ዓርብ 5 ጁን 2020

ሕይወትን እንደ ንሥር አሞራ ኑር!


ንስር አሞራ ፀሐይን ቀጥ ብሎ ማየት የሚችል ወደ ፀሐይ አቅጣጫ ጨረሩን እያየ መብረር የሚችል ብቸኛው ፍጡር ነው። ሌሎች ቁራዎችና ጭልፊቶች 100 ወይም 200 ሆነው ከበው ሲጮሁበት ወደ ፀሐይ እያየ ከፍ ብሎ ይበራል። ሌሎቹ ፍጥረቶች ወደ ፀሐይ እያዩ መብረር ስለማይችሉ ይጠፋባቸዋል!!
- ንስር ከሰው አይን 8 እጥፍ የተሻለ ማየት ይችላል፣
- ንስር ከ 2.30-3 ሜ ይረዝማል፣
- ንስር ከ5-7 ኪሎሜትር ያለን ለማደን የሚፈልገውን ነገር በደንብ ለይቶ ማየት ይችላል፣
- ንስር ለአደን እስከ 120 ኪሎሜትር አካሎ ይበራል፣
- ንስር መጠለያ ከሌለበት አካባቢ ሆኖ ኃይለኛ ዝናብ ቢመጣ ወደላይ በመምጠቅ ከደመና በላይ በሮ ዝናብና ወጀቡን ከስር ያደርጋል እንጂ በዝናብ አይቀጠቀጥም፣
- ንስር አድኖ እንጂ ጭራሽ የሞተ አይበላም፣
- ንስር ሲታመም ፀሐይን አተኩሮ በማየት ነው ህክምና የሚያገኘው፣
- ንስር 340° ማየት ይችላል። ከ360° በአንድ እይታ 340° ማየት ይችላል። ሰው 180° አካባቢ ነው ማየት የሚችለው፣
- ንስር አሞራ እስከ 70 አመት የሚኖር የእድሜ ባለፀጋ ነው ካልክ ልክ ነህ። ግና 70 አመት ሙሉ በደስታ ከመኖሩ በፊት በእድሜው አጋማሽ ማለትም በ35 - 40 ባለው እድሜው ላይ ከባድ ነገር ይገጥመዋል።
የመጀመሪያው ፤
ምግቡን ለማደን የሚገለገልበት ጥፍሮቹ ከመጠን በላይ ስለሚያድጉ ምግቡን ከመሬት ላይ ማንሳት ያቅተዋል፣
ሁለተኛው ፤
አጥንትን ሳይቀር መስበር አቅም ያለው አፉ (መንቁሩ) ስለሚታጠፍና ስለሚጣመም ምግቡን እንደወትሮው መመገብ ይሳነዋል፣
ሶስተኛው፤
ክንፉና በአካሉ ላይ ያሉ ላባዎች ስለሚከብዱት ያ ሰማየ ሰማያትን እየሰነጠቀ ይበር የነበረው ሀይሉ ይክደዋል።
እነዚህ ሶስት ከባድ ነገሮች ንስር አሞራ በእድሜው አጋማሽ የሚያጋጥሙት ከባድ ችግሮች ናቸው። አሁን ንስር አሞራ ያለው ምርጫ ሁለት ነው።
1ኛ. ካረጀ አካሉ ጋር ዝም ብሎ በመቀመጥ ሞቱን መጠበቅ ?
2ኛ. አምስት ወር የሚፈጅ ስቃይና መከራ ያለበት መስዋዕትነትን ከፍሎ ቀሪውን 35 አመት በደስታ ማሳለፍ ?
የመጀመሪያውን ከመረጠ በእድሜው አጋማሽ ይሞታልና ታሪኩ እዛ ጋር ያበቃል።
ሁለተኛውን ምርጫ ከመረጠ ግን እነዚህን አምስት መስዋዕትነቶች ማለፍ ይኖርበታል።
፩ኛ. ከፍተኛ ተራራ ላይ በመውጣት የብቻውን ጎጆ ይቀልሳል።
፪ኛ. ጎጆ ከቀለሰ በኋላ የመጀመርያ ስራዉ የአፉን መንቁር ከአለት ጋር በማጋጨት ነቅሎ ይጥላል።
፫ኛ. ይህን ካደረገ በኋላ አዲስ መንቁር ይወጣለታል፡፡ መንቁሩ እስኪያድግ ድረስ ታግሶ በጎጆው ምንም አይነት ምግብ ሳይመገብ መቆየት ግዴታው ይሆናል፡፡
፬ኛ. አዲስ መንቁር ከበቀለለት በኋላ በአዲሱ መንቁሩ የገዛ እግሩን አሮጌ ጥፍር ነቃቅሎ ይጥለዋል።
፭ኛ. አዲሱ የእግር ጥፍር ከበቀለለት በኋላ ደግሞ ይህንን አዲስ ጥፍር እንደ መሳርያ በመጠቀም በሰዉነቱ የተጣበቁትን እንዳይበር እንቅፋት የሆኑትን የገዘፉና ያረጁ ላባዎችን ነቃቅሎ ይጥላል። በምትኩ አዲስ ላባ ያበቅላል። ይህን 5 ወር በዚህ መልኩ በጀግንነት ከተወጣ በኋላ እንደገና ራሱን በራሱ ወልዶና ወጣት ሆኖ ወደ ንስሮች መንደር ብቅ ይላል፡፡
ንስር እጅግ ግዙፍ፣ እጅግ ጠንካራ፣ በሰማይ ከሚበሩ ሁሉ እጅግ የተለየ ባህርይ ያለው፣ ረጅም እድሜ መኖር የሚችል ሲሆን ድንቢጥ ግን ይህን ልዩ ፍጥረት ትፈታተነዋለች። ድንቢጥ ንስርን ፈተና የምትሆንበት ክንፎቹ ሥር በመግባት በመንከስ ነው።
ንስር ምንም እንኳን ድንቢጥ ፈተና ብትሆንበትም በቀላሉ እጅ አይሰጥም፤ በከፍታ በመብረር ብቃቱ ተጠቅሞ ወደ ላይ ይበራል። ድንቢጥ ንስር ሊደርስበት የሚችለው ክልል መብረር አቅሙ የላትምና ትወድቃለች። ድንቢጥም ፈተና ከመሆን አልፋ ትፈተናለች ትወድቃለችም።
ወዳጄ ሆይ:
ችግር ገጠመኝ ብለህ ያዙኝ ልቀቁኝ አትበል ፣ ችግሬ ...ችግሬ ... እያልክም ነጠላ ዜማ አትልቀቅ ፣ ፊትህንም ችግር ፊት አታስመስል ፣ ጥቅም ላይ እያፈጠጠ የሚከተል ሰው በበዛበት አለም ላይ መውደቅህን መጥሪያ ካርድ አታሰራበት ፣ መራብ መጠማትህን ፖስት ለማድረግ አትቸኩል ፣ መገፋትህን እንደ ትልቅ ነገር ቆጥረህ ኡ.ኡ.. አትበል ፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን የተሻለ ነገር ለመስራት ጣርና ሕይወትህን ቀይር!
ሰው ነህና የሥነፍጥረት ሁሉ ገዥ ተደርገህ ተፈጥረሃልና ሃይልህን፣ ጥበብህን ተጠቀም።
እንደ ድንቢጥ የሚፈታተንህ ዘረኝነት፣ ብሔርተኝነት፣ ፖለቲካ፣ የእምነት ጽንፈኝነት፣ አክራሪነት፣ ሙስና ወዘተ ሊጥልህ ከክብርህ ዝቅ ሊያደርግህ ይጥራልና በከፍታ ብረር፣ በአስተዋይነት ተንቀሳቀስ፣ የዘረኝነት መንደር፣ የብሔርተኝነት የፖለቲካ ጎጥ ውስጥ አትርመጥመጥ፣በሙስና ለመበልጸግ በእምነትህ ልትከፋፈል እጅ አትስጥ።
ለነዚህ ሥትል ከሰውነት ክብርህ ዝቅ አትበል። ሰው ሆነህ እንደተፈጠርክ ሰው ሆነህ ኖረህ ሰው ሆነህ እለፍ።
ፈተናዎችን እንደ ንስር በጥበብ እለፍ።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...