ሰወቹ
እጅግ የተከበሩ እንዲያዉም ለምድር ለሰማይ የከበዱ ፣ የታፈሩ፣ ባእለጠጋ፣ሳርቅጠሉ አንቱ እያለ የሚያከብራቸዉ፣እነርሱን በመንገድ
እንዃን ሰዉ ቀድሞ የማይሻገራቸዉ፣በእግሩ የሚሄድ ቆሞ፣ በፈረስ ያለዉ ወርዶ እጅ ነስቶ አክብሮ የሚሸኛቸዉ፣የሰዉ ፍቅር እንደ ምድር
አሸዋ የበዛላቸዉ፣… ሁለት ሰዎች ነበሩ በትዳር ምሥጢር አንድ የሆኑ፤ መቸስ ላለዉ ይጨመርለታል ነዉና በዚህ በአደባባይ በሚታይ
ፍቅርና ክብራቸዉ ላይ በአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስተር የአረንጓዴ ተሸላሚ አርሶ አደር በመባል ሜዳልያና ዳጎስ ያለ ሽልማት በተደጋጋሚ
ተቀብለዋል፣ከወረዳ እስከ ዞን ከዚያም እስከ ክልል ድረስ የተለያዩ የምስክር ወረቀቶችን ተሸልመዋል፣ሞዴል አርሶ አደር በመባልም
ለልምድ ልዉዉጥ ብለዉ ባህር ተሻግረዉ ሄደዋል፡፡
በዚህ
ተደራራቢ ክብራቸዉ የተጣሉ በማስታረቅ ወደር አይገኝላቸዉም፤ሞዴል አርሶ አደር ብቻ ሳይሆን አርአያ ሽማግሌም በመባል በአካባቢዉ
ማህበረሰብ ዘንድ ይታወቃሉ፡፡ እንግዳ ተቀባይ፣የተራበ የሚያበሉ፣የተጠማ
የሚያጠጡ፣የታረዘ የሚያለብሱ፣…. ሩህሩህ ናቸዉ፡፡ወንዝ ተሻግሮ ስማቸዉን
ጠርቶ ከችግሩ የሚላቀቅ፣ከደረሰበት ተከብሮና ተፈርቶ ተስተናግዶ የሚመለስ ስፍር ቁጥር የለዉም፡፡ እንዲያዉም አንዳንዶች የ21ኛዉ
መ/ክ ዘመን አብርሃም እና ሳራ እያሉ እስከመጥራት ደርሰዋል፡፡
እንደተሰጣቸዉ
ቅፅል ስም ቤታቸዉ እለት እለት እንግዳ አያጣዉም ጠፋ ከተባለ አንድ ሰዉ ከቤታቸዉ ሳያድር አይቀርም፤ እንዲሁ ከዕለታት አንድ ቀን
አንድ ፀበልተኛ አመሻሽ ላይ ይመጣና «አሳድሩኝ የእግዚአብሔር እንግዳ ጠበልተኛ ነኝ »ይላቸዋል፡፡እነርሱም ቤት የእግዚአብሔር እንደሆነ
ገልፀዉ በደሰታ ተቀብለዉ አሳደሩት፡፡ እንደተለመደዉ ዉሃ አሙቀዉ እግር አጥበዉ፣ራት አብልተዉ፣መኝታ አዘጋጅተዉ ሊያስተኙት ዝግጅታቸዉን
ካጠናቀቁ በኋላ አካባቢዉ መብራት ሃይል ፊቱን ያላዞረበት ቀበሌ ገበሬ ማህበር ስለሆነ ጉቶ እያነደዱ ለብርሃንም ለሙቀትም እየተጠቀሙ
ዙርያዉን ከበዉ ጥሬ እየቆረጠሙ ይጫወቱ ጀመር እንግዳዉም እንግድነት ሳይሰማዉ፣ባይተዋር ሳይሆን፣ እንደቤቱ እግሩን ዘርግቶ፣ከነርሱ
ጋር ጨዋታዉን አድርቷል፡፡
ጨዋታዉ
ከገጠር እስከ ከተማ፣ ከሴት ወንድ ሳይል፣ከጨዋዉ እስከ ተማረዉ ሊቅ፣ከባለትዳሩ እስከ ፈቱ፣ ከካህን እስከ ደብተራ…. ምኑ ቅጡ ብቻ በደፈናዉ ያልተነሳ የለም ማለት ይቀላል፡፡በዚህ በደራ ጨዋታ
መሃከል እንደ ድንገት አለመግባባት ተፈጠረ እነዚያ በሰዉ ፍቅር ያበዱ ሰወች ለራሳቸዉ የሚሆን ፍቅር ሊኖራቸዉ ተሳናቸዉ፡፡ትዕግስት የሚባል፣ መከባበር የሚመስል ነገር ከስፍራዉ
ጠፋ፤ … ቀስ በቀስ ፍሙ ከተንተረከከዉ እሳት ዉስጥ ፍልጡን መመዥረጥ ጀመሩ ባልም ሚስት አንዳንድ በእጃቸዉ አስገቡ እንግዳዉም
በነገሩ ግራ እየተጋባ እህል ዉሃ የማያስብል ፍልጥ መዘዝ አርጎ በእጁ አስገባ፡፡ባልም ሚስትም ደንግጠዉ ተያዩ እሱንም ደጋግመዉ
ተመልክተዉ እንደገና ተያዩ በየልባቸዉ ባል ሆዬ ምንም ብታናድደኝ ሚስቴን ቸብቸብ አደርጋት እንደሆነ እንጂ አልጎዳትም አለ፤ሚስትም
እንዲሁ በልቧ እንዴ ባሌን ተናድጄ እንጂ በርሱ የሚጨክን አንጀት የለኝ እንዲሁ የአመል ባርያዎች አድርጎን እንጂ ጠዋት ማታ የምንጣላዉ
ተጨካክነን አይደለም ጉድ ሊሰራኝ በዚህ እህል ዉሃ በማያሰኝ ዱላ ባለቤቴን አናቱን ሊለዉ ነዉንዴ በማለት ተደናገጠች፡፡ ደጋግማመዉ
ተያዩና ባልየዉ ቀደም አሉና እንግዳዉን ሰዉ አንተ ደግሞ አነሳስህ እንደምን ነዉ? ምን ልትሆን ነዉ እንጨቱን ማለቴ ዱላዉን ማንሳትህ?
እንግዳዉም ሰዉ ደንገጥ በማለት ግራ በተጋባ መንፈስ ኧረ ምን ገዶኝ
እኔ ማንሳቴ የቤቱ ስርአት ቢመስለኝ እንጂ ምን አደርግ ብዬ በጌቶች ላይ በትር አነሳለሁ? …. ታድያ እኛ ትንሽ ተጋጭተን በትር
ብናነሳ አንተም ብታነሳ ተደናግጠን ነዋ አሉት፡፡
እንዲሁ
በየጣሪያዉ ስር የተከበሩ የተፈሩ ትልቅ የሚመስሉ ትናንሽ ጠባቸዉ፣አለመግባባታቸዉ፣ንትርካቸዉ፣ጭቅጭቃቸዉ፣… የቤቱ ስርአት የሚመስልባቸዉ
ስንቶች ናቸዉ? የቤት ቀጋ የዉጭ አልጋ የሆኑ አባወራዎችና እማወራዎችን
ቤት ይቁጠራቸዉ፡፡ከዉጭ ለሚያያቸዉ መላዕክት የሚመስሉ ዉስጣቸዉ ሲፈተሽ ባዶዎች፣ዉጭ አስታራቂ እቤት ነገር ጫሪዎች፣እዉጪ መሬት
እቤት ሬት የሆኑ የትዳር ቅንቅኖች፣… እጅግ ብዙዎች ናቸዉ፡፡ከዉጭ ላያቸዉ የሚያብረቀርቁ ዉስጣቸዉ ግን የተለሰነ መቃብር የሚመስሉ
ከንቱዎች ስፍር ቁጥር የላቸዉም፤…
አንድ
እንግዳ አስቀምጠዉ መታገስ የተሳናቸዉ፣መቻቻል የማይታይባቸዉ፣ፍቅር በዞረበት ያልዞሩ አስመሳዮች ፀባቸዉ የቤቱ ስርአት እስኪመስል
ሰወችን የሚያሰናክሉ፣የሰዉን ማንነት የሚያጎድፉ፣እንደመሰናክል ከወፍጮ ድንጋይ ለሰማይ ለምድር የከበዱ አስቸጋሪዎች፣ትዉልድ የሚያሰናክሉ
መሰሪዎች፣… ብዙ ናቸዉ፡፡ እስኪ እኛስ ማን ነን? ለወለድናቸዉ ልጆቻችን ከትዳራችን ምን አይነት ፍሬ እያበላናቸዉ ነዉ? የፀብ
ወይስ የፍቅር ፍሬ? የመቻቻል ወይስ የትዕቢት ፍሬ?.... የትኛዉ ነዉ ከቤታችን እየታጨደ ያለዉ? ዉጭ ማነን ቤት ዉስጥስ? የቤታችን
ስርአት ምንድን ነዉ ፀብ ወይስ ፍቅር? መከባበር ወይስ መናናቅ? ትህትና ወይስ ትዕቢት? ልጆቻችንን ምን እያስተማርናቸዉ ነዉ?
በቤታችን ጥላ ስር ያሉትን ምን እያወረስናቸዉ እንገኛለን? የዉጭ አልጋዎች የቤት ቀጋዎች/ የማናስለቅስ የምናስነባ/ የምናደማ አይደለንም?እስኪ
ዉሎአችንና አዳራችን ይፈተሽ፤
በአንድ
ወቅት ልጅ እያለሁ የማዉቃቸዉ ባልና ሚስቶች ነበሩ እነዚህ ባለትዳሮች ባላንጣዎች ብላቸዉ ሳይሻል ይቀራል? በስራቸዉ የሚያስተዳድሯቸዉ
ይሁን የሚያሰቃዩዋቸዉ ሶስት ሴት ልጆች ነበሩዋቸዉ አንዷ ነፍስ ያወቀች ሁለተኛዋ ዕድሜዋ ከአምስት ያልበለጠ ሶስተኛዋ ገና ድክድክ
የምትል ነበረች ሰዉ የዘራዉን ያንኑ ያጭዳልና ትልቋ ልጅ ወላጆቿ በልቧ የዘሩትን እንክርዳድ ታፈራላቸዉ ጀመር፤ ያኔ ቢበዛ የአስረኛ
ክፍል ተማሪ ነች ጊዜዉ ከአስራ ስምንት አመት በፊት ስለነበር በዛን ጊዜ ለነበሩት ገና ልጅ ናት የዛሬዎቹ ገና አስረኛ ሳይደርሱ
ቢወልዱም አይደንቅምና ዘመኑም ልጆቹም ፈጣን ስለሆኑ፡፡ ይህች ልጅ በአጭሩ ከሶስት ጊዜ በላይ እንዳስወረደች ከእናቷ አንደበት ሰምቼዋለሁ
እንድመክራትም አደራ ተብዬ ስለነበር ታሪኩን በደንብ አዉቀዉ ነበር
ከዕለታት አንድ ቀን እቤት ሄጄ እንደመክራት እቤት በተጠራሁት መሰረት እቤት ተገኝቼ ያየሁት የቤቱ ስርአትና የልጅቱ ህይወት ተመሳስሎ
ስትመለከቱት የቤቱ ባህል ቢመስላችሁ ምንም አይገርምም፡፡ የሚገርመዉ ነገር ወላጅ እናቷ ልጃቸዉን እንድመክራት ይሁን ራሳቸዉን እንድመክራቸዉ
ግራ ገባኝ ምክንያቱ የቤታቸዉ ባህል ራሱ ያስጠላ ነበርና ራሱ የተበላሸን ነግር ምን ያደርጉታል? ለዚህ ምክር እቤታቸዉ ስሄድ ታናሼ
የምትሆነዋን ልጃቸዉን ለመምከር ነበር የሆነዉ ነገር ግን እነሱን ወደ ላይ መምከር ሆኖ ተገኘ ምነዉ ቢሉ እሷ ተሽላ ተገኝታለችና
፡፡
እንዲሁ
አባወራዎች/እማወራዎች ሆነዉ በአደባባይ እዩልኝ ስሙልኝ ካሉና ልጅ ከወለዱ በዃላ ልጅነታቸዉ የሚያገረሽባቸዉ ከንቱ ነገር የቤታቸዉ
ባህል የሆነባቸዉ ብዙ ናቸዉ፤በየመስሪያ ቤቱ፣በየሃይማኖት ተቋማቱ፣ በየፖለቲካ ፓርቲዉ፣ ወዘተ ያሉቱ በሙስና መዘፈቁ፣ፆታዊ ትንኮሳዉ፣የዝምድና
ስራዉ፣ያለ ችሎታና የትምህርት ደረጃ ምደባዉና እድገቱ…ወዘተ ሲታይ ያገሪቱ ባህልና ህገ መነግስቱ የሚፈቅደዉ ይመስላል፡፡
የቤታችን
ስነ ምግባር እንግዳ የሚያሰደነግጥ ዘመድ የሚሳፍር ቤተሰብ አንገት የሚያስደፋና የሚያሸማቅቅ ትዉልድ የሚያመክን ሆኖብናል፣ የሃይማኖት
መምህራኖቻችንና መሪዎቻችን አንገታቸዉን አደንድነዉ አንገታችንን ከሰበሩት ሰንብተዋል፣ የሀገር መሪዎች ህዝቡን ከማሰተዳድር የራሳቸዉን
ጥቅም በማሳደድ ባተሌ መሆናቸዉ ሀገራትን ለዉድቀት እየዳረገ ሲመረጡ ቃል የገቡትንና ስራ ሲጀምሩ ቃል የገቡትን ተስፋ ሰጪ እድገት
ዉሃ በልቶታል፣ ትዳሮች ሲመሰረቱ በልዑል እግዚአብሔር ፊት የተገባዉ ቃል አስታሽ አጥቷል፣ … በአጠቃላይ የትዉልዱ ምግባር አስደንጋጭና አሳፋሪ አንዳንዴም
በአሸዋ ላይ የተመሰረቱትን አሳታፊ አድርጓል፡፡
የተፈራን
የተከበርንና የተወደድን ህዝቦች ሆይ መልካም ስራችን በአደባባይ እንዲበራ ይሁን ከቀጣዩ ትዉልድ የተሻልን እንሁን ፤ ለቀጣዩ ትዉልድም
የተሻለ ነገርም እናስቀምጥ፡፡
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ