ሐሙስ 29 ኦክቶበር 2020

ሁለት ምርጫ አለን

 ሁለት ምርጫ አለን

ደረሰ ረታ
19/2/2013

ሕጻናት ንጽሕ ናቸው፤ ለዚህም ነው ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋእለ ሥጋዌው ስለ መንግሥተ ሰማያት ሲያስተምር " እንደ ሕጻናት ካልሆናችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት አትወርሱም" ሲል ያስተማረው።

ሕጻናት:-
ከእናት እና ከአባታችሁ ማንን ትወዳላችሁ?
ከከረሜላ እና ከቸኮሌት የቱን ትመርጣላችሁ?
ከእናት ከአባት ከእህት ወንድማችሁ ማንን የበለጠ ትወዳላችሁ?
ወዘተረፈ
ተብለው ለምርጫ ሲጠየቁ
እናቴንም አባቴንም፣
ከረሜላም ቸኮሌትም፣
እናቴንም አባቴንም እህት ወንድሜንም ይሏችኋል።
ደግማችሁ ከሁለቱ አንዱን ምረጡ ብላችሁ ስታስገድዷቸው ሁሉቱንም/ሁሉንም ብለው ድርቅ ይላሉ። ሕጻናት ንጽህ ናቸውና። እምቢ ብትሏቸው እንኳን እምቢ ተጣልቼሃለው/ሻለሁ ብለው ጥለዋችሁ ይሄዳሉ አንዱን ብቻ አይመርጡም። ሌላኛውን ማጣት አይፈልጉምና።

እኛስ?

ከገንዘብና ከሰው፣
ከእምነትህ እና ከፖለቲካ፣
ከአገርህ እና ከጥቅምህ፣
ከወንድምና ከእህትህ፣
ከሥራህ እና ከሃላፊነትህ፣
ወዘተረፈ
ተብለን ስንጠየቅ ምላሻችን ብለን የምንሰጠው ይበልጣል ብለን ያሰብነውን አንዱ ነው እንጂ ምንም አይነት ማስረጃ አግኝተን አይደለም።ተልቀናል/አድገናል ብለን ስለምናስብ ስሌት ( calculation) ውስጥ እንገባለን።

አለማወቃችን ግን ከልጆች የዋህነት እና የልብ ንጽሕና ስለማይበልጥ ምርጫችን ስሕተት ይኖርበታል። በምሳሌ ስንመለከት ጥያቄው ከእናት እና ከአባት ለመምረጥ ምን መስፈርት ተቀምጦልን ነው አንደኛቸውን የመረጥነው? ከገንዘብ እና ከሰው እንዴት ልንመርጥ ቻልን? ሁለቱን አንድ የሚያደርጋቸው ምን መለኪያ ተገኝቶ ነው? እነዚህም እስኪ ይቅሩና ማን ነው አንዱን ብቻ ምረጡ ያለን? እንዲሁ ከሁለት ነገሮች መካከል አንዱን መምረጥ በምርጫ ሕግ ሥለምናውቅ እንጂ።

ሕጻናት ግን በቅንነት እና በፍቅር ሁለቱንም ይመርጣሉ።

አንዳንዶች ሰውን ከገንዘብ፣ ገንዘብን ከሰው ጋር ያነጻጽሩልንና አንዱን ከፍ አንዱን ዝቅ አድርገው በግድ አንዱን ምረጥ ይሉናል። ሁለቱም አስፈላጊነታቸውና መለኪያቸው ለየቅል ነውና።

ስለዚህ እንደ ሕጻናት ስንሆን ሁሉም የኛ ይሆናል። በ"እውቀት" ውስጥ ያጣነውን በየዋህነት እና በቅንነት ውስጥ ሁለቱንም እናገኘዋለን።

ሕይወትን በስሌት መኖር ሐጥያት ባይሆንም ቅሉ በየዋሕነት ሁለቱንም መምረጥ ግን ብልሕነት ነው ሁለቱንም ያስገኘናል እንጂ አያሳጣንም።

ገንዘብንም ሰውንም ይዞ መኖር ይቻላልና።

ከገንዘብ እና ከጤና ምረጡ ለሚሏችሁ ገንዘብንም ጤናንም እንደምትመርጡ ንገሯቸው።

አገርና እምነትን ለሚያስመርጧችሁ ሁለቱንም እንደምትመርጡ ንገሯቸው።

ከፖለቲካ እና ከመንፈሳዊነት ሲያስመርጧችሁ ሁለቱም ምርጫችሁ እንደሆኑ አረጋግጡላቸው።

የሰውን ልጅ ትክክል የሚያደርገው ከሁለት አንዱን መምረጡ ሳይሆን የመረጠውን እንዴት ይጠቅምበታል የሚለው ነውና። አንዳንዶች ገንዘብ ሃጢያት እንደሆነ ያወሩናል ድሕነት ጽድቅ ነው ወይ? ብዬ እጠይቃቸዋለሁ።

እንደዛ ቢሆን ኖሮ ድሆች ሁሉ ጻድቅ ሐብታም ሁሉ ሐጥአን በሆኑ ነበር። ነገር ግን እውነታው ሐብትን በአግባብ መጠቀም አለመቻል ነው ጽድቁም ሐጥያቱም።

ስለዚህ ሁላችንም ሁለት ምርጫ አለን። አንድም ሁለቱን አንድም ሁሉንም መምረጥ።

#######$$#######$$$#######

እኔን ለማግኘት ጽሁፎቼን ለመከታተል ከዚህ በታች የተጠቀሱት ሁሉ ወደ'ኔ ይመሩዎታል።

My Facebook page link (በፌስቡክ ገጽ እንገናኝ)

https://www.facebook.com/deresse2020/

Main facebook account (ዋናው የፌስ ቡክ ገጼ ይቀላቀሉት)

https://www.facebook.com/DeresseReta

Follow me through telegeram (በቴሌግራም ሊከታተሉኝ ከፈቀዱ) ሁሉም ምልከታዬን የማጋራባቸው ማህበራዊ ድረ ገጾች ናቸው።

https://t.me/deressereta

ከአሥር አመት በላይ ከ50ሺ በላይ አንባቢዎች ያሉት መጦመሪያም አለ።

www.deressereta.blogspot.com 

ረቡዕ 28 ኦክቶበር 2020

ባለሁበት አከባቢ መኖሬ እንዲታወቅ እፈልጋለሁ።

 ባለሁበት አከባቢ መኖሬ እንዲታወቅ እፈልጋለሁ።


ደረሰ ረታ
18/2/2013

ፍቅር ቃላት ብቻ ሳትሆን መስዋእትነትን፣ ክርስትና ምኞት ሳትሆን ሕይወት ናትና መኖርን፣ ማድረግን፣ ትሻለች። የአገር እና የቤተ እምነቶች ጥቃት፣ የክርስቲያኖችን እና የሙስሊሞች ስደትና ሞት፣ የአንድነታችን መላላት እየተመለከትን እንዲህ ቢሆን ኖሮ፣ እንዲህ ባይደረግ ኖሮ፣ እያልን ከመመኘት ባለፈ በተግባር የተፈተሸ፣በአርአያነት የተሞላ ማንነት፣ ፍቅርና ሕይወት ይፈልጋል።

ስለዚህ ባለን አጋጣሚ ሁሉ በተሰጠን እድሜና ጤና በየአጥቢያችን፣ በተለያዩ መንፈሳዊ ማህበራት፣ ተሰባስበን በያለንበት የተለያዩ ሕብረቶች በመሳተፍ መንፈሳዊነታችንን መገንባት፣ አገልግሎትን ማበርከት፣ አብያተ እምነትን እና ምእመናንን መርዳት፣ ወዘተ ይጠበቅብናል።ከአንድ ሁለት ይሻላልና።

አንዳንዶቻችን ከንፈር ስንመጥ እና ነገሮች አቅጣጫቸውን እንዲስቱ የተነሱበትን አላማ ይበልጥ እንዲያሳኩ ከማራገብ የዘለለ ፋይዳ የለንም።

አንዳንዶች ደግሞ አይተው፣ ሰምተው፣ ስሜቱን ተገንዝበው ዝምምምም የሚሉ አሉ። አይጠቅሙ አይጎዱ።

ነገር ግን ይህቺን አገር ወደፊት ለማስቀጠልም ሆነ ከጉዞዋ አደናቅፈው ወደኋላ ከሚያስቀሯት ይልቅ አፋቸውን ለጉመው ዝምታን በሚመርጡት ነው። ከአጥፊዎች ይልቅ የ"ገላጋዮች" ቁጥር እጅጉን ይልቃልና።

በልማትም ይሁን በጥፋቱ የሚሳተፉ፣ በማሳደድም ይሁን በማፈናቀል፣ በመግደልም ይሁን አካል በማጉደል፣ በመቀማትም ይሁን ባለማገላገል ከሚሳተፉት እንደ አገርም ሆነ እንደ መንደር ቁጥራቸው የሚበዛው አያገባንም ብለው ዝም ብለው የተቀመጡት ናቸው።

አገርም ሆነ ሕዝቡ አብዝቶ የሚጎዳውም ይሁን የሚጠቀመው ባጥፊዎች ወይም ባልሚዎች ሳይሆን በብዙ ዝምተኞች ምክንያት ነው።

አብዛኛው ሰው በመኖሪያ ቤቱ፣ በመኖሪያ ሰፈሩ፣ በመሥሪያ ቤቱ፣ በእድር በማህበሩ፣ በእቁብ በስብሰባው፣ መኖሩ አይታወቅም፤ እርሱም ብቻ አይደለም ምንም አስተዋጽኦ አያደርግም።ስለዚህ ሰዎች መኖሩን አያውቁትም። በክፉም በደግም ሥሙ አይነሳም።

እኔ ግን ባለሁበት አካባቢ፣ ባለሁበት ማህበረሰብ፣ ባለሁበት መሥሪያ ቤት፣ ባለሁበት እቁብና እድር ትልቅ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን ቢያቅተኝ መኖሬ እንዲታወቅ እፈልጋለሁ። ኖሬ ከሌሎች በተሻለ ባልጠቅምም የለም በሚባል ግን በሥሜ ችግር እንዲፈጸም፣ በዝምታዬ ብዙዎች እንዳይጎዱ ስለምፈልግ።

እስኪ በየስብሰባው በዝምተኞች ችግር በጥቂት ተናጋሪዎች ስንት ውሳኔ እንዳለፈ፣ ስንት ጥፋት እንደተፈጸም፣ ስንት ሐብት እንደተመዘበረ፣ ስንት ሕይወት እንደተቀጠፈ፣ ስንት ትዳር እንደፈረሰ፣ ስንት ቤተሰብ እንደተበተነ፣ ስንትና ስንት ውድቀት አገሪቱ ላይ እንደ ደረሰ።

ከእድር ስብሰባ እስከ ፓርላማ ስብሰባ ስንት ዝምተኞች ስንት መኖራቸው እንኳን የማይታወቁ ሰዎች ዋጋ እንዳስከፈሉን የደረሰብን እናውቃለን።

ባላችሁበት ስፍራ፣ የሃላፊነት ቦታ፣ የተወከሉበት መድረክ፣ በተሰጠዎት አደራ፣ ... ብናገር ባልናገር ባደርግ ባላደርግ በማለትዎትና ዝም በማለትዎ ስንቶች ዋጋ ከፍለዋል? አገር ዋጋ ከፍላለች?

ትልቅ ቦታ አይሁን ተቀጥረውም ይሁን ተመርጠው፣ ተወክለውም ይሁን በበጎ ፈቃደኝነት በሚያገለግሉበት ቦታ የርስዎ ድርሻ ትልቅ እንደሆነ ያምናሉ? ሚሊዮኖች ከጀርባዎ እንዳሉ ይገነዘባሉ? የርስዎ ዝምታ፣ የርስዎ ዝንጋታ፣ የርስዎ አይቶ ማለፍና ሰምቶ መቻል ዋጋ እንደሚያስከፍል ምን ያህል ይሰማዎታል?

ባሉበት ቦታ የርስዎ እንዳሉ/መኖርዎ መታወቅ ማድረግ፣ ተጽእኖ መፍጠር፣ ድርሻዎትን በአግባቡ መወጣት፣ ... የምርጫ ጉዳይ አይደለም። የግዴታ ጉዳይ እንጂ።

ብዙዎች እያሉ እንደሌሉ ተቆጥረዋል፣ ብዙዎች ድምጸ ተአቅቦ አድርገዋል፣ ብዙዎች እስከ መፈጠራቸው ተዘንግተዋል፣ ... በነዚህ ምክንያት አገርና ሕዝቡ ዋጋ እየከፈሉ ነው።

እኔ ባለሁበት አከባቢ መኖሬ እንዲታወቅ እፈልጋለሁ። እርስዎስ?

#$$$#####@@@@####$$$$$&&&&$$#

እኔን ለማግኘት ጽሁፎቼን ለመከታተል ከዚህ በታች የተጠቀሱት ሁሉ ወደ'ኔ ይመሩዎታል።

My Facebook page link (በፌስቡክ ገጽ እንገናኝ)

https://www.facebook.com/deresse2020/

Main facebook account (ዋናው የፌስ ቡክ ገጼ ይቀላቀሉት)

https://www.facebook.com/DeresseReta

Follow me through telegeram (በቴሌግራም ሊከታተሉኝ ከፈቀዱ) ሁሉም ምልከታዬን የማጋራባቸው ማህበራዊ ድረ ገጾች ናቸው።

https://t.me/deressereta

ከአሥር አመት በላይ ከ50ሺ በላይ አንባቢዎች ያሉት መጦመሪያም አለ።

www.deressereta.blogspot.com 

ማክሰኞ 27 ኦክቶበር 2020

ከ"ሚሰበር ይሰንጠር"

 ከሚሰበር ይሰንጠር

ደረሰ ረታ
17/2/2013

አንዳንዶች ከትህትናም ይሁን ከስንፍና በተለይ መንፈሳዊ ነገሮችን ላለማድረግ እኔ ይቅርብኝ፣ እኔ ለዚህ ነገር ብቁ አይደለሁም፣ ከኔ የተሻሉ ሌሎች አሉ፤ በማለት ወደኋላ ሲያፈገፍጉ ይታያሉ።

ይሕ ተግባር ንሰሐ ለመግባት፣ ትዳራቸውን በመንፈሳዊ መንገድ ለመጀመር፣ በአገልግሎት ለመሳተፍ፣ ከዚህም አልፈው ስለአገራዊ ጉዳይ እነርሱን እንደማይመለከት ይሰማቸዋል። አገር የምትመራው በፖለቲከኞች ብቻ ይመስላቸዋል፤ ቢሆንም ቅሉ ፖለቲካን ይፈሩታል ይሸሹታልም።

ነገር ግን የእምነት ተቋምም ይሁን አገር ባላዋቂዎች ባህር ላይ እንዳለች ታንኳ ስትናጥ እነርሱም በዚህ ጉዳይ ጤናቸውን ያጣሉ። ደስታቸውም ሆነ ሰላማቸው ከሁለቱ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነውና።

ስለዚህ:-

ጸሎት ከሚቀር በዝንጉእ ልቡናም ቢሆን ይጸለይ፣
ጾም ከሚቀር ንሰሐ ባንገባም ምጽዋት ባንሰጥም እንጹም፣ በጥቂቱ ስንታመን በብዙ የሚሾም ፈጣሪ ያበረታናልና።

ሥራችን ውጤት አልባ፣ ፍሬ ቢስ ቢሆንም፣ ምንም እንኳን እኛ ብንደክምም፣ ጥቅም ባናገኝበትም እንሥራ፣ ጋን በጠጠር እንዲደገፍ አገርም የኔ ድጋፍ ያስፈልጋታልና።

ውሃ ቢወቅጡት እንቦጭ የሆነ ማንነት ቢኖረንም ቅሉ ተመልሶ ጭቃ ብንሆንም ንስሐ እንግባ፤ እንጹም፣ እንጸልይ፣ ሥጋውን ደሙን እንቀበል፣ እናገልግል፣ ከስንፍና በራቀ ትህትና ውስጥ ሆነን ማገልገል ይጠበቅብናል መንፈሳዊነትም ይገባናል እንበል።

ሰይጣን እና ውሻ አንድ ናቸው፤ ውሻ የእውሩን በትር እንቅስቃሴ አይቶ እንዲሸሽ አይነስውርነቱ ውሻን በበትሩ መከላከል እንዳያግደው ሁሉ እንዲሁ ሰይጣንም በኛ ጸሎት እንደዛው ነው የምንጠራው ሥመ አምላክ ሃይል አለውና። ምንም የልብ ንጽሕና ባይኖረንም የአፋችንን እንቅስቃሴ ተመልክቶ ይሸሻልና እንጸልይ። ጸሎት ካለመጸለይ ይሻላልና። አገርን ማገልገል ካለማገልገልና በሙስና አገርን ከማቆርቆዝ ይሻላልና። ሁሉም ባለበት መስክ ታማኝ ሆኖ ካገለገለ አገር ትበለጽጋለችና።

እያንዳንዱ ሰው በየቤቱ በሕይወቱ ውስጥ እምነቱ የሚያስገድደውን ተግባር በትንሹም ቢሆን ቢያከናውን ካለማድረግ ይሻላል። ከ"ሚሰበር ይሰንጠር" ይላሉና አበው፤ የአገር ጉዳይ የአብያተ እምነት ጉዳይ ተሰብሮ ከሚጣል ተሰንጥሮም ቢሆን ቢቀጥል ይሻላልና። ነገ ስንጥሩ መደፈኑ አይቀርምና።

ስለዚህ ከአገር እና ከየእምነት ሥፍራችን ጋር ያለን ቁርኝት ተሰብሮ ከሚቀር ተሰንጥሮም ቢሆን ይቀጥል ነገ ሌላ ቀን ነውና።

በሌሎች አስተማሪ ጽሑፎች እንድንገናኝ ከታች ያሉትን ሊንኮች ይጠቀሙ።

My Facebook page link (በፌስቡክ ገጽ እንገናኝ)

https://www.facebook.com/deresse2020/

Main facebook account (ዋናው የፌስ ቡክ ገጼ ይቀላቀሉት)

https://www.facebook.com/DeresseReta

Follow me through telegeram (በቴሌግራም ሊከታተሉኝ ከፈቀዱ) ሁሉም ምልከታዬን የማጋራባቸው ማህበራዊ ድረ ገጾች ናቸው።

https://t.me/deressereta

ከአሥር አመት በላይ ከ50ሺ በላይ አንባቢዎች ያሉት መጦመሪያም አለ።

www.deressereta.blogspot.com 

እሑድ 11 ኦክቶበር 2020

በኛ ይብቃ ...

 በኛ ይብቃ ...

ደረሰ ረታ
1/2/2013

አደጋዎች በሽ ናቸው።

የትራፊክ አደጋ፣ በህክምና ስህተት የሚደርስ አደጋ፣ በብሔር ግጭት የሚደርስ አደጋ፣ በሃይማኖት ጥላቻ የሚደርስ አደጋ፣ በፖለቲካዊ አስተሳሰብ የሚደርስ አደጋ፣ በተፈጥሮ ክስተት የሚደርስ አደጋ፣ በሰው ሰራሽ በእቅድ የሚደርስ አደጋ፣ ወዘተረፈ በእነዚህና በሌሎች አደጋዎች የብዙዎች ንብረት ወድሟል፣ አካል ጎድሏል፣ ለስደት ተዳርገዋል፣ ለሞት ተዳርገዋል።

የተረፉት፣ የተጎጂዎች ቤተሰብ፣ የቅርብ ሰዎች በየሚድያው ይቀርቡና "በኛ ይብቃ ... ከኛ ተማሩ" ሲሉ ይደመጣል።

ከመች ወዲህ ነው ጥቃት መማሪያ የሚሆነው?

ከመች ወዲህ ነው ጥቃት መማሪያ የሆነው?

በምን መልኩ ነው መገደል መማሪያ ሊሆን የሚችለው?

እነማንስ ተምረው ድርጊታቸውን አቆሙ?

ከዚህ ልምድ የሚቀስሙት ገዳዮች ወይስ ሟች ነው ትምህርት የሚወስደው?

እኔ በበኩሌ ከዚህ አልማርም፤ በገዳዮች ስሕተት መሞት በቃኝ። በአጥፊዎች ተገፍቼ መኖር በቃኝ። በአሳዳጆች መፈናቀል በቃኝ።

እመራሃለሁ የሚለኝ መንግሥት ከስጋት ነጻ ሊያደርገኝ ይገባል፣ በዚህ ላይ ለተሰማሩት ፍርዲ ሊሰጥልኝ ይገባል፣ ሁሉንም እኔ እየሆንኩ በኔ ይብቅ እያልኩ መኖር በቃኝ።

በብሔር ግጭት የምሰደድ የምሞት እኔ፣ በፖለቲካ ሽኩቻ ንብረቴ የሚዘረፍ እና የሚወድም እኔ፣ በሐይማኖት ግጭት የምገፋ የማምለክ ነጻነቴን የማጣ እኔ፣ ... በቃኝ።

በኛ ይብቃ እያልኩ አልኖርም፤ ፍትህ ይገባኛል።

በሕክምና ስሕተት ህይወት የሚቀጥፉ፣ በፖለቲካ ቁማር ጫወታ ሕዝብ የሚያሰቃዩ አገር የሚያተራምሱ፣ በተረኝነት መንፈስ በሕዝብ ገንዘብ የሚጫወቱ፣ በግዴለሽነት በትራንስፖርት በመኪና አደጋ አካል የሚያጎድሉ ንብረት የሚያወድሙ ሕይወት የሚቀጥፉ የሚቀጡበት ሕግ ይሻሻልልን። ደማችን ፈሶ፣ ንብረታችን ተዘርፎ፣ ተስፋችን ሰልሎ፣ ሕይወታችን አልፎ አይቅር።

"በኛ ይብቃ" ይብቃን። በእነርሱም ተመጣጣኝ ቅጣት ይጣል።

#በወሊድ_ምክንያት_በሕክምና_ስሕተት_መሞት_በቃን
#በመኪና_አደጋ_መሞት_በቃን፣
#በሐይማኖት_ተለይቶ_መሞት_በቃን፣
#በእርስ_በርስ_ግጭት_መሞት_በቃን፣
#በተረኝነት_መገፋፋት_በቃን።

@deressereta

ከወደዱት ያስተምራል ብለው ካሰቡ like እና share ያድርጉ።
My Facebook page link (በፌስቡክ ገጽ እንገናኝ)

https://www.facebook.com/deresse2020/

Main facebook account (ዋናው የፌስ ቡክ ገጼ ይቀላቀሉት)

https://www.facebook.com/DeresseReta

Follow me through telegeram (በቴሌግራም ሊከታተሉኝ ከፈቀዱ) ሁሉም ምልከታዬን የማጋራባቸው ማህበራዊ ድረ ገጾች ናቸው።

https://t.me/deressereta

ከአሥር አመት በላይ ከ50ሺ በላይ አንባቢዎች ያሉት መጦመሪያም አለ።

www.deressereta.blogspot.com 

ረቡዕ 30 ሴፕቴምበር 2020

አርአያነት

 "አርአያነት"


ከምትሰሩት ይልቅ ስለምታጠፉት ነገር ተጠንቀቁ።

ደረሰ ረታ


ሰው የዘራውን ያንኑ ያጭዳልና እያንዳንዳችን ከምንሰራው ይልቅ ስለምናጠፋው ነገር ልንጠነቀቅ ይገባናል።


የአለማችን ትላልቅ ሰዎች ይጠቅማል ያሉት እና እውቀታቸውን ተጠቅመው የሰሯቸው የአእምሯቸው ውጤት ጥፋት ያስከተለባቸው ብዙዎች ናቸው።


የኖቬል ሥራዎች


ጠቢባን እውቀት አይነጥፍባቸውምና ባለቸው እውቅና እና እውቀት ተጠቅመው ጥፋትን አምክነዋል፣ እድሉን ያላገኙት ደግሞ በሌሎች ጠቢባን ጥፋታቸው እንዲመክን ተደርገዋል።


ዛሬ አለማችን በብዙ አቅጣጫ በብዙዎች ስህተት እና ክፋት ጥንስስ እየታመሰች ትገኛለች። አገራችንም ኢትዮጵያ በ"ምሁሮቻችን" ያልተገባ ንትርክ እና ትርክት፣ በልሂቃን ዝምታ፣ በሆድ አደሮች ጫጫታ፣ በፖለቲከኞቻችን ጽንፈኝነት፣ እየታመሰች ነው።


አንዳንዶች ሊነጋ ሲል ይጨልማል ሲሉ ገሚሶች ደግሞ ከድጡ ወደማጡ እያሉ የዳቦ ሥም ያወጡለታል። ግራም ነፈሰ ቀኝ ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል።


ታድያ እኛ ከየትኛው ነን?


እያወቁ ከሚያጠፉት ወይንስ እየሰሩ ከሚጠፋባቸው ወገን ነን?


እንደ አብይ ያነሳነው የመዳሰሻ ርእሳችን "ከምትሰሩት ይልቅ ስለምታጠፉት ነገር ተጠንቀቁ" የተሰኘው ቃላችን ብዙዎቻችን አንድን ተግባር ስንከውን የሚታየን ፊትለፊት ያለው በጎ ነገር እንጂ ከበስተጀርባው ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ልብ አንለውም። ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ጥፋተኝነቱንም ለመቀበል እንቸገራለን።


ለዚህም ነው ችግሩ ከመከሰቱ አስቀድሞ ጥንቃቄ እንድናደርግ ለማሳሰብ የተገደድኩት። ወድጄም አይደለም ጥፋቱ በራሴው ስለተከሰተ ላስተምርበትም ብዬ እንጂ።


ነገሩ እንዲህ ነው፦ ትንሽ ልጅ አለችኝ ሁለት አመት ከመንፈቅ ሆኗታል። እንደ አብዛኛው ቤተሰብ ልጅ ሞባይል ትወዳለች።ሞባይል እጇ እንደገባ "ዩቲዩብ" ውስጥ ገብታ የልጆች መዝሙር እና ጨወታ ትከፍታለች። የሚገርመው ደግሞ አገርኛ አትወድም የውጭውን ካልሆነ በቀር። ይህ ድርጊቷ እንደ አገር በልጆች ፍላጎት ላይ ብዙ መሥራት ያለብን ነገር እንዳለ ይሰማኛል። ይሁን እንጂ "የኢትዮጵያ ልጆች ቴሌቪዥን" ሳላመሰግን አላልፍም።


ወደጉዳዬ ስመለስ ሞባይል መውደዷ እንዳለ ሆኖ ዛሬ ያስተዋልኩባት ነገር ትንሽ ሳይሆን በደንብ ትኩረቴን ስቧል። መሉ በሙሉ ጥፋቱ የኔ ነው። አሁን የጻፍኩላችሁንም ጨምሮ የምጽፈው ሞባይሌን ተጠቅሜ ነው። ታክሲ ውስጥም ሆነ የትኛውም ቦታ ላይ ሆኜ እጽፋለሁ። ርእሴ ማህበረሰቡ ስለሆነ የትም ሆኜ ይጎነትለኛልና።


ይህ የአጻጻፍ ክስተት እቤት ድረስም ይዘልቃል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ታድያ የመጻፍ ትእዛዝ ከውስጤ ሲደርሰኝ፣ መጽሐፍ የማንበብ ዛር ሲመጣብኝ፣ ድካሜን ለማራገፍ ስሻ መኝታ ቤት የመግባት ልምድ አለኝ። ልጄ ሶልያናም የኔ ነገር መጣባት መሰል ወደ መኝታ ቤት ትገባለች። እኔ እንደማደርገው በጀርባዋ ተኝታ፣ እግሯን አነባብራ፣ ሲያሻት በሆዷ ተኝታ ሞባይሏን ትመለከታለች።


እዚህ ጋር ነው ስብራቱ። 


ልጄ ሶልያና ለሁላችንም በኔ በኩል ተናገረች፤


ልጄ ሶልያና ለኔም ለናንተም የሚሆን መልእክት አስተላለፈች መሰል አጋራኋችሁ።


በድርጊቶቻችን መካከል ሁሌም ልብ ልንለው የሚገባ ነገር እንዳለ ይሰማኛል፣ እንቅስቃሴያችን ድርጊታችንን ከመከወን ባሻገር አርአያነት ያለውና ከመሰናክልነት እስከሚችለው አቅም ድረስ የጸዳ መሆን አለበት።


ሁላችንም እንዲህ ነን ሥንሰራ እንስታለን፣ ሥንሰራ እናጠፋለን፣ ሥንሰራ ያልጠበቅናቸው ብዙ ነገሮች ይከናወናሉ፣ ሥለዚህ ስለምንሰራው ብቻ ሳይሆን ከበስተጀርባው ስላለው ስህተት እንድናስብ መልእክቴን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ።


እኔ ለልጄ አርአያነት የጎደለው ተግባር በማሳየቴ አልያም ለስለስ ስናደርገው የምሰራውን ነገር ብቻ ስመለከት ያላየሁት ነገር ልጄ ላይ ተጽእኖ አሳድሯል። ስለምጽፈው ነገር፣ ስለማነበው ጉዳይ፣ ስለምሰራው ሥራ ብቻ ሲሆን በተዘዋዋሪ ግን ስህተት እየሰራሁ እንደሆነ ልብ አላልኩም።


ልክ እንደዚሁ ሁላችንም ለምናደርጋቸው ነገሮች ጥንቃቄ እናድርግ እላለሁ። በመቀጠልም ከፍ ስንል እንደ አገር እንደ ተቋም ትዝብቴን ልሰንዝር።


የተቋማት ሰው ሃይሎች ስለሚቀጥሩት እንጂ ስለሚያባርሩት የቀድሞ ሰራተኛቸው ጥንቃቄ ይጎድላቸዋል። (በአንድ ወቅት በምሰራበት ተቋም አዲስ ተቀጣሪ ሰራተኞች ሥራ ጀምረው ወራት አልያም አመት ይሰሩና ይለቃሉ፣ አልያም በዚያው ይቀራሉ፣ የቅርብ አለቆችም ማስታወቅያ ያወጣሉ በራሱ የለቀቀውን ሰራተኛ ያሰናብታሉ፣ ይሕን ነገር በተደጋጋሚ ማየቴ ሰላም አልሰጥ ሲለኝ ዋና የሥራ ሃላፊውን ገብቼ አነጋገርኩት "ሰራተኞች ከዚህ ክፍል ለምን በብዛት ይለቃሉ? የሚለው ቢጠና ሃላፊነቱ የሰው ሃይል ቢሆንም exit interview እየተጠሩ/መልቀቂያ ለሚወስዱት ቢደረግ" ብዬ ላቀረብኩት ሐሳብ የሚያሳዝን ምላሽ ነበር ያገኘሁት። " ከዚህ የተሻለ ክፍያ የሚያገኙ ከሆነ ይሂዱ እኛም ሌላ እንቀጥራለን" ነበር ያለኝ። እዚህ ጋር ነው ችግሩ ስለምንቀጥረው እንጂ ስለምንለቀው ሰራተኛ አንጨነቅም።


ሐሳቤና ሐሳቡ ተቃርኖ ነበረው እኔ ከስህተታችን እንድንማርበት ስፈልግ እርሱ ስለሚተካው ሰራተኛ ነበር፤ የለቀቅናቸውን ሰራተኛ ክብርና ጥንቃቄ ከሌለን በእጃችን ስላሉት ያለን ጥንቃቄ ምን ዋስትና አለው።


የሥራ ሃላፊዎች ስለሚያሰሩት ሥራ እንጂ ሥለሚሰራው ሰው ጥንቃቄ ይግግድላቸዋል።


የጦር መሪዎች ነጻ ስለሚያወጡት አገር እንጂ በጦርነቱ ስለሚገደሉት፣ ጥቃት ስለሚፈጸምባቸው፣ ስለሚወድመው ንብረት፣ ተልእኮ አሰጣጥ ላይ ጥንቃቄ ጉድለት ይታያል።


ቴሌ፣ መብራት ሃይል፣ ውሃና ፍሳሽ፣ መንገዶች ባለስልጣን ሥራዎቻቸውን ሲያከነውኑ የሚሰሩትን ብቻ ሳይሆን ስለሚጠፋው ነገር የተጠያቂነት ሥሜት ሊሰማቸው ይገባል።


መንገድ ሲቆረጥ እና መስመር ሲዘረጋ የሕብረተሰቡ መሰረተ ልማት እንዳይደረግ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል።


ግለሰቦች አጥራቸውንም ሲጠግኑም ይሁን ሕንጻዎችን ሲገነቡ የነዋሪዎችን እንቅስቃሳ በማያደናቅፍ እና ሕይወታቸውን በማያናጋ መልኩ እንዲሆን ይጠበቃል።


ሁሌም አንድ ወደልቤ የሚመጣ ጉዳይ ላንሳና ላጠናቅ።


አገሪቱ ላይ የተለያዩ ችግሮች ሲከሰቱ፣ የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር፣ ኢኮኖሚው መረጋጋት ሲሳነው፣ ባለሃብትና ነጋዴዎች ለመንግሥት ቅሬታቸውን/አቤቱታቸውን ሲያቀርቡ ሁሉም መንግሥትን ጨምሮ መፍትሔ ሲሰጡ ጫናው የሚያርፈው ድምጽ በሌለው ሰፊው ሕዝብ ላይ ነው።


በቅርቡ የኮቪድ19 የኮረና አለም አቀፍ ወረርሽኝ ወቅት ኑሮ በሁሉም ላይ በትሩን ሲያሳርፍ፣ ኢኮኖሚው አለምን ባሽመደመደበት ዘመን የጤና ተቋማት እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አካል የሆነው የትራንስፖርት አጠቃቀም ውሳኔ የትራንስፖርት ወጪውን እንዲሸፍን የተደረገው ድሃው ሕዝብ ነው።


ስለዚህ ውሳኔዎቻችን አንዱ ጋር መፍትሔ ሰጪ ሲሆኑ ሌላ ሥፍራ ችግር ፈጣሪ እንዳይሆኑ ልንጠነቀቅ ይገባል እላለሁ። ይህ የግሌ እይታ ነው።


እኛ ምርጥ የሚባሉ ሥራዎችና ሐሳቦች ይኖሩን ይሆናል፤ አሉንም። ታድያ እንዚህን እንደ ልጃችን እንደምንሰስትለት ሁሉ ሌላኛውን ያላየናቸውንም እንድናያቸው መልእክቴን አስተላልፋለሁ። ሥራዎቻችን ሃላፊነት እና አርአያነት የጎደለው እንዳይሆን ጥንቃቄ እናድርግ። ከምንሰራው እኩል ስለሚጠፋብን ነገር ትኩረት እንስጥ።


Follow me through 

@deressereta

እሑድ 27 ሴፕቴምበር 2020

ኦርቶዶክሳዊ የአለም እይታችን

 ኦርቶዶክሳዊ የዓለም እይታችን

( Orthodoxy Interpretive frame work )

የዓለም እይታችን በዓለማችን ውስጥ ነገሮች እንዴት እንደሚከናወኑ ለመረዳት እንዲያስችለን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በአእምሮአችን የምንይዛቸው የግምቶች (assumptions) ስብስብ ነው። በእለት ተዕለት ከተፈጥሮ ጋር በምናደርገው ግንኙነት ከእውነታው የራቀ ምኞታችንን የሚወስኑ እነዚህ ግምቶች ናቸው ፡፡

እነዚህ ግምቶች ወደ አዕምሯችን የምንወስዳቸውን ነገሮች የሚተረጉሙበት ለአዕምሯችን እኛን ለመምራት በሚያስችል መልኩ አንድ አምሳያ(model) ይሰጡናል ፡፡

የአስተሳሰባችን እና የሕይወታችን አንድነት አንዲሠምር መሰረት ስለሚያደርግ ይህ የዓለም እይታ ለእኛ በጣም አስፈላጊያችን ነው። ጥሩ ሕይወት ምን ማለት እንደሆነ እና ትርጉም ያለው ምን እንደሆነ ሕይወት እንድንረዳ ያስችለናል ፡፡ ከአካባቢያችን የሚፈጥሩት ተጽእኖዎችን በምንጋፈጥበት ጊዜ ወዲያውኑ ሀሳባችንን እና ድርጊቶቻችንን እንድንመርጥ ይረዳናል ፡፡

የዓለም እይታ ከሌለ በእያንዳንዱ ቅጽበት የሚኖሩ ሁሉንም የስሜት ህዋሳት ግብዓቶችን መረዳት አንችልም ነበር። እኛ ሁላችንም የዓለም እይታ አለን ፡፡ ጥያቄው የእኛ የዓለም እይታ በምን ዓይነት ግምቶች ላይ የተመሠረተ እንደሆነ እናውቃለን? ወይ ነው

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆላስይስ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ በጣም ግልፅ በሆነ ሁኔታ ለክርስቲያኖች በሰጠው ማስጠንቀቅያ- " እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን ፣ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና እና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ ። " ቆላ 2:8 ብሏቸዋል፡፡

የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን ማስጠንቀቂያ በማዳመጥ ከክርስቶስ ይልቅ በዓለም እና በዓለም ባህላዊ ባህሎች በኩል የሚሰጡን ፍልስፍና ማታለያዎች (philosophical deceptions) ምንድናቸው?

ጥቂቶችን እነሆ :-

1. ምክንያታዊነት (Rationalism)

ምክንያታዊነት ለሚደርስባቸው መደምደሚያዎች በአመክኖአዊ አዕምሮአችን ላይ ሙሉ እምነትን ይሰጣል ፡፡ የእውነት ምንነት የሚረጋገጥው እና የሚወሰነው በአእምሮ የማስተዋል አቅምና በሥነ አመክንዮታዊ አስተሳሰብ ላይ ስንደገፍ ብቻ ነው የሚል አመለካከት ነው ፡፡ “I think, therefore I am” የሚለው የፈረንሳያዊ ሬኔ ዴካርት የተለመደው ጥቅስ አስተሳሰባችን ማን እንደሆን እና እኛ የሃሳባችን ድምር እንደሆንን የሚገልጽ አመለካከት ነው።
በሃሳባችን ወይም በምክንያቶቻችን ላይ ሙሉ በሙሉ እምነት ሊኖረን እና እንደ ሥጋችን እና ደማችን እንደሆን አድርገን እንድንጠብቀው ይገፋፋናል።
ይህ አመለካከት የእኛን ፈቃድ በማስቀደም የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደ ሁለተኛ ስለሚቆጥር ከኦርቶዶክሳዊው የዓለም እይታ ጋር ይጋጫል ፡፡ ይህ ደግሞ አስተሳሰባችንን በእጅጉ ወደ ሚቆጣጠሩት ወደ ሌሎች ብዙ ጎራዎች ይመራናል ፡፡

2. ተሞክሮነት / ተዳሳሽነት (Empiricism)

ይህ አመለካከት የእውቀት መሠረት ከስሜታችን አንጻር ሲታይ ተሞክሮአችን እንደሆነ ይገምታል። ይህ የሳይንሳዊ ዘዴ መሠረት ነው። የዚህ አይነት የዓለም እይታ ፍፁም እውነት የሚገኘው ስሜቶቻችን ከሚሰጡን እና እኛ የምናውቀውን በስርዓት ባለው መልኩ በተደረገ ጥናት አማካይነት ብቻ መሆኑን ያረጋግጣል ፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ የተመዘገበውን የመለኮታዊ መገለጥን እውነት ውድቅ ያደርገዋል።

3. ሰብአዊነት / ግለሰባዊነት

ሰብአዊነት እና ግለሰባዊነት የተመሰረተው እውነት እና ሥነ-ምግባራዊ በሆነ መንገድ በሚፈለጉት ግምት ነው። ይኸውም የግለሰቦችን ራስን በራስ ማስተዳደር እና እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ወይም የራሷን እውነት መፈለግ አለበት የሚለውን ሀሳብ ይወስዳል። ይህ በእምነት እና መለኮታዊ በሆነ መንገድ በተገለጡት በእግዚአብሔር ሕግጋት ላይ የተመሠረተ ጥገኛነትን ስለማይቀበል ከኦርቶዶክሳዊው የዓለም እይታ ጋር ይጋጫል ፡፡ ከቤተክርስቲያኒቱ ስልጣን ይልቅ ለእያንዳንዱን ግለሰብ አመለካከት እና ውሳኔ ከፍተኛ ቦታ ይሰጣል ፡፡ ይህ ደግሞ ከመንፈሳዊ እሴቶቻችን ሁሉ አርቆ ፍጹም ወደሆነው አለማዊነት (secularism) ይወስደናል፡፡

4. አንጻራዊነት(Relativism )

አንጻራዊነት መነሻው የሁሉም የፍርድ መሠረቱ አንጻራዊ ነው በማለት ሲሆን ፣ ይህም እንደ ሁኔታውና እንደግለሰቡ ወይም ድርጊቱን ግለሰቡ እንደሚያይበት ሁኔታ ይለያያል ማለት ነው፡፡ የግለሰቡ ወይም የሰዎች ስብስብ እምነቶች እና ሃይማኖት ለእነሱ “እውነት” ነው ብሎ ያስባል ፣ ግን ለሌሎች ግን የግድ እውነት አይሆንም ፡፡ በዚህ ግምቶች ስብስብ በዓለም አቀፍም ሆነ ሙሉ በሙሉ እውነት የሆነ ሃይማኖት የለም ፡፡ እንደዚሁም ሥነ ምግባራዊ ፍፁምነት የሉም ፣ ትክክለኛ ወይም የተሳሳቱ የሥነምግባር አቋሞች የሉም ፡፡ ሁሉም የሞራል እሴቶች ለአንዳንዶች እውነት ናቸው ግን ለሌሎች ግን አይደሉም ፡፡ ይህ ከኦርቶዶክስ ዓለም እይታ ጋር ይጋጫል ክርስትና ፍጹም እውነት ነው ፡፡ ፡ በአንጻራዊነት አመለካከት ምክንያት የራሳችንን እውነት አንዳንድ ጊዜ እንክዳለን ፡፡ ዘመናዊነት ሁሉንም ባህሎች እና ትውፊቶች አይቀበልም ፡፡ የቀደመውን እና የቀደመውን ዘመን “የጨለማ ዘመን” ነው ብሎ ይገምታል። ይህ አመለካከት በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተካተቱትን የቤተክርስቲያን አባቶች እና የቤተክርስቲያኒቷን ሁሉንም ትውፊት በእጅጉ ዋጋ ያሳጣችዋል ፡፡

እነዚህን ሁሉ አንድ ላይ ስናመጣቸው ወደ እግዚአብሔር መኖሩ አይታወቅም ( agnosticism) ወደማለት እና ፈጽሞ እስከመካድ (atheism) ያደርሳል ፡፡ በእነዚህ ሁሉ ጎራዎች እና በውስጣቸውም በያዙት ድብቅ ግምቶች (assumptions) በእኛ ላይ ተጽዕኖ እያሳደሩብን መሆኑን እና በኦርቶዶክሳዊው የሕይወት መንገዳችን ላይ በተቃራኒው እንደቆሙ መገንዘብ አለብን ፡፡ የክርስቶስን እና የቤተክርስቲያኒቷን ትምህርት ሙሉ በሙሉ ለመቀበል እንችል ዘንድ የራሳችንን የዓለም እይታዎችን መመርመር ፣ የተደበቁ ግምታችንን ማሻሻል ፣ መመርመር እና አስፈላጊ ከሆነ እንዲለወጡ መፍቀድ አለብን።

አምላካችን በቅዱሳኑ አድሮ እና በሥጋዌው የተገለጠውን እውነት ሁሉ ተቀብለን ቤተክርስቲያናችንን የነፍሳችን መዳኛ እና የደስታችን ቦታ ማድረግ ይኖረብናል። የራሳችንን የአዕምሯዊ ግንባታ በመተው ፣ “ጌታ ሆይ የማይገባኝ አገልጋይህን እዝነኝ ፥ ባለማወቄና እርዳኝና በእውነትህ ውስጥ ምራኝ ”እንበለው ።

ታሪካችንን አስታውሰን ፣ ኦርቶዶክሳዊነት ያለመለወጥ በሐዋርያት በኩል የጌታችን እና የአዳኛችን ትምህርቶች መሆኑን ተረድተን እንደ የማይለዋወጥ የእውነት ምንጭ መቀበል ይገባናል።

የኦርቶዶክስ የዓለም እይታ ምንድነው?

እኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በአዕምሮአችን የማሰብ ችሎታ ብቻ ለመረዳት ከሚያስችለን በላይ የሆነ እምነት አለን ፡፡ እግዚአብሔር ከሁሉም ምክንያታዊ እውቀት በላይ መሆኑን እናውቃለን ፡፡ በምክንያታዊ ሂደት ወይም በሳይንሳዊ ዘዴ ሊብራሩ የማይችሏቸውን ተዓምራቶች ለመቀበል ምንም ችግር የለንም። ሃይማኖታችን ፍጹም በተገለጠው እውነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ምስጢራዊ እና የማይታየውን እንቀበላለን ፡፡ሁሉን ቻይ እና ፍጥረቱን አፍቃሪ በሆነ አምላክ እናምናለን እንዲሁም ሙሉ በሙሉ እንታመናለን። ከዚህ ሥጋዊ ዓለም ባሻገር በሚመጣው ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ድህነትን እና ከእርሱ ጋር ህብረት እንዲኖረን እንፈልጋለን ፡፡ ኑሯችን በቁሳዊ ደህንነታችን እና ደስታን በመፈለግ ላይ የተመሠረተ የሕይወት መንገድ አይደለም። የቤተክርስቲያኗን ትውፊት እንቀበላለን እናም መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ቤተክርስቲያን ስጦታ አድርገን እንቆጥረዋለን። እኛ በቤተክርስቲያን እና በትውፊታዊ አውድ መሠረት እንተረጉማለን ፡፡ የቤተክርስቲያናችን አባቶች ያቆዩልንን ጥበብ በቀላሉ መጣል አንችልም። በቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜያችን ውስጥ ልንመለከተው ይገባል ፡፡

እንደ ቤተክርስቲያኗ አባልነታችን የክርስቶስ ምስጢራዊ አካል አባላት ነን። ዘመናዊው ማኅበረሰባችን ያስተዋወቀንን የሐሰት እውነቶችን እና ወጎችን በመከተል ወጥመድ ውስጥ እንዳንወደቅ እና መዳንን እና ዘላለማዊ ህይወትን ከእኛ በማራቅ ከእግዚአብሔር ህብረት እንዳይለዩን ከሐሰት ግምቶች መራቅ አለብን። ይህ ቀላል ጉዳይ አይደለም ፡፡ የቤተክርስቲያኗን እውነቶች እና ልምዶች ለመከተል በመወሰናችንም ምናልባትም ከብዙኅኑ ጋር ማለት በሚያስችል ሁኔታ ተቀባይነትን ልናጣ እንችላለን ፡፡
አሁን ያለንበት እውነታ በአእምሯችን ውስጥ የተገነባው በዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤያችን ፣ በኦርቶዶክስ ባልሆኑ ክርስትያኖች በሚሰጡ ትምህርቶች እና የዘመናዊው ትምህርት ስርዓቶቻችንን በሚመሠርቱ ጎራዎች ላይ በመመስረት የተደበቁ ግምቶች ናቸው ፡፡ እነዚህ መሠረተ ቢስ ግምቶች እምነታችንን ያዳክማሉ። እነሱን መመርመር እና ከእምነታችን ጋር የማይሄዱትን በደንብ መለወጥ አስፈላጊ ነው ፡፡ የኦርቶዶክስ የሕይወት መንገድ የኃጢያተኛ አኗኗራችንን እንድንከፍት ፣ የተሳሳቱ አመለካከቶችን እንድንገለጥ እና ባህርያችንን እንድንለውጥ ይመራናል።

እነዚህን የተደበቁ ግምቶች በውስጣችን መኖራቸውን መመርመር የመጀመርያው ሂደት ነው ፡፡ ከኦርቶዶክሳዊው የሕይወት መንገዳችን ጋር የሚጋጩ በገሃዱ ዓለም ያሉ አንዳንድ ነገሮችን ለመለየት የተወሰነ ጊዜ ውሰዱ ፡፡ ከዚያ እራስዎን ይጠይቁ ፣ ቤተክርስቲያኒቷ በእነዚህ ሁሉ ተቃርኖዎች በቅዱሳት መጻህፍቶችዋ እና በትውፊቷዋ እንዴት ልትረዳኝ ትችላለች? ብለው ይማጸኗት

እንጂ

• ብሔረተኛ ሆኖ ኦርቶዶክስ መሆን አይቻልም ! ! !
• እየተሳደቡ ኦርቶዶክስ መሆን አይቻልም ! ! !
• በሰዎች ላይ እየተደገፉ ኦርቶዶክስ መሆን አይቻልም ! ! !
• ቤተክርስትያን ያወገዘችውን እየተከተሉ ኦርቶዶክስ መሆን አይቻልም ! ! !

መልካም ቀን
ዲ. ኤልያስ ደፋልኝ 

በምን መታወቅ ይፈልጋሉ?

 በምን መታወቅ ይፈልጋሉ?

(ምን ሰርተው ታወቁ?)


ከስብ ሥም ይሸታል ይላሉ አባቶቻችን ሲተርቱ። ልጅ እያለሁ ለበአል የቤታችን ግድግዳ ከሚዋብባቸው ጋዜጦች ላይ ከማነባቸው አምዶች መካከል "ምን ሰርተው ታወቁ?" የሚሰኘው ቀልቤን ይገዛዋል።

ኢትዮጵያ የጀግኖች አገር እና ሉአላዊት አገር ለመሆኗ ማረጋገጫው "የአድዋው ጦርነት" ድል የግንባር ላይ ምልክት ያህል ይሁን እንጂ ያኔም ሆነ በዚሁ በዘመናችን ብዙ በሥም ጠቅሰን የማንጨርሳቸው የጦር ሜዳ ጀግኖች አሉን።

ዘመን ተሻጋሪ የአትሌቲክስ ጀግኖች ለመዘርዘር ከመነሳት አለመጀመሩ ሳይሻል አይቀርም። ሰማይና ምድር እንዳይቆጡን በሁለት ወገን የተሳለ ስይፍ የመሰለውን እንቋችንን አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴን አለማንሳት ነውር ነው እንደ ምሳሌ እንጥቀሰው።

መጽሐፍ "እንቁዎቻችሁን በእርያዎች ፊት አታስቀምጡ" የሚለውን ዘንግተን በእርያ ፊት በግብር ስንኩላን ከሆኑት ፊት ሃይሌን በማስቀመጣችን በእጅ የያዙት ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል እንዲሉ ሆነብን።

እርሱ ግን ጽናቱ እና ጀግንነቱ በድቡሽት መሬት ላይ ሳይሆን በአለት ላይ የተመሰረተ ነውና ወይ ፍንክች ያባ ቢላዋ ልጅ ሆኖ አግኝተነዋል። ለማንኛውም ኃይሌ በሁሉም መስክ ጀግናችን ነው።

እስኪ ወደራሳችን እንመለስ።

ምን ሰርተን መታወቅ እንሻለን?

ምንስ እየሰራን ነው ያለነው?

በአንድ ወቅት ካነበብኩት ነገር የማስታውሰው "በሕይወት ዘመንዎ ፍጻሜ በእርስዎ የቀብር ሥነሥርዓት ላይ የሕይወት ታሪክዎ ምን ተብሎ እንዲነበብልዎ ይፈልጋሉ?" የሚል ነበር።

እያንዳንዳችን የሕይወት ታሪካችንን በተግባር እየጻፉ/እየተገበሩ ማለፍ ግድ ቢሆን ሥምዎ በምን እንዲጠራ ይፈልጋሉ?

በሕይወት ዘመንዎ በምን መታወቅ ይፈልጋሉ?

ተማሪ ከሆኑ መምሕሮችዎ ምን አይነት ተማሪ ነበር ብለው እንዲያስታውስዎ ይፈልጋሉ? የትምህርት ቤት ጓደኞችዎሰ?

የመንግሥት ሠራተኛ ከሆኑስ ቀጣሪዎችዎ አልያም የቅርብ አለቃዎ በምን እንዲያውቁዎ/ ምን አይነት ሰው ነው ብለው እንዲጠሩዎ ይፈልጋሉ? የሥራ ሃላፊስ ከሆኑ ምን አይነት አለቃ መባል ይፈልጋሉ?

አገር ቢመሩ?
በንግዱ አለም ቢሆኑ?
የቤተሰብ አስተዳዳሪ (ባል/ሚስት) ሆነውስ?
ልጅ እያሉስ ቢሆን?
የሰፈር ሰው እና ጎረቤትስ?

ሥም ከስብ ይሸታልና እንዲህ ተባልኩ፣ ሰው አይወጣልኝም፣ ደመ መራራ ነኝ፣ እድሌ ጠማማ ነው፣ ወዘተረፈ ከማለት የነገ ሥምዎት ላይ ዛሬ አቅደውና አውቀው ቢሰሩ ይሻላል።

ሥምን ለመገንባት የሚፈጀውን ያህል ሥም ለመጥፋት ጊዜ አይፈጅበትምና በጥንቃቄ እንንቀሳቀስ።

አገሬ ምንም አላደረገችልኝም ከማለት ለአገሬ ምን አደረኩላት የሚለውን አስተሳሰብ እናበልጽግ።

አገር የምታድገውና የምትበለጽገው ተባብረን ሥንቦጠቡጣት ሳይሆን ተባብረን ሥንሰራላት ነውና።

ወጣቶች፣ አረጋውያን፣ ምሁራን፣ የእምነት ተቋማት መምህራን፣ የተቋማቱ መሪዎች፣ የቢሮ ሃላፊዎች፣ ሰራተኞች፣ ነጋዴዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራርና አባላት፣አገር መሪዎች ወዘተረፈ ሁላችንም ከወዲሁ እናስብ፤ ምን ሰርተን መታወቅ? ምን ሰርተን አገራችንን ማስጠራት እንፈልጋለን?

ልብ በሉ ምን ሰርተው እንጂ ምን ሰርቀው አላልኩም።

ሁላችንም እድል ተሰጥቶናል የአዲስ አመት የመጀመሪያው ወር የመጀመሪያው ሳምንት ላይ ስለሆንን እቅዳችንን እናስተካክል፣ ያላቀድን እናቅድ፣ ያቀድን እንኑረው።

ልጆቻችንም ወላጆቻቸው ምን ሰርተን እንዳለፍን የሚመረምሩት ታሪክ ይኑራቸው፣ ያልፈጸምነው እነርሱ የሚጨርሱትን በጎ ነገር እንተውላቸው።

ቸር ይግጠመን።
ደረሰ ረታ
8/1/2013
@deressereta

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...