ትልቁ ዋርካ ዛፍ በእድሜ ብዛት ወገባቸው ቢንቋቋም ተነስተው ከመቆም፣ ሥርአት ከማክበር፣ ለተተኪ ትውልድ አርአያ ከመሆን፣ የተረከቡትን ሥርአት ከማስረከብ ያገዳቸው አልነበረም።
ይህ ተግባር ሰወች ዘንድ ቢኖር አለም እንዴት ለሰወች ምቹ በሆነች ... አለም መሪ እንጂ አርአያ የለትም ለዚያውም በአግባቡ ከመሩ ማለት ነው።
እርሳቸው ተነስተው ሲቆሙ ሰብሳቢም፣ ተሰብሳቢም ሁሉም በክብር ከመቀመጫቸው ተነሳላቸው።
አይገባም ቁጭ በሉ፣
በእግዚአብሔር ተቀመጡ፤
ፈጣሪ ያክብራችሁ፣ የኔን እድሜ ይስጣችሁ፣ እኔ ያየሁትን እዩ፣ እኔ ያገኘሁትን ክብር አግኙ። በሉ ተቀመጡ ... አሉ ትልቁ የዋርካ ዛፍ እሳቸው ሲነሱ ተሰብሳቢው የተጠለለባት የዋርካ ዛፍ አንሳ ታየች።
በትህትና ዝቅ ብለው ሁሉንም እጅ ነሱ።
እርጋታቸው፣ ግርማ ሞገሳቸው፣ ከአንደበታቸው የሚወጣው ቃል ልብ ያርዳል ... እንደ ማእበል ያናውጻል። ግን ትልቁ ዛፍ የቁጣ ቃል ከአንደበታቸው አይወጣም። ንቀት የሚባል ነገር በጭራሽ አያውቁም። እውቀት እና ጥበብ እርሳቸው ዘንድ ናት። የሚናገሩት ቃል ከቅርንጫፍ አንስቶ ሥር ድረስ ዘልቆ ይገባል።
እንደ አዋቂ ሳይሆን እንዳላዋቂ ነው የሚናገሩት ነገር ግን አንዲት መሬት ጠብ የምትል ቃል ከአንደበታቸው አይወጣም።
አሉ እንጂ ጥራዝ ነጠቆች፣ ሰወች ... ከእውቀት ነጻ የሆኑ ደፋሮች ትህትና በልባቸው ሳይሆን በአጥራቸው ያልዞረ።
አልፎ አልፎ ከአንደበታቸው የሚወጣ ምርቃት ሊረግፍ የደረሰ የደረቀ ቅጠል እድሜ ያረዝማል፣ ልምላሜ ይሰጣል፣ ያበቡትን እንዲያፈሩ፣ ያፈሩትን ፍሬያቸው እንዲበዛ ያደርጋል።
አይራገሙም።
አይሳደቡም።
አይበሳጩም።
የእድሜያቸው መርዘም፣ የቁመታቸው ትልቀት፣ የቅጠላቸው ውበት፣ የቅርንጫፎቻቸው ብዛት ምሥጢሩ ይህ ሳይሆን አይቀርም።
አንድ ጊዜ ሁሉንም ታዳሚ ዛፎች ዘወር ብለው ቃኙዋቸው፤ "በእርግጥ አሉ ... " ትልቁ ዋርካ ዛፍ። በእርግጥ በእድሜ እበልጣችኋለሁ። ጓደኞቼ በእድሜ ብዛትም ይሁን አሁን እዚህ በሚጠቃቀሱትም ምክንያት አጠገቤ የሉም። በሕይወት የሉም። በቁም ግን የተወሰኑት አሉ። ልጆቼ በሕይወት መኖርና በቁም መኖር ይለያያል። እናንት በሕይወት ስላላችሁ ነው እዚህ የታደማችሁት በቁም ያሉት እዚህ ሊገኙ አልቻሉም። የተለያዩ ችግሮች ጠፍንገው ይዘዋቸዋልና።
አንድ አርሶ አደር ትዝ አለኝ ወቅቱ አከባቢው ረሃብ ያንዧበበት ነበር፤ ታድያ ሰውየው እጃቸው ላይ የሚላስ የሚቀመስ ባይኖራቸውም ማሳ ላይ የደረሰ ሰብል ነበራቸውና ሲደርስ ብድሬን እመልሳለሁ እያሉ እየተበደሩ ያንን ክፉ ቀን ያልፉት ነበር። ከእለታት አንድ ቀን ታድያ እኚህ አርሶ አደር ወደ እርሻ ስፍራቸው ሄደው ዘወር ዘወር እያሉ ይመለከቱት ጀመር። ታድያ የተበደሩትንና የበሉትን ማሳው ላይ ያለውን ሲመለከቱ የሚተርፋቸው ያለ አልመስል ሲላቸው። "ያለሽ መስሎሻል ተበልተሽ አልቀሻል" ብለው ወደቤታቸው ተመለሱ።
እስኪ ወደ ሰፈራችን፣ መንደራችን፣ አገራችን እንመልከት ማነው በቁም ያልተበላ? ፖለቲካ ያልበላው? ዘረኝነት ያልበለው? መንደርተኝነት ያልበላው? ... የቆምን መስሎናል ተበልተን፣ ተባልተን አልቀናል።
ሁላችን ባለእዳ ነን፣
የልጆቻችንን አገር የደም ምድር አድርገናል፣
ወደፊት መጓዝ ቢሳነን እንደሎጥ ሚስት ታሪክን ወደኋላ ማየት ላይ ተጠምደናል፤
ሽማግሌው ዋርካ እንዲህ አሉ፦ችግሮቹ ሰው ሰራሽ፣ እንስሳ ሰራሽ፣ ተፈጥሮ ሰራሽ፣ እጽዋትን የሚያጠቃ በሽታ ወዘተ... እያልን ልንዘረዝራቸው እንችል ይሆናል። ችግሩ ምክንያቱ አይደለም እዚህ አለመገኘታቸው፣ እኛ ለተቀመጥንበት አላማ ለአንዴና ለዘለዓለም መቀመጥ አለመቻላቸው ነው።
በሰውኛ ምን ይባላል መሰላችሁ " ይህንን እናንተ የምታዩትን፣ የምትሰሙትን ብዙዎች ሊያዩ ሊሰሙ ወደዱ አላዩም አልሰሙም። ይህንን ያዩ አይኖቻችሁ የሰሙ ጆሮዎቻችሁ ንኡዳን ክቡራን ናቸው" ይባላል።
ምን ለማለት ፈልጌ መሰላችሁ ምንም እንኳን ሰወች፣ ተፈጥሮ፣ እንስሳት የሚያደርሱብን በደል እጅግ ቢበረታም ዛሬ ይህን በደል ለማስቆም መሰባሰባችን መነጋገራችን ትልቅ ነገር ነው። ይህን ሽተው ያላዩ ይኽን የመሰለ እድል ያልገጠማቸው ቤተሰቦቻችን እጽዋት እንዲሁ እድሜያቸው ተቀጭቷል፤ ገሚሶችም ለሌሎች መኖር እነርሱ ትልቁን የመኖር ጉጉታቸውን መስዋእት አድርገዋል።
እኛ እድለኞች ነን። እድላችንን እንዳያመልጠን በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል። መደማመጥ መከባበር ይገባናል። አንዱ ሲናገር ሌላው አድማጭ መሆን አለበት። የሌላውን ሐሳብ እናክብር። አንዳችን ለአንዳችን እንደምናስፈልግ እንመን። በተናጠል መቆም ለአጥቂዎች ተጋላጭ ከመሆን የዘለለ ጥቅም እንደሌለው ልብ እንበል።
እስኪ ከሰወች እንማር፤ ሰወች ክቡር ሆነው ከአንድ አዳም ተፈጥረው ዛሬ በ21ኛው ክ/ዘመን እንደ ግመል ሽንት ወደኋላ ሄደው ዘር ይቆጥራሉ፣ ነጭ ጥቁር ይላሉ፣ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ፣ ወዘተ እያሉ ይከፋፈላሉ።
እስኪ ማን ይሙት ኢትዮጵያ ውስጥ ለዚያውም የሰው ዘር መገኛ በሆነች በሉሲ አገር እንዴት ይከፋፈላል?
በየእምነት ተቋሞቻቸው ስለ ሥነ ፍጥረት እየተማሩ የሰው ልጅ ከአንድ አዳም እንደተገኘ እየተናገሩ መከፋፈልን ከወዴት አመጡት? ከመከፋፈልስ ምን አተረፉ?
ወገኖቼ አሉ እኝህ ታላቅ ዋርካ፦
ምንም እንኳን የረባ ከእናንተ የተሻለ ሐሳብ ባይኖረኝና እድሜ ቢገፋ አሁንም ከእናንተ እኩል የመኖር ጉጉት እንዳለኝ አውቃለሁ።በአጭሩ መቀጨት አልፈልግም። ዝምታው በረጅም ሳቅ ተሰበረ። በጭበጨባ እና በሳቅ አጀቧቸው።
ተናጋሪው ዋርካ እውነቴን ነው ምን ያስቃችኋል? መኖር እኮ የሚጣፍጠው ጣእሙ የሚገባችሁ ስትኖሩ ነው። እኔ ረጅም እድሜ ስለኖርኩ በቃኝ ከማለት ይልቅ የመኖር ትርጉም ስለገባኝ ለመኖር እጓጓለሁ።
ሌሎች እኛን የማጥፋት እና እኛን በአጭሩ የመቅጨት ምክንያት ከመኖር ጉጉታቸው የመነጨኮ ነው ከክፋት አይደለም። ከእኛስ መካከል አሉ አይደል ለመኖር ሲሉ የነፍሳትን እድሜ የመኖር ተስፋ በአጭሩ የሚቀጩ ... የነርሱን ከርሱ ለይታችሁ አትዩት፤ ይልቅስ ... የዛፎች ጉርምርምታ ሐሳባቸውን ገታባቸው። እርሷቸውም ከመናገር ተቆጠቡ ... የአነጋገራቸው አድናቂ፣ የምልካተቸው ተማራኪ ንግግራቸውን እንዳናጠባቸው ትልቁ ዋርካ አወቁ።
አመሰግናለሁ።
አመሰግናለሁ።
ይበቃል፤ ይበቃል ጓዶች።
" ... ይልቅስ ለችግሮች መፍትሔ ለመፈለግ ወደ ውጭ ከማየት አስቀድመን ወደ ውስጥ እናተኩር፤" ብለው ንግግራቸውን ገታ አደረጉት።
አዳማጭን ገረመሙት ....
ሰብሳቢዎችንም በአይናቸው ቃኟቸው...
ሁሉም እየተከታተላቸው ነው ...
ሐሳባቸው ጭንጫ መሬት ላይ እንዳልወደቀ ልብ አሉ።
" ... ልብ ብላችሁ አዳምጡኝ፤ ሐሳቤን እዚህ ጋር ስለሆነ ልብ ብላችሁ አዳምጡ። አልደግመውም።
ጸጥታ ሰፈነ ... አድማጭ የተናጋሪውን የመፍትሔ ሐሳብ ለመስማት ጓጓ፤
ተናጋሪው ዋርካ ዛፍ መልእክታቸውን ለማስተላለፍ ጉሮሮቸውን ጠራረጉ። አሁንም ደግሜ እላለሁ። ልብ ብላችሁ አድምጡኝ፥ ወደ ራሳችን እንመልከት።
ይከታተሉን።
ሐሳብ አስተያየትዎን ከመስጠት አይቆጠቡ።
መልካም ቀን ይሁንልዎ።
ደረሰ ረታ
ነሐሴ 10/2012 አ.ም.
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ