ነሐሴ 11/2012 አ.ም.
እንደ ሰው ልጅ በምክንያት በሰበብ ጥፋተኝነታችንን ወደሌላ አናሸጋግር ሰወች ለችግራቸው መፍትሔ ያጡት ችግሩ ስለከበደ አይደለም። የችግሩ ባለቤት ራሳቸው ሆነው ሳለ መፍትሔ የሚፈልጉት ከሌላ ጉያ ነው። ራሳቸው ላጠፉት ጥፋት ምክንያት ይደረድራሉ።
ሁላችሁም እንደምታውቁት ሁላችንም የተፈጠርነው ለአዳም ጥቅም ሲባል ነበር ነገር ግን የሰው ልጅ የክፋት ሁሉ ምንጭ የሆኑት አዳምና ሔዋን እርስ በርስ ባለመተማመናቸው እና ሐላፊነትን ባለመውሰዳቸው አትብሉ በተባሉት አንዲት ዛፍ ፍሬ አንዳንዳቸው በአንዳቸው ሲመከኛኙ ከገነት ተባረሩ።
እኛስ ለችግራችን መፍትሔ እንድናገኝ እዚህ ተሰብስበን ከሆን መፍትሄውን ከልባችን ሽተን ከሆነ መፍትሔ ከሌላ ስፍራ ከመፈለጋችን በፊት እስኪ ራሳችንን እንመርምር፣ ራሳችንን እንይ፣ ችግሩ የመነጨው ከውስጥ ነው ከውጭ የሚለውን በጥሞና እንፈትሽ።
የሰው ልጅ በዚህ በ21ኛው ክ/ዘመን እንዲህ የሚባላው፣ የሚተላለቀው የችግሩን ምንጭ ባለማግኘቱ ነው። ችግሩን ከጉያቸው ተሸክመው መፍትሔውን ከአጎራባች አገር፣ ከታናናሽ አገር፣ ከኢኮኖሚው አቻቸው፣ ከፖለቲካ ተፎካካሪዎቻቸው ዘንድ ስለሚፈልጉ ነው፤ ይህ ደግሞ ከሰው ልጅ የምንማረው እነርሱ እንደሚተርቱት " ላም ባልዋለት ኩበት ለቀማ " ይሆንብናል።
ስለሰወች ልጆች በማውራት ጊዜያችንን አናባክን እስኪ ሁላችንም ራሳችንን እንይ ... የጥፋታችን ምንጭ ምንድን ነው? ጠላታችን ማነው? ማነው ያጠቃን ማንስ ነው ያጠፋን? ያልን እንደሆነ ሁላችሁም ከዚህ ቀደም ደጋግሜ እንደጠቀስኩት የሰው ልጅ፣ እንስሳት፣ በሽታ እነዚህ ዋነኛ ተጠቃሽ ነው። ነገር ግን እነዚህ እንደ ዋና ችግር የሚጠቀሱ ሲሆን ዋናው ተዋናይ እኛው ነን።
ጉርምርምታው ጨመረ፣ የነበረው ጸጥታ ደፈረሰ፣ ዋርካው ዛፍ አንገታቸውን ዘንበል አርገው ዝም አሉ። በየ አቅጣጫው ጫጫታው ሰሚ አጣ ሁሉም ተናጋሪ ሆነ፤ አድማጭ ጠፋ ሽማግሌው ዛፍ ንትርኩ ማብቂያ እንደሌለው ሲገነዘቡ ከቦታቸው አረፍ አሉ።
ተንጫጭተው ሲያበቁ ወደ ተናጋሪው ቢመለከቱ የሉም። መናገሩን ትተው ዝም ብለው ቁጭ ብለዋል። ይንጫጫ የነበረው ሁላ ተደናግጦ ዝም አለ።
ሰብሳቢ ተሰብሳቢ ጠፋ ሁሉም መንጋ ሆነ ... መንጋነትን ሰወች ከእንስሳት ተረከቡ ዛሬ ደግሞ እጽዋት ከሰወች ተረከቡት ማለት ነው።
የሰው ልጅ መስማት/ማድመጥ ስለተሳነው ነው ዛሬ እንደ እንስሳ ክብሩን የተነጠቀው እና ማስተዋል የተሳነው። ለዚህ ነው እንደተንቀሳቃሽ ሮቦት በሰው አስተሳሰብ የሚነዳው። ክፉና ደጉን መለየት ያቃተው። ሰው በሰው ላይ በራሱ ወገን ላይ በጠላትነት የተነሳው።
አዛውንቱ ዛፍ ብድግ አሉ፤ ሁሉም አፍሮ አቀረቀረ። ጸሐይ እንደመታው ለጋ ቅርንጫፍ በእፍረት ጠወለጉ። እኚህ ትልቅ ዛፍ አንድ የተጣመመ ዛፍ በእጃቸው ምልክት ሰጥተው ወደርሳቸው እንዲመጣ ጠሩት ... መጣ ... ይታያችኋል? ... እስኪ ለሁሉም እንድትታያቸው ወደ መድረኩ ውጣ ... እስኪ ከዚህ ወንድማችን ከዚህ ዛፍ ምን ተመለከታችሁ? ሁሉም በአንድ ድምጽ ከየአቅጣጫው ጠማማ ነው፣ ጎባጣ ነው፣ ... እያለ በተለያየ ቃላት ዛፉን የሚገልጠውን ነገር ተናገረ።
በሰው ልጆችም መካከልም ስንት ጠማማ፣ ስንት ጎባጣ አስተሳሰብ ሰው ያለ መሰላችሁ?
ከዚህ ዛፍ ምን ተማራችሁ?
ይህ ዛፍ የሰው ልጅ እጅ ሲገባ ምን የሚሆን ይመስላችኋል?
ዝምታ ሰፈን።
አይዟችሁ ድፈሩ ... ዝምታችሁ እውነታውን አይቀይረውም።
አብረን እንደመኖራችን ከሰው የወረስነው ብዙ ጠባይ አለ፤ ሰወችም ልክ እንደ እናንተው ናቸው ጥፋተኝነታቸውን ለመሸሸግ፣ እውነትን ለመሰወር፣ ... ዝም ይላሉ።
እውነት ሩቅ ብትሆንም ተሰውራ አትቀርም ፤ ትገለጣለች። የተገለጠች ቀን አንዳች ከፊቷ የሚቆም የለም። እስከዚያ ግን ትንሹም ትልቁም በጠማማ ልቡ ንጹሑን ያጎድፋል፣ ድሃውን ይበድላል፣ ፍርድ ያጓድላል፣ ያሳድዳል፣ ያፈናቅላል፣ ይገድላል።
እኛንም በዚህ ክፋቱ እኛኑ ተጠቅሞ በዚህ በምትመለከቱት ጠማማ ጫፍ ላይ መጥረቢያ ሰክቶ ይጨፈጭፈናል። ያወድመናል። ወደ እሳትም ይማግደናል። ይኽ ጥፋታችን ተሰውሮብን ወደ ወጥመዱ እንንደረደራለን፣ የክፉ ሰወች መጠቀሚያ እንሆናለን።
ሰውም እንዲህ ነው እርስ በርስ በዘር ፣ በሐይማኖት፣ በቀለም፣ በሰፈር፣ ... እየተከፋፈለ የሚጨራረሰው።
"ችግሩን አግኝተናል" አሉ ሰብሳቢው ዛፍ በተናጋሪው ጣልቃ ገብተው፤ ተናጋሪውን ማቋረጥ ፈልገው አይደለም።በስሜት እንጂ መልሳቸው ልባቸው ስለኮረኮረ እነርሱ ያልተመለከቱትን ስላስገነዘቧቸው ለትልቁ ዋርካ አድናቆታቸውንም ለመግለጥ እንጂ።
ጭብጨባ ከአራቱም ማእዘን አስተጋባ።
ችግኞች ፣መካከለኛ ዛፎች፣ ዋርካዎች እየደጋገሙ አጨበጨቡ።
ዋርካው ዛፍ ወደ መቀመጫቸው አመሩ፤
ይቆየን። ወደ አራተኛ ክፍል ሰላም ያሻግረን።
ይከታተሉን።
ሐሳብ አስተያየትዎን ከመስጠት አይቆጠቡ።
መልካም ቀን ይሁንልዎ።
ደረሰ ረታ
ነሐሴ 11/2012 አ.ም.
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ