"አቤቱ የሆነብንን አስብ" ሰቆቃው ኤርሚያስ 5 : 1
ኢትዮጵያ እንደ አገር ሕዝቦቿም እንደ ሕዝብ በአራቱም አቅጣጫ ያልሆነባት ነገር የለም። ሕዝቦቿ አንዱን መከራ ተሻገርን ሲሉ ሌላ መከራ ይደቀንባቸዋል።
የተፈጥሮ ሲባል ፣ ሰው ሰራሽ ፣ ሰው ሰራሹን አለፍን ሲሉ ሌላ ይደቀናል።
ወደ መንግስት ጮኽን ወደ አንተ አንጋጠጥን መልስ አላገኘንም። አቤቱ እባክህ ቸሩ ሩህሩህ ይቅር ባይ አምላካችን ሆይ የሆነብንን አስብ።
• ሴት ልጅ እስከ ጽንሷ ተገድላ ከሜዳ ላይ ተጥላለች፣
• ህጻናት ያለወላጅ ቀርተዋል፣
• አባት በሚስቱ እና በልጆቹ ፊት ተገድሏል፣
• ልጃገረዶች ተደፍረዋል፣
• ወጣቶች ተሰደዋል ተገድለዋል፣
• የሰው ልጅ እንደ እንስሳ ተቆጥሯል፣
• አሟሟታችን ከእንስሳት አንሷል፣
• ተገድለን ቁልቁል እየተሰቀልን፣
• ሞተን መቀበር ቅንጦት ሆኗል፤ አቤቱ የሆነብንን አስብ።
• በአሕዛብ ፊት መሰደቢያ ሆነናል፣
• የመገናኛችን ቤተመቅስ ተቃጥሏል አጥር ቅጥርህ ተደፍሯል፣
• አምላኬ ሆይ፥ በፊትህ የምንለምን ስለ ብዙ ምሕረትህ ነው እንጂ ስለ ጽድቃችን አይደለምና ጆሮህን አዘንብለህ ስማ፤ ዓይንህን ገልጠህ ጥፋታችንና ስምህ የተጠራባትን ከተማ ተመልከት። አቤቱ፥ ስማ፤ አቤቱ፥ ይቅር በል፤ አቤቱ፥ አድምጥና አድርግ፤ አምላኬ ሆይ፥ ስምህ በከተማህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቶአልና ስለ ራስህ አትዘግይ።" ትንቢተ ዳንኤል 9 : 16 - 19
እስላም ክርስቲያኑ በአንድነት ጸሎት አውጆ ከፊትህ ተንበርክኳል ወደ አንተ ይጮዃል ያነባል። አቤቱ የሆነብንን አስብ።
ረሐብ ቸነፈር በሽታ አንበጣ ጦርነት ስድት በዚህ ያልጠና ሰውነት እንዴት ይቻለናል?
ስለህጻናቱ ስትል ማረን፣ ጤዛ ልሰው ድንጋይ ተንተርሰው ስለሚማልዱት ብለህ ማረን፣ በጾም በጸሎት በፊትህ በአንድነት ስለወደቁት ብለህ ማረን፣ ይልቁንም ከሴቶች ሁሉ ስለተለየችው ጸጋን ስለተሞላችው ቅድስት ድንግል ማርያም ስትል ማረን፣ ስለአለሙ ሁሉ ስትል በቀራንዮ አደባባይ ስለቆረስከው ስጋህ ስላፈሰስከው ደምህ ብለህ ማረን ይቅርም በለን።
የሰው ልጅ ወደ ልቡ ይመለስ ዘንድ በዘር ከመከፋፈል ይልቅ ከአንድ አዳም መፈጠሩን ያስብ ዘንድ ሁሉም አንድ መሆኑን የቋንቋው እንደ የቀለሙ መለየት ልዩነት እንዳያደርግ በዚህም ተከፋፍሎ እንዳይተላለቅ እባክህ ፍቀድ።
በሽታውን አስታግስልን፣
ለነፍሰ ገዳዮች ልብ ስጥልን፣
የተጨነቁትን ልባቸው የተሰበረውን አካላቸው የጎደለውን አጽናናልን፣ ነፍስ ከሥጋቸው በክፉዎች ያለፉትን ማረፊያ በአንተ ዘንድ አዘጋጅላቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ፍጹም መጽናናትን አድልልን።
አቤቱ የሆነብንን አስብ።
ቤተመቅደስ ሲቃጠል ግድ ይበልህ።
እኛ ቤተመቅደሶችህ ስንገደል ግድ ይበልህ።
በስም የተጠራን ልጆችህ እረኛው እንደተመታ መንጋ ስንበተን፣ ስንሳደድ ግድ ይበልህ።
እንባችን በላያችን ደርቋልና በግፍና በበደል ደማችን በከንቱ ፈሷልና የምህረት ዐይንህ ወደኛ ይመልከት።
አቤቱ ሆይ ፥የሆነብንን አስብ።
አሜን።
ይቆየን።
የእለት ተለት ጽሑፎቼን ለመከታተል ከዚህ በታች ባሉት ሁሉ እገኛለሁና ይከታተሉኝ። ከተመቸዎት ለሌሎች ያጋሩት።
My Facebook page link (በፌስቡክ ገጽ እንገናኝ)
https://www.facebook.com/deresse2020/
Main facebook account (ዋናው የፌስ ቡክ ገጼ ይቀላቀሉት)
https://www.facebook.com/DeresseReta
Follow me through telegeram (በቴሌግራም ሊከታተሉኝ ከፈቀዱ) ሁሉም ምልከታዬን የማጋራባቸው ማህበራዊ ድረ ገጾች ናቸው።
https://t.me/deressereta
ከአሥር አመት በላይ ከ50ሺ በላይ አንባቢዎች ያሉት መጦመሪያም አለ።
www.deressereta.blogspot.com
https://anchor.fm/deresse-reta/episodes/ep-ev5j5o