ሰው ማለት በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚድያ ሕግ የሚወጣለት፣ የራሱ ጉዳይ ስንት እያለ በየሚድያው ስለራሱ ሳያወራ አንድ ማስታወቂያ ሰምተን እንመለሳለን እያለ ስለቁሳቁስ ትልቅነት ይደሰኩራል፣ አንድም ቀን ስለ ሰው ልጅ ትልቅነት ስለ ዛፎች አስፈላጊነት ጊዜ ተሰጥቶ አይወራም፣ ይኸው አንድ መሪ ከወደ ኢትዮጵያ ቢገኝ እና ዛፍ እንትከል ቢላቸው የሰው ዘር ከምድረ ገጽ እንንቀል ያላቸው ይመስል ጠምደው ይዘውታል። እነ ሥመ አይጠሬ ሰው እናፈናቅል ሲሏቸው አይደለም ቀን ሌሊት ይወጣሉ።
ምድራችን ዛሬም ስለ አስገድዶ መደፈር ሕግ ላይ ይጨቃጨቃል፣ ክቡር የሰው ልጅ መሰረታዊ አስፈላጊ ነገር አልተሟላለትም፣ ረሐብ፣ በሽታ፣ ጦርነት፣ የተፈጥሮ አደጋ፣ ሰው ሰራሽ አደጋ፣ የራስ ምታት ሆኖበታል።
ሰው ምድር ላይ ክቡር ፍጡርነቱ ተዘንግቶ ገራሚ የፊልም ስክሪፕት ሆኗል።
አስቂኝ፤ መሳለቂያ።
ትውልዱ በሰለጠነ ዘመን ቁልቁል ሄዷል፤ ለምን የሚል ከተገኘ መፍትሄው ቅርብ ነው።
እኔ በዘመኔ ገና ችግኝ ሳለሁ አባቶቻችን ትላልቅ ዛፎችና ዋርካዎች በየደብሩ፣ በየገዳማቱ፣ በየመስኪዱ፣ እና በየቄዬው ቁምነገር መገበያያ ነበሩ።
የተጣላ የሚታረቅበት፣ መንገደኛ የሚያርፍበት፣ እረኛ ጸሐይ የሚያበርድበት፣ ታሪክ የሚነገርበት፣ እድር እቁብ የሚጠጣበት፣ እውቀት የሚገበይበት ነበር።
የሰው ልጅ አስተሳሰቡ የተቃኘው ዛፍ ስር ነው፤
እውቀት የገበየው ዛፍ ሥር ነው፤
ሥንትና ሥንት አገራዊ ጉዳዮች ውሳኔ ያገኙት ዛፍ ሥር ነው፤ ጥቅማችን የትዬለሌ ነው። ለዚህ አለም ከመጥፋታችን መኖራችን ነበር የሚጠቅመው። ዛሬ ግን ለራሱ ክብር የነሳው የሰው ልጅ ጥቅማችንን ዘነጋው።
እኛ ዛፎች በጥንት ሰወች እንደሚነገረው ከሰው መርጦ ለሹመት ከእንጨት መርጦ ለታቦት ተብሎ የተነገረልን ነን። የሰው ልጅ ሥለ ራሱ ምን እንደሚያስብ ማወቅ ቢከብድም አሁንም ቢሆን እኛ ዛፎች ትልቅ ነን ስለትልቅነታችን፣ ስለ አስፈላጊነታችን ነው የማምነው። እኛ ከሌለን ፍጥረት መኖር ይከብደዋል። እኛ የምንመኘው ለኛ ሕልውና ሲባል ሰወች እንዲኖሩ ጸሎታችን ነው። የእነርሱን ስለኛ ያላቸውን አመለካከት ባናውቀውም።
ታናናሾቼ ዛፎች ቅድም ወዳነሳሁት ታሪክ ልመልሳችሁና አብዛኛው የእምነት አባቶች ውሎና አዳራቸው ዛፍ ሥር ነበር። ገና ከጨቅላ እድሜያቸው አንስቶ ፊደል የቆጠሩት፣ ምንባብ እና ዜማ የቀጸሉት እኛ ዛፍ ሥር ነው፤ ሥነምግባር እና ብዙ እውቀት የገበዩት እዚሁ ነው።
ታሪክ ያልኳችሁ ዛሬ ይኽ የለም ብዙ የእውቀት መገብያ ወንበሮች ታጥፈዋል፣ የቆሎ ተማሪው ሊቁ ከተማ ገብቶ ሎተሪ አዟሪና ተሸካሚ ሆኗል፣ አድባራትና ገዳማት ሊቃውንት ተራቁተዋል፣ ካድሬ ተሰግስጎባቸው ክብራቸውን አጥተዋል፣ሥለ ፍርድ መጓደል ሥለ ድሃ መበደል የሚሟገት ጠፍቷል፣ እውቀትን እውነትን የሚያስተምር የላቸውም፣ መሥጊዶች ውበታቸው፣ ግዝፈታቸውና ይዞታቸው እንጂ ኡስታዞች ሼኮች ኡለማዎች ሰሚ አጥተዋል።
አደባባዮች የጲላጦስ አደባባይ ሆነዋል ንጹሕ የሚሰቀልባቸው ቆሻሻውና ነውረኛው የሚነግስበት።
ትምህርት ቤቶች ትውልዱ መክኖ የሚወጣበት ከሆነ ከረመ፣ ሥነምግባር አይነገርበት፣ ሥለ አገር ፍቅር አይሰበክበትም፣ ታሪክ ይንጋደድበታል፣ ጥላቻ ይሰበክበታል፣ ጭንቅላት ይንጋደድበታል፣ አክቲቪስት/አፈ ክፍት/ ፣ ፖለቲከኛ ይፈለፈልበታል።
ሰውና አለሙ እንዲህ ነው፤
ሥንጠቀልለው ችግራችን ራሳችን ነን ራስን ተጠያቂ ማድረግ እንልመድ። የጠፋነው ራስችን ጠማማ፣ ቆልማማ ሆነን ነው ለአጥፊዎቻችን የተመቸነው።
በፍጹም ቀጥ ብለን እስካላደግን ስለመጥፋታችን በሌሎች ላይ ጣታችንን አንቀስር፣ አንድ እንሁን አንለያይ፣ እኔ በሚል ትብታብ አንተብተብ፣ እኛ በሉ፣ ለመወፈር ሌላውን አናቀጭጨው፣ ትልቅ ለመምሰል ሲሉ ሌላውን ማቅለል ማሳነስ የክፉ ሰው ተግባር ነው፤ ዛፎች ይህ የለብንም የሚታይብን ይኸንን በአስቸኳይ እናስወግድ።
እንደምትመለከቷቸው ሰወች ናቸው ትልቅ መስለው ለመታየት ትልቅ ሰው የሚሳደቡት፣ የሚያንቋሽሹት፣ የሚዘረጥጡት፣ ... አንዳንድ ሰወች ከአስተሳሰባቸው ማነስ የተነሳ ብሔርን ሳይቀር፣ ቋንቋን ሳይቀር፣ እምነትን፣ ባሕልን፣ ... ሳይቀር የነርሱ ካልሆነ አሳንሰው ያያሉ። ይህ ትልቅ ስህተት ነው አያኗኑርም ያጋጫል። ግጭቱ እንዲህ በቀላሉ የሚቋጭ እንኳን አይደለም ከትውልድ ወደ ትውልድ ይሸጋገራል።
በዚህ ዘመን ትልቅ ሰው አይከበርም፣
ሐሳብ ያለው አይወደድም፣
ለምን? ብሎ የሚጠይቅ ሰው እርኩስ ነው፣
አድር ባይ ሲሊኩት ሄዶ ሰፈር እንደ ችቦ የሚለኩስ፣ መንገድ እንደ ደጃፍ የሚዘጋ ይፈራል ይከበራል ይሾማል ይሸለማል፣
ችግር የሚባል አይደርስበትም፣
ንጹሕ ሰው ተሳቆ ይኖራል፣
ሽማግሌ የሐይማኖት አባት አይሰማም አይከበርም፣ ሥነ ምግባር፣
ግብረ ገብነት አይነገርም፣
ቀጥ ያለ አይወደድም፣
ወደ ፊት መጓዝ ሳይሆን እንደ ሎጥ ሚስት ወደ ኋላ መመልከት የአገሪቱ/የትውልዱ ማነቆ ነው።
ይከታተሉን።
ሐሳብ አስተያየትዎን ከመስጠት አይቆጠቡ።
መልካም ቀን ይሁንልዎ።
ደረሰ ረታ
ነሐሴ 13/2012 አ.ም
እንኳን ለደብረ ታቦር (ቡሄ) በአል አደረሳችሁ።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ