ማክሰኞ 14 ጁላይ 2015

ሳይማር ያስተማረን … … … ሳይማር ያስመረቀን ትዉልድ




የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት
የሚሊንየም አዳራሽ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች በተለያየ የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ፣የሁለተኛ እና የዶክትሬት ትምህርታቸዉን ያጠናቀቁ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ለግማሽ ቀን ያህል አስተናግዶ ዉሎአል፡፡ይህንን ታላቅ የምርቃት በዓል አስመልክቶ ታዋቂዉ የኤፍ.ኤም.ሬድዮ ጣቢያ እዚያዉ ከሚገኘዉ ጊዜያዊ ጣቢያዉ የተማሪዎችን፣ የዩኒቨርስቲዉን መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች፣ የተመራቂ ተማሪዎችን ወላጅ ዘመድ ጓደኞች የእንኳን ደስ አላችሁ እና የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ቀጥታ ስርጭት እያስተላለፈ ይገኛል፡፡
አድማጮቻችን ዛሬ በልዩ ፕሮግራም ከቦሌ አዉሮፕላን ማረፊያ ፊት ለፊት በሰፊዉ ሜዳ ላይ ተንጣሎ ከሚገኘዉ የሚሊንየም አዳራሽ ጊዜያዊ የማሰራጫ ጣቢያችን ይህንን በዓይነቱ ልዩ የተመራቂ ተማሪዎች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ቀጥታ ተቀብለን ለማስተላለፍ እና ከማለዳዉ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ከስፍራዉ በመገኘት ለስለስ ባሉ ጣዕም ባላቸዉ ሙዚቃዎች ስናዝናናችሁ መቆየታችን ይታወሳል፡፡
ለስለስ ያለዉን ሙዚቃ ከዚህ ጊዜያዊ የማሰራጫ ጣቢያችን ያስደመጡንን የስቲዲዮ ባለሞያዎቻችን፣ የደቡብ ሱዳኑን፣ የቻይናዉን እና የደቡብ ኮርያዉን አቀንቃኞች በቅደም ተከተላቸዉ ላመሰግን እወዳለሁ፡፡
አስቀድሜ እንደነገርኳችሁ የዛሬዉ በዓል እጅግ ልዩ ነዉ፤ ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል የአሜሪካዉ ፕሬዘዳንት እዚህ ጎረቤታችን ኬንያ መጥተዉ ጎብኝተዉ በተመለሱበት ማግሥት እና ወደ ኢትዮጵያም በተመሳሳይ ሁኔታ ጉብኝታቸዉን ያደርጋሉ ተብሎ ከሚጠበቅበት ዋዜማ መሆኑ ነዉ፡፡
አድማጮቻችን እንግዲህ የምረቃ መርሀግብሩ እየተጠናቀቀ እና በስፍራዉ የታደሙ የተመራቂ ተማሪ ቤተሰቦች ከአዳራሽ እየወጡ መሆኑ በርቀት ይታየኛል፤ በዚህ ታላቅ የምረቃ በዓል ላይ ክቡር ሚኒስትሩ ባይገኙም የተከበሩት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የአንድ ቋሚ ኮሚቴ ሠብሳቢ የሆኑት እኚህ ሠዉ ከክልል ከመጡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጋራ በጋራ በመሆን ተማሪዎቹን ለማስመረቅ ተገኝተዋል፡፡
ክቡራን አድማጮቻችን እነኚህን ሁለት የአገራችን ታላላቅ ሰወች ስለምርቃቱ እና አንዳንድ ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች አንስተን በሰፊዉ እናወራቸዋለን በጥሞና ተከታተሉን፡፡ እስከዛዉ በጣም የምንወደዉ እና የኢትዮጵያ ወዳጅ እና ባለዉለታ የቦብ ማርሊን stand up for your right የሚለዉን ተጋብዛችኋል፡፡
አድማጮቻችን ሁለቱን የአገሪቱን ታላቅ ባለስልጣናት አየር ላይ ልናቀርብላችሁ የሞከርነዉ ሙከራ ባለስልጣናቱ ለአስቸኳይ አገራዊ ጉዳይ ተጣድፈዉ ባልጠበቅነዉ የመዉጫ በር ስለወጡብን ሙከራችን አልተሳካም፡፡
አድማጮቻችን እንደሚታወቀዉ ብዙ ተማሪዎች ጥሩ ዉጤት በማስመዝገብ የዋንጫ እና የሚዳልያ ተመራቂዎች እንዳሉ ሰምተናል፤ ከነዚህ መካከል አንድ ልጅ እዚህ አጠገቤ አለ ከእርሱ ጋር የማደርገዉን ቆይታ ተከታተሉን፡-
እስኪ ስምህንና እዚህ የተገኘህበትን ምክንያት ለአድማጮቻችን ግለፅልን
̋ ሴባ እባላለሁ የመጣሁት የትምህርት ጊዜዬን አጠናቅቄ ለምርቃት ነዉ የተገኘሁት ˝
እንኳን ደስ አለህ
̋እንኳን አብሮ ደስ አለን  ̋
ሴባ በዛሬዉ ዕለት በመመረቅህ ምን ተሰማህ?
˝ እንዴ! … በጣም … በጣም … ግልግል ነዋ! ትልቅ ግልግል ̋
በምን የትምህርት ዘርፍ ነዉ የተመረከዉ?
˝̋ በFBI ነዉ የተመረኩት፤ ˝
ከFBE ፋክልቲ ማለትህ ነዉ?
˝ ያዉ ነዉ … ምን ልዩነት አለዉ ፍሬንድ  ̋
ከየት አካባቢ ነዉ የመጣኸዉ?
˝ እዚሁ ነኝ ከየትም አልመጣሁም  ̋
ሥምህ ለየት ያለ ነዉ ትርጉሙን ብትነግረኝ?
˝ ጓደኞቼ ናቸዉ ያወጡልኝ እንደምታየዉ ፀጉሬን ሹሩባ መሰራቴን ተከትሎ እና ሴባስቶፖል የሚለዉን ሲያቆላምጡ ነዉ ሴባ ያሉኝ  ̋
ኦ! ሴባስቶፖል ነዉ ሰምህ?
˝ ኖ! ስሜ ቴዎድሮስ ነዉ  ̋
በጣም ጥሩ የዋንጫ ተሸላሚ ነህ መሰለኝ ዋንጫም በእጅህ ሜዳልያዉንም አንገትህ ላይ እንደማየዉ ባለድርብ ድል ነህ፤
˝ አቦ ለገተታ ነዉ ባክሽን … … ከፍሬንዳችን ለፎቶ ተቀብዬ ነዉ  ̋
እናመሰግናለን፡፡
አድማጮቻችን የመጀመሪያዉን ቆይታችንን ተከታትላችሁታል በጣም አዝናኝ እና አስተማሪ ነበር ቀጣዩን ደግሞ አንዲት ወጣት ተመራቂ ከጎናችን ትገኛለች ከእርሳ ጋር ጋር ያለንን ቆይታ ተከታተሉን፡፡
እህታችን እንኳን አደረሰሽ ደስም አለሽ
˝ እንኳን አብሮ ደስ አለን  ̋
ስምሽን እና ስለዛሬዉ በዓል ለአድማጮቻችን የሚሰማሽን ነገር በአጭሩ ብትገልጭልን?        
˝ ስሜ እንኳን ይለፈኝ በአጭሩ የማስተላልፈዉ በዛሬዉ በደስታዮ ዕለት ሳይማሩ ያስተማሩኝን አርሶ አደር ቤተሰቦቼንና ሳይማሩ እዚህ በክብር እንግድነት ተገኝተዉ ያስመረቁንን የክብር እንግዶች፣ የትምህርት ቤቱን ማህበረሰብ ፣ አራት ነጥብ አምጥቼ እንድመረቅ ላበቁኝ መምህራኖቼ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፤ ˝
አድማጮቻችን መርሀግብሩ እንደቀጠለ ነዉ ተከታተሉን … …

ማክሰኞ 16 ጁን 2015

ከእናንተ መካከል ንፁህ የሆነ ይዉገራት (ለአሌክስ አብርሃም)

https://www.facebook.com/alex.abreham.31/posts/1607429286206948
ማህደር የእኛን ማህደር ስትከፍተው !!
(አሌክስ አብርሃም) ለተፃፈዉ ምላሽ ...


“ የተኛዉን በሬ ቆስቁሰዉ አደረጉት አዉሬ ”  ይላል የአገሬ ሰዉ፤ ሰምቼ መፃፍ ያላሰኘኝ ነገር ቢኖር የቢግ ብራዘሩ የሃና ጉዳይ፣ ሊቢያ ላይ የተፈፀመዉ የንፁሐን ዜጎች ደም በከንቱ በኤሲስ መፍሰስ እና መሰዋት፣ አሁን ደግሞ ከግራ ወደ ቀኝ እንደመሰለን ትንሽ ነገር አንጠልጥለን የነፈስንበት የአርቲስት ማኅደር አሰፋ ጉዳይ ናቸዉ፡፡ አሁን ግን የማደንቀዉ ጸሐፊ (ጦማሪ) አሌክስ አብርሃም ፅንፈኛ ሆኖ የፃፈዉ እና ህዝቡን የዘለፈበት ጉዳይ ዝምታን እንዳልመርጥ አድርጎኛል፡፡
1ኛ. ይህ ወዳጄ መጽሐፍ ቅዱስን ደስ ሲለን ብቻ የምንጠቀምበት፣ ሐብታሞች የማይነቀፉበት እና የማይገሰፁበት፣ እሱ ብቻ ሲፈቅድ ለአዕምሮዉ የሚመቸዉ ተግሣፅ ሲሆን ይለፍ የሚለዉ ጉዳይ አስመስሎታል፣ ተግሣፆችንም እንደሱ ፅሑፍ እኔ ካላረምኳቸዉ አይነት ነገር አይቼበታለሁ፣ ሌላዉ ለአሌክስ አብርሃም አክብሮቴ እና አድናቆቴ እንዳለ ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስን እንደ አንድ ተራ ጥራዝ ባያየዉ እመርጣለሁ፡፡
2ኛ.እንደ አንዳንድ የሥነ ፅሑፍ ስነምግባር ያልገባቸዉ የኔ ቢጤዎች ዘለፋ የበዛበት ነገር ባይፅፍ ለዚያዉም አግባብነት የጎደለዉ እንዲህ ስል ግን ተጨባጭነት ያለዉ ተግሳፅ አይገባም ማለቴ አይደለም፡፡
3ኛ. ሰዉየዉ ሃብታም ስለሆኑ ብቻ የሳቸዉ ጉዳይ በክፉ አይነሳ ብሎ አግባብነት የጎደለዉ ሙገሳ ቢያቆም፤ እኚህ ሰዉ በአንድም በሌላም ምክንያት ለዚህ ህዝብ ባለዉለታ መሆናቸዉ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚነገረዉ አይደለም፡፡ ገንዘብ ሰጡ ማለት ንፁህ በኩለሄ (ሁሉም ቦታ ንፁህ ) ናቸዉ ማለት እንዳይደለ ልብ ቢል ሰብአዊነታችን በሳንቲም ድቃቂ ሲገዛ ዝም የምንል ህዝቦች መሆን የለብንም እና፡፡
4ኛ. ሌሎች ሃብታሞች በየጓዳ ጎድጓዳዉ ያሻቸዉን ስለሚሰሩ እሳቸዉን ዝም ማለት ከየት የመጣ የበደል ማጣፊያ ነዉ? አልገባኝም
5ኛ. አዎ ማኅደር አገር የሚያደንቃት ባለሙያ ነች ይህ ማለት ግን እንዳሻት እንድትሆን ማካካሻ አይደለም፤ እርሷ ስታጠፋም ዝም እንድንላት ይህን ያህል የወረደ ሞራል እንደሌለን ልብ በል፡፡ ይህ ህዝብ እንኳንስ በቴሌቭዢን መስኮት ያያትን ማኅደርን ይቅርና አንተን የሚያደንቁ አድናቂዎችህ ፅሑፍህን ታዝበዉ እንዴት አስተያየት እንደሚሰጡህ ልብ በል፡፡
6ኛ. እዛዉ ማኅደር ላይ ባለህ አቋም እርሷ ለዚህ መጪ ትዉልድ (ህፃናት) አርአያ ካልሆነች ማን ሊሆን ነዉ ሲጀመር እኮ አንተ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ጥፋቷ እንደወደድካት ህዝቡም (ህጻናትም) እንደዚያዉ ማድረግ እንዲችሉ ማድረግ አይቻልም፡፡
ሳጠቃልለዉ እንደጦማሪነትህ ሃላፉነትህ ይህ ነዉ? እንዲህ ሽንጥህን ገትረህ የተከራከርከዉ፣ አርቲስት መሐሙድን፣ ባለፀጋዉ የለገሱትን ገንዘብ እያጣቀስክ የፃፍከዉ እንደ አርቲስቶቹ የብር ሽልማቶችን ሽተህ ይሆን? ሰዉየዉ እንኳን ፅፈህ … ካልፈለጉ አይሰሙም፤ ህዝቡን ያዝ …
እኔ እና እኔን ለምትመስሉት፡­
በሰዉ በደል ሆያ ሆዬ ለምንል እስኪ የሌሎችን ጉድፍ ትተን የራሳችን ምሰሶ ዞር ብለን እንመልከት፤ አሌክስን ባስቆጣዉ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዳለዉ ታሪክ ( አንዲት ሴት ስታመነዝር ቢያገኙዋት ጌታ ጋር ይዘዋት በመሄድ ከሰሱዋት እንዲህ በማለት “ ስታመነዝር አገኘናት  ስለዚህ እንደ ስርአታችን በድንጋይ ወግረን እንድንገድላት ፍቀድልን ” በማለት  ጌታም “ በአጭሩ ከእናንተ ንጹሕ የሆነ ይዉገራት … ) በደላቸዉን ያዉቀዉ ነበር እና እንዲህ አለ፡፡ አሁንም እኔም እላለሁ ከማኅደር ንጹሕ የሆነ ፌስ ቡክ ላይ ይፃፍ፣ ይተቻት፣ ይማት፣ ይስደባት፣ ….
የተሻለ ነገር አለን የምንል ደግሞ ለዚህ ትዉልድ በጎዉን ቃል እንፃፍ ፣ በጎዉን ነገር እናሳይ፣ በጎዉን እንኑር፣ …   

ሕዝብ ለምን ይቆጣል?



ሕዝብ ፡­ በቋንቋ:በሃይማኖት፡በሕገ መንግሥት፡በታሪክ፡በልማድ፡በኑሮ አንድነት ኅብረት ያንድ መንግሥት አጽቅነት ማለት ነዉ፡፡ከሣቴ ብርሃን ተሰማ የአማርኛ መዝገበ ቃላት እንደሚለዉ፤
የኢትዮጵያ ህዝብ የራሱ የሆነ ቋንቋ ፣ሃይማኖት፣ሕገ መንግሥት ፣ታሪክ ፣ልማድ፣ኑሮ፣ባህል፣ያለዉ ቢሆንም ለረጅም አሥርት ዓመታት እየተፈራረቁ ሲገዙት ወይም ሲያስተዳድሩት ከነበሩት መንግሥታት ( ነገሥታት ) ክፋት እና በጎ አሳቢነት ከማጣት ፣ከልማት ይልቅ       “ ረሃብ ” ሲጫወትበት ኖሯል፡፡ ከዚህም ባሻገር አገሪቱ በዉስጥም ሆነ በዉጭ ጠላቶቿ ሠላም በማጣት ልጁን ለጦርነት እየማገደ ፣ ራሱም በረሃብና በበሽታ አለንጋ እየነደደ 21ኛዉ መቶ ክ⁄ዘመን ላይ ደርሷል፡፡ይሁን እንጂ ኑሮዉ ያልተሻሻለ ፣ ስላሙ ያልተረጋጋለት የህብረተሰብ ክፍል በሃገሪቱ ላይ በብዛት ይገኛል፡፡ እንኳን የገጠሩ የከተማዉ ነዋሪ የተሻለ ኑሮ ይኖራል፣ የተሟላ ነገር አለዉ፣ ለዕድገት እና ለለዉጥ ቅርብ ነዉ፣ … ወዘተ የተባለዉ ህይወቱ የሃዘን እንጉርጉሮ የበዛበት ነዉ፡፡ መፈጠሩን እስኪጠላ ይማረራል፡፡እንደ ትናንቱ ለመሬት ከበርቴዉ እና ለወኪሉ የጉልበት አገልግሎት አይስጥ እንጂ ዛሬም ህብረተሰቡን ሙስና አቅሙን አሳጥቶታል፡፡ አጥር ማጠር፣ቤት ማደስ፣የወር ተራ ገብቶ በዘበኝነት ማገልገሉ፣ በእርሻ መሳተፉ ቢቀርለትም በየቢሮዉ ጉዳዩን ለማስፈፀም ደፋ ቀና ማለት፣ነገ ተመለስ፣ ጉዳዩን የሚያከናዉንልህ አለቃ ስብሰባ ላይ ነዉ፣ ማኅተም የምታደርገዋ ፀሐፊ ዛሬ ስራ አልገባችም፣ እገሌ የሚባሉት ሰዉ ዛሬ ⁄ ሰሞኑን የሉም፣ … ወዘተ የሚሉ ምክንያቶች ደሃዉን ሆነ ሃብታሙን የህብረተሰብ ክፍል ቀና ብሎ እንዳይሄድ አድርገዉታል፤ ከትላንት የተሻለ ቀንም እንዳይወጣለት አድርገዉታል፡፡ከዚህም ባሻገር በየተቋማቱ ያሉ ( የተንሰራፉ ) ዘረኝነት፣ ጎጠኝነት፣ በፖለቲካ የልዩነት ፍጭት፣ ትልቅ የራስ ምታት እና ሰፊዉ ህብረተሰብ አገልግሎት ለማግኘት ሁለተኛ እዚህ ስፍራ ብደርስ ብሎ እንዲማረር አድርጎታል፡፡ ( ዝሆኖች ሲራገጡ ሳሩ ይጎዳልና ህብረተሰቡ ትልቅ በደል እና ጉዳት ደርሶበታል ) ከትናንት በስትያ ፣ ትናንት እና ዛሬም ድረስ የዘለቀዉ ዘመን ተሻጋሪ ነቀርሳ ኢትዮጵያ ሰፊ መሬት ያጣች ይመስል በልማት ሰበብ የህዝቡ ለዓመታት ይኖርበት ከነበረ ፣ ተወልዶ ካደገበት ማፈናቀልና በየሄደበት ቦታ ከነባር ነዋሪዉ ጋር ግጭት መፍጠር፣ አልነሳም ትነሳለህ በሚል ክርክር ከገዢዉ ጋር እሰጣገባ ዉስጥ መግባት፣ ሃብት ንብረቱን ብቻ ሳይሆን ድበደባ ፣ እስር ፣ እንግልት፣ ጤናዉን ማጣት፣ሰደት፣ አልፎ ተርፎም ሞት ይደርስበት ነበር፡፡
በቀደሙት ስርዓት አርሶ አደሩ ካረሰዉ እና ከሚያረባዉ ለከበርቴዎች እንደሚገብረዉ ሁሉ ዛሬም ህብረተሰቡ ትናንት በወጣዉ የግብር ተመን መሠረት ( ህብረተሰቡን ለሞት ለእስር ለእንግልት ) የዳረገዉን የተለያየ ቁጣ ያስነሳዉን የግብር ተመን አሁንም ያለምንም ማሻሻያ ገበሬዉም ነጋዴዉም የመንግሥት ሠራተኛዉም የቀን ሠራተኛዉም ሁሉም እኩል እንደ ገቢዉ መጠን እስከ 35% ድረስ ይገብራል ( ይበዘበዛል)፡፡

ሰኞ 15 ጁን 2015

የህይወት ታላቁ ፈተና “ጠላትህን ዉደድ” (ክፍል ሦስት)



ባለፉት ሁለት ተከታታይ ክፍሎች “ ጠላትን ” ስለመዉደድ ጥቂት ነገር ብለናል በዛሬዉ ፅሁፋችን ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የመጨረሻዉን ክፍል እንመለከታለን፤ እግዚአብሔር “ጠላቶቻችን” እንድንወድ ያስችለን፡፡
ጠላቴን ለመዉደድ የሚያስችለኝ ነገር ምን ላድርግ? (ምን መደረግ አለበት?)
ጠላትህን ለመዉደድ እነዚህን ነገሮች ሳታወላዉል አድርግ!
ምናልባት እነዚህን የተዘረዘሩትን ነገሮች በሙሉ በአንዴ ለማድረግ ይከብዱ ይሆናል፤ ይከብዳሉም፡፡ ነገር ግን የሚከብደዉን ሁሉ እንተወዋለን ፣ እንሸሸዋለን ማለት አይደለም፡፡ ማንኛዉም የዓለማችን ነገሮች የመለማመድ ዉጤት ናቸዉና ዘወትር በድርጊታችን ዉስጥ እንለማመዳቸዉ፡፡ በእርግጠኝነት ለዉጥ እናመጣባቸዋለን … ለዚያዉም በጣም የሚያስደንቅ … ነገር ግን ብዙ መንገድ ያስጉዙናል፡፡ቢሆንም ግን ጥቂቶች ለእኔ እስከ አሁን ጠቅመዉኛል በእርግጠኝነት አንተንም ይጠቅማሉና ሞክራቸዉ፤ ከታች በዝርዝር የተቀመጡትን ፈፅማቸዉ፡፡
        i.        ጠላቴ ስለምትለዉ ሰዉ ከዚህ ቀደም የሚሰማህን ነገር ማሰብ አቁም፡­ በፊት ስለሚሰማህ ስሜት ደጋግመህ አስብ ( አስር ጊዜ )፤ አሁን ደግሞ የሚሰማህን አስብ እዉነት ያንን ነገር ማቆምህን ራስህን ገምግመዉ እርግጥ ነዉ በአንዴ ሃሳብህን መቆጣጠር ሊከብድህ ይችላል ነገር ግን ደጋግመህ አድርገዉ ( እርሳዉ )
       ii.        ራስህን በእርሱ ቦታ አድርገህ አስብ፡­ ያኔ በዉስጥህ የሚመጣዉን ጥላቻ ታስወግደዋለህ፤ እርሱ ያደረገዉን ድርጊት አንተም እርሱ ቦታ ብትሆን ታደርገዋለህና፡፡በቃ አሁን ያ ሰዉ ማለት አንተ ነህ፡፡ ያ ሰዉ እንደ አንተ ትክክለኛ ሰዉ የነበረ ነዉ ያ አጋጣሚ በርሱ ላይ ይህን ክፉ ድርጊት አመጣበት እንጂ፤ ስለዚህ ይህን ሰዉ ከመጥላት ያንን ክፉ ድርጊት ጥላ፡፡ በዚህ አጋጣሚ የለጠልህ ጥሩ ሰዉ ሁን፡፡ የሰዉ ልጅ በጠቅላላ ጥሩ ነገር ለማድረግ ይጥራል ነገር ግን ስህተት ይሰራል፡፡ ስህተት እና ጥፋት ይለያያል፡፡ እንኳን ለተሳሳተ ላጠፋም ይቅርታ ማድረግ ግድ ይለናል፡፡ አለበለዚያ በድርጊቶች ላይ የተለያየ አመለካከት አለዉ፡፡ አንድን ነገር ከተለያየ ቦታ ላይ መመልከት እጅግ ይከብዳል ግን እጅግ ይጠቅማል “ 6 ” ይህን ቁጥር አንተ ስትፅፈዉ ስድስት ስትለዉ ከፊት ለፊትህ ለተቀመጠዉ ደግሞ “ 9 ” ሆኖ ስለሚታየዉ ዘጠኝ ሊለዉ ይችላል፡፡ ችግሩ ከቁጥሩ  ወይንም ከሰዉየዉ ሳይሆን ሰዉየዉ ከተቀመጠበት ቦታ ነዉ፤ ስለዚህ አንድን ነገር ከመወሰናችን በፊት ራሳችንን ከሰዉየዉ ቦታ አድርገን ብንመለከተዉ መልካም ነዉ፡፡
      iii.        ልትረዳዉ ሞክር፡­ በርሱ ቦታ ራስህን የማስቀመጥ ዋና ዓላማዉ ይህ ነዉ፤ እርሱ ያደረገዉን ነገር ለምን እንዳደረገዉ ከተረዳኸዉ ቀጣዩ ድርጊትህ መረዳት ይሆናል፡፡ እዉነት እልሃለዉ ጠላቴ የምትለዉን ሰዉ ከምንም በፊት ችግሩን ልትረዳዉ ሞክር እዉነቱን ታገኛለህ፤ ምናልባት ይህ ሃሳብ ላይዋጥልህ ይችላል ነገር ግን አድርገዉ፡፡

ሰኞ 8 ጁን 2015

የህይወት ታላቁ ፈተና “ጠላትህን ዉደድ” (ክፍል ሁለት)



ባለፈዉ በመግቢያችን ላይ ጠላትን ስለመዉደድ አንስተን  በቀጣዩ ክፍል በሰፊዉ ቀሪዎቹን እንደምንዳስስ ተቀጣጥረን ነበር በቀጠሮአችን መሰረት እነሆ በክፍል ሁለት ተገናኘን፤
ü ጠላትህን ዉደድ ምን ማለት ነዉ?
ደስ የሚልና ጥሩ ጥያቄ ነዉ፤ ነገር ግን እንደየሰወች አስተሳሰብ እና አተረጓጎም ይለያያል፡፡ ትንሽ ገለፃ ለማድረግ ያህል “ ጠላት ”  የሚለዉን አስቀድመን ማየት ይጠበቅብናል፡፡ጠላት ማለት ለዚህ ምንባብ  አንባቢ ልብ እንዲለዉ የሚፈለገዉ የአገር ጠላት ማለት እንዳልሆነ ላሳስብ ወዳለሁ፡፡ስለአሸባሪዎች ማዉራት እንዳልፈለኩ አንባቢ ልብ ይለዋል፡፡ በመሰረታዊነት በፅሑፍ ለማንሳት የተፈለገዉ ስለሰዉ ልጅ ሲሆን በማንኛዉም መንገድ አንወዳቸዉም ብለን ስለፈረጅናቸዉ ሰወች ነዉ፤እንደዚህ ዓይነት ሰወች በሁላችንም ሕይወት ዉስጥ አሉና፡፡ የኛንም ሰላም የሚነሱን ከእግዚአብሔር ጋርም የሚያጋጩን ፤… 
ü ጠላቶቻችን እነማን ናቸዉ?
1)     ምናልባት ገና ስማቸዉ ሲጠራ የሚያበሳጨን ፣ ወይንም ስማችንን ሲጠሩን ሊያመን የሚደርስ፣ በዚያም ሆነ በዚህ የነርሱ ነገር የሚያሳምመን ዓይነት ሰወች ፣ መጠኑ ይለያይ እንጂ በነርሱ ነገር ላይ ቅሬታ ያለን ዓይነት ሰወች፤ ( እነዚህ ሰወች ፍቅረኛችን የነበሩ ሊሆኑም ይችላሉ አንድ ያልተጠበቀ አጋጣሚ ጠላት ያሰኛቸዉ ጠላት ያደረጋቸዉ)
2)    ምናልባትም የቤተሰብ አባል የሆኑና በመካከላችን ትልቅ ቅራኔ ያለን፣ ወይንም በአንድ ወቅት በማይረባ ጉዳይ ተጋጭተን የነበርን፤
3)    ምናልባትም በምናዉቃቸዉ ወይም በምንወዳቸዉ ሰወች ላይ ከህሊናችን አልጠፋ ያለ በደል ያደረሱ ሰወች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡( ከአካል ጉዳት እስከ ያላቸዉን ግንኙነት ሊጎዳ የሚችል ድረስ )
4)    ምናልባትም መምህራኖቻችን (የፈተና ዉጤት አበላሽተዉብን፣ የማይሆን ነገር ጠይቀዉን ፣ ዉጤት ስጡን ብለናቸዉ እምቢ ብለዉን )፣ የሥራ ባልደረቦቻችን ፣ የፍቅር ወይንም የትዳር አጋሮቻችን፣ አለቆቻችን ወይንም አሰሪዎቻችን፣የአገር መሪዎች፤
ታዲያ እነዚህን ሰወች “ ጠላትህን ዉደድ ” ማለት ምን ማለት ነዉ?
ዉደድ ሲል በግልፅ ማስቀመጥ የምፈልገዉ ነገር የተለያዩ ፆታዎች የፍቅር ስሜት ያለበት ለማለት እንዳልተፈለገ በግልፅ ማስቀመጥ ነዉ፡፡ ከዚሁ ጋር ማያያዝ የምፈልገዉ ሌላኛዉ ነገር ልጆቻችንን፣ ወንድሞቻችንን፣ የቤተሰብ አባላቶቻችንን፣ የልብ ጓደኞቻችንን፣ … የምንወደዉ መዉደድ እንደሚለያየዉ ሁሉ ይህም ከዚያ ይለያል፡፡ (መቸስ የትዳር አጋራችንን እና የልብ ጓደኛችንን የምንወደዉ ምን ያህል እንደሚለያይ አንባቢ ይለየዋልና ) ስለዚህ በጎ ያደረጉልንን ሰወች ፍቅር⁄መዉደድ ፣ የምናዉቃቸዉን ወይም በፍፁም የማናዉቃቸዉ ሰወች መልካም ነገር ሲያደርጉ ስናያቸዉ የምንወዳቸዉ ፣ አለበለዚያ ለትናንሽ ህፃናት የምናሳየዉ ፍቅር፣ ይህንን መዉደድ⁄ ፍቅር ነዉ እንግዲህ ለነዚህም ከላይ ለዘረዘርናቸዉ በደል ፈፃሚያን የምንሰጣቸዉ ፡፡
v  ወሲባዊ ⁄ የፍቅር ስሜት የሌለዉ መዉደድ ለሌላ ሰዉ ከቤተሰባችን አባል ⁄የቅርብ ጓደኞቻችን ለምንላቸዉ ⁄ ዉጭ እናደርጋለን?
v  ይህንን መፈፀም ያለምንም ጥርጥር ዋጋ አያሳጣንም ፣ ምንም አያጎድልብንም፤ እንዲሁ ለሌላዉም ቢሆን
v  በእርግጠኝነት ይህንን የሚተገብሩ ከሆነ ስለሰዉ ልጅ ያለዎት አስተሳሰብ መልካም ይሆናል ( ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን )
v  ከዚህ የላቀዉ ደግሞ ይህንን ማድረግ ላቃታቸዉ ማገዝ የበለጠ የሚደነቅ እና በሁላችንም ዉስጥ ከሰረፀ በዓለም ላይ የሰፈነዉ እልቂት ⁄ መጠፋፋት በእርግጠኝነት ይቀየራል፡፡ መሪዎች ተፎካካሪዎቻቸዉን እስር ቤት አያጉሩም ፣ ሊያጠፉ አይሯሯጡም ፣ተቃዋሚዎች ለአመፅ አይነሱም ሰይፍ አይመዙም፣ በየምክንያቱ አይጠላለፉም ይልቅስ ተነጋግረዉ ለአገር እና ለህዝብ የሚበጀዉን ይሰራሉ እንጂ፡፡
ነገር ግን ጠላትን መዉደድ ወዳጅን የመዉደድ ያህል ቀላል ነገር ባይሆንም ያንን ስሜት ግን ማምጣት ይቻላል፤ ፀብን ፣ ጥላቻን የለመደ አብሮ አደግ ማንነታችን እንዲሁ በቀላሉ ባይቀየርም ጥረት ግን ይቀይረዋል፡፡ ስለዚህ ጠላታችንን ለመዉደድ ምን ማድረግ አለብን ⁄ ይጠበቅብናል?

እሑድ 31 ሜይ 2015

የህይወት ታላቁ ፈተና “ጠላትህን ዉደድ”



ክርስቲያን ሆንን አልሆንን፣ወደድንም ጠላንም፣በየትኛዉም የእምነት አስተምህሮ ዉስጥ ብንሆንም በጌታችን በመድሃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርተ ወንጌል ዉስጥ ለማንኛዉም የሰዉ ልጅ ጥሩ የመሆን ፍላጎት ሊሆን ከወደደ የሚገደደዉ ወይም ሊቀበለዉ ግድ የሚለዉ መሰረታዊ ነገር አለ፤ (ፀሐፊዉ ሊዮ ባኩታ በገፀ ድሩ እንዳሰፈረዉ)
ü  በአቅራቢያችን የሚገኙ ጎረቤቶችን መዉደድ አይደለም፣
ü  የሚወዱንን ስለሚወዱን አፀፋ ለመመለስ መዉደድ አይደለም፤ ነገር ግን
v   ጠላቶቻችንን፣ የሚጠሉንን፣ በህይወት መኖራችንን የማይፈልጉትን፣ የእኛን ማግኘት ፣የእኛን ጤና መሆን፣ ወጥቶ መግባት ፣ ሰርቶ ማግኘት ፣ ነግዶ ማትረፍ፣ ዘርቶ መቃም፣ ወልዶ መሳም፣… በጭራሽ የማይፈልጉትን መዉደድ፡፡
ይህ አባባል ፣ ይህ ድርጊት፤ የዚህ ፅሑፍ ዋና መልዕክት ነዉ “ ጠላትህን ዉደድ ” የህይወታችንም ትልቁ ፈተና ፣ ሰዉ የመሆናችን እና የእምነታችን መለኪያዉ ነዉ፡፡
ይህ መልዕክት ትልቅነቱ ∕ ጥቅሙ ⁄ ለምን አስፈለገ?
ይልቁንም ሃይማኖተኛ ለሆነዉም ላልሆነዉም ለምን መልዕክቱ መተላለፍ አስፈለገዉ?
( የዚህ ፅሑፍ ዋና ዓላማ የእምነት ትምህርት ማስተማር ላይ ያዘነበለ አይደልም፤ ምንም እንኳን የሃይማኖት ትምህርት ማስተማር ችግር ባይኖረዉም እና ይልቁንም ክብር ያለዉ እና ዋጋዉም እጅግ እጥፍ ድርብ ክፍያዉም በሰማይ የሆነ ቢሆንም  ) ዋናዉ መነሻዬ በመላዉ ዓለም እና በሁሉም የሰዉ ዘር መካከል የጠፋ ትልቅ ቁምነገር (ሀብት) ከመሆኑ የተነሳ እንጂ፡፡“ ጠላትህን መዉደድ ” እምነት ቢኖርህም ባይኖርህም ችግር የሌለዉና ልታደርገዉ የሚገባ ቁልፍ ጉዳይ ነዉ፡፡ ( ነገር ግን በዓለም ላይ ትልቁ ችግር ፣ ዓለምም ያጣችዉ እና የጎደላት ጉዳይ ቢኖር ጠላትን መዉደድ ነዉ፡፡)

ሐሙስ 26 ማርች 2015

"እንድትዋረድስ የምትታሰርበት ምን እንደሆነ እባክህ ንገረኝ"



ይህንን ሀይለ ቃል ለሶምሶን የተናገረችዉ ደሊላ የምትባል በሶሬቅ ሸለቆ የምትገኝ ሴት ናት፡፡ ደሊላ ይህንን ቃል የተናገረችበት ምክንያት ፍልስጥኤማዉያንን በጣም ስላስቸገራቸዉ ከነርሱ መካከልም ብዙ ሰዉ ስለገደለባቸዉ፣ የፍልስጥኤም ነገሥታት እና መኳንንት ደሊላን እያንዳንዳችን 1100 ብር እንሰጥሻለን በምን እንደሚደክም ጠይቂዉ አሏት፤ እርሷም እንዲወዳት ካደረገች በኋላ ወደርሷ አስጠግታ እያሻሸችዉ ይህን ጥያቄ አቀረበችለት፡፡ እርሱም መግለፅ ስላልፈለገ ባይሳካለትም ሦስት ጊዜ እንዲህ እያለ ዋሻት፡-
      I.        1.በሰባት ባልደረቀ በእርጥብ ጠፈር ቢያስሩኝ እደክማለሁ እንደሌላዉም ሰዉ እሆናለሁ፣
     II.       2. ሥራ ባልተሰራበት በአዲስ ገመድ ቢያስሩኝ እድክማለሁ፤
   III.        3.የራሴን ጠጉር ሰባቱን ጉንጉን ከድር ጋር ብትጎነጉኚዉ በችካልም ብትቸክይዉ እደክማለሁ እንደሌላዉም ሰዉ እሆናለሁ አላት፡፡
እነዚህን ጠቅሶ ከዋሻት በኋላ እርሷም እወድሻለሁ ብለኸኝ ለካስ  አትወደኝምየምትወደኝ ቢሆን ኖሮ እንድዋረድ የምትታሰርበትን ምን እንደሆነ በነገርከኝ ነበር አለችዉ፡፡

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...