ሐሙስ 26 ማርች 2015

"እንድትዋረድስ የምትታሰርበት ምን እንደሆነ እባክህ ንገረኝ"



ይህንን ሀይለ ቃል ለሶምሶን የተናገረችዉ ደሊላ የምትባል በሶሬቅ ሸለቆ የምትገኝ ሴት ናት፡፡ ደሊላ ይህንን ቃል የተናገረችበት ምክንያት ፍልስጥኤማዉያንን በጣም ስላስቸገራቸዉ ከነርሱ መካከልም ብዙ ሰዉ ስለገደለባቸዉ፣ የፍልስጥኤም ነገሥታት እና መኳንንት ደሊላን እያንዳንዳችን 1100 ብር እንሰጥሻለን በምን እንደሚደክም ጠይቂዉ አሏት፤ እርሷም እንዲወዳት ካደረገች በኋላ ወደርሷ አስጠግታ እያሻሸችዉ ይህን ጥያቄ አቀረበችለት፡፡ እርሱም መግለፅ ስላልፈለገ ባይሳካለትም ሦስት ጊዜ እንዲህ እያለ ዋሻት፡-
      I.        1.በሰባት ባልደረቀ በእርጥብ ጠፈር ቢያስሩኝ እደክማለሁ እንደሌላዉም ሰዉ እሆናለሁ፣
     II.       2. ሥራ ባልተሰራበት በአዲስ ገመድ ቢያስሩኝ እድክማለሁ፤
   III.        3.የራሴን ጠጉር ሰባቱን ጉንጉን ከድር ጋር ብትጎነጉኚዉ በችካልም ብትቸክይዉ እደክማለሁ እንደሌላዉም ሰዉ እሆናለሁ አላት፡፡
እነዚህን ጠቅሶ ከዋሻት በኋላ እርሷም እወድሻለሁ ብለኸኝ ለካስ  አትወደኝምየምትወደኝ ቢሆን ኖሮ እንድዋረድ የምትታሰርበትን ምን እንደሆነ በነገርከኝ ነበር አለችዉ፡፡

ማክሰኞ 24 ማርች 2015

ፍቅር!



ፍቅር
ስለፍቅር እናዉራ ካልን እጅግ ተቀድመናል፣ ብዙዎች ባማረ ስንኝ በተዋበ ዜማ አወድሰዉታል አብጠልጥለዉታልም፤ የልብ ብሔራዊ ዜማ እስኪሆን እያነባንና እየደማን የልብን ሰንደቅ እየሰቀልን እና እያወረድን እያከበርንና እየተዋረድን ብዙ አዚመናል፡፡ እንደያቅማችን እኛም ቢሆን በጊዜዉ ስንኝ ቋጥረናል፤ እንዲህ እያልን
                                    ኤድያ! ፍቅር
አበድን ….
        ከነፍን ….
 አለኝ
        አልበላ
አላት
       አልጠጣ
አቅበጠበጠን
      አንዘፈዘፈን
ግሞ ተጋግሞ
 … ተቀጣጥሎ መተንፈሻ
አሳጥቶን
ጣን
   ዓይን ገባን
ከዓይን ያዉጣችሁ
    ያዝልቃችሁ
       አሉን
" አሜን" ሳንል
ከአንደበታቸዉ ሳይጨርሱት
            መርቀዉን
            እንደተገናኘን
አፍታም ሳንቆይ ወዲያዉ ተለያየን፡፡
(ደረሰ ረታ)
ቋጠሮ ቋጥረን እምባችንን አብሰን መሃላችንን አፍርሰን ዳግም እንደገና ለፍቅር ስንል በፍቅር ጦር ሜዳ እንሰለፋለን ሌላ ምንም አይደለም በቃ ፍቅር ስለሆነ ብቻ!
ደግሞ ትንሽ እንቆይና
ሌላ የስንኝ ቋጠሮ ይገመዳል፤
……
እንሰነባብትና ምሬታችንን መለኪያ ቋጠሮ …. በየጎዳናዉ እንቀባጥራለን፤
" ይህቺ ሴት "
ያቺም ኋሜተኛ ይቺም ስሞተኛ
ላላማት ላታማኝ
ከማን ተነጥዬ
ከየትኛዋ ልተኛ?
እኔንስ ጨነቀኝ እኔንስ ጠበበኝ
ከጎኔ የሳባት አጥንት እየወጋችኝ
ሥሄድ ተከትላኝ ስመጣ እየገፋችኝ
መቆሚያ መቀመጫ
መሞቻ አሳጣችኝ፡፡
እስኪ ስለፍቅር እንቀኝለት ቅኔ!
(ደረሰ ረታ)
ያለፍቅር እንደማይሆን ስናዉቀዉ በተደበላለቀ ስሜት ለእርግማንና ለፀፀት እንዲህ ስንኛችንን እንቋጥራለን
መከራዬ ትንገስ
ችግሬም ትወደስ
እስከ ዘለዓለም ትሁን የኔ ቅርስ
በድዬ ከሆነ ፍቅሬን ገፍቼ
አርክሼም ከሆነ ክብሩን ረስቼ
…. … አልያ ግን  …. አልያ ግን
በዳዮቼን ሁሉ ገፊዎቼን ሁሉ
ይገፉ አልልም!
ይከፉም አልልም!
… … ግን … …
ይማሩ … ተበዳይን ይካሱ፣
ፍቅርን ከል ጥቀርሻ ስላለበሱ
… … ፍቅር ሆይ …
መስክሪኝ! ፍረጂኝ!
ይህን ክፉ በደል
ክፈይኝ ወረታዉን
የፍቅር ምላሹን፡፡
(ደረሰ ረታ)
ደግሞ ስናገኝ ጮቤ እንረግጣለን፤ ስንጎዳ እናለቅሳለን፡፡ ነገር ግን ሁላችንም ልብ የማንለዉ ነገር መበደላችንን፡፡
እናቅርብ ዉዳሴ ሲያሰኘን ወቀሳ
ለትንታኔዉ በካህሊል ጊብራን ድርሰት እንዲህ እያልን እንነሳ
ፍቅር!
መንገዶቹ አስቸጋሪ አቀበት ቢሆኑም ፍቅር ሲጠቅሳችሁ ተከተሉት፡፡ በላባዎች መካከል የተደበቀዉ ሰይፍ ሲያቆስላችሁ ክንፎቹም ሲያቅፋችሁ ተሰጡት፡፡
የሰሜኑ የነፋስ የአትክልት ስፍራን እንደሚያወድም፣
ድምፁ ህልሞቻችሁን ቢበትንም፣
ሲያናግራችሁ እመኑት፡፡ ፍቅር እንደሚያነግሳችሁ ሁሉ ይሰቅላችኋልና፡፡ለዕድገታችሁ እንደሆነዉም ሁሉ ለምልመላችሁ ነዉና፡፡
ወደ ጫፋችሁ ወጥቶ በፀሐይ ዉስጥ የሚያርገደግዱትን እጅግ ለስላሶች ቅርንጫፎቻችሁን በፍቅር እንደሚዳብሰዉ ሁሉ፣ እንዲሁም ወደ ሥሮቻችሁ ወርዶ በመሬት ዉስጥ በይዞታችሁ ይነቀንቃችኋል፡፡
እንደ ስንዴ ነዶ ወደ ራሱ ይሰበስባችኋል፡፡
እርቃን ሊያደርጋችሁ ይወቃችኋል፡፡
በገለባዎቻችሁ እንድትለዩ ያነፍሳችኋል፡፡
ለንጣት ይፈጫችኋል፡፡
እስክትለስልሱ ያቦካችኋል፡፡
ለእግዚአብሔር ቅዱስ ግብዣም ቅዱስ እንጀራ እንድትሆኑ ከዚህ በኋላ ለቅዱስ እሳቱ ይዳርጋችኋል፤
የልባችሁን ምሥጢሮች እንድታዉቁና በዚህ ዕዉቀት የልብ ሕይወት መአዛ እንድትሆኑ ፍቅር እነዚህን ነገሮች ሁሉ ያደርግባችኋል፡፡
ነገር ግን ከፍርሃታችሁ የተነሳ የፍቅርን ደስታ ብቻ ብትፈልጉ እርቃናችሁን ሸፍናችሁ ከፍቅር አዉድማ ገለል ብትሉ ይሻላችኋል፡፡ … ፍቅር ራሱን እንጂ ምንም አይሰጥም፡፡ ከራሱም በቀር ምንም አይቀበልም፡፡
ፍቅር ማንንም ገንዘቡ አያደርግም፡፡ለማንም ገንዘብ አይሆንም፤ፍቅር ለራሱ በቂ ነዉና፡፡
ስታፈቅር " እግዚአብሔር በልቤ ዉስጥ ነዉ " አትበል፤ ይልቁን ግን " እኔ በእግዚአብሔር  ልብ ዉስጥ ነኝ " በል እንጂ፡፡
የበቃህ ሆነህ ካገኘህ ፍቅር ጎዳናህን ይመራልና የፍቅርን ጎዳና መምራት የምትችል አይምሰልህ፡፡ ራሱን ከመሙላት በቀር ለፍቅር ሌላ ምኞት የለዉም፡፡
ነገር ግን ካፈቀራችሁና ምኞቶች እንዲኖራችሁ ከፈለጋችሁ ምኞቶቻችሁ እነዚህ ይሁኑ፤
ቀልጦ ቃናዉን ለሌሊት እንደሚያዜም ጅረት መሆን፤ 
የርህራኄን ብዛት ህመም ማወቅ (መቅመስ)፤
 በጋዛ ራሳችሁ የፍቅር ማስተዋል መቁሰል በፈቃደኝነትና በደስታም መድማት፤
ክንፍ ባለዉ ልብ በጎህ ተነስቶ ስለሌላዉ የፍቅር ቀን ምስጋና ማቅረብ ፡፡
በቀትር ሰዓት አርፎ የፍቅርን በረከት ማሰላሰል፤
ማታም በምስጋና ወደ ቤት መመለስ፡፡
ከዚያ በኋላ በልባችሁ ዉስጥ ለተወዳጆቻችሁ ፀሎት በከንፈሮቻችሁ ላይ በዉዳሴ ዜማ መተኛት፡፡   
ፍቅር ወደድንም ጠላንም እዉነቱ ይህ ነዉ፤ 
እዉነትም የፍቅር ትርጉሙ ያልገባን ገብቶንም እንዲህ መኖር ያልፈለግን ከፍቅር አዉድማ ገለል እንበል፡፡ ቅዱሱን ስፍራ በረከሰ ማንነታችን አናርክሰዉ፡፡ ወልደ አምላክ የደም ዋጋ የከፈለበት ነዉና፡፡

እሑድ 22 ፌብሩዋሪ 2015

ዋጋ ሲተመን!




ሰዉየዉ ቤታቸዉን ለመሸጥ ቆርጠዉ ተነስተዋል፤ የመንደሩ ሰዉና ደላላ ከጠዋት የእርሳቸዉን ቤት መሸጥ መነጋገሪያ ከማድረጉ ባሻገር የማሻ ልመንህ ዋጋዉን ጣሪያ ማስነካት ገዢዎችን ከስፍራዉ ዝር እንዳይሉና ቤቱን እንኳን መግዛት ማየት እንዳይችሉ አድርጓቸዋል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን በዕድሜ ጠና ያለ ሰዉ መጥቶ ደጅ ይጠፋል(ያንኳኳል) የቤቱ ጠባቂም ደጁን ይከፍትና ማንን ፈልገዉ እንደሆነ ይጠይቃቸዋል፡፡ የቤት ገዢ መሆናቸዉን እና የቤቱን ባለቤት (ሚስትየዉን ) እንደሚፈልጉ ይነግሩትና ይጠራላቸዋል፡፡
ሁለቱ ሰወች ስለቤቱ ጥሩነት ግቢዉም ሰፊ መሆኑን ነገር ግን ዋጋ እጅግ ዉድ እንደሆነ አዉርተዉ ገዢዉ ሴትዬዋን ለባለቤታቸዉ ዋጋዉን እንዲቀንሱላቸዉ አደራ ጭምር ነግረዉ ይሄዳሉ፤ ሚስትም ቀን እንደተባሉት አባወራ ወደቤት ሲገቡ የእግር ዉሃ  አቅርበዉ እግር እያጠቡ (ጊዜዉ እንደዛሬ የሴቶች እኩልነት ባልነበረበት ሰዓት /ፍቅር እንዲህ ዝቅ ብለዉ የሚገልፁበት ወቅት/ ወንዶች የበላይ ነን ብለዉ የሚመኩበት ዘመን/ ነበር) ቀና ይሉና ባሻዬ ዛሬኮ አንድ ሰዉ መጥቶ ቤቱን እንደሚሸጥ ጠየቀኝ እኔም እንደሚሸጥና እርሶ የሚሉትን ዋጋ ነገርኳቸዉ፤
ምን ማለት ነዉ " አንተ የምትለዉን "ማለት አንቺስ የቤቱ ባለድርሻ አይደለሁም ነዉ ወይስ ነገሩ እንዴት ነዉ?
"ማለቴ" እያሉ ቀጠሉ ሴትዮዋ ፈራ ተባ እያሉ " ሰዉየዉ እንዳሉት ዋጋዉ ትንሽ ወደድ ብሏል ለማለት ፈልጌ ነዉ"
አንቺ ሴትዮ በጤናሽም አይደለሽ? አንዴ አንተ እንዳልከዉ፣ አንዴ ደግሞ ሰዉየዉ እንዳለዉ የሚያሰኝሽ ምንድን ነዉ? ገዢ ነሽ ሻጭ?
እህ እንደዛ አላልኩም እርሶም ያሉት ዋጋ እንኳን ለገዢነት ለሻጭም ጥሩ አይደለም ይወደዳል እዚህም እንደሆነ ይህን ያህል ዋጋ ያወጣ ቤት ስላላየሁ ነዉ እንደዛ ማለቴ ሰዉየዉም ሲያዩዋቸዉ ገዢ ይመስላሉ ስለዚህ የሚሉትን ቁርጥ ያለ ዋጋ ይንገሩዋቸዉና እንሽጥ ለማለት ነዉ፡፡
እንግዲህ እኔ ያልኩትን ብያለሁ! የሚገዛ ከመጣ እንሸጣለን አለበለዚያ ቤታችን ከእኛ ጋር እነሱም ገንዘባቸዉ ከራሳቸዉ ጋር ምን ያጋጨናል ገዢ ከጠፋ እኛዉ እንኖርበታለን ምን አስጨነቀን ባዶዉን አይሆን፤
ካሉ ጥሩ! ብለዉ ሴትዮዋ እግር አጥበዉ እንደጨረሱ እራት አቅርበዉ በልተዉ ከጨረሱ በኋላ ወደ መኝታ ሄዱ፡፡
ሌላ ቀን ደግሞ የሁነ ሰዉ እንዲሁ መጣ! ዋጋ ተነጋገሩ ሳይስማሙ ቀሩ ሄደ!
በሌላኛዉም ቀን ብዙ ሰዎች መጡ ሳይስማሙ ቀርተዉ ተመልሰዉ ሄዱ!
አንድ ቀን ግን የመጡት ሰዉ አጥብቀዉ ተከራከሩአቸዉ ገዢም እንደሆኑ አስረግጠዉ ነገሩአቸዉ፤ ባለቤትየዉም እንድዲህ ቤቱን ከወደዱት ገንዘብ መያዝ ሳይሆን ወጣ አድርጎ መግዛት ነዉ እያሉ ከረር ብለዉ ተናገሩ፡፡ ሰዉየዉ እንዲቀንሱላቸዉና ቀብድም ሰጥተዉ ሊሄዱ እንደሚፈልጉ ቢነግሯቸዉ ሻጭ አሻፈረኝ አሉ፡፡
ከገዢ ጋር የመጡት ሰዉ ሁለቱን ለማስማማት የተወሰነ ሙከራ አደረጉ ግን ሰሚ አላገኙም፤ ሻጭ ይልቅስ የምተገዙ ከሆነ በደንምብ ዙሪያዉን እዩት፣ የግቢዉንም ስፋት ተመልከቱት፣ ካርታዉም በጄ ነዉ፣ ደግሞ በዚህ ላይ እዚህ ግቢ ዉስጥ ያለ አትክልት አመቱን ሙሉ ገበያ አያስመኛችሁም ከጊቢዉ ዞርዞር ብላችሁ ብትመለከቱ የምታጡት ነገር የለም፡፡ይልቅስ ንትርኩን ትተን ተስማምተን እናንተም ቤታችሁን ዉሰዱ እኔም የሚደርሰኝን ነገር ስጡኝና ወደሚሄድበት ልሂድ በማለት ነገሩን ቋጩት፡፡
ገዢ የሚለዉ ቢጠፋዉ "ለመሆኑ ዋጋዉ እንዲህ ጣሪያ የነካዉ ይሄ ቤቴ (ሊገዛዉ እንደሆነ ሲወስን ነዉ ቤቴ ማለት የጀመረዉ) የተለየ ከሌላዉ ምን የተለየ ቢኖረዉ ነዉ?" ብሎ ጠየቀ፤
ምን ቀረዉ ሰፊ መሬት አለህ፣ ይህን የሚያክል ትልቅ በዚህ ግቢ ላይ የተንጣለለ ቤት አለዉ፣ የአትክልቶቹን ነገር አታንሳዉ ይህ ሁሉ ተደምሮ ብለዉ ድምር ዋጋዉን ነገሩት፤
"የተቀረዉስ ገንዘብ?" ገዢ ጠየቀ
የተቀረዉማ ሰፈሩን እንደምትመለከተዉ ጥሩ መኖሪያ ነዉ፣ አየሩንም ልብ ብለህ ካየኸዉ ጤና ነዉ! እነዚህም የየራሳቸዉ ዋጋ አላቸዉ ብለዉ ዋጋቸዉን ነገሩት፤ አሁንም ሂሳቡን ቢያሰላዉ ዋጋዉ እኩል አልመጣም " የቀረዉስ?" አላቸዉ
"የቀረዉ ደግሞ በሶስቱም ማዕዘን ያሉ ጎረቤቶችህ ዋጋቸዉ ከቤቱ በላይ ነዉ ሰወች እንዳይመስሉህ  አብረሃቸዉ መኖር ስትጀምር እንዲያዉም ከመላዕክት ጋር የተጎራበትክ ነዉ የሚመስልህ እነሱም በዚህ ቤት ዋጋ መጨመር ላይ ትልቅ ድርሻ አላቸዉ፡፡እንዲያዉም እንዳልጎዳህ ብዬ ነዉ እንጂ ያንሳቸዋል! ያንሳቸዋል፤ የጎረቤቶችህ ዋጋቸዉ የሶስቱንም ደምሬ በቤቱ ላይ 200 መቶ ሺ ብር ጨምሬበታለሁ ጠቅላላዉን ስትመታዉ (ሰትረደምረዉ) ልክ አይመጣም?"
ይመጣል!
"እና ያተረፍኩብህ ነገር አለ?"
የለም!
"በል እንግዲህ የምትገዛ ከሆነ ይኸዉልህ ቤቱ ፡የማትገዛ ከሆነ ደግሞ…."
አላስጨረሳቸዉም ለቀብድ የሚሆን በእጁ የያዘዉን ጥሬ ገንዘብ ሰጥቶ ነገ ተመልሶ አጠናቆ እንደሚከፍል ተናግሮ እየተገረመና እየተደመመ ከስፍራዉ ጠፋ፡፡
ሁላችንም የምንፈልገዉ እና የጎደለብን እንዲህ አይነት ቤት እና ሰፈር ነዉ፤ የገዛናቸዉና የሸጥናቸዉ ቤቶች የህን አሟልተዉ ይሆን?
ምንደሮቻችንስ ዝም ብለን በዘልማድ ስንኖርባቸዉ ስለኖርን ነዉ ወይንስ እዉነት መኖሪያ ሰፈር ናቸዉ? ልጆች አድገዉ ለቁምነገር የሚበቁበት ናቸዉ?ጎረቤቶቻችንስ፣ እኛስ ብንሆን ለጎረቤትነት ብቁ ነን? ለኛ ዋጋ ቢወጣልን ዋጋ እናወጣለን ይሆን ወይስ ኪሳራ?

ሴት ሐዋርያ



ቤተክርስትያን በክርስቶስ ኢየሱስ ደም የተመሰረተች መሰረቶቿ ከዐለት እጅግ የጠነከሩ፡ ሐዋርያት ከዳር ዳር ተዘዋዉረዉ ወንጌልን በማስተማር ያፀኗት፡ ሰማዕታት ደማቸዉን አፍሰዉ አጥንታቸዉን ከስክሰዉ ያቆዩዋት፡ ደናግላን÷ መናኞች÷ባህታዉያን በገዳም ጤዛ ልሰዉ ድንጋይ ተንተርሰዉ ድምፀ አራዊቱን ፀበ አጋንንቱን ታግሰዉ በፆምና በጸሎት ያቆዩዋት  ቅድስት ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር ደጅ ነች፡፡ ከነዚህ ቤተክርስትያንን ለዛሬ ካደረሱት መካከል ሴቶች ከፊሉን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ ሴቶች (እናት፡ ሚስት፡ እህት፡ … ከመሆን ባሻገር ይልቁንም በአገራችን በኢትዮጵያ ትልቅ ተሳትፎ በሁሉም ስፍራ ሲያበረክቱ ይታያሉ፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የገጠሯ ሴት በብዙ ቦታ ጉልህ ድርሻ አላት፡ ልጅ ወልዳ አሳድጋ እድሜዉ ለአቅመ ትምህርት ሲደርስ እርሷ ሳትማር ልጇን ለትምህርት ያላትን ቋጥራ ከየኔታ ጋር ሰዳ ፊደል ቆጥሮ፡ መዝሙረ ዳዊት ደግሞ፡ ቅዳሴ ተምሮ፡ ቅኔ ተቀኝቶ፡ … ቤተክርስትያንን እንዲያገለግል ወይም እርሱም መፅሓፍ ዘርግቶ እንዲያስተምርና ተተኪ እንዲያፈራ የምታደርግ የቤተክርስትያን ባለዉለታ እና መከታ የሆነች ሴት ናት፤ ከዚህም ባሻገር የበረቱት እንደ እማሆይ ጀማነሽ ያሉቱ መፅሃፍ ዘርግተዉ ደቀመዛሙርት ሰብስበዉ አስተምረዉ የሚያስመረቁ ሴቶች አልታጡም ይህ ሰማአዕትነት፡ ሐዋርያነት ነዉ፡፡ በመፅሐፍ ቅዱስም ብዙ መልካም ስራን የሰሩ ለቤተክርስትያን ማገር ዋልታ የሆኑ ብዙ ተጠቃሽ ሴቶች አሉ፡ የሐዋርያትን ፍኖት ተከትለዉ ከጌታ እግር  ስር የተማሩ 36ቱ ቅዱሳን እንስት ሌላ ተጠቃሽ ሴቶች ናቸዉ፡፡
     ዛሬም ቤተክርስቲያን ልጆቿን የእግዚአብሔር መንግሥት የምታስወርስ የሴት ሐዋርያ ትፈልጋለች /ያስፈልጋታል/፡፡
ሴት፡- ስንል ሌላ ተዓምር ማለታችን አይደለም እግዚአብሔር በመልኩና በአርአያው በመጀመሪያ ከወንድ የፈጠራት ፍጥረት ማለት ነው፡፡ ሴት /ሔዋን/ የህያዋን ሁሉ እናት ከአባታችን ከአዳም የግራ ጎን በተፈጠረች ጊዜ የቤተክርስቲያን መጽሐፍት /ታሪክ/ እንደሚነግረን ስላሴ የሰውን ልጅ እንፍጠር ብለው በተመካከሩ ሰዓት አብና መንፈስ ቅዱስ አዳም ደካማ ባህርይ /የሚሳሳት/ ስለሆነ አንፈጥርም ሲሉ ወልድ እዋሰዋለሁ ብሎ ሊፈጠር ችሏል፤ ለዚህ ድካሙ ረዳት አጋዥ ትሆነው ዘንድ የተፈጠረችለት የመዳን የብርታት የጥንካሬ ሐዋርያ ሌላ ወንድ አልነበረም ሴት /ሔዋን/ እንጂ፤
          ዛሬም ደካማውን መሳት ያለበትን አዳም ልትጥለው ልትገረስሰው ምክንያተ ስህተት የምትሆንበት ሳይሆን

ኦ! ቤተልሔም



ሰላምና ጤናን ዘወትር የምመኝልሽ ቤተልሄም እንደምን ሰንብተሻል አሁንም ደግሜ እላለሁ ሰላም ጤና ዕድገት ብልጽግና የእግዚአብሔር ቸርነት ካንቺ ጋር ይሆኑ ዘንድ የዘወትር ምኞቴና ጸሎቴ ነው፡፡
          የእንጀራ ቤት እያሉ የሚጠሩሽ ከኢየሩሳሌምም በስተደቡብ 10ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኚ እነ ቢታንያ÷ ቁምራን÷ ኬብሮን… የሚያዋስኑሽ የአባቶቻችን አምላክ ልዑለ ባህርይ ቅዱስ እግዚአብሔር የሚለመንባቸው የያዕቆብ የሥጋው ቁራጭ የአጥንቱ ፍላጭ የደሙ ምጣጭ /ሚስት/ ዐረፍተ ዘመን ሲገታት መዋቲ ሥጋዋ ግብዐተ መሬት የተከናወነብሽ ቅድስት ሀገር፤
          በመሳፍንትም ዘመን የኢብዳንና የቦዔዝ÷ የሩት የእሴይና የዳዊት ከተማ የነበርሽ÷ ልዑል እግዚአብሔር "እንደ ልቤ የሚሆን የእሴይን ልጅ አገኘሁ" የተባለለት÷ ንጉስ ዳዊት በነቢዩ ሳሙኤል የተቀባብሽ፣ ነቢያት ትንቢት ተናግረው ይወርዳል፣ ይወለዳልም በማለት ሱባኤ ገብተው መድህኒዓለም ክርስቶስ የተወለደብሽ፤ በመወለዱም እረኞቹ በኋላም ስብአ ሰገል መጥተው የጎበኙሽ ጌታንም ሲያገኙ ያመሰገኑብሽ÷ተድላ ደስታ የተፈፀመብሽ ሰውና መላዕክት በአንድነት ህብረት የፈጠሩብሽ÷ በአንድ ቋንቋ በአንድ ዜማ አምላከ አማልክት የሆነ ጌታን ያመሰገኑብሽ÷ ቤተልሔም ዛሬን እንደምን ደረስሽ? እድሜያቸው ሁለት ዓመት ያልሞላቸው ህፃናትን ሄሮድስ ባያስፈጃቸውና ደስታው ወደ ሃዘን ባልተለወጠና በጉያቸው ህፃን ታቅፈው የሰነበቱ እናቶች የሃዘን ፍም በማህፀናቸው÷ የሐዘን በትር ጀርባቸውን÷ የሃዘን ሰይፍ በጉያቸው ተሰንዝሮ ሃዘንን ባያከናንባቸው ኖሮ ምንኛ ደስ ባለ፤ አንቺ ቅድስት ሃገር ቤተልሔም ዛሬስ መንደሮችሽ፣ ጉድባዎችሽና አደባባዮችሽ ሐዘን ነው ደስታ የተንሰራፋባት? ነገሥታትና መኳንንቶችሽስ እንደምን ሰንብተዋል? እንደዚያኔው ‹የመጥረቢያ ልጅ መዘለፊያ› እንዲሉ የሄሮድስ የልጅ ልጅ ይሆኑ? ወይስ?...  ሕዝቦችሽስ እንደምን ናቸው? ከብቶችሽስ?
          መልአኩ የዳዊት ከተማ በሆንሽ በቤተልሔም በከብቶች በረት በግርግም መወለዱን ለመልዓክ ፍራት ማራቅ ልማዱ ነውና ‹‹አትፍሩ›› እያለ ታላቅ የምሥራችን ‹‹እነሆ ለሕዝብ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና›› ሉቃስ 2÷10-11 በማለት የተናገረ መልዓክ ዛሬስ እየመጣ ሕዝቦችሽን ከፍርሃት ያድናቸዋል? የምስራችን ያበስራቸዋል?

ሰኞ 9 ፌብሩዋሪ 2015

ሟችና መልዐከ ሞት



ሟችና መልዐከ ሞት

እስኪ ይፍረዱ፤
እርስዎ እያሉ እነማን ይሂዱ?
ታሪኩ እንዲህ ነዉ ሰዉየዉ በዕድሜ እጅግ በጣም እጅግ የገፉ ናቸዉ ከዕለታት አንድ ቀን አጅሬ ሞት በድንገት ከተፍ ይልባቸዉና "ይነሱ ልወስድዎት ነዉ ተልኬ የመጣሁት "ብሎ በሰዉኛ ያናግራቸዋል፤ ሰዉየዉም እስከዛሬ ባላዩት እንግዳ ሰዉ እና እንዲህ አይነት አስደንጋጭ መልዕክተኛ ግራ በመጋባትም በመደናገጥም "አንተ ማነህ? ከወደየትስ ነዉ የመጣኸዉ? የላከህስ ማነዉ?" ይሉታል፡፡
መልዕክተኛዉም "እኔ መላከሞት ነኝ! የላከኝ ፈጣሪ ነዉ" ብሎ አሳጥሮ ይነግራቸዋል፤
"እህሳ ለምን መጣህ?"
"ልወስዶት ተልኬ"
"ለምን ቢባል?"
"የመሔጃ ጊዜዎት ስለደረሰ ልወስዶት… "
"በል እንግዲህ ይህን መልዕክት ይዘህ መጥተህ የለም፤ መልዕክቴንም አድርስልኝ መሔጃዬ ሲደርስ እኔ ራሴ ሰዉ እልክብሃለዉ በልልኝ" ብለዉ መልአከ ሞትን ሸኙት፤ ሞትም ተመልሶ ሄደ፡፡
ከዓመታት በኋላ ብዙ ሰዉ ከሞተ በኋላ እንዲሁ እንደከዚህ በፊቱ የነፍሳቸዉን ደጅ ይጠፋል(ያንኳኳል)
"ማነህ?"
"እኔ ነኝ!"
"አንተ ማን ….  ስም የለህም?"
"መልዐከ ሞት ባለፈዉ መጥቼ የመለሱኝ"
"ታድያ ለምን መጣህ? አትምጣ እኔ ራሴ ሰዓቴ ሲደርስ መልዕክተኛ እልክብሃለዉ ብዩህ የለ?"
"አይ ይበቃዎታል፤ እርሶ እድሜ ልክዎትን ቢጠበቁ ጊዜዬ ደርሷል ብለዉ ሰዉ አይሰዱም ይልቅስ አሁን ይነሱ እና እንሂድ አላቸዉ"
እሳቸዉ ግን በፍፁም ሊሄዱ ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ መልዕክተኛዉም መልአከ ሞት እንደምንም ሊያግባባቸዉ ሞከረ፤ እሳቸዉ ግን አሻፈረኝ አሉት፡፡ ሞትም ቀረብ ብሏቸዉ
" እስኪ ይፍረዱ ፤
እርስዎ እያሉ እነማን ይሂዱ?" አላቸዉ ይባላል፡፡
አሁንም ስልጣንን መልቀቅ እና ሞትን የሚፈሩ ብዙዎች ናቸዉ፤ ሆኖም ግን መልዐከ ሞት እንዳለዉ እናንተ እያላችሁ እነማን ይሙቱ? እነማንስ ከስልጣን ይዉረዱ?
ጆሮ ያለዉ ይስማ! ልብ ያለዉ ልብ ይበል!

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...