ረቡዕ 30 ሴፕቴምበር 2020

አርአያነት

 "አርአያነት"


ከምትሰሩት ይልቅ ስለምታጠፉት ነገር ተጠንቀቁ።

ደረሰ ረታ


ሰው የዘራውን ያንኑ ያጭዳልና እያንዳንዳችን ከምንሰራው ይልቅ ስለምናጠፋው ነገር ልንጠነቀቅ ይገባናል።


የአለማችን ትላልቅ ሰዎች ይጠቅማል ያሉት እና እውቀታቸውን ተጠቅመው የሰሯቸው የአእምሯቸው ውጤት ጥፋት ያስከተለባቸው ብዙዎች ናቸው።


የኖቬል ሥራዎች


ጠቢባን እውቀት አይነጥፍባቸውምና ባለቸው እውቅና እና እውቀት ተጠቅመው ጥፋትን አምክነዋል፣ እድሉን ያላገኙት ደግሞ በሌሎች ጠቢባን ጥፋታቸው እንዲመክን ተደርገዋል።


ዛሬ አለማችን በብዙ አቅጣጫ በብዙዎች ስህተት እና ክፋት ጥንስስ እየታመሰች ትገኛለች። አገራችንም ኢትዮጵያ በ"ምሁሮቻችን" ያልተገባ ንትርክ እና ትርክት፣ በልሂቃን ዝምታ፣ በሆድ አደሮች ጫጫታ፣ በፖለቲከኞቻችን ጽንፈኝነት፣ እየታመሰች ነው።


አንዳንዶች ሊነጋ ሲል ይጨልማል ሲሉ ገሚሶች ደግሞ ከድጡ ወደማጡ እያሉ የዳቦ ሥም ያወጡለታል። ግራም ነፈሰ ቀኝ ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል።


ታድያ እኛ ከየትኛው ነን?


እያወቁ ከሚያጠፉት ወይንስ እየሰሩ ከሚጠፋባቸው ወገን ነን?


እንደ አብይ ያነሳነው የመዳሰሻ ርእሳችን "ከምትሰሩት ይልቅ ስለምታጠፉት ነገር ተጠንቀቁ" የተሰኘው ቃላችን ብዙዎቻችን አንድን ተግባር ስንከውን የሚታየን ፊትለፊት ያለው በጎ ነገር እንጂ ከበስተጀርባው ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ልብ አንለውም። ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ጥፋተኝነቱንም ለመቀበል እንቸገራለን።


ለዚህም ነው ችግሩ ከመከሰቱ አስቀድሞ ጥንቃቄ እንድናደርግ ለማሳሰብ የተገደድኩት። ወድጄም አይደለም ጥፋቱ በራሴው ስለተከሰተ ላስተምርበትም ብዬ እንጂ።


ነገሩ እንዲህ ነው፦ ትንሽ ልጅ አለችኝ ሁለት አመት ከመንፈቅ ሆኗታል። እንደ አብዛኛው ቤተሰብ ልጅ ሞባይል ትወዳለች።ሞባይል እጇ እንደገባ "ዩቲዩብ" ውስጥ ገብታ የልጆች መዝሙር እና ጨወታ ትከፍታለች። የሚገርመው ደግሞ አገርኛ አትወድም የውጭውን ካልሆነ በቀር። ይህ ድርጊቷ እንደ አገር በልጆች ፍላጎት ላይ ብዙ መሥራት ያለብን ነገር እንዳለ ይሰማኛል። ይሁን እንጂ "የኢትዮጵያ ልጆች ቴሌቪዥን" ሳላመሰግን አላልፍም።


ወደጉዳዬ ስመለስ ሞባይል መውደዷ እንዳለ ሆኖ ዛሬ ያስተዋልኩባት ነገር ትንሽ ሳይሆን በደንብ ትኩረቴን ስቧል። መሉ በሙሉ ጥፋቱ የኔ ነው። አሁን የጻፍኩላችሁንም ጨምሮ የምጽፈው ሞባይሌን ተጠቅሜ ነው። ታክሲ ውስጥም ሆነ የትኛውም ቦታ ላይ ሆኜ እጽፋለሁ። ርእሴ ማህበረሰቡ ስለሆነ የትም ሆኜ ይጎነትለኛልና።


ይህ የአጻጻፍ ክስተት እቤት ድረስም ይዘልቃል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ታድያ የመጻፍ ትእዛዝ ከውስጤ ሲደርሰኝ፣ መጽሐፍ የማንበብ ዛር ሲመጣብኝ፣ ድካሜን ለማራገፍ ስሻ መኝታ ቤት የመግባት ልምድ አለኝ። ልጄ ሶልያናም የኔ ነገር መጣባት መሰል ወደ መኝታ ቤት ትገባለች። እኔ እንደማደርገው በጀርባዋ ተኝታ፣ እግሯን አነባብራ፣ ሲያሻት በሆዷ ተኝታ ሞባይሏን ትመለከታለች።


እዚህ ጋር ነው ስብራቱ። 


ልጄ ሶልያና ለሁላችንም በኔ በኩል ተናገረች፤


ልጄ ሶልያና ለኔም ለናንተም የሚሆን መልእክት አስተላለፈች መሰል አጋራኋችሁ።


በድርጊቶቻችን መካከል ሁሌም ልብ ልንለው የሚገባ ነገር እንዳለ ይሰማኛል፣ እንቅስቃሴያችን ድርጊታችንን ከመከወን ባሻገር አርአያነት ያለውና ከመሰናክልነት እስከሚችለው አቅም ድረስ የጸዳ መሆን አለበት።


ሁላችንም እንዲህ ነን ሥንሰራ እንስታለን፣ ሥንሰራ እናጠፋለን፣ ሥንሰራ ያልጠበቅናቸው ብዙ ነገሮች ይከናወናሉ፣ ሥለዚህ ስለምንሰራው ብቻ ሳይሆን ከበስተጀርባው ስላለው ስህተት እንድናስብ መልእክቴን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ።


እኔ ለልጄ አርአያነት የጎደለው ተግባር በማሳየቴ አልያም ለስለስ ስናደርገው የምሰራውን ነገር ብቻ ስመለከት ያላየሁት ነገር ልጄ ላይ ተጽእኖ አሳድሯል። ስለምጽፈው ነገር፣ ስለማነበው ጉዳይ፣ ስለምሰራው ሥራ ብቻ ሲሆን በተዘዋዋሪ ግን ስህተት እየሰራሁ እንደሆነ ልብ አላልኩም።


ልክ እንደዚሁ ሁላችንም ለምናደርጋቸው ነገሮች ጥንቃቄ እናድርግ እላለሁ። በመቀጠልም ከፍ ስንል እንደ አገር እንደ ተቋም ትዝብቴን ልሰንዝር።


የተቋማት ሰው ሃይሎች ስለሚቀጥሩት እንጂ ስለሚያባርሩት የቀድሞ ሰራተኛቸው ጥንቃቄ ይጎድላቸዋል። (በአንድ ወቅት በምሰራበት ተቋም አዲስ ተቀጣሪ ሰራተኞች ሥራ ጀምረው ወራት አልያም አመት ይሰሩና ይለቃሉ፣ አልያም በዚያው ይቀራሉ፣ የቅርብ አለቆችም ማስታወቅያ ያወጣሉ በራሱ የለቀቀውን ሰራተኛ ያሰናብታሉ፣ ይሕን ነገር በተደጋጋሚ ማየቴ ሰላም አልሰጥ ሲለኝ ዋና የሥራ ሃላፊውን ገብቼ አነጋገርኩት "ሰራተኞች ከዚህ ክፍል ለምን በብዛት ይለቃሉ? የሚለው ቢጠና ሃላፊነቱ የሰው ሃይል ቢሆንም exit interview እየተጠሩ/መልቀቂያ ለሚወስዱት ቢደረግ" ብዬ ላቀረብኩት ሐሳብ የሚያሳዝን ምላሽ ነበር ያገኘሁት። " ከዚህ የተሻለ ክፍያ የሚያገኙ ከሆነ ይሂዱ እኛም ሌላ እንቀጥራለን" ነበር ያለኝ። እዚህ ጋር ነው ችግሩ ስለምንቀጥረው እንጂ ስለምንለቀው ሰራተኛ አንጨነቅም።


ሐሳቤና ሐሳቡ ተቃርኖ ነበረው እኔ ከስህተታችን እንድንማርበት ስፈልግ እርሱ ስለሚተካው ሰራተኛ ነበር፤ የለቀቅናቸውን ሰራተኛ ክብርና ጥንቃቄ ከሌለን በእጃችን ስላሉት ያለን ጥንቃቄ ምን ዋስትና አለው።


የሥራ ሃላፊዎች ስለሚያሰሩት ሥራ እንጂ ሥለሚሰራው ሰው ጥንቃቄ ይግግድላቸዋል።


የጦር መሪዎች ነጻ ስለሚያወጡት አገር እንጂ በጦርነቱ ስለሚገደሉት፣ ጥቃት ስለሚፈጸምባቸው፣ ስለሚወድመው ንብረት፣ ተልእኮ አሰጣጥ ላይ ጥንቃቄ ጉድለት ይታያል።


ቴሌ፣ መብራት ሃይል፣ ውሃና ፍሳሽ፣ መንገዶች ባለስልጣን ሥራዎቻቸውን ሲያከነውኑ የሚሰሩትን ብቻ ሳይሆን ስለሚጠፋው ነገር የተጠያቂነት ሥሜት ሊሰማቸው ይገባል።


መንገድ ሲቆረጥ እና መስመር ሲዘረጋ የሕብረተሰቡ መሰረተ ልማት እንዳይደረግ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል።


ግለሰቦች አጥራቸውንም ሲጠግኑም ይሁን ሕንጻዎችን ሲገነቡ የነዋሪዎችን እንቅስቃሳ በማያደናቅፍ እና ሕይወታቸውን በማያናጋ መልኩ እንዲሆን ይጠበቃል።


ሁሌም አንድ ወደልቤ የሚመጣ ጉዳይ ላንሳና ላጠናቅ።


አገሪቱ ላይ የተለያዩ ችግሮች ሲከሰቱ፣ የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር፣ ኢኮኖሚው መረጋጋት ሲሳነው፣ ባለሃብትና ነጋዴዎች ለመንግሥት ቅሬታቸውን/አቤቱታቸውን ሲያቀርቡ ሁሉም መንግሥትን ጨምሮ መፍትሔ ሲሰጡ ጫናው የሚያርፈው ድምጽ በሌለው ሰፊው ሕዝብ ላይ ነው።


በቅርቡ የኮቪድ19 የኮረና አለም አቀፍ ወረርሽኝ ወቅት ኑሮ በሁሉም ላይ በትሩን ሲያሳርፍ፣ ኢኮኖሚው አለምን ባሽመደመደበት ዘመን የጤና ተቋማት እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አካል የሆነው የትራንስፖርት አጠቃቀም ውሳኔ የትራንስፖርት ወጪውን እንዲሸፍን የተደረገው ድሃው ሕዝብ ነው።


ስለዚህ ውሳኔዎቻችን አንዱ ጋር መፍትሔ ሰጪ ሲሆኑ ሌላ ሥፍራ ችግር ፈጣሪ እንዳይሆኑ ልንጠነቀቅ ይገባል እላለሁ። ይህ የግሌ እይታ ነው።


እኛ ምርጥ የሚባሉ ሥራዎችና ሐሳቦች ይኖሩን ይሆናል፤ አሉንም። ታድያ እንዚህን እንደ ልጃችን እንደምንሰስትለት ሁሉ ሌላኛውን ያላየናቸውንም እንድናያቸው መልእክቴን አስተላልፋለሁ። ሥራዎቻችን ሃላፊነት እና አርአያነት የጎደለው እንዳይሆን ጥንቃቄ እናድርግ። ከምንሰራው እኩል ስለሚጠፋብን ነገር ትኩረት እንስጥ።


Follow me through 

@deressereta

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...