እሑድ 7 ጁን 2020

ዕርገተ ሕሊና - የሀሳብ ከፍታ በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ


"ዓረገ ውስተ አርያም ጼዊወከ ጼዋ፣ ወወሀብከ ጸጋከ ለእጓለ እመሕያው - ምርኮን ማርከህ ወደ አርያም ወጣህ፣ ለሰው ልጆችም ጸጋህን ሰጠሐቸው" /መዝ 67/8 ፤ 18/

ጌታችን ያድነን ዘንድ ሰው ሆነ፡፡ በዕለተ ትስብእቱም (ሰው በሆነባት ዕለት) ባሕርያችን አከበረ፡፡ በዚያች ሥጋችንና ነፍሳችንን በተዋሐደባት ቅጽበት ባሕረየ ሰብእ በዘባነ ኪሩብ በየማነ አብ ተቀምጧል፡፡
ሰው ሆኖም ሀፍረታችንና ውርደታችን ሁሉ ይቅር ይለንና አሳፋሪ ከመሆንም ያድነን ዘንድ እርሱ ስለእኛ ተዋረደ፣ የአይሁድን ርኩስ ምራቅ ታገሠ፤ ሐፍረትንም ሁሉ ንቆ ክብር ይግባውና ስለሁላችን ድኅነት ራቁቱን ተሰቀለ፡፡ ስለእኛ ሞተ፣ ተቀበረ፣ ተነሣ፣ በዐርባኛውም ቀን ክብር ይግባውና ዐረገ፡፡

ይህ ሁሉ ከጽንሰት እስከ ዕርገት ያለው ሰውን ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ ከዚያም ላቅና ከፍ ወዳለ ጸጋ ለማድረስ ነው፡፡ ከእነዚህ ጸጋዎች አንዱ ዕርገተ ኅሊና ወይም የሀሳብ ከፍታ ነው፡፡

 ይህነን ከፍታ በአጭሩ በሁለት ወገን ከፍሎ መመልከት ይቻላል፡፡ አንደኛው ለሰው የተሰጠውን ጸጋ ተረድቶ በሕግ በአምልኮ እርሱን በመከተል ወደ ሰማያዊ ምሥጢራት በመመንጠቅ ነው፡፡

ይኸውም አባታችን ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ከምድር እስከ ሰማይ ተዘርግታ በላይዋ እግዚአብሔር ተቀምጦባት መላእክት ሲወጡባት ሲወርዱባት እንዳየ ቅዱሳንም እንደ መሰላሉ ቋሚዎች ባሉ ብሉይና ሐዲስ፣ በመሰላሉ ላይ እንዳሉት ርብራቦች ደግሞ በምገባራት ሠናያት (ከጾምና ከጸሎት ሳይለዩ መልካም ተጋድሎን በየደረጃው በመጋደል) ወደ እግዚአብሔር በተጋድሎ ይጓዛሉ፣ ጸጋ እግዚአብሔርን፣ ትርጓሜና መሥጢራትን ተቀብለው ይዘው ይወርዳሉ፤ በትምህርትም ለሰው ዘር ያደርሳሉ፡፡ ይህ መንፈሳዊው ዕርገተ ኅሊና ነው፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ሁላችንንም የሚመለከተው ዕርገተ ኅሊና ወይም የሀሳብ የዕቅድ የተግባር ከፍታን የሚመለከተው ነው፡፡

ይህንንም በምሳሌ አስቀድሞ አስረድቶናል፡፡ በኦሪት ዘሌዋውያን እንደተጻፈው ንጹሐን ስለሆኑት እና ስላልሆኑት፣ ስለሚበሉትና ስለማይበሉት እንሥሣት ሕግን በሰጠበት አንቀጽ ላይ ስለዐሦች የተናገረበት ክፍል ሁላችንንም የሚመለከት ነው፡፡ የሚበሉት የዐሣ ዘሮች ቅርፊትና ክንፍ ያላቸው እንዲሆኑ ታዝዟል፡፡ የዚህም ምሳሌነቱ ግልጽ ነው፡፡

ቅርፊት ለዐሣዎች ራሳቸውን ከሌላ መርዛማ የባሕር ውስጥ አውሬ የሚጠበቁበት ነው፡፡ ክርስቲያንም አብሮት በዚህ ዐለም ከሚኖር የሰው የነገር፣ የክህደትና የጥላቻ መርዝ መጠበቅ ካልቻለ ተጓድቷልና ንጹሕ አይደለም ማለት ነው፡፡

ክንፋቸው ደግሞ መንሳፈፊያቸው የባሕሩ ወለል ላይ ከመንፏቀቅ የታደጋቸውና የባሕሩ ጠለል ድረስ ከፍ ብለው ተንሣፈው ከባሕሩ ውጭ ያለውን ዐለም እንኳ ለመቃኘት የሚያስችላቸው ሀብታቸው ነው፡፡ ክርስቲያንም በሚኖርበት ዐለም በመጨረሻው በዝቀተኛው ደረጃ መሬት ለመሬት ማለትም ምድራዊና ሥጋዊ ነገርን ብቻ በመከተል ራሱን ደካማ ማድረግ የለበትም፡፡ ወደ ክፍታ ብቅ ማለት መቻል አለበት፡፡

ስለዚህም በጥቅምና በክብር፣ በጌጥና በልብስ፣ በምግብና በመጠጥ፣ በቤትና በመኪና ፍላጎት ብቻ ናላው የሚዞር ወይም ለሚያገኘው ምድራዊ ነገር ብቻ የሚንገበገብ እንስሳ መሆነ የለበትም፡፡ ይልቁንም ከራሱ አልፎ ለሌሎች፣ የእኔ ከሚላቸው ተሸግሮ ሌሎች ለሚላቸው፣ ከሰው አልፎ ለፍጥረት ሁሉ የሚያስብ ደግ መሆን አለበት፡፡

ከጊዜያዊ አልፎ ለዘላለማዊው፣ ከቅርቡ አልፎ ለሩቁ ፣ ከምድራዊው ሕይወት አልፎ ለሰማያዊው፣ ከዛሬ አልፎ ለነገ እያሰበ የሚናገር የሚሠራ የሚያቅድ ከፍ ያለ መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡
በባሕርይው ምሉዕ በኩለሔ የሆነው አምላክ ያረገው እኮ የባሕርያችን የእኛን ከፍታ ለመግለጽ እንጂ እርሱማ ሁልጊዜም ልዑል ነው፡፡ በሁሉም ያለ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የተሸከመ እርሱ ነው፡፡

እንግዲያውስ ከዕርገቱ ከፍታን እንማር፡፡ የአነጋገር፣ የአስተሳሰብ የውይይት ባሕል ዝቅታ ይብቃን፡፡ ከወረድንበት አዲስ እንጦሮጦስ እንደምንም ተጎትተን እንውጣ፡፡
ከደንቁርና አዘቅትም ተንደርድረን እውጣ፡፡ ታላቂቱን ቤተ ክርስቲያን በእኛ ደንቁርናና አለማወቅ፣ አለማሰብና አለማቀድ አናሰድባት፡፡

ትልቅ ገደል ውስጥ መሆናችን ተገንዝበን ወደ ላይ ለመውጣት ከፍ ለማለት እንጣጣር፡፡ ከፍ ያደርገን ዘንድ ዐርጓልና ዝቅ ማለት ይበቃን፡፡ እንኳን ለዕርገተ እግዚእ  አደረሳችሁ፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...