በምን መታወቅ ይፈልጋሉ?
(ምን ሰርተው ታወቁ?)ከስብ ሥም ይሸታል ይላሉ አባቶቻችን ሲተርቱ። ልጅ እያለሁ ለበአል የቤታችን ግድግዳ ከሚዋብባቸው ጋዜጦች ላይ ከማነባቸው አምዶች መካከል "ምን ሰርተው ታወቁ?" የሚሰኘው ቀልቤን ይገዛዋል።
ኢትዮጵያ የጀግኖች አገር እና ሉአላዊት አገር ለመሆኗ ማረጋገጫው "የአድዋው ጦርነት" ድል የግንባር ላይ ምልክት ያህል ይሁን እንጂ ያኔም ሆነ በዚሁ በዘመናችን ብዙ በሥም ጠቅሰን የማንጨርሳቸው የጦር ሜዳ ጀግኖች አሉን።
ዘመን ተሻጋሪ የአትሌቲክስ ጀግኖች ለመዘርዘር ከመነሳት አለመጀመሩ ሳይሻል አይቀርም። ሰማይና ምድር እንዳይቆጡን በሁለት ወገን የተሳለ ስይፍ የመሰለውን እንቋችንን አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴን አለማንሳት ነውር ነው እንደ ምሳሌ እንጥቀሰው።
መጽሐፍ "እንቁዎቻችሁን በእርያዎች ፊት አታስቀምጡ" የሚለውን ዘንግተን በእርያ ፊት በግብር ስንኩላን ከሆኑት ፊት ሃይሌን በማስቀመጣችን በእጅ የያዙት ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል እንዲሉ ሆነብን።
እርሱ ግን ጽናቱ እና ጀግንነቱ በድቡሽት መሬት ላይ ሳይሆን በአለት ላይ የተመሰረተ ነውና ወይ ፍንክች ያባ ቢላዋ ልጅ ሆኖ አግኝተነዋል። ለማንኛውም ኃይሌ በሁሉም መስክ ጀግናችን ነው።
እስኪ ወደራሳችን እንመለስ።
ምን ሰርተን መታወቅ እንሻለን?
ምንስ እየሰራን ነው ያለነው?
በአንድ ወቅት ካነበብኩት ነገር የማስታውሰው "በሕይወት ዘመንዎ ፍጻሜ በእርስዎ የቀብር ሥነሥርዓት ላይ የሕይወት ታሪክዎ ምን ተብሎ እንዲነበብልዎ ይፈልጋሉ?" የሚል ነበር።
እያንዳንዳችን የሕይወት ታሪካችንን በተግባር እየጻፉ/እየተገበሩ ማለፍ ግድ ቢሆን ሥምዎ በምን እንዲጠራ ይፈልጋሉ?
በሕይወት ዘመንዎ በምን መታወቅ ይፈልጋሉ?
ተማሪ ከሆኑ መምሕሮችዎ ምን አይነት ተማሪ ነበር ብለው እንዲያስታውስዎ ይፈልጋሉ? የትምህርት ቤት ጓደኞችዎሰ?
የመንግሥት ሠራተኛ ከሆኑስ ቀጣሪዎችዎ አልያም የቅርብ አለቃዎ በምን እንዲያውቁዎ/ ምን አይነት ሰው ነው ብለው እንዲጠሩዎ ይፈልጋሉ? የሥራ ሃላፊስ ከሆኑ ምን አይነት አለቃ መባል ይፈልጋሉ?
አገር ቢመሩ?
በንግዱ አለም ቢሆኑ?
የቤተሰብ አስተዳዳሪ (ባል/ሚስት) ሆነውስ?
ልጅ እያሉስ ቢሆን?
የሰፈር ሰው እና ጎረቤትስ?
ሥም ከስብ ይሸታልና እንዲህ ተባልኩ፣ ሰው አይወጣልኝም፣ ደመ መራራ ነኝ፣ እድሌ ጠማማ ነው፣ ወዘተረፈ ከማለት የነገ ሥምዎት ላይ ዛሬ አቅደውና አውቀው ቢሰሩ ይሻላል።
ሥምን ለመገንባት የሚፈጀውን ያህል ሥም ለመጥፋት ጊዜ አይፈጅበትምና በጥንቃቄ እንንቀሳቀስ።
አገሬ ምንም አላደረገችልኝም ከማለት ለአገሬ ምን አደረኩላት የሚለውን አስተሳሰብ እናበልጽግ።
አገር የምታድገውና የምትበለጽገው ተባብረን ሥንቦጠቡጣት ሳይሆን ተባብረን ሥንሰራላት ነውና።
ወጣቶች፣ አረጋውያን፣ ምሁራን፣ የእምነት ተቋማት መምህራን፣ የተቋማቱ መሪዎች፣ የቢሮ ሃላፊዎች፣ ሰራተኞች፣ ነጋዴዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራርና አባላት፣አገር መሪዎች ወዘተረፈ ሁላችንም ከወዲሁ እናስብ፤ ምን ሰርተን መታወቅ? ምን ሰርተን አገራችንን ማስጠራት እንፈልጋለን?
ልብ በሉ ምን ሰርተው እንጂ ምን ሰርቀው አላልኩም።
ሁላችንም እድል ተሰጥቶናል የአዲስ አመት የመጀመሪያው ወር የመጀመሪያው ሳምንት ላይ ስለሆንን እቅዳችንን እናስተካክል፣ ያላቀድን እናቅድ፣ ያቀድን እንኑረው።
ልጆቻችንም ወላጆቻቸው ምን ሰርተን እንዳለፍን የሚመረምሩት ታሪክ ይኑራቸው፣ ያልፈጸምነው እነርሱ የሚጨርሱትን በጎ ነገር እንተውላቸው።
ቸር ይግጠመን።
ደረሰ ረታ
8/1/2013
@deressereta
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ