ሰኞ 26 ኤፕሪል 2021

ሰሙነ ሕማማት ሰኞ ( መርገመ በለስ)

 ሰሙነ ሕማማት ሰኞ ( መርገመ በለስ)

ማቴዎስ 21 : 10 - 19

ከእለተ ሆሳእና ማግስት ኢየሱስ ክርስቶስ ተራበ ይለናል። ፍጹም ሰው መሆኑን ለማጠየቅ ተራበ ተብሎ ተጻፈ። ስለተራበም ረሃቡን ማስታገሻ ምግብ ፈለገ። አንዲት በለስ ተመልክቶ ወደርሷ አመራ። ከቅጠልም ብቻ በቀር ምንም አላገኘባትምና " ለዘለዓለሙ ፍሬ አይገኝብሽ አላት " በሌሊትም ያንን ጊዜውን ደረቀች።

ወንጌላዊው ማቴዎስ በሰሙነ ሕማማት ሰኞ ስለተፈጸመው ተግባር ሲጽፍ ጌታ የረገማት በለስ ወዲያው እንደ ደረቀች የጌታ ደቀመዛሙርትም ይህን አይተው እንደተደነቁ ይነግረናል።

በሌሊቱ የተረገመችው በለመለመችና ፍሬ በምታፈራበት ወቅት ነበረ። ይህን ሲያስረግጥልን ቅዱስ ማርቆስ በምዕራፍ 11 ቁጥር 13 ላይ " የበለስ ወራት አልነበረምና " ይለዋል።

ታዲያ ቅዱስ ማርቆስ የበለስ ወራት እንዳልሆነ ካረጋገጠልን ጌታ ስለምን ከበለሲቱ ፍሬ ፈለገ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል።

አባቶቻችን እንዲህ ብለው ይኸን ጥያቄ ይመልሱታል። ከበለሷ ፍሬ መፈለጉ፥
• አንዳንድ በኩረ በለስ አይታጣም ብሎ ነው ይላሉ፣
• አንድም አላዋቂ ሥጋን እንደ ተዋሃደ ለማጠየቅ ነው ይሉናል፣
• አንድም አውቃለሁ ብሎ ሥራውን አይተውምና በዚያው ሥራውን ለመሥራት ነው።
ቅዱስ ማቴዎስ እና ቅዱስ ማርቆስ የጻፉለት በለስ ምሳሌ አላት። በበለስ የተመሰለው:-
፩. እስራል ናት

በበለሷ በረሃብ ሰአት የሚባላ መልካም ፍሬ ሊያገኝባት በወደደ እና በፈቀደ ጊዜ እንዳላገኘባት ሁሉ በእስራኤልም እንዲሁ ሃይማኖት፣ ምግባር ባገኝባቸው ብሎ ሄደ። አንዳች አላገኘባቸውም እስራኤል ከመባል በቀር። ደግ ሰው አይገኝብሽ ብሎ ረገማት። ያን ጊዜ ደግ ሰው ጠፋ።
" አቤቱ አድነኝ ደግ ሰው ጠፍቷልና " እንዲል ልበ አምላክ ንጉስ ዳዊት።

በለሷ እንደ ደረቀች እስራኤልም የተሰጣቸው የመመለሻ 40 ዘመን ሲያልቅ ምድረ እስራኤል ጠፋች።

፪. ህገ ኦሪት ናት

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እስራኤል ሰው ፣ ምግባር ፣ ሃይማኖት ፣ በጎነት ፣ፍለጋ እንደ ሄደ ነገር ግን የሚገድል እንጂ የሚያድን ህግ ሆኖ አላገኘውም።

ህገ ኦሪት ሰውን አልጠቀመምና ህገ ኦሪትን አሳለፈው። ሻረው።

ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ሮሜ ሰወች በላከው መልዕክቱ ምዕራፍ 8፥2 ላይ " በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአት ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና። " እንዲል ሕገ ኦሪት የሞት ሕግ ነበረ ማለት ነው።

ኦሪት ሕግና ሥርአት ነበራት የማይጠብቋትን መቀጣጫ ናት።

፫ . ኃጢአት ናት

ኃጢአት እንደ በለስ ቅጠል ሰፍታ በዚህ ዓለም ሞልታ አግኝቷታልና ረገማት። ኃጢአት በሶስት ነገር በበለስ ተመስላለች።
1. አዳምን ከገነት ያህል ቦታ እንዲወጣ እግዚአብሔርን ከመሰለ ጌታ የለየችው ዕፀበለስ ናትና።
2. የበለስ ቅጠል ሰፊ እንደመሆኑ መጠን የኃጢአትም መንገድ ሊጓዙበት የሚያመች ሰፊ መሆኑን ሲያጠይቅ።
3. በለስ ሲበሉት እንደሚጣፍጥ ሲቆይ እንዲመር ኃጢአትም ሲሰሩት ለሥጋ ደስታን የሚሰጥ ፣ ስሜትን የሚያረካ ነገር ግን ፍፃሜው ሞት እና መከራ ያለበት ህይወት ነው።
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ይግባውና ስለ ናትናኤል ሲናገር " ፊሊጶስ ሳይጠራህ ከበለስ በታች ሳለህ አየሁህ አለው " ዮሐንስ 1፥49

በለስ የኃጢአት ምሳሌ ነውና ኃጢአት ሰርተህ በበለስ ስር በተሸሸግህ ጊዜ አውቅሃለሁ ማለቱ ነበር። በአንድ ወቅት ናትናኤል የሰው ሕይወት አጥፍቶ በበለስጨስር ቀብሮ ነበረና።

በለስን መርገሙ ኃጢአትን መርገሙ ነው። መርገሙ ከዚህ በኋላ በሃጢአት አንዳች ሰው አይያዝ ማለቱ ነው።

ለዚህም ነው አባቶቻችን በቀመራቸው የሕማማትን ሰኞ መርገመ በለስ ብለው መሰየማቸው።

ምድራችን የሰው ልጅ ከኃጢአት ርቆ ከእግዚአብሔር ተጣብቆ የሚኖርባት ትሆንልን ዘንድ የእግዚአብሔር አምላካችን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን።

ይቆየን።
አሜን።


የእለት ተለት ጽሑፎቼን ለመከታተል ከዚህ በታች ባሉት ሁሉ እገኛለሁና ይከታተሉኝ። ከተመቸዎት ለሌሎች ያጋሩት።
My Facebook page link (በፌስቡክ ገጽ እንገናኝ)

https://www.facebook.com/deresse2020/

Main facebook account (ዋናው የፌስ ቡክ ገጼ ይቀላቀሉት)

https://www.facebook.com/DeresseReta

Follow me through telegeram (በቴሌግራም ሊከታተሉኝ ከፈቀዱ) ሁሉም ምልከታዬን የማጋራባቸው ማህበራዊ ድረ ገጾች ናቸው።

https://t.me/deressereta

ከአሥር አመት በላይ ከ50ሺ በላይ አንባቢዎች ያሉት መጦመሪያም አለ።

www.deressereta.blogspot.com

https://anchor.fm/deresse-reta/episodes/ep-ev5j5o

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...