ማክሰኞ 18 ማርች 2014

ይድረስ ለመንግስታችን፡

አንዲት አገር በማደግ ላይ ካለች ችግሮች እንዳሉ ይታወቃል ህብረተሰቡም ደግሞ የሚቻለዉን ያህል ሊረዳና ችግሮችን ሊቋቋም ግድ ይላል እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ጨዋ ህዝቦች ከማንም በላይ ናቸዉ፤ ሆኖም ግን እየተካሄደ ያለዉ ግን ከመጠን በላይ እየሆነ ስለሆነ መንግስታችን እና ባለ ድርሻ አካላት አፋጣኝ የሆነ መፍትሄ እና ተለዋጭ አቅርቦቶችን ሊያቀርቡ ግድ ይላል፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ መብራት ሃይልም ሆኑ የኢትዮ ቴሌኮም ባለስልጣናት ከዚህ ቀደም አገልግሎት ለሚሰጡት ህዝባቸዉ የገቡት ቃል ኪዳን ሊጠበቅ ይቅርና ተጨማሪ ቃል ኪዳን የሚያስፈልገዉ ሆኖ እየተገኘ ያለ ሁኔታ ላይ እነገኛለን፡፡ የተቀሩትም እንደ ዉሃ እና ፍሳሽ ያሉት በብርሃን ፍጥነት እየተከተሉት ይገኛሉ ከዚህ ቀደምም አልተለዩትም፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪ ቁጥር ከዕለት ወደ እለት እየጨመረ መምጣቱ እየታወቀ ተመጣጣኝ የሆነ የዉሃ አቅርቦት ዝግጅት እንዳልተደረገበት መንግስታችንም የሚክደዉ ጉዳይ አይደለም፤ ምናልባት የተደረገ ተጨማሪ ነገር ቢኖር ለጽዳትና ዉበት ክፍያ ተጨምሯል በዉሃ ቢል ላይ፡፡

መብራት ኃይልና ቴሌ ግን ከዕለት ወደ ዕለት ህብረተሰቡን በብርሃንና በኔትወርክ  ማጥት ከማስመረሩ ባሻገር የዕለት ከዕለት ስራዉን እያደናቀፈበት ይገኛል፡፡ መብራት ኃያሎችም ባንድ ወቅት ካሁን በኃላ ሻማ የምታበሩት ለልደት ብቻ ነዉ  በማለት አላግጠዉብን ነበር፤ ቴሌዎችም ኦፕቲካል ፋይበሩን ዘርግተን ስንጨርስ …. … … ወዘተ ወዘተ ብለዉ ያወሩት ጉዳይ ኦፕቲካል ፋይበራቸዉ አንጀት ሆኖ ይኸዉ በኔትወርካቸዉ አንጀታችንን በክፍያቸዉ ኪሳችን እየመለጡት ይገኛሉ፡፡(ይሁን እንግዲህ እነሱን አያሳጣን ማንን እናማ ነበር አንድም ማን ላይ ቁጭብለሽ ማንን ታሚያለሽ እንዲሉ…..)
ክቡር መንግስታችን የሆነዉስ ሆነና፡-
 ሻማ መግዣ ገንዘብ ኪሳችን ሳናስቀር ለአባይ ግድብ ማስፈፀሚያ ደሞዛችንን እየሰጠን እንዴት መብራት ታጠፋብናለህ?፣
 አባይ ተገድቦ እስኪጠናቀቅ ልጆቻችንን ወተት አናቀምስም ብለን ከልክለን ለአባይ መዋጮ ቦንድ እየገዛን እንዴት ለልጆቻችን ዉሃ ትነፍጋቸዋለህ?፣
ስንት እንቅፋት ቤቶችን (መሸታ ቤቶችን መሆኑ ነዉ) አልፈን በጊዜ ወደ ቤታችን እንዳንገባ መንገዱን ዘግተህ አጠላልፈህ አጠላልፈህ ተቀያሪ መንገድ እንኳን ሳታዘጋጅ እንዲህ ሌሊት ወጥተን በሌሊት እንግባ? የባቡር መንገዱ እስኪጠናቀቅ ከዘመድ ተቆራርጠን እንቅር በትራንስፖርት ምክንያት፤
ክቡር መንግስታችን የሚገርመዉ ነገር በሰፈራችን ይልቁንም በቤታችን የተጀመረዉ እንጀራ ስንመገብ ትንታ ማስታገሻ ዉሃ መሰጣጣት በዉሃ መጥፋት ምክንያት መቅረት ለአገሪቱ ቱባ ባህል መጥፋት እንደመጠቀሻ እያሰጋን ይገኛልና ለክቡር የዉሃ ሚኒስትሩ አሳስቡልን፤
እስኪ እግረ መንገዴን (መቸስ ለአዲሱ መንገድና ትራንስፖርት ሚኒስትሩ በአንዴ ተዛማጅ ወዳልሆነ ሙያ ከመንገድ ላይ ህዝብ ማሳደድ ወደ መንገድ ትራንስፖርት ሚኒስተርነት ከባድ መሆኑ የማይካድ ቢሆንም ቅሉ) የባቡር ሃዲዱ አንድያዉን ለልማት ስለሆነና ዉጤቱንም እያየነዉ ያለነዉ ጉዳይና በአምስት ዓመት ስለማለቁ የምናየዉ ነገር ምስክር እንደሆነ ሁላችንም ምስክር ነን፤ ይሁን እንጂ በከተማዉ ግንባር ግንባር ቦታዎችን በማጠር ህዝብ የሰፈረበትን ሰፈር በማስፋፊያ ምክንያት በማስፈረስና በማሳጠር የሚታወቁት ባለሃብታችን እንዲያዉም ሰሞኑን በአገር አቀፍ ስፖርት ፌስቲቫል ላይ (ምን እሱ ብቻ በየትላልቅ አዉዶች መገኘትስ ምን ብርቃቸዉ ነዉ ባለስልጣኖቻችንም እሳቸዉ ከሌሉ ብርድ ብርድ ይላቸዉ ይመስል ሸጎጥ ሳያደርጓቸዉ የሚቀርቡበት አጋጣሚ የለም) ባህርዳር ዝግጅት ላይ በቴሌቭዥን መስኮት ያያቸዉ አንዱ ወዳጄ፡-
 አየሃቸዉ አለኝ 
ማንን አልኩት
እኚህ ከፍተኛ ምክትል ሚኒስትሩን ነዋ አለኝ
እኔም ባለችኝ መጠነኛ ግንዛቤ ሳልጠራጠር ሚኒስትር ፍለጋ ዓይኔን መወርወር ….  በዚያ ማዕረግ የሚጠሩ ባለስልጣን አጣሁና እንደዉም ጠባቂዎቹን ሁሉ ጠረጠርኩ …..
አገኘሃቸዉ አለኝ
እያቅማማሁ አ…….አ….አይ አልኩት
እስኪ ደግመህ ፈልግ አለኝ
አዲስ ተሿሚ ናቸዉ ወይስ ነባር
እረ ነባር
አላወኩም
ሞክር
አላቅማ
ኮፍያ ያደረገዉ ….ጥቁር መነፅር የሰካዉ….
የቱ?
ወፍራሙ
አትቀልድ እንጂ የምሬንኮ ነዉ …..እየቀለድክብኝ እንዳይሆን?
ከት ብሎ ሳቀብኝና….. ….. ነገረኝ
ክዉ ብዬ ቀረሁ ጠላትዎት (የግብፁ ድርቅ ብለዉ ይቅሩና)  ሰዉ ባንዴ እንዲህ ድርቅ ይላል? ባላቃትም ያቺ  በሐጥያቷ እርሶ እንኳና ጎበዝ መጽሐፍ ቅዱስ አጥኚ ስለነበሩ በደንብ የሚያዉቋት ይመስለኛል እቺ ማን ነበረች …. … እስኪ ስሟን አዉሱኝ ይቺ እንኳን የጨዉ ሃዉልት ሆነች ነዉ ምን ሆነች ነዉ? የተባለችዉ እኔም ያለሐጥያቴ እንደዚያ ሆኜሎት ነበር ጌታ አተረፈኝ፡፡
በልማት ሰበብ (ድንቄም አልሚ) ሰፈር መንደሩን ሁሉ እያሳጠሩ የጨረሱት ባለማልማታቸዉ ምክንያት ያሳጠሩትን ሊነጠቁ ነዉ እየተባለ ልባችን ስንቴ ቀጥ ልትል መሰሎት እሳቸዉ ግን የባለስልጣናቱን ልብ በቱባ ገንዘባቸዉ ጠንቅቀዉ ስለሚያዉቁት ደንገጥም አይሉ (አሁን ግን ያሁኑ ከንቲባ ደግሞ ማን ሊሞት እንደሆነ እንጃ አልያም በደምብ አያዉቃቸዉ እንደሁ ሸበሌ ጋር ያለዉን ቦታ ነጠቃቸዉ አሉ … አሉ ነዉ)፤
እሳቸዉ ግን የምር የማያለሙት አሊያም የማይደፈሩትና የማይነጠቁበት ምክንያቱ ምንድን ነዉ?
ስንት ከንቲባ ስልጣን ላይ ወጥቶ ወረደ መሰሎት አንዳች ነገር ሳያደርግ መሬቱ እንደታጠረ
ያኛዉም ራዕያቸዉን የምናስፈፅምላቸዉ ወዳጃችን (ሟቹ) ማለቴ ነዉ ፈረንሳይ በ1935ዓ.ም. በሊግ ኦፍ ኔሽን ኢትዮጵያን ለማስወረር ከጣሊያን እንደ ወገነች እሳቸዉም ከኚሁ ባለሃብት ወግነዉ ሳያስፈፅሙ በድንገት ሄዱብን፤ እርስዎም መጠራት መቼ እንደሆነ የሚታወቅ ነገር ስለሌለ በአዲስ አበባ መስተዳድር ጉዳይ ጣልቃ ገብተዉ ነጥቀዉ ለሚያለማ ይስጡልን፡፡ የሚያለማ ከጠፋ የመዘጋጃ ቤቱን ለቤተክርስቲያኗ መልሱላት ግፍ ነዉና መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ካሉ ደግሞ እኛ ወጣቶች መዋያ ስላጣን ለወጣቶች መዋያ ትንሽ ሜዳ ስለሚያስፈልገን ጀባ እንዲሉን ጌታ መንፈስ ቅዱስ ያመልክትዎት፡፡
ነገሬን ጠቅለል ሳደርገዉ የመንገዱ ጉዳይ በሰዓቱ እስሚጠናቀቅና እስኪከፈት ድረስ የታጠሩትና የማይለሙት ስፍራዎች መንገድ እንዳይዘጉብን ይከፈቱልን፡፡ 
የጋራ መኖሪያ ቤት ዕቅድ በኛ ስመጥሩ ሰዉ አማካይነት ወደ አገራችን ፅንሰ ሃሳቡ ሲገባ ኃላቀር የነበረዉን የአኗኗር ዘይቤዉን ጭምር ይቀይራል የሚል እምነት ነበረዉ፤(ከሰል ማንደድ ፣ የጭስ ቤት መጠቀም፣….) ነገር ግን ዕድሜ ለመብራት ኃይላችን ይኸዉ ያ ሁሉ ቀርቶ ጥለን የመጣነዉ የከሰል ምድጃ ና የጭስ ቤት ዳግም ተከትሎን መጣ፡፡የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ (ኮንደሚኒየሞች) እንደጠላ ጋን በየጊዜዉ ጭስ እየታጠኑ ነዉ፣ ጥቀርሻና ሸረሪት ቤታችንን ደባልነት ሳያስፈቅዱ እየገቡ ናቸዉ፡፡ ይህ አካሄድ በቸልታ ከታየ እና በዚሁ ከቀጠለ የዉሃም ነገር ከኩሬ እና ከወራጅ ወንዝ ካልጠጠን ብለን በዉሃ ወለድ በሽታ ህዝብዎ በአንድ ጀምበር እመሽክ ብሎ ሊያድር እንደሚችል ስጋቴን ስናገር ሟርተኛ እንደማይሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ጌታዬ የኔትዎርኩንስ ነገር ተዉት ቢተዉት ይሻላል በደና ጊዜ እዛ ቤተመንግስት ገብተዉ ከሰዉ ተራርቀዋል እንጂ እንደድሮ ብዙ ጓደኝ ቢኖርዎት እና ጉዳይ ቢጤ ቢገጥምዎትና ቢቀጣጠሩ በቴሌ ምክንያት ከዘመድ ከጓደኛዎ ጋር ተቆራርጠዉ ነበር ፤ ለነገሩ እርስዎ በደህና ጊዜ ተቆራርጠዋል፡፡ ድሮም ሲያቀብጠን እንጂ ነጋሪትና ጥሩምባ መች አነሰንና ነዉ ለከፉም ሆነ ደግ መንገሪያ ስልክ ያስፈለገን፤ ሲጠፋም ችግር ሲሰራም ከችግሩ ወዲያ ያየንበት ጥቅም እንደሌለ የአገሬዉ ሰዉ በጠቅላላዉ የኑሮ መወደዱ፣ የጤፍ  ዋጋ መናር፣ የቤት ኪራይ በየወሩ መጨመር አናታችንን ያዞረዉ ሞባይል ከመጣ መሆኑን እያነሳ ትልቅ ትንሹ እየተማረረበት ይገኛልና፡፡
እንዲያዉም ህዝቡ እየተቀኘዉ ያለዉን እንደማስረጃ ብጠቅስልዎ (ከዚህ ቀደም ሰምተዋትም ከሆነ እንዳልሰማ ይስሙኝ አደራ እንዳያሳፍሩኝ) ነገሩን ያጠናክረዋል እንጂ አንሶ የሚገኝ አይመስለኝም፤
ኧረ ጥራኝ ጫካዉ ኧረ ጥራኝ ዱሩ፤
ኔትወርክ እና ባቡር ሥራ እስኪጀምሩ፡፡
ይህ እንግዲህ የሚያሳየዉ ምን ያህል ከተሜ መሆን እንዳስጠላ በደንብ ያመላክታል፡፡ ክቡር መንግሥታችን ህብረተሰቡ መናገሩን አይጥሉት እዛ ፓርላማ ከሚሰበሰቡት እና እጅ በመስቀል ከሚተባበርዎት ለመንግሥትዎ የተሻለ ጥቅም ይሰጣሉና፤ ህብረተሰቡን ይስሙት አይፍሩት ወረድም ብለዉ ይስሙት፤ህብረተሰብ መፈራት ያለበት ዝም ያለ እንደሆነ ነዉ፡፡ ከተናገረ መንግሥት ይሰራልናል ለዉጥ ያመጣልናል የሚል እምነት በመንግሥቱ ላይ ሲኖረዉ ነዉና የሚናገረዉ፡፡ ህብረተሰብ ተስፋ ከቆረጠና በመንግሥት ካቄመ ዝም ይላልና፡፡አንድም ሠዉ ከተናገረ ሃሳቡን በቀላሉ ማወቅ ይቻላል ዝም ካለ ግን ዝምታዉ ዉስጥ ምን እንዳለ እንኳን ማወቅ መገመትም አዳጋች ነዉ፡፡
ባለፈዉ ነግሬዎት እንደሆነ እንጃ የአባይ ነገርም (ከዛ በፊት እንደ አስተያየት የምነግርዎት ነገር ይህ በየምክንያቱ የሚወጡ ወጪዎች ለምሳሌ የሆነ ነገር 1ኛ፣2ኛ፣3ኛ ዓመት በዓል እየተባለ ለማክበሪያ የሚወጣ ወጪ ፣ የአባይ ጉዳይ ራሱ ስንት ወጪ እያለብን የርሱን የልደት በዓል ለማክበር ይህን ሁሉ ድግስና ወጪ ለምን አስፈለገ?፣ መቸስ ኢህአዴግ ስንት ፕሮጀክት እያለበት የግንቦት 20 በዓል አከብራለሁና ብር ቢለኝ በሳቅ እሞትቦታለሁ፣አሁን እስኪ ማን ይሙት…. ተዉት ይቅርብኝ፤ )በአንዳንድ አላዋቂ ሳሚ ሹሞችዎ ና የቢሮ ሐላፊዎች በኩል ስልጣናቸዉን ለማቆየት ሲሉ ሕዝቡ እንዲያዋጣ እየተደረገ ያለበት መንገድ የማስፈራሪያ ዓይነት ከዉክቢያ አይተናነስም ይህ ሙሉ የአንድ ወር ደሞዝ በአንድ ዓመት ማስቆረጥ፡፡(በኑሮ ዉድነት ላይ መዋጮዉ በእቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖበታል፤ ለነገሩ እርሶ ተረት አያቁም ለካ ዝም ብዬ ለፋሁ) ቅስቀሳዉ ለ3ኛዉ ዙር ማስተካከያ ካልተደረገበትና ህብረተሰቡ ዉስጥ የእኔነት መንፈስ እስካልተፈጠረ ድረስ አባይን ለመገንባት ገንዘብ ከማዋጣት ይልቅ ግብፅን ለመመከት ህይወት መሰዋት ሳይሻለዉና ሳይመርጥ አይቀርም፤ ጌታዬ እንግዲህ ይኼ የኔ ግምት ስለሆነ ብሳሳትም አይፍረዱብኝ የሰዉን ምሬት መስማት ናላዬን ስላዞረዉ ነዉ፤ መጥኔ እንግዲህ ለርስዎ የሰዉን ሮሮ ጆሮ ሰጥተዉ ሰምተዉት ከሆነ ብዙም የሞቆዩ አይመስለኝም፡፡አደራ ገንዘብ ገንዘቡን ስንል ይህን ህዝብ የአገር ፍቅሩን እንዳናሳጣዉ ፈራለሁ (እርሶ ብቻ የሚያነቡትን አንድ ግብፃዊ ባለስልጣን ያለዉን ላጫዉትዎት ምን አለ መሰልዎት አገሩ ግብፅ የአባይን ግድብ ለማስቆም የምታደርገዉን የላይ ታች መንፈራገጥ አይቶ ታዘበና …. መንግስታችን ትላልቅ አገራትን ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ በቴክኖሎጂ እንዳይደግፉ ከሚቀሰቅሱ ኢትዮጵያዉያንን ቢቀሰቅስ ይቀለዋል ሲል ሰማሁ፤ እንግዲህ ይህ አባባል በኔ አረዳድ በጣት የሚቆጠሩ አገራትን ለማሳመንና ይሳካ አይሳካ ሳይታወቅ ከመልፋት ትልቅ እምቅ አቅም ያለዉን የኢትዮጵያ የመንግስት ሰራተኛ ቢያሳምፅ ያሻለዋል ለማለት ፈልጎ ይመስለኛል፡፡) እዉነትኮ  ነዉ ይህ መንግስት ሠራተኛ የግብር ሰዓት አለፈ ቅጣት ልትቀጣ ነዉ ሳይባል፣ ሳያጭበረብር፣ ቀጥ አርጎ ግብሩን የሚገብር፣ ለድርቅ፣ለልማት፣ ለተቸገረ ሰዉ፣ ለጦርነት ፣ለሰላም … ወዘተ አዋጣ ሲባል ግንባር ቀደም ተሳታፊኮ ነዉ፤ ታዲያ ሰዉየዉ ይህንን ሃይል ቢያገኝ …. … የጠላት ጆሮ ይደፈን፤ ኧረ በኢየሱስ ስም ፣ ጌታ ይገስፀዉ፡፡ ጌታዬ አንድ ነገር ብዬ መቋጫ ላብጅለት እኛ ወኔ እንጂ ገንዘብ የለንምና መዋጮ አያብዙብን!!!!!!! 

 ገና ለገና ከዉሃ የኤሌክትሪክ ሃይል አመንጭቼ የዉጭ ምንዛሪ አስገኛለሁ ብለዉ ይህንን እምቅ ሃይል (የሰዉ ልጅ) በጠራራ ፀሐይ እንዳያጡ ፈራለሁና ምክሬን ስሙ፡፡ ሁሉ ነገር በቅጡ ሲሆን ይሻላልና፡፡  አንድን ማህረሰብ በግድ አይደለም በፍቅርም ለመግዛት ጥበብና ማስተዋል ስለሚጠይቅ ጥበብና ማስተዋልን ከንጉስ ሰሎሞን ይዋሱት፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...