ሰኞ 8 ጁን 2015

የህይወት ታላቁ ፈተና “ጠላትህን ዉደድ” (ክፍል ሁለት)



ባለፈዉ በመግቢያችን ላይ ጠላትን ስለመዉደድ አንስተን  በቀጣዩ ክፍል በሰፊዉ ቀሪዎቹን እንደምንዳስስ ተቀጣጥረን ነበር በቀጠሮአችን መሰረት እነሆ በክፍል ሁለት ተገናኘን፤
ü ጠላትህን ዉደድ ምን ማለት ነዉ?
ደስ የሚልና ጥሩ ጥያቄ ነዉ፤ ነገር ግን እንደየሰወች አስተሳሰብ እና አተረጓጎም ይለያያል፡፡ ትንሽ ገለፃ ለማድረግ ያህል “ ጠላት ”  የሚለዉን አስቀድመን ማየት ይጠበቅብናል፡፡ጠላት ማለት ለዚህ ምንባብ  አንባቢ ልብ እንዲለዉ የሚፈለገዉ የአገር ጠላት ማለት እንዳልሆነ ላሳስብ ወዳለሁ፡፡ስለአሸባሪዎች ማዉራት እንዳልፈለኩ አንባቢ ልብ ይለዋል፡፡ በመሰረታዊነት በፅሑፍ ለማንሳት የተፈለገዉ ስለሰዉ ልጅ ሲሆን በማንኛዉም መንገድ አንወዳቸዉም ብለን ስለፈረጅናቸዉ ሰወች ነዉ፤እንደዚህ ዓይነት ሰወች በሁላችንም ሕይወት ዉስጥ አሉና፡፡ የኛንም ሰላም የሚነሱን ከእግዚአብሔር ጋርም የሚያጋጩን ፤… 
ü ጠላቶቻችን እነማን ናቸዉ?
1)     ምናልባት ገና ስማቸዉ ሲጠራ የሚያበሳጨን ፣ ወይንም ስማችንን ሲጠሩን ሊያመን የሚደርስ፣ በዚያም ሆነ በዚህ የነርሱ ነገር የሚያሳምመን ዓይነት ሰወች ፣ መጠኑ ይለያይ እንጂ በነርሱ ነገር ላይ ቅሬታ ያለን ዓይነት ሰወች፤ ( እነዚህ ሰወች ፍቅረኛችን የነበሩ ሊሆኑም ይችላሉ አንድ ያልተጠበቀ አጋጣሚ ጠላት ያሰኛቸዉ ጠላት ያደረጋቸዉ)
2)    ምናልባትም የቤተሰብ አባል የሆኑና በመካከላችን ትልቅ ቅራኔ ያለን፣ ወይንም በአንድ ወቅት በማይረባ ጉዳይ ተጋጭተን የነበርን፤
3)    ምናልባትም በምናዉቃቸዉ ወይም በምንወዳቸዉ ሰወች ላይ ከህሊናችን አልጠፋ ያለ በደል ያደረሱ ሰወች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡( ከአካል ጉዳት እስከ ያላቸዉን ግንኙነት ሊጎዳ የሚችል ድረስ )
4)    ምናልባትም መምህራኖቻችን (የፈተና ዉጤት አበላሽተዉብን፣ የማይሆን ነገር ጠይቀዉን ፣ ዉጤት ስጡን ብለናቸዉ እምቢ ብለዉን )፣ የሥራ ባልደረቦቻችን ፣ የፍቅር ወይንም የትዳር አጋሮቻችን፣ አለቆቻችን ወይንም አሰሪዎቻችን፣የአገር መሪዎች፤
ታዲያ እነዚህን ሰወች “ ጠላትህን ዉደድ ” ማለት ምን ማለት ነዉ?
ዉደድ ሲል በግልፅ ማስቀመጥ የምፈልገዉ ነገር የተለያዩ ፆታዎች የፍቅር ስሜት ያለበት ለማለት እንዳልተፈለገ በግልፅ ማስቀመጥ ነዉ፡፡ ከዚሁ ጋር ማያያዝ የምፈልገዉ ሌላኛዉ ነገር ልጆቻችንን፣ ወንድሞቻችንን፣ የቤተሰብ አባላቶቻችንን፣ የልብ ጓደኞቻችንን፣ … የምንወደዉ መዉደድ እንደሚለያየዉ ሁሉ ይህም ከዚያ ይለያል፡፡ (መቸስ የትዳር አጋራችንን እና የልብ ጓደኛችንን የምንወደዉ ምን ያህል እንደሚለያይ አንባቢ ይለየዋልና ) ስለዚህ በጎ ያደረጉልንን ሰወች ፍቅር⁄መዉደድ ፣ የምናዉቃቸዉን ወይም በፍፁም የማናዉቃቸዉ ሰወች መልካም ነገር ሲያደርጉ ስናያቸዉ የምንወዳቸዉ ፣ አለበለዚያ ለትናንሽ ህፃናት የምናሳየዉ ፍቅር፣ ይህንን መዉደድ⁄ ፍቅር ነዉ እንግዲህ ለነዚህም ከላይ ለዘረዘርናቸዉ በደል ፈፃሚያን የምንሰጣቸዉ ፡፡
v  ወሲባዊ ⁄ የፍቅር ስሜት የሌለዉ መዉደድ ለሌላ ሰዉ ከቤተሰባችን አባል ⁄የቅርብ ጓደኞቻችን ለምንላቸዉ ⁄ ዉጭ እናደርጋለን?
v  ይህንን መፈፀም ያለምንም ጥርጥር ዋጋ አያሳጣንም ፣ ምንም አያጎድልብንም፤ እንዲሁ ለሌላዉም ቢሆን
v  በእርግጠኝነት ይህንን የሚተገብሩ ከሆነ ስለሰዉ ልጅ ያለዎት አስተሳሰብ መልካም ይሆናል ( ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን )
v  ከዚህ የላቀዉ ደግሞ ይህንን ማድረግ ላቃታቸዉ ማገዝ የበለጠ የሚደነቅ እና በሁላችንም ዉስጥ ከሰረፀ በዓለም ላይ የሰፈነዉ እልቂት ⁄ መጠፋፋት በእርግጠኝነት ይቀየራል፡፡ መሪዎች ተፎካካሪዎቻቸዉን እስር ቤት አያጉሩም ፣ ሊያጠፉ አይሯሯጡም ፣ተቃዋሚዎች ለአመፅ አይነሱም ሰይፍ አይመዙም፣ በየምክንያቱ አይጠላለፉም ይልቅስ ተነጋግረዉ ለአገር እና ለህዝብ የሚበጀዉን ይሰራሉ እንጂ፡፡
ነገር ግን ጠላትን መዉደድ ወዳጅን የመዉደድ ያህል ቀላል ነገር ባይሆንም ያንን ስሜት ግን ማምጣት ይቻላል፤ ፀብን ፣ ጥላቻን የለመደ አብሮ አደግ ማንነታችን እንዲሁ በቀላሉ ባይቀየርም ጥረት ግን ይቀይረዋል፡፡ ስለዚህ ጠላታችንን ለመዉደድ ምን ማድረግ አለብን ⁄ ይጠበቅብናል?

1)     እነዚህ ሰወች አደረጉብን የምንላቸዉን ነገሮች በጠቅላላ ከልቡናችን ዉስጥ ማስወገድ እና ከምንወዳቸዉ ሰወች እኩል ለመዉደድ መጣር፣ ልምምድ ማድረግ ( ጥላቻንም በተፈጥሮ ሳይሆን በልምምድ ያመጣነዉ ነገር ነዉና)፤
2)    ልጆቻችንን ፣ ቤተሰባችንን … የምንወደዉን ያህል ልወድ አልችልም የሚለዉን እንደቆሻሻ ነገር ከዉስጣችን ማስወገድ፤
3)    ማድረግ ያለብን እነርሱን የመዉደድ ስሜት ይኑረን ፣ …. ከቻልን ያንን መዉደዳችንን በቃላት በመግለፅ ፣ መልካም ነገር በማድረግ፣ በጥሩ ፈገግታ መግለፅ፡፡
የፍቅር ረሃብን ማስታገስ የምግብ ረሃብን ከማስታገስ እጅግ ይከብዳል ” ማዘር ቴሬዛ 
ü ጠላቴን የምወደዉ ለምንድን ነዉ?
ይህ ጥያቄ ለብዙዎቻችን አዲስ ነገር አይደለም፤ ይህም ነዉ የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ አንባቢም ቢሆን ለማንበብ የተነሳበት ምክንያት ይህ ጥያቄ ሁል ጊዜ ዉስጣችን ስለሚፈጠር ነዉ፡፡ ያለምንም ጥርጥር ከዚህ በኋላ የሰዉ ጠላት እንደሌለን ማመን እንችላለን፤ ነበሩ ብለን የምናስባቸዉንም እንወዳቸዋለን፡፡ በቃ አከተመለት ይህ መንፈስ ለዘለዓለም ከኛ ይርቃል፡፡ ይህም ሰዉ ከዛሬ በኋላ በእኔ ላይ መጥፎ ነገር ሊያደርግ አይችልም፤ …
በዚህ ምድር ስኖር ለሰዉ ልጅ ፍቅር እሰጠዋለሁ፣ ሁሉንም እወደዋለሁ፡፡ ግን ለምን? ለምንድን ነዉ የምወደዉ? የመዉደዴ ጥቅሙ ምንድን ነዉ?
ይህ ጥያቄ ቀላል ጥያቄ አይደለም፡፡ ነገር ግን ምላሽ የለዉም ማለት አይደለም፡፡ የሚቻለዉን ያህል ከጥቂት ማብራሪያ ጋር ለመግለፅ ሞክሬአለሁ፡፡
1)     ደስተኛ ትሆናለህ፡­ ከዚህ ቀደም ስትጠላዉ የነበረዉን ሰዉ ዉስጥህ የነበረዉ አላስፈላጊ መንፈስና ምክንያቶች አስወግደህ መዉደድ በመቻልህ የመጀመሪያዉ የዚህ መዉደድ ፍሬ ቀማሽ አንተ ነህ ፍፁም ደስተኛ ትሆናለህ፡፡ ከዚህ ቀደም በዚህ የተነሳ ያንተን እርዳታ የሚፈልጉ በዙሪያህ ያሉ ሰወችን ባለማድረግህ የጎዳሃቸዉ ፣ ያልደረስክላቸዉ ሁሉ፣ ዛሬ ስለምትደርስላቸዉ ደስታህ እጥፍ ድርብ ነዉ፡፡
2)    የዚያን ሰዉ ሕይወት ትቀይራለህ፡­“ ጠላትህ ”የሰዉ ልጅ እንደመሆኑ መጠን እንደጠላት የመተያየቱ ጉዳይ የሚመጣዉ ከንዴት ፣ ከአዕምሮ ጭንቀት፣ በዚያ ሰዉ ከመጣላት፣ … የመነጨ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ሰዉ በአፀፋዉ ወዳጁ ነህና በመካከላችሁ መዋደድ ስፍኗልና ይወድሃል፡፡ አንተን መዉደድ በመቻሉ ህይወቱ ተቀይሯል፡፡ እንዲህ በማድረግህ እርሱን ደስተኛ ልታደርገዉ ችለሃል፡፡  
3)    ጓደኛህ ልታደርገዉ ትችላለህ፡­ ጠላትህን መዉደድ መቻልህ ጠላትህን ወዳጅህ ማድረግ የማስቻል አቅም አለዉ፡፡ ከጠላት ጋር ከመዋጋት ይልቅ ጠላትህን መዉደድ ምርኮዎችህን ያበዛዋል፡፡በህይወትህ ዉስጥ የበለጠ ዉጤታማ እና የጓደኞችህን ቁጥር የመጨመር ትልቁ መንገድ “ ጠላቶችህን ” መዉደድ ነዉ፡፡ ከነበሩህ ጓደኞችህ ይልቅ ጓደኝነቱ የላቀ ፍቅሩ የጠነከረ ይሆናል በደሉን ይቅር ብለኸዋልና፡፡ጓደኝነቱም እስከ ቤተሰባዊነት የዘለቀ ይሆናል፡፡
4)    ለሌሎች ትልቅ ምሳሌ መሆን ትችላለህ፡­ እያንዳንዱ ድርጊታችን ለሌሎች ምሳሌ መሆን የሚችል መሆን ይኖርበታል ፤ የመጥፎ ነገር መጠቋቆሚያ ከመሆን ይልቅ፡፡ ለምሳሌ ልጆች ( ታናናሾች ) ቢኖሩህ ከምንም ይልቅ የሚማሩት ከምታደርጋቸዉ ነገር ነዉ፡፡ ጥላቻ መቸስ ልታስተምራቸዉ ከምትፈልጋቸዉ ነገር መካከል አንዱ እንደማይሆን መጠራጠር ያለብኝ አይመስለኝም፡፡
5)    ለማህበረሰቡ ጥቅም ትሰጣለህ፡­ ምንም እንኳን ትንሽ የምንለዉ ግላዊ ጉዳይ በማኅበረሰቡ ዉስጥ ጉልህ ሚና አለዉ ተብሎ ባይደመደምም እኔ ጠላቴን ከጠላሁ ማነዉ ጠላቱን የሚወድ የሚለዉ ጥያቄ ምላሽ ማኅበረሰብን አደጋ ላይ ይጥላል፡፡ ከዚህም ባሻገር እያንዳንዱ ጠላቱን ከወደደ አንዲት አገር ( ዓለም ) የጦርነት አዉድማ መሆኗ ይቀራል፤ የእያንዳንዱ አስተዋፅኦ ለሰፊዉ ማኅበረሰብ ትልቅ ጥቅም ይሰጣል፡፡ ነገር ግን እኛ ሁላችን ጥላቻን የምናዘወትር ከሆነ ጦረኛ ፣ ብስጩ፣ ተንኮለኛ ትዉልድ ፣… እናፈራለን፡፡ መገናኛ ብዙሃኖቻችን የሚያወሩት ፣ ባህሎቻችን፣ ፖለቲካችን፣ የግብይት ስርአታችን ፣… ሁሉ የተረበሸ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ ለማንም ጥቅም አይደለም በአንፃሩ በተቃራኒዉ ብናደርግ ማኅበረሰቡ በሁሉም አቅጣጫ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡  
6)    ማንነትህ ለራስህ ትርጉም አለዉ (ይጥምሃል) ትወደዋለህ፡­ ለሌሎች ለጊዜዉ ምንም ላይመስለዉ ይችላል ለራስህ ግን ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል፡፡ ጥሩ ሰዉ መሆንህን ባሰብከዉ ቁጥር ከራስ ፀጉርህ እስከ እግር ጥፍርህ የሚወርህ ትልቅ ደስታ ይሰማሃል፡፡እስኪ ልብ ብለህ አስበዉ እንኳን ጠላትህን ወደህ አይደለም ቤተሰብህን የምትወድ ሰዉ ስትሆን የሚሰማህ ደስታ፤ ቤተሰብን ጓደኛ ላደለዉ መዉደድ ቀላል ነዉ ስለጠላትህ ( ስለምትጠላዉ ) ሰዉ ያለህን አስተሳሰብ ከራስህ ጋር ታግለህ ቀይረህ “ጠላትህን” መዉደድ መቻል ትልቅ ትርጉም ነዉ ያለዉ፣ ትልቅ መስዋዕትነት የሚጠይቅ ነዉ፡፡  ትልቅ እንደመሆኑ መጠንም ፈታኝ ነዉ፤ በድርጊት የተሞላ ነገር ነዉ፡፡ በህይወት ዘመናችን ትልቁ ፈተና ነዉ፡፡ ማርቲን ሉተር ኪንግ እንዲህ ብሎ ነበር “ ፍቅር ⁄ መዉደድ ጠላትህን ወደ ወዳጅ ለመቀየር የሚያስችል አማራጭ የሌለዉ ሃይል ነዉ
ለዛሬዉ ሁተኛዉን ክፍል እዚህ ላይ አጠናቀቅን ቀጣንና የመጨረሻዉን ክፍል ጠላቴን ለመዉደድ የሚያስችለኝ ነገር ምን ላድርግ? (ምን መደረግ አለበት)? የሚሉትን እና ሌሎችንም  እንዳስሳለን ፤ ቸር ይግጠመን፡፡ ይቆየን፡፡

for more information join my telegram channel
https://t.me/deressereta

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...