ያለው ዕለት ለንጋቱ ቦታውን ለመልቀቅ መሰናዶውን ያጠናቀቀ ይመስላል በቤቴ መስኮት ቀዳዳ የሚገባው የንጋት ብርሃን “ነግቷል ተነስ” የሚል ሰው ያህል ከፊት ለፊት በቀዳዳው እየገባ ይጎነትለኛል የጭላንጭሉን ብርሃን ተልዕኮ የሚያጨናግፈው ድብርት “አይዞህ ተኛ ገና ነው” እያለ ያዘናጋኛል፤ አሁንም በመስኮቱ የሚገባው የብርሃን ጭላንጭል ገብቶ ገብቶ ቤቱን በሰፊው ተቆጣጥሮታል፣ አካላቴ ሁሉ ሳምንቱን መንገድ ሲጓዝ እንደከረመ አንጓዎቼ በሙሉ የመዛል ስሜት ይሰማባቸዋል፡፡ ከሁለቱ አንደኛዋ አይኔ ብቻ ብርታት ይሰማታል እንጂ ሁለተኛዋ ጭራሽ የለችም ማለት ይችላል፤ አንደኛው ሲተኛ እርሷ ነቅታለች እርሱን ለመቀስቀስ ባደረገችው ጥረት እርሷም ድካም ተሰምቷት ማሸለብ ጀመረች የሌላት ልብሴን ገላልጣ ለመውጣት ጡንቻዋን ያፈረጠመችው ክንዴ ብርድ ሲያኮማትራት ተመልሳ ከብርድልብሱ ሾልካ ገባች ገና ተመኝታ የተገናኘች ይመስል እንቅልፍ ጣማት በዚያቹ በቀጫጫ ክንዷ ራሷን በራሷ እቅፍ አድርጋ ጋደም እንዳለች የእንቅልፍ ማዕበል ይዟት ጥርግ አለ፡፡ በልቦናዋ በብርቱው ምሽት ያሰበችው የዕለት ሰንበት የቅዳሴ መርሃግብርና ጠዋት በብርሃኑ ጭላንጭል መካከል ትዝ ያላት ልቡናዋን እንደብል በልቶ ጨርሷታል ሰውነቴ ለእንቅልፍ ተማርካ ከሞቀው መኝታዋ በመሆን ቅዳሴን ታስቀድስ ጀመር፤ ልክ ከመቅደሱ ፊት እንደቆመ አስቀዳሽ አሁን ለዛለችው ገላዬ ንፍቁ ዲቆኑ “ጸልዩ በእንተ ያበውኡ መባእ …” የሚለውን አዚሞ ሕዝቡም “ተወከፍ መባኦሙ ለአኃው” የሚለውን ጨርሶ ዲያቆኑ በድጋሜ “ስግዱ ለእግዚአብሔር በፍርሃት” ብሏል የዛለው ገላዬም “ቅድሜከ እግዚኦ ንሰግድ ወንሴብሐከ” ብላ ሰግዳለች
እስከዚህ ድረስ በደንብ አውቃለሁ፤ እንዲሁ እያልኩ (እያስቀደስኩ) ተሰጥኦ እየተቀበልኩ ልቤን ዘና አድርጌ ተጋድሜአለሁ ‹‹ፃኡ ንዑስ ክርስቲያን ሲል የመኝታዬ ዲያቆን የተከራየሁበት ግቢ ደጃፍ ከመጠን በላይ ሲያንኳኳ የነቃሁና የንጋት ዜና አብሳሪ የነበረው ንጋት ፍንጣቂ ብርሃን ቤቱን በሙሉ ወርሶት ዙሪያዬን ከቦኝ “አሁንም ተኝተሃል?” የሚለኝና ‹በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ 1ዱ አምላክ› … በማለት ከመኝታዬ ዘልዬ በመነሳት ፊቴን ሽልንግ በምታክል መዳፌ አባብሼ በርና መስኮቱን ሳልከፍት የሌሊት ልብሴን ቀይሬ ካልሲ በማድረግ ማታ አዘጋጅቼ ካስቀመጥኩበት ስፍራ ነጠላና የፀሎት መፅሃፌን በጥድፊያ ብድግ አድርጌ በሬን በርግጄ ከክፍሌ በመውጣት ሩጫዬን በአቅራቢያ ከሚገኙት ሁለት አብያተ ክርስቲያናት መንታ መንገድ ላይ በመቆም ጊዮርጊስ ልሂድ ገብርኤል አልኩኝ ፍርሃትና እፍረት ልቤን ወርሰው ገብርኤል ብሄድ መንገዱን ሞልቶት ያለው ሕዝብ ቢያየኝ ይስቅብኛል፣ ጊዮርጊስስ በዚህን ሰዓት ስሄድ ያየኝ ሰው ከአጥሩ ሥር ቁጭ ብሎ ሲጋደም ነጋበት ብሎ ይዘባበትብኛል፣ በማለት አሰብኩ ሚካኤል ሂድ ማንም አያይህም አለኝ አንደኛው ልቤ እንደ ደህና አማካሪ መንገዱን ጀመር እንዳደርኩኝ ለመሆኑ የምትሄደው ተገደህ ነው ወደህ ለሰው ብለህ ነው ለራስህ ለመዳን በራስህ አነሳሽነት ከሆነ የሰው አንደበት እሳት ውስጥ በመራመድ አልፈህ ነግቶበት ያልነጋለትን ሕዝብ እያሰብክ ገብርኤል ሂድ አለኝ ደፋሩ ልቤ ድፍረት አግኝቼ ጉዞዬን ወደ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አቀናሁ የሰፈሬን መንደር ትንሽ አለፍ እንዳልኩ የከተማው ሰው ግማሹ ቁርሱን ሊገዛ ወደ ዳቦ ቤት ወንደላጤው ወደሚቀለብበት ቤት ያመራል አንዳንዱም ወዴት እንደሚሄድ ግራ የገባው ይመስል ተክዞ በየደጃፉ የቆመ አለ በአንዳንዱም ግቢ ውስጥ ከአጥር ቀዳዳ የአይን እይታዬ ማየት እስከሚችለው ስመለከት ዱብ ዱብ እያለ ስፖርት ይሰራል ከፊሉም ከስፖርት ሜዳ ቁና ቁና እየተነፈሰ ኑሮውን ታግሎ ለማሸነፍ ሲጥር ያላበው ገብሬ ይመስል ላቡ በጆሮ ግንዱ በኩል ወደ ሠራ አካላቱ በደረቱ በጀርባው በአንገቱ ሥር የላቦቱን ጠረን ለመንገደኛው እየተወ ይሹልከለካል ይህንን እየቃኘሁ ከምኔው ነግቶላቸው እንደተገናኙ እንጃ የወሬ እቁብተኞች የሚመስሉት ከዚያ ቦታ የማይጠፉት የቦታው የዕለት ዕለት ደንበኞች አዛውንቶችና ጎረምሶች ከሰዎች መሸጋገሪያ ፊት ለፊት አንድ ጥግ ይዘው እያወሩ ያውካካሉ ከማዶው ከነርሱ ትይዩ ከሚገኘው ቡና ቤት አጥር ሥር የመንደሩ ጠብደል ጎረምሶች /ለመንገደኛው/ ለአላፊ አግዳሚው ለትንሽ ለትልቁ አቃቂሪ እያወጡ ይሳሳቃሉ እነርሱ ዘንድ ልደርስ ጥቂት እንደቀረኝ እግሬ መተሳሰር ጀመረ የእግሬ አንጓዎች እርስ በርስ ይጣላሉ አንዱ ወደፊት ሲቀድም አንዱ ወደ ኋላ ይቀር ጀመር ቁርጭምጭሜቶቼ ሲጋጩ የሕመም ስሜት ውስጤ ተፈጠረ መራመዴን አልገታሁም ቸኩያለሁ ሮጣለሁ ነገር ግን ምንም ያህል አልተራመድኩም የሰው ፊት እሳት ሆኖ ያቃጥለኛል እንቅፋት ሆኖ ያናቅፈኝ ጀመር፤

ሞት ይቅር ይላሉ ሞት ቢቀር አልወድም
ድንጋዩም አፈሩም ከሰው ፊት አይከብድም
የሚለው ማታ የሰማሁት የበገና መዝሙር በውስጤ አቃጨለብኝ በጣም አጤንኩት እውነትም መቃብር ከሰው ፊት አይከብድም አልኩኝ ቆየት እንኳን ሳልል እንዴት? አልኩ እንዴት መቃብር አይከብድም እሺ መቃብርስ አይክበድ ከመቃበር በፊት ያለው ሞትስ ላልተዘጋጀው አይከብድም እንዴ? ይከብዳል ስለዚህ ሞት ላልተዘጋጀ እንቅልፍ እንኳን ለሚረታው በሐሳብ ተብከንክኖ ላላበቃው ለእኔ ብጤው ቆይ ይቅር ባይቀርም እስክዘጋጅ ዘግየት ይበል አልኩኝ፡፡ ከሐሳቤ መለስ ብዬ መንገዴን ሳስበው እነዚያ መንገደኛ ተናዳፊ ተርቦች የሚመስሉት አሽሙረኞች መካከል ገባሁ ንዳድ(ወባ) ያለበት ሰው ያህል ሰውነቴ ይንቀጠቀጣል ጉልበቴ ይብረከረካል ጥርሴ ይንቀጫቀጫል በውስጤ ‹‹ወላዲተ አምላክ …›› ‹‹አንተ ቅዱስ ገብርኤል ዛሬን ብቻ ከውርደት አውጣኝ እዚህ ሕዝብ መሐል እንዳትቀጣኝ ሰው ፊት ጥለኸኝ የሰው መሳቂያ እንዳታደርገኝ›› በማለት በልቤ እማፀን ጀመር፤ ጊዜው ሄዷል የጠዋት ፀሐይ ፏ ብላ ወጥታለች ሰው ሁላ ይሞቃታል ሁለት ሰዓት ገደማ ይሆናል አሻግሬ ስመለከት ብዙ ሰው ነጠላና ጋቢውን አጣፍቶ መቋሚያውንና ከዘራውን ይዞ ዳዊቱን አንግቶ መቁጠሪያውን በአንገቱ አንጠልጥሎ ዝርዝር ሳንቲሙን በኪሱና በመቀነቱ ቋጥሮ ወደ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ያመራል ግማሹን እቁብ፣ እድር ሌላ ሌላም ጉዳይ ያለበት ተሳልሞ ፀሎቱን አድርሶ የሚመለስ አለ፤ በዚያ ልክ መጠን በየመንገዱ የቆመም ከልጅ እስከ አዋቂ ሞልቷል መንገዱን አላሻግር ያሉኝ እነዚህ ናቸው ፍርሃቄ ጭንቀቴ እየጨመረ ወደ እሳት እየተጠጋ እንደሚሄድ ቅቤ ሠውነቴ ቀልጦ ሊያልቅ ሆነ ራሴን አማረርኩ አርፌ ለምን ዝም ብዬ ጊዩርጊስ አልሄድኩም አለበለዚያም ቢርቅምኮ ሚካኤል ብሄድ ኖሮ ይሄ ሁላ መረበሽ አልነበረም ምነው እግሬን በሰበረው ወይንም ደግሞ እንቅልፉ ቀርቶብኝ ሌሊት ተነስቼ በመጣሁ ኖሮ በማለት ውስጤ ለኔ ለራሴ ሲያደፋፍረኝ ሹክ አለኝ ‹‹አይዞህ በርታ ይኸንንም አንተ ስለሆንክ ነው፤ ሌላውማ ሲነጋበት ሠው ምን ይለኛል ብሎ ቀርቶ የለ፣ አብዛኛውስ የሞተው ሕዝብ በዚህን ሰዓት የት መሄድ እንዳለበት ዘንግቶ ጠባቂ /አስተማሪ/ እንደጠፋው የበግ መንጋ የትም ተበትኖ ቀርቶ የለ? አለኝ…›› እውነትም ብዬ በድፍረት አካባቢዬን እቃኝ ጀመር በዙሪያ ቆመው የቆዘሙትን ተሰብስበው የሚስቁትን አላፊውን አግዳሚውን ቆመው ከራስ እስከ እግር እያዩ አቃቂር የሚያወጡትንና የሚያሽሟጥጡትን እቃኛቸው ጀመር የሁሉም ስሜት በየቋንቋቸው በውስጤ የልቡናቸውን ሃሳብ ያወሩልኝ ጀመር፡፡
ዝም ብሎ ቆዝሞ የቆመውን ስመለከት የቀጣዩ ቀን ውሎው ግራ ገብቶት መሽቶበት ብቻ ከመኝታው ተሳፍሮ በሐሳብ ሲያማትር አድሮ ሳይነጋ ነግቶበት ተነስቶ ባዶ ቤቱን በመሸሽ ወጥቶ መላ የሚገኝ መስሎት ከአውላላ ሜዳ ላይ ሐሳቡን የሚካፈልለትን ቢጤውን የሚፈልግ ይመስላል፤ ዝም ብሎ ደግሞ የሚስቀው እርሱ ምን ቸገረው እናቱ ወይ አባቱ የሰው ፊት አይተው በኑሮ ተጠብሰው እዚያም እዚህም ብለው ልጄ የሚበላው አይጣ በማለት በቁራሽ ሆዱን በዕራፍ ጨርቅ ገላውን የሸፈኑለት የምስኪናን ወላጆች ልጆች ናቸው ብዬ በመላ ገመትኩ ተቀጥቶ ያደገማ በዚህን ሰዓት ከዚህ ምን ይሰራል ወላጆቹ ሰርተው እንዳለፈላቸው ሠርቼ ይለፍልኝ በማለት ኑሮን ከወላጆቹ ጉያ ሥር ቁጭ ብሎ ይማራል እንጂ የታደለውም ቤተክርስቲያን ከወላጁ ጋር ቅዳሴ ሄዷል አልኩ፡፡ ከፊሉ ደግሞ አሳዳጊ የበደለው የመጥረቢያ ልጅ መዘሊያ እንዲሉ ቀጥተው ያላሳዳጉት ውጣ ግባ ብለው የማይቆጣጠሩት የትም ውሎ የትም የሚያድር መረን (በረንዳ አዳሪ) … ነው በማለት ሳማትር ቆይቼ ቅኝቴን በይደር ገትቼ ተፈትልኬ ሥፍራውን ለቅቄ ወደ ገብርኤል ቤተክርስቲን አመራሁ ከደጁ ስደርስ ከአፍ እስከ ገደፉ ሕዝቡ ሙልት ብሏል ነጠላዬን አጣፍቼ አማትቤ ተሳለምኩ፡፡
ቀና እንዳልኩ ካህኑ ‹‹ሀበነ ንኅበር በዘዚአከ መንፈስ ቅዱስ ወፈውሰነ በዝንቱ ጵርሶፎራ ከመብከ ንሕየው ዘለኩሉ ዓለም ወለዓለም ዓለም›› እያሉ ነው በመደናገጥ አሁንም በማማተብ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አልኩና ሰዓቴን ስመለከት ሁለት ሰዓት ተኩል ይላል በጣም አፈርኩ ተሸማቀቅሁ ዙሪያዬን ስቃኘው ሁሉም በፀጥታ በተመስጦ በመሆን በዜማ ካህኑ ያለው በድጋሜ ተቀብለው ይፀልያሉ እኔም አብሬ ‹‹ሀበነ ንኅበር በዘዚአከ መንፈስ ቅዱስ …›› ማለት ጀመርኩ ካህኑም ሲል ዲያቆኑም ሲቀጥል ምዕመኑም ሲቀበል ቆይተን ዲያቆኑ ጸልዩ ብሎ አቡነ ዘበሰማያት በዜማ ስንል አንድ ድምፅ ከበስኋላዬ ሰማቱ ‹‹ወደ ቀኝ ነው ወደግራ?›› አሉ አንዷ ሴት ‹‹ምኑ!›› አለች ቅዳሴ ላይ ሲወራ በመናደድ ‹‹የገብርኤል ቤተክርስቲያን›› አሉ እኚያ አባት ማየት የተሳናቸው ኖረዋልና፡፡ ‹‹ደርሰዋል በቃዎት ዝም ብለው ይቁሙ›› አሉዋቸው አንድ እናት ‹‹ስለ መልዐኩ ስለ ገብርኤል …›› አሉ ድምጣቸውን በማሰማት ‹‹ኧረ እባክዎ፤ትን ዝም ይበሉ ቅዳሴ ላይ ናቸው›› ይላሉ ከደጅ ቆሞ የሚያስቀድሰው ሕዝብ ሰውየው አልሰሙም ‹‹ስለ አይነብርሃን …›› ይላሉ ‹‹ልቡም ጆሮውም ታውሯል ማለት ነው ይኸ ሰውዬ ብለው አንድ አዛውንት ጠጋ አሏቸውና አንተን እኮ ነው የምንልህ ቅዳሴ ላይ ናቸው ዝም ብለህ ቁምና በኋላ ትለምናለህ…›› አሉት አዛውንቱ ሠውዬ ‹‹እሺ፤ እሺ›› አሉ የኔ ቢጤው እኔም ውስጤ መናገር እየፈለገ አርፍጄ መጥቼ ምን አፍ አለኝ ብዬ ዝም አልኩ ብዙ ነገር ታወሰኝ ከአስተማሪ እጦት በመሻር ዛሬ የደረሱት የቤተክርስቲያናችን ሥርዓት በሙሉ ከፊቴ ድቅን አሉብኝ ‹‹… ለመሆኑ ተደፍኖ እስከ መቼ ነው የሚቆየው … የኔ ቢጤዎችስ መቼ ነው ራሳቸውን እንደ አንድ ምዕመን በማየት ሥርዓት ጠብቀው ቆመው የሚያስቀድሱት መቼ ነው ራሳቸውን ጌታ ለፍርድ ሲመጣ እነርሱንም ጭምር እንደሚፋረዳቸው አውቀው ንሰሐ የሚገቡትና የሚቆርቡት … በቅዳሴ ሠዓትስ መቼ ነው ሥርዓት የሚይዙት አልኩኝ የሕዝቡ ተዳፍኖ ይቆይ በማለት እንዲህ ስብጠለጠል እንደቆየሁ አንድ አለባበሳቸው የከተማ ሰው ያስመሰላቸው በአንድ እጃቸው መቋሚያ በአንድ እጃቸው የቤተክርስቲን ጃንጥላ በአንገታቸው መቁጠሪያ በዓይናቸው መነፅር የሰኩ አዛውንት ገፍተርተር እያደረጉ ከኋላዬ ደረሱና እኔንም መገፈታተሩን ጀምረው ቆም አሉ ኮስተር በማለት ዘወር ብዬ አርፈው አይቆሙም ያህል ተመለከትኳቸው ‹‹… ውይ፤ ውይ ዛሬስ ጉድ ሆኛለሁ ቆይ አልነጋም እያልኩ ቅዳሴው ይረፍድብኝ እኔኮ መጀመሪያ እንደነቃሁ ቁጭ ልበል ብል እነርሱ ናቸው ቆይ ገና ነው ተኚ የአገሩን ሌሊት ስለማታውቂ ነው እኛ እንቀሰቅስሻለን ብለው ጉድ የሰሩኝ …›› በማለት የገረፏቸው ያህል ይለፈልፋሉ ሠው ሁሉ እየዞረ ይገላምጣቸዋል እርሷቸውም አውርተው ስለጨረሱ ዝም አሉ ፀጥ ረጭ ብሏል ደጁ ከግልምጫው ቻቻታ በስተቀር ዲያቆኑ ‹‹ስግዱ ለእግዚአብሔር በፍርሃት›› ሲል ሁላችንም ‹‹ቅድሜከ እግዚኦ ንሰግድ ወንሴብሐከ›› ካልን በኋላ ግማሹ መቀመጥ ግማሹ መንበርከክ ጀመረ በዚህን ሰዓት ነበር ከአጠገቤ የነበሩት አንድ አዛውንት ሴትዬ ‹‹ማረኝ … ማረኝ›› ይቅር በለን ………ይ ……..ቅር በለ….ን›› ይላሉ ሌላው ደግሞ ‹‹ስገዱ ነው እንጂ የተባለው ቁጭ በሉ አልተባለ የምን ስርዓት ማፋለስ ነው ….›› እያለ የቤቱ ቅናት እያቃጠለው ይበሳጫል አንዳንድ የኔ ቢጤ አርፋጁ ‹‹ከምኔው ቅዳሴውን አጣደፉት …›› ይላል ሌሊት የመጡት ሲጎትቱ ሶጎትቱት መቸስ ሊጨርሱ ነው ተገላገልን ይላል ብቻ የቤተክርስቲያኗ ደጃፍ ብዙ ዓይነት ሰው ይዛለች ከየተቀመጥንበትና ከየተንበረከክንበት እንደተነሳን ከመጣሁ ጀምረው ከፊታችን ተደፍተው የነበሩትም አብረውን ብድግ አሉ ፊታቸውን እያሻሹ አንደኛዋ ሴትዬ ‹‹… እንዴ ይሄ ሁላ ሰው ከየት መጣ?...›› አሉ በመገረም አንደኛዋ ደግሞ ‹‹… በስመ አብ የዛሬ ቅዳሴ ደግሞ ከምኔው ይፈጥን ጀመር አሁን ዲያቆኑ ‹‹በእንተ ቅድስት ሲጸልይ አልነበረም እንዴ ታዲያ ከምኔው እግዚኦታ ተዳረሰ አሉ›› እግዚኦታ ላይ ነበረና እኔም ከአፌ ሳይወጣ በልቤ ለመጀመሪያዋ ‹‹ከተኛበት እንደርስ ነቅቶ መጥቶ ነው›› ለሁለተኛዋ ደግሞ ‹‹ከመተኛትዎ መፍጠን ጀመረ›› አልኩና እግዚኦታውን ቀጠልኩ በዙሪያዬ ያለውን የእግዚኦታ ዜማ ስቆጥር ከቅዳሴው በልጦ አገኘሁት ግዕዝ አትለው አራራይ እዘል አይባል መላቅጡ የጠፋ አንዴ የተባለውን አንዴ ማለት ሲገባው ሦስት ጊዜ የሚለው አለ የዜማው የቅዳሴው ሥርዓት ከተነሳ ሞልቷል ግማሹ ድርሻውን አያውቀውም እንደ ጆከር ሁሉም ቦታ ይገባል የካህኑንም የዲያቆኑንም ከ‹‹አሃዱ አብ…›› ብቻ በቀር እርሱን ከተወሰኑት ሌላው አክብሮት ይላል፡፡ ‹‹አሜን›› ተብሎ ዲቆኑ ‹‹አጽንኦ አርእስቲክሙ ቅድመ እግዚአብሔር አምላክነ፤ በእደ ገብሩ ካህን ከመ ይባርክነ›› ብሎ ካህኑም ‹‹እግዚአብሔር ምስለኩልክሙ›› በማለት ባርኮ ካጠናቀቀ ዲቆኑም ‹‹እትው በሰላም›› በሰላም ግቡ ብሎ እንዳሰናበተ ካህኑ እየዞሩ ሲባርኩ ቅዳሴ ጠበልም ሲታደል ለመባረክ ገና ‹‹እትው …›› ከመባሉ በካህኑ እጅ ሳይባረክ ወደ ቤቱ የሚበረውን እያየሁ ወደ ውስጥ ገባሁና ወደ ካህኑ ጠጋ ብዬ በመባረክ ተሳልሜ ተመለስኩና አንድ ከማውቃቸው ሴትዬ አጠገብ ለመቆም እንደምን አደሩ ብዬ ሰላም ለማለት ትከሻቸውን ስስም ከእንቅልፍ እንደሚባንን ሰው በመሆን ደህና አደርክ ልጄ በማለት ሰላም አሉኝና ቀና እንዳሉ እንዴ ቅዳሴ አልቆ ነው ማለት ነው አሉኝ አዎ አልኳቸው አቀርቅረው ሊባረኩ ሄዱ በመገረም እስከአሁን እዚህ ቆመው አልሠሙም አላዩም ነበር ማለት ነው አልኩኝ ከዚያ መለስ ብዬ ‹‹አዎ ሰው ስንት አይነት ነው ስንቱ ቆሞ እንዳልቆመ የነቀዘች ሕይወት የሚንቀሳቀስ አለ ስንቱስ የአማረበት የተደሰተ መስሎ የሃሳብ ብል የበላውን ሰውነት ተሸክሞ የሚቆም አለ ግን ማን የውስጡን ያውቅለታል ማንስ ችግሩን ተረድቶለት ወገኔ ተቸግሯል ብሎ ካልተናገረ በቀር ይደርስለታል ቢናገርስ ቆሞ በመሄዱ ደምቆ በመታየቱ ብቻ ምነዋል እያልኩ እኔም ስቆዝም ቆይቼ በተራዬ ተአምረ ማርያም ተነቦ ወንጌል ተሰብኮ የቅዳሴው ፍፃሜ ሆኖ ሕዝቡ ሲሰናበት ነቅቼ ወደ ቤቴ የመጣሁ ይመስለኛል ከእንቅልፌ ስነቃ ይሄ ሁላ እስከአሁን ለካ በወኔ ሳይሆን የቅዳሴው ስርዓት በእንቅልፍ ልቤ ኖሯል፡፡ ከዚህ ይሰውረን!!
ይቆየን
በክፍል 2 ያገናኘን
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ