ማክሰኞ 23 ኦክቶበር 2012

የኢየሩሳሌም የመንፈስ ተጓዥ




የኢየሩሳሌም የመንፈስ ተጓዥ


…እነሆ ለሕዝብ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ
የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ዛሬ በዳዊት ከተማ
መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ መርገመ ሥጋ መርገመ
ነፍስ የሌለበት በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ የሚያድል የዓለም
መድኃኒት የሚሆን የባህርይ አምላክ ክርስቶስ በዳዊት ከተማ
በዳዊት ባህርይ ተወልዶላችኋላና..
                                                                                                                                             አዘጋጅ ፡-ደረሰ ረታ
ዘመነ ጽጌ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ስርአትና ደምብ መሠረት በየዓመቱ ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 6 ቀን ድረስ ወቅቱ ዘመነ ጽጌ ወይም ወርሐ ጽጌ  የሚባል ሲሆን፡ ይህ ወቅት በቤተክርስትያን ስርዐት መሰረት በየሳምንቱ ቅዳሜ ምሽት በዝማሬና በምስጋና ሊቃዉንተ ቤተክርስትያን እግዚአብሔርን እና እመቤታችንን ሲያመሰግኑ ያነጋሉ። ሊቃዉንቱ ምስጋና የዘወትር ስራቸዉ ቢሆንም ቅሉ ይህንን ወቅት ደግሞ በተለየ ሁኔታ ማኀሌተ ጽጌ በሚባለዉ ዜማ እመቤታችንን ሲያመሰግኑ ያድራሉ፤ የሊቃዉንቱ በረከት ይደርብንና እኛም በማብዛት ሳይሆን በማሳነስ፣ በማስረዘም ሳይሆን በማሳጠር እንዲህ በማለት እናመሰግናታለን።   

ድንግል ሆይ ለምስጋና በሚመች ቃላትና አንደበት አይደለም የማመሰግንሽ በረከሰ አንደበቴ ነዉ እንጂ፣ መላዕክት ዘወትር የሚያመሰግኑሽ ቅዱሣንም እንዲሁ በመራድና በመንቀጥቀጥ ያለማሰለስ የሚያመሰግኑሽ የእኔ ምስጋና እንደምን ያንስ ይሆን? ማርያም ሆይ ያንን በረሃ በጽምና በረሃብ ስለኔ  ሐጥያትና በደል ማቋረጥ ሳያንስሽ ማዘንሽ? በዚያ በበረሃ ለተንከራተቱት በበረሃዉ ሙቀት ለተቃጠሉት እግሮችሽ፣ ባዘንሽ ጊዜ ላነቡት አይኖችሽ፣ የበረሃዉ ግለት በፈጠረዉ ጽም የተነሳ ለደረቁት ከንፈሮችሽና ጎሮሮዎችሽ፣ ክብር ምስጋና ይገባቸዋልና አመሰግንሻለሁ።
  ድንግል ሆይ በደሌ ከአዳምና ሔዋን በደል እጅጉን ልቋልና፡ ነፍሴም ጎስቁላለችና የእናት ልመና ፊት አያስመልስ አንገት አያስቀልስምና ለበደሌ አሳስቢ!
ይህንን ወቅት አስመልክቶ መጠነኛ ዝግጅት እነሆ!!!!
                     በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
አሜን
የኢየሩሳሌም የመንፈስ ተጓዥ
ክፍል ፩
    

-->
ማናችሁ ?ምንድናችሁስ? ስራችሁስ ምንድን ነው? ብትሉ፤ የሰው ልጆች ፍጥረት የመጀመሪያ የአዳም የልጅ ልጅ የሆን  የስላሴ አርአያ እና አምሣያ በስተምሥራቅ አፍሪካ ከምትገኝ ከኢትዮጵያ የፈለስን ስንሆን፣ስራችን ታሪክ ፀሐፊነት ነዉ፡፡
ታዲያ እኔና የስራ ባለደረባዬ ለስራችን የሚያገለግሉንን መሣሪያዎች አንግተን የበረሀውን ንዳድ ታግሰን ከፊታችን ደረቱን አስጥቶ የሚጠብቀንን የተያያዘ ዳገት ስንወጣ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ያላየውንና የፎቅ መውጫ መውረጃ/ሊፍት/ሳያስፈልገን ቁልቁለቱን ስንወርድ ከርመን የእግራችን አሻራ እስኪጠፋ  በመጓዝ በዚያን ጊዜ ዘመን ተቆጥሮለት ትንቢት ተነግሮለት ስለተወለደው ህጻን  የመወለዱን ዜና ለመዘገብ እንዲሁም ፈርኦን ሊገለዉ ያሳድደዉ ስለነበር ወደ ግብጽ ስለተሰደደዉ ስለዚሁ ህጻን ለማወቅ በመንፈስ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘናል። ኢሣይያስ አማኑኤል ብሎ ከ740 ዓመት በፊት በትንቢት የተናገረለት ዩሴፍም በትንቢቱ መሰረት በተወለደ በስምንተኛው ቀን ኢየሱስ ብሎ  ስለሰየመው ድንቅ ነገር ለመጻፍ ከስፍራችን ይህ ምሥጢር ወደተፈጸመበት እና ወደሚያቁት ሰዎች አመራን፡፡
ታሪኩንም በደንብ ግልጽ ሆኖልን እንድናውቀው ትንቢት የተናገሩለትንም አንዳንድ የእድሜ ባለፀጋ በሕይወት ስለምናገኛቸው ከልደቱ ጀምረን ያለውን ለማወቅ የዳዊት ከተማ ወደሆነች በያዕቆብ ዘመን ኤፍራታ እየተባለች   ወደምትጠራዋ ከአየሩሳሌም ወደ ደቡብ   ዘጠኝ (9) ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኝ ቤተልሔም ተጓዝን፡፡
-ቤተልሔም ማለት የስሟትርጓሜ የእንጀራ ቤት ማለት ነው፡፡
የታሪኩን ሙሉ መረጃ ለማግኘት ያነጋገር ነው የባለታሪኩን እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያምን፣ ጠባቂዋ/እጮኛዋ/ የነበረውን የዕድሜ ባለፀጋ የሆነው ቅዱስ ዩሴፍን፣ በተተነበየለት ትንቢት መሰረት እስከዚያን ዕለት እና ከዚያም በኋላ የቆየውንና በጣም አርጅቶ ሳለ ህጻኑን ሲታቀፍ እርጅናው የታደሰለትን ስምኦንን የልደቱን ሁኔታ ለማየት በሰዓቱ ከሩቅ ምስራቅ መጥተው የነበሩ ሰብዓ ሰገልን እና እረኞችን እንዲሁም  የአካባቢዎች ሰዎች ነበር፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ ግን ያመራነውናጥያቄያችንን ያነሣነው ለሰብዓ ሰገል እና ለእረኞች ነበር፡፡  ከሁሉም በፊት የምናምንበትን ፈጣሪ ስራችንን እንዲባርክ በጸሎት በመጠየቅ ነበር፡-
ቅድመ ዓለም የነበርክ ዛሬም ያለህ ዓለምንም አሣልፈህ ለዘለዓለም የምትኖር ያለትናንት ቀዳማዊ ያለነገ ደሀራዊ የምትባል ጥንታዊ እና ቀዳማዊ የሆንክ በባህሪ ሞት በመንግሥትህ ሽረት የሌለብህ የሠራዊት ጌታ  እግዚአብሔር  አምላክ  ሆይ ራስህን ዝቅ በማድረግ በቤተልሔም በከብቶች በረት ውስጥ ከእናትህ ከድንግል ማርያም የተወለድህ ክብር ምስጋና ይድረስህ፡፡
በመቀጠልም የአምላክነቱ ድንቅሥራ ተደርጎላቸሁ በቦታው በመገኘት እና ታላቅ ምሥጢሩን ለማየት የታደላችሁ ቅድስት ሰሎሜ እና ቅዱስ ዩሴፍ እንዴት አላችሁ?እናንተስ በአካባቢው ሰዎች ዘንድ ተንቆ የነበረን ስራ በመስራት በእረኝነት ላይ ያላችሁ የሀገረ ገሊላ እረኞች ዛሬን እንዴት ደረሣችሁ? ሠላምታችንን እንዲህ ከጀመርን በሁላ ጥያቄያችንን የቀጠልነው እንዲህ በማለት ነበር፡፡
ከሩቅ ምሥራቅ ኮከብ መርቷችሁ ለአምላካችሁ እጅ መንሻን ለማቅረብ ወደጌታ ዘንድ የቀረባችሁ ሰብዓሰገል ከመንገዱ ብዛት የተነሣ ካልደከማችሁ አንዲት ጥያቄን ልጠይቃችሁ?
ዘጋቢው፡-ለመሆኑ ጌታ እንደሚወለድ እንዴት አወቃችሁ?
ከቦታችሁስ ስትነሱ ብዛታችሁ ስንት ነበር? ይህ መንፈሳዊ ጉዞአችሁሰ ስንት ቀን ፈጀባችሁ? እናንተስ በመላእክት አብሣሪነት መወለዱን ያወቃችሁ እና በእልልታና በዝማሬ ጌታችሁን ያመሰገናችሁ የሀገረ ገሊላ አረኞች፡ መወለዱን ሥትሰሙ ምን ያህል ደነገጣችሁ፤ በእውነቱ መወለዱን አይታችሁ ሥተመለሱስ የቱን ያህል ተደሰታችሁ?
ሰብዓሰገል፡- የጌታን መወለድ ያወቅነው ነበዩ ሚኪያስ በትንቢት ተናገሮ ስለነበረ በዚያ ምክንያት እና ጊዜውም መድረሱን በአባታቻን ጃንደራሽ ትምህርት አማካይነት ኮከቡን በማየት ነበር፡፡ ከቦታችንም ስንነሣ ከየነገዳችን ከካም ነገድ ሶስት እልፍ፡ ከሴም ነገድ ሶስት፡ እልፍ ከያፌት ነገድ ሶስት፡ እልፍ በአጠቃላይ ዘጠኝ እልፍ በመሆን ነበር፡፡
ጉዞአችንም ኮከቡን በምስራቅ እያየን በኮከብ እየተመራን ሄሮድስ በተንኮል እንደነገረን ሣይሆን በህልም መልዐኩ እንደነገረን በሌላ ጐዳና በመሄድ ነበር የደረስነው፤ ወዴት ነው? እያልን እንዳልመጣን አገኘነው እያልን ተመለሰን፣ ንጉስ አይሁድ ብለን እንዳልሄድን አምላክ መሆኑን አምነን/አውቀን/ተመለስን፣ ስንሄድ ድፍን ሁለት ዓመት ሙሉ እንዳልፈጀብን በ40 ቀናችን ሀገራችን ተመልሰን ገባን፡፡
እረኞች፡-  መወለድ የሚለው ቃል ምንም አያስደነግጥም ትንሽ ግራ የሚገባው እና የማያስደነግጠው ምንም እንኳን ትንቢት ተነግሮለት ዘመን ተቆጥሮለት ሱባዔ ተገብቶለት የተወለደ ቢሆንም የሰዎችን ልጆች ለመውለድም ሆነ ለመወለድ የሚያበቃ አምላክ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ለዚያውም በከብቶች በረት መወለዱ ነበር ያሰደነገጠንና ግራ ያጋባን፡፡
መወለዱን አይተን ደስታውን እየተካፍለን ስንመለስ የተሰማን ደስታ ልክና መጠን የለውም ይህን ይመስላል፣ ይህን ያክላል አይባልም፡፡ አንልምም፡፡
---የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው ? እያላችሁ ስትመጡና ንጉስ ሄሮድስ ግቢ ስትደርሱ ንጉስ ሆኖ ሣለ ሌላ ንጉስ ወዴት ተወለደ ብላችሁ በመጠየቃችሁ አልፈራችሁም?
ሰብዓሰገል፡-ንጉስ ሲባል እንኳን ሠራዊቱን አልፎ ድርጊቱንና አስፈሪውን ፊቱን ታይቶ ይቅርና ስሙ ራሱ ሲጠራ በጣም ያስፈራል፡፡  ከዚያም ባሻገር ንጉስ እራሱን ሌላ እርሱን የሚተካ ከስልጣን የሚያወርደው ንጉስ የታለ ብሎ መጠየቅ ያስፈራል፡፡ ነገር ግን ነብዩ ኢሳይያስ እንደሚለው ኃያልነቱ በግፍ ተገዝተን ችግር ተደራርቦብን የኑሮ ጫና ወገባቸውን ያጐበጠውን የግፍ አገዛዝ የመረረንን ያስወግድልናል፣ ያቃናልናል፣ ከበታቹም ቀኝ አዝማች እና ግራ አዝማች ብሎ ይሾመናል፣ የቅርብ ወዳጆቹም የመንግስቱ አማካሪዎችም ያደርገናል ብለን አስበን ስለነበር የወደፊት ደስታችን/ተስፋ/የዚያን ሰዓቱን ፍራቻችንን አስወግዶልን ስለነበር አልፈራንም፡፡
-ሁለት ዓመት ሙሉ ተጉዛችሁ ቤተልሔም ዋሻ ስትደርሱ ምን ተሰማችሁ?
ሰብዓሰገል፡- መቸስ የእግር ጉዞ ስትጓዝ ምን ያህል አድካሚ እንደሆነ ልነግርህ አልችልም፤ እንኳን እኛ ህፃኑን ለማግኘት የተጓዝነው ቀርቶ እናንተ ይህንን ጥያቄ ለእኛ ለማቅረብ የፈለጋችሁትን ፍለጋ ብዙ እንዳደከማችሁ አይታችኋል፡፡  እኛ እንግዲህ ስንጓዝ አንድ ነገር ማለትም የምናገኘውን ንጉስ /አምላክ/ ተስፋ አድርገን ስለነበረ ተስፋው ያበረታን ነበር በተጨማሪም ይመራን የነበረው መልዐክ ስለሚያጽናናን አንዳች ፍራቻ የለብንም ። በጉዞአችን ያጋጠሙን ገጠመኞች ደስታ ስለነበሩ ከደስታው በቀር ሌላ የምናስታውሰው አንዳችም የለም፡፡እንግዲህ የተሰማን ደሰታ ብርታት ነበር፡፡
--አስቀድመን ጥያቄውን እንደጀመርንላቸሁ በቂውን መልስ ማግኘት የምንችለው ከእናንተ መሆኑንና በዕለቱም እንደነበራችሁ ተነግሮናል ይህ እንዴት ነበር?
እረኞች፡-የዚህን ታሪክ መፈጸም ልጆች ስለነበርን ከሰዎች ጋራ ስለማንገናኝ እንዲሁም ሁልጊዜ ውሉአችን ከከብት ጋር ስለነበር ምንም የምናውቀው ነገር የለም ነበር። ነገር ግን ድንገት ከብቶች እያገድን ሳለን ከሰዎች ወገን ያልነበረ ነጭ ልብስ የለበሰው መጣ፤ ወደኛ ዘንድም የሚያበራው ብርሃን እየቀረበን ሲመጣ ከታላቅ ምስጢርነቱም በተጨማሪ ልጅነትም ስለነበር ከመደናገጣችን የተነሳ ያቺን ዕለት ረገምን የተፈጠርንባትን ቀን እንደ ዕለተ ሞታችን አየናት መሬት ተስንጥቃ ብትዉጠን ተመኘን። መቸስ የዚያን ዕለት ፍራቻና ደስታ ምን ቃላት ይገልጸዋል እጅግ ፈራን እጅግም ደስ አለን፡፡
---ምን ደስ የሚያስኝና የሚያስፈራ ነገር አያችሁ?
እረኞች፡-እኛ እረኞች ስለሆንና በሰዎች ሁሉ ዘንድ የተናቅን ስንሆን ይህን ከሰው ወገን ያልሆነ ነገር ማየት እጅግ ያስፈራን ነበር (መልዐክ ማየታችን)፡፡  ምክንያቱም ለማጥፋትም ለመራዳትም ይመጣሉና፡፡
--ይህ ወደ እናንተ የመጣው ነጭ ልብስ የለበሰ መልዐክ ምን አላችሁ?
እረኞች፡- ይህ ግርማ ሞገሱ የሚያስፈራ መልዐክ ወደኛ ሲመጣ እንዲህ የሚል ቃል ነበር የተናገረን… …  እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምስራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለበት፤ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ የሚያድል፣ የዓለም መድኃኒት የሚሆን የባህረይ አምላክ ክርስቶስ በዳዊት ከተማ በዳዊት ባህርይ ተወልዶላችኋልና  አለን፡፡  ለመልዐከ  ፍርሃት አርቆ መናገር ልማድ ነውና አትፍሩ አለን። ይህ ቃል ነበር በተለይ በጣም ደስ እንዲለን ያደረገው፡፡  ያው እኛም ስለተደናገጥን  ለተወሰነ ሰዓት በመካከላችን ዝምታ ሰፈነ ድንገት እንደመጣ ድንገት በአፋጣኝ ሁኔታ ተለይቶን ሣይሄድ መጠየቅ ያለብንን ጥያቄ አቀረብን ጥያቄውም እርሱ መሆኑን በምን ዓይነት ምልክት ማወቅ ይቻላል? የሚል ነበር እርሱም ለጥያቄያችን መልስ እንዲህ ሲል ነገረን … “….ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግም ተኝቶ ታገኙታላችሁ” ብሎን ወደ መጣበት ሄደ፡፡ እኛም እርስ በርስ መልዐኩ የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር ለማየት ወደቤተልሔም እንሂድ በመባባል ጉዞአችንን ወደ ቤተልሔም ቀጠልን፡፡
-ለመሆኑ ወደዚህ ወደተባለው ሥፍራ ሥትጓዙ ሁላችሁም ተስማምታችሁ ነው የሄዳችሁት? ምንም ችግርስ የለም ነበር?
እረኞች፡- መቸስ አንድ ነገር ሲታቀድ እንከን አያጣውም ገና ከመጀመሪያው ጀምሮ ፍርሀት  በውስጣችን ነግሶ፤  በመሐል ላይም አለመግባባት ተፈጥሮ ስለነበር ግማሾቻችን እንሂድ ስንል ግማሹ አይ አንሄድም ምን እንደሆነ አውቀን ነው የምንሄደው? መሽቶብናል፣ ስንቅም ጨርሰናል፣ አንሄድም የሚል አለ። ከፊሉ ደግሞ ይህ አሁን ተገልጾ የተሰወረው ያኔ አዳምን “… እኔ የብርሃን መልዐክ ነኝ” ብሎ ይዞ ከወጣ በኋላ ደም እንደ ጅረት እስኪፈሳቸዉ ድረስ የወገራቸው ሰይጣን ቢሆንስ ብሎ ያመነታ ነበር፡፡
--መጠርጠር መልካም ነው፡- ታዲያ በጨረሻ ምን ላይ ደረሳችሁ?
እረኞች፡-በመጨረሻ ሰዓት እግዚአብሔር የወደደውን እና የፈቀደውን ነውና የሚያደርገው ሁላችንም የምስጢሩ /የደስታው/ ተካፋይ ሆንን፡፡
-ወደእዚሀ ስፍራ ስትደርሱ ማንን አገኛችሁ?
እረኞች፡-  ይህንን ስፍራ ከዚህ ቀደም ምንም እንኳን ብናውቅም በዚህን ዕለት ግን በጣም ለየት ያለ ነበር፡፡  ቦታዋ እንኳን እጅግ ከብራለች ጸጋንም ተጐናጽፈለች፣ከዚህ ቀደም የምናዉቃት መንደር አትመስልም። በዚህ የተከበረ ስፍራ በሐመልማለ ሲና የምትመሰለዋን ምራገ ጸሎት የሆነች የህፃኑን እናት ማርያምንና ዩሴፍን ህፃኑን በግርግም/ በከብቶች በረት/ ተኝተው አገኘነው፡፡
----እንኳን እናንተ ተአምረኛውን ያገኛችሁ እኛ እናንተን ስናገኛ በጣም ደስታ ተሰምቶናል፡፡  እናንተስ ምን ተስምቷችሁ ነበር ምንስ አላችሁ?
እረኞች፡- መቸስ በልቦናችን የተሰማንን ደስታ ለመግለጽ  ቃላት አይገኝለትም ብቻ ባጭሩ ወደር የማይገኝለት ደስታ ተሰምቶናል፡፡ እንደደረሰንም በህፃኑ ፊት ፍግም ብለን ከሰገድን በኋላ ስለእርሱ የተነገረን ነገር ነገርናቸው ከመላዕክትም ጋራ አመሰገንነው፡፡
-እዚያ ስትደርሱ ምንም ችግር አላጋጠማችሁም ነበር?
እረኞች፡- አጋጥሞን ነበር አንድ ሀሩር የሚባል ሰው ህፃኑ የተወለደበትን ቦታ ላሳያችሁ ብሎ በልቡ ተንኮል አስቦ ወደሌላ ስፍራ ሊወስደን ቢል መላዕክት አንገቱን ቆርጠው ጥለዉት እኛም አንገቱን  ቅሌ/ገና/ ተጫውተንበታል፡፡
-እረኝነት ብዙ ሰዎች እነደተራ ይቆጥሩታል፡፡ እናንተስ እረኝነተችሁን እንዴት ትመለከቱታላችሁ?
-   እረኞች፡-  ሁሉም ነገር ክብደትና ቅለት የሚሰጠው እንደተመልካቹ እና እንደነገርየው ዓይነት ነው፡፡ እኛም ምስጢሩን ስንመለከት የዓለም ጠባቂ/እረኛ/ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ምሣሌ መሆን ማለት በጣም ትልቅ ክብር ነው፡፡  ስለዚህ ይህ ክብር ለእኛ በፍጹም የሚገባ አልነበረም፡፡  ታናናሾችን ከፍ የሚያደርግ አምላክ ግን ሁሉን አደረገ፡፡
-ለጊዜው ከእረኞች ጋር ያለንን ጥያቄ  በዚህ አቋርጠን አብረው ወደነበሩት ሰብዓሰገል ጥያቄአችንን እንዲህ በማለት ሰነዘርን፡-
እንግዲህ ባለፈው ስንነጋገር ከሩቅ ምስራቅ ለህፃኑ  ልትሰግዱ የመጣችሁት በነቢዩ ሚክያስ ትንቢት መሰረት እንደሆነና ስትመጡም ወደ ንጉስ ሄሮድስ ዘንድ እንደደረሣችሁ ነበር የነገራችሁን መንገዱም ሁለት ዓመት መፍጀቱን ነገራችሁናል፡፡ ለመሆኑ  ወደ እዚህ  ስፍራ  ስትመጡ ሁለት ዓመት በመጓዝ ከዚያ ደረሳችሁ ንጉስ ሄሮድስ ፈት ስትቀርቡ ህፃኑ ወዴት እንዳለ ሲነግራችሁ ያላችሁ ነገር ነበር?

ሰብዓሰገል፡-   ንጉስ ሄሮድስ ጋርም ስንደርስ ህፃኑን አገኝታችሁ ሰግዳችሁ ስትመለሱ መጥታችሁ ለእኔም ወዴት እንዳለ ንገሩኝና ሄጄ እሰግድለታለሁ ብሎ ነበር፡፡  እኛ ግን ስንመለስ በዚያ አልተመለስንም፡፡
ንጉሥ ሄሮድስ እኔም እንድሰግድለት መጥታችሁ ንገሩኝ  ሲላችሁ ለምን ነበር ያልነገራችሁት  ለምንስ በሌላ መንገድ ሄዳችሁ?
-ሰብዓሰገል፡-  “ሄጄ እስግድለታለሁ” የሚለው ቃል ደባን ያዘለ ቃል ነበረና፤ሊሰግድለት ሣይሆን ሊገለው ነበር ተመልሣችሁ ንገሩኝ ያለው ለዛብለን ነዉ። አንድም መልዐኩ በመጣችሁበት በኩል አትሂዱ ስላለን ነበር በዚያ ያልተመለሰነውና በሌላ መንገድ የሄድነው።
-ይመራችሁ የነበረው ኮከብ ሁለቱንም ዓመት ያበራ ነበር እንዴ?
ሰብዓሰገል፡-መንደር ሲገባ ከሰው ሥንገናኝ ይሰወራል፡፡  በረሀ በረሀውን ስንጓዝ ግን አቅጣጫውን ይመራን  ነበር፡፡
- ከዚህ ቀደም አመጣጣችሁ ከወዴት ነው ስንላችሁ ከሩቅ ምስራቅ እንደመጣችሁ ነበር የገለጻችሁት ከሩቅ ምስራቅ ስትሉ ከየት ከየት አካባቢ ነበር?
-ሰብዓሰገል፡- ከብዙ ቦታ ቢሆንም ልብ አምላክ ዳዊት በትንቢቱ፡- “በፊትም ኢትዮጵያ ይስግዳሉ ጠላቶቹም አፈር ይልሣሉ” መዝሙር 71፣9 የሚል ስላለ ከኢትዮጵያም የመጣን ነበርን፤



-->
-ሰብዓሰገልንም በዚሁ መልኩ ጥያቄአችንን ካቀረብንላቸው በኋላ በቀጣዩ ደግሞ በስደቱ ላይ አብረው ወደነበሩት አምርተን ቅዱስ ዩሴፍን ቀዳሚ ተጠያቂ አድርገናል፡፡  በዘመኑ ወደነበረው ቆጠራ ሄዶ ስለነበር ለምን እንደሄደ  ላነሳንለት ጥያቄ እርሱም እንዲህ ሲል መልሶልናል፡፡
..ዩሴፍ፡- ለቆጠራ የሄድኩት ሰው ሁሉ ይቆጠር ዘንድ ለ41 ዘመናት በሮም የነበረ አገረ ገዥ አውግስጦስ ቄሳር ባወጣው ትእዛዝ መሰረት ለመቆጠር ነዉ፡፡
--ለ41 ዘመን በሮም ላይ አገረ ገዥ የነበረው የአውግስጦስ ቄሳር ማን ነዉ እንደሆነ ብትነግረን?
ዩሴፍ፡- አባቶቻችን ፡ውሃ ከጥሩ ነገር ከስሩ ይላሉ እኔም ታሪኩን ከስር መሰረቱ ልንገራችሁ ድሮ ያኔ የሮም ንጉስ  ከአንድ ጐልማሣ ሚስት ዘንድ ያለፈቃድዋ ደረሰባት/ደፈራት/ ባልዋን  ከልብ የምታፈቅር ሴት ነበረችና ያለፈቃድዋ ሌላ ወንድ ስለደረሰባት ታንቃ ሞተች፡፡ ወንድሞቿ እህታችን የሞተችው በእርሱ ምክንያት ነው ብለው ከቤተ ጣዖት ገብቶ ሲወጣ አንቀው ገደሉት፣ ኋላም ሕዝቡ እርሱም እርሷም የሞቱት አንድ ሰው ኃጢያት ሲሰራ ዝም ስላልን አይደለምን? ብለው ነገር የሚወስኑላቸው 120 ሽማግሌዎች ሾመዋል፡፡ ከ120 ሽማግሌ የአንዱ ሽማግሌ ሚስት ጸንሣ ሳለች በምትወልድበት ግዜ ሞተች ገንዘን እንቀብራለን ሲሉ ጽንሱ በማህጠኗ ተንቀሣቀሰ፣ ሕያውን ከምውት ጋር እንቀብራለን? ብለው ሆዷን ቀደው አወጡት አደገ ኃያልና ምሁር ሆነ፡፡  በስተመጨረሻም ሁሉንም አጥፍቶ ለንግስና በቅቷል ታሪኩ እንዲህ ነበር፤ተረዳችሁ?
- አመጣጡን ና አነጋገሱን እንዴት እንደነበር ግልጽ ብታደርግልን?
ዩሴፍ፡- ሽማግሌዎች ወገን ስለነበር /ስለተወለደ/ ስሙን ብልዮስ ቄሳር ብለዉታል።ብልዮስ ቄሳር ጋስዮስ ቄሳርን ጋስዮስ ቄሳር አዉግስጦስ ቄሳርን ይወልዳል፤የአዉግስጦስ ቄሳር አመጣጥ እንግዲህ  ይህንን ይመስል ነበር።አነጋገሱ ደግሞ ህዝቡ በሀገራቸው አንድ ኃይለኛ ጠላት ተነስቶ አስቸገራቸዉ አጥፋልንና  እናነግስሀለን አሉት፡፡ እርሱም ኃያል ስለነበር በኃይሉ ተማምኖ ከአነገሣችሁኝ እሺ  በእጄ ብሎ አጥፍቶላቸዋል፡፡  እነርሱም ቃል  እንደገቡለት አንግሰውታል፡፡በቃ…..
-ታድያ አዉግስጦስ ቄሳር ህዝቡ እንዲቆጠር ያደረገዉ ለምንድን?
ይህንን እና ሌሎችን ቀሪ ምሥጢር በክፍል ሁለት እንዳስሳለን፤ በመንፈስ አብራችሁን ስለተጓዛችሁ እያመሰገንን ለክፍል ሁለት ያበቃን ዘንድ ጸልዩ። መልካም የጽጌ ዘመን ይሁንልን፣ ይቆየን።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...