ምሴተ ሐሙስ / ጸሎተ ሐሙስ
" እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና። "
የዮሐንስ ወንጌል 13፥1-15 ፣ ማቴዎስ 26፥1-
(በደረሰ ረታ)
በሕማማት ሳምንት በዕለተ ሐሙስ ጌታ ደቀመዛሙርቱን እግር ያጠበበት ነው፤ ሌሎቹ ፈቅደው ወደው ሲታጠቡ ቅዱስ ጴጥሮስ አታጥበኝም ብሎ አስቸግሮት ነበረ። ምሥጢሩን እና ምሳሌውን አላስተዋለም ነበረና።
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮ መክሮ ገስጾ መልሶታል። እርሱም ለመመለስ ልቡ ቅርብ ነበረና እሺ በጄ ብሎ ታጥቧል።
ይህ ዕለት የትህትና ዕለት ነው። ጌታ እግራቸውን አጥቦ ሲጨርስ እኔ መምህር ስሆን ዝቅ ብዬ የተማሪዎቼን / የደቀመዛሙርቴን እግር ካጠብኩ እናንተም እንዲሁ አድርጉ ብሎ አስተማራቸው።
ቅዱስ ያሬድም ስለዚች ዕለት ይለናል፦
“ሐዋርያቲሁ ከበበ
እግረ አርዳኢሁ ሐጸበ
ኮኖሙ አበ ወእመ
ወመሀሮሙ ጥበበ”
ሲተረጎም፦ ሐዋርያቱን ሰበሰበ፤ የደቀ መዛሙርቱንም እግር አጠበ፤ እንደ አባትና እናት ኾናቸው የትሕትና ጥበብን አስተማራቸው። ማለት ነው።
ከዚህ ዕለት ብዙ የምንማረው ነገር ቢኖርም አንዱና ዋነኛው የጌታን ትሕትና ነው። ጌታ ሲሆን እግር አጠበ። በተግባር ያሳየ የትህትና መምህር ነው።
ቅድስት የሆነች ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን በየአመቱ ይህን ምሥጢር በጸሎተ ሐሙስ ታከናውናለች። ከቅዱስ ፓትሪያርኩ ጀምሮ ዐዕይንተ እግዚአብሔር ካህናት በእርሱ ምሳሌ የምዕመኑን እግር ወገባቸውን ታጥቀው ዝቅ ብለው ያጥባሉ። ምሳሌ ነው።
መምህረ ትህትና ኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ ጴጥሮስ እግሩን አልታጠብም ብሎ እንዳስቸገረ እንዲሁ መምህራንን ቅድስ ቤተክርስቲያንን አስተምሮቷን አንቀበልም የሚሉ ለሥርአቷ የማይገዙ ደንዳና ልብ ያላቸው አሉ። እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ያሉ ትምህርት ሲያገኙ የሚመለሱ አሉ። እነዚህን አስተምራ ትመልሳለች እንደ ይሁዳ ያሉትን ልበ ደንዳኖች አውግዛ ትለያለች።
እኛም አስተምህሮቷ ገብቶን እና የምሥጢሩ በረከት ተገብቶ ይድረሰን።
የሰው ልጅ ክቡር እና እኩል ቢሆንም ቅሉ። ካለንበት እንዳለንበት ደረጃ በትህትና ዝቅ ብለን ልንታዘዝ፣ ልናገለግል ይገባናል።
ትሕትና የመንግሥተ ሰማያት መወጣጫ መሠላል ናትና ትሕትናን ገንዘብ እናድርግ። እርፍ የጨበጠ መሰላል ላይ የወጣ ከመጨረሻው እስኪደርስ ድረስ ወደኋላ አይልምና ዘወትር ትሕትና አይለየን።
ይሕ ቀን ሌላ ተግባር ተከናውኖበታል። በአልአዛር እና ኒቆዲሞስ ቤት ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ለደቀመዛሙርቱ ይህ ነገ የሚፈሰው ደሜ፣ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው ጠጡ ፥ብሎ ሰጣቸው። ምሥጢረ ቁርባንን የጀመረበት ዕለትም ነው። የአዲስ ኪዳን ተግባር የተጀመረበት ዕለት ነው።
ሥጋውን ደሙን ከመቀበላቸው አስቀድሞ በእግራቸው በኩል ሕሊናቸውን፣ ሰውነታቸውን፣ ነፍሳቸውን አጽድቶ አጥቦ ለቁርባን አቀረባቸው።
እኛም ርስት መንግሥተ ሰማያትን የሚያወርሰውን ሥጋውንና ደሙን እንድመገብ ንሰሐ ገብተን ጸድተን እና ነጽተን እንቀረብ፤ ለዚህም እግዚአብሔር ይርዳን።
አምላካችን ዐይን ያላየውን፣ ጆሮ ያልሰማውን፣ በሰው ልቡና ያልታሰበውን፣ እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ያዘጋጀውን ርስት መንግስተ ሰማያትን ያውርሰን።
ይቆየን።
አሜን።