እሑድ 22 ፌብሩዋሪ 2015

ሴት ሐዋርያ



ቤተክርስትያን በክርስቶስ ኢየሱስ ደም የተመሰረተች መሰረቶቿ ከዐለት እጅግ የጠነከሩ፡ ሐዋርያት ከዳር ዳር ተዘዋዉረዉ ወንጌልን በማስተማር ያፀኗት፡ ሰማዕታት ደማቸዉን አፍሰዉ አጥንታቸዉን ከስክሰዉ ያቆዩዋት፡ ደናግላን÷ መናኞች÷ባህታዉያን በገዳም ጤዛ ልሰዉ ድንጋይ ተንተርሰዉ ድምፀ አራዊቱን ፀበ አጋንንቱን ታግሰዉ በፆምና በጸሎት ያቆዩዋት  ቅድስት ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር ደጅ ነች፡፡ ከነዚህ ቤተክርስትያንን ለዛሬ ካደረሱት መካከል ሴቶች ከፊሉን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ ሴቶች (እናት፡ ሚስት፡ እህት፡ … ከመሆን ባሻገር ይልቁንም በአገራችን በኢትዮጵያ ትልቅ ተሳትፎ በሁሉም ስፍራ ሲያበረክቱ ይታያሉ፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የገጠሯ ሴት በብዙ ቦታ ጉልህ ድርሻ አላት፡ ልጅ ወልዳ አሳድጋ እድሜዉ ለአቅመ ትምህርት ሲደርስ እርሷ ሳትማር ልጇን ለትምህርት ያላትን ቋጥራ ከየኔታ ጋር ሰዳ ፊደል ቆጥሮ፡ መዝሙረ ዳዊት ደግሞ፡ ቅዳሴ ተምሮ፡ ቅኔ ተቀኝቶ፡ … ቤተክርስትያንን እንዲያገለግል ወይም እርሱም መፅሓፍ ዘርግቶ እንዲያስተምርና ተተኪ እንዲያፈራ የምታደርግ የቤተክርስትያን ባለዉለታ እና መከታ የሆነች ሴት ናት፤ ከዚህም ባሻገር የበረቱት እንደ እማሆይ ጀማነሽ ያሉቱ መፅሃፍ ዘርግተዉ ደቀመዛሙርት ሰብስበዉ አስተምረዉ የሚያስመረቁ ሴቶች አልታጡም ይህ ሰማአዕትነት፡ ሐዋርያነት ነዉ፡፡ በመፅሐፍ ቅዱስም ብዙ መልካም ስራን የሰሩ ለቤተክርስትያን ማገር ዋልታ የሆኑ ብዙ ተጠቃሽ ሴቶች አሉ፡ የሐዋርያትን ፍኖት ተከትለዉ ከጌታ እግር  ስር የተማሩ 36ቱ ቅዱሳን እንስት ሌላ ተጠቃሽ ሴቶች ናቸዉ፡፡
     ዛሬም ቤተክርስቲያን ልጆቿን የእግዚአብሔር መንግሥት የምታስወርስ የሴት ሐዋርያ ትፈልጋለች /ያስፈልጋታል/፡፡
ሴት፡- ስንል ሌላ ተዓምር ማለታችን አይደለም እግዚአብሔር በመልኩና በአርአያው በመጀመሪያ ከወንድ የፈጠራት ፍጥረት ማለት ነው፡፡ ሴት /ሔዋን/ የህያዋን ሁሉ እናት ከአባታችን ከአዳም የግራ ጎን በተፈጠረች ጊዜ የቤተክርስቲያን መጽሐፍት /ታሪክ/ እንደሚነግረን ስላሴ የሰውን ልጅ እንፍጠር ብለው በተመካከሩ ሰዓት አብና መንፈስ ቅዱስ አዳም ደካማ ባህርይ /የሚሳሳት/ ስለሆነ አንፈጥርም ሲሉ ወልድ እዋሰዋለሁ ብሎ ሊፈጠር ችሏል፤ ለዚህ ድካሙ ረዳት አጋዥ ትሆነው ዘንድ የተፈጠረችለት የመዳን የብርታት የጥንካሬ ሐዋርያ ሌላ ወንድ አልነበረም ሴት /ሔዋን/ እንጂ፤
          ዛሬም ደካማውን መሳት ያለበትን አዳም ልትጥለው ልትገረስሰው ምክንያተ ስህተት የምትሆንበት ሳይሆን
በደከመ ጊዜ ልታበረታው በወደቀ ጊዜ ልታነሳው በተፍገመገመ ጊዜ ልትደግፈው በአጠቃላይ ምክንያተ ድኅን የምትሆን ሴት ዛሬም ያስፈልገናል፡፡
          በብሉይ ኪዳን ባሎቻቸውን /ወንዶችን/ ሲራዱ ሲያበረቱ ከነበሩት መካከል ጥቂቶቹን መመልከት ሌላ ማጠናከሪያ ነው፡፡
ሣራ፡- እግዚአብሔር አምላክ አባታችን አብርሃምን ከእናትና አባቱ አገር እትብቱ ከተቀበረበት መንደር ተወልዶ ካደገበት ይልቁንም ከሸመገለበት ቄዬ ወደማያውቁም ወደ ባዕዳን አገር ማቄን ጨርቄን ሳይል ‹‹እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ›› ዘፍ 12÷1 ካለው ጊዜ አንስቶ እስከምትሞትበት ጊዜ ድረስ በደስታውም ይሁን በሐዘኑ ጊዜ በሰላም ከአባቶቹ ከዘመዶቹ አገር ከነበረበት እስከ ስደቱ ጊዜ ያልተለየችው ሴት ሐዋርያ ነበረች፡፡ ዘፍ 23÷1
ርብቃ፡- የአብርሃም ወንድም የናኮር የልጅ ልጅ የላባ እህት ናት የይስሐቅም ሚስት ከሆነችበት ጊዜ አንስቶ ዘፍ 24÷  መካንም በነበረች ጊዜ፣ የመካንነቷ ጊዜ አልፎ ያዕቆብንና ዔሳውን በወለደች ጊዜ ከዚያም ከባሏ ከይስሐቅ ጋር አረፍተ ዘመን ( ሞት )ገትቷቸው አባታቸው አብርሃም በገዛው መቃብር እስኪከተቱ ድረስ መልከ መልካም ትጉ ልበ ቆራጥ የሴት ሐዋርያ ነበረች፡፡ ዘፍ 49÷31
ራሔል፡- ራሔል ከላባ ሁለት ሴቶች ልጆች ታናሺቱ ናት፤ ያዕቆብን አግብታ ትዳርን ከመሰረቱበት ጊዜ አንስቶ መካን በነበረችም ጊዜ ብንያምንና ዮሴፍንም በወለደች ከዚያም መንትያ ልጆቿን በፈርኦን የግፍ አገዛዝ ከጭቃ ጋር በረገጠች ጊዜ ሞታም እስከምትቀበር ድረስ ከባሏ አጠገብ ያልተለየች ምክንያት ስህተት ያልሆነችበት ከግራ ጎኑ ተፈጥራ ውጋት ያልሆነችበት አጥንት ሆና ወጥታ ሴት ሆና እንዳልተፈጠረች አጥንተ ሰባራ አድርጋው ያላስቀረችዉ ጠንካራ ትዳርን አክባሪ ተልዕኮዋን በሚፈለገው ውጤት ድል ያደረገች የሴት ሐዋርያ ናት፡፡
 ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎችም አያሌ ሴቶች በዘመነ ብሉይ የነበሩ ለዛሬም ሴቶች አርአያ የሚሆኑ እናቶች ናቸው፡፡
          በአንጻሩም ደግሞ የወንዶችን ደካማ ጎን እያጠኑ ጥሩ ሰው በመምሰል እየቀረቡ ምክንያተ ሥህተት የሚሆኑ ብዙ ሴቶች ሞልተዋል፡፡ ዛሬ ድረስ ቤተክርስቲያንን እንደ አጋም ተጠግተው በጥፋታቸው እንደ ቁልቋል የሚያስነቧትና የሚያደሟት ጥቂት አይደሉም፤ ቤተክርስቲያን ግን እንዲህ አይነት ተኩላ ሳይሆን የናፈቃት ከመጥፎ ምግባሩ ታርሞ የሚመለስና በህይወቱ የጨለመውን የደከመውን የወንዱን ህይወት ብርሃንና ብርቱ የምታደርግ ሴት ሐዋርያ ትፈልጋለች፡፡ ስለሐይማኖታቸው ሲሉ ስለ እግዚአብሔር መንግስት ሲሉ ህዝብህ ሕዝቤ ንብረትህ ንብረቴ ሐብትህ ሐብቴ ሳይሆን አምላክህ አምላኬ ይሆናል በማለት የወንዱን ደካማ ጎን የምታበረታ አለሁልህ መከራህ መከራዬ ነው ስቃይ ድካምህ የኔም ጭምር ነው ደስታህም እንደዚያው የምትል ዛሬም ከማህሎን ባለቤት ከሩት የማትተናነስ ለዘመናት በመልካምነቷ ታሪክ እንዳይዘክራት የሚያግዳት ነገር አንዳች አይኖርም፡፡
ከዚህ ባሻገርም ሴትነታቸዉን ለበጎ ነገር ማዋል ሲገባቸዉ ለመጥፎ ነገር ያዋሉና ወንድንም ያሳሳቱ ቤተክርስትያንንም ያስመረሩ እንደ ደሊላ ያሉ ደሊላዉያን በዘምናችን እንደ እባብ ቤተክርስትያንን እንደካብ ተጠግተዉ (እባብ የሚናደፈዉ ካብ ተጠግቶ ነዉና) ምዕመናን የሚያስለቅሱ፡ ቤተክርስትያንን የሚመዘብሩ በርካቶች ናቸዉ፡-
ደሊላ፡- ኃያል ጀግና በእምነቱ ጽኑ የነበረውን ሶምሶንን ድል እንዲሆን ኃይሉንም እንዲያጣ ዓይኑንም እስኪያወጡት ድረስ ድካም እንዲሰማው ያደረገችው ሴት ናት የወደደችው ያፈቀረችው በመምሰል ሶምሶንን በመጠጋት ደካማ ጎኑን አጢና በፍቅር ወጥመድ ውስጥ አስገብታው በፍቅሯ ልቡ በተነካና አቅም ባጣ ሰዓት ድካም ተሰምቶት የርሷ ማበረታታት ማጽናናት በሚያሻው ሰዓት በመጣችበት ዓላማ ፍቅሩን ለመስዋዕትነት ወድቆ ለመቅረት ኃይልን ወደ ማጣት ክብርን ለመነጠቅ አሳልፋ ሰጠችው፡፡
          ዛሬም ብዙዎች ሴቶች እንደ ደሊላ ፍቅርን ሽፋን በማድረግ ሞትኩልህ አበድኩልህ እያሉ በቃላት በመሸንገል ከተዋደዱ ከተፋቀሩ ወዲያ ወንዱ ራሱን አሳልፎ ከሰጣቸው በኃላ ደሊላዊ ባህሪያቸውን የሚገልጡ በበጎች መካከል እንደሚመላለሱ ተኩላዎች የተናጣቂነታቸው ባህርይ የሚያይልበት ጊዜ ይቃረባል፡፡
          በአዲስ ኪዳንም እነ ቅድስት ኤልሳቤጥን የመሰለ /የካህኑ የዘካርያስ ባለቤት/ ለባሎቻቸው በቅንነት የሚታዘዙ መዋደዳቸውን በሚያብረቀርቅ ነገር ያለወጡ ከንቱ ነገር ሐዋርያዊ ጉዞአቸው ላይ ሳንካ ያልሆነባቸው የሴት ሐዋርያ ናቸው፡፡
          ዛሬስ የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሴቶች ሐዋርያነታቸው የፍቅር አተረጓጎማቸው የትዳርን አክባሪነታቸው እንዴት ይሆን? ያሉበት ጓዳ ይቁጠራቸው፡፡ ታምነው ፀንተው ያሉትን እግዚአብሔር ዋጋቸውን እጥፍ ድርብ አድርጎ ይክፈላቸው አለመታመን አለመጽናት ያየለባቸውን እግዚአብሔር ይሁናቸው መተላለፋቸውን ይደምስስላቸው፡፡
          ዛሬ ቤተክርስቲያን ሐዋርያ ሲያስፈልጋት በዓለም ጨለማነት ውስጥ ተመላልሶ ጨለማውን ብርሃን የሚያደርግላት ሰው ሲያሰኛት ክርስትናን በዕውቀት ሳይሆን በመኖር የሚያሳያት ሲያሰኛት አንድ እኔ ነኝ፣ አለሁልሽ የሚላት ሲጠፋ ከዚህ በላይ አንገቷን የሚያስደፋት ነገር አይኖርም፡፡
          ልጆቿ ከፀጋ እግዚአብሔር መራቆታቸው ሳያንስ ከእራፊ ጨርቅ እርቃነ ገላቸውን መራቆታቸው ቤተክርስቲያንን እጅግ ያሳዝናታል መሪር እንባንም እንድታነባ ያደርጋታል፡፡ የራሳቸዉ መራቆት ሳያንስ ለወንዱ ስንፈትና ዉድቀት በመሆን ከደሊላ ያልተናነሰ ምግባር ያላቸዉ ብዙ ሴቶች መንገዱን ሞልተዉታል፤ ኢትዮጵያዊ ባህልን አጉድፈዉ ሐይማኖትን ለማርከስ የተዘጋጁ ጥቂት አይደሉም፡፡ ለዚህ ሁሉ ምክንያት የሆኑት የትላንትና ለአገርና ለቤተክርስትያን ኩራትና ተስፋ የሆኑ እናቶች መጥፋት ነዉ፡፡ አንድም የዛሬዎቹ እናቶች (ሁሉን ማለቴ እንዳልሆነ ግምት ዉስጥ ይግባልኝ) ከልጆቻቸዉ የተሻለ ነገር ስለሌላቸዉ ነዉ፡፡ አንድም ከስሩ እቤት እቤት የሚለብሷት ቢጥሌ (እራፊ ጨርቅ) ሱቅም ሲላኩ እየለበሷት ሲወጡ ዝም ባይባሉ (ምነዉ እናቴ በእንቁላሉ ጊዜ በገረፍሽኝ እንደተባለዉ) ቢገሰፁ ኖሮ ለዚህ ለከፋ አለባበስና ጭን እየገለጡ ፡ጀርባን ባዶ አርጎ መሄድ ባልመጣ ነበር፡፡ ለወንድሞቻቸዉም መሰናክል ባልሆኑ ነበር፤ … ዛሬም አልመሸም፡፡ ምናለበትን ትተን ዛሬ እንደቀላሉ ያየነዉ ጥቂት ነገር ነገ እግዚአብሔር አያድርገዉና ጨርቅ የሚያስጥል ነገር ቢኖር የሚደርስና ሆስፒታል የሚወስደን አይኖርም እኛ ቀድመን አብደናልና እሷ ልማዷ ነዉ እንደምንባል አልጠራጠርም፡፡(ከዚህ ይሰዉረን)
          እግዚአብሔር ከከንፈራቸው ፍሬ ምሥጋናን ሲጠብቅ ደም የላሰች ውሻ መስሎ መታየት ያሳዝነዋል፡፡ ‹‹ለወይኔ ያላደረግሁለት ከዚህ ሌላ አደርግለት ዘንድ የሚገባኝ ምንድር ነው? ወይንን ያፈራል ብዬ ስተማመን ስለምን ሆምጣጤ ፍሬ አፈራ?...›› ኢሳ 5÷4 ያሰኘዋል፡፡ ታዲያ ምን ይሆን በመልካም ሥነ-ምግባር የታነፅን ልንሆን ሲገባን እንደ ቀደምት ሴቶች እናቶቻችን ሐዋርያነት ሲጠበቅብን ሐሳዊያን አሳች ሐዋርያት ሆንን? ምንስ ይሆን ድካም በሚሰማው ማበርታት በሚጠበቅብን ወንድማችን ፊት ገላችንን እርቃን አድርገን እንድንሄድ ያደረገን? ምንስ ይሆን የዝሙት ፆር በሚሰብቅ ገላችንን ተወጣጥረን እንድንሄድ የገፋፋን? ከማንስ የተማርነው የአለባበስ ባህል ይሆን እንብርት ድረስ የማይዘልቅ ጥብቆ እንድንለብስ ያደረገን? ከጭን ወረድ ያላላ ቀሚስ ያለበሰን?
እነሆ ዘመኑም ቀርቧልና መንሹም ተዘጋጅቷልና ስንዴዉን ከገለባ የሚለየዉ መልሶ ለፍርድ ሳይመጣ ዘይታችንን አዘጋጅተን መብራታችንን አብርተን ተግተንና ነቅተን እንጠብቀዉ፤ ኑ እናንተ የአባቴ ብሩካን …. ለመባልም እንብቃ፡፡ ተሰናክሎ ከማሰናከል ይሰዉረን፣ ከቀደሙት ንፁሐን እናቶች አንድነት ይደምረን፤ በረከታቸዉን ረድኤታቸዉን ያሳድርብን፡፡
ሐዋርያትን ዓለምን በወንጌል ማስተማር ያፀና፣ አባቶችና እናቶችን በገዳም ያፀና እኛንም በሃይማኖት በመልካም ስነ ምግባር ያፅናን፡፡ አሜን!
ይቆየን!!

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...