ዓርብ 26 ማርች 2021

የጾም ምግብ ቤቶች

 የጾም ምግብ ቤቶች


በየከተማችን የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን የአጽዋማት ጊዜ ጠብቀው ምግብ ቤቶች በአዲስ መልክ ማስታወቂያ መስራት የተለመደ ነው።


አንዱን ብንመለከት የአብይ ጾምን ምክንያት በማድረግ የጾም ቡፌ፣ በየአይነቱ፣ ዓሣ አዘጋጅተናል። የምትል ትገኝበታለች። 


ማስታወቂያዎቹ ለጾም እና ጸዋሚ "ተጨንቀው" ምግብ እንደ ማዘጋጀታቸው ጥራጥሬ፣ ሽንብራ፣ ደረቅ ቂጣ አያዘጋጁም። ዝግጅቱ ለጾም ሳይሆን ለመብል ነውና።


ፍትሐ ነገሥት ስለ አጽዋማት በሚናገረው አንቀጹ አንቀጽ 15 ላይ በ572ኛው ቁጥር ላይ " በእነዚህ በታዘዙት ጾሞች ከቀኑ እስከ ዘጠኝ ሰአት ድረስ ይጹም ከዓሣ በቀር ሥጋ አይብሉባቸው። " ይላል።


ግእዙ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፦" ... ወኢይብልዑ ቦሙ ሥጋ ዘእንበለ ዓሣ ..." እዚህ ጋር ሊቃውንቱ እንደሚነግሩን "ዘእንበለ" ፍችው ብዙ ከመሆኑ የተነሳ ሲያጨቃጭቅ ቆይቷል። ቤተክርስቲያኒቱ ለዚህ መፍትሔ ይሆን ዘንድ ከመጽሐፍ ጠቅሳ ዓሣ የሥጋ ዘር ነውና። ደምም አለውና ጾም እንደሆነ በሲኖዶስ ደንግጋለች።


ፍትሐ ነገሥትም በዚሁ አንቀጽ ቁጥር 584 ላይ " በጾም ምክንያት ጠብ ክርክር ቢሆን መጾም ይገባል። ከመብላት በጣም ይሻላል።" ይለናል። 


ነገር ግን ጸዋሚው የቅድስት ቤተክርስቲያን ልጅ ራሱ ለምግብ ሲቀመጥ ዓሣ አልጾምም ሲል ይደመጣል። ለነፍሱ ሊያደላ በሚገባው ወቅት ለሥጋው ያደላል።


"ከዓሣ በቀር ሥጋ አይብሉባቸው።" በሚለው ቃል ዓሣን አልጾምም የሚለው "ጸዋሚ" ከፍ ብሎ " ከቀኑ እስከ ዘጠኝ ሰአት ድረስ ይጹሙ " የሚለውን አያነበውም፤። አይተገብረውም።


" ጾምስ በሕግ ውስጥ በታወቀው ጊዜ የሰው ከምግብ መከልከል ነው በደሉን ለማስተሰረይ ዋጋውን ለማብዛት እርሱን ወዶ ሕግን ለሠራለት እየታዘዘ የፈቲውን ኀይል ያደክም ዘንድ ለነባቢት ነፍስም ትታዘዝ ዘንድ " የተሰራ መንፈሳዊ ተግባር እንደመሆኑ መጠን በጾም ወቅት መከልከል ከሚገባን ነገር ሁሉ ልንከለከል ይገባናል፣ በደላችንን ለማስተስረይ ንሰሐ ገብተንም ልንጾም ይገባል፣ ወደን ፈቅደን ሕግንም ለሰራልን ልንታዘዝ ይገባል፣ ሥጋችንንም ለነፍሳችን ልናስገዛም ይገባል።


ጾም ከምግብ መክልከል ሥጋን ማድከም ነፍስን ማለምለም እስከሆነ ድረስ ምግብ ቤቶቻችን በአንጻሩ ምነው በምግብ ማስታወቂያ ለዚያውም ለመጾም በማይጋብዙ የምግብ ዝርዝሮች ጠብ እርግፍ አሉ?


የምግብ ቤቱን አነሳን እንጂ ከወትሮው በተሻለ በየሁላችን ቤት ከፍስኩ ጊዜ ይልቅ የምግብ አይነቱ በጾም ወቅት አይደለምን? ከዚህ ምን እናተርፋለን? ወይንስ እንዲሁ እንዘጭ እንዘጭ ነው?


መጾም ይገባልና ከመብላትም በጣም ይሻላልና ጾመን በረከትን እናግኝ፣ በደላችንንም እናስቀር፣ ስንጾም ብልቶቻችን ሁሉ (ዓይን፣ ጆሮ፣እግር፣ አንደበት፣ወዘተ) ይጹሙ። 


የጾም ምግብ ቤቶችም በስመ ጾም ከመነገድ ቢታቀቡ መልካም ነው፤ እኛም ስንመገብ በማካካሻ መልክ በሚመስል ባንመገብ መልካም ነው።


ስለ አጽዋማት ያለን አመለካከት ይቀየር የቄስ፣ የመነኩሴ፣ የሕጻናት፣ የሚባል ጾም የለም። እድሜው ሰባት አመት የሞላው የጤና እክል እና በንሰሐ አባቱ በኩል በተለያዩ ምክንያት ከሚፈቀድ በቀር ሰባቱም ጾሞች ሊጾሙ ይገባቸዋል።


" ከዚህ ከታዘዘው አብልጦ የጾመ ግን ዋጋው ይበዛለታል። " እንዲል።


አብዝተን ጾመን የበረከቱ ተሳታፊ ለመሆን ያብቃን። ጾሙ የሐጥያት መደምሰሻ፣ የዲያብሎስ ድል መንሻ፣ የመንግሥተ ሰማያት መውረሻ ያድርግልን።

አሜን።

ይቆየን።


@deressereta


comment እና subscribe ማድረግ አይርሱ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...