እሑድ 7 ጁን 2020

ዸራቅሊጦስ (መንፈስ ቅዱስ)


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ኃይማኖታዊ ሥርዓት መሠረት የዛሬዋ እሁድ በዓለ ጰራቅሊጦስ ይባላል።

 "ወላጆች_እንደሌላቸው_ልጆች_አልተዋችሁም" (ዮ.ሐ14፥18)

✍️ጰራቅሊጦስ፡- ቃሉ ግሪክ ነው፡፡ ጰራቅሊጦስ ማለት

#መጽንኢ በእምነት የሚያጸና፣
#መንጽሒ ከኃጢአት የሚያነጻ፣
#ናዛዚ ያዘኑትን የሚያረጋጋ፣
#መስተፍስሒ፣ የተጨነቁትን የሚያስደስት፣
#ከሣቲ ምስጢርን የሚገልጽ ማለት ነው፡፡

#ጰራቅሊጦስ፡- መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ የጰራቅሊጦስ በዓል ታሪክም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም የሚሠራውን ሥራ ከጨረሰ በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያትን ወደ አባቴ እሄዳለሁ (አርጋለሁ) ሲላቸው ደነገጡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም መደንገጣቸውን አይቶ👉 (ልባችሁ አይደንግጥባችሁ በእግዚአብሔር እመኑ በእኔም እመኑ በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ ማለት ባባቴ ቤት በመንግሥተ ሰማያት ብዙ ማዕርገ ሀብታት አለ) /ዮሐ. 14፥1) እንዲሁም /በዚሁ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 14፥18/ ላይ እንደተጻፈው (ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም) ሲል መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳን ሐዋርያትን አጽናንቷቸዋል፡፡ /በሉቃስ ወንጌል 24 -:- 49/ ላይ እንደተጻፈው የሰላም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊያርግ ሲል ቅዱሳን ሐዋርያትን ( እናንተ ግን ከላይ ኃይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ተቀመጡ) አላቸውና ዐረገ፡፡ እነርሱም ይህን አምላካዊ ቃል መሠረት በማድረግ በኢየሩሳሌም በጽርሐ ጽዮን በማርቆስ እናት በማርያም ቤት ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው ተሰብስበው ሳሉ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአረገ በአሥረኛው ቀን በተነሣ በሃምሳኛው ቀን የጰራቅሊጦስ እለት ጧት በሦስት ሰዓት ለቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ በእሳት አምሳል ወረደላቸው ከዚህ በኋላ ፍርሃት ከውስጣቸው ወጣ መንፈሳዊ ድፍረት አገኙ፡፡

✍️አንድ የዕብራይስጥ ቋንቋ ብቻ ነበር የሚያውቁት ሰባ አንድ ዓይነት ቋንቋ (የአገሩ ሁሉ ቋንቋ) ተገለጸላቸው፡፡ ከእነርሱ ጋር በሰባ ሁለት ዓይነት ቋንቋ ተናገሩ፡፡ የአገሩ ሁሉ ቋንቋ የተገለጸላቸውም ሁሉንም በአገሩ ቋንቋ እንዲያስተምሩ ነው፡፡ ከተለያየ ክፍለ ዓለም የመጡ ነበሩ፡፡ እነዚህ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? እንዴት የእኛን አገር ቋንቋ ሊናገሩ ቻሉ? በማለት ተገረሙና አመንትተው እርስ በርሳቸው እንጃ ይህ ምን ይሆን? አሉ፡፡ ሌሎች ግን ጉሽ የወይን ጠጅ ጠጥተው ሰክረው ነው አሉ  ነገር ግን ቅዱስ ጴጥሮስ ከአሥራ አንዱ ጋር ቆመ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፡- የይሁዳ ሰዎች በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁላችሁ፡- ይህ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን ቃሎቼንም አድምጡ፡፡ ለእናንተ እንደመሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደሉም ከቀኑ ገና ሦስተኛ ሰዓት ነውና ነገር ግን ይህ በነቢዩ ኢዩኤል የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ነው፡- ይህም ‹‹እግዚአብሔር ይላል በኋለኛይቱ ቀን እንዲህ ይሆናል ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች አገልጋዮች ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ ትንቢትም ይናገራሉ፡፡ ድንቆችንም በላይ በሰማይ ምልክቶችንም በታች በምድር ደምም፣ እሳትም የጢስ ጭጋግም ይሆናል የታወቀችዋም ታላቅዋ የእግዚአብሔር ቀን ሳትመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣል የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል›› / ኢዩ. 2፥28-32/ ይህን መሠረት በማድረግ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ልብን የሚነካ ትምህርት ሰጠ፡፡

👉ሕዝቡም ቅዱስ ጴጥሮስ በሰጠው ትምህርት ልባቸው ተነካ ቅዱስ ጴጥሮስንና ሌሎቹንም ሐዋርያት ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ? አሉአቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ንስሐ ግቡ ኃጢአታችሁም ይሠረይ ዘንድ ተጠመቁ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ፡፡ የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነው ስለዚህ ራሳችሁን ከዚህ ክፉ ዓለም አድኑ ብሎ መከራቸው፡፡ በዚህ ቀን ሦስት ሺህ ሰዎች አምነው ተጠመቁ፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው የሞቱና የትንሣኤው ምስክሮች ሆኑ፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በነሱ ላይ ሲያድር ለቤተክርስቲያን ጉዞ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ፡፡

✍️ ይህ የጰራቅሊጦስ በዓል በግሪኮች ቋንቋ #ጰንጠቆስጤ ይባላል፡፡ #ጰንጠቆስጤ ማለት #ሃምሳኛ ማለት ነው፡፡ ጌታችን ከተነሣ በኋላ ሃምሳኛው ቀን ነው፡፡ ይህም ዕለት በዓለ ሃምሳ፣ በዓለ ጰራቅሊጦስ ነው፡፡
✍️ እንዲሁም ታላቁ ሊቅ ቅ/ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን በዓል በሚገባ አነጋገር ‹‹የቤተክርስቲያን የልደት ቀን›› ብሎታል፡፡ ይህ በዓል በብሉይ ኪዳን የእሸት በዓል (በዓለ ሰዊት) ይባላል፡፡ እስራኤል የነጻነት በዓላቸውን ከሚያከብሩበት ከበዓለ ፋሲካ ጀምረው ሃምሳውን ቀን በዓል አድርገው ይሰነብታሉ፡፡ በሃምሳኛው ቀን በዓለ ሰዊትን (የእሸት በዓላቸውን) ያከብራሉ፡፡ በሀገራቸው ከመጋቢት እስከ ግንቦት ያለው ወቅት በሀገራችን ከመስከረም እስከ ኅዳር እንዳለው የእሸት ወራት (የጸደይ ወራት) ነውና የእሸት በዓላቸውን የሚያከብሩት በኦሪት ዘሌዋውያን / ምዕራፍ 23፥10-17/ በታዘዘው መሠረት ማንኛውም እሥራኤላዊ ገበሬ ከዘራው ሁሉ በያይነቱ እሸቱን ቆርጦ ተሸክሞ ወደ ምኩራቡ ይመጣል፡፡
✍️በቤተ መቅደስ የሚያገለግለው ካህን ተቀብሎ ባርኮ ጸልዮ የሚጠበሰው እየተጠበሰ የሚታሸው እየታሸ በማኅበር አንድነት ይበላል፡፡ ይህም ‹‹ #ቀዳምያት›› ይባላል፡፡ የመጀመሪያው ማለት ነው፡፡ ከማንኛውም በረከት የመጀመሪያው እግዚአብሔር ፊት መቅረብ፣ ለእግዚአብሔር መሰጠት እንዳለበት ታዟልና፡፡

✍️ በዚህ መሠረት ከበዓለ ጰራቅሊጦስ የምንማረው፡-ጌታችን አምላካች መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳን ሐዋርያትን ‹‹እናንተ ግን ከላይ ኃይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ተቀመጡ›› ባላቸው መሠረት በኢየሩሳሌም ተቀምጠው ተስፋውን ሲጠባበቁ መንፈስ ቅዱስ ወርዶላቸዋል፡፡ ዛሬ መንፈስ ቅዱስ የሚወርድባት ኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን ናት (ይህች ቀንም ያህል የምታስፈራ ናት? ይህች ሰዓት ምን  ያህል የምታስጨንቅ ናት? መንፈስ ቅዱስ ከሰማየ ሰማያት የሚወርድባት)  /ሥርዓተ ቅዳሴ/ ለቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ እንደ ወረደላቸው ለእኛም እንዲወርድልን ሁልጊዜ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ይገባል፡፡ ከቤተክርስቲያን ተለይቶ ጽድቅ የለም ቤተ ክርስቲያን፡- የመንግሥተ ሰማያት በር ናት (ይህች የሰማይ ደጅ ናት) /ዘፍ 28፥17/ በዚህ መሠረት ለእኛም በ40 ቀንና በሰማንያ ቀን የተሰጠን ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እንዳይለየን ሕጉን ትእዛዙን መጠበቅና ጧት ማታ ወደ ቤተ ክርስቲያን መገስገስ ይገባል፡፡ ለዚህም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንዲሁም ቅዱሳን በአማላጅነታቸው ይርዱን፡፡

እንኩዋን ለበዓለ ዸራቅሊጦስ (መንፈስ ቅዱስ) ዓመታዊ  በዓል በሰላም አደረሳችሁ::

በዛሬ እለት ከ1,978 ዓመታት በፊት አምላካችን መንፈስ ቅዱስ በቅዱሳን ሐዋርያት ላይ መውረዱን እናስባለን::

ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ

ቸር አምላክ ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ሲል፡-
👉ከልዑል ማዕርጉ ወርዶ:
👉በማሕጸነ ድንግል ተጸንሶ:
👉በኅቱም ድንግልና ተወልዶ:
👉ከኃጢአት በቀር በግዕዘ ሕጻናት አድጐ:
👉30 ዘመኑ ተጠምቆ:
👉ቅድስት ሕግ ወንጌልን አስተምሮ:
👉በፈቃዱ ሙቶ:
👉በባሕርይ ስልጣኑ ተነስቶ:
👉በአርባኛው ቀን ያርጋል::

ታዲያ ደቀ መዛሙርቱን የቅዱስ መንፈሱን ጸጋ ተስፋ እንዲያደርጉ ነግሯቸው ነበርና በተነሳ 50ኛው ቀን: በዐረገ 10 ቀን ተስፋውን ፈጸመላቸው:: እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ እንድትይዝ
በአንድ ላይ ሰብስባ ለክብረ መንፈስ ቅዱስ አብቅታቸዋለች:: 120 ቤተሰብ ከጌታችን እናት ጋር ሲጸልዩ መንፈስ ቅዱስ በአውሎ ንፋስ አርአያ ወርዶ በአምሳለ እሳት አደረባቸው::

👉ቅዱሳን ሐዋርያት ፈሪዎች የነበሩ ደፋሮች: አሮጌ ሕሊና የነበራቸው ሐዲሶች ሆኑ:: በአዕምሮ ጐለመሱ: ቁዋንቁዋ ተናገሩ: ምሥጢርም ተረጐሙ:: በቅጽበትም ብሉይ ከሐዲስ በልቡናቸው ውስጥ ተሞላ::

ሐዋርያቱ ቅዱስ መንፈስን ተቀብለው ዓለምን በወንጌል ዕርፈ መስቀል አርሰዋል:: አልጫውን ዓለም ጨው ሆነው አጣፍጠዋል:: ሳይሳሱም አንገታቸውን ለሰይፍ ሰጥተዋል:: "ኪያሁ መንፈሰ ነሢኦሙ ለለአሐዱ: ሐዋርያት ለሰቢክ አሕጉራተ ዓለም ዖዱ: ሰማዕትኒ ለሕማም ነገዱ::" እንዳለ ደራሲ::

በዚህ ቀን 2 ነገሮች በትኩረት ይነገራሉ:-
📌1."የመንፈስ ቅዱስ የባሕርይ አምላክነት:-"
እርሱ ከአብ የሠረጸ: ቅድመ ዓለም የነበረ: በባሕርይ ስልጣኑ ከአብና ከወልድ ጋር እኩል የሆነ: የራሱ ፍጹም አካል ያለው ፍጹም አምላካችን
ነውና::

2."ቅድስት ቤተ ክርስቲያን:-"
አብ ያሰባት: ወልድ በደሙ የቀደሳት: መንፈስ ቅዱስ በጸጋው ያጸናት የክርስቲያኖች አማናዊት አንድነት: አንድም ቤት ናትና:: ዛሬ በጉባዔ
ተመስርታለች::

=>አምላከ አበው ከቅዱስ መንፈሱ ጸጋ ለኃጥአን ባሮቹ ያድለን::

" በዓለ ሃምሳም የተባለው ቀን በደረሰ ጊዜ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ ድንገት እንደሚነጥቅ አውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምጽ መጣ::
ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው:: እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው:: በእያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው:: በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው:: መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር:: +"+ (ሐዋ. 2:1-4)

ወስብሐትለእግዚአብሔር                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                             

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...