ማክሰኞ 16 ኦክቶበር 2012

የጉዞ ማስታወሻ


     የጉዞ ማስታወሻ

እንደባቡር ፋርጎ ሳይነጣጠሉ እደተቀጣጠሉ መጓዝ ግድ ይላል ትልቁ ትንሹን ትንሹ ትልቁን በስተጀርባው እያስከተለ መጓዝ ግድ ይላል የቸኮለከሰንሰለተማው የጎዞ ውህደት ውስጥ ይነጠላል ደርቦ ማለፍ ለማለፍ መንሰፍሰፍ መሽሎኪያ ቀዳዳ መፈለግ የሾፌሮች ስራ ነው ተሳፋሪመጣደፉ መሳቀቅ መፀለይ የየሰዓቱ ሥራቸው ነው 12፡30 ከአ.አ መነሐሪያ የወጣው 2ኛ ደጃ አውቶብስ 2፡10 ደብረ ዘይት መንገድደረሰን መንጋቱን ማመለከቻውና የቁርስ ሰዓት ብስራቱን ለማሰማት ሁለት የመኪናው ረዳቶች ከፊት ከኋላ ፌስታለቸውን ማንኮሻኮሽ ጀመሩአፍታም ሳይቆይ አንባሻዎችን ለተሳፋሪ ማደል ጀመሩ፡፡ ቁርስ መሆኑ ነው ቁርሱን ምሳውና እና እራቱን የሰነቀው መኪና በአሽከርካሪው አማካይነት አስፋልቱን ለሁለት እየሰነጠቀ ይፈተለካል ወደ ሐረር የመቻቻልና የትብብር ከተማ፡፡
     የደብረ ዘይት (ቢሾፍቱን) እንደ ወጡ ትላልቅ ድንኳን የመሰሉ ቤቶችን ማየት ሲጀምሩ የኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆንዎን መዘንጋት የለብዎትም በአንጻሩም ያቆጠቆጡ ሰብሎችና ጥቋቁር መሬቶች የአይንዎ ማረፊያ ናቸው ጆሮዎትን ጣል ካደረጉ ፌስታል የሚል ሰው ድምጽ ይሰማሉ ሊያባላሹም ይችላሉና፡፡ ሽንቱ የመጣበት ሰው እንዲሁ ለረዳቱ ያሳውቃል ረዳቱ ለሹፌር መኪና ይቆማል ተንፍሰው ይመለሳሉ አንዳንድ ቤቱ የደረሰ ይመስለውና ወደ መኪናው በቶሎ ባለመመለስ ጉዞውን ያዘገያል የተለመነው የመኪና ረዳት እባካችሁ ግቡ በማለት ተሳፋሪውን ያስገባል፡፡ ግራ ቀኙን እየቃኙ ተፈጥሮን እያደነቁ ይሄዳሉ 2፡35 ሞጆ ከእንቅልፍ ነቅታ ተግታ ህዝቧን ለሥራ እያሰማራች ነው እኛም ወደ ጉዞአችን ሞጆ ሜዳ ላይ ደረቱን ያሰጣው ደረቅ ወደብና ተርሚናል መንጋቱ ስለሆነ ፀጥረጭ ብሏል፡፡
     በየመንገዱ ግራ ቀኝ ቅጠሎቻው ረግፈው ቅርንጫፎቻቸው የቀሩ የግራር ዛፎች የክረምቱን የምስራች ድምጽ ሰምተው ማቆጥቆጥ አንገታቸውን ቀና ማድረግ ጀምረዋል፡፡
     ከንፋስ የኤሌክትሪክ ኃይልን የሚሰጡ ተርባይን ሲመለከቱ የአዳማ መዳረሻ ምልክት እንጂ ሌላ ስራ ያለው አይመስልም እንደየዋህ ፀባዩን አሳምሮ ቆሞ ሲመለከቱት እርሱን እየተመለከቱ ሲጓዙ ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅን ያገኙታል፡፡
     የአዳማ ውበት አባ ገዳ ህንጻ አ.አ ሳትነቃ አመልጣችው የመጣችው ተጓዦች እንኳን ደህና መጣችሁ ይህ ሥፍራ የስምጥ ሸለቆዋ እንቁ የአዳማ ከተማ ነው ይላችኋል፡፡ አሁን ከነጋ 3፡00 ሠዓት ሆኗል፡፡
     ይቺን ሞቃታማ ከተማ የኦሮሚያ ክልል ንግሥት እንደ ዋዛ የክረምት ጎም እንዳጠላበት እንደከረፈች ፈገግታዋን ሳናይ ጥለናት እብስ አልን እኛም ቅር ብሎን እርሷም ከአቅሜ በላይ ነው ጊዜው ክረምት ነው እያለች ህፃን ልጅ ከእናቱ እንዲነጠል ተነጣጠልን፡፡ ጊዜው እርሷ ዝናብን እያነባች እኛም እያዘንን እርስ በርስ ተያይዞ የቆመውን ተራራማ ምድር እየሰነጠቅን በመጓዝ ወለንጭቲን ያለፍነው ጠዋት 3፡30 ሰዓት ላይ ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን ደፍሮ እንደሰንሰለት የተያያዙትን ተራሮች ሊለያያቸው የሚችል የለም፡፡ ለእድሜ ዘመናቸው ላይለያዩ በምድር ተማምለው ፍቅር መስርተዋልና አሁንም አብረው ናቸው፡፡ ወደ ፊትም አይለያዩም የፈጠራቸው ደግሞ እሰኪመጣ በዚህ መድር ላይ ዘር ሊዘራ ሲወጣ የግራር ዛፍ ብቻ የዘራ ይመስላል በተንጣለለው አስፋልት ግራና ቀኝ ተበትነው ሲመለከታቸው ከአብ ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ አንጥረኛው የቱ ነው እስኪሉ የኢትዮጵያ መልክዐ ምድር ማድነቅ የተለመደ ቢሆንም እኛም የአዋሽ አዋሳኝ የሆኑትን ሰንሰለታማ ኮረብቶች አሰፋፈር እያደነቅን ድፍን 4፡00 ሰዓት ሆኗል፡፡
     ግራና ቀኛችንን አልፎ አልፎ እንደ ግራር ዛፍ አጃበውን የሚጓጓዙት የከፍተኛ ኃይል የኤሌክትሪክ ተሸካሚ ማማዎችን ለምስራቅ የአገራችን ክፍል ብርሃን ላመዳፈም እየገሰገሱ ይመስላሉ፡፡
     አልፎ አልፎ ጣል ጣል ብለው የሚያገኛቸው ጎጆ ቤቶች እንኳንስ የእህል ማጠራቀሚያ ጎተራ ሥንቅ መቋጠሪያ አገልግሎት ከቤት ያላቸው አይመስሉም፡፡ በየቦታው ስፍራው በረሃውን ከማድመቅ ውጭ ከአዋሽ ሃይቅ ደረቱን ስትሮ ሲመለከቱት ለጥፋት እንጂ ለልማት አለመሆኑን ሲያዩ እጅግ ያዝናሉ ዛሬም ዓባይን በደፈርንበት ዘመን አልደፈር እጄን አልሰጥ ብሎ ይልቅስ ነዋሪውን ዕንባ እያራጨ ከማፈርቀል ባሻገር አዋጅ ማን ያውቃል አንድ ቀን እንደ ባንኩ የበረሃው የልምላሜ የብልጽግና ፈር ቀያሽ ይሆንና ታሪክ ይቀየር ነገር ይገለበጥና የተሰደደው የተፈናቀለው ሁሉ መልሶ ሰፋሪ ይሆናል፡፡ ማን ያውቃል? ማንም
     አውራ ጎዳናዎቹ መኪናዎቹ ሰው ብቻ አይደለም ወደ ማቅረብም አ.አ መኪናውም መኪና ጭኖ መኪና ነዳጅ ጭኖ ላይ ታች ሲል ይታዘባሉ የአ.አ ጎዳናዎች የመኪና ማቆሚያ ሥፍራዎች በመኪና ተጨናንቀው የገባው ሥፍራ ሳያገኝ ዛሬም መኪና ተጭኖ ይሄዱለታል፡፡ የሚገርመው ግን ያ ሁሉ መኪና አ.አበባን አጨናንቆ የዚያኑ ያህል በትራንስፖርት እጥረት መሰቃየቱን ሥናይ ግራ ያጋባል፡፡ ሲባል እንደሰማሁት ጁቡቲያውያን ወደ ኢትዮጵያ የሚገባውን የመኪና ብዛት ተመልክተው በመገረም ኢትዮጵያውያን ምግብ መብላት ትተው መኪና መብላት ጀምረዋል ወይ? አሉ የተባለውን በድጋሚ ይህ መንገድ እንደገና አስታወሰኝ፡፡
     አሁንም አዋሽን በስተቀኝ እያየን እንጓዛለን 4፡20 ሠዓት ሆኗል፡፡ በስተግራ የሰንሰለታማዋን ተራራ አብይ ቅርንጫፍ እየታከክን በአዋሽ ምድር ላይ ከኤሌክትሪክ ምሶሶ በስተቀር ለመሃላም ቢሆን ሌላ ዛፍ አይመለከቱም የአዋሽን ሙቀትና ከተማ ‹‹እንግዲህ ቻው ቻው›› በማለት ጥቂት ደቂቃዎች ይቀሩታል፡፡
     የአዋሽን ሐይቅ እየታከለ የሚሄደው አውራ ጎዳና በመሰራት ላይ ስለሆነ ተለዋጩን መንገድ መጠቀም የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ የግድ ነው፡፡ ምንም ክረምት ቢሆን ቦታው አዋሽ ነውና የሰውነት ሙቀትም መጨመር ግዜ ይለዋል፡-
     አሁን አዋሽን በሩቅ ማየት የለም አዋሽ በርሶ ግራ እና ቀኝ እርሶ ደግሞ አዋሽን ለሁለት ከፍሎ መጓዝ (ሰንጥቆ) መጓዝ ግድ ይላል፡፡ አዋሽን ለሁለት ተባብረው የሰነጠቁትን የመኪና መንገድና የድሮ የባቡር ሐዲድ(የግመል ሃዲድ) ከሐይቁ ጋር ውሃ ልካቸውን ሲመለከቱ ዕፁብ ድንቅ እያሉ ሐይቁን ግድብ ያስገዛ ፈጣሪ እያመሰገነ መተሐራ ከመግባት በስተቀር አማራጭ የሉትም፤ሀይቁ ቢያገሳ፣ አሻፈረኝ እምቢኝ ቢል በአንበሳው ሐይቅ ከመዋጥ የዘለለ ዕጣ ፈንታ የሉትምና፡፡ መተሐራ 4፡40 ሠዓት አዲሱ ነገር የመተሐራ ትራፊኮች መግቢያና መውጫ ላይ ሁለት ጊዜ ያስቆማሉ አለመቀናጀታቸው ሲያሻቸው የበረሃ አበል ይቀበላሉ ተብለው ይታማሉ፡፡ ትርፍ ቢኖረው ባይኖረውም ቢሳሳቱም ባይሳሳቱም ተሳፋሪው መኪናው ቆሞ ትራፊክ ሲገባ ሆዳም፣ ከርሳም፣ የሚሉ ድምጾች ይሰማሉ እኛም እንሰማለን ትራፊኩም ይሰማል፡፡
     መተሐራ ካለፉ ሰንሰለታማው ተራራ እየተበጣጠሰ በስተቀኝ ያለው እየራቀ ሥፍራውን ለተንጣለለ ሜዳ ይለቃል፡፡ ቁጥቋጦውና ግራሩ ግን የት ድረስ እንደሚሄድ አይታወቅም ይከተሎታል፡፡ ከ12ቱ ሐዋርያት ቅ/ዮሐንስ ብቻ እስከ መስቀሉ እንደ ዘለቀ ከመሐል አገር የተነሱት ዕፅዋቶች ከግራር በስተቅ በመንገድ የሚከተልዎት የለም ከከተማ ሲወጡ ይክድዋታል፡፡ ግራር ሆይ ብፅዕ ነህ ባህር ዛፍ ከከተማ ስርቅ ትከዳኛለህ፡፡
     6፡10 ሠዓት አዋሽ 7ኪሎ 3ኛው ትራፊክ 20 (ሃያ ብር) ተቀበለ፡፡ አዋሽ 7ኪሎ ሙቀቷ ከመጨመር በቀር ልማት አይታይበትም እንዲያውም በድንጋይ ካብ የታጠሩ ባዶ ስፍራዎች ይበዙበታል፡፡ ለመሃላ ከተማዋን ወጣ ብሎ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ጋን የመሰለ ነገር የአይን ማረፊያ አለ፡፡
     ከጁቡቲ አዲስ አበባ የሚያስመጣው የባቡር ሃዲድ  ፍተሻውን ሳይደርስ ከምድር ከፍ ያለው ድልድይ ዛሬ የጦጣ መሸጋገሪያ ኖኗል፡፡ አዋሽ አርባን እያለፉ ሲጓዙ ከተማን የሚያስታውስዎት ሁሉት ህንጻዎች ከመንገድ በስተቀኝ ቆመው ያገኛሉ፡፡
     አስቀድመው መተሐራ ላይ የከዱትና የተለዩን ስንሰለታማ ተራራዎች በስተቀኙን እንደተማረከ የጠላት ወታደር እጃቸውን ወደ ላይ ይዘረጋሉ ምህረት ጥያቃ እንከተላችሁ፣ አብረን እንሂድ በማለት። በስተ ግራ ግን ለጥ ያለው ሜዳ ላይ ከበረሃው ባቡር (ከግመል) በስተቀር ሰንሰለተማው ተራራ ላይታይ ምሏል መሰል የለም፡፡ ጊዜ ታክሲ አይደለም ቆም አይጠብቅም 5፡25 ሠዓት ለመሐላ በረሃ ውስጥ ያገኘናቸው ምሶሶዎች የበረሃውን ግለት አልቻሉም መሰል በየቦታው ወድቀዋል በቦታቸው የአርማታ ምሶሶ ቆሟል ከወደቀበት ቀና ሳያደርገው፡፡
     ቦርዳዴን ወደ ቀኝ በመተው 5፡35 ሰዓት መሆኑን ስናውቅ ወደ አሰበ ተፈሪ አመራን፡፡ 316 ኪ.ሜ መጓዝ ግድ ይላል ከተራራ ግርጌ የምትገኘዋን አሰበ ተፈሪ ለማግኘት ምሳ ሠዓት ደመቅ ሸብረቅ ሽርጉድ ትላለች እንግዶቿን ለማስተናገድ ‹‹ጥሩነሽ ምግብ ቤት›› አንዱ ነው፡፡ ‹‹እንኳን ደህና መጣችሁ›› ብለው ይቀበላችኋል ምሳዎትን ይበላሉ፡ ቡና በጀበና እዚያው ይጠጣሉ፡ አዲስ አበባ ላይ ጉሊት ሽንኩርት፣ ጎመን፣ በቆሎ ሲሸጥ እዚያው ሆቴሎች በር ላይ ጫት እንደ ጎመን ይሸጣል፡፡ ፡ምሳ ሰዓት ተጠናቀቀ፡ አሰበ ተፈሪ ደህና ሰንብች 7፡20 ሠዓት አሰበን ሻገር ካሉ ለምለሚቷን ምስራቃዊ ክፍል እየጎበኙ ሞቀታማውን በተመጣጠነ አየር ያጣጥሙታል፡፡
     ኦሮሚያ ክልል ቱሉ አረዳ ላይ ሌላ ትራፊክ 4ኛ 20 ብር ወጪ ተደርጓል ኬላ መሻገሪያ፡፡ ደበሶ 8፡00 ሠዓት ።የትራፊኮችን ጉዳይ መንግስትም ህብረተሰብም አንድ ሊላቸዉ ይገባል፡ህዝብን ሊያገለግሉ እንጂ ሊበዘብዙ አይደለምና አደራ የተጣለባቸዉ። ለመሆኑ 300 እና 400 ኪ.ሜ. ከአዲስ አበባ ሳንርቅ እንዴት እንዲህ አይነት ተግባር ሲፈፀም መንግስት ዝም ይላል? ደሞዝ አይከፈላቸዉ ይሆን?
     …ሜዳው ጨርሰን ዳገት ወተን ወደ ሂረና ለመግባት ደግሞ ቁልቁለት መውረድ ግድ ይላል፡፡ (ጠሎ ወረዳ) ከአሰበ ተፈሪ ወጥተን የሐረማያ ዮኒቨርስቲን እንዳለፉ ከአራት ሠዓታት በላይ የሚፈጀውን ዳገታማ ስፍራ ዓይንዎትን እስኪደክምዎት ግራ ቀኙን መቃኘት ነፍስ ይማርካል መቸስ የዚህ መንገድ ልምላሜ ዋነኛው ምሥጢር አልፎ አልፎ የሚታየው የበቆሎ ተክልና ከጫት ተክል ያለፈ አይደለም፡፡
     ሂረና ፣ ገለምሶ፣ ካራሚሌ፣ ቆቦ፣ ሜታወረዳን እንዳጠናቀቅን ቁልቢ 10፡25 ሠዓት ደረስን ሙስሊሙም ክርስቲያኑም ቁልቢ ከተማ አፋፍ ላይ የሚገኝን ተአምረኛውን የቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን መኪናው ከፍና ዝቅታ ያሳልመዋል ከሩቅ ያለ የሚመስለው ቤተክርስቲያን እንደ እኔ ለቦታው እንግዳ ከሆኑ ገና ለገና እደርስበታለሁ ሲሉ ተራራውን በስተግራ እየታከኩ ያልፉት ጳንገጐ ይገባሉ፡፡

     ከቁልቢ (ቁልቢ በኦሮምኛ ሽንኩርት ማለት ነው) የአንድ ሰዓት መንገድ ከተጓዙ በኋላ የበረሃዋን ንግስት ድሬን በስተግራ በመተው ለሃያ ደቂቃ ከተጓዙ በኋላ የሐሮማያ ዩኒቨርስቲ ዋና ካምፓስ መቀመጫ የሆነውን አለማያን ያገኟታል ጉዞአችን በህዝብ ትራንስፖርት እንደመሆኑ መጠንና ወቅቱም ሐምሌ ስለነበር የሐሮማያ የሐረር የጅጅጋ ዮኒቨርስቲ ተማሪዎች ነበሩ የተጓዡች ቁጥርን አብላጫ የያዘውና አለማያ ላይ ለ30 ደቂቃ ያህል ቆመናል የጫኑትን ሻንጣዎች ቁሳቁሶች እስኪያወርዱ፡፡
     ከአሥር እና አስራ አምስት ደቂቃ ጉዞ በኋላ ምስራቅ ውስጥ በትክክል መድረስዎትን የምታበስራዋ አንዳንዴም የአረቡ ክፍለ ዓለም ውስጥ ነው ወይስ ቻይና ነው ያለሁት ብለው እስኪጠረጠሩ ድረስ ሰዎች በሥራ ላይ የሚያዩበትን ከተማ አወዳይን ያገኛሉ፡ ጊዜው ባይመሽና 12፡00 ሠዓት ባይሆን (ይቅርታ አወዳይ ላይ ጀንበር አትጠልቅም፡ ድካም ዝር አይልም፡ የሚዘጉ በሮች የሉም፡ ሁሉም ቀን ከሌሊት ለሥራ ይፋጠናል፡ አረንጓዴ ወርቃቸውን ወደተለያየ አቅጣጫ ለመላክ ይፋጠናሉ እንጂ፣) ጎራ ብዬ ባያት ቁጭ ብዬ ብታደማት ደስ ባለኝ ነበር እኔም ጎራ ሳልልባት እናንተንም ሳላስቃኝ ማለፌ እኔንም ቅር አሰኝቶኛል፡፡
12፡20 ሐረር የአምስት በሮች እመቤት ምሥራቃዊና ጥንታዊት ከተማ የብሔር ብሔረሰቦች መገኛ ሐረር፤
ሐረር ሲገቡ በየትኛውም አቅጣጫ ሲመጡ አምስቱም በሮች እንኳን ደህና መጡ እያሉ አቀባበል ያደርጉልዎታል፡፡ ሸዋ በር፣ ፈላና በር፣ ዱክ በር፣ኤረር በርና ሰንጋ በር ምሽት ላይ ቀዝቃዛ የምትለዋ የሐረር ከተማ ምንም አስቸጋሪ ነገር አይታይባትም ወደፈለጉት ለመጓዝ በጃጆች ሁሌ ንቁ ሁሌም ዝግጁዎች ናቸው፡፡ ታክሲዎችም እንዲሁ የምሥራቁ እመቤት ሐረር ሙስሊሙም ክርስቲያኑም በጋራ የሚኖሩበት ፍቅር የሆነች ከተማ ብትሆንም ጊዜ ያመጣውን ጊዜ እስኪፈታው እምነትን ሰበብ እያደረጉ የሚመጡ በሽታዎቸ (ግማቶች) አይታጡም በቤተክርስቲያን ላይ ድንጋይ መወርወር፣ አማራው ላይ መዛት፣ ጊሌ ይዞ ሰላማዊ ሰልፍ መውጣት፣ ፓሊስ ሳይቀር ከእምነት የፀዳ ተቋማዊ ግዴታን አለመወጣትና ለእምነት እያደሉ ፀጥታን ያለማስከበር መጠነኛ ድክመቶች አሉባልታ ይሁን እንጂ የሐረርን ፀጥታ ለማስከበረ መንግስት አይተኛም አያንቀላፋም ፈጣን እርምጃ ከድሬደዋ በሚመጡ ፌዴራል ፖሊስ ሁከታውን ብጥብጡን ዛቻና ማስፈራራቱን ድንጋይ ውርወራውን ፀጥ ረጭ ያደርገዋል፡፤

     አዲስ አበባ ሆነው በመገናኛ ብዙሐን ሐረር ሲነሳ ለማዳ ጅቦች፣ የጃጎል ግንብ፣ አምስቱ የሀረር በሮች፣ የሐረር ሰንጋ…..ወዘተ የሚዘነጉና የማይጎበኙ አይደሉም። ፈጣሪ ዕድሉን ከሰጠን ጊዜው ካደረሰን አብረን እንጎበኘዋለን፡፡ ሐረር ልትተኛ ነው እኔም ድካም ተጫጭኖኛል ሰላም እደሩ ሐረር ሥትነቃ እኔም በርትቼ ስነሳ አብረን የሐረርን ጓዳ ጎድጓዳ እንቃኛለን ሐምሌ 12 ቀን 2004 ዓ.ም ፡፡
     ንጋት ሐምሌ 13 ቀን 2004 ዓ.ም የሐረር ሌሊት ለንጋት ቦታውን በመልቀቅ 12፡30 ሰዓት ሆኗል፡፡ አየሩ መጠነኛ ቅዝቃሴ ይታይበታል፡፡ አገር ለማየት ቆርጦ የመጣ ብርድ ሙቀት ዝናብ ንፋስ ብሎ መተኛት አይጠበቅበትምና በጠዋት ተነስቻለሁ ጉዞ ከሸንኮር በእግር ወደ ሐረር እምበርርት በሐረር በር አድርገን ወደ ጨለንቆ አደባባይ፤ ከጨለንቆ አደባባይ ወደ ተለያየ አቅጣጫ መጓዝ ይቻላል አንደኛ መንገድ (ወደኤራር በር)፣ ወደ ሐረር በር፣ ወደ ሸዋ በር፣ ወደ ጀጎል በር፡ሰንጋ በር(ጅቦች ወደሚታዮበት) እዛው ጨለንቆ አደባባይ ላይ አሚር አብዱላሂ አዳራሽ (የቀድሞው የራስ መኮንን አዳራሽ) ይገኛል:: ለሁሉም ጊዜ አለውና ታሪክ በታሪክ ተደምስሷል በአንደኛ መንገድ ሲጓዙ እንዲሁ የታሪክ ሹም ሽረት ጥንት ጁግለን ይባል የነበረው ጁገል ሆስፒታል በመባል ተቀይሮ ያገኙታል ሙዝየሞች የባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች የሐረሪ ብሔረሰብ ባህላዊ ሙዝየም ሁለት መስጅዶች… ያገኛሉ፡፡ እዚሁ ወደ ጨለንቆ አዳባባይ መግቢያ ላይ ሁላችን በተለያዩ መገናኛ ሚዲያ የምናየው የሐረር በር አንድ ነገር ያመላክተናል፡፡ ‹‹ሐረር የሰላም የመቻቻልና የትብብር ከተማ›› ሐረር ጃጎል የዓለም ቅርስና የመጨረሻው የሐረር ንጉስ ፎቶ ግራፍ የአሚር አብዱላሂ ይታያል፡፡ 

   በአካባቢው ሲንቀሳቀሱ ይህቺ በ72 ነገስታት ሥትመራ ወይም ስትገዛ የኖረች ጥንታዊት ሀገር ባላት የውስጥ ለውስጥ ሽኩቻ እውን የመቻቻል አገር ናት? ብለው ጥያቄ ሊያነሱ ግድ ይልዎታል፡፡ የዛሬን አያርግና የፍቅር፡ የመቻቻል ከተማ ነበረች ነገም ተስፋ አለን ጠንካራ ህዝብ ነዉና ህዝቡ ታሪኩን ቀይሮ እንደገና ያመጣዋል።እንግዳ ኖትና አቦ ይመችዎት ወቅቱ ስለሆነ ዛሬ በሚዛን ቢሸጥም ድካሙን ያስረሳልና ማንጎ ይብሉ ተጋብዘዋል፡፡
ድሬ የምሥራቅ የበረሃዋ ንግስት የምትገኘው በ90 28.1 እና 90 49.1 በስተሰሜን ላቲቲውድ በ410 38.1 በስተምስራቅ እና በ420 19.1 ምስራቅ ሎንጊትውድ መካከል ሲሆን 505 ኪ.ሜ ከአ.አ ርቀት ላይ የምትገኝና በ1288 ኪ.ሜ ካሬ ላይ የሠፈረች፡ ደረቅና ሞቃታማ ስትሆን በ31.40Cከፍተኛ እና በ18.20C ዝቅተኛ መካከል ትገኛለች ዓመታዊ የዝናብ መጠኗ 604 ሚሊ.ሜትር እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከባህር ጠለል በላይ ከ960-2500 ሜትር መካከል ያለች ውብ ከተማ ናት። ህዝቦቿ ተግባቢና የሥራ ፍቅር ያላቸው እንግዳ ለመቀበል የማይሰለቻቸውና በብዙ ብሔር ብሔረሰብ ስብጥርና ዕምነት ደምቃ ያለች በብዛት የውጭ ዜግነት ያላቸው ሰፈርውባት ያለች ከተማ ናት፡፡
 አስራ ስምንት ኪሎ ሜትር ወደ ታች ቁልቁል መውረድ ይጠበቅብዎታል ድሬ ከባህር ጠለል 960-2500 ሜትር የምትገኝ ሲሆን በኢትዮጵያው ውስጥ በፌዴራል ከሚመሩ ሁሉት ከተሞች ከአ.አበባ በመቀጠል የምትገኝ ሞቃታማ፣ደማቅ፣ ግርግር ቀን ከሌሊት የማይለያት፣ ሃያ አራት ሰዓት በስራ ላይ የተጠመደች፡ የተለያዩ የብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ፣ የእንዱስትሪ መገኛ፡ የሸቀጣ ሸቀጥ መደብር፣ የዕውቀት ምንጭ፣ የቆንጆዎች ምድር፣ መቃሚያ ቦታ፣ መጨፈሪያ መድረክ፡ መገበያያ መደብር …..በቃ ድሬን ቃላት አይገልጻትም፣ ዓይን አይቶ አይጠግባትም፣ ቢኖሩባት ቢኖሩባት አትሰለችም ሲገቡ ተንደርድረው ደስ እያለዎት ወደ ከተማዋ ይገባሉ መውጣት ምጥ ነው፣ እጅግ ይጨንቃል፡፡ ድሬ መጥተው የት አርፋለሁ ብለው አይጨነቁም እርሶ ተዘጋጅተው ይምጡ እንጂ የፀዱ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎቻቸው በራቸውን ከፍተው “እንኳን ደህና መጡ” ብለው ይቀበልዎታል፡፡ በአንዱ ሆቴል የእረፍት ጊዜውን አድርገው ገላዎትን ከተለቃለቁ በኋላ ወጣ ይበሉ የትራንስፖርት ችግር የለም አያስቡ ባጃጅ ሞልቷል ሁለት ብር ከፍለው መንሸራሸር ነው አሥር ብርማ ከከፈሉ የሚፈልጉት ቦታ ይደርሳሉ፤ ብቻ እርሶ የት መሄድ እንደሚፈልጉ፣ ምን ማየት እንደናፈቁ ዝግጁ ይሁኑ እንጂ ለዛሬ ብቻ መሄድ እንጂ ወደየት መሄድ እንዳለቦት ግራ ከገባዎት መንገድዎን ለባጃጅ ሹፌር ይስጡ እርሱ ያስጎበኝዎታል፡፡
     ደቻቱ ሠፈር፣ መጋላ ሠፈር፣ ኮኔል ድልድይ፣ ከዚራ፣ ሳብያን፣ ነምበርዋን፣ ታይዋ፣ ፖሊስ ሜዳ፣ ለገሃሬ፣  አሸዋ፣ ወዘተ… የሚጎበኙ ናቸው፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...