እሑድ 22 ፌብሩዋሪ 2015

ኦ! ቤተልሔም



ሰላምና ጤናን ዘወትር የምመኝልሽ ቤተልሄም እንደምን ሰንብተሻል አሁንም ደግሜ እላለሁ ሰላም ጤና ዕድገት ብልጽግና የእግዚአብሔር ቸርነት ካንቺ ጋር ይሆኑ ዘንድ የዘወትር ምኞቴና ጸሎቴ ነው፡፡
          የእንጀራ ቤት እያሉ የሚጠሩሽ ከኢየሩሳሌምም በስተደቡብ 10ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኚ እነ ቢታንያ÷ ቁምራን÷ ኬብሮን… የሚያዋስኑሽ የአባቶቻችን አምላክ ልዑለ ባህርይ ቅዱስ እግዚአብሔር የሚለመንባቸው የያዕቆብ የሥጋው ቁራጭ የአጥንቱ ፍላጭ የደሙ ምጣጭ /ሚስት/ ዐረፍተ ዘመን ሲገታት መዋቲ ሥጋዋ ግብዐተ መሬት የተከናወነብሽ ቅድስት ሀገር፤
          በመሳፍንትም ዘመን የኢብዳንና የቦዔዝ÷ የሩት የእሴይና የዳዊት ከተማ የነበርሽ÷ ልዑል እግዚአብሔር "እንደ ልቤ የሚሆን የእሴይን ልጅ አገኘሁ" የተባለለት÷ ንጉስ ዳዊት በነቢዩ ሳሙኤል የተቀባብሽ፣ ነቢያት ትንቢት ተናግረው ይወርዳል፣ ይወለዳልም በማለት ሱባኤ ገብተው መድህኒዓለም ክርስቶስ የተወለደብሽ፤ በመወለዱም እረኞቹ በኋላም ስብአ ሰገል መጥተው የጎበኙሽ ጌታንም ሲያገኙ ያመሰገኑብሽ÷ተድላ ደስታ የተፈፀመብሽ ሰውና መላዕክት በአንድነት ህብረት የፈጠሩብሽ÷ በአንድ ቋንቋ በአንድ ዜማ አምላከ አማልክት የሆነ ጌታን ያመሰገኑብሽ÷ ቤተልሔም ዛሬን እንደምን ደረስሽ? እድሜያቸው ሁለት ዓመት ያልሞላቸው ህፃናትን ሄሮድስ ባያስፈጃቸውና ደስታው ወደ ሃዘን ባልተለወጠና በጉያቸው ህፃን ታቅፈው የሰነበቱ እናቶች የሃዘን ፍም በማህፀናቸው÷ የሐዘን በትር ጀርባቸውን÷ የሃዘን ሰይፍ በጉያቸው ተሰንዝሮ ሃዘንን ባያከናንባቸው ኖሮ ምንኛ ደስ ባለ፤ አንቺ ቅድስት ሃገር ቤተልሔም ዛሬስ መንደሮችሽ፣ ጉድባዎችሽና አደባባዮችሽ ሐዘን ነው ደስታ የተንሰራፋባት? ነገሥታትና መኳንንቶችሽስ እንደምን ሰንብተዋል? እንደዚያኔው ‹የመጥረቢያ ልጅ መዘለፊያ› እንዲሉ የሄሮድስ የልጅ ልጅ ይሆኑ? ወይስ?...  ሕዝቦችሽስ እንደምን ናቸው? ከብቶችሽስ?
          መልአኩ የዳዊት ከተማ በሆንሽ በቤተልሔም በከብቶች በረት በግርግም መወለዱን ለመልዓክ ፍራት ማራቅ ልማዱ ነውና ‹‹አትፍሩ›› እያለ ታላቅ የምሥራችን ‹‹እነሆ ለሕዝብ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና›› ሉቃስ 2÷10-11 በማለት የተናገረ መልዓክ ዛሬስ እየመጣ ሕዝቦችሽን ከፍርሃት ያድናቸዋል? የምስራችን ያበስራቸዋል?
ሕዝብሽስ መልዓኩን እንደምን ይቀበለዋል? አግልሎታል ወይስ ተቀብሎታል? የተወለደውንስ ህፃን ዛሬም እንደ ህፃን /እንደሰው/ ምድራዊ ንጉስ ነው ብሎ ነው እየተቀበለ ያለው ወይስ ፈጣሪ፣ አምላክ፣ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አምኗል? ወይንስ እያሳደደው ይሆን? ዛሬም ሕዝቦችሽ ከእንስሳት አንሰው የምስጋና ትንፋሽ ነስተውት ፍጡር ነው ብለው አምላክነቱን ዘንግተዉ ይሆን? ሰብዐ ሰገል አገር አቋርጠው ባህር ተሻግረው በመምጣት ወርቁን ለመንግሥቱ፣ ዕጣኑን ለክህነቱ፣ ከርቤውን ለሞቱ እንደቃየል ምራጩን ሳይሆን ንፁሐ ባህርይ ነህ ሲሉ ንፁሁን አምጥተው ሲገብሩ፡ እንደተኙቱ ዛሬም እንዳንቀላፉ ናቸውን?
          የነገሥታት÷ የመኳንንት ፣የእረኞች አገር እንግዳ ተቀባይቱ ደገኛይቱ አገር ቤተልሔም ሆይ አሁንም የመድኃኒዓለም ክርስቶስ ሰላም መጎብኘት ፍቅር ካንቺ ጋር ይሁን፡፡
          ስምን መልዓክ ያወጣዋል ይላሉ አባቶቻችን ድሮ ድሮ ሲናገሩ ለዛሬው ልጅ ቢቢ፣ ቲቲ፣ ጢጢ ….. እያለ የሚያወጣው /የፈረንጅ ውሻ ሥም/ ማን እንደሆነ የተረጋገጠ ነገር ባይኖርም፡፡
          ዛሬም ሥም አጠራራቸውና ግብራቸው መገናኘቱን ባናውቀውም ሥማቸውን ‹‹መልአክ›› ያወጣላቸው የሚመሥል ብዙ ሥሞች በምድራችን ሞልተዋል ውቃው÷ ደብልቀው÷ ድፋባቸው ÷ሽናባቸው÷ ሽመክት ÷ሽመልስ÷ ጥላዬ ….. እየተባሉ የሚጠሩም ደግሞ በአንፃሩ አልታጡም ይህንን ደግሞ ማንኛው መልዓክ ይሆን ያወጣላቸዉ? የብርሃን ወይስ? ………
          ብቻ ምናገባን ከሥሙ ምን ገዶን ከግብሩ እንጂ ሥም ቢወጣልንስ ቢውልበት አያመሹበት መሐል ፒያሳ ዳንኤል የተባለው ቦሌ ሲደርስ ዴቪ ሚክያስ የተባለው ሚኪ ወዘተ መባሉ ተለምዷል ኢንባሲ ግቢ የመግባት እድሉ ካጋጠመ ክርስትያኑ (አብደላ ÷መሐመድ….. ፋጡማ፣ ዘይነባ …. ) ሙስሊሙም እንዲሁ እንዳይል የሚያግደው የአባት እዳ /ሃይማኖት/ ስለሌለ እዳው ገብስ ነው፡፡
          ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል ይባል የለ? ስለዚህ እርሱን እንተወውና ሥማቸው ቤተልሔም እየተባለ የተሰየመላቸው ግብራቸው ‹የእንጀራ ቤት› ከተባለችው ከቤተልሔም ጋር ምን ያህል ቀረቤታ ሥምምነትና የጋራ የሆነ ግብር ይኖራቸው ይሆን?
          እኔ ነገር አላበላሽም ከሰውም ጋር አልቀያየምም ፍርዱን ሥሙን ላወጣላቸው መልዓክና በቤተልሔም ለእረኞች ፍርሐትን ላስወገደላቸው የምሥራችንም ለነገራቸው ከሰው ጋር ‹‹ሥብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብዕ÷ ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ›› በማለት ላመሰገነው መልዓክ ትቼዋለሁ፡፡
          ግና መልዓኩ በማያውቃቸው ወይ መልዓኩን በማያውቁ መካከል ፍርድ እንዲሆን በይነሃልና ፍርድ ይገባሃል የሚለኝ እንዳይኖር እፈራለሁ፡፡ ቢሆንም ግን እውነት ይዘገያል እንጂ እንዳይከስም እንዳይጠፋ እኔም ያሉትን ይበሉ እንጂ ከመናገር ወደኋላ አልልም፡፡
          ዘመኑ የኢንፎርሜሽን ስለሆነ ደግሞም ‹‹እንግዲህ እስከ ቤተልሔም ድረስ እንሂድ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንይ ተባባሉ›› ስለሚል እኔም አዲስ ነገር ምን እንዳለ ወደ ቤተልሔም ልሒድ፡፡
          ‹ቤተልሔም› ስል በተናጠል እንዳልተጣራሁ ይታወቅልኝ ቤተልሔም እየተባልን ዛሬ ባንጠራ ከሥሙ ማማር ከፊደሉ አጣጣል የተነሳ ሁላችንም ብንሆን ሆኖልን ቤተልሔም ተብለን በተጠራን ብለን ሳንመኝ አልቀረንምና ሁላችንንም ቤተልሔም ብያለሁ ማዳላት እንዳይሆንብኝ አንድም ከልጅ ልጅ ቢለዩ የሚለው ተረት እንዳይፈፀምብኝ፡፡
‹‹አንቺ ቤተልሔም ኤፍራት ሆይ÷ አንቺ ከአእላፋት መካከል ትሆኝ ዘንድ ታናሽ ነሽ÷ በአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ በእስራኤል ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል›› ሚክ 5÷2
        ነቢዩ እንዲህ ብሎ የተናገረው በቤተልሔም አንፃር ሲያልፍ ሲሆን በነቢዩ ዳዊት ጊዜ የተከበረች ስፍራ እንዳልነበረች ሁሉ እርሱ ሲያያት ግን ሥም አጠራሯ ጠፍቶ ውበቷ ከስሞ በዳዋና በጥሻ ተሞልታ ከተማዋ ተፈትታ ሲመለከታት ዛሬ መጎስቆሏን ነገ ግን መድኅኒ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚወለድባት ተመልክቶ የተናገረው ነበር፡፡
          ቤተልሔም ጌታችን በተወለደ ጊዜ እንስሳት ትንፋሻቸውን የገበሩበት፣ ስውር መላዕክት በአንድነት የዘመሩባት ሰብአ ሰገልን ይመራቸው የነበረው ኮከብ የቆመበት ቅድስት ከተማ ናት፡፡
          ትናንት ከትናንት በስትያ አምሮብን ደምቆብን ሰው መስለን ሰው አክለን የነበርን ሃይማኖት ከምግባር ተዋህዶልን የኖርን ሥማችንና ግብራችንን ሰዎች ተመልክተው ሥምን መልዐክ ያወጣዋል የተባለልን ዛሬስ እኛ ማንነን? ትላንት የተመለከቱን ዛሬ ደግመው ቢጎበኙን እንዴት እንገኛለን ያዝኑብን ወይስ ይኮሩብን ይሆን?
          ‹‹ሰው ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም እንስሳትን መሰለ›› እንኳን ቢባልብን ቅሉ ክቡር እኮ ነበርን፤ ታናሽ ስንሆን ታላቅ እኮ ነበርን፡፡ ምንም እንኳ ኃጢአት ቢያጎሳቁለን፣ ምንም እንኳን የምንሰራው ሁሉ ለታይታ ቢሆን እግዚአብሔር መርጦ ወዶ የለበሰውን ክቡር ሥጋ የለበስን፣ በእግዚአብሔር አርአያና አምሳያ የተፈጠርን ነበርንኮ ዛሬ ማመን መታመን ከኛ ቢርቅ ቁም ነገር ቢጠፋ በክርስቶስ ኢየሱስ ክርስቲያን የተሰኘን እርሱ ባርኮ ቀድሶ በወጠነልን መንገድ የምንጓዝ ነበርን፤ ዛሬ ወዴት ነን? እንደ አባታችን አዳም ወደ ጥሻ ወደ ጉድጓድ ወደ ጥፋት ወደ ክህደት … ይሆን? ለመጥፋታችንና ለመዳናችን ምክንያት እንሻ ይሆን? አዳም ሆይ ወሬት ነህ? እንደተባለ እኛ ብንጠራ ከወደየት ይሆን መገኛችን?
ጫት ቤት?
ሽሻ ቤት?
መጠጥ ቤት?
ከአመንዝራዎች ጉያ?
መተተኞች ዘንድ?
ጉቦ የሚቀበሉና/የሚሰጡት ደጅ?
ነፍሰ ገዳዮች አምባ?
ወዴት ነን!?
          እንደሆነ መድኃኒዓለም ክርስቶስ በሞቱ ሞታችንን በስቃዩ ሥቃያችንን አስወግዶልን ርስት መንግሥተ ሠማያትን አውርሶናል በገነት ኑሩ ተብለናል፤ ታዲያ ማንን ይሆን እንደ አዳም ‹‹ይህቺ የሰጠኸኝ ሄዋን አሳሳተችኝ›› የምንለውን ከዚያች አገር ከቤተልሔም የአለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደወጣ እንደተገኘ ከኛስ ‹ክቡር› ከተባልነው ከሰው ልጆች ምን ይገኝ፣ምንስ ይወጣ ይሆን? ሕይወት ወይስ ሞት? ለኛ ለራሳችንስ በውኑ መልካም ነገር ይገኝ ይሆን?
          ከቤተልሔም የወጣው አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ ዘላለማዊ ነው እኛስ ‹ሐሳባቸው ምድራዊ› እንደተባለው ሐሳባችን ምድራዊና ጊዜያዊ ነው? ‹ክብራቸው በነውራቸው› እንደተባለው ክብራችን በነውራችን ይሆን?
ስመአጠራራችንን ያጎደፈ ዉሎአችንን አቅንተን ምግባራችንን ለዉጠን መወቃቀሻ ሳንሆን ምሳሌ ለመሆን ያብቃን!
አሜን!
ይቆየን፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...