12/12/12
ጎበዝ መጨረሻችን የመጥረብያ እጀታ አይሁን፣
ቅርንጫፎቻችንን አንመልከት ቅርንጫፎቻችንን ከተመለከትን ብዙ የተራራቅን ይመስለናል፤ ሥሮቻችንን ተመልከቱ እንዲህ አምሮብን ዘመናትን ያስቆጠርነው የሥሮቻችን ተጋምደው መኖር ነው ምሥጢሩ።
እንደ ሰው ልጅ ፍላጎት ቢሆን ገና ድሮ አልቀናል፤
ምድር ተራቁታ ድርቅ ምድረ አዳምን ከምድረ ገጽ ባጠፋ ነበር።
ጨከን ብለን ለራሳችንም ሆነ ለሰው ልጅ ሥንል እንኑር።
እኛኮ ከአንድ ለም አፈር የበላን ከአንድ ምንጭ የጠጣን የአንድ ምድር ውጤቶች ነን። ቅርንጫፎቻችንን አንይ ሥራችን አንድ ነው። ቅርንጫፎቻችንን ላየ በቀላሉ ሊለየን ይችላል ሥራችንን ዘልቆ የተመለከት ማንም አይለየንም።
የሰው ልጅም እንዲህ የሚባላው ቅርንጫፉን እየተመለከተ ነው፣ ቀለሙን ፣ ሐይማኖቱን፣ ጎሳውን፣ ቋንቋውን፣ አከባቢውን፣ ... ነገር ግን የትመጣውን ቢመረምር ከአንድ አፈር ነው። ይህ ጠፍቶት ነው የሚባላው።
እድሜዬ ጠና እንደማለቱ ብዙ የሰው ልጅ ጠባይ አውቃለሁ። መኖር ደጉ ይኸውላችሁ ... ብለው አንገታቸውን አቀረቀሩ በሐሳብ እሩሩሩሩሩቅ ሄዱ፤ ጸጥታው ሰፈነ ... አልተመለሱም።
በምርኩዛቸው ምድርን ቆረቆሩ፣ እንባቸው በአራቱም ማእዘን ወረደ። ጭንቅላታቸውን ነቀነቁ። ይህቺ ምድር ትፍረዳ ብለው አንገታቸውን ቀና አደረጉ።
ይህቺ ምድር እና እኔ ስንቱን አየን ምድር ሥንቱን ደጋግ አባቶች ከጉያዋ ሸሸገች? ጓደኞቼ ለሥንቱ መቀበሪያ ሣጥን ሆኑ?
ሥንት ጀግና ሥንት አገር ወዳድ ሥንት ለሰው ሟች በቀለባት ይህቺ ምድር? ዛሬ አቃፊ ነን ባይ እንጂ እንግዳ እንኳን በቅጡ የሚያስተናግድ የለባትም ምድራችን፣ እሾክና አሜኬላ አበቀለች ምድር፣ ያለ ማዳበሪያ ፍሬ አልሰጥ ካለች ሰነበተች፤
ለምን? ብሎ የሚጠይቅ ትውልድ የለም።
ተገዶ ሳይሆን ወዶ ትውልዱ እንደ እኛ ለሚጨርሱት እጀታ ሆኗል እንደ እኛ።
እጀታ ሆኖ እርስ በርስ ከተጨራረሰ በኋላ ጨረሱን ይላል መለስ ብሎ ... ለምን? እንዴት? አይልም።
ግርርርርር ከማለት ምን ይገኛል?
ያለ ጎረቤት ብቻውን ምን ሊሆን ነው?
ጓዶች ያለ ሰውኮ ይህቺ ምድር ጨው እንደሌለው ወጥ ነው፤ ቀምሼ ባላውቀውም አሉ ታላቁ ዛፍ/ ዋርካው። ዛፎች ፈገግ አሉ በትልቁ ዋርካ አነግስገር።
ተመልከቱ አሉ እጃቸውን ወደ ማዶ እየጠቆሙ ያ የምትመለከቱት ቤት ባለቤት ወላጆቻቸውን ወደ ኋላ ተመልሶ የሚያጠና ቢገኝ የነርሱ ቤተሰብ የኋላ አመሰራረት እና የዛሬ ልጆቻቸው ታሪክ ለየቅል ነው።
ወላጆቻቸው መንገደኛ እንግዳ ተቀባይ፣ የተራበ የሚያበሉ፣ የተጠማ የሚያጠጡ፣ የታረዘ የሚያለብሱ፣ የታመመ የሚጠይቁ፣ ... ነበሩ። የዚህ ቤት ታሪክ "ነበር" ላይ ተገትሮ ቆሟል፤ ቶሎ የሚደርስለት ትውልድ ካልተገኘ አደጋ ላይ ነው።
ዛሬ ቤቱን ብትመለከቱ ብዙ ክፍሎች ተዘገተው ተቀምጠዋል። እንኳን እንግዳ ሊቀበሉ ልጆቻቸው መጻተኛ ሆነው በየአለማቱ ተበትነው እንግዳ ሆነው ይኑራሉ። ይህ ቤተሰብ የሁሉም ቤተሰብ ምሣሌ ነው። የአገር ምሣሌ ነው። ቤትና አገር አንድ ነው ብዙ የሚያመሣሥላቸው ነገር አለ ሁላችንም እንዳየነው ቤት ተሰርቶ ሰው ገብቶ ካልኖረበት ይፈርሳል። አገርም አያድርግባቸውና እንደዛው ነው። ክልሎች ከኛ ሰው ውጭ አይኑርበት ብለው የሚያፈናቅሉት ጥቅማቸውን ነው እየነኩ ያሉት የሰው ልጅን ጥቅም ሥላልተረዱት።
ቢገባቸው ኖሮ እንኳን ሊያሳድዱ፣ ሊያፈናቅሉ፣ ሊገድሉ፣ ሐብትና ንብረታቸውን ሊያወድሙ ይቅርና ሙሉ ወጪያቸውን ችለው ባኖሯቸው ነበር። የሰው ልጅ መኖሩ ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው። ምድር ተራቁታ በረሃነት ባልሰፋ ፣ ምድር ለምነቷን ባላጣች፣ እኛ ተጨፍጭፈን ብቻ ባላለቅን፣ ሰው በተፈናቀለ ቁጥር ቤት ሊሰራ ባልመነጠረን ነበር፤ ወገኖቼ ታሪኩ ብዙ ነው ስንቱ ተዘርዝሮ ያልቃል።
በአጭሩ እንኳን ሰው እና ሰው እኛና ሰው ተለያይተን መኖር አንችልም። ወደ ዋና ጉዳዬ ስመጣ እኛና ሰወች ጠላቶች አይደለንም ተመጋጋቢዎች ነን። አንዳንችን ለአንድኛችን አስፈላጊ ነን። የምንጠፋፋ አይደለንም። እኛ ያለነሱ እነርሱ ያለኛ አንኖርም። እነርሱ ራሳቸው ሰወች እንዳጠኑት በሳይንሳቸው ከነርሱ በሚወጣ የተቃጠለ አየር እኛ ስንኖር እነርሱ ከኛ በሚወጣ አየር ይኖራሉ።
እናንት ወገኖቼ አስቀድማችው እንደ ጠቀሳችሁት ሰወች ጨረሱን፣ ጨፈጨፉን፣ ወዘተ ያላችሁት ትንሽ እውነት አለው። ነገር ግን ትንሽ እውነት ትልቁን እውነት አይበልጠውም። ሂሱን ዋጡት ለመቼ ሊሆናችሁ ነው ዋናው የራሳችን ችግር እራሳችን ዛፎች ነን። ተንጋደን እናድጋለን ለመጥረቢያ እጀታ እንሆናለን የሰው ልጅም በመጥረቢያ እየጠረበ ይማግደናል። መፍትሄው ጨረሱን እያሉ ከማዜም ተንጋዶ አለማደግ ነው።
እድሜ እንዳስተማረኝ የሰው ልጆች ተንጋዶ ማደግ ለእርስ በርስ እልቂት ዋናው መንስኤ ነው። አስተዳደግ ወሳኝ ነው። በተለይ የሰው ልጅ ሲያድግ ዝም ብሎ እንዳገኘ ማደግ የለበትም። አስተዳደጉ መጨረሻውን ይነግረናል። ምን በልቶ አደገ ብቻ ሳይሆን ምን ሰምቶ፣ ምን ተምሮ፣ ምን አይቶ፣ ወዘተ አደገ የሚለው ለሰው ልጅ መሰረታዊ ጥያቄ ነው።
ዛሬ የሰው ልጅ ስለሚለብሰው፣ ስለሚጫማው፣ ስለሚይዘው ሞባይል፣ ስለሚያሽከረክረው መኪና፣ ... እንጂ ስለሌላው አይገደውም።
ሌላው ቢቀር በያዘው ሞባይል ስንት ሸርና ተንኮል እንደሚንሸራሸርበት አይመረምርም። ያገኘውን ሁሉ ያምናል። ተነስ ሲሉት ይነሳል ፣ ተቀመጥ ሲሉት ይቀመጣል፣ መንገድ ዝጋ ሲሉት ይዘጋል፣ አቃጥል፣ አፈናቅል፣ ግደል፣ ስቀል፣ ሲሉት ያሉትን ሁሉ አምኖ ያደርጋል።
ትውልዱ የአክቲቪስቶች፣ የፖለቲከኞች፣ የክፉ ሰወች፣ ... ማስፈጸሚያ እጀታ ሆኗል። አይመረምርም። አይመራመርም።
ይኸን ዝም ብሎ መነዳት፣ አስፈጻሚ፣ ፈጻሚ መሆን እኛ ከሰው ተማርን? ወይንስ ሰው ከኛ ተማረው?
መልስ አልነበራቸውም።
እንዲህ ከተሰባሰብን አይቀር ብዙ የማጫውታችሁ ነገር አለ እንኳን ስለኛ ሰለ ሰውም ጭምር።
ይከታተሉን።
ሐሳብ አስተያየትዎን ከመስጠት አይቆጠቡ።
መልካም ቀን ይሁንልዎ።
ደረሰ ረታ
ነሐሴ 12/2012 አ.ም.
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ