ቅዳሜ 22 ኦገስት 2020

+ እግዚአብሔር እንዴት ይፈርዳል? +



+ እግዚአብሔር እንዴት ይፈርዳል? + 
(ጊዜ ወስደው ያንብቡት አያጥር ነገር ታሪክ ሆኖ ነው)
አንድ ግብፃዊ መነኩሴ ለገዳሙ መርጃ የእጃቸው ሥራ የሆኑትን ቅርጫቶች ሊሸጡ ወደ እስክንድርያ ለመጓዝ በጠዋት ተነሡ፡፡
በመንገድ ላይ ታዲያ ትልቅ የቀብር ሥነ ሥርዓት ለማድረግ የሚጓዝ ሕዝብ ገጠማቸው፡፡ ሟቹ ዝነኛ አረማዊ ገዢ ሲሆን በዘመነ ሰማዕታት በሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያኖችን የገደለ ሰው ነበር፡፡ አሁን ዕድሜ ጠግቦ ሞቶ ነው፡፡ ቀኑ ውብ ፀሐያማ ቀን ነበርና የሀገሩ ዜጎች በነቂስ ወጥተው ገዢያቸውን እየቀበሩ ነው፡፡
ይህንን ያዩት መነኩሴ ጉዳያቸውን ፈጽመው ወደ ገዳም ሲመለሱ አሳዛኝ ዜና ሰሙ፡፡ ለስድሳ ዓመታት በበረሃ በብሕትውና ቅጠልና የበረሃ ፍሬ ብቻ እየበላ የኖረ ባሕታዊ በዚያች ዕለት በጅብ ተበልቶ ሞቶ ነበር፡፡
መነኩሴው እጅግ ጥልቅ ኀዘን ውስጥ ሆነው እንዲህ ሲሉ አሰቡ ፦
‘በሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያኖችን የገደለው አረማዊ ሰው በታላቅ ክብር ታጅቦ ሲቀበር ሕይወቱን ሙሉ በጾምና በጸሎት ፈጣሪውን ያገለገለው ባሕታዊ በጅብ ተበልቶ የተዋረደ አሟሟት ሞተ፡፡ይህ እንዴት ዓይነት ፍርድ ነው? እግዚአብሔር ከመልካምነቱ ሁሉ ጋር ኢፍትሐዊ ነገሮች ሲሆኑ ዝም ብሎ ይፈቅዳል፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ ሰዎች የፈጣሪን መኖር ይጠራጠራሉ፡፡ እኔም ፍርዱን እንዲገልጽልኝ መጸለይ ይኖርብኛል’ አሉ፡፡
ከዚያች ቀን ጀምሮ መላልሰው ወደ ፈጣሪ ‘’ፍርድህን ግለጽልኝ’ ብለው ደጋግመው ጸለዩ፡፡ ብዙም ሳይቆይ እግዚአብሔር ፍርዱን እንዲህ ገለጠላቸው፡፡
ከሳምንታት በኋላ እንደተለመደው ወደ እስክንድርያ የሦስት ቀን ጉዞ ሊሔዱና ቅርጫታቸውን ሊሸጡ ተነሡ፡፡መንገዱን እንደጀመሩ ድንገት አንድ ወጣት መነኩሴ ወደ እርሳቸው ሲመጣ ተመለከቱ፡፡
‘’አባቴ ይባርኩኝ’
‘እግዚአብሔር ይባርክህ ልጄ’
‘አባቴ ወዴት ይሔዳሉ?’ አለ ወጣቱ መነኩሴ
‘ወደ እስክንድርያ ቅርጫቴን ልሸጥ እየሔድኩ ነው’ አሉት
‘ጥሩ አጋጣሚ ነው አባ እኔም ወደዛ እየሔድኩ ነው’ አለ በትሕትና
‘ጎሽ አብረን እንጓዛለና’ አሉ አባ፡፡ ወጣቱ መነኩሴ ከእጃቸው ሸክማቸውን ተቀበለ፡፡ ጥቂት እንደሔዱ እንዲህ አላቸው፡፡

የአዳል በግ

 

አንዱ ደወለልኝና የአገራችን ደቡባዊት ከተማ ስም ጠራልኝና እዛ ከተማ ውስጥ እና ዙርያዋ የሚገኙ ወጣቶች የአዳል በጎች ናቸው እንዴ? አለኝ።
እኔ እስከማውቀው የአዳል በግ ባለቤት/ባለበጉ ያልሆነ ከግልገልነት እስከ ሙክትነት እድሜው ዘወር ብሎ ያላየው ገዝቶ እየነዳ ወስዶ የሚያተርፍበት፣ የገዛ አርዶ አወራርዶ ነግዶ የሚያተርፍበት፣ ሌላው የደላው ደግሞ በልቶ ከርሱን የሚሞላበት ነው።
ሻጭም በርሱ ስሜት እየለካ በጉን ብሔርና ክልል ይሰጠዋል፤ ከበግነት ማንነት የአዳል በግነት መለያ ያላብሰዋል።የበጉን ሥጋና ቆዳ አዋዶ ይሸጠዋል።
ይሕንን የዋህ ሲጠሩት አቤት፣ ሲሸጡት ገዢን ተከትሎ የሚሄድ፣ ሲያርዱት ለምን ብሎ በማይጠይቅ በግ ለሰው የተመሰለው፤ ለዚያውም በክፉ ሰው ከሰውነት ልክ በወረደ ክብርን ጠርቶ ውርደትን በመረጠ ሰው አለማቀፋዊ ማንነቱን በውስን ሥፍራ በጠባብ መንደር በብሔር የተሸበበ ሰውን ይወክል ዘንድ የተገደደ በግ ነው። የአዳል በግ።
እነዚህ ሰወች ደግሞ ከሰውም ይልቅ ለአውሬነት የሚቀርቡ፣ አውሬያዊ ጸባይ ያላቸው። ሰውን ቁልቁል ዘቅዝቀው የሚሰቅሉ፣ ብሔርን መሰረት አድርገው ለይተው ገድለው አስክሬንን የሚያክል ነገር ያለ ባህላችንና እምነታችን መሬት ለመሬት የሚጎትቱ፣ እንደ አገር ድሃ እና ለማኝ አገር፣ እንደ ሕዝብ ለሰው ልጅ የሚገባውን የተመጣጠነ ምግብ መመገብ አይደለም በአግባቡ በልተን የማናድር፣ እንዲሁ ብሔርና ሐይማኖትን መሠረት በማድረግ ሐብት ንብረትን ለማውደም እንደ መንጋ የሚነዱ፣ መንግሥትን ያህል ተቋም በጥቅም በመገዛት ለዚያውም ለጠላት አገር መንግሥት ለመገልበጥ ላይ ታች የሚሉ የሰው እንክርዳዶች።
እነዚህ ናቸው በየዋሁ በግ የተመሰሉት፤ በአንድ በኩል እውነትም ሲታዩ በጎች ናቸው ለሚያርዳቸው የሚታዘዙ፣ ገድሎና ዘልዝሎ ሊበላቸው ከቋመጠ ጋር የሚውሉ። በሬ ካራጁ እንዲሉ። ክፋታቸው እንዳለ ሆኖ ያሳዝናሉ።
እንደ በግ ግር የሚሉ፣ የማያስቡ የማያስተውሉ፣ የሚጠቅማቸውን ለይተው የማያውቁ። ከትናንት ውድቀትና ስህተት የማይማሩ። አልፎ ተርፎ ከራሳቸውም ሥህተት ጭምር የማይማሩ።
ይህ ጓደኛዬ ስለነዚህ ወጣቶች ሲያወራልኝ በስሜት ነበር በውስጡ የሚንተከተከው ደም የቆዳውን ከለር እስኪቀይር ነበር ደሙ ፈልቶ በስሜት እያወራኝ ያለው።
እውነት ግን ምን ሆነናል?
ምንስ እየሆንን ነው?
ምንድን ነው የነካን?
እስከማውቀው ኢትዮጵያዊነት እንዲህ አልነበረም፤ እርግጥ ነው ጥንትም አንዳንድ አገርና ሕዝብን ለጥቅም ሲሉ አሳልፈው የሚሸጡ አሉ። ነበሩም በመጠን እና በይዘታቸው ግን ይሕን እንደማያክሉ የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ። "የአበሻ ጀብዱ" የሚለው መጽሐፍ ቋሚ ምሥክር ነውና።
ይህ ተግባር ጓደኛዬ በጠቀሳት አንዲት ከተማ የተወሰነ የተወገዘ ተግባር ብቻ አይደለም። ዋና ከተማችንን ጨምሮ እንጂ።
የወደሙ ሐብት ንብረቶች፣ የሞቱ ሰወች፣ የጎደለ አካል ከአንድ የጦርሜዳ ውሎ በላይ ነው። እንደ አገርም እንደ ሕዝብም በአለም መድረክ የተዋረድንበት። ገዳይም ሟችም እኛው ራሳችን ... የሆንበት አሳፋሪ ተግባር።
የሚላስ የሚቀመስ የሌለው መናጢ ድሃ ወጣት ንብረት ሲያወድም የሥራ ገበታው ሥራ አጥ ወገኖቹ ሰርተው ደመወዝ አግኝተው ቤተሰብ የሚያስተዳድሩበትን ሥፍራ ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ንብረት የሚያቃጥል።
በደጉም በክፉም ጊዜ ጸጥታ በማስፈን፣ ሰላማችን እንዳይደፈርስ ዘብ የሚቆሙ የጸጥታ አካላትን መግደል፣ አካል ማጉደል ያጎረሰ እጅ ነካሽነት ነው።
ለነዚህ አረመኔዎች የአዳል በግነት ምግባራቸውን የሚገልጥ የነውረኝነታቸው መገለጫ ሥም ሳይሆን የክብር ሥም ነው የሚሆነው። ለአዳል በጎች ደግሞ እንዲህ ጭካኔ በተሞላ ተግባር በሚሰማሩ ከሰውነት ክብር በወረዱ በመንጋ በሚያስቡ በመንደር በተወሰኑ ወጣቶች መመሰል ስድብ ነው።
ቀጣይ ትውልድ የማፍራት ተግባር ላይ ቤተሰብ ትልቅ ድርሻ እንዳለው እሙን ነው በመቀጠል የአካባቢው ማህበረሰብ የሐይማኖት አባቶች የአገር ሽማግሌዎች የትምህርት ቤት መምህራን ወዘተ እያለ ይቀጥላል። እስከ ማስታውሰው እነዚህ አካላት በኔ ማንነት ውስጥ ድርሻቸውን ስለምገነዘብ ለነዚህ አካላት ትልቅ ክብር ነበረኝ። እነርሱ በውስጤ ባሰረጿት የአንዲት ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ውስጤ በፍቅር ብርሃን ይንቦገቦጋል የመንደርተኝነት ጨለማ አልዋጠኝም። "ኑ ቡና ጠጡ" የምትል የመልእክት ድምጽ ከወላጆቼ እንደሰማሁ በቀጫጭን እግሮቼ ብን ብዬ በርሬ ዘር፣ ቀለም፣ ሐይማኖት፣ ብሔር ሳልለይ ቡና ጠጡ ብዬ ከመጥራት ወዲያ መከፋፈልን ባላየሁበት ማህበረሰብ ውስጥ እንዴት ዛሬ በሐይማኖት፣ በብሔር ተከፋፍሎ ጸብ ግድያ ማፈናቀል ንብረት ማውደም ከየት መጣ?????
ማንስ በመካከላችን የሐሳብ እንክርዳድ ዘር ዘራ?
የሐይማኖት መምህራን በምሣሌ ሲያስተምሩ አንድ ገበሬ መሬቱን አርሶ አለስልሶ ስንዴ ዘራበት ሰብሉ ከቡቃያነት አልፎ ከፍ ማለት ሲጀምር እርሻውን ቢመለከት አረም ወርሮታል እንደልማዱ ቤተሰቡን ሰብስቦ የአከባቢውን ሰው ደቦ ጠርቶ የበቀለውን አረም አረመው። በመቀጠልም የዘራው ዘር አብቦ ካፈራ በኋላ ተመልሶ ቢመለከተው ንጹሕ የስንዴ እርሻ በእንክርዳድ ተወርሯል። የእምነት መምህራን ይህንን የስንዴ እርሻ በእንክርዳድ መወረር አመስጥረው ሲያስተምሩ "እንክርዳዱን" የዘራው ጠላት ሰይጣን እንደሆነ ያስተምራሉ።
በዚህ ትውልድ መካከልም የሰው ልጅ እንደ ሰው ሲፈጠር እንዲህ በመከፋፈል ሳይሆን ከአንድ አዳም እንደተገኘን አሁንም የእምነት ተቋማት የሥነ ፍጥረት ትምህርት አስተምህሮ ያስረዳናል። እንዲህ በመከፋፈል እንድንባላ እንድንጋጭ አንዱ ሌላኛውን እንዲያሳድድ ንብረት እንዲያወድም አገር እስከ ማፍረስ የሚያደርስ ግጭት እንዲፈጠር የሚያደርጉ ተግባራት ይከናወናሉ። ይህን እንዲሆን ማን አደረገ? ካልን ሁላችንም የምንገነዘበው የሰይጣንን ተግባር የሚተገብሩ በትውልድ መካከል የእንክርዳድ ዘርን የሚዘሩ አክቲቪስቶች፣ ፖለቲከኞች፣ "ከእውቀት ነጻ " ምሁራን ተብዬዎች፣ ሚዲያዎች ወዘተ ናቸው።
ችግሩን ማወቅ የመፍትሔው አጋማሽ ነው እንዲሉ ምሁራን ትውልዱ ራሱን እንዲህ በውስጣችን እንክርዳድ የሚዘሩትን ምን ማድረግ ይጠበቅበታል? መንግሥት? የእምነት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ወዘተ ምን ያድርጉ?
አስቀድመን እንደተናገርን በስንዴ እርሻ ውስጥ የበቀለውን የእንክርዳድ ዘር ገበሬው በመኸር ወቅት ስንዴውን ከእንክርዳዱ በጥበብ እንዲለይ በየደረጃው ያለን ስለ ሕዝባችን ሃላፊነት የሚሰማን ግለሰብ እና በተለያየ የመንግሥት ሃላፊነት በመውሰድ ሠላም የማስፈን፣ ጸጥታ የማስከበር፣ ሕግን የማስከበር ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላት በጥበብና በማስተዋል እራሳችንንና ወገናችንን ከጠላት ዲያቢሎሳዉያን ልንጠብቅ እና ልንከላከል ይገባል።
ወደ መሬት ስናወርደው ሕብረተሰቡ የሚደርሰውን መረጃ ከማህበራዊ ሚዲያ፣ ከኤሌክትሮኒክ ሚዲያ፣ ከህትመት ሚዲያ፣ ወዘተ የምናገኛቸውን መረጃዎች ብስል ከጥሬ መለየት የሚጠቅመውን ከማይጠቅመው፣ እውነተኛውን ከሐሰተኛው መለየት ይጠበቅበታል።
ሕዝብን ከጥፋት አገርን ከመበታተን ሐብትና ንብረትን ከውድመት የሚታደጉ የጸጥታና የደህንነት አካላት አገርንና ሕዝብን ለመታደግ ያገኙትን ሳይንሳዊ ጥበብ ፖለቲከኞችን እና መሪዎችን ከመጠበቅ፣ ተፎካካሪዎችን መረጃ ከመጥለፍ እና ከማገት ተጠብቀው አገርን እና ሕዝብን ከጥፋት ለመታደግ የእለት ተለት አገር ውስጥ የሚሰራጩ መረጃዎችን በማሰስ በመተንተን ጥፋት ከመፈጠሩ ንብረት ከመውደሙ የሰው ህይወት ከማለፉ አስቀድሞ ሊያከሽፍ ጥፋተኛውንም በቁጥጥር ሥር ማዋልና ለሕግ ማቅረብ ይኖርበታል።
የሕግ አስፈጻሚ አካላት እና በተለያዩ ተግባራት ላይ የተሰማራው ባለስልጣን ህግን ከለላ በማድረግ ጥፋት ላይ የተሰማሩትን ፈቃድ ከመስጠት በዘለለ የየእለት ተግባራትን ትክክለኛነት መመዘን፣ እርምትና እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል። ይህንን ካልከወንን ጥፋቱ ቀላል አይሆንምና። እንደ ምሳሌ ብናነሳ በማህበረሰብ መካከል የመከፋፈል ቅስቀሳ የሚያደርጉ ሚዲያዎች አስቀድመው ሕጋዊ ከለላ ለማግኘት በሕጋዊ መልኩ ፈቃድ ወስደው ሥራ ጀምረዋል። ግብር ይከፍላሉ። ሕግ ባለበት አገር ውስጥ ሕጋዊ መስለው ይንቀሳቀሳሉ። ይህ ብቻ በቂ አይደለም። ብሮድካስት ባለስልጣን በየወቅቱ ሥራቸውን መፈተሽ፣ እርምት መውሰድ፣ እርምጃ መውሰድ፣ ወዘተ ይኖርበታል። ይህ ሳይሆን ሲቀር ግን የሚደረገው ሩጫ "ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ" ይሆንብናል። እነርሱ የተቋቋሙበትን አላማ ካሳኩ በኋላ ማስጠንቀቅያ መሥጠት፣ ለመዝጋት መሯሯጥ በሕዝብ ላይ መዘባበት ይሆናል። ሌሎችም እንዲሁ ተጠቅሰው ተዘርዝረው የማያልቁ አስቀድመን አስበን በመከወን ከጥፋት ልንታደግ የሚገቡ ተግባራት አሉን።
ብዙውን ጊዜ እንደታዘብኩት ከሆነ አንድ ነገር ከሆነ በኋላ ህጉን ስንተች ስለ አገሪቱ ሕግ መላላት ስናወራ ይደመጣል። እንደ ኢትዮጵያ ከ98% በላይ ሐይማኖተኛ በሆነ ማህበረሰብ መካከል ስለ ምድራዊ ሕግ መጨቃጨቅ ለኔ ውሃ የማያነሳ ሀሳብ ነው ምክንያቱም እንደ ሐይማኖተኛነታችን እምነትን እንደተቀበለ እና እንደመንፈሳዊ ሰው ምድራዊ ሕግ ለሰው ልጅ ኢምንት ነውና። ምድራዊ ሕግ ስለ መደፈር ፍትሕ ከመስጠቱ በፊት መረጃና ማስረጃ ይሻል። መንፈሳዊ ሕግ ግን ስለ ዝሙት "ያየ የተመኘ አመነዘረ" ይላል። በእምነት ጥላ ሥር ላደገ ማህበረሰብ ሴትን ልጅ ለመድፈር አይነሳሳም። ሕጉ ላልቷል ሥጋት አይሆንበትም። ሕጉን ሳይሆን የሚያወግዘው ዝሙትን ነውና። ስለዚህ የእምነት ተቋማት እና የእምነት ተቋማት መምሕራን ትውልድን በመቅረጽ ላይ ድርሻና ግዴታ አለባቸው። እንዲህ ስንል ግን በእምነት ስም የሚነግዱትን ስመ አምላክ ነጋድያንን ልብ ልንል ይገባል። እነርሱም የትውልዱ ነቀርሳዎች ስለሆኑ።
እንግዲህ እንደ በግ እንዳንነዳ ምን እናድርግ?
በግ ላለመሆን ያለን ብቸኛ አማራጭ ሰው መሆን ነው።
ሰው ስንሆን:-
እንደ ሰው እናስባለን
እንደ ሰው እንኖራለን
ሰዋዊ እሳቤ ይኖረናል
እንተሳሰባለን
እንከባበራለን
በሐሳብ የበላይነት እናምናለን
የሰውን ክቡርነት እናምናለን
ለሕግ እንገዛለን
በጥቅም አንገዛም
አገርና ሕዝብን አንሸጥም
ሕዝብን ለፖለቲካ ፍጆታ አናባላም
ንብረት አናወድምም
አካል አናጎድልም
ሕይወት አንቀጥፍም።
ሰው ክቡር ሆኖ ሳለ አያስተውልም እንስሳትን መሰለ እንዲል እኛም ወደ ማስተዋል ተመልሰን እንደ ሰው እንኑር።
ደረሰ ረታ
ሐምሌ 7/2012

እንደ ሰው ልንኖር

 

የከሰል ጭስን አደገኝነት አውቆ ከሰልን የሚፈራ እና የሚጠላ ከመሸ በኋላ ከሰል አቀጣጥሎ ቤቱ አስገብቶ የሚቆልፍ ሰውና በዘር/ብሔር /በሃይማኖት ግጭት የሚመጣን እልቂት የሚጠላ ነገር ግን ጸቡን የሚያቀጣጥል ሰው ይመሳሰሉብኛል።
መቸስ ግጭት አንዴ ከተቀጣጠለ በኋላ አደጋ እንዳያደርስ የሚያደርግ ብልሃት እንደሌለው አገር ያወቀው ጸሃይ የሞቀው ነው።
አሳን መብላት በብልሃት እንዲሉ ማንኛውም ግጭት ዋስትና የለውምና ሁላችንም ከብሔራችን ሰውን አስቀድመን እንተዛዘን እንከባበር።
እዚህ ቤት ያለ እሳት እዛም ልብ እያልን ቢሆን መልካም ነው።
ዛሬን ለመኖር ትናንትን ምክንያት በማድረግ ከነገ መጨናገፍ ኋላቀርነት ነው።
ትናንት ጡት ተቆረጠ በሚል ትርክት ዛሬ እየቆረጡ ነገን ማበላሸት የትናንት ትርክት እውነት እንኳን ቢሆን በዚህ ዘመን እንዲህ አይነት ተግባር መከወን ከትናንቶቹ እጅግ አንሶ መገኘት ነው።
ትናንት በባሪያ ንግድ ዘመን አባቶቻችን ይህን ኋላቀርነት ለማስቀረት ብዙ ዋጋ እንዳልከፈሉ ዛሬ አለም በዘመነበት ሰአት እንዲህ እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ መሄድ ነው። ድርጊታችንም ሰወች እንዲህ አድርጉ እያሉን እንደ ሮቦት ሳያገናዝቡ መነዳት ዘመናዊ ባርነት ነው።
እምቢኝ ብለን ወደ ኋላ ዘመን የሚያስጉዙንን ልናወግዛቸው የተልእኳቸው አስፈጻሚ ከመሆን በመቆጠብ አገራችንን በልማት እና በሰላም ማስከበሩ ጎን ልንቆም እንደ ፍጥረታችን እንደ ሰው ልንኖር ይገባል።
ደረሰ ረታ
ሐምሌ 29/2012

ለራሳችን ያለን አመለካከት- SELF IMAGE

 ለራሳችን ያለን አመለካከት-

 SELF IMAGE 

****************************************************************

ከምንም በላይ አንዳችንን ከሌላኛችን የሚለየን ነገር ቢኖር ለራሳችን ያለን አመለካከት ወይም ምስል በእንግሊዘኛው ደግሞ Self Image ነው። የስነ ልቦና ባለሙያዎች ስለዚህ የስነ ልቦና ጥበብ መጀመሪያ ባጠኑበት ወቅት፤ ታላቁ የስነልቦና ግኝት ብለውት ነበር። ሁላችንም በዚህ አለም ላይ ስንኖር የኑሮዋችን መጠንና ልኩ የሚወሰነው ለራሳችን ባለን አመለካከት ወይም በአይምሮዋችን ውስጥ ስለራሳችን በምንቀርጸው ምስል ነው። ባህሪያቶቻችን፤ ውሳኔዎቻችን፤ አጋጣሚዎቻችንና በህይወታችን የምንስባቸው ሰዎች በሙሉ ለራሳችን ባለን አመለካከት ተጽዕኖ ስር ይወድቃሉ።
ለራስ የሚሰጥ አመለካከት (self Image) በህይወታችን እጅግ ወሳኝ ነገር ነው። አንድ ሰው ስኬታማና ደስተኛ ሊሆን የሚችለው ለራሱ የተስተካከለና አወንታዊ አመለካከት ሲኖረው ብቻ ነው። ችግሩ ይህንን እውነታ ማንም ሰው ከልጅነታችን ጀምሮ ስለማያስተምረን አብዛኛዎቻችን ለራሳችን የተሳሳተ አመለካከት በመያዝ እናድጋለን። አቅምና ችሎታችንን የሚገድቡ እምነቶች ( Self Limiting beliefs) ሳናውቀው በአይምሮዋችን ውስጥ ስር ይሰዳሉ። እኒህ አመለካከቶቻችን ናቸው የምንፈልገውን ኑሮ እንዳንኖር እንቅፋት የሚሆኑብን።
“እርሱ እችላለሁ የሚለውም፤ አልችም የሚለውም ሁለቱም ትክክል ናቸው”- ኮንፊሺየስ
ህይወታችንን ሊቀይሩ የሚችሉ እውነታዎች በሙሉ ቀላልና ያልተወሳሰቡ ሀሳቦች ናቸው። ምናልባት ለዛም ይሆናል በቁም ነገር ወስደን የማንተገብራቸው። እኛ ሰዎች በተፈጥሮዋችን የተወሳሰበና ከባድ ነገር ይበልጥ ተዓማኒነት ያለው ይመስለናል። ለችግሮቻችን መፍትሄ ስንፈልግ እንኳን ቀለል ያለ ሃሳብ አንቀበልም። እቃ ስንገዛ የተወደደው እቃ ሁሌም ከረከሰው የተሻለ ይመስለናል፤ በወረፋ ካልተሰለፍን በቀር የምናገኘው አገልግሎት ጥራት ያለው አይመስለንም። ተሻምተን ካላገኘናቸው በቀር ነጻ ለምናገኛቸው ነገሮች ዋጋ አንሰጥም። እራሳችንን ለመለወጥ ስናስብም እንደዛው፤ በቀላሉ አስተሳሰባችንን በመቀየር ህይወታችንን መቀየር እንደምንችል አምነን መቀበሉ ይከብደናል። ሰው አስተሳሰቡን በመቀየር ኑሮውን መቀየር እንደሚችል ለብዙ መቶ አመታት ሲንገር የነበረ ቢሆንም፤ ግልጽና ቀልላ ሀሳብ ስለሆነ ነው መሰል እምነት አንጥልበትም።
እያንዳንድችን ስለራሳችን በአይምሮዋችን የምንቀርጸው ምስል አለ። ይህ ምስል መልካም ምስል ካልሆነ በኑሮዋችን ላይ የሚጸባረቁት እውነታዎችም ከዚህ ምስል የተለዩ አይሆኑም። በተቃራኒው ስለራሳችን ያለን አመለካከት ወይም በውስጣችን የምንስለው ምስል መልካም፤ጠንካራና አወንታዊ ከሆነ፤ በኑሮዋችን ላይ የሚንጸባረቁት እውነታዎች በሙሉ የአወንታዊው አመለካከታችን ነጸብራቆች ይሆናሉ። ይህ ለራሳችን የምንሰጠው አመለካከትና ግምት ነው፤ በራሳችን ላይ የሚኖረንን እምነት የሚወስነው። በራስ መተማመናችን የሚበቅለው ለራሳችንን ባለን አመለካከት አፈር ላይ።
በትምህርትም ሆነ በስራ፤ በፍቅርም ሆነ በግል ህይወታችን ውስጥ የምናገኛቸው ውጤቶች ለራሳችን ካለን አመለካከት የሚመነጩ ናቸው። ምናልባት እዚህኛው ጽሁፌ ላይ ትንሽ ስለራሴ መናገር ያለብኝ ይመስለኛል። ከአመታት በፊት ስለራሴ የነበረኝ አመለካከትና አሁን ስለራሴ ያለኝ አመለካከት እጅግ የተራራቁ ናቸው። ለራሴ አነስተኛ አመለካከት በነበረኝ ወቅት ብዙ ነገሮችን “በአልችልም” ስሜት ሸሽቻለሁ። አቅሜን ባለማወቄ ከሚገባኝ በታች የሆኑ ነገሮችን አሜን ብዬ ተቀብዬ ነበር። የተሻለ ህይወት ለሌሎች እንጂ ለእኔ የሚገባኝና የሚቻል ስላልመሰለኝ እራሴን ወደኋላ ጎትቼዋለሁ። ሆኖም ግን እራሴ ላይ መስራት ከጀመርኩኝ ጀምሮ ( After I embarked on the journey of personal development) ኑሮዬ የሚወሰነው ለራሴ ባለኝ አመለካከት መሆኑን ለመረዳት ግዜ አልፈጀብኝም። ደስታና ስኬት፤ ፍቅርና ክብር፤ መውደድና መወደድ ለሁላችንም የቀረቡ ገጸ በረከቶች ናቸው። ለራሳችን አወንታዊ አመለካከት ሲኖረን ብቻ ነው እኛም እንደማንኛውም ሰው ከኒህ ገጸ በረከቶች የፈለግነውን ያህል መቋደስ እንደምንችል የምናምነው።
ለራሳችንን ያለንን አመለካከት መለወጥ እረጅም መንገድ ነው (It’s a Never Ending Process)። ምክንያቱም ስለራሳችን በውስጣችን የምንስለው ምስል የተሳለው በእኛ ብሩሽ ብቻ አይደለም። ቤተሰብ፤ ማህበረሰብ፤ ጓደኛ፤ አስተማሪ እንዲሁም ሌሎች አጋጣሚዎች የየራሳቸውን አሻራ አኑረውበታል ወደፊትም ከተጽዕኖ ሙሉ በሙሉ ማምለጥ አንችልም። ሆኖም ግን አመለካከታችንን የመለወጥ ሙሉው ሃላፊነት የማንም ሰው ሳይሆን የራሳችን ብቻ መሆኑን ማመን መቻል አለብን። ይህ እምነት የመጀመሪያው እርምጃ ስለሆነ።
ስለራሳችን ስናስብ የሚመጣብን ምስል አወንታዊ ካልሆነ በእርግጠኝነት አመለካከታችን ለማስተካከል እራሳችን ላይ መስራት አለብን ማለት ነው። በአይምሮዋችን ውስጥ የምንፈልገውን ኑሮ መኖር እንደማንችል የሚነገርን ድምጽ ካለ፤ በፍርሃትና በአልችልም ስሜት የሚያስፈራራን ምስል በውስጣችን ካለ፤ ለራሳችን ያለንን አመለካከት የተሳሳተ እንደሆነ የሚያረጋገጡልን ምልክቶች ናቸው። ለራሳችን የምንሰጠው አመለካከት የኑሮዋችን ካርታ ነው። አወንታዊና ገንቢ አመለካከት ሲኖረን አቅጣጫችን ወደ ተሻለ ህይወት ነው። በተቃራኒው ለራሳችን ያለን አመለካከት ዝቅተኛ ከሆነና ስለራሳችን ስናስብ አሉታዊ ምስል የሚቀረጽብን ከሆነ እየተጓዝን ያለነው ወደማይጠቅመን ጎዳና ነው። ደስተኛ ለመሆን የተስተካከለ አመለካከት ወሳኝ ነው፤ ስኬታማ ለመሆን ስለራሳችን አወንታዊ ምስል በውስጣች ሊኖር ግድ ይለናል። ይህ ሀሳብ እጅግ ሰፊ ነው፤ ጽሁፌን ግን ማንዴላ በእስር ሳለ ብርታት ይሰጠው ከነበረው ድንቅ ግጥም ውስጥ በተወሰደች ስንኝ ልቋጭ።
“እኔ ነኝ የእድሌ ወሳኝ፤ የእጣ ፋንታዬ መሪ
የነፍሴ ጀልባ ቀዛፊ፤ የኑሮዬ ሹፌር ዘዋሪ”
“It matters not how strait the gate,
How charged with punishments the scroll.
I am the master of my fate:
I am the captain of my soul.”- Invictus poem by William Ernest Henley.
@mindsetethiopia

እራስን ተጠያቂ ማድረግ መለማመድ (ክፍል ስድስት)

 

ይህቺ ምድር መሽቶ እስኪ ነጋ ነግቶ እስኪመሽ ጉድ ነው የሚሰራባት አስቀድሜ እንደነገርኳቸው ትንንሾች ትልቅ የሆኑ የሚመስላቸው ትልቁን ሲያጠፉ፣ አንገት ሲያስደፉ፣ አገር ሲያጠፉ፣ ትውልድ ሲያመክኑ ነው።
አንዳቸውም ጠቋሚ ጣታቸውን ወደራሳቸው አያዞሯትም፤ ወደሰው ከመቀሰር ውጪ። ራስን ለማየት አልታደሉም።
በአንድ ወቅት ነው አሉ ሰውየው ሚስቱን አየሻቸው እያለ ወደ ጎረቤትየው ቤት ያመለክታታል ሚስትም ወዳሳያት ትመለከታለች። ታጥቦ የተሰጣው ልብስ በደንብ እንዳልታጠበ የጎረቤታቸው ሴትዮ ልብስ እንኳን ማጠብ እንደማትችል ይነግራታል። ሌላ ቀንም እንዲሁ ያየውን ያሳያታል ሚስትም አይታ መልስ ሳትሰጠው ትሄዳለች። እንደለመደው በሶስተኛው ቀን ወደ መስኮቱ ይመለከታል ጎረቤቱን ለመተቸት ያየውን ነገር ማመን ይከብደዋል። ሚስቱን ጠራት ያየውን ነገር በመደነቅ ያወራላታል፤ ይህን የማይታመን ነገር አየሽ? ሴትዮዋ ሰራተኛ ቀጥራ ነው ወይስ እንዴት እንዲህ ባለሙያ ብትሆን ነው ያጠበችው የጠራላት? ሚስትም መለሰችለት።
እስከዛሬም ጎረቤታችን ባለሙያ ነበረች ሁሌም ልብስ የምታጥበው ጥርት አድርጋ ነው በዚህ ምንም እንከን አይወጣላትም። ችግሩ ያለው ያየህበት ሁኔታ ያየህበት መንገድ ነበር ችግር የነበረበት።
እቤት ተቀምጠህ በመስኮት ነበር የምትመለከተው የመስኮታችን መስታወት ደግሞ አጽድቼው ስለማላውቅ ቆሽሿል። ከዚህ የተነሳ የጎረቤታችንን ንጹሕ የተሰጣ ልብስ በቆሻሻ መስታወት ውስጥ ስታየው ቆሻሻ መሰለህ። ችግሩ ከልብሱ አልያም ከአጣቢዋ ሳይሆን ካየህበት ከኛው መሥታወት መቆሸሽ ነው ብላ ከስህተቱ አረመችው።
ስንቱ ተመልካች ይሆን የራሱን ቆሻሻ እይታ የሌላኛውን ንጽሕና ያጎደፈው?
ስንቱ ይሆን በራሱ ሸውራራ እይታ ቀጥ ያለውን ነገር ያጎበጠው?
ስንቱስ ይሆን በእንደዚህ አይነት ተመልካቾች ውሳኔው የተዛባው? ፍርድ የተጓደለው? ድሃ የተበደለው?
ስንትትቻችውስ ይሆኑ የራሳችው ቆሻሻ እይታቸውን የጋረደባቸው?
በምድር ዛፍ ሆነን ባሳለፍንባቸው ዘመናት አብያተ እምነቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ተቋማት፣ መሪዎች፣ ሕዝቡ፣ ወዘተ ራሳቸውን እንደማየት ጊዜያቸውን ሌሎችን በማየት የሚያባክኑ።
ሁሉም በጉያቸው ትልቅ ችግር ተሸክመው ጠላታችን እገሌ ነው በማለት ጣታቸውን ይቀስራሉ፤ ለዚህ ነው ለችግራቸው መፍትሔ ያላገኙት።
እስኪ በአገራችን የእምነት ተቋማትን ተመልከቱ በውስጥ ችግር ላይ አተኩሮ ከመጠናከር፣ በአንድነት እምነታቸውን ከማጠንከር፣ እርስ በርስ ላይ የተመሰረተ ህብረት ላይ እይታቸውን ከማድረግ ይልቅ እይታቸውን ሌላ ነገር ያተኩራሉ። ሁሉም ከራሳቸው የላቀ ጠላት የላቸውም።
ሁሉም በጉያቸው ብዙ ቁጥር ያለው መናፍቅ፣ ባንዳ፣ ሌባ፣ ተሸክመው ከጥቂቶች ጠላቶች ራሳቸውን ለመከላከል ይጥራሉ። ውጤቱን ገምቱት
እኛም ዛፎች ይህ ችግር ይታይብናል።
ይህ ችግራችን ነው ዛሬ ተሰባስበን ጊዜያችንን እያባከንን የምንገኘው፤ የችግሩን ምንነት ሳንለይ ለመፍትሔ የተሰበሰብነው።
በሰው ዘንድም ብዙ በጀት ተመድቦ፣ ጊዜ ወስደው፣ ጥናት አስጠንተው፣ በስብሰባ እድሜያቸውን ያለ መፍትሔ የፈጁት ከችግር ጋር ተወልደው ያረጁት ምክንያቱ ችግሩን ሳይለዩ ለመፍትሔ ስለሚቀመጡ ነው።
እኛ ጠላት ብለን የተቀመጥነው መሉ በሙሉ የፈረጅነው የሰው ልጅ ነው፤ ነገር ግን በጥልቀት ስንመረምረው የራሳችን ጥመት ተጣሞና ተንጋዶ ማደግ ለመጥረቢያ መመቸት ነው።
ሰውም እንዲሁ ለጥቃት መመቻቸት፣ ተጋልጦ መሰጠት ነው የጎዳቸው እንጂ ሌላ ስራ ፈትቶ እነሱን ለማጥቃት የሚደክም የለም። እስከነ ተረቱም አህያቸውን ውጪ እያሳደሩ ጅብን ነገረኛ ያደርጋሉ እንደሚባለው ነው።
በሉ እንግዲህ ከምንም በፊት እራሳችንን እንመርምር፣ ሌላው ላይ ከመፍረዳችን በፊት ከችግሩ ንጹሕ መሆናችንን እናጥራ፣ የችግሮች ሁሉ መፍትሔ ሩቅ አይደለም ሌላ ቦታ ሳይሆን እኛው ጋር ነው።
ሌሎችን ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ ራሳችንን ተጠያቂ ማድረግ እንለማመድ።
በጎቹን ተኩላ የነጠቀው/የበላቸው እረኛው ችግር ስላለበት ነው፤
ርስታችን የተወረሰው ርስታችንን ምንም ስላልሰራንበት ነው፤
ሌሎች መጥተው የደፈሩን እኛ ስላልተከባበርን ነው፤
የገደሉን ፍቅር ስላልተሰጣጠን ነው፤
ቤታችንን የበረበሩት አጥራችንን ስላላጠበቅን ነው፤
ጠላታችን እኛ ራሳችን ስለሆንን ራሳችንን ማሸነፍ፣ ተጠያቂ ማድረግ እንልመድ፣ እኛ ቀዳዳችንን መድፈን ስንለምድ ጠላትን እንዴት መከላከል እንዳለብን ይገባናል።
ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ።
ተፈጸመ።
የዘመንን ወለምታ፣ የትርክትን ስብራት፣ ሸውራራ እይታን፣ በቀና አስተምህሮ እንጠግናለን።
ይከታተሉን።
ሐሳብ አስተያየትዎን ከመስጠት አይቆጠቡ።
መልካም ቀን ይሁንልዎ።
ደረሰ ረታ
ነሐሴ 13/2012 አ.ም

እራስን ተጠያቂ ማድረግ መለማመድ (ክፍል አምስት)

 

ሰው ማለት በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚድያ ሕግ የሚወጣለት፣ የራሱ ጉዳይ ስንት እያለ በየሚድያው ስለራሱ ሳያወራ አንድ ማስታወቂያ ሰምተን እንመለሳለን እያለ ስለቁሳቁስ ትልቅነት ይደሰኩራል፣ አንድም ቀን ስለ ሰው ልጅ ትልቅነት ስለ ዛፎች አስፈላጊነት ጊዜ ተሰጥቶ አይወራም፣ ይኸው አንድ መሪ ከወደ ኢትዮጵያ ቢገኝ እና ዛፍ እንትከል ቢላቸው የሰው ዘር ከምድረ ገጽ እንንቀል ያላቸው ይመስል ጠምደው ይዘውታል። እነ ሥመ አይጠሬ ሰው እናፈናቅል ሲሏቸው አይደለም ቀን ሌሊት ይወጣሉ።
ምድራችን ዛሬም ስለ አስገድዶ መደፈር ሕግ ላይ ይጨቃጨቃል፣ ክቡር የሰው ልጅ መሰረታዊ አስፈላጊ ነገር አልተሟላለትም፣ ረሐብ፣ በሽታ፣ ጦርነት፣ የተፈጥሮ አደጋ፣ ሰው ሰራሽ አደጋ፣ የራስ ምታት ሆኖበታል።
ሰው ምድር ላይ ክቡር ፍጡርነቱ ተዘንግቶ ገራሚ የፊልም ስክሪፕት ሆኗል።
አስቂኝ፤ መሳለቂያ።
ትውልዱ በሰለጠነ ዘመን ቁልቁል ሄዷል፤ ለምን የሚል ከተገኘ መፍትሄው ቅርብ ነው።
እኔ በዘመኔ ገና ችግኝ ሳለሁ አባቶቻችን ትላልቅ ዛፎችና ዋርካዎች በየደብሩ፣ በየገዳማቱ፣ በየመስኪዱ፣ እና በየቄዬው ቁምነገር መገበያያ ነበሩ።
የተጣላ የሚታረቅበት፣ መንገደኛ የሚያርፍበት፣ እረኛ ጸሐይ የሚያበርድበት፣ ታሪክ የሚነገርበት፣ እድር እቁብ የሚጠጣበት፣ እውቀት የሚገበይበት ነበር።
የሰው ልጅ አስተሳሰቡ የተቃኘው ዛፍ ስር ነው፤
እውቀት የገበየው ዛፍ ሥር ነው፤
ሥንትና ሥንት አገራዊ ጉዳዮች ውሳኔ ያገኙት ዛፍ ሥር ነው፤ ጥቅማችን የትዬለሌ ነው። ለዚህ አለም ከመጥፋታችን መኖራችን ነበር የሚጠቅመው። ዛሬ ግን ለራሱ ክብር የነሳው የሰው ልጅ ጥቅማችንን ዘነጋው።
እኛ ዛፎች በጥንት ሰወች እንደሚነገረው ከሰው መርጦ ለሹመት ከእንጨት መርጦ ለታቦት ተብሎ የተነገረልን ነን። የሰው ልጅ ሥለ ራሱ ምን እንደሚያስብ ማወቅ ቢከብድም አሁንም ቢሆን እኛ ዛፎች ትልቅ ነን ስለትልቅነታችን፣ ስለ አስፈላጊነታችን ነው የማምነው። እኛ ከሌለን ፍጥረት መኖር ይከብደዋል። እኛ የምንመኘው ለኛ ሕልውና ሲባል ሰወች እንዲኖሩ ጸሎታችን ነው። የእነርሱን ስለኛ ያላቸውን አመለካከት ባናውቀውም።
ታናናሾቼ ዛፎች ቅድም ወዳነሳሁት ታሪክ ልመልሳችሁና አብዛኛው የእምነት አባቶች ውሎና አዳራቸው ዛፍ ሥር ነበር። ገና ከጨቅላ እድሜያቸው አንስቶ ፊደል የቆጠሩት፣ ምንባብ እና ዜማ የቀጸሉት እኛ ዛፍ ሥር ነው፤ ሥነምግባር እና ብዙ እውቀት የገበዩት እዚሁ ነው።
ታሪክ ያልኳችሁ ዛሬ ይኽ የለም ብዙ የእውቀት መገብያ ወንበሮች ታጥፈዋል፣ የቆሎ ተማሪው ሊቁ ከተማ ገብቶ ሎተሪ አዟሪና ተሸካሚ ሆኗል፣ አድባራትና ገዳማት ሊቃውንት ተራቁተዋል፣ ካድሬ ተሰግስጎባቸው ክብራቸውን አጥተዋል፣ሥለ ፍርድ መጓደል ሥለ ድሃ መበደል የሚሟገት ጠፍቷል፣ እውቀትን እውነትን የሚያስተምር የላቸውም፣ መሥጊዶች ውበታቸው፣ ግዝፈታቸውና ይዞታቸው እንጂ ኡስታዞች ሼኮች ኡለማዎች ሰሚ አጥተዋል።
አደባባዮች የጲላጦስ አደባባይ ሆነዋል ንጹሕ የሚሰቀልባቸው ቆሻሻውና ነውረኛው የሚነግስበት።
ትምህርት ቤቶች ትውልዱ መክኖ የሚወጣበት ከሆነ ከረመ፣ ሥነምግባር አይነገርበት፣ ሥለ አገር ፍቅር አይሰበክበትም፣ ታሪክ ይንጋደድበታል፣ ጥላቻ ይሰበክበታል፣ ጭንቅላት ይንጋደድበታል፣ አክቲቪስት/አፈ ክፍት/ ፣ ፖለቲከኛ ይፈለፈልበታል።
ሰውና አለሙ እንዲህ ነው፤
ሥንጠቀልለው ችግራችን ራሳችን ነን ራስን ተጠያቂ ማድረግ እንልመድ። የጠፋነው ራስችን ጠማማ፣ ቆልማማ ሆነን ነው ለአጥፊዎቻችን የተመቸነው።
በፍጹም ቀጥ ብለን እስካላደግን ስለመጥፋታችን በሌሎች ላይ ጣታችንን አንቀስር፣ አንድ እንሁን አንለያይ፣ እኔ በሚል ትብታብ አንተብተብ፣ እኛ በሉ፣ ለመወፈር ሌላውን አናቀጭጨው፣ ትልቅ ለመምሰል ሲሉ ሌላውን ማቅለል ማሳነስ የክፉ ሰው ተግባር ነው፤ ዛፎች ይህ የለብንም የሚታይብን ይኸንን በአስቸኳይ እናስወግድ።
እንደምትመለከቷቸው ሰወች ናቸው ትልቅ መስለው ለመታየት ትልቅ ሰው የሚሳደቡት፣ የሚያንቋሽሹት፣ የሚዘረጥጡት፣ ... አንዳንድ ሰወች ከአስተሳሰባቸው ማነስ የተነሳ ብሔርን ሳይቀር፣ ቋንቋን ሳይቀር፣ እምነትን፣ ባሕልን፣ ... ሳይቀር የነርሱ ካልሆነ አሳንሰው ያያሉ። ይህ ትልቅ ስህተት ነው አያኗኑርም ያጋጫል። ግጭቱ እንዲህ በቀላሉ የሚቋጭ እንኳን አይደለም ከትውልድ ወደ ትውልድ ይሸጋገራል።
በዚህ ዘመን ትልቅ ሰው አይከበርም፣
ሐሳብ ያለው አይወደድም፣
ለምን? ብሎ የሚጠይቅ ሰው እርኩስ ነው፣
አድር ባይ ሲሊኩት ሄዶ ሰፈር እንደ ችቦ የሚለኩስ፣ መንገድ እንደ ደጃፍ የሚዘጋ ይፈራል ይከበራል ይሾማል ይሸለማል፣
ችግር የሚባል አይደርስበትም፣
ንጹሕ ሰው ተሳቆ ይኖራል፣
ሽማግሌ የሐይማኖት አባት አይሰማም አይከበርም፣ ሥነ ምግባር፣
ግብረ ገብነት አይነገርም፣
ቀጥ ያለ አይወደድም፣
ወደ ፊት መጓዝ ሳይሆን እንደ ሎጥ ሚስት ወደ ኋላ መመልከት የአገሪቱ/የትውልዱ ማነቆ ነው።
ይቆየን።
ክፍል ስድስትን ያገናኘን።
የዘመንን ወለምታ የትርክትን ስብራት በቀና አስተምህሮ እንጠግናለን።
ይከታተሉን።
ሐሳብ አስተያየትዎን ከመስጠት አይቆጠቡ።
መልካም ቀን ይሁንልዎ።
ደረሰ ረታ
ነሐሴ 13/2012 አ.ም
እንኳን ለደብረ ታቦር (ቡሄ) በአል አደረሳችሁ።

እራስን ተጠያቂ ማድረግ መለማመድ (ክፍል አራት)

 

12/12/12
ጎበዝ መጨረሻችን የመጥረብያ እጀታ አይሁን፣
ቅርንጫፎቻችንን አንመልከት ቅርንጫፎቻችንን ከተመለከትን ብዙ የተራራቅን ይመስለናል፤ ሥሮቻችንን ተመልከቱ እንዲህ አምሮብን ዘመናትን ያስቆጠርነው የሥሮቻችን ተጋምደው መኖር ነው ምሥጢሩ።
እንደ ሰው ልጅ ፍላጎት ቢሆን ገና ድሮ አልቀናል፤
ምድር ተራቁታ ድርቅ ምድረ አዳምን ከምድረ ገጽ ባጠፋ ነበር።
ጨከን ብለን ለራሳችንም ሆነ ለሰው ልጅ ሥንል እንኑር።
እኛኮ ከአንድ ለም አፈር የበላን ከአንድ ምንጭ የጠጣን የአንድ ምድር ውጤቶች ነን። ቅርንጫፎቻችንን አንይ ሥራችን አንድ ነው። ቅርንጫፎቻችንን ላየ በቀላሉ ሊለየን ይችላል ሥራችንን ዘልቆ የተመለከት ማንም አይለየንም።
የሰው ልጅም እንዲህ የሚባላው ቅርንጫፉን እየተመለከተ ነው፣ ቀለሙን ፣ ሐይማኖቱን፣ ጎሳውን፣ ቋንቋውን፣ አከባቢውን፣ ... ነገር ግን የትመጣውን ቢመረምር ከአንድ አፈር ነው። ይህ ጠፍቶት ነው የሚባላው።
እድሜዬ ጠና እንደማለቱ ብዙ የሰው ልጅ ጠባይ አውቃለሁ። መኖር ደጉ ይኸውላችሁ ... ብለው አንገታቸውን አቀረቀሩ በሐሳብ እሩሩሩሩሩቅ ሄዱ፤ ጸጥታው ሰፈነ ... አልተመለሱም።
በምርኩዛቸው ምድርን ቆረቆሩ፣ እንባቸው በአራቱም ማእዘን ወረደ። ጭንቅላታቸውን ነቀነቁ። ይህቺ ምድር ትፍረዳ ብለው አንገታቸውን ቀና አደረጉ።
ይህቺ ምድር እና እኔ ስንቱን አየን ምድር ሥንቱን ደጋግ አባቶች ከጉያዋ ሸሸገች? ጓደኞቼ ለሥንቱ መቀበሪያ ሣጥን ሆኑ?
ሥንት ጀግና ሥንት አገር ወዳድ ሥንት ለሰው ሟች በቀለባት ይህቺ ምድር? ዛሬ አቃፊ ነን ባይ እንጂ እንግዳ እንኳን በቅጡ የሚያስተናግድ የለባትም ምድራችን፣ እሾክና አሜኬላ አበቀለች ምድር፣ ያለ ማዳበሪያ ፍሬ አልሰጥ ካለች ሰነበተች፤
ለምን? ብሎ የሚጠይቅ ትውልድ የለም።
ተገዶ ሳይሆን ወዶ ትውልዱ እንደ እኛ ለሚጨርሱት እጀታ ሆኗል እንደ እኛ።
እጀታ ሆኖ እርስ በርስ ከተጨራረሰ በኋላ ጨረሱን ይላል መለስ ብሎ ... ለምን? እንዴት? አይልም።
ግርርርርር ከማለት ምን ይገኛል?
ያለ ጎረቤት ብቻውን ምን ሊሆን ነው?
ጓዶች ያለ ሰውኮ ይህቺ ምድር ጨው እንደሌለው ወጥ ነው፤ ቀምሼ ባላውቀውም አሉ ታላቁ ዛፍ/ ዋርካው። ዛፎች ፈገግ አሉ በትልቁ ዋርካ አነግስገር።
ተመልከቱ አሉ እጃቸውን ወደ ማዶ እየጠቆሙ ያ የምትመለከቱት ቤት ባለቤት ወላጆቻቸውን ወደ ኋላ ተመልሶ የሚያጠና ቢገኝ የነርሱ ቤተሰብ የኋላ አመሰራረት እና የዛሬ ልጆቻቸው ታሪክ ለየቅል ነው።
ወላጆቻቸው መንገደኛ እንግዳ ተቀባይ፣ የተራበ የሚያበሉ፣ የተጠማ የሚያጠጡ፣ የታረዘ የሚያለብሱ፣ የታመመ የሚጠይቁ፣ ... ነበሩ። የዚህ ቤት ታሪክ "ነበር" ላይ ተገትሮ ቆሟል፤ ቶሎ የሚደርስለት ትውልድ ካልተገኘ አደጋ ላይ ነው።
ዛሬ ቤቱን ብትመለከቱ ብዙ ክፍሎች ተዘገተው ተቀምጠዋል። እንኳን እንግዳ ሊቀበሉ ልጆቻቸው መጻተኛ ሆነው በየአለማቱ ተበትነው እንግዳ ሆነው ይኑራሉ። ይህ ቤተሰብ የሁሉም ቤተሰብ ምሣሌ ነው። የአገር ምሣሌ ነው። ቤትና አገር አንድ ነው ብዙ የሚያመሣሥላቸው ነገር አለ ሁላችንም እንዳየነው ቤት ተሰርቶ ሰው ገብቶ ካልኖረበት ይፈርሳል። አገርም አያድርግባቸውና እንደዛው ነው። ክልሎች ከኛ ሰው ውጭ አይኑርበት ብለው የሚያፈናቅሉት ጥቅማቸውን ነው እየነኩ ያሉት የሰው ልጅን ጥቅም ሥላልተረዱት።
ቢገባቸው ኖሮ እንኳን ሊያሳድዱ፣ ሊያፈናቅሉ፣ ሊገድሉ፣ ሐብትና ንብረታቸውን ሊያወድሙ ይቅርና ሙሉ ወጪያቸውን ችለው ባኖሯቸው ነበር። የሰው ልጅ መኖሩ ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው። ምድር ተራቁታ በረሃነት ባልሰፋ ፣ ምድር ለምነቷን ባላጣች፣ እኛ ተጨፍጭፈን ብቻ ባላለቅን፣ ሰው በተፈናቀለ ቁጥር ቤት ሊሰራ ባልመነጠረን ነበር፤ ወገኖቼ ታሪኩ ብዙ ነው ስንቱ ተዘርዝሮ ያልቃል።
በአጭሩ እንኳን ሰው እና ሰው እኛና ሰው ተለያይተን መኖር አንችልም። ወደ ዋና ጉዳዬ ስመጣ እኛና ሰወች ጠላቶች አይደለንም ተመጋጋቢዎች ነን። አንዳንችን ለአንድኛችን አስፈላጊ ነን። የምንጠፋፋ አይደለንም። እኛ ያለነሱ እነርሱ ያለኛ አንኖርም። እነርሱ ራሳቸው ሰወች እንዳጠኑት በሳይንሳቸው ከነርሱ በሚወጣ የተቃጠለ አየር እኛ ስንኖር እነርሱ ከኛ በሚወጣ አየር ይኖራሉ።
እናንት ወገኖቼ አስቀድማችው እንደ ጠቀሳችሁት ሰወች ጨረሱን፣ ጨፈጨፉን፣ ወዘተ ያላችሁት ትንሽ እውነት አለው። ነገር ግን ትንሽ እውነት ትልቁን እውነት አይበልጠውም። ሂሱን ዋጡት ለመቼ ሊሆናችሁ ነው ዋናው የራሳችን ችግር እራሳችን ዛፎች ነን። ተንጋደን እናድጋለን ለመጥረቢያ እጀታ እንሆናለን የሰው ልጅም በመጥረቢያ እየጠረበ ይማግደናል። መፍትሄው ጨረሱን እያሉ ከማዜም ተንጋዶ አለማደግ ነው።
እድሜ እንዳስተማረኝ የሰው ልጆች ተንጋዶ ማደግ ለእርስ በርስ እልቂት ዋናው መንስኤ ነው። አስተዳደግ ወሳኝ ነው። በተለይ የሰው ልጅ ሲያድግ ዝም ብሎ እንዳገኘ ማደግ የለበትም። አስተዳደጉ መጨረሻውን ይነግረናል። ምን በልቶ አደገ ብቻ ሳይሆን ምን ሰምቶ፣ ምን ተምሮ፣ ምን አይቶ፣ ወዘተ አደገ የሚለው ለሰው ልጅ መሰረታዊ ጥያቄ ነው።
ዛሬ የሰው ልጅ ስለሚለብሰው፣ ስለሚጫማው፣ ስለሚይዘው ሞባይል፣ ስለሚያሽከረክረው መኪና፣ ... እንጂ ስለሌላው አይገደውም።
ሌላው ቢቀር በያዘው ሞባይል ስንት ሸርና ተንኮል እንደሚንሸራሸርበት አይመረምርም። ያገኘውን ሁሉ ያምናል። ተነስ ሲሉት ይነሳል ፣ ተቀመጥ ሲሉት ይቀመጣል፣ መንገድ ዝጋ ሲሉት ይዘጋል፣ አቃጥል፣ አፈናቅል፣ ግደል፣ ስቀል፣ ሲሉት ያሉትን ሁሉ አምኖ ያደርጋል።
ትውልዱ የአክቲቪስቶች፣ የፖለቲከኞች፣ የክፉ ሰወች፣ ... ማስፈጸሚያ እጀታ ሆኗል። አይመረምርም። አይመራመርም።
ይኸን ዝም ብሎ መነዳት፣ አስፈጻሚ፣ ፈጻሚ መሆን እኛ ከሰው ተማርን? ወይንስ ሰው ከኛ ተማረው?
መልስ አልነበራቸውም።
እንዲህ ከተሰባሰብን አይቀር ብዙ የማጫውታችሁ ነገር አለ እንኳን ስለኛ ሰለ ሰውም ጭምር።
ለክፍል አምሥት ይቆየን። የኚህን ታላቅ ዋርካ የታሪክ ምሥክርነት የመፍትሔ አቅጣጫ እንዳስሳለን።
ይከታተሉን።
ሐሳብ አስተያየትዎን ከመስጠት አይቆጠቡ።
መልካም ቀን ይሁንልዎ።
ደረሰ ረታ
ነሐሴ 12/2012 አ.ም.

እራስን ተጠያቂ ማድረግ መለማመድ (ክፍል ሶስት)

 

ነሐሴ 11/2012 አ.ም.
እንደ ሰው ልጅ በምክንያት በሰበብ ጥፋተኝነታችንን ወደሌላ አናሸጋግር ሰወች ለችግራቸው መፍትሔ ያጡት ችግሩ ስለከበደ አይደለም። የችግሩ ባለቤት ራሳቸው ሆነው ሳለ መፍትሔ የሚፈልጉት ከሌላ ጉያ ነው። ራሳቸው ላጠፉት ጥፋት ምክንያት ይደረድራሉ።
ሁላችሁም እንደምታውቁት ሁላችንም የተፈጠርነው ለአዳም ጥቅም ሲባል ነበር ነገር ግን የሰው ልጅ የክፋት ሁሉ ምንጭ የሆኑት አዳምና ሔዋን እርስ በርስ ባለመተማመናቸው እና ሐላፊነትን ባለመውሰዳቸው አትብሉ በተባሉት አንዲት ዛፍ ፍሬ አንዳንዳቸው በአንዳቸው ሲመከኛኙ ከገነት ተባረሩ።
እኛስ ለችግራችን መፍትሔ እንድናገኝ እዚህ ተሰብስበን ከሆን መፍትሄውን ከልባችን ሽተን ከሆነ መፍትሔ ከሌላ ስፍራ ከመፈለጋችን በፊት እስኪ ራሳችንን እንመርምር፣ ራሳችንን እንይ፣ ችግሩ የመነጨው ከውስጥ ነው ከውጭ የሚለውን በጥሞና እንፈትሽ።
የሰው ልጅ በዚህ በ21ኛው ክ/ዘመን እንዲህ የሚባላው፣ የሚተላለቀው የችግሩን ምንጭ ባለማግኘቱ ነው። ችግሩን ከጉያቸው ተሸክመው መፍትሔውን ከአጎራባች አገር፣ ከታናናሽ አገር፣ ከኢኮኖሚው አቻቸው፣ ከፖለቲካ ተፎካካሪዎቻቸው ዘንድ ስለሚፈልጉ ነው፤ ይህ ደግሞ ከሰው ልጅ የምንማረው እነርሱ እንደሚተርቱት " ላም ባልዋለት ኩበት ለቀማ " ይሆንብናል።
ስለሰወች ልጆች በማውራት ጊዜያችንን አናባክን እስኪ ሁላችንም ራሳችንን እንይ ... የጥፋታችን ምንጭ ምንድን ነው? ጠላታችን ማነው? ማነው ያጠቃን ማንስ ነው ያጠፋን? ያልን እንደሆነ ሁላችሁም ከዚህ ቀደም ደጋግሜ እንደጠቀስኩት የሰው ልጅ፣ እንስሳት፣ በሽታ እነዚህ ዋነኛ ተጠቃሽ ነው። ነገር ግን እነዚህ እንደ ዋና ችግር የሚጠቀሱ ሲሆን ዋናው ተዋናይ እኛው ነን።
ጉርምርምታው ጨመረ፣ የነበረው ጸጥታ ደፈረሰ፣ ዋርካው ዛፍ አንገታቸውን ዘንበል አርገው ዝም አሉ። በየ አቅጣጫው ጫጫታው ሰሚ አጣ ሁሉም ተናጋሪ ሆነ፤ አድማጭ ጠፋ ሽማግሌው ዛፍ ንትርኩ ማብቂያ እንደሌለው ሲገነዘቡ ከቦታቸው አረፍ አሉ።
ተንጫጭተው ሲያበቁ ወደ ተናጋሪው ቢመለከቱ የሉም። መናገሩን ትተው ዝም ብለው ቁጭ ብለዋል። ይንጫጫ የነበረው ሁላ ተደናግጦ ዝም አለ።
ሰብሳቢ ተሰብሳቢ ጠፋ ሁሉም መንጋ ሆነ ... መንጋነትን ሰወች ከእንስሳት ተረከቡ ዛሬ ደግሞ እጽዋት ከሰወች ተረከቡት ማለት ነው።
የሰው ልጅ መስማት/ማድመጥ ስለተሳነው ነው ዛሬ እንደ እንስሳ ክብሩን የተነጠቀው እና ማስተዋል የተሳነው። ለዚህ ነው እንደተንቀሳቃሽ ሮቦት በሰው አስተሳሰብ የሚነዳው። ክፉና ደጉን መለየት ያቃተው። ሰው በሰው ላይ በራሱ ወገን ላይ በጠላትነት የተነሳው።
አዛውንቱ ዛፍ ብድግ አሉ፤ ሁሉም አፍሮ አቀረቀረ። ጸሐይ እንደመታው ለጋ ቅርንጫፍ በእፍረት ጠወለጉ። እኚህ ትልቅ ዛፍ አንድ የተጣመመ ዛፍ በእጃቸው ምልክት ሰጥተው ወደርሳቸው እንዲመጣ ጠሩት ... መጣ ... ይታያችኋል? ... እስኪ ለሁሉም እንድትታያቸው ወደ መድረኩ ውጣ ... እስኪ ከዚህ ወንድማችን ከዚህ ዛፍ ምን ተመለከታችሁ? ሁሉም በአንድ ድምጽ ከየአቅጣጫው ጠማማ ነው፣ ጎባጣ ነው፣ ... እያለ በተለያየ ቃላት ዛፉን የሚገልጠውን ነገር ተናገረ።
በሰው ልጆችም መካከልም ስንት ጠማማ፣ ስንት ጎባጣ አስተሳሰብ ሰው ያለ መሰላችሁ?
ከዚህ ዛፍ ምን ተማራችሁ?
ይህ ዛፍ የሰው ልጅ እጅ ሲገባ ምን የሚሆን ይመስላችኋል?
ዝምታ ሰፈን።
አይዟችሁ ድፈሩ ... ዝምታችሁ እውነታውን አይቀይረውም።
አብረን እንደመኖራችን ከሰው የወረስነው ብዙ ጠባይ አለ፤ ሰወችም ልክ እንደ እናንተው ናቸው ጥፋተኝነታቸውን ለመሸሸግ፣ እውነትን ለመሰወር፣ ... ዝም ይላሉ።
እውነት ሩቅ ብትሆንም ተሰውራ አትቀርም ፤ ትገለጣለች። የተገለጠች ቀን አንዳች ከፊቷ የሚቆም የለም። እስከዚያ ግን ትንሹም ትልቁም በጠማማ ልቡ ንጹሑን ያጎድፋል፣ ድሃውን ይበድላል፣ ፍርድ ያጓድላል፣ ያሳድዳል፣ ያፈናቅላል፣ ይገድላል።
እኛንም በዚህ ክፋቱ እኛኑ ተጠቅሞ በዚህ በምትመለከቱት ጠማማ ጫፍ ላይ መጥረቢያ ሰክቶ ይጨፈጭፈናል። ያወድመናል። ወደ እሳትም ይማግደናል። ይኽ ጥፋታችን ተሰውሮብን ወደ ወጥመዱ እንንደረደራለን፣ የክፉ ሰወች መጠቀሚያ እንሆናለን።
ሰውም እንዲህ ነው እርስ በርስ በዘር ፣ በሐይማኖት፣ በቀለም፣ በሰፈር፣ ... እየተከፋፈለ የሚጨራረሰው።
"ችግሩን አግኝተናል" አሉ ሰብሳቢው ዛፍ በተናጋሪው ጣልቃ ገብተው፤ ተናጋሪውን ማቋረጥ ፈልገው አይደለም።በስሜት እንጂ መልሳቸው ልባቸው ስለኮረኮረ እነርሱ ያልተመለከቱትን ስላስገነዘቧቸው ለትልቁ ዋርካ አድናቆታቸውንም ለመግለጥ እንጂ።
ጭብጨባ ከአራቱም ማእዘን አስተጋባ።
ችግኞች ፣መካከለኛ ዛፎች፣ ዋርካዎች እየደጋገሙ አጨበጨቡ።
ዋርካው ዛፍ ወደ መቀመጫቸው አመሩ፤
ይቆየን። ወደ አራተኛ ክፍል ሰላም ያሻግረን።
ይከታተሉን።
ሐሳብ አስተያየትዎን ከመስጠት አይቆጠቡ።
መልካም ቀን ይሁንልዎ።
ደረሰ ረታ
ነሐሴ 11/2012 አ.ም.

እራስን ተጠያቂ ማድረግ መለማመድ (ክፍል ሁለት)

 

ትልቁ ዋርካ ዛፍ በእድሜ ብዛት ወገባቸው ቢንቋቋም ተነስተው ከመቆም፣ ሥርአት ከማክበር፣ ለተተኪ ትውልድ አርአያ ከመሆን፣ የተረከቡትን ሥርአት ከማስረከብ ያገዳቸው አልነበረም።
ይህ ተግባር ሰወች ዘንድ ቢኖር አለም እንዴት ለሰወች ምቹ በሆነች ... አለም መሪ እንጂ አርአያ የለትም ለዚያውም በአግባቡ ከመሩ ማለት ነው።
እርሳቸው ተነስተው ሲቆሙ ሰብሳቢም፣ ተሰብሳቢም ሁሉም በክብር ከመቀመጫቸው ተነሳላቸው።
አይገባም ቁጭ በሉ፣
በእግዚአብሔር ተቀመጡ፤
ፈጣሪ ያክብራችሁ፣ የኔን እድሜ ይስጣችሁ፣ እኔ ያየሁትን እዩ፣ እኔ ያገኘሁትን ክብር አግኙ። በሉ ተቀመጡ ... አሉ ትልቁ የዋርካ ዛፍ እሳቸው ሲነሱ ተሰብሳቢው የተጠለለባት የዋርካ ዛፍ አንሳ ታየች።
በትህትና ዝቅ ብለው ሁሉንም እጅ ነሱ።
እርጋታቸው፣ ግርማ ሞገሳቸው፣ ከአንደበታቸው የሚወጣው ቃል ልብ ያርዳል ... እንደ ማእበል ያናውጻል። ግን ትልቁ ዛፍ የቁጣ ቃል ከአንደበታቸው አይወጣም። ንቀት የሚባል ነገር በጭራሽ አያውቁም። እውቀት እና ጥበብ እርሳቸው ዘንድ ናት። የሚናገሩት ቃል ከቅርንጫፍ አንስቶ ሥር ድረስ ዘልቆ ይገባል።
እንደ አዋቂ ሳይሆን እንዳላዋቂ ነው የሚናገሩት ነገር ግን አንዲት መሬት ጠብ የምትል ቃል ከአንደበታቸው አይወጣም።
አሉ እንጂ ጥራዝ ነጠቆች፣ ሰወች ... ከእውቀት ነጻ የሆኑ ደፋሮች ትህትና በልባቸው ሳይሆን በአጥራቸው ያልዞረ።
አልፎ አልፎ ከአንደበታቸው የሚወጣ ምርቃት ሊረግፍ የደረሰ የደረቀ ቅጠል እድሜ ያረዝማል፣ ልምላሜ ይሰጣል፣ ያበቡትን እንዲያፈሩ፣ ያፈሩትን ፍሬያቸው እንዲበዛ ያደርጋል።
አይራገሙም።
አይሳደቡም።
አይበሳጩም።
የእድሜያቸው መርዘም፣ የቁመታቸው ትልቀት፣ የቅጠላቸው ውበት፣ የቅርንጫፎቻቸው ብዛት ምሥጢሩ ይህ ሳይሆን አይቀርም።
አንድ ጊዜ ሁሉንም ታዳሚ ዛፎች ዘወር ብለው ቃኙዋቸው፤ "በእርግጥ አሉ ... " ትልቁ ዋርካ ዛፍ። በእርግጥ በእድሜ እበልጣችኋለሁ። ጓደኞቼ በእድሜ ብዛትም ይሁን አሁን እዚህ በሚጠቃቀሱትም ምክንያት አጠገቤ የሉም። በሕይወት የሉም። በቁም ግን የተወሰኑት አሉ። ልጆቼ በሕይወት መኖርና በቁም መኖር ይለያያል። እናንት በሕይወት ስላላችሁ ነው እዚህ የታደማችሁት በቁም ያሉት እዚህ ሊገኙ አልቻሉም። የተለያዩ ችግሮች ጠፍንገው ይዘዋቸዋልና።
አንድ አርሶ አደር ትዝ አለኝ ወቅቱ አከባቢው ረሃብ ያንዧበበት ነበር፤ ታድያ ሰውየው እጃቸው ላይ የሚላስ የሚቀመስ ባይኖራቸውም ማሳ ላይ የደረሰ ሰብል ነበራቸውና ሲደርስ ብድሬን እመልሳለሁ እያሉ እየተበደሩ ያንን ክፉ ቀን ያልፉት ነበር። ከእለታት አንድ ቀን ታድያ እኚህ አርሶ አደር ወደ እርሻ ስፍራቸው ሄደው ዘወር ዘወር እያሉ ይመለከቱት ጀመር። ታድያ የተበደሩትንና የበሉትን ማሳው ላይ ያለውን ሲመለከቱ የሚተርፋቸው ያለ አልመስል ሲላቸው። "ያለሽ መስሎሻል ተበልተሽ አልቀሻል" ብለው ወደቤታቸው ተመለሱ።
እስኪ ወደ ሰፈራችን፣ መንደራችን፣ አገራችን እንመልከት ማነው በቁም ያልተበላ? ፖለቲካ ያልበላው? ዘረኝነት ያልበለው? መንደርተኝነት ያልበላው? ... የቆምን መስሎናል ተበልተን፣ ተባልተን አልቀናል።
ሁላችን ባለእዳ ነን፣
የልጆቻችንን አገር የደም ምድር አድርገናል፣
ወደፊት መጓዝ ቢሳነን እንደሎጥ ሚስት ታሪክን ወደኋላ ማየት ላይ ተጠምደናል፤
ሽማግሌው ዋርካ እንዲህ አሉ፦ችግሮቹ ሰው ሰራሽ፣ እንስሳ ሰራሽ፣ ተፈጥሮ ሰራሽ፣ እጽዋትን የሚያጠቃ በሽታ ወዘተ... እያልን ልንዘረዝራቸው እንችል ይሆናል። ችግሩ ምክንያቱ አይደለም እዚህ አለመገኘታቸው፣ እኛ ለተቀመጥንበት አላማ ለአንዴና ለዘለዓለም መቀመጥ አለመቻላቸው ነው።
በሰውኛ ምን ይባላል መሰላችሁ " ይህንን እናንተ የምታዩትን፣ የምትሰሙትን ብዙዎች ሊያዩ ሊሰሙ ወደዱ አላዩም አልሰሙም። ይህንን ያዩ አይኖቻችሁ የሰሙ ጆሮዎቻችሁ ንኡዳን ክቡራን ናቸው" ይባላል።
ምን ለማለት ፈልጌ መሰላችሁ ምንም እንኳን ሰወች፣ ተፈጥሮ፣ እንስሳት የሚያደርሱብን በደል እጅግ ቢበረታም ዛሬ ይህን በደል ለማስቆም መሰባሰባችን መነጋገራችን ትልቅ ነገር ነው። ይህን ሽተው ያላዩ ይኽን የመሰለ እድል ያልገጠማቸው ቤተሰቦቻችን እጽዋት እንዲሁ እድሜያቸው ተቀጭቷል፤ ገሚሶችም ለሌሎች መኖር እነርሱ ትልቁን የመኖር ጉጉታቸውን መስዋእት አድርገዋል።
እኛ እድለኞች ነን። እድላችንን እንዳያመልጠን በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል። መደማመጥ መከባበር ይገባናል። አንዱ ሲናገር ሌላው አድማጭ መሆን አለበት። የሌላውን ሐሳብ እናክብር። አንዳችን ለአንዳችን እንደምናስፈልግ እንመን። በተናጠል መቆም ለአጥቂዎች ተጋላጭ ከመሆን የዘለለ ጥቅም እንደሌለው ልብ እንበል።
እስኪ ከሰወች እንማር፤ ሰወች ክቡር ሆነው ከአንድ አዳም ተፈጥረው ዛሬ በ21ኛው ክ/ዘመን እንደ ግመል ሽንት ወደኋላ ሄደው ዘር ይቆጥራሉ፣ ነጭ ጥቁር ይላሉ፣ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ፣ ወዘተ እያሉ ይከፋፈላሉ።
እስኪ ማን ይሙት ኢትዮጵያ ውስጥ ለዚያውም የሰው ዘር መገኛ በሆነች በሉሲ አገር እንዴት ይከፋፈላል?
በየእምነት ተቋሞቻቸው ስለ ሥነ ፍጥረት እየተማሩ የሰው ልጅ ከአንድ አዳም እንደተገኘ እየተናገሩ መከፋፈልን ከወዴት አመጡት? ከመከፋፈልስ ምን አተረፉ?
ወገኖቼ አሉ እኝህ ታላቅ ዋርካ፦
ምንም እንኳን የረባ ከእናንተ የተሻለ ሐሳብ ባይኖረኝና እድሜ ቢገፋ አሁንም ከእናንተ እኩል የመኖር ጉጉት እንዳለኝ አውቃለሁ።በአጭሩ መቀጨት አልፈልግም። ዝምታው በረጅም ሳቅ ተሰበረ። በጭበጨባ እና በሳቅ አጀቧቸው።
ተናጋሪው ዋርካ እውነቴን ነው ምን ያስቃችኋል? መኖር እኮ የሚጣፍጠው ጣእሙ የሚገባችሁ ስትኖሩ ነው። እኔ ረጅም እድሜ ስለኖርኩ በቃኝ ከማለት ይልቅ የመኖር ትርጉም ስለገባኝ ለመኖር እጓጓለሁ።
ሌሎች እኛን የማጥፋት እና እኛን በአጭሩ የመቅጨት ምክንያት ከመኖር ጉጉታቸው የመነጨኮ ነው ከክፋት አይደለም። ከእኛስ መካከል አሉ አይደል ለመኖር ሲሉ የነፍሳትን እድሜ የመኖር ተስፋ በአጭሩ የሚቀጩ ... የነርሱን ከርሱ ለይታችሁ አትዩት፤ ይልቅስ ... የዛፎች ጉርምርምታ ሐሳባቸውን ገታባቸው። እርሷቸውም ከመናገር ተቆጠቡ ... የአነጋገራቸው አድናቂ፣ የምልካተቸው ተማራኪ ንግግራቸውን እንዳናጠባቸው ትልቁ ዋርካ አወቁ።
አመሰግናለሁ።
አመሰግናለሁ።
ይበቃል፤ ይበቃል ጓዶች።
" ... ይልቅስ ለችግሮች መፍትሔ ለመፈለግ ወደ ውጭ ከማየት አስቀድመን ወደ ውስጥ እናተኩር፤" ብለው ንግግራቸውን ገታ አደረጉት።
አዳማጭን ገረመሙት ....
ሰብሳቢዎችንም በአይናቸው ቃኟቸው...
ሁሉም እየተከታተላቸው ነው ...
ሐሳባቸው ጭንጫ መሬት ላይ እንዳልወደቀ ልብ አሉ።
" ... ልብ ብላችሁ አዳምጡኝ፤ ሐሳቤን እዚህ ጋር ስለሆነ ልብ ብላችሁ አዳምጡ። አልደግመውም።
ጸጥታ ሰፈነ ... አድማጭ የተናጋሪውን የመፍትሔ ሐሳብ ለመስማት ጓጓ፤
ተናጋሪው ዋርካ ዛፍ መልእክታቸውን ለማስተላለፍ ጉሮሮቸውን ጠራረጉ። አሁንም ደግሜ እላለሁ። ልብ ብላችሁ አድምጡኝ፥ ወደ ራሳችን እንመልከት።
ለክፍል ሶስት ይቆየን። የኚህን ትልቅ ዋርካ የመፍትሔ ሐሳብ እንቃኛለን።
ይከታተሉን።
ሐሳብ አስተያየትዎን ከመስጠት አይቆጠቡ።
መልካም ቀን ይሁንልዎ።
ደረሰ ረታ
ነሐሴ 10/2012 አ.ም.

እራስን ተጠያቂ ማድረግ መለማመድ (ክፍል አንድ)

 

እራስን ተጠያቂ ማድረግ መለማመድ
ክፍል አንድ
ነሐሴ 10/2012 አ.ም
ነገሩ እንዲህ ነው፤ ዛፎች ስለሆነባቸው፣ እየሆነባቸው ስላለ፣ ሊሆንባቸው ስላለው ጉዳይ ለመምከር ስብሰባ ተቀመጡ።
አጀንዳዎቻቸውን አንድ በአንድ ነቅሰው አውጥተው ከተወያዩ እና በብዙ ጉዳይ መግባባት ላይ ከደረሱ በኋላ በአንደኛው አብይ ጉዳይ ላይ መግባባት ባለመደረሱ ምክንያት ስብሰባው አጀንዳውን በይደር አሳድሮ ተስማምቶ ተበተነ።
በበነጋታው በተለመደው ሰአት፣ በተለመደው ቦታ፣ ሁሌም በስብሰባው ላይ የሌሎች ዛፎች ጥቃት የኛም ጥቃት ነው የነርሱ ጉዳት እኛንም ያገባናል የሚሉ ገንቢ ሐሳብ ለመስጠት ውይይቱን በሐሳባቸው ለማዳበር፣ የተጣመመውን ለማቃናት፣ የጎበጠውን ለማቅናት፣ የጎደለውን ለመሙላት፣ ወዘተ የሚገኙ የተለመዱ ዛፎች በመሰብሰቢያው ዋርካ ጥላ ስር ተሰድረዋል።
ሰብሳቢውና ምክትል ሰብሳቢው በሰአታቸው ቢገኙም ጸሐፊው የክብር መዝገቡን ይዞ በሰአቱ ባለመገኘቱ የስብሰባው መጀመሪያ ሰአት ወደፊት ገፍቷል።
በዚህም የተነሳ ብዙዎች ዛፎች ማጉረምረም ጀምረዋል። ከየቦታው የግል ወሬ፣ ሐሜት፣ በትናንትናው እለት ፋይላቸው የተዘጉትን ጉዳዮች በተናጠል እያነሱ ክርክር ጦፏል፣ አስተያየት ሰጪ ዛፎችን ትችት እና ድጋፍ በየቦታው ይወራ ጀመር፣ ገሚሱ ስብሰባው ላይ መገኘቱን እየኮነነ ያልተገኙትን ዛፎች ማድነቅ ተያይዞታል፣ ...
ከመድርኩ ላይ ተገማሽረው የተቀመጡት ምክትል ሰብሳቢ ጠና ያሉ ዛፍ የጊዜውን መሄድ ጀንበሯን በመመልከት ወደ ዋናው ሰብሳቢ ጆሮ ጠጋ በማለት አንሾካሸኩ ዋና ሰብሳቢው ዛፍም ሰአቱ በመሄዱ እና በጸሐፊው ማርፈድ መጨነቃቸው ከፊታቸው ላይ ይነበባል። ከአንደበታቸው አውጥተው አይናገሩት እንጂ ብስጭትም ይታይባቸዋል። ምላሻቸውን ጭንቅላታቸውን በመነቅነቅ ገለጡላቸው።
ተሰብሳቢው ጫጫታው የንብ መንጋ መስሏል ድምጹ በአራቱም አቅጣጫ ይተማል። አንዳንዶችም አርፋጆች እየተንጠባጠቡ ያልተጀመረውን ስብሰባ ምንም እንዳልተፈጠረ ማርፈዳቸው እንኳን ሳይታወቃቸው ይቀላቀሉ ጀመር።
የስብሰባው አጀንዳ ይለያይ እንጂ የስብሰባው ይዘት እና የተሰብሳቢ ግዴለሾች መብዛት ከሰው ልጅ ስብሰባ ጋር ብዙ አንድ የሚያደርገው ነገር አለ።
ጸሐፊው እየተንጎማለሉ በተሰብሳቢው መካከል አአልፈው መድረኩ ላይ ተሰየሙ፤ መዝገባቸውን ገለጥ ገለጥ አደረጉ፣ ከደረት ኪሳቸው የንባብ መነጥራቸውን አወጡ ... "ጸጥታ" አሉ። ፍየል ከመድረሷ ... አሉ አበው። የሰማቸው አልነበረም። አሁንም "ጸጥታ" አሉ ... ድምጹ በረታ። ድምጻቸውን ለማስተካከል በሚመስል ሁኔታ ጉሮሯቸውን ጠራረጉ። ይኸን ጊዜ የድምጡ ሃያልነት ጋብ እያለ መጣ።
ሰብሳቢው ዛፍ የምንተፍረታቸውን ተሰብሳቢውን ይቅርታ ጠየቁ።
የተሰብሳቢው ዛፍ ቁጣ ጨመረ፣ ማጉረምረሙ በረታ፣ ተቃውሞቸውን በጭብጨባም በፉጨትም ገለጡ ... ተቃውሞው ጸሐፊው አርፍደው መጥተው ይቅርታ መጠየቅ ሲገባቸው እንዴት ከኛ እኩል የተገኙት ሰብሳቢ ይቅርታ ይጠይቃሉ አይነት እንድምታ አለው።
ስብሰባው ተጀመረ።
ሐሳቦች መንሸራሸር ጀመሩ።
ጉርምርምታ አልፎ አልፎ እንዳለ ነው፤ ከሚሰጠው አስተያየት በይዘትም በጥራትም ጉርምርምታው ውስጥ ይንጸባረቅ ነበር። ነገር ግን እጃቸውን አውጥተው የመናገር መብታቸውን ተጠቅመው አይናገሩም፣ አስተያየታቸውን አይሰጡም፣ ወይ ተቋውሟቸውን አይገልጡም። ዛፎችንም ከሰው የሚያመሳስላቸው ጸባይ ያለ ይመስላል።
ጉርምርምታው ይኑር እንጂ ስብሰባው ቀጥሏል አስተያየቶችም ከየቦታው ይሰጣሉ።
አለመግባባቶች በረቱ፤
ደርበብ ያሉት ምክትል ሰብሳቢ ተናጋሪውን ዛፍ እና የሚያጉረመርሙትን በመሃል እያቋረጡ፥ ይቅርታ ዛፎች ሳቋርጣችሁ እጅግ እያፈርኩ ነው። ጭርንጫፎቻቸውን በሐዘኔታ እየነቀነቁ "ምን ነካን?
ኧረ ተው ሰሚ ምን ይለናል?
ተመልካችስ ቢሆን?
ለአገር ምድሩ ለሰው ቢባል ለእንስሳ ስንት አይነት መድሃኒት እየሆንን እንዴት ለራሳችን ጊዜ አንዲት መፍትሔ እንጣ ... ዛፎች? ኧረ ተው ኧረ እግዜሩስ ምን ይላል? ከምድር በታች ያሉትስ አባቶቻችን አያዝኑብንም?" አሉ እጅግ በመከፋት።
ስብሰባው ቀጠለ፤
ስርአት አልበኛው እና ቆንጠር ቆንጠር የሚሉት አጭሩ ጸሐፊ ቆጣ ብለው "ስርአት ይዛችሁ ስብሰባውን ትከታተሉ እንደሁ ተከታተሉ አንዳንድ የምትረብሹ ዛፎችም አደብ ብትገዙ ይሻላል። አይ የምትሉ ከሆነ ደግሞ በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት ቅጣቱን መጣል አቅቶን አይደለም ትዕግስታችን በርትቶ እንጂ ..."
የተሰብሳቢው ጫጫታ የጸሐፊውን ንግግር አቋረጣቸው፤ ጸሐፊው አርፍደው ከመምጣታቸው ይቅርታ አለመጠየቃቸው ከዚያም አልፎ ተርፎ ሥርአት ለማስያዝ ስለቅጣት ማንሳታቸው ዛፎችን አስቆጣቸው።
ሰብሳቢው ራሳቸውን ታመሙ በሰላም ተጀምሮ በሰላም ይጠናቀቃል ብለው ያሰቡት ስብሰባ በመዘግየት ተጀምሮ በጭቅጭቅ እና በንትርክ አጀንዳው ላይ ረብ ያለው ሐሳብ ሳይነሳ ሰአቱ ነጎደ።
ለግላጋ ቁመና ያላቸው ዛፍ ከመቀመጫቸው ብድግ አሉ እርሳቸው ከመቀመጫቸው ብድግ ሲሉ የመሰብሰቢያው ዋርካ ቅጠሎች ረገፉ፤ ጎንበስ ብለው ተሰብሳቢውን ይቅርታ ሲጠይቁ ጸጥታ ሰፈነ፣ ሠላም ወረደ በጫጫታው ምክንያት እየጨመረ የመጣ ሙቀት ረገብ አለ።
ስብሰባው በተለመደው ግርማ ሞገሱ ተጀመረ ስርአት ነገሰ።
ተናጋሪ ሲናገር አድማጭ ጸጥ አለ፤
አስተያየቱን ሲጨርስ ደጋፊ ሲያጨበጭብ ተቃዋሚ አልያም ሌላ አስተያየት ያለው እጅ በማውጣት ሐሳቡን መሥጠት ቀጠለ።
ይሁን እንጂ ምንም የረባ፣ ለመፍትሔ የቀረበ አስተያየት እስከ አሁን አልተሰነዘረም።
ሁሉም አስተያየቶች ከመፍትሔው ይልቅ ችግሩ ላይ ያጠነጠኑ ውይይቶች ነበሩ።
እርግጠኛ ሆኖ ከሚናገረው ይልቅ ይመስለኛል እያለ የሚናገረው አስተያየት በቁጥር ይበዛ ነበር።
ጊዜው እየገፋ ተሰብሳቢውም እየተሰላቸ ሰብሳቢዎችም ስብሰባው በይደር እንዳይቀጥል በስጋት እየተዋጡ ተሰብሳቢዎችም ጉዳያቸውን ከመጤፍ ሳይቆጥሩ ስብሰባውን እየተው ሹልክ እያሉ መውጣት ጀምረዋል።
ይህ ድርጊት ደግሞ የሰብሳቢዎችን እና የቀሩትን ተሰብሳቢ ቀልብ እየሰረቀው መጣ።
አስተያየት ስጪዎች ሐሳብ ከመጨረሳቸው የተነሳ ይሁን ምክንያቱ በውል ባልታወቀ ምክንያት እየተነሱ እገሌ እንዳለው እያሉ አስተያየት በመሥጠት ተሰብሳቢውን አሰለቹት፦
"አካሄድ" አሉ ጸሐፊው "እባካችሁ ጊዜያችሁን ለመጠቀም ሌሎች ያነሱትን ሐሳብ ስለያዝን አትድገሙት አዲስ ሐሳብ ከሌላችሁ ስብሰባውን እንጠቅልለው" አሉ። ሲመጡ አርፍደው ለመሄድ ፈጣን የሆኑ ኮሚቴ እግዜር ይሰውር።
ሰብሳቢው ስብሰባውን እየመሩ እንደሆነ ለማጠየቅ በተረጋጋ መንፈስ "ግድየለም ይምሽ ይኸንን ጉዳይ ሳንቋጭ ለተበዳዮች መፍትሔ ሳናመጣ፣ እንባቸውን ሳናብስ፣ እልቂታቸውን ማቆም ቢያቅተን መቀነስ የሚያስችል መፍትሔ ሳናመጣ ጉባኤው አይፈታም" አሉ።
አስተዋይ ይኑር።
በእድሜ ጠና ያሉት ዋርካ ወገባቸው እየተንቋቋ ከመቀመጫቸው ብድግ እንደማለት አሉ፥
ሁሉም ዛፍ በአንድ ድምጽ ይቀመጡ አይነሱ ... በአባቶቻችን ተቀምጠው ይናገሩ ... አሏቸው።
ግድየለም እግዜሩም እናንተም እንድትሱሙኝ ቁሜ ልናገር ብለው ተነሱ።
በክፍል ሁለት የቀረውን እንድንቀጥል ይቆየን።
የቴሌግራም አድራሻዬ ይከታተሉኝ።
ለሎሎች ይደርሳቸው ዘንድ ማጋራትን አይርሱ።
ሐሳብ አስተያየትዎን ለመስጠት አይቆጠቡ።
ነሐሴ 10/2012 አ.ም
ደረሰ ረታ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...