ባለሁበት አከባቢ መኖሬ እንዲታወቅ እፈልጋለሁ።
ደረሰ ረታ
18/2/2013
ፍቅር ቃላት ብቻ ሳትሆን መስዋእትነትን፣ ክርስትና ምኞት ሳትሆን ሕይወት ናትና መኖርን፣ ማድረግን፣ ትሻለች። የአገር እና የቤተ እምነቶች ጥቃት፣ የክርስቲያኖችን እና የሙስሊሞች ስደትና ሞት፣ የአንድነታችን መላላት እየተመለከትን እንዲህ ቢሆን ኖሮ፣ እንዲህ ባይደረግ ኖሮ፣ እያልን ከመመኘት ባለፈ በተግባር የተፈተሸ፣በአርአያነት የተሞላ ማንነት፣ ፍቅርና ሕይወት ይፈልጋል።
ስለዚህ ባለን አጋጣሚ ሁሉ በተሰጠን እድሜና ጤና በየአጥቢያችን፣ በተለያዩ መንፈሳዊ ማህበራት፣ ተሰባስበን በያለንበት የተለያዩ ሕብረቶች በመሳተፍ መንፈሳዊነታችንን መገንባት፣ አገልግሎትን ማበርከት፣ አብያተ እምነትን እና ምእመናንን መርዳት፣ ወዘተ ይጠበቅብናል።ከአንድ ሁለት ይሻላልና።
አንዳንዶቻችን ከንፈር ስንመጥ እና ነገሮች አቅጣጫቸውን እንዲስቱ የተነሱበትን አላማ ይበልጥ እንዲያሳኩ ከማራገብ የዘለለ ፋይዳ የለንም።
አንዳንዶች ደግሞ አይተው፣ ሰምተው፣ ስሜቱን ተገንዝበው ዝምምምም የሚሉ አሉ። አይጠቅሙ አይጎዱ።
ነገር ግን ይህቺን አገር ወደፊት ለማስቀጠልም ሆነ ከጉዞዋ አደናቅፈው ወደኋላ ከሚያስቀሯት ይልቅ አፋቸውን ለጉመው ዝምታን በሚመርጡት ነው። ከአጥፊዎች ይልቅ የ"ገላጋዮች" ቁጥር እጅጉን ይልቃልና።
በልማትም ይሁን በጥፋቱ የሚሳተፉ፣ በማሳደድም ይሁን በማፈናቀል፣ በመግደልም ይሁን አካል በማጉደል፣ በመቀማትም ይሁን ባለማገላገል ከሚሳተፉት እንደ አገርም ሆነ እንደ መንደር ቁጥራቸው የሚበዛው አያገባንም ብለው ዝም ብለው የተቀመጡት ናቸው።
አገርም ሆነ ሕዝቡ አብዝቶ የሚጎዳውም ይሁን የሚጠቀመው ባጥፊዎች ወይም ባልሚዎች ሳይሆን በብዙ ዝምተኞች ምክንያት ነው።
አብዛኛው ሰው በመኖሪያ ቤቱ፣ በመኖሪያ ሰፈሩ፣ በመሥሪያ ቤቱ፣ በእድር በማህበሩ፣ በእቁብ በስብሰባው፣ መኖሩ አይታወቅም፤ እርሱም ብቻ አይደለም ምንም አስተዋጽኦ አያደርግም።ስለዚህ ሰዎች መኖሩን አያውቁትም። በክፉም በደግም ሥሙ አይነሳም።
እኔ ግን ባለሁበት አካባቢ፣ ባለሁበት ማህበረሰብ፣ ባለሁበት መሥሪያ ቤት፣ ባለሁበት እቁብና እድር ትልቅ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን ቢያቅተኝ መኖሬ እንዲታወቅ እፈልጋለሁ። ኖሬ ከሌሎች በተሻለ ባልጠቅምም የለም በሚባል ግን በሥሜ ችግር እንዲፈጸም፣ በዝምታዬ ብዙዎች እንዳይጎዱ ስለምፈልግ።
እስኪ በየስብሰባው በዝምተኞች ችግር በጥቂት ተናጋሪዎች ስንት ውሳኔ እንዳለፈ፣ ስንት ጥፋት እንደተፈጸም፣ ስንት ሐብት እንደተመዘበረ፣ ስንት ሕይወት እንደተቀጠፈ፣ ስንት ትዳር እንደፈረሰ፣ ስንት ቤተሰብ እንደተበተነ፣ ስንትና ስንት ውድቀት አገሪቱ ላይ እንደ ደረሰ።
ከእድር ስብሰባ እስከ ፓርላማ ስብሰባ ስንት ዝምተኞች ስንት መኖራቸው እንኳን የማይታወቁ ሰዎች ዋጋ እንዳስከፈሉን የደረሰብን እናውቃለን።
ባላችሁበት ስፍራ፣ የሃላፊነት ቦታ፣ የተወከሉበት መድረክ፣ በተሰጠዎት አደራ፣ ... ብናገር ባልናገር ባደርግ ባላደርግ በማለትዎትና ዝም በማለትዎ ስንቶች ዋጋ ከፍለዋል? አገር ዋጋ ከፍላለች?
ትልቅ ቦታ አይሁን ተቀጥረውም ይሁን ተመርጠው፣ ተወክለውም ይሁን በበጎ ፈቃደኝነት በሚያገለግሉበት ቦታ የርስዎ ድርሻ ትልቅ እንደሆነ ያምናሉ? ሚሊዮኖች ከጀርባዎ እንዳሉ ይገነዘባሉ? የርስዎ ዝምታ፣ የርስዎ ዝንጋታ፣ የርስዎ አይቶ ማለፍና ሰምቶ መቻል ዋጋ እንደሚያስከፍል ምን ያህል ይሰማዎታል?
ባሉበት ቦታ የርስዎ እንዳሉ/መኖርዎ መታወቅ ማድረግ፣ ተጽእኖ መፍጠር፣ ድርሻዎትን በአግባቡ መወጣት፣ ... የምርጫ ጉዳይ አይደለም። የግዴታ ጉዳይ እንጂ።
ብዙዎች እያሉ እንደሌሉ ተቆጥረዋል፣ ብዙዎች ድምጸ ተአቅቦ አድርገዋል፣ ብዙዎች እስከ መፈጠራቸው ተዘንግተዋል፣ ... በነዚህ ምክንያት አገርና ሕዝቡ ዋጋ እየከፈሉ ነው።
እኔ ባለሁበት አከባቢ መኖሬ እንዲታወቅ እፈልጋለሁ። እርስዎስ?
#$$$#####@@@@####$$$$$&&&&$$#
እኔን ለማግኘት ጽሁፎቼን ለመከታተል ከዚህ በታች የተጠቀሱት ሁሉ ወደ'ኔ ይመሩዎታል።
My Facebook page link (በፌስቡክ ገጽ እንገናኝ)
https://www.facebook.com/deresse2020/
Main facebook account (ዋናው የፌስ ቡክ ገጼ ይቀላቀሉት)
https://www.facebook.com/DeresseReta
Follow me through telegeram (በቴሌግራም ሊከታተሉኝ ከፈቀዱ) ሁሉም ምልከታዬን የማጋራባቸው ማህበራዊ ድረ ገጾች ናቸው።
https://t.me/deressereta
ከአሥር አመት በላይ ከ50ሺ በላይ አንባቢዎች ያሉት መጦመሪያም አለ።
www.deressereta.blogspot.com
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ