እሑድ 22 ፌብሩዋሪ 2015

ዋጋ ሲተመን!




ሰዉየዉ ቤታቸዉን ለመሸጥ ቆርጠዉ ተነስተዋል፤ የመንደሩ ሰዉና ደላላ ከጠዋት የእርሳቸዉን ቤት መሸጥ መነጋገሪያ ከማድረጉ ባሻገር የማሻ ልመንህ ዋጋዉን ጣሪያ ማስነካት ገዢዎችን ከስፍራዉ ዝር እንዳይሉና ቤቱን እንኳን መግዛት ማየት እንዳይችሉ አድርጓቸዋል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን በዕድሜ ጠና ያለ ሰዉ መጥቶ ደጅ ይጠፋል(ያንኳኳል) የቤቱ ጠባቂም ደጁን ይከፍትና ማንን ፈልገዉ እንደሆነ ይጠይቃቸዋል፡፡ የቤት ገዢ መሆናቸዉን እና የቤቱን ባለቤት (ሚስትየዉን ) እንደሚፈልጉ ይነግሩትና ይጠራላቸዋል፡፡
ሁለቱ ሰወች ስለቤቱ ጥሩነት ግቢዉም ሰፊ መሆኑን ነገር ግን ዋጋ እጅግ ዉድ እንደሆነ አዉርተዉ ገዢዉ ሴትዬዋን ለባለቤታቸዉ ዋጋዉን እንዲቀንሱላቸዉ አደራ ጭምር ነግረዉ ይሄዳሉ፤ ሚስትም ቀን እንደተባሉት አባወራ ወደቤት ሲገቡ የእግር ዉሃ  አቅርበዉ እግር እያጠቡ (ጊዜዉ እንደዛሬ የሴቶች እኩልነት ባልነበረበት ሰዓት /ፍቅር እንዲህ ዝቅ ብለዉ የሚገልፁበት ወቅት/ ወንዶች የበላይ ነን ብለዉ የሚመኩበት ዘመን/ ነበር) ቀና ይሉና ባሻዬ ዛሬኮ አንድ ሰዉ መጥቶ ቤቱን እንደሚሸጥ ጠየቀኝ እኔም እንደሚሸጥና እርሶ የሚሉትን ዋጋ ነገርኳቸዉ፤
ምን ማለት ነዉ " አንተ የምትለዉን "ማለት አንቺስ የቤቱ ባለድርሻ አይደለሁም ነዉ ወይስ ነገሩ እንዴት ነዉ?
"ማለቴ" እያሉ ቀጠሉ ሴትዮዋ ፈራ ተባ እያሉ " ሰዉየዉ እንዳሉት ዋጋዉ ትንሽ ወደድ ብሏል ለማለት ፈልጌ ነዉ"
አንቺ ሴትዮ በጤናሽም አይደለሽ? አንዴ አንተ እንዳልከዉ፣ አንዴ ደግሞ ሰዉየዉ እንዳለዉ የሚያሰኝሽ ምንድን ነዉ? ገዢ ነሽ ሻጭ?
እህ እንደዛ አላልኩም እርሶም ያሉት ዋጋ እንኳን ለገዢነት ለሻጭም ጥሩ አይደለም ይወደዳል እዚህም እንደሆነ ይህን ያህል ዋጋ ያወጣ ቤት ስላላየሁ ነዉ እንደዛ ማለቴ ሰዉየዉም ሲያዩዋቸዉ ገዢ ይመስላሉ ስለዚህ የሚሉትን ቁርጥ ያለ ዋጋ ይንገሩዋቸዉና እንሽጥ ለማለት ነዉ፡፡
እንግዲህ እኔ ያልኩትን ብያለሁ! የሚገዛ ከመጣ እንሸጣለን አለበለዚያ ቤታችን ከእኛ ጋር እነሱም ገንዘባቸዉ ከራሳቸዉ ጋር ምን ያጋጨናል ገዢ ከጠፋ እኛዉ እንኖርበታለን ምን አስጨነቀን ባዶዉን አይሆን፤
ካሉ ጥሩ! ብለዉ ሴትዮዋ እግር አጥበዉ እንደጨረሱ እራት አቅርበዉ በልተዉ ከጨረሱ በኋላ ወደ መኝታ ሄዱ፡፡
ሌላ ቀን ደግሞ የሁነ ሰዉ እንዲሁ መጣ! ዋጋ ተነጋገሩ ሳይስማሙ ቀሩ ሄደ!
በሌላኛዉም ቀን ብዙ ሰዎች መጡ ሳይስማሙ ቀርተዉ ተመልሰዉ ሄዱ!
አንድ ቀን ግን የመጡት ሰዉ አጥብቀዉ ተከራከሩአቸዉ ገዢም እንደሆኑ አስረግጠዉ ነገሩአቸዉ፤ ባለቤትየዉም እንድዲህ ቤቱን ከወደዱት ገንዘብ መያዝ ሳይሆን ወጣ አድርጎ መግዛት ነዉ እያሉ ከረር ብለዉ ተናገሩ፡፡ ሰዉየዉ እንዲቀንሱላቸዉና ቀብድም ሰጥተዉ ሊሄዱ እንደሚፈልጉ ቢነግሯቸዉ ሻጭ አሻፈረኝ አሉ፡፡
ከገዢ ጋር የመጡት ሰዉ ሁለቱን ለማስማማት የተወሰነ ሙከራ አደረጉ ግን ሰሚ አላገኙም፤ ሻጭ ይልቅስ የምተገዙ ከሆነ በደንምብ ዙሪያዉን እዩት፣ የግቢዉንም ስፋት ተመልከቱት፣ ካርታዉም በጄ ነዉ፣ ደግሞ በዚህ ላይ እዚህ ግቢ ዉስጥ ያለ አትክልት አመቱን ሙሉ ገበያ አያስመኛችሁም ከጊቢዉ ዞርዞር ብላችሁ ብትመለከቱ የምታጡት ነገር የለም፡፡ይልቅስ ንትርኩን ትተን ተስማምተን እናንተም ቤታችሁን ዉሰዱ እኔም የሚደርሰኝን ነገር ስጡኝና ወደሚሄድበት ልሂድ በማለት ነገሩን ቋጩት፡፡
ገዢ የሚለዉ ቢጠፋዉ "ለመሆኑ ዋጋዉ እንዲህ ጣሪያ የነካዉ ይሄ ቤቴ (ሊገዛዉ እንደሆነ ሲወስን ነዉ ቤቴ ማለት የጀመረዉ) የተለየ ከሌላዉ ምን የተለየ ቢኖረዉ ነዉ?" ብሎ ጠየቀ፤
ምን ቀረዉ ሰፊ መሬት አለህ፣ ይህን የሚያክል ትልቅ በዚህ ግቢ ላይ የተንጣለለ ቤት አለዉ፣ የአትክልቶቹን ነገር አታንሳዉ ይህ ሁሉ ተደምሮ ብለዉ ድምር ዋጋዉን ነገሩት፤
"የተቀረዉስ ገንዘብ?" ገዢ ጠየቀ
የተቀረዉማ ሰፈሩን እንደምትመለከተዉ ጥሩ መኖሪያ ነዉ፣ አየሩንም ልብ ብለህ ካየኸዉ ጤና ነዉ! እነዚህም የየራሳቸዉ ዋጋ አላቸዉ ብለዉ ዋጋቸዉን ነገሩት፤ አሁንም ሂሳቡን ቢያሰላዉ ዋጋዉ እኩል አልመጣም " የቀረዉስ?" አላቸዉ
"የቀረዉ ደግሞ በሶስቱም ማዕዘን ያሉ ጎረቤቶችህ ዋጋቸዉ ከቤቱ በላይ ነዉ ሰወች እንዳይመስሉህ  አብረሃቸዉ መኖር ስትጀምር እንዲያዉም ከመላዕክት ጋር የተጎራበትክ ነዉ የሚመስልህ እነሱም በዚህ ቤት ዋጋ መጨመር ላይ ትልቅ ድርሻ አላቸዉ፡፡እንዲያዉም እንዳልጎዳህ ብዬ ነዉ እንጂ ያንሳቸዋል! ያንሳቸዋል፤ የጎረቤቶችህ ዋጋቸዉ የሶስቱንም ደምሬ በቤቱ ላይ 200 መቶ ሺ ብር ጨምሬበታለሁ ጠቅላላዉን ስትመታዉ (ሰትረደምረዉ) ልክ አይመጣም?"
ይመጣል!
"እና ያተረፍኩብህ ነገር አለ?"
የለም!
"በል እንግዲህ የምትገዛ ከሆነ ይኸዉልህ ቤቱ ፡የማትገዛ ከሆነ ደግሞ…."
አላስጨረሳቸዉም ለቀብድ የሚሆን በእጁ የያዘዉን ጥሬ ገንዘብ ሰጥቶ ነገ ተመልሶ አጠናቆ እንደሚከፍል ተናግሮ እየተገረመና እየተደመመ ከስፍራዉ ጠፋ፡፡
ሁላችንም የምንፈልገዉ እና የጎደለብን እንዲህ አይነት ቤት እና ሰፈር ነዉ፤ የገዛናቸዉና የሸጥናቸዉ ቤቶች የህን አሟልተዉ ይሆን?
ምንደሮቻችንስ ዝም ብለን በዘልማድ ስንኖርባቸዉ ስለኖርን ነዉ ወይንስ እዉነት መኖሪያ ሰፈር ናቸዉ? ልጆች አድገዉ ለቁምነገር የሚበቁበት ናቸዉ?ጎረቤቶቻችንስ፣ እኛስ ብንሆን ለጎረቤትነት ብቁ ነን? ለኛ ዋጋ ቢወጣልን ዋጋ እናወጣለን ይሆን ወይስ ኪሳራ?

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...