ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጸጋ እንዳለበት ያሳየናል፤ ይኽም የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ አስቀድሞ በኤልሳቤጥ ሲታወቅ ገና እመቤታችን ደርሳ ሰላምታን ስትሰጣት ቅዱስ ወንጌል “በኤልሳቤጥ ላይ መንፈስ ቅዱስ መላባት” በማለት እንደመሰከረ እናያለን (ሉቃ ፩፥፵፩)፡፡
♥️ ጌታ በዐረገ በ10ኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ ስለምን ወረደ ቢሉ፡-
1ኛ)10ሩን ሕዋሳት 10ሩን ቃላት በእውነት ብንጠብቅ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እንደሚሰጠን ለማጠየቅ፡፡
2ኛ) ከ10ኛው መዐርግ የገባን እኛ ነበርንና ከጥንተ ቦታችን ክብራችን እንደተመለስን ለማጠየቅ ነው፡፡
♥️ ይኸውም ለሐዋርያት በአምሳለ ነፋስ የተገለጸው መንፈስ ቅዱስ ነው ለምን በነፋስ አምሳል ተገለጸ ቢሉ መተርጉማነ መጻሕፍተ ሐዲሳት ያመሰጥሩታል፦
✔️ነፋስ ረቂቅ ነው መንፈስ ቅዱስም ረቂቅ ነውና፤
✔️ነፋስ ኀያል ነው መንፈስ ቅዱስም ኀያል ነውና፤
✔️ነፋስ ፍሬውን ከገለባው ይለያል መንፈስ ቅዱስም ጻድቃንን ከኃጥኣን ይለያልና፤
✔️ነፋስ በምላት ሳለ አይታወቅም ባሕር ሲገሥፅ ዛፍ ሲያናውፅ ነው እንጂ መንፈስ ቅዱስም በምላት ሳለ አይታወቅም ቋንቋ ሲያናግር ምስጢር ሲያስተረጒም ነውና፤
✔️ነፋስ መንቅሂ ነው መንፈስ ቅዱስም መንቅሂ ነውና፤ ✔️ነፋስ መዐዛ ያመጣል መንፈስ ቅዱስም መዐዛ ጸጋን ያመጣልና ነው፡፡
♥️ ከዚያም “ወአስተርአይዎሙ ልሳናተ እሳት ክፉላት ከመ እሳት ዘይትከፈል” ይላል እንደ እሳትም የተከፋፈለ ልሳን ኹኖ በያንዳንዳቸው ላይ ተቀምጦባቸዋል፤ ይኸውም ልሳን ላንቃ ማለት ቋንቋን ማውጫ መነጋገሪያ እንደኾነ ኹሉ ሰዎች የሚግባቡበት ትክክለኛ መግባቢያ የኾነ፤ ሊጻፍ ሊሰማ ሊያግባባ የሚችል የቋንቋ ሀብትን መንፈስ ቅዱስ በእሳት ላንቃ አምሳል አሳድሮባቸዋል፡፡
♥️ መንፈስ ቅዱስ በእሳት አምሳል መውረዱ ምሳሌነት ያለው ነው፤ ይኸውም እሳት ምሉእ ነው መንፈስ ቅዱስም ምሉእ ነውና፤
✔️ እሳት በምላቱ ሳለ ቡላድ ካልመቱ አይገለጽም መንፈስ ቅዱስም ቋንቋ ሲያናግር ምስጢር ሲያስተረጉም እንጂ ዐድሮ ሳለ አይታወቅምና፤
✔️ እሳት ከቡላዱ ሲወጣ በመጠን ነው ኋላ በዕንጨት እያቀጣጠሉ ያሰፉታል መንፈስ ቅዱስም በ፵ በ፹ ቀን በጥምቀት ሲሰጥ በመጠን ነው ኋላ በሥራ ያሰፉታልና፤
✔️ እሳት ጣዕምን መዐዛን ያመጣል መንፈስ ቅዱስም ጣዕመ ጸጋን መዐዛ ጸጋን ያመጣልና፤
✔️እሳት በመጠኑ የሞቁት እንደኾነ ሕይወት ይኾናል ከመጠን ዐልፎ ቢሞቁት ያቃጥላል መንፈስ ቅዱስም በሚገባ በተጻፈው የመረመሩት እንደኾነ ሕይወት ይኾናል በማይገባ ከተጻፈው ወጥተው የመረመሩት እንደኾነ ይቀሥፋልና፤
✔️እሳት ያቀረቡለትን ያቃጥላል መንፈስ ቅዱስም የጸለዩትን ጸሎት ያቀረቡለትን መሥዋዕት ይቀበላልና፤ ✔️እሳት ውሃ ገደል ካልከለከለው ኹሉን ላጥፋ ቢል ይቻለዋል መንፈስ ቅዱስም ቸርነቱ ካልከለከለው ኹሉን ላጥፋ ቢል ይቻለዋልና፤
✔️እሳት ዱር ይገልጻል መንፈስ ቅዱስም ምስጢርን ይገልጻልና፤
✔️እሳት የበላው መሬት ለእኽል ለተክል ይመቻል መንፈስ ቅዱስም ያደረበት ሰውነት ለገድል ለትሩፋት ይመቻልና ርሱ ባወቀ በእሳትና በነፋስ አምሳል ወርዷል፡፡
♥️ ከዚያም በኹሉም መንፈስ ቅዱስ መልቶባቸው ዓለም በሚሰማው ኹሉም በሚረዳው በ፸፪ቱ ቋንቋ ተናግረዋል፤ በሐዋርያት 72 ቋንቋ አልተከፈለባቸውም፤ የቀሩት ግን ከ15 በታች የወረደ የለም እንጂ 20ም 30ም 40ም 50ም 60ም የተገለጠላቸው አሉ፡፡
♥️ እስራኤል ከምርኮ መልስ በኋላ በወደዱት ሀገር በሕጋቸው ይኖራሉ፤ ለበዓለ ፋሲካ ወደ ኢየሩሳሌም ይመጣሉ፤ በዓለ ፋሲካን አክብረው ከዚያ አያይዘው ሰባት ሱባዔ ቈጥረው በ50ኛዪቱ ዕለት በዓለ ሰዊትን ያከብሩ ነበርና በዓለ ፶ን ለማክበር ከየዓለማቱ የመጡት በእጅጉ ተገርመው:- “እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋችንን እንዴት እንሰማለን?፤ የጳርቴና የሜድ የኢላሜጤም ሰዎች በኹለት ወንዝም መኻከል በይሁዳም በቀጰዶቅያም በጳንጦስም በእስያም በፍርግያም በጵንፍልያም በግብጽም በቀሬናም በኩል ባሉት በሊብያ ወረዳዎች የምንኖር በሮሜም የምንቀመጥ አይሁድም ወደ ይሁዲነትም የገባን የቀርጤስና የዐረብ ሰዎች የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በልሳኖቻችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን” በማለት በእጅጉ ተደነቁ፡፡
♥️ ያን ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ተነሥቶ ነቢዩ ኢዩኤል በምዕ 2፡28-29 ላይ “ከዚህም በኋላ እንዲህ ይሆናል መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፥ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልምን ያልማሉ፥ ጐበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ ደግሞም በዚያ ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎች ላይ መንፈሴን አፈስሳለሁ” ብሎ የተናገረው መፈጸሙን ጠቅሶ ሰፋ አድርጎ ነገረ ክርስቶስን ቢያስተምራቸው ቃሉን ተቀብለው ሦስት ሺሕ ሰዎች አምነው ተጠምቀዋል፡፡
♥️ሊቃውንትም ይኽነን በመያዝ በተለይ እነቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ዕለቷን “የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን” ብለዋታል፡፡
♥️እመቤታችን በመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን በማርቆስ እናት ቤት በሰገነት ላይ በመስቀል ሥር በአደራ የተቀበለቻቸው በልጇ በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት የሚያምኑ የአደራ ልጆቿን ሐዋርያትን ይዛ እንደተገኘች ዛሬም በልጇ ደም በተመሠረተችው ሐዋርያዊት በኾነችው በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተሰብስበን የልጇን የባሕርይ አምላክነት የርሷን ወላዲተ አምላክነት በመመስከር እንኖራለን፡፡
♥️ “ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ እግዚእ ማሕየዊ ዘሠረጸ እምአብ ንስግድ ሎቱ ወንሰብሖ ምስለ አብ ወወልድ ዘነበበ በነቢያት” (ጌታ ማሕየዊ በሚኾን ከአብ በሠረጸ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን፤ በነቢያት ዐድሮ የተናገረ ለርሱ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እንስገድለት እናመስግነው) አሜን።
ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ