" አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል "
" በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ደኅና ሁኑ። ፍጹማን ሁኑ፥ ምክሬን ስሙ፥ በአንድ ልብ ሁኑ፥ በሰላም ኑሩ፥ የፍቅርና የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል።"
2ኛ ቆሮንቶስ 13 : 11
ለሶስተኛ ጊዜ ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሰወች በሄደ ጊዜ በመጨረሻው ምእራፍ ላይ ያስቀመጠላቸው መልእክት ነው።
ደህና ሁኑ የሚለው ቃል ሁላችንም እንደምንረዳው የስንበት የመለያየት የመጨረሻ ቃል ነው። ቅዱስ ጳውሎስ በመግቢያው እንደተናገረው " ነገር በሶስት ይጸናልና " እንዳለው ትምህርቱ በልባቸው እንዲጸና ለሶስት ጊዜ ተመላልሶ አስተምሯቸዋል።
በመቀጠልም " ፍጹማን ሁኑ " አላቸው። የሰው ልጅ በመንፈሳዊ ህይወት ሲኖር የሚደርስበት የፍጹምነት ደረጃዎች አሉና እነርሱን ለማስመዝገብ ዝም ብላችሁ ቃሉን የምትሰሙ ነገር ግን የማትተገብሩት ሳትሆኑ በሕይወት የምትኖሩ ሁኑ ሲላቸው ነው።
አንድም በቃሉ የምትሰናከሉ ሳትሆኑ ለሌሎች ምሳሌ የምትሆኑ ሁኑ ሲላቸው ነው።
አንድም እንዲሁ በከንቱ ያለምንም ዋጋ ላይ ታች የምትሉ ሳትሆኑ 30፣ 60፣ 100 ያማረ ፍሬ አፍርታችሁ የዘላለም መንግሥትን ገነትን ውረሱ ሲላቸው ፍጹማን ሁኑ አላቸው።
በመጨረሻም ሲያስተምራቸው ሲመክራቸው እንደመክረሙ ሁሉ ማሳረጊያ " ምክሬን ስሙ፥ በአንድ ልብ ሁኑ፥ በሰላም ኑሩ፥ የፍቅርና የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል " አላቸው።
ምክሩም እንዲህ የሚል ነው " በአንድ ልብ ሁኑ፥። በሰላም ኑሩ " ወንድሞች በአንድ ልብ እና በሰላም ሲኖሩ መልካም ነውና። ፍጻሜውም ያማረ ነውና። ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ወንድሞች አስረግጦ እንደተናገረው የፍቅርና የሰላምም አምላክ ከእኛ ጋር ይሆናል።
ዓለም ለምንድን ነው ከጫፍ ጫፍ ፍቅርና ሰላም ያጣችው?
ለምንስ የዓለማችን ሃያላን አገራት መሪዎች ሰላምን ለማምጣት ያልተቻላቸው?
ለምንስ ነው የየእምነት ተቋማት መሪዎች ፍቅርና ሰላም በምድር ላይ እንዲሰፍን ማድረግ የተሳናቸው?
ለምንስ ነው አባወራዎች የቤቱ እራስ እንደመሆናቸው ፍቅርና ሰላምን በቤታቸው ጣሪያ ስር ማምጣት ያልቻሉት?
ወንድም እህቶቼ የቅዱስ ጳውሎስን ምክር ካለመስማታችን የተነሳ አይመስላችሁም። እኔ በበኩሌ ያለምንም ማመንታትና ጥርጥር ምክንያቱ እርሱ ይመስለኛል፤። ነውም ደግሞ። እስኪ ሁላችንም ሕይወታችንን እንፈትሽ ሠላምና ፍቅራችን አንጻራዊ ነው ወይስ ፍጹም ሠላምና ፍቅር ነው።
ካልሆነ ሕይወታችንን እንፈትሽ በአንድ ልብ በሰላም እንኑር። ያኔ የሰላምና የፍቅር አምላክ ልዑል እግዚአብሔር እንደ ዓለም ሰላም ያልሆነውን ፍቅር እና ሰላም ሊሰጠን ከእኛ ጋር ይሆናልና።
ሁላችንም እንደ ቃሉ ተመላልሰን በአንድ ልብ በሰላም ኖረን ዓለምና በዓለም ያለን የጎደለውን ፍቅርና ሰላም እግዚአብሔር ያድለን።
አሜን።
ይቆየን።
እያተረፉ እውቀት ለመገብየት በሁሉም ሚዲያ ይከታተሉን።
My Facebook page link (በፌስቡክ ገጽ እንገናኝ)
https://www.facebook.com/deresse2020/
Main facebook account (ዋናው የፌስ ቡክ ገጼ ይቀላቀሉት)
https://www.facebook.com/DeresseReta
Follow me through telegeram (በቴሌግራም ሊከታተሉኝ ከፈቀዱ) ሁሉም ምልከታዬን የማጋራባቸው ማህበራዊ ድረ ገጾች ናቸው።
https://t.me/deressereta
ከአሥር አመት በላይ ከ50ሺ በላይ አንባቢዎች ያሉት መጦመሪያም አለ።
www.deressereta.blogspot.com
https://anchor.fm/deresse-reta/episodes/ep-ev5j5o
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ