ማክሰኞ 14 ጁላይ 2015

ሳይማር ያስተማረን … … … ሳይማር ያስመረቀን ትዉልድ




የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት
የሚሊንየም አዳራሽ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች በተለያየ የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ፣የሁለተኛ እና የዶክትሬት ትምህርታቸዉን ያጠናቀቁ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ለግማሽ ቀን ያህል አስተናግዶ ዉሎአል፡፡ይህንን ታላቅ የምርቃት በዓል አስመልክቶ ታዋቂዉ የኤፍ.ኤም.ሬድዮ ጣቢያ እዚያዉ ከሚገኘዉ ጊዜያዊ ጣቢያዉ የተማሪዎችን፣ የዩኒቨርስቲዉን መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች፣ የተመራቂ ተማሪዎችን ወላጅ ዘመድ ጓደኞች የእንኳን ደስ አላችሁ እና የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ቀጥታ ስርጭት እያስተላለፈ ይገኛል፡፡
አድማጮቻችን ዛሬ በልዩ ፕሮግራም ከቦሌ አዉሮፕላን ማረፊያ ፊት ለፊት በሰፊዉ ሜዳ ላይ ተንጣሎ ከሚገኘዉ የሚሊንየም አዳራሽ ጊዜያዊ የማሰራጫ ጣቢያችን ይህንን በዓይነቱ ልዩ የተመራቂ ተማሪዎች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ቀጥታ ተቀብለን ለማስተላለፍ እና ከማለዳዉ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ከስፍራዉ በመገኘት ለስለስ ባሉ ጣዕም ባላቸዉ ሙዚቃዎች ስናዝናናችሁ መቆየታችን ይታወሳል፡፡
ለስለስ ያለዉን ሙዚቃ ከዚህ ጊዜያዊ የማሰራጫ ጣቢያችን ያስደመጡንን የስቲዲዮ ባለሞያዎቻችን፣ የደቡብ ሱዳኑን፣ የቻይናዉን እና የደቡብ ኮርያዉን አቀንቃኞች በቅደም ተከተላቸዉ ላመሰግን እወዳለሁ፡፡
አስቀድሜ እንደነገርኳችሁ የዛሬዉ በዓል እጅግ ልዩ ነዉ፤ ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል የአሜሪካዉ ፕሬዘዳንት እዚህ ጎረቤታችን ኬንያ መጥተዉ ጎብኝተዉ በተመለሱበት ማግሥት እና ወደ ኢትዮጵያም በተመሳሳይ ሁኔታ ጉብኝታቸዉን ያደርጋሉ ተብሎ ከሚጠበቅበት ዋዜማ መሆኑ ነዉ፡፡
አድማጮቻችን እንግዲህ የምረቃ መርሀግብሩ እየተጠናቀቀ እና በስፍራዉ የታደሙ የተመራቂ ተማሪ ቤተሰቦች ከአዳራሽ እየወጡ መሆኑ በርቀት ይታየኛል፤ በዚህ ታላቅ የምረቃ በዓል ላይ ክቡር ሚኒስትሩ ባይገኙም የተከበሩት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የአንድ ቋሚ ኮሚቴ ሠብሳቢ የሆኑት እኚህ ሠዉ ከክልል ከመጡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጋራ በጋራ በመሆን ተማሪዎቹን ለማስመረቅ ተገኝተዋል፡፡
ክቡራን አድማጮቻችን እነኚህን ሁለት የአገራችን ታላላቅ ሰወች ስለምርቃቱ እና አንዳንድ ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች አንስተን በሰፊዉ እናወራቸዋለን በጥሞና ተከታተሉን፡፡ እስከዛዉ በጣም የምንወደዉ እና የኢትዮጵያ ወዳጅ እና ባለዉለታ የቦብ ማርሊን stand up for your right የሚለዉን ተጋብዛችኋል፡፡
አድማጮቻችን ሁለቱን የአገሪቱን ታላቅ ባለስልጣናት አየር ላይ ልናቀርብላችሁ የሞከርነዉ ሙከራ ባለስልጣናቱ ለአስቸኳይ አገራዊ ጉዳይ ተጣድፈዉ ባልጠበቅነዉ የመዉጫ በር ስለወጡብን ሙከራችን አልተሳካም፡፡
አድማጮቻችን እንደሚታወቀዉ ብዙ ተማሪዎች ጥሩ ዉጤት በማስመዝገብ የዋንጫ እና የሚዳልያ ተመራቂዎች እንዳሉ ሰምተናል፤ ከነዚህ መካከል አንድ ልጅ እዚህ አጠገቤ አለ ከእርሱ ጋር የማደርገዉን ቆይታ ተከታተሉን፡-
እስኪ ስምህንና እዚህ የተገኘህበትን ምክንያት ለአድማጮቻችን ግለፅልን
̋ ሴባ እባላለሁ የመጣሁት የትምህርት ጊዜዬን አጠናቅቄ ለምርቃት ነዉ የተገኘሁት ˝
እንኳን ደስ አለህ
̋እንኳን አብሮ ደስ አለን  ̋
ሴባ በዛሬዉ ዕለት በመመረቅህ ምን ተሰማህ?
˝ እንዴ! … በጣም … በጣም … ግልግል ነዋ! ትልቅ ግልግል ̋
በምን የትምህርት ዘርፍ ነዉ የተመረከዉ?
˝̋ በFBI ነዉ የተመረኩት፤ ˝
ከFBE ፋክልቲ ማለትህ ነዉ?
˝ ያዉ ነዉ … ምን ልዩነት አለዉ ፍሬንድ  ̋
ከየት አካባቢ ነዉ የመጣኸዉ?
˝ እዚሁ ነኝ ከየትም አልመጣሁም  ̋
ሥምህ ለየት ያለ ነዉ ትርጉሙን ብትነግረኝ?
˝ ጓደኞቼ ናቸዉ ያወጡልኝ እንደምታየዉ ፀጉሬን ሹሩባ መሰራቴን ተከትሎ እና ሴባስቶፖል የሚለዉን ሲያቆላምጡ ነዉ ሴባ ያሉኝ  ̋
ኦ! ሴባስቶፖል ነዉ ሰምህ?
˝ ኖ! ስሜ ቴዎድሮስ ነዉ  ̋
በጣም ጥሩ የዋንጫ ተሸላሚ ነህ መሰለኝ ዋንጫም በእጅህ ሜዳልያዉንም አንገትህ ላይ እንደማየዉ ባለድርብ ድል ነህ፤
˝ አቦ ለገተታ ነዉ ባክሽን … … ከፍሬንዳችን ለፎቶ ተቀብዬ ነዉ  ̋
እናመሰግናለን፡፡
አድማጮቻችን የመጀመሪያዉን ቆይታችንን ተከታትላችሁታል በጣም አዝናኝ እና አስተማሪ ነበር ቀጣዩን ደግሞ አንዲት ወጣት ተመራቂ ከጎናችን ትገኛለች ከእርሳ ጋር ጋር ያለንን ቆይታ ተከታተሉን፡፡
እህታችን እንኳን አደረሰሽ ደስም አለሽ
˝ እንኳን አብሮ ደስ አለን  ̋
ስምሽን እና ስለዛሬዉ በዓል ለአድማጮቻችን የሚሰማሽን ነገር በአጭሩ ብትገልጭልን?        
˝ ስሜ እንኳን ይለፈኝ በአጭሩ የማስተላልፈዉ በዛሬዉ በደስታዮ ዕለት ሳይማሩ ያስተማሩኝን አርሶ አደር ቤተሰቦቼንና ሳይማሩ እዚህ በክብር እንግድነት ተገኝተዉ ያስመረቁንን የክብር እንግዶች፣ የትምህርት ቤቱን ማህበረሰብ ፣ አራት ነጥብ አምጥቼ እንድመረቅ ላበቁኝ መምህራኖቼ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፤ ˝
አድማጮቻችን መርሀግብሩ እንደቀጠለ ነዉ ተከታተሉን … …

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...