ቅዳሜ 22 ኦገስት 2020

እራስን ተጠያቂ ማድረግ መለማመድ (ክፍል ስድስት)

 

ይህቺ ምድር መሽቶ እስኪ ነጋ ነግቶ እስኪመሽ ጉድ ነው የሚሰራባት አስቀድሜ እንደነገርኳቸው ትንንሾች ትልቅ የሆኑ የሚመስላቸው ትልቁን ሲያጠፉ፣ አንገት ሲያስደፉ፣ አገር ሲያጠፉ፣ ትውልድ ሲያመክኑ ነው።
አንዳቸውም ጠቋሚ ጣታቸውን ወደራሳቸው አያዞሯትም፤ ወደሰው ከመቀሰር ውጪ። ራስን ለማየት አልታደሉም።
በአንድ ወቅት ነው አሉ ሰውየው ሚስቱን አየሻቸው እያለ ወደ ጎረቤትየው ቤት ያመለክታታል ሚስትም ወዳሳያት ትመለከታለች። ታጥቦ የተሰጣው ልብስ በደንብ እንዳልታጠበ የጎረቤታቸው ሴትዮ ልብስ እንኳን ማጠብ እንደማትችል ይነግራታል። ሌላ ቀንም እንዲሁ ያየውን ያሳያታል ሚስትም አይታ መልስ ሳትሰጠው ትሄዳለች። እንደለመደው በሶስተኛው ቀን ወደ መስኮቱ ይመለከታል ጎረቤቱን ለመተቸት ያየውን ነገር ማመን ይከብደዋል። ሚስቱን ጠራት ያየውን ነገር በመደነቅ ያወራላታል፤ ይህን የማይታመን ነገር አየሽ? ሴትዮዋ ሰራተኛ ቀጥራ ነው ወይስ እንዴት እንዲህ ባለሙያ ብትሆን ነው ያጠበችው የጠራላት? ሚስትም መለሰችለት።
እስከዛሬም ጎረቤታችን ባለሙያ ነበረች ሁሌም ልብስ የምታጥበው ጥርት አድርጋ ነው በዚህ ምንም እንከን አይወጣላትም። ችግሩ ያለው ያየህበት ሁኔታ ያየህበት መንገድ ነበር ችግር የነበረበት።
እቤት ተቀምጠህ በመስኮት ነበር የምትመለከተው የመስኮታችን መስታወት ደግሞ አጽድቼው ስለማላውቅ ቆሽሿል። ከዚህ የተነሳ የጎረቤታችንን ንጹሕ የተሰጣ ልብስ በቆሻሻ መስታወት ውስጥ ስታየው ቆሻሻ መሰለህ። ችግሩ ከልብሱ አልያም ከአጣቢዋ ሳይሆን ካየህበት ከኛው መሥታወት መቆሸሽ ነው ብላ ከስህተቱ አረመችው።
ስንቱ ተመልካች ይሆን የራሱን ቆሻሻ እይታ የሌላኛውን ንጽሕና ያጎደፈው?
ስንቱ ይሆን በራሱ ሸውራራ እይታ ቀጥ ያለውን ነገር ያጎበጠው?
ስንቱስ ይሆን በእንደዚህ አይነት ተመልካቾች ውሳኔው የተዛባው? ፍርድ የተጓደለው? ድሃ የተበደለው?
ስንትትቻችውስ ይሆኑ የራሳችው ቆሻሻ እይታቸውን የጋረደባቸው?
በምድር ዛፍ ሆነን ባሳለፍንባቸው ዘመናት አብያተ እምነቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ተቋማት፣ መሪዎች፣ ሕዝቡ፣ ወዘተ ራሳቸውን እንደማየት ጊዜያቸውን ሌሎችን በማየት የሚያባክኑ።
ሁሉም በጉያቸው ትልቅ ችግር ተሸክመው ጠላታችን እገሌ ነው በማለት ጣታቸውን ይቀስራሉ፤ ለዚህ ነው ለችግራቸው መፍትሔ ያላገኙት።
እስኪ በአገራችን የእምነት ተቋማትን ተመልከቱ በውስጥ ችግር ላይ አተኩሮ ከመጠናከር፣ በአንድነት እምነታቸውን ከማጠንከር፣ እርስ በርስ ላይ የተመሰረተ ህብረት ላይ እይታቸውን ከማድረግ ይልቅ እይታቸውን ሌላ ነገር ያተኩራሉ። ሁሉም ከራሳቸው የላቀ ጠላት የላቸውም።
ሁሉም በጉያቸው ብዙ ቁጥር ያለው መናፍቅ፣ ባንዳ፣ ሌባ፣ ተሸክመው ከጥቂቶች ጠላቶች ራሳቸውን ለመከላከል ይጥራሉ። ውጤቱን ገምቱት
እኛም ዛፎች ይህ ችግር ይታይብናል።
ይህ ችግራችን ነው ዛሬ ተሰባስበን ጊዜያችንን እያባከንን የምንገኘው፤ የችግሩን ምንነት ሳንለይ ለመፍትሔ የተሰበሰብነው።
በሰው ዘንድም ብዙ በጀት ተመድቦ፣ ጊዜ ወስደው፣ ጥናት አስጠንተው፣ በስብሰባ እድሜያቸውን ያለ መፍትሔ የፈጁት ከችግር ጋር ተወልደው ያረጁት ምክንያቱ ችግሩን ሳይለዩ ለመፍትሔ ስለሚቀመጡ ነው።
እኛ ጠላት ብለን የተቀመጥነው መሉ በሙሉ የፈረጅነው የሰው ልጅ ነው፤ ነገር ግን በጥልቀት ስንመረምረው የራሳችን ጥመት ተጣሞና ተንጋዶ ማደግ ለመጥረቢያ መመቸት ነው።
ሰውም እንዲሁ ለጥቃት መመቻቸት፣ ተጋልጦ መሰጠት ነው የጎዳቸው እንጂ ሌላ ስራ ፈትቶ እነሱን ለማጥቃት የሚደክም የለም። እስከነ ተረቱም አህያቸውን ውጪ እያሳደሩ ጅብን ነገረኛ ያደርጋሉ እንደሚባለው ነው።
በሉ እንግዲህ ከምንም በፊት እራሳችንን እንመርምር፣ ሌላው ላይ ከመፍረዳችን በፊት ከችግሩ ንጹሕ መሆናችንን እናጥራ፣ የችግሮች ሁሉ መፍትሔ ሩቅ አይደለም ሌላ ቦታ ሳይሆን እኛው ጋር ነው።
ሌሎችን ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ ራሳችንን ተጠያቂ ማድረግ እንለማመድ።
በጎቹን ተኩላ የነጠቀው/የበላቸው እረኛው ችግር ስላለበት ነው፤
ርስታችን የተወረሰው ርስታችንን ምንም ስላልሰራንበት ነው፤
ሌሎች መጥተው የደፈሩን እኛ ስላልተከባበርን ነው፤
የገደሉን ፍቅር ስላልተሰጣጠን ነው፤
ቤታችንን የበረበሩት አጥራችንን ስላላጠበቅን ነው፤
ጠላታችን እኛ ራሳችን ስለሆንን ራሳችንን ማሸነፍ፣ ተጠያቂ ማድረግ እንልመድ፣ እኛ ቀዳዳችንን መድፈን ስንለምድ ጠላትን እንዴት መከላከል እንዳለብን ይገባናል።
ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ።
ተፈጸመ።
የዘመንን ወለምታ፣ የትርክትን ስብራት፣ ሸውራራ እይታን፣ በቀና አስተምህሮ እንጠግናለን።
ይከታተሉን።
ሐሳብ አስተያየትዎን ከመስጠት አይቆጠቡ።
መልካም ቀን ይሁንልዎ።
ደረሰ ረታ
ነሐሴ 13/2012 አ.ም

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...