" እነዚህን ነቢያት እኔ አላክኋቸውም "
ትንቢተ ኤርሚያስ 23 : ከቁጥር 9 ጀምሮ ብናነብ እግዚአብሔር በሐሰተኞቹ በሰማሪያ ነቢያት ምን ያህል እንደተማረረ እንመለከታለን። እነዚህን ነቢያት እኔ አላክኋቸውም እስኪል ድረስ።
ወዳጄ ብዙ ሰው ያውቅህ ይሆናል፤ ታዋቂነትህም ከአገር አገር የናኘ ሊሆን ይችል ይሆናል። ብዙ ተከታዮችም ይኖርህ ይሆናል። በዚህም የተነሳ ክብርህ ጥግ ደርሶ ሊሆን ይችላል።
ነገሮች ሁሉ ተቃንተውልህ የትናንት ሕይወትህ ተቀይሮ ሊሆን ይችላል። የመርገም አንደበትህ የምርቃት፣ የውሸት አንደበትህ የእውነት የሆነውን ቃል ትጠቅስበት ይሆናል፣ የድህነት ታሪክህ በባለጸግነት፣ ማይምነትህ በአዋቂነት ሥም ተተክቶልህ ሊሆን ይችላል፣ የትናንቱ እግረኛ ዛሬ የዘመናዊ መኪና ባለቤት ሆነህ ሊሆን ይችላል፣ በአጠቃላይ ታሪክህ ተቀይሯል።
ስለ እውነት አንተ ተቀይረሃል?
ባለጸጋ ስትባል ነፍስህን አላጎደልካትም?
ለሌሎች የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ወተት ስትግት አንተ ግን ቃሉን አልተጠማህምን?
ምድራውያን ሰወች ሲያከብሩህ ዋጋህን በምድር ስትቀበል በሰማይ ያለውን የአባትህን ዋጋ አልተነጠክም?
ነብይ ነኝ ስትል፣ ሐዋሪያ ነኝ ስትል፣ ወንጌላዊ ነኝ ስትል፣ አገልጋይ ነኝ ስትል፣ አጥማቂ ነኝ ስትል፣ ባህታዊ ነኝ ስትል፣ ወዘተ ብዙዎች ሁሉን ትተው ተከትለውህ አደባባዮችህ ደምቀው መድረኮችህ ጠጠር መጣያ እንኳን ጠፍቶ ሊሆን ይችላል። ወዳጄ በእግዚአብሔር ዘንድ እንደ አለመታወቅ አሳፋሪ ነገር የለም።
እግዚአብሔር በሚያውቅህ ልክ እንጂ ዋጋህን የምትቀበለው በታዋቂነትህ ልክ አይደለም።መድረክህ ስትይዝ የእግዚአብሔርን ቃል ጠንቅቀህ ማወቅህ እንጂ ታዋቂነትህ ለአድናቆትህ ሽፋን እንጂ የሚሆንህ ለመዳንህ ምክንያት አይሆንህም።
እነዚህን ነቢያት እኔ አልላኳቸውም እንደመባል አሳፋሪ ነገር የለም። አንተ ከየትኛው ነህ?
ወዳጄ አንተ የምትከተለው "አገልጋይ" ከየትኛው ወገን ነው? ተከታዮቹ ስለበዙ መድረኩ ስለደመቀ፣ ድምጹ ነጎድጓዳማ ስለሆነ፣ የልብህን መሻት ስለሚነግርህ፣ ስለማይገስጽህ፣ ወይንስ የእግዚአብሔር አገልጋይ ስለሆነ ነው?
• 2ኛ ቆሮንቶስ 11 : 13
" እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ፥ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች ናቸውና። "
ስለሚልባቸው በእነርሱ ላይ ያለው እናንተ እየተከተላችሁት ያለው መንፈስ የትኛው እንደሆነ መርምሩ " መንፈስን ሁሉ አትመኑ "ይላልና።
• 2ኛ ጢሞቴዎስ 3 : 1- 6
ነብያትን ነን እያሉ ምእመናንን የሚያስጨንቁ፣ ሐብትና ንብረትን የሚነጥቁ፣ ሴቶችን ከክብራቸው የሚያነውሩ፣ ቃለ እግዚአብሔርን ቁጭ ብለው ሳይማሩ ቆመው የሚያስተምሩ፣ ርኩስ መንፈስ የሚጫወትባቸው ናቸው።
ገንዘብን ከመውደዳቸው የተነሳ የማያደርጉት ነገር የለም፤ ትእቢተኞች እና ተሳዳቢዎች ናቸው። ክብራቸው በነውራቸው ሐሳባቸው ሁሉ ምድራዊና ብልጭልጩ አለም የሆነ። ጽድቅን በምድራዊ ስኬታቸው የሚያወዳድሩ ከንቱዎች ናቸው።
የእግዚአብሔርም ቃል ከነዚህ ራቁ ይለናል። ተከታዮቻቸው ግን ብዙ ናቸውና የተቀሩትም የተከታዮቻቸውን ብዛት ተመልክተው ይከተሏቸዋል።
ጠማማ ትውልድ ምልክትን ይሻልና 'ድንቅ ተአምር' እናያለን፣ 'ፈውስ' እናገኛለን፣ በማለት በሐሰት ትርክታቸው ተታለው እዚያው ይቀራሉና ከነዚህ ደግሙ ራቁ ለማለት እወዳለሁ።
" ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ። "
ሐሰተኛ ነቢያት እንደመኖራቸው መጠን እውነተኞች መኖራቸው እሙን ነው። ቃሉም ስለ እውነተኞቹ ነቢያት ሲናገር እናያለን ኤርሚያስ 1 : 5 እና ሕዝቅኤል 3 : 17 እንዲሁም የሐዋርያት ሥራ 9 : 15 ላይ ይመሰክርላቸዋል።
ከእናታቸው ማህጸን ጀምሮ የተመረጡ እንዳሉ የተለያየ አገልገሎትም እንደሰጣቸው ለሕቡም ጠባቂ እንዳደረጋቸው እናያለን።
ነቢዩ ኤርሚያስ ግን በእግዚአብሔር ተገብቶ እንዲህ እያለ ይናገራል።
" እኔ ሳልልካቸው እነዚህ ነቢያት ሮጡ፤ እኔም ሳልነግራቸው ትንቢትን ተናገሩ። በምክሬ ግን ቢቆሙ ኖሮ፥ ለሕዝቤ ቃሌን ባሰሙ ነበር፥ ከክፉም መንገዳቸው ከሥራቸውም ክፋት በመለሱአቸው ነበር። አለምሁ አለምሁ እያሉ በስሜ ሐሰትን የሚናገሩትን የነቢያትን ነገር ሰምቻለሁ። "
ቃሉ እነዚህን ራሳቸውን ነቢያት ነን ባዮችን እግዚአብሔር እንደማያውቃቸው ያስረግጥልናል።
ስለዚህ እግዚአብሔር ቅር ከተሰኘበት መንገድ እንድንመለስ ሰውንም ከመከተል እንድንታቀብ በሐሰተኞቹም እንዳንታለል አደራ እላለሁ።
ይቆየን።
@deressereta
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ