ሐሙስ 26 ማርች 2015

"እንድትዋረድስ የምትታሰርበት ምን እንደሆነ እባክህ ንገረኝ"



ይህንን ሀይለ ቃል ለሶምሶን የተናገረችዉ ደሊላ የምትባል በሶሬቅ ሸለቆ የምትገኝ ሴት ናት፡፡ ደሊላ ይህንን ቃል የተናገረችበት ምክንያት ፍልስጥኤማዉያንን በጣም ስላስቸገራቸዉ ከነርሱ መካከልም ብዙ ሰዉ ስለገደለባቸዉ፣ የፍልስጥኤም ነገሥታት እና መኳንንት ደሊላን እያንዳንዳችን 1100 ብር እንሰጥሻለን በምን እንደሚደክም ጠይቂዉ አሏት፤ እርሷም እንዲወዳት ካደረገች በኋላ ወደርሷ አስጠግታ እያሻሸችዉ ይህን ጥያቄ አቀረበችለት፡፡ እርሱም መግለፅ ስላልፈለገ ባይሳካለትም ሦስት ጊዜ እንዲህ እያለ ዋሻት፡-
      I.        1.በሰባት ባልደረቀ በእርጥብ ጠፈር ቢያስሩኝ እደክማለሁ እንደሌላዉም ሰዉ እሆናለሁ፣
     II.       2. ሥራ ባልተሰራበት በአዲስ ገመድ ቢያስሩኝ እድክማለሁ፤
   III.        3.የራሴን ጠጉር ሰባቱን ጉንጉን ከድር ጋር ብትጎነጉኚዉ በችካልም ብትቸክይዉ እደክማለሁ እንደሌላዉም ሰዉ እሆናለሁ አላት፡፡
እነዚህን ጠቅሶ ከዋሻት በኋላ እርሷም እወድሻለሁ ብለኸኝ ለካስ  አትወደኝምየምትወደኝ ቢሆን ኖሮ እንድዋረድ የምትታሰርበትን ምን እንደሆነ በነገርከኝ ነበር አለችዉ፡፡
እርሱም ብዙ አወጣ አወረደ በጣምም ተጨነቀ ለብዙ ጊዜ ደጋግማ መጠየቋን ተመልክቶ መጨረሻ ላይ ነገራት እንዲህም ብሎ ነገራት፡፡
" ከእናቴ ማሕፀን ጀምሮ ለእግዚአብሔር የተለየሁ ነኝና በራሴ ላይ ምላጭ አልደረሰም የራሴንም ጠጉር ብላጭ ኋይሌ ከእኔ ይሄዳል፣ እደክማለሁ፤ እንደ ሌላም ሰዉ እሆናለሁ ብሎ የልቡን ሁሉ ገለጠላት፡፡ "
በዚህን ጊዜ ጉልበቱ የሚደክምበትን አወቀች እንቅልፍ በያዘዉም ጊዜ ፀጉሩን ላጨችዉ አሳልፋም ለፍልስጥኤማዉያን ሰጠችዉ እነርሱም ይዘዉ ዓይኑን አወጡት በናስ ሰንሰለትም አስረዉ በግዞት እህል ፈጪ አደረጉት፡፡
ሶምሶን በዘመነ መሳፍንት የነበረ ናዝራዊ ( ናዝራዊ ማለት የተቀደሰ የተለየ ማለት ነዉ፤) ሲሆን ከመካን ቤተሰብ የተወለደ ነዉ፡፡ አስቀድሞ በፍልስጥኤማዉያን ላይ ምክንያት በመፈለግ አንዲት ፍልስጥኤማዊት አገባ፤ በእርስዋም ምክንያት በተጣሉ ጊዜ እህላቸዉን አቃጠለ ብዙዎቻቸዉንም ገደለ፡፡ መሳፍንት 14 ቁ 1-15
የይሁዳ ሰዎች የተቆጡትን ፍልስጥኤማዊያን ፈርተዉ አሳልፈዉ ሊሰጡት ተስማሙ ሶምሶን ግን የአህያን መንጋጋ ይዞ በአህያዉ መንጋጋ እየተዋጋ ከጠላቶቹ አንድ ሺ ገደለ፡፡  መሳፍንት 15 ቁ 9-19
ጠላቶቹ በጋዛ ሊይዙት ሲሉ የከተማይቱን በር መዝጊያ ነቃቅሎ አመለጠ፡፡ መሳፍንት 16 ቁ 1-3
ሶምሶን ይህንን ሁሉ ከማድረጉ ባሻገር የአንደሳ ደቦል (ልጅ) በእጁ ጨብጦ የገደለ ሐያል ነበርና ፍልስጥኤማዉያን ሊያሸንፉት ባለመቻላቸዉ ደሊላን በጎን ላኩበት (ደሊላ አህዛብ ነበረች) ምሥጢሩን አወቁ አሸነፉትም፡፡
ከሶምሶን እና ከደሊላ የህይወት ተሞክሮ ምን እንማራለን?
1)    1.ከማይመስሉን ጋር አለመግጠም፡-
እርሱ የእግዚአብሔር ሰዉ ሆኖ ሳለ ካላመነች ከአህዛብ ጋር በመዋሉ በፍቅር መጠመዱ ሃይሉ እንዲደክም ጠላት እንዲዘባበቱበት ሆነ፤ ከማይመስለዉ ጋር ሶምሶን ሲወዳጅ እንደወደቀ እኛም ዳግም ክርስቲያኖች ስንሆን ካላመኑት( ከአህዛብ ጋር) በዕምነት ከማይመስሉን ጋር በምን አለበት ብንወዳጅ ምሥጢራችንን ብንገልፅ ለዉድቀት እንዳረጋለን፡፡ሐዋሪያዉ ቅዱስ ጳዉሎስ " ከማያምኑ ጋር በማይመች  አካሔድ አትጠመዱ " 2ኛ ቆሮንጦስ 6 ቁ 14 እንዳለዉ ከማይመስሉን ጋር ልንጠመድ አይገባም፡፡
ምን አለበት እያልን ጫት ከሚቅመዉ ፣ ጠጥቶ ከሚሰክረዉ፣ ከአጫሹ ጋር፣ ከአመንዝራዉ ጋር፣ በየስራ ገበታቸዉ ስራ ከሚጠሉ፣ ያለበቂ ምክንያት አለቆቻቸዉን የስራ ባለደረቦቻቸዉን  መንግስትን የሚነቅፉ፣ … ብንዉል ዛሬ ተመልካች ነገ ተግባሪና የችግሩ ተጠቂዎች እንሆናለንና ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡
ሶምሶን ሲወዳጃት ይሆናል ይመጣብኛል ብሎ ያልገመተዉ ዉርደት እንደደረሰበት ሁሉ እኛም ካልሆኑ ሰወች ጋር ስንቀራረብ የማናስበዉ የማንጠብቀዉ ነገር ስለሚገጥመን ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡
2)   2.ምሥጢርን መጠበቅ፡-
" የተቀደሰዉን ለዉሾች አትስጡ" እንደተባለ ሁሉ ይህን የመሰለ የእግዚአብሔር ኋይል ያለበትን ምሥጢር ለደሊላ ባይነግራት ኖሮ ባልተዋረደ ነበር፡፡እኛም እግዚአብሔር እንድናገለግልበት፣ እንድንጠቀምበት፣ ከክፉ ነገር እንድንጠበቅበት የተሰጠንን ምሥጢር ያለቦታዉ ልብ ሳንል ለማይገባዉ ሰዉ ለማያምኑ ለማይታመኑ 'ምሥጢር' ለማይጠብቁ ሰወች መናገር የለብንም፤ ከክብራችን ያዋርደናልና፡፡የተሰጠን ስጦታችን ከኛ ላይ ይገፈፋልና፡፡ ሚክያስ 7 ቁ 5 ላይ " ባልንጀራን አትመኑ በወዳጅም አትታመኑ የአፍህን ደጅ በብትህ ከምትተኛ (ከሚስትህ) ጠብቅ … " ይላልና፡፡ ስለዚህ ከሚስትም ከልጅም ቢሆን ምሥጢርን መጠበቅ መልካም ነዉ፤ ለማንም አይነገርምና ለጓደኛ የሚነገር  ምሥጢር አለ የማይነገር ምሥጢር አለና፡፡ከአፍ የወጣ አፋፍ እንዲባል … የህይወታችንን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የስራ ገበታችንን ምሥጢር ወሬ ለማሳመር አዋቂ ለመባል ለክብርና ለዝና ላገኘነዉ ሁሉ መዘርዘር አዳማጩ ብዙ እንደመሆነ መዘዙም ብዙ ነዉ፡፡
ደሊላ ሶምሶንን መጀመሪያ ላይ ስትጠይቀዉ ሶስት ጊዜ ደበቃት ስትመላለስበት ጊዜ አላስችል ብሎ ነገራት ለመዋረድም በቃ እኛም ዛሬ ከእግዚአብሔር የምንርቅበት (ከመምህራነ ንስሃ የምንለይበት) ለሰይጣን የምንጋለጥበት ፣ለሰይጣናዊ ስራ ቅርብ የምንሆነዉ፣ከደረጃችን ዝቅ የምንለዉ፣ ከስራችን የምንባረረዉ  … ድካማችንን ለሰወች አላስችል ብሎን እንገልፅና ተዋርደን ወድቀን እንቀራለንና ምሥጢራችንን መጠበቅ አለብን፡፡
ምሥጢር የሆነ ነገር በህልም ሲታየን ፣ በቃል ሲነገረን ፣ በራዕይ ሲገለጥልን እንደ ሶምሶን ምሥጢር መጠበቅ ካቃተን የፍልስጥኤም ወታደሮች ዓይኑን እንዳወጡት አጋንንትም የኛን ዓይነ ልቡና ያወጣሉና ምሥጢር ልንጠብቅ ይገባናል፡፡አንዳንዶች የባልንጀሮቻቸዉን ምሥጢር መጠበቅ አቅቷቸዉ ለማንም ይዘከዝኩና መጨረሻ ላይ ወሬዉ ከባለቤቱ ጋር ሲደርስ ማዉራታቸዉም ሲታወቅባቸዉ መግቢያ ቀዳዳዉ ይጠብባቸዋል፡፡
የሶምሶን ዓይነ ልቡና ካወጣ መዘባበቻ እንዳደረጉት በወይኒም ጥለዉ እህል ፈጪ እንዳደረጉት አጋንንት እኛንም ዓይነ ልቡናችንን ካወጡ መዘባበቻ ያደርጉናል፣ ማስተዋልም ስለሚሳነን ፈቃዳቸዉንም ስንፈፅም እንድንኖር በሲዖል ይጥሉናል፡፡
3)   3.የምንዋረድበትን አለመናገር፡-
ፍልስጥኤማዉያን ደሊላን ወደ ሶምሶን የላኩበት ደካማ ጎኑን እንድታጠና ነበር፤ ዛሬ እኛንም ዓለም የምታጠናዉ ደካማ ጎናችንን የኛ በምንላቸዉ ነፍስና ስጋችንን በሰጠናቸዉ 'ወዳጆቻችን' በኩል ነዉ፡፡
በፆም በፀሎት በስግደት … ብንበረታ በፍቅረ ነዋይ ፣ ትዕግሥት በማጣት ፣ በሐሜት … ድካማችን ሊገለጥ ይችላል፤ ስለዚህ ይህንን ድካማችንን ቶሎ ማስወገድ ለእግዚአብሔር መንገር እንጂ ለዓለም ልናሳዉቃት ልንገልፅላት አይገባም፡፡ ለአጋንንት ነግራ ድል እንድንሆን ታደርገናለችና፡፡
ይህንን ድካማችንን ሰይጣን ቢሰማ የእግዚአብሔር ልጅነታችንን ይነጥቅብናል የራሱ ባሪያም ያደርገናል፡፡ ዛሬ በተለይ ወጣቱን ክፍል በዝሙት ፣ በትዕቢት ፣ ገንዘብ በመዉደድ፣ … ይፈታተናል፡፡ደካማ ጎናችንን ይፈልጋል አዛዉንቶችን ደግሞ በሐሜት ፣ ባዕድ አምልኮ በማስመለክ፣ ከሥጋወደሙ (ቁርባን )፣ከንስሐ በማራቅ … ይፈታተናቸዋል፡፡ድካማቸዉንም ያጠናል፡፡
ደሊላ ማን ናት ፡- የህይወት ታሪኳን ከዚህ ቀደም እንዳየነዉ ሲሆን የዓለም ምሳሌ ናት፡፡አታላይዋ ዓለም እኛንም እንዲሁ ተብረቅርቃ እና ተብለጭልጫ ታሳስተናለች፡፡ ይሁዳ አስቀድሞ የገንዘብ ፍቅር እንዳለበት ሰይጣን ያዉቅ ነበርና ምንም እንኳን በጌታ እግር ስር ቁጭ ብሎ ቢማር ደካማ ጎኑን ተጠቅሞ 30 ዲናር እሰጥሃለዉ ብሎት በደካማ ጎኑ ገባበት አምላኩንም አሳልፎ ለሞት እንዲሰጠዉ አደረገ፡፡ይሁዳን ያሸነፈ ሰይጣን እኛንም ምንም እንኳን በቤቱ ብንመላለስ ፣ ቃሉን ብንማር ብናስተምር ድካማችንን ካገኘ ይጥለናል፡፡ይሁዳ በገንዘብ ፍቅር አምላኩን እንደካደ እኛን ደግሞ በተለያዩ ደካማ ጎኖቻችን ግብቶ ፈጣሪን እንድንክድ እምነታችንን እንድንቀይር ምግባራችን እንዲበላሽ ታማኝነት እንድናጣ ወዘተ … ያደርገናል፡፡
ዛሬ ትዉልዱ ሐይማኖት  አልባ እየሆነ በተለያዩ ባእዳን ነገሮች በአላስፈላጊ ምግባሮች እየተጠመደ ያለዉ እንደ ሶምሶን ምሥጢርን ያለመጠበቁ፣ እንደ ይሁዳ ደካማ ጎኑን ለሰይጣን ግልፅ በማድረጉ ነዉ፡፡ደካማ ጎናቸዉን ቢጠብቁ ኖሮ ጥቅስ ቢደረደር፣ ገንዘብ ቢከመር፣ልብስ ቢዥጎደጎድ፣ ችግር ቢያጎሳቁላቸዉ፣ስልጣኔ ጫፍ ቢደርስ … አንዳች ነገር ከፈጣሪያቸዉ መንገድ አያስወጣቸዉም ነበር፡፡
ድካማቸዉ/ችግራቸዉ/ ርሃብ ፣መራቆት፣መጠጥ … ነበርና ተመዘገቡ፤ ይሰጣችኋል አሏቸዉ ምግባራቸዉን ሸጡ ፡፡ እምነታቸዉን ለወጡ ፣ ከፀጋቸዉ ተራቆቱ፣ ብኩርናቸዉን ለምስር ለወጡ፣ምናለበት በሚል ሰበብ ከማይወጡበት ማጥ ገቡ፣ አጋንንትም ዳግም ወደ ጥንተ ማንነታቸዉ እንዳይመለሱ አድርገዉ ልቡናቸዉን ሰወሩባቸዉ፤ ይኸዉ በባርነት (በሱስ በመጠመድ፣ ባልሆነ አምልኮ፣ በግብረ ሰዶማዊነት፣ …) ተጠምደዉ ያሉበትን መለየት ተስኗቸዉ ይገኛሉ፡፡
ሶምሶን ምሥጢሩን ለመደበቅ ሦስት ጊዜ ሞክሮ ነበር አላስችል አለዉ እንጂ፤እኛም ደግሞ ሞከርኩት ሞከርኩት እምቢ አለኝ ተዉኩት እያልን ወደ ሞት የተጓዝንበት፣ በሴት ጭን ስር የወደቅንብት፣ ቤታችን ጠርሙስ ስር የሆነብን፣ ጭሳጭስ እና ቅጠላ ቅጠል መንፈሳችንን የሚያረካልን፣ …ወዘተ ሙከራ ሶምሶንን ስላልበጀዉ ድካማችንን መግለፅ ፍፃሜዉ አያምርም፡፡ አመንዝራነት በሽታን እንጂ ጤናን እንዳላመጣ፣ መጠጥ ጨጓራ በሽተኛ ከማድረግ እና መልካችንን ከማጥፋት ገንዘብን ከመጨረስ ሌላ ጥቅም እንደሌለዉ፣ በመቃምና ሽሻ በመሳብ የተገኘ ምንም ሰላም እንደ ሌለ በኛ ሳይደርስ በሌሎች ከደረሰባቸዉ እንማር፡፡ብልህ ሰዉ ከሰዉ ይማራልና፤ …
ሶምሶን ድል ያደርጋቸዉ ከነበረዉ፣ ይፈሩት ይንቀጠቀጡለት ከነበረዉ ሕዝብ መካከል ቁጭ ብሎ መዘባበቻ ያደረገዉ ከማትመስለዉ ከደሊላ ጋር መቅረቡ፣ ምሥጢሩን አለመጠበቁ፣ የሚዋረድበትን መናገሩ፣ …እንደሆነ እኛም አጋንንት በፆም በፀሎት በስግደት … ድል የምናደርጋቸዉ አጋንንት በደካማ ጎናችን፣ በጓደኞቻችን፣ በማይመስሉን፣ … በኩል መጥቶ ድል እንዳይነሳን ከክፉ ሰወች ልንርቅ ምሥጢራችንን ልንጠብቅ የምንዋረድበትን አለመናገር ይኖርብናል፤ ልብህን ጠብቅ፣ አንደበትህን ጠብቅ፣ …ተብለናልና፡፡
እኔኮ  እንደዚህ ካላደረኩ አይሆንልኝም፣ እንደዛ ካላደረኩ አያስችለኝም፣ እንትንማ ስወድ አቤት እሱን ካጣሁ ነፍሴ ልትወጣ ነዉ የምደርሰዉ እያልን ደካማ ጎናችንን ከመዘርዘር ተጠብቀን ፣ራሳችንን ጠብቀን፣ ሃይላችን ከኛ ሳይለይ፣ ድል የምንሆንበትን ምሥጢራችንን ጠብቀን፣ … በመንፋሳዊ ህይወታችን ፀንተን ክብራችንን ጠብቀን ለመኖር ያብቃን፡፡ እንዲህ ነበርኩ እንዲህ በማድረጌ እንዲህ ሆንኩ ብለን ዉድቀታችንን እያወራን በፀፀት ከመሸማቀቅ ይሰዉረን፣ ከከፍታ ዝቅ ከማለት እግዚአብሔር አምላካችን ይጠብቀን፤ አፈጣጠራችን ትልቅ ነበርና በትልቅነታችን ያፅናን፡፡ አሜን!ይቆየን!      

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...